በኮሙዩኒኬተር ስም የተሰገሰጉ አድርባዮች አደብ ይግዙ!!

Wednesday, 11 November 2015 13:38

 

 

- አቶ ረድዋን በተለይ በአንዳንድ ብሔሮች ላይ የከረረ ጥላቻ እንዳላቸው አውቃለሁ

ከለይኩን ብሩክ

ሰሞኑን የፃፍኩትን ፅሑፍ እንደ መነሻ ወስደው አንድ ፀሐፊ “አቶ ሬድዋን ከሚኒስትር ማዕረግ ወደ ሙሉ ሚኒስትር ከፍ ነው ያሉት” በሚል ርእስ ፅፈዋል። የፅሑፉ መነሻ ስለ አቶ ሬድዋን የፃፍኩትን ጭብጦች ተረድተው ለመመለስ ነው። ከፃፉት ርእስ ልነሳና አቶ ሬድዋን ከስልጣናቸው ዝቅ ብለው ተመድቧል የሚል ጭብጥ አላስቀመጥኩም። ፀሐፊው የፃፍኩትን አርቲክል መሰረታዊ ሃሳብ ሳይረዱ በችኮላ ወደ መልስ መንደርደራቸው ከአማተርነት በዘለለ መልኩ ብስለታቸው እስከምን ድረስ እንደሆነ ለመገንዘብ ችያለሁ። የሆነ ሆኖ የመሰላቸውን ሃሳብ ማቅረባቸው ሳላደንቅ አላልፍም። በያንዳንዷ ያነሷትን ሃሳብ መልስ ለመስጠት መሞከር የናንተ የጋዜጣ ዓምድ ማጨናነቅ እንዲሁም ለአንባቢያን ማሰልቸት ስለሚሆን በአንኳር አንኳር ጉዳዮች ላይ ማተኮር መርጫለሁ።

በፅሁፌ ካነሳሁት ዋና ዋና ጭብጦች መካከል አቶ ሬድዋን በኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ከተሾሙ በኋላ በፅሕፈት ቤቱ የተሰሩ ስራዎች ካሉ ንገሩን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን፣ አድርባይነትን፣ ዘረኝነትን፣ ቡዱንተኝነትን በአስተሳሰብና በተግባር ተዋግተዋል የምትሉ ከሆነ ሞግቱኝ የሚሉ ነጥቦች ነበሩ። በነዚህ ጉዳዮች ፀሐፊው ብዕሩ ሊያነሳ አልቻለም። ይሄን ጭብጥ ወደጎን በመተው በከተማ ያሉ ነባር ኮሙዩኒኬተሮች እና ከወረዳ የመጡ ኮሙዩኒኬተሮች በማለት በአዲስ አበባ በየመስሪያቤቱ ያሉት ኮምዩኒኬተሮች በሁለት ፈርጇቸዋል። በፀሐፊው አባባል ከተሜ የሚባል የአዲስ አበባ ተወላጅ ከአዲስ አበባ ውጪ የመጣ ደግሞ የወረዳ ኮምዩኒኬተር ለማለት ሞክሯል። ከወረዳ የመጡ ኮምዩኒኬተሮች ማለት ምናልባት ምንም የማያውቁ፣ የገጠር ሰዎች ፋራዎች፣ አሪፍ ያልሆኑ እና ሌሎች ተመሳሳይ ቃላቶች ባይደረድርም በፅሑፉ ያለውን ሰምና ወርቅ ወደነዛ ቃላቶች ይፈታሉ። ወረዳ ማለት በአንድ የተወሰነ ግዛት የሚኖሩ ህዝቦች ለማስተዳደር በሚያመች መልኩ የምታካልለው ድንበር ነው። ወረዳ የፋራዎች/ምንም የማያውቁ ወይም የገጠሬዎች ልዩ ስም አይደለም።

አዲስ አበባ 116 ወረዳዎች አላት። የአዲስ አበባ ህዝብ በተለያዩ ወረዳዎች ነው የሚኖረው። ወረዳ 1፣ 2፣ 3 እያለ ይቀጥላል። አንድ የወረዳ 1 የአዲስ አበባ ነዋሪ በወረዳ ስለሚኖር ፋራ፣ ሁሉ ብርቁ ልትለው አትችልም። ነገር ግን በነዚህ ወረዳዎች አሪፍም፣ ሌባም፣ ጥሩም፣ አድርባይም፣ ጎበዝም፣ ሰነፍም አለ። ሁሉም ዓይነት የህብረተሰብ ክፍሎች ይኖራሉ። በሌሎች የአገራችን ቦታዎችም እንዲሁ የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ይኖራሉ። ግለሰቡ/ቡዱኑ ከወረዳ ስለመጣ ሳይሆን በውስጡ ያለውን አመለካከት እና አስተሳሰብ ነው መታየት ያለበት። ፀሐፊው የወረዳ ሰው እና የከተማ ሰው ብሎ የሰጠው ፍረጃ ከአመክንዮ የራቀ እንደሆነ ለማሳየት ነው። አቶ ሬድዋን ከገጠር ወረዳ የተገኙ መሆኑንም ልብ ይሏል።

በሁለተኛ ደረጃ የአገራችን ህዝብ ወደ 86.4 ፐርሰንቱ አርሶ አደር ነው። ከተሞች የሚቆረቁሯቸው እነዛ ህዝብ ናቸው። በከተማ የሚኖር በገጠር ከሚኖሩ ህዝቦች ጋር ንክኪ የሌለው የለም። ምናልባት የሌላ አገር ዜጋ ካልሆነ በስተቀር። ስለዚህ ዋና የመልዕክቱን ምሶሶው ረስተህ ወደ ሌላ አመለካከት እልም ብለህ መግባትህ ስሜታዊነትህን እና ችኩልነትህን ነው የሚያሳየው። አቶ በረከት ገጠሬዎች ነው የሚወደው የሚል ድምዳሜ ያደረሰህ የኢህአዴግ ፕሮግራም የኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አንቀሳቃሽና ዋናው ምሶሳችን አርሶ አደሮቻችን ናቸው ስለሚል ነው። ይህ ፕሮግራም ከአዲስ አበባ ውጪ ካሉ የአገራችን ክፍሎች ከመጡ ዜጎች ጋር እያመሳሰልክ ወደማይፈለገው ስህተት የገባህ ይመስለኛል። ይህ ደግሞ የአዕምሮ ግሽበት ውስጥ መኖርህን ያሳያል።  

ፀሐፊው ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተውጣጡ ኮምዩኒኬተሮች ወደየ መስሪያ ቤቱ በኮሙዩኒኬሽን ባለሙያነት ተመድበዋል ያለውን ትክክል ነው። አቶ በረከት የገጠሬውና የከተሜው ኮሙዩኒኬተር በአንድ ዓይን አያዩም ነበር፣ ለገጠሬዎቹ ያዳሉ ነበር የሚለው ሃሳብ ግን ስህተት ነው። አቶ በረከት ኮምዩኒኬተር በዘር፣ በኃይማኖት፣ በጎጥ ለይተው አላዩም። በነገራችን ላይ በኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ሚንስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ለገሰ “ባለቤት አልባ ከተማ” በሚል መፅሐፋቸው በገፅ 236 ላይ ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ስለ መጡ ኮምዩኒኬተሮች እንዲሁም የተደረገላቸው ችሮታ ፅፏል። የአቶ ኤርሚያስ ዋነኛ ማጠንጠኛ አዲስ አበባዎች ተገልለው ሌሎች እየተጠቀሙ ነው በሚል መነሻ የተፃፈ ነው። ፀሐፊው የአቶ ኤርሚያስ ለገሰ መፅሐፍ ሳያላምጥ ነው የዋጠው። እያንዳንዷ በመፅሐፉ ያለችው ሃሳብ ነው ያስቀመጠው። ይሄ የሚያሳየው በኮሙዩኒኬተር ስም የተሰገሰጉ ብዙ ኤርሚያሶችና ሞላጫ ሳሙናዎች በኛ ፅ/ቤት በብዛት እንዳሉ ነው።

አቶ ሬድዋን ከሚኒስትር ማዕረግ ወደ ሙሉ ሚኒስትር ነው የተሸጋሩት የተባለው ጉዳይ ፀሐፊው ስለ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ያለውን ዕውቀት ሚጢጢዬ እንደሆነች ያሳያል። አቶ ሬድዋን በኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች በነበሩበት ጊዜ ሚኒስትር ነበሩ። ወደ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ተዘዋውረውም ሚኒስትር ናቸው። በሚኒስትር ማዕረግ ነበሩ ተብሎ መፃፉ አጥፊ ስህተት (fatal mistake) ነው። የኮሙዩኒኬሽን ፅ/ቤት ኃላፊ በሚኒስትር ማዕረግ ነው ከተባሉ ዴኤታዎቹስ ምን ሊባሉ ነው። ፀሐፊው በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ናቸው ይለን ይሆናል። አቶ ሬድዋን ዕድገት አገኙ ብሎ ለማወጅ እና ለማስጮህ ካለህ ጉጉት ተነስተህ ወደማያስፈልግ ስህተት መግባትህ የቲፎዞ/ቡድንተኝነት አባዜ መሆኗ ገብታኛለች።

ፀሐፊው ሲያጠቃልል የአቶ ሬድዋን ብስለት አሁን ካሉት ተተኪ አመራሮች በላይ የተሻለ እንደሆነ ገልፆልናል። መቼም ለምን ይሄን አልክ አይባልም። አቶ ሬድዋን ወደ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሲመጡ በመጀመሪያ የተጣሉ ከሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሽመልስ ከማል ጋር ነው። አቶ ሽመልስ በዕውቀቱና በፖለቲካ ብስለቱ ከአቶ ሬድዋን እጅግ የተሻለ እና በመንግስት አቋም ላይ ፅኑ እምነት ያለው ነገሮችን ፊት ለፊት የሚያፈርጥ አብዛኛው የፅ/ቤቱ ሰራተኞች የሚወዱት አመራር ነው። አቶ ሬድዋን ይሄን የአቶ ሽመልስ ብቃትና ብስለት ብሎም አቋም አልወደዱለትም ነበር። አቶ ሬድዋን አብዛኛውን ጊዜ በቢሆን ዓለም ስለሚዋልሉ፣ አቶ ሽመልስ ተቀብለው ግልፅ ያልሆኑትን የአቶ ሬድዋን አሻሚ ንግግሮች በማብራራት ተጠምደው ነበር። በተለይ አክራሪ ጽንፈኛ የሃይማኖት ኃይሎችን በጥናት በተደገፉ ማስረጃዎች በግልጽ ቋንቋና አቋም የሚታገል መሆኑ ደግሞ ለአቶ ሬድዋን ሌላ ራስ ምታት መሆኑን የምናውቅ እናውቃለን። ይህም በመሆኑ አቶ ሬድዋን ለስልጣን ካላቸው ጥማት የተነሳ አቶ ሽመልስን እንደ ስጋት ማየት ጀመሩ። የተለያዩ ምክንያቶችም መደርደር ጀመሩ። በስራ ሰዓት ቢሮህ አትገባም። በምፈልግህ ሰዓት ቢሮህ ውስጥ አትገኝም። ስራዎችን ችላ ትላለህ እያሉ አቶ ሽመልስን እንደ ተራ ኤክስፐርት ማዋከብ ተያያዙት። በሁለቱ ዝሆኖች የነበረው ግጭት ከማኔጅመንቱ አልፎ ሰራተኛው ጭምር አሳስቦት ነበር። ለዚህ አለመስማማታቸው ይመስለኛል ፀሐፊው፣ ካሉት ተተኪ አመራሮች ውስጥ በተሻለ ደረጃ አቶ ሬድዋንን ያስቀመጣቸው።

በዚህ ሳምንት በነበረው የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውይይት አብዛኛውን ሰራተኛ ለምንድነው አስተያየቱ ያልሰጠው? ኮምዩኒኬተር ማለት በስብሰባዎች ወንበር አሙቆ የሚሄድ ዜጋ ማለት ነው እንዴ? እንዲያውም ከየትኛውም ተቋም በላይ የሃሳብ ፍጭት እና የመድረክ ግለት ሊኖር የሚገባው በኮምዩኒኬሽን ፅ/ቤት ነበር። አቶ ሬድዋን ግን በአመራር ጊዜያቸው ይሄ ሁሉ እንዳልነበረ አድርገው ነው የሄዱት። ይሄ ነው ከሌሎች ተተኪ አመራች በላይ በቁንጮነት ያስቀመጣቸው?

ፀሐፊው የአቶ ኤርሚያስ ለገሰን መፅሐፍ ሳያላምጥ መዋጡ ካልቀረ ሙሉ መፅሐፋቸው ተቀብሎ ቢሆን ይመረጣልና፣ በገፅ 253 ስለ አቶ ሬድዋን ሲናገሩ አቶ ሬድዋን ማለት ለብሔር አደረጃጀት ጥላቻ ያለውና ለስልጣን መቆናጠጫ ሲል ብቻ ከኪሱ መዞ የሚያወጣ ሰው ነው ብሏቸዋል። አቶ ሬድዋን በተለይ በአንዳንድ ብሔሮች ላይ የከረረ ጥላቻ እንዳላቸው አውቃለሁ። በጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ሰዎችን መንጥረው ለማባረር ያደረጉት ሙከራ፣ ወደ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ተመድበው በህዝብ ግንኙነት አመዳደብ ላይ ከገፅታ ግንባታው ዳይሬክቶሬት በመሆን አማርኛ አብጠርጥሮ የማይናገር ኮሙዩኒኬተር አያስፈልገኝም በማለት ድብቅ አጀንዳቸውን የተወጡበት የመመንጠር ስራ ሳይ አቶ ሬድዋን ለብሔር አደረጃጀት ብቻ ሳይሆን ጥላቻ ያላቸው፣ ለተወሰኑ ብሔሮችም ጭምር እንደሆነ በግልፅ የሚያሳይ ነው። ይሄን ለማስረዳት የፖለቲካ ጥገኛው የአቶ ኤርሚያስ ለገሰን መፅሐፍ መጥቀሱ አስፈላጊ እንዳልሆነ አውቃለሁ፣ ነገር ግን ፀሐፊው በአቶ ኤርሚያስ መፅሐፍ ውስጥ ያለውን ሀሳብ እያስተጋባ በመሆኑ እሾህን በእሾህ ለማለት ነው። 

አንባቢው ሊረዳልኝ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር ከወረዳ የመጡ የተባሉትም ይሁኑ ከተሜው ነን ላሉ ሰዎች አንዱን በማውገዝ ሌላውን በማሞገስ እየፃፍኩ አለመሆኔ ነው። በፅ/ቤቱ በአጠቃላይ ያለውን ችግር የሁላችን የጋራ ችግር ነው። የጋራ ችግር ሲባል ግን በደፈናው ለሁሉም አካላት በእኩል ማካፈል መሆን የለበትም። በጋራ የምንወስደው እንደተጠበቀ ሆኖ በየግላችን የምንጠየቅበት ራሳችንን የምናይበት ለነገ የኮሙዩኒኬሽን ስራዎቻችን የምናጠናክርበትና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተነደፉት ዕቅዶች በህዝቡ ንቅናቄ ዳር እንዲደርሱ የአንበሳ ድርሻ የምንወስድበት ሊሆን ይገባል። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በፅ/ቤቱ ውስጥ እና በየፌዴራል መስሪያቤቱ ያሉ ኮሙዩኒኬተሮች ከገቡበት የአስተሳሰብና የድርጊት ዝቅጠት ሲላቀቁ ነው። በአንዳንድ መስሪያቤቶች በጠባብነት፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ግንባር ቀደም የሆኑ ኮሙዩኒከተሮች አሉ። በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ነበር በቅርቡ የሆነውን ነገር ያስታውሳሉ። በሌሎች መስሪያቤቶችም ተነግሮ የማያልቅ መዓት ችግር አለ። በብልሹ አሰራርና በሙስና ተገምግመው ከፖለቲካ ፓርቲ  በይፋ የተባረሩ ነገር ግን እስካሁኗ ጊዜ ድረስ በኃላፊነት እየሰሩ ያሉ ኮሙዩኒከተሮችም አሉ። በዚህ ፅ/ቤት ያለውን ጉራማይሌ አሰራር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግዶ ሞላጫ ሳሙናዎቹ ቢቻል ተመክረው የሚታረሙበት ካልሆነ ግን “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ…” የሚባሉበት ጊዜ መምጣት አለበት።

መንግስት በኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ያለውን ዝቅጠት መላ እንድታበጁለት የመደባችሁ የበላይ አመራሮች ማለትም ሚኒስትሩና ሁለቱ ዴኤታዎች ለፅ/ቤቱ አዲስ ከመሆናችሁ ጋር ተያይዞ በአጠገባችሁ ካሉ ነባር ዳይሬክቶሬቶች የምትመገቡት መረጃ በጥንቃቄ ልትገመግሙት ይገባል። እንደ ኮሙዩኒኬተር ነገሮችን እስከ ታች ድረስ ወርዳችሁ አብጠርጥራችሁ ካላያችሁና እነሱ በሚሰጧችሁ መረጃ ውሳኔዎች ማስተላለፍ ከጀመራችሁ ነገሮችን መበላሸታቸው አይቀርም። ምክንያቱም ከገፅታ ግንባታ ዳይሬክቶሬት ጀምሮ ሌሎችም በአንድ ሰው ውሳኔ ብቻ በኢ-ምክኒያታዊነት መንገድ የተሾሙ ሰዎች በብዛት ስላሉበት በኮምዩኒኬተር ስም ከተሰገሰጉት ሞላጫ ሳምናዎች ተጠንቀቁ እላለሁ።     

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
940 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us