አንዳንድ ነጥቦች፤ ስለ አቶ ሬድዋን ሁሴን ከኮምዩኒኬሽን ፅ/ቤት ስንብት ጉዳይ

Wednesday, 28 October 2015 13:50


ከለይኩን ብሩክ


ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የካቢኒያቸው ሹመት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ሲያቀርቡ እጅግ ካስደሰቱኝ እና ካስፈነደቁኝ አንዱ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ከቦታቸው መነሳታቸው አንዱ ነው። አቶ ሬድዋን በፅ/ቤቱ የተሾሙት በቅርብ ጊዜ ከመሆኑ አኳያ ከቦታቸው ይነሳሉ የሚል ግምትም ሆነ ሀሳብ አልነበረንም። ይልቁንስ በፅሕፈት ቤቱ የተንሰራፋውን የዘር፣ የጥቅምና የቡዱንተኝነት አመለካከት እና ድርጊት በተጠናከረ መንገድ ለረጅም ጊዜ መርተው ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ይወስዱታል የሚል ሥጋቱ ነበረን። ይህ ያልኩበት ዋንኛ ምክንያት ፅ/ቤቱ አቶ በረከት ስምኦን ይመሩት በነበሩበት ጊዜ ከፍተኛ አመራሩ ኃላፊነቱ እና ስራው በቅጡ አውቆ፣ አንዱ ዳይሬክቶሬት ከአንዱ ሳይፋለስ በመርህ የሚመራ እና አመራሮቹ ሆኑ ሠራተኞች በፍቅር፣ በቁርጠኝነት እና በእልህ የሚሰሩበት፣ እንደ ማንኛውም ተቋም የተወሰነ ክፍተት የነበረበት ቢሆንም አዲስ ተቋም እና አዲስ መዋቅር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጥንካሬውን የጎላ ነበር።

አቶ በረከት ከኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ተነስተው በምትካቸው አቶ ሬድዋን ከተሾሙ በኋላ የፅ/ቤቱ ራዕይና ተልዕኮ ጎልቶ የሚወጣበት አቅጣጫ መቀየስ ሲገባቸው የተወሰኑ ጀነራል ዳይሬክተሮች የሚደመጡበት፣ አንዳንዴም እንዳሻቸው የሚፈነጩበት፣ ሌሎች ዳይሬክቶሬቶች የተገለሉበት እና ዋና ስራቸው ወደጎን በመተው የበይ ተመልካች የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በፅ/ቤቱ የነበረውን የመተጋገል መንፈስ ነፋስ እንደነካው ጤዛ ተኖ እንዳልነበረ ሆኗል። በተቋሙ አሉባልተኞችና አድርባዮች ተመቻችተው በመረብ ተጠላልፈው የሚኖሩበትና የሚጠቀሙበት፣ የትግል ወኔ ያልተለየው አልሞት ባይ ታጋይ ደግሞ በተለያዩ ጫናዎች ስነልቦናዊ ጦርነት ውስጥ የወደቀበት እና የተገለለበት ወቅት ነበር። መቼም ነበር እያልን ብናወራው ይሻላል ብዬ ነው። ክቡር ሚኒስትሩ ከአሁን በኋላ ወደ ሌላ አዲስ ተቋም ተልከው የለ!

አቶ ሬድዋን በቢሆንስ ዓለም አዙሪት ውስጥ ገብተው የተጨበጠ ነገር ለማውራት የሚችሉ አልነበሩም። ብዙ ማውራትና የተጨበጠ፣ ግልፅና አሳማኝ ነገር ማውራት ይለያያሉ። እንደ አመራር ቁርጥ ያለ ነገር ከመናገር ይልቅ በቢሆንስ ዓለም ላይ በማተኮር መካከለኛ አመራሩም ሠራተኛውም ንግግራቸው በየራሱ እየተረጎመና የተለያየ አመለካከት እየያዘ ሲዳክር ከርሟል። ሁሉም በሚመቸው መንገድ እየተረጎመ ይከራከራል። አመራርስ ሁሉም በሚገባው ቋንቋ እንቅጩ ሲናገር ነው የሚያረካኝ። አቶ በረከት ስምኦን በዚህ ጉዳይ እጅግ የተካኑ ነበር።

ለዚህም ነው በወቅቱ አቶ ሬድዋን ከኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት መሰናበታቸው በተሰማ ማግስት አብዛኛዎቹ የፅ/ቤቱ ሠራተኞች በደስታና ፈንጠዚያ የሰከሩት።

የአቶ ሬድዋን አስተዳደር ፅሕፈት ቤቱን ለሁለት የከፈለ አስተዳደር ነው። ሁሉም ነገር በፀጋ የሚቀበሉ፣ ነገሮችን ሳያላምጡ የሚውጡ፣ እግር እግራቸው የሚሯሯጡ በአንድ በኩል፣ በዕውቀትና ፖለቲካዊ ብስለት ላይ የተመሰረተ አዲስ ሀሳብ የሚያፈልቁ፣ በመርህ ላይ የሚያምኑና የማያጎበድዱ በሌላ በኩል የተመደቡበት ሁኔታ ነው ያለው።

በፅሕፈት ቤቱ ማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራ አንድ ባለሙያ በፌስቡክ ገፁ እንዲህ ሲል አሞካሽቷቸዋል።

«አቶ ሬድዋን ማለት ኃላፊነትን ለመወጣት ከልብ የሚሰራ፣ የመርህ ሰዉ፣የሥራ ሰዉ፣ የሰዉን ጠንካራ ጎኑን ፈልጎ የማግኘት አቅሙ ከፍተኛ የሆነ፣ዉሸትና አስመሳይነትን የማይወድ፣ መካሪአባት፣ አቅጣጫ ጠቋሚ፣ የምትችለዉን ዘርፍ ካወቀ በዚያዉ የበለጠ ዉጤታማ እንድትሆን ተግቶ የሚሰራ፣ ፈረንጆች born to lead የሚሉት ዓይነት፣ ለመሪነት የተፈጠረ ቅን ሰዉ፣ ሙሉ ትኩረቱ ሥራ ላይ የሆነና ትልቅ እምቅ አቅም ያለዉ። ሰዉን የማይንቅ፣ ለሥራ ያለህን ጥንካሬና መሰጠትን የሚያይ፣ ነገሮችን በአንድ ቀዳዳ ብቻ ሳይሆን ከብዙ አቅጣጫ የሚያይ አስተዋይ፣ ብልህና ለዓላማ ጽኑ ሰዉ በነበረኝ አጭር ጊዜ በሕይወቴ እጅግ ከማከብራቸዉና ከማደንቃቸዉ ሰዎች አንዱ ሆነዉ ነው ያገኋቸው» ሲል አሞካሽቷል። ለአቶ ሬድዋን በፅ/ቤቱ በተጨባጭ ካለው ሁኔታ ጋር እጅግ የሚጣረስ ተክለ ሰውነት ለመስጠት ጥረት አድርጓል።

የፅ/ቤታችን የማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያው በዚህ አላበቃም። ከማድነቅ አልፎ ለማምለክም ቆርጦ ተነሳና እንዲህ ስል ፅፏል። «በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ካለ አንድ ቃል ጋር ተመሳሰለብኝ። እግዚአብሄር አንዲያ ልጁን አሳልፎ እስክሰጥ አለምን እንዲሁ ወደደ የሚል። ልጃችንን/አቶ ሬድዋንን ለሌላ ተቋም አሳልፈን ሰጠን በማለት አቶ ሬድዋንን እንደ ክርስቶስ ለማየት እና ለማስመሰል ሞክሯል። ይሄ ፀሐፊ ለኔ ትክክለኛ ኮምዩኒኬተር ሳይሆን አዝማሪ ኮምዩኒኬተር ይመስለኛል። ትንሽ ጉርሻ ለማግኘት ያለ የሌለ በማስተጋባት ላይ ያለ አዝማሪ።

“ልማታዊ ኮምዩኒኬተር” ማለት ለጥሩም ለመጥፎም መልካም ነው እያለ እንደ መሸታ ቤት አዝማሪ እያንቆለጳጰሰ የሚኖር ማለት አይደለም። ይልቁንስ ያሉትን ተጨባጭ ነገሮች ለህብረተሰቡ እያደረሰ ለችግሮችንም ጭምር ዕውቅና እየሰጠ ለነገ እንዳይደገሙ እየታገለና እያታገለ የሚሄድ ነው።

አቶ በረከት ከኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሲለቁ ለምን እንዲህ አልተሞገሱም። አቶ በረከት በዚህ ፅ/ቤት የነበራቸው እጅግ ጠንካራ የስራ መንፈስ እና ኃላፊነት ብሎም ተጠያቂነት በየደረጃው ላለው አመራር ሰጥተው ተተኪዎች ለማፍራት ያደረጉትን ጥረት እና ውጤት ለምን በየማህበራዊ ሚዲያዎቻችን አላስተጋባንም? ይሄ ያልተደረገበት ዋነኛ ምክንያት ሚኒስትሩ ያዋቀሩት መዋቅር እና የአመዳደብ ስርዓት ከአድልዎ የፀዳ እና የሚመለከታቸው ሁሉ አሳትፈው ስለሰሩ ነው። ቡድንተኝነት ስላልተፈጠረ ነው። ሠራተኛው እና አመራሩ ለግል ስራቸው ሳይሆን ለስርዓቱ በማድነቁ ነው። አቶ በረከት ለክብርና ስም የሚጨነቁ ስላልነበሩና የዲሞክራሲያዊ ልማታዊ አስተሳሰብ በማስረፅ የተጠመዱ መሪ ስለነበሩ ነው። ግለሰብን ሳይሆን ስርዓት የሚያመልክ ኮምዩኒኬተርን ስለፈጠሩ ነው። ለዚህም ነው በፅ/ቤቱ ያለውን ማህበረሰብ ሰውየውን ሳይሆን ስርዓቱን፣ ግለሰቡን ሳይሆን ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብን ወደ ውስጡ በማስረፅ እናመሰግናለን ብሎ በትንሽ ድግስ የሸኛቸው።

የአሁኑ የአቶ ሬድዋን ስንብት አስመልክቶ በየማህበራዊ ሚዲያ በአንዳንድ የዋሆች አማካኝነት እየተለቀቀ ያለው ግን ሚኒስትሩ በቡድን ያደራጇቸውን ጥቂት ግለሰቦች በቀቢፀ ተስፋ እያንጎራጎሩት ያሉ ዲስኩር ነው። በተለይ በአመራር ደረጃ ያሉት የሬድዋን አምላኪዎች አንዳንድ የማስተዋወቅ ስራ ቢሰሩም በአብዛኛው ግን እዛ ውስጥ ባሉ የዋህ ሰራተኞች በማህበራዊ ሚዲያ እንዲጫን ጥረት በማድረግ ላይ መጠመዳቸው አይተናል። አንዳንዶቹማ ለምን አቶ ሬድዋን በፅ/ቤቱ የሰሩትን ገድል በኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ፌስቡክ ላይ አንጭነውም የሚል አስተያየት ሲሰጡም አድምጠን ታዝበናል።

አቶ ሬድዋን በኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ከተመደቡ በኋላ የተሰሩ አዳዲስ ስራዎች ካሉ እስኪ ንገሩኝ? በአቶ ሬድዋን ስርወ-መንግስት በፅ/ቤቱ የአስተሳሰብ ልህቀት ላይ የተሰራ ስራ ካለ አውሱኝ እና ልወቀው? በአቶ ሬድዋን ጊዜ በፅ/ቤቱ የነበረውን ኪራይ ሰብሳቢነትን፣ ዘረኝነትን፣ ቡድንተኝነትን፣ ግለኝነትን፣ አድርባይነትን የመዋጋት፣ የመታገልና የማታገል መንፈስ እንዴት እንደነበረ ሞግቱኝ።

አቶ ሬድዋን ከስራቸው ከነበሩት አመራሮች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ዴሞክራሲያዊ መርህ የተከተለ ነበር የምትሉኝ እስኪ እጃችሁ አውጡ? ለምን ይዋሻል?

እኔ እሰከማውቀው ድረስ አቶ ሬድዋን እግራቸው ወደ ፅ/ቤቱ ከገባ በኋላ በኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች የነበረውን የፖለቲካ ግለት እና የአቋም ፅናት ላይመለስ ተኖ አመራሮች የየራሳቸው ቡድን ያዋቀሩበት፣ የአቶ ሬድዋን ቡድን በተለይ በገፅታ ግንባታ ዳይሬክቶሬት ጀነራል እየታገዘ በፌዴራል መስሪያ ቤቶች የሚመደቡ ኮምዩኒኬተሮች ከፖለቲካ ብስለታቸው፣ ከስራ ልምዳቸው እና ከስራ ብቃታቸው አኳያ በመመዘን ሳይሆን በዘር፣ በጥቅም በኃይማኖትም ጭምር አድልዎ በመፈፀም እየሰራ እንደነበር ፀሐይ የሞቀው ሐቅ አይደለምን?

አሁን የሄ ሁሉ አልፏል። የፅ/ቤቱ ራእይና ተልዕኮ ወደኋላ ተመልሷል። ቢሆንም መንግስት ቶሎ በመድረሱ አቶ ሬድዋንን ከቦታቸው አስነስተዋል። እኛም ደስ ብሎናል። በቅርቡ ፅ/ቤቱ እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳ ይሄን ጉዳይ በደንብ ያጤኑታል ብዩም ተስፋ አደርጋለሁ። በአድርባይ አመራር ላይ የማያዳግም እና አስተማሪ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል። ከእርምጃው በፊት ግን ከላይ እስከ ታች ሰፊ ግምገማ ሊካሄድ ይገባል። በግምገማው ከፅሕፈት ቤቱ ሰራተኞች በተጨማሪ በየፌዴራል መስሪያ ቤቶች እየሰሩ ያሉትን ኮምዩኒኬተሮች ባካተተ መልኩ ሊሆን ይገባል። አንድ ኮምዩኒኬተር ስንት አጀንዳ አሳተመ፣ ስንት ሁነቶችን ፈጠረ፣ ከኃላፊው ጋር ያለው ሙድ/መግባባት አሪፍ ነው ወይ፣ በፌስ ቡክ አካውንቱ የመንግስት አቋም ያጋራል ወይ፣ በክላስተር ግምገማ ስንት አመጣ፣ ለገፅታ ግንባታ ዳይሬክተር ጀነራል ክብር ይሰጣል ወይ የሚሉ ከአመለካከት እና ብቃት ያልተያያዙ እና የጋራ መግባባት ለመፍጠር ብዙም ከማይጠቅሙ ቀሽም ቀሽም የግምገማ ነጥቦች ተላቆ በጠባብነት፣ በትምክህተኝነት። በኪራይ ሰብሳቢነት፣ በአድርባይነት፣ በቡድንተኝነት እና በሌሎች የጋራ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ማነቆ በሚሆኑና ስራን የሚያጓትቱ ችግሮች ላይ አትኩሮት ተሰጥቶ ምህረት የለሽ ግምገማ ሊካሄድ ይገባል። በግምገማው ክፉኛ የሚተቹ መካከለኛ አመራሮች በተለይ በተለይ ከህዝብ ግንኙነት አካላት ጥብቅ ትስስር ያለው በገፅታ ግንባታ ዳይሬክቶሬት እየተሰሩ ያሉ አሳፋሪ ስራዎች የሚፈተሹበትና ችግሮቹን ነጥረው የሚወጡበት ብሎም አስቸኳይ እና አስተማሪ እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ የደረሰ ይመስለኛል።

ከዚህ ግምገማ በኋላ የሽግሽግ ስራ መኖሩ ስለማይቀር የአቶ በረከት የተጠናከረ መዋቅር በአቶ ሬድዋን ተበላሽቶ ቢቆይም በአዲሱ ሚኒስትር በአቶ ጌታቸው ስህተቱ እንዳይደገም ሁላችንም የተቋሙ ሠራተኞች የበኩላችን ልንወጣ ይገባል።¾

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
2317 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us