እውነተኛ ደስታ ያለው በፍቅር ለሌሎች በመኖር ውስጥ ነው!!

Wednesday, 28 October 2015 13:52


በዲ/ን ኒቆዲሞስ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.


ለዚህ ለዛሬው ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ በቀድሞው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት በነበሩት በመ/አ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ መኖሪያ ቤት በሰላምና በአረንዴ ልማት ጉዳይ ላይ በተጠራ ስብሰባ ላይ ያገኘሁት ሰው ነው። ይህ ሰው እጅግ ባለ ጠጋና የተሳካለት የሚባል፣ በበርካታ የንግድ ሥራዎች ላይ የተሰማራ፣ በጎልማሳ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ የአምስት ልጆች አባትና የቤተሰብ ሓላፊ ነው። ታዲያ ስብሰባው እስኪጀመር ከዚህ ሰው ጋራ በሕይወት ዙርያ ላይ አንዳንድ ቁም ነገሮችን አንሥተን ጨዋታ ጀመርን።

በጨዋታችን መካከልም ይህ ሰው በሥራ አጋጣሚ አብሮት ይሠራ የነበረው ወዳጁ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እንደካደውና በጊዜው እጅግ መራርና ሊቀበለው ያዳገተው ይህ መጥፎ አጋጣሚም ለሕይወት የነበረውን ምልከታ እንዴት ሊያስቀይረው እንደቻለም እንዲህ ሲል አወጋኝ።

በዚህ መጥፎ አጋጣሚ በሚያምነው ወዳጁ የለፋበትን ገንዘቡን በጠራራ ፀሐይ የተከዳውና ልቡ እጅጉን ያዘነበት ይህ ሰው ሰዎች ለምን እንዲህ ክፉ ይሆናሉ፣ ለምንስ ፈጣሪን አይፈሩም፣ እንዲህ ዓይነቶቹ የራሳቸው ባልሆነ ላብና ወዝ በሌሎች ሰዎች ድካምና ልፋት ላይ ተረማምደው ሀብት ለማካበት የሚጥሩ፣ እጃቸው በሌሎች ደም የጨቀየ፣ የብዙዎች የግፍ እንባና እሮሮ የሚከሳቸው ሰዎችስ ሕሊናቸው አይፈርድባቸውምን…!? ስለ ምንድነው ግፈኞች፣ ጨካኞች፣ ስግብግቦችና በቃኝ ማለትን የማያውቁና ሁሉን ለእኔ የሚሉ ሰዎች በዚህች ምድር ላይ እንዲህ ተንደላቀው ሲኖሩ እውነትን የሙጥኝ ያሉ- ፍቅርን፣ በጎነትን፣ ርኅራኄንና ደግነትን ገንዘብ ያደረጉ ሰዎች በጨካኞች እግር ስር ወድቀው የሚረገጡበትና ፍትሕ የሚያጡበት ምክንያቱ ምን ይሆን በማለት አብዝቶ ራሱን መጠየቅ ይጀምራል።

ለዚህ ጥያቄው መልስ ለማፈላለግ ሲልም ፊቱን ወደ ሃይማኖት ያዞራል። ታዲያ በአንድ አጋጣሚ ይህ ሰው በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ን አንድ መምህር ሲያስተምረው የነበረው ትምህርት ለበርካታ ዓመታት ደስታን በሀብትና ብዙ ገንዘብን በማከማቸት፣ በመጠጥ፣ በፌሽታና በፈንጠዝያ ለማግኘትና ሲያደርግ የነበረውን ከንቱ ልፋትና በአጠቃላይም ለሕይወት የነበረውን ምልከታውን ፈጽሞ ቀየረለት። የሕይወትን ክቡር ዋጋ ገንዘብን በማካበት በሚደርግ እረፍት የለሽ ሩጫና ልፋት ይመዝን ለነበረው ለዚህ ሰው ሕይወት ከገንዘብና ሀብትን ከማከማቸት የሚያልፍ ከፍቅር በፍቅር የሆነ ታላቅ ትርጉም ያላት የፈጣሪ ውብ ስጦታ እንደሆነች መገንዘብ ይጀምራል።

በክርስትናው ዓለም ‹‹ወርቃማው ሕግ›› ተብሎ በሚጠራው ‹‹ሌሎችን እንደራስ አድርጎ በመውደድ››፤ ያለንን በፍቅርና በርኅራኄ ከማካፈል ጀምሮ ራስን ለሌሎች አሳልፎ እስከ መስጠት በሚዘልቀው ፍቅር ውስጥ ያለውን አስደናቂ ውብ ሕይወት ማየትና መጣጣም የጀመረው ይህ ሰው ባለው ነገር ደስተኛ መሆን እንዳለበትና ለሌሎች መኖርን፣ ለድሆችና ለችግረኞች ማካፈልን የሕይወቱ አንድ መርሕ አድርጎ ሕይወትን እንደ አዲስ ሀ ብሎ ይጀምራል። እንዲሁም በስም ብቻ የሚያውቀውን እምነቱን በሚገባ በመማር፣ የፍቅርን ሕይወት በተግባር በመኖር፣ ፈጣሪን የሚፈራ ደስተኛ ቤተሰብን በመመሥረት የክርስትናን ውብና ጣፋጭ ሕይወትንም ማጣጣም ይጀምራል።

ይህ ሰው ያገኘውን ሕይወትም ሌሎች የሥራ ባልደረቦቹና በሀብት የከበሩ ጓደኞቹ ይካፈሉት ዘንድ በማሰብ ማኅበር በማቋቋም ጧሪና ቀባሪ የሌላቸውን አረጋውያንን፣ ወላጅ አልባ ሕፃናትንና ችግረኞችን በመርዳት እንቅስቃሴ ማድረግን ሥራው አደረገው። እውነተኛ ደስታ፣ የሕይወት ሙሉዕ ትርጉም ያለው ሌሎች በመኖር፣ ለሌሎች በማካፈል ውስጥ እንደሆነ ከማስተዋል ባለፈ ሌሎችም ይህን የሕይወት ጎዳና ይከተሉ ዘንድ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘውን ፍቅር፣ ፍጹም ሰላምና ደስታ ለሌሎች ባልንጀሮቹና የሥራ ባልደረቦቹ መናገር ይጀምራል።

እስቲ እዚህች ጋራ ከዚህ ገጠመኜ ጋራ በተያያዘ ጥቂት ቁምነገሮችን ላንሣ። በእርግጥም የሕይወት ትርጉም ያለው ስለ ራስ አብዝቶ በመጨነቅና በማሰብ ውስጥ ሣይሆን ለሌሎች በመኖር ውሰጥ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። በዓለማችን የሚገኙ አብዛኛዎቹ የእምነት ተቋማትም ይህን እውነታ፣ ይህን ‹‹ወርቃማ ሕግ›› ደግሞ ሁሉም ቢያንስ በመርሕ ደረጃ የሚስማሙበት ነው።

በዘመናችንም በሳይንሱ ዓለም ያሉ ምሁራንም ሰዎች ደስታን በሀብትና በቁሳዊ ነገሮች ውስጥ በመፈለግ በሚያደርጉት ሩጫና ልፋት እንዲሁም ብዙዎች ስለ ራሳቸው በማሰብና በመጨነቅ ውስጥ ደስታ ቢሶች፣ አእምሮአቸው እየታወከ፣ ለበርካታ በሽታዎች እንደሚዳረጉ ባደረጓቸው ጥናቶቻቸው መግለጽ ከጀመሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል። የሥነ-ልቦና ምሁራን እንደሚናገሩትም የሰው ልጅ አካላዊና መንፈሳዊ ጤንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን፣ ደስተኛና ፍቅርን ተስፋን የተሞላ ሕይወት ሊኖር የሚችልበት ጥበብ ያለው ለሌሎች በመኖር፣ ለሌሎች በማካፈል ባለ የፍቅር ሕግ ውስጥ እንደሆነ ያሰምሩበታል።

እስቲ ለአብነት ያህል በዚህ በአገራችን ካሉ አንድ ሁለት ሰዎችን ላንሣ። ‹‹የሺዎች እናት››፣ ‹‹አፍሪካዊቷ ማዘር ቴሬዛ›› በሚል ስም የሚሞካሹት አበበች ጎበና የእናትነት ፍቅራቸውንና ርኅራኄያቸውን ለማካፈልና ለሌሎች በመኖር ውስጥ የሄዱበት ጎዳና ወይም ውሳኔ ብዙ ዋጋ ያስከፈላቸው ቢሆንም በሕይወታቸው ግን እጅግ ደስተኛ፣ ፍቅር፣ ተስፋና ሐሤት የተሞላ እንዳደረገው ግን ግልጽ ነው። ለሌሎች በመኖር ውስጥ ያለውን ውብ ሕይወት፣ ፍቅርንና ደስታን ያስቀደሙ እኚህ እናት የፍቅርና የደግነት ተምሳሌት በመሆን በዓለም ሁሉ ስማቸውን ሁሌም በመልካም ያነሣዋል፣ ይዘክረዋል።

ልክ እንደ አበበች ጎበና ሁሉ የመቄዶንያው መስራች ወጣቱ ብንያም በለጠም ከሀገረ አሜሪካ የድሎትና የተንደላቀቀ ሕይወት ይልቅ የወገንን ችግርና መከራ በመካፈል ውስጥ ያለውን የፍቅር፣ የደስታንና የሐሤትን ውብ ሕይወት አሻግሮ አይቷልና ራሱን ለሌች መሥዋዕት በማድረግ ሌሎች በመኖር ውስጥ የሚገኘውን ደስታ በተግባር እየመሰከረልን ነው። ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ወደሆነኝ ሰው ገጠመኜ ስመለስም አንድ በመጨረሻ ያጫወተኝን ቁምነገር በተመለከተ አንድ ነገር ልበልና ጽሑፌን ልቋጭ።

ይህ ባለ ጠጋ ሰው ከዓለማውያኑና ከፖለቲከኞች መንደር አልፎ ወደ ሃይማኖት ተቋማቶች ዘልቆ የገባውን ዘረኝነትና ጎጠኝነት የሰዎች ክፉ አስተሳሰብ ውጤት መሆኑን ለመግለጽና ክርስትና የዘር ድንበር የሌለው ሁሉን በፍቅር የሚያቅፍ የፍቅር ሃይማኖት መሆኑን ለመግለጽ በማሰብ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ከአማራ፣ ከትግሬ፣ ከጉራጌ፣ ከኦሮሞ … ወዘተ የመጡ ይህ ሰውና ሌሎች ባለ ሀብት ጓደኞቹ የተሰባሰቡበት በአዲስ አበባ በአንድ ሪል ስቴት ውስጥ በማኅበር ሆነው፣ ዘርና ጎሳ የማይለየው በፍቅር የሆነ አንድነታቸውን ለመግለጽ ሲሉ የመኖሪያ ቤት እየገነቡ እንዳለም አጫወተኝ።

በእርግጥም ወደንና ፈቅድን ኦሮሞና አማራ ባልሆንበት እንደው በፈጣሪ ውሳኔ ለተገነኘንበት ዘር ወይም ጎሳ ጥብቅና የቆሙ ሰዎች፣ ከሰውነት ክብርና ተራ ወርደው ሌሎችን ዝቅ አድርገው ሲመለከቱና በተገኙበት ዘር ሲኩራሩ ከማየት ባለፈ ምን የሚያሳፍርና የሚያሸማቅቅ ነገር ይኖራል! ከትግሬ ወይም ከአማራ አሊያም ከኦሮሞ ወይም ከጉራጌ ብሔር ለመፈጠራችን ለመሆኑ የእኛ አስተዋፅዖ ምንድን ነው! ይህ እውነት ያልገባቸው ወይም እንዲገባቸው ማይፈልጉ ሰዎች በዘርና በጎሳ አጥር ውስጥ ተከልለው ሌሎችን በቂም በቀል ለማጥፋት ሲደክሙ ማየት በእጅጉ ያሳዝናል።

ይህ ክፉ የዘረኝነትና የጎጠኝነት አስተሳሰብ ከዓለማዊ ጎራ ወጥቶ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ እንኳን ሣይቀር ገብቶ ከሃይማኖት አባቶችና መንፈሳዊ መሪዎች እስከ አገልጋይና ምእመናን ድረስ ዘልቆ መንጋውን ሲያተራምሰውና ያለ እረኛ ሲያስቀረውና ለነጣቂ ተኩላ አሳልፎ ሲሰጠው ማየት ደግሞ እጅጉን ልብን ያደማል። እውነታው ግን ክርስትና ዘር፣ ቋንቋ ድንበር የሌለው ሁሉን በፍቅር የሚያቅፍ ሰፊ የምሕረትና ይቅርታ ልቦች፣ በፍቅርና በርኅራኄ የሚዘረጉ እጆች ያሉት ውብና አስደሳች ሕይወት ነው።

በመጨረሻም በአንድ በግሪካውያን ጥንታዊ አባባል ጽሑፌን ልደምድም። ‹‹ነብርን አትፍታው፣ ከፈታኸው ግን ጥፋቱ ምን ሊሆን እንደሚችል አስበውኻል! ሰዎች ሃይማኖት እያላቸው እንኳን እንዲህ የከፉ፣ ጨካኞችና ምሕረት የለሾች ከሆኑ ጭራሽ ሃይማኖት ባይኖራቸውማ ጥፋታቸው፣ ክፋታቸው የፈታውን ነብር ያህል ሊሆን እንደሚችል አስብ።›› በማለት ሃይማኖት የሰው ልጆችን በፍቅር፣ በሥነ ምግባርና በሥርዓት ሊመሩ የሚችሉበት መልካም ልጓም እንደሆነ ያሰምሩበታል። አበቃሁ!!

ሰላም!n

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
2920 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us