አቶ ሬድዋን ከሚኒስትር ማዕረግ ወደ ሚኒስትር ከፍ ነው ያሉት

Wednesday, 04 November 2015 14:15


- ውሾቹ ቢጮህም…ግመሉ ግን ጉዞውን ቀጥሏል…

ገብረእግዚአብሄር ሀጎ

 

ባለፈው ሳምንት በጋዜጣችሁ “አንዳንድ ነጥቦች ስለ አቶ ሬድዋን ሁሴን ከኮሙዩኒኬሽን ፅ/ቤት ስንብት ጉዳይ” በሚል ርእስ የተፃፈውን ፅሑፍ አነበብኩና ይሄን ጉዳይ መልስ ያስፈልገዋል በማለት ነው ለመፃፍ ያሰብኩት ። በመጀመሪያ ፅሁፉ የአንድ ጀማሪ የአርቲክል/ፊቸር ፀሐፊ የሚፅፈው ዓይነት ፈረንጆች ‘amateur’ እንደሚሉት ዓይነት ነው። ፀሐፊው በፅሕፈት ቤቱ ያለውን አሰራር ስለተበላሸ ነው በኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች በሚኒስትር ማዕረግ የነበሩትን አቶ ሬድዋን ሁሴን ከፅሕፈት ቤቱ የተባረሩት የሚል የፈጠራ ወሬ አስተጋብቷል።

በመጀመሪያ አቶ ሬድዋን ከሚኒስትር ማዕረግ ወደ ሙሉ ሚኒስትር ነው የተሸጋገሩት። ይሄ ማለት ከነበራቸው የማዕረግ ስልጣን በላይ ነው። በአገራችን አንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ነው ያሉት፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ ግን ሁለት ሰዎች አሉ፡፡ ዶክተር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤልና ወ/ሮ አስቴር ማሞ፡፡ ዶ/ር ደብረጽዮን እና ወ/ሮ አስቴር ሙሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አይደሉም፡፡ በስልጣን ደረጃ አቶ ደመቀ መኮንን ከሁለቱ በመዓረግ ደረጃ ያሉት ሰዎች በላይ ስልጣን አላቸው፡፡

የአቶ ሬድዋንም እንደዚሁ ነው፡፡ በሚንስትር ማዕረግ ነበር ስልጣናቸው አሁን ግን ሙሉ ሚኒስትር ሆኑ። ተጨማሪ ስልጣን አገኙ እንጂ ከነበራቸው ስልጣን በታች አልተመደቡም። የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር ሆነው ነው የተመደቡት። ይሄ የሚያሳየው ደግሞ በኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች በነበሩበት ጊዜ ተልዕኳቸውን በብቃት እየተወጡ እንደነበር መንግስት ዕውቅና ሰጥቷቸዋል የሚል ነው። ስለዚህ ፀሐፊው ያነሱት ሀሳብ ውሃ የማይቋጥር እንደሆነ በግልፅ ያሳያል።

ስለ አቶ በረከት እና አቶ ሬድዋን በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ያነሱት ነጥብ ላይም የተንሸዋረረና የተዛነፈ አስተያየት አቅርበዋል። ፅሕፈት ቤቱ እንደ አዲስ ሲዋቀር ከተለያዩ ወረዳዎች በአመራር ደረጃ የነበሩ ሰዎች የለብለብ ስልጠና ወስደው ስራ የጀመሩበት ሁኔታ ነበር። እነዚህ ለከተማይቱም ለኮሙዩኒኬሽን ስራውም ገና አዲስ የነበሩ የወረዳ ሰዎች ከነባር ሰራተኛው ጋር ተቀላቅለው ሲሰሩ አቶ በረከት ከወረዳ ለመጡ ሰዎች የተለየ ትኩረት ይሰጡ ነበር። ሁሉም የሃላፊነት ደረጃዎች ከወረዳ ለመጡ ሰዎች ተሰጠ። ነባር ሰራተኛው የሚገባውን እያጣ፣ እያየ እንዳላየ ዝምታን መረጠ። ከወረዳ ለመጡ ሰዎች ለሁሉም እንደየፍላጎታቸው የኪራይ ቤቶች ቤት ተሰጣቸው። ደሞዛቸው ከሌላው ሰራተኛ በተለየ መልኩ ደረጃ ወጣለት። ይሄ ሁሉ መልካም ስራ የሚሰሩላቸው አቶ በረከት ነበሩ። ስለዚህ አቶ በረከትን እንደ ፈጣሪያቸው አድርገው እስከ ማየት ደርሰዋል። እኛ ነባሮች በበኩላችን፣ ከወረዳ ለመጡና ካለ ብቃታቸው ላያችን ላይ የተጫኑብን ሰዎች የአቶ በረከት ልጆች እንላቸው ነበር። እነሱም ደስ ይላቸው ነበር። አሁንም ደስ ይላቸዋል። ስለ አቶ በረከት አንድም መጥፎ ነገር እንድትነሳ አይፈልጉም። አቶ በረከት ማለት እጅግ ጠንካራና አስተዋይ መሪ እንደሆነ እኔም አውቃለሁ። እኔ የአቶ በረከት ብቃት እና አመራር የምወደውና የማደንቀው ግን፣ ለአገሪቷ ካደረጉት ገድል አንፃር ነው። ከወረዳ የመጡ ሰራተኞች የሚያደንቁት ግን የአቶ በረከት ብቃትና ብስለት ብሎም አመራር ለግላቸው ካደረጉላቸው መልካም ስራ እንጂ ለአገሪቷ ካደረጉት አስተዋፅኦ አንፃር አይደለም።

አቶ በረከት ወደ ሌላ ቦታ ተዛውሮ በአቶ ሬድዋን ሲተኩ፣ አቶ ሬድዋን ሁሉንም ሰራተኞች በእኩል ዓይን ማየት ጀመሩ። ሁሉም ሰራተኛ በእኩል መታየቱ ከወረዳ ለመጡ ሰዎች ምቾት አልሰጣቸውም። ለራሳቸው የሰጡት ሚዛን ከፍተኛ ስለነበር የአቶ ሬድዋንን ስም ማጥፋት ተያያዙት። በተለይ በፅሕፈት ቤቱ ያሉትን የዳይሬክተር ደረጃ በአንፃራዊ መልኩ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በአመራር ደረጃ ለነበሩ ከተማ ቀመስ እንዲመደቡ ሲደረግ፣ የወረዳ ሰዎቹ ክፉኛ ተንጫጭተው ነበር። አሁን ሁለቱንም ማለትም አቶ በረከት እና አቶ ሬድዋን ሚዛን ላይ ማስቀመጥ ነው። ከተለያዩ የገበሬ ማህበርና የወረዳ አመራር የመጡ ሰዎች ብቻ ትኩረት ሰጥቶ ሌላው ዜጋ በማግለል የሰራ ሰው ነው የሚሞገሰው ወይስ ከገጠር ለመጣም በከተማ ላለም ለሁሉ በእኩል የሚያይ አመራር ነው? ይሄ ለአንባቢያን ልተወው።

ከወረዳ የመጡ ሰራተኞች ኦሬንቴሽን ሲሰጣቸው በአዲስ አበባ ያሉትን የኃላፊነት ቦታዎች ከናንተ ውጪ ለማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ አይመለከተውም የተባሉ ይመስል ከተሜው አንድ የኃላፊነት ቦታ ሲሰጠው ስራቸው መንጫጫት ነው። በጓደኝነት ልንቀርባቸው ብንሞክርም እንኳ በአይነ ቁራኛ ነው የሚመለከቱን። ካለነሱ ለመንግስት ታማኝ ያለ አይመስላቸውም። ግጭታቸው ከከተሜው ብቻ ቢሆን አይከፋም ነበር። ራሳቸው በራሳቸውም አይዋደዱም። በዘርና በጎሳ መከፋፈል እንደ ዘመናዊነት ይቆጥሩታል። በየመጠጥ ቤቱ አንዱ ብሔር ለአንዱ ብሔር ማጥላላት ለእነሱ አሪፍነት ነው። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ማለት የራስህን ብሔር ተወላጅ ወደ ስልጣን ማምጣት፣ የራስህን ብሔር ተወላጅ መጥቀም መሆኑ የጋራ መግባባት ላይ የደረሱ ይመስላሉ። በጨዋታቸው መሀከል ገብተህ ልታስተካክል ከሞከርክ ይሄ የትምክህተኝነት አስተሳሰብ ነው፣ የጉልበት አንድነት ነው፣ ራሳችን በራሳችን የመወሰን ስልጣን ገደብ የለሽ ነው እያሉ የቱ ከየቱ እንደሚያይዙት ግራ ይገባሃል። በመከባበር እና በመቻቻል እየተጠናከረ ያለውን አንድነታችን በቅጡ የተገነዘቡትም አይመስለኝም።

ለዚህም ነው የኮሙዩኒኬሽን ፅ/ቤት ከሌሎች የፌዴራል መስሪያቤቶች በባሰ መልኩ ሰራተኞች ከሰራተኞች፣ ኃላፊዎች ከሰራተኞች መነቋቆር እና ፍትጊያ የሚበዛው። ይሄ ያለመስማማት እና ተግባብቶ ያለመስራት ችግር ከበላይ አመራር ከአቶ ሬድዋን ጋር የሚያያዝ አይደለም። ከፅ/ቤቱ አተካከል እና አበቃቀል ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው። ለዚህ ጉዳይ ጦስ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሳይሆኑ፣ አቶ በረከት ናቸው። አተካከሉ ያማረ እና አበቃቀሉ የተገራ ፅ/ቤት ቢሆን ኖሮ አሁን ያለውን አስተሳሰብ አያፈራም ነበር። አቶ ሬድዋን የተረከቡት አተካከሉና አበቃቀሉ ያላማረ ተቋም ነው። ስለዚህ ዋና ተጠያቂ ተክሎ ያበቀለው እንጂ፣ ፍሬውን ተረክቦ ወደ ስራ የገባ አይደለም።

በሁሉም የፌዴራል ተቋማት ያሉ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች መቶ በመቶ በሚባል መልኩ በአቶ በረከት ጊዜ ከገበሬ ማህበርና ወረዳ መጥተው በለብ ለብ የኮሙዩኒኬሽን ስልጠና ታግዘው የተመደቡ ናቸው። እነዚህ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በመልካም አስተዳደር፣ በሙስና፣ በኪራይ ሰብሳቢነት፣ በአድርባይነት፣ በጠባብነት፣ በትምክህተኝነት ዙሪያ መንግስት በሚፈልገው አቅጣጫ እየሰሩ ናቸው ወይ? ተብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። ከፀሐፊው ጋር የምጋራው ነጥብ እዚህ ላይ ነው። ለእነዚህ ሰዎች በየዓመቱ መፅሔት፣ የግድግዳና የጠረጴዛ ካላንደር እንዲሁም ፖስት ካርድ ማሳተም እንደ ቁልፍ ስራ ነው የሚወስዱት። በየዓመቱ የእንኳን አደረሳችሁ ፖስት ካርድ በማሳተምና የራሳቸው ስምና ማህተም በፖስት ካርድ በማሳረፍ ወደመጡበት ወረዳ ፖስት ካርድ እየበተኑ የሚውሉ ብዙ ናቸው። ይሄ ስራ ለነሱ በጣም ያረካቸዋል። ፖስት ካርድ ማሳተም ራሱ ብርቃቸው ነው። እየተደዋወሉ ፖስት ካርዱ እንዴት አየኸው ቀለሙ ያምራል አይደል? ትንሽ ተለቀ አይደል? ለመጪው አስተካክላታለሁ እየተባባሉ የሚሞጋገሱ ብዙ ናቸው። በመልዕክት ቀረፃ፣ በመንግስት አቋም፣ በወቅቱ አጀንዳ ላይ ትኩረት አድርገው ከመስራት ይልቅ ወደ ማይረባ ነገር የማዘንበል አዝማሚያ አለ። እዚህ ላይ ፀሐፊው በትክክል ስላስቀመጠው የምጋራው ይሆናል።

የዚህ ዋነኛ ተጠያቂ ህዝብ ግንኙነቶች ለመምራት በኮምዩኒኬሽን ፅ/ቤት የተዋቀረ ዳይሬክቶሬት ነው። ዳይሬክቶሬቱ እና ዳይሬክቶሬቱ ለመምራት የተዋቀረውን ዘርፍ ከአቅም ግምባታ ጀምሮ እስከ ምደባ ያለው ስርዓት ምን ይመስላል? የመንግስት ተልዕኮ በሚገባ ተገንዝቦ ወደ ኮሚዩኒኬተሮች የሚያስተላልፉበት ስልት እንዴት ነው? የሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ቢሰጠው የሚለውን ጉዳይ የጋራ ሃሳብ ነው። ዳይሬክቶሬቱ እንዲመሩ ኃላፊነቱ የተሰጣቸው አካል በእርሻ ወኪልነት ተሰማርተው እየሰሩ የነበሩና ከአንድ ከገበሬ ማህበር የመጡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ወደ ተለያዩ መስሪያቤቶች የሚመደቡ ኮሙዩኒኬተሮች የወረዳ ሰዎች ናቸው። ከተሜዎች ይሄ ጉዳይ አግባብ አለመሆኑ ብዙ ጊዜ ሀሳብ ብናቀርብም የሚሰማን አልተገኘም። ከእኛ ከተበዳዮች በላይ በዳይሬክቶሬቱ ብዙ ቅሬታ የሚያቀርቡት ግን ከወረዳ የመጡ ኮሙዩኒኬተሮች መሆናቸው ልብ ይላሉ። ከላይ እንደገለፅኩት የጠባብነት ልክፍት ስላላቸው እንትና የተመደበው መዳቢው አመራር የአገሩ ልጅ ስለሆነ ነው፣ እገሌ የተዘዋወረው በጓደኝነት ነው፣ እሷ እዚህ የተቀመጠችው በጥቅማጥቅም ነው የሚሉ ስሞታዎች እጅግ በርካታ ናቸው። አንዳንዶቹ ጥሬ ሐቅ ናቸው። በዚህ ስራ የተሰማራው ኃላፊ ምላሱ በእውነት ቀብቶ ውስጡ በውሸትና በማስመሰል የተሞላ እንደሆነ መላው የፅ/ቤቱ ሰራተኞች ያውቃሉ። ሁላችንም በጋራ ሆነን በአንድ ልብ ልንታገለው ግን አንችልም። ምክንያቱም ቅድም እንዳልኩት የጠባብነት አመለካከት የበላይነቱ የያዘበት ተቋም ስለሆነ ግለሰቡ መንካት ማለት፣ ብሔሩ እንደመንካት ስለሚቆጠር። በአብዛኛው ጊዜ ገምጋሚው የሌላ ብሔር ተወላጅ ስለሚሆን የተገምጋሚው ብሔር ተወላጅ የሆኑት ሰዎች ተገምጋሚውን የሚደግፉበት አጋጣሚ ይታያል። ይሄ በሽታ እንደ ጋንግሪን ሕመም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ እየሄደ ያለ መድሃኒት ያልተገኘለት ነው።

በመጨረሻ ፀሐፊው የአቶ ሬድዋን ስም ከእውነት በራቀ መልኩ ጥላሸት ለመቀባት ሙከራ ማድረጉ ተገቢነት የሌለውና ምክንያታዊነት የጎደለው እንደሆነ ለማስገንዘብ እወዳለሁ። ማንኛውም ሰው የመሰለውን ሀሳብ የመፃፍ መብት እንዳለው ግንዛቤ ቢኖረኝም የመፃፍና ሃሳብህን የመግለፅ መብት በመጠቀም ከሐቅ የራቀ የስም ማጥፋት ዘመቻ ማካሄድ አግባብ አይሆንም። አቶ ሬድዋን የፖለቲካ ብስለታቸው አሁን ካሉት ተተኪ የበላይ አመራሮች እጅግ የተሻሉ፣ ሀሳባቸውን አደራጅተው ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሚገባው ቀላል ቋንቋ የሚያስረዱ በዚህ ክህሎታቸው አንቱ የተባሉ የምንኮራባቸው ሚንስትር ናቸው። አንዳንድ የግል ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት ያለ የሌለ ድስኩራቸው ቢነዙም ውሻው ይጮሃል ግመሉ ግን ጉዞውን ይቀጥላል እላለሁ።n

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
784 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us