ኑ እንዋቀስ ይላል ጌታ በስመ አብ ወወለድ ወመንፈስ ቅዱስ አሜን

Wednesday, 18 November 2015 14:22

 

 

…ባለፈው በጋዜጣዋ እትም ስለአባታችን መምህር ግርማ አንድ ማስታወሻ በብእር ስሜ ሻሎም ሻሎም በሚል ጽፌ መላኬ ይታወሳል። ሆኖም በአደባባይ ዝርፊያለው አርእስት ብቻ መልክቱ ያለምንም መሸራረፍ ሳይገጥመው ለንባብ በመውጣቱ ላመስገን ይፈቀድልኝ። ብእር ስሜ ባለመገለጹ አላኮረፍም፤ ምክንያም ሊያጋጥም የሚችል ስህተት በመሆኑና ከዋናው አዘጋጅም ጋር ተነጋገረን፤ ተመካክርን ያለፍን ስለሆነ መልእክቱ የሰናይ ደጉ ሳይሆን የሻሎም ሻሎም መሆኑ በድጋሚ ይታወቅልኝ።

…ይህ በአርእስት የገለጽኩት የመጽሀፍ ቅዱስ ቃል ዘወትር ይገርማኛል፤ ይደንቀኛል፤ መንፈሳዊ ጥማቴን ያረካኛል። ለማንኛውም ሀጢያተኛና (ቅዱስ ሰው የለም እንጂ) ለቅዱስም ሰው የሚማርክ ቃል ነው ብዬ አስባለሁ።

ጌታ አምላከችን ኑ እንዋቀስ፤ እስቲ ቅረቡኝና እንነጋገር፤ የበደልኩዋችሁን ንገሩኝ፤ ጥፋት ካለብኝ፤ ካሳዝንኩዋችሁ፤ ካስቀርሁባችሁ፤ ከተሳሳትኩ፤ ውቀሱኝ ማለቱ ነበር። እሱ ግን አያጠፋም፤ ስህተትም አይገኝበትም እንጂ። ማንም ሰው በደል ቢያገኝብኝ ውቀሱኝ ብሎ በነጻነት በትንቢተ ኢሳያስ የተናገረው ቃል ነው። እኛንማ የሚወቅስበት በርካታ ምክንያቶችና ስህተቶች፤ ሀጢያቶች አሉት። ይህ ቅዱስ አምላክ አባት ኑ እንወቃቀስ ሲል የሰው ልጅ ግን እንኳን ውቀሱኝ ሊል ቀርቶ ስህተቱን ቢነግሩት የማይወድና የሚያኮርፍ ፍር ነውና ይህ ቃል ከአንደበቱ አይወጣውም።

ይህን ቃል ኑ እንዋቀስ፤ ኑ እንተራረም ብላ ቤተክርስቲያንም፤ ሌሎች የሀይማኖት ተቋማትም፤ ማህረ ቅዱሳንም ወኔው ኖሮአዋቸው አምላካቸውን ለማስመሰል እንኳ አይጠቀበትም። አንዳንዴ በዚህ ዳይ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቃሉን በተግባር ባያውሉትም ለየስላ ይጠቀበታል ብዬ አስባለሁ። ግምገማን እንደዋቢ አድርጌ መቁጥር እችላለሁና።

ይህ የመግቢያ መንደርደሪያ ያነጣጠረው በአባታችን መምህር ግርማ በሰሞኑ በእስር ላይ መገኘት ብቻ ሳይሆን የወደፊትም ጉዞአቸውን በተመለከተና በአገልጋዮችና በቤተክርስቲያን መካከል ሊኖረው የሚገባውን ግንኙነትና አሰራር ከወዲሁ አንድ ነገር ለማለት ይረዳ ዘንድ በማሰብ ነው።

አባታችን የተከሰሱበትን ጉዳይ አግባብ ነው፣ አይደለም የሚለውን የህግ አግባብ ለመተቸት ፍላጎት የለኝምና ወደ ክስ ፋይል ቻርጅ መግባት አያስፈልገኝም። ምክንያቱም እውነቱ በማንም ምእመናን ዘንድ ይታወቃልና። ከዛም በላይ ቅንብሩና፤ ዝግጅቱ በማን እንደተከናወን ስለምናውቅ ብዙ አሳሳቢ አይደለም። ኧረ እንዲያውም ጠላቶቻቸው ለዚህ ምግባራቸው ይባረኩ። የሚያሳዝነውየፍርዱእልባትበተወሰነጊዜእንዳያልቅየተለያዩሰበቦችንበማቅረብተለዋጭቀነቀጠሮበመጠይቅየአባታችንንሞራልለመንካትመድከምከንቱነትይመስለኛል።አባታችንመንፈሳዊበመሆናቸውከዚህምበላይለሆነቸግርራሳቸውንሳያዘጋጁጌታንለማገልገልቆርጠውአይነሱምናሁላችንምምእመናንበጸሎትእንድናስባቸውጌታእግዚአብሄርእውነተኛዳኛእሱስለሆነፍርዱንእንዲሰጠንበዚህአጋጣሚበጌታስምእጠይቃለሁ።

ጥፋት ተገኘ፤ ስህተት ተፈጸመ ተብሎ ቢታመንበት እንኳ በአባታችን አገልግሎት ላይ መንፈሳዊ አባቶች ከአባታችን መምህር ግርማ ጋር ሊወቃቀሱ፣ ሊነጋገሩ በተቻለ ነበር። ቤተክርስቲያንም አባታችንን ጠርታ ምነው ይህ ያለ ፈቃድ መንቀሳቀስ እኮ አግባብ አይደለም። ደግሞም እርስዎ በቤተክርስቲን ያደጉ አባትና አገልጋይ ነዎት ብላ መውቀስ የምትችል እናት ናት። ሆኖም ለምን ይህ አልተፈጸመም ተብሎ ጣትን መቀሰር ባይገባም እባካችሁ አስቡበት ለማለት ግን የሚቻል ይመስለኛል።  

የአባታችንን ክስ ለማቀነባበር ከፍተኛ የድራማ ባለያዎች ለመሳተፋቸው አስረጂ ባይገኝም የተዶለተች ክስ ለመሆኗ አያጠያይቅም። የህግ ጠበቆችንም አስተዋል፤ አባታችንን ያለ ስማቸው ስም ሰጥተው አደባባይ አውጥተዋቸዋል፤ መንግስትንም አዘናግተዋል፤ መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ ገባ ተብሎ እንዲታማ ቢያደርጉ ምን ይባላል? እነማን ናቸው? ድራማው በማን እንደተቀነባበረ ?ይህንን የአምላክ ፈቃድ በመጣ ጊዜ ሚስጥሩ ከጣላቶቻቸው ጉያ ትወጣለች። ያውም ጉድ የሚያስብል የደባ ሽረባ ይዛ።

አባታችን ለምን ተከሰሱ

መቼም የአባታችንን አገልግሎት በተመለከተ ብዙ ከመባሉም አልፎ አገልግሎታቸውን በውጭው አለም ለማዳረስና ምእመናንን ከአጋንንት እስራት ለማውጣትና ከአምላክ የሚላከውን ፈውስ በአባታችን በኩል ለማድረስ ጌታን ለማገልገላቸው ምስጋና መስጠትና ክብር ሊቸራቸው ሲገባ ያለ ሲኖዶሱ (ይህንን ፈቃድ ሰጭ አካል በውል ባለማወቄ ነውና ከተሳሳትኩ ይቅርታ) ፍቃድ ነው የሚያገልግሉት ብሎ መወንጀል ተገቢ አይመስለኝም። አስፈላጊም ከሆነ ይህንን ፈቃድና የመድረክ ፕሮግራም ዝግጅት ማመቻቸት የሚገባት ቤተክርስቲያን ነበረች። ለምእመኗ በማዘንና አገልግሎት ለመሰጥት እረኛ እንደመሆኗ።

እንዲሁም ቤተክርስቲያን የአባታችንን አገለግሎትና ለቤተክሰርስቲያን ከምእመናን በስጦታና በስለት የሚያስገቡትን ገቢ በማየት አስፈላጊውን ድጋፍ ተጠይቃ ሳይሆን የቤተክርስቲያናትና የአድባራት በርን ለመክፈት ኃላፊነት ያለባት አካል በመሆኗ ይህንን ባለማድረጓ ልትወቀስ ይገባታል ባይ ነኝ።

በቅናትም ይሁን ባለመረዳት የአባታችንን አገልግሎት የሚቃወሙትን ማህበረ ቅዱሳንና፤ ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጽህፈት ቤት እስቲ ጥያቄዎችን ላቅርብ

$1§  ለመሆኑ ጌታ ኢየሱስ የመረጣቸው ደቀ መዛሙርቶች በወቅቱ ከነበረችው ቤተክርስቲያን በየአመቱ የሚታደስ ፍቃድ ተሰጥቷቸው ይሆን?

$1§  ጌታንስ ለማገልገልና የአምላክ ስጦታና ጸጋ የተሰጠውንና ለአገልግሎት የመረጠውን ሰው እንዲያገለግል ፈቃድ ለመስጠት ብቃት ያለው ምድራዊ ባለስልጣን ማን ይሆን?

$1§  ጌታ አምላካችንስ አገልጋዮቹን እንዲያገለግሉት ሲመርጣቸው በምን መስፈርትስ ነበር? ፈቃድ ሊያወጡ የሚችሉት? እነማንስ ነበር ፈቃድ ማውጣት ያለባቸው? በእርሱ የሚያምኑትን ወይስ የቤተክርስቲያንን ህግ ብቻ የሚያከብሩትን ወይስ ዘመድ አዝማዶቻቸው በስልጣን እርከን ላይ ያሉ አገልጋዮች? መቼም ለዚህ መልስ አገኛለሁ ብዬ ባላስብም ጌታ አምላከችን ኑ እንዋቀስ እንዳለ ሁሉ እባካችሁ እናንተ የጌታ አገልገይ ነን ባዮች፤ እናንተም የቤተክርስቲያን ጠባቂ ነኝ ባዮች እባካችሁ ጌታን ትመስሉ ዘንድ በጌታ ፍቅር ለምንኩዋችሁ። ቅረቡና ተወቃቀሱ፤ በእናንተ ምክንያት ምእመናን ግራ አይጋባ፤ ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ አይጉደፍ።

ለነገሩ ሀዋሪያው ጳውሎስ በወቅቱ ሚስጥሩ ሳይገለጥለት የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት በማሳደድና የጌታን አገልጋይ ኢስጢፋኖስን በድንጋይ አስወግሮ ወደ ሞት አለም የሸኘ አልነበረምን? ዛሬም አባታችንን ከዚህም በላይ ቢያስድዷዳቸው አይገርመኝም። እስከ ደማስቆስ ድረስ ሊጓዙ ይችሉ ይሆናል ከዛ ኢየሱስ በብርሀን ተገልጦ ..እናንተ ማህበረ ቅዱሳን፣ እናንት የሲኖዶስ አባላትና ወግ አጥባቂዎች ለምንስ ታሳድዱኛላችሁ ብሎ አይናቸውን አሳውሮ ሂዱ ወደ ወንድማችሁና አባታችሁ መምህር ግርማ የአይናችሁን ቅርፊት ያነሱላችኋል ማለቱ አይቀርም ብዬ አምናለሁ።

ሁለተኛ የተከሰሱበት ጉዳይ ላይ አስተያየት ባይሰጥበት የተሻለ በመሆኑ ዝም፤ ጭጭ፤ ጸጥ፤ ማለትን መርጫለሁ። ምክንያቱም ወደፊት በሰፊው ከኔ የተሻሉ የነዛ ወገን የድራማው ተዋንያኖች እርስ በርስ በመጋጨት እውነቱን ማንም ሰው ሳይጠይቃቸው ጌታ እግዚብሄር አዞአቸው በራሳቸው ጊዜ ይቅርታ የሚጠይቁበት ጊዜው ቅርብ ነውና።

የኦርቶዶክስ ሀይማኖታችንና አገልጋዮችን ሊቃወም የሚችል ቢኖር እንኳ ከክርስትና እምነት ውጭ ያለ ሀይማኖት እንጂ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ የሚያምን የቤተ እምነትና አገልጋይ መሀከል እርስ በርስ እንዲህ ያለ ያገጠጠና ያፈነገጠ ጥላቻ ይደርሳል ብዬ ለማመን እቸገራለሁ።

የባህታዊ ገ/መስቀል መወገዝ፤ የማህበረ ቅዱሳን በሲኖዶሱ ጽ/ት ቤት መረገም፤ የቅዱስኤልያስ ተከታዮች ናቸሁ ተብለው እግራችሁ ቤተክርስቲያን ድርሽ እንዳይል መባል፤ የነዲያቆን በጋሻው አገልግሎት ጥላሸት መቀባት፤ የዘማሪያን አገልግሎት ተቀባይነት ማጣት፤ በሲኖደሱ ጽህፈት ቤትና በውስጡ ባሉት ዲያቆናትና ቀሳውስት ያለ መከፋፈል፤ የአባታችን መምህር ግርማ አገልግሎት ታላቁዋንና ታሪክ ያላት ቤተክርስቲያናችንን መደሰት ሲገባት በጥላቻና በጥርጣሬ አይን ማየት፤ ሁሉ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ላይ ያነጣጠረና የተወረወረ ፍላጻ ጉዳዩ በቀላሉ የማይታይና ሊታሰብበት ይገባል ባይ ነኝ። መቼ? ዛሬውኑ ተለያይተው ሳይነቋቆሩ በመቀራርብ እየተወቃቀሱ፤ እየተራረሙ፤ እየተመካከሩ በጋራ እየጸለዩ ሲሄዱ መፍትሄው ያኔ ይገኛል።

እንደ ግሌ ከላይ ስለጠቀስኳቸው ማንነትና የውስጣቸውን ጉድለት እንዲሁም ከመሰረቱ ማንታቸውን የማወቅ እድል ስላጋጠመኝ ለዚህ ድርጊታቸው በተለይም በአባታችን መምህር ግርማ ላይ የተነሱበትን ዋንኛ አላማ በማስረጃ ለማቅረብ ጥቂት ቀናትን ይፈጅብኛል እንጂ መቻሌን በእርግጠኛነት ናገር እችላላሁ። ግን ምን ሊራባ? ምን ሊፈይድ?

አንድ በማህበረ ቅዱሳንና ቀድም ሲል በሲኖዶስ ጽህፈት ቤት ያገልግል የነበረ ወዳጄ በነበረበት የግል ጉዳይ ወደ ክፍለ ሀገር ለተወሰነ ቀናት ከጓደኞቹ ጋር አብሬያቸው ሄጄ ነበር። በቆይታችን ውስጥ ስለበርካታ ጉዳዮች አንስተን ስንወያይ ቆይተን ስለማህበረ ቅዱሳን አመሰራረትና አገልግሎት በሰፊው አነሳን። መጥፎውንና በጎ ጎን ተመለከትን። ያኔ አንዱ ተሳታፊ ለማመን የምቸገርበት ግን እውነት የሆነ ጉድ አፍረጠረጠው።

አንድ በአንድ አንስቶ ካስፈለገም ማስረጃ ሁሉ እንዳለው አረጋግጦ እውነት ይህ እየተፈጸም ነው እስከምል ድረስ ብዙ ያማላውቃቸውን ጉድ የሚያስብል ሚስጥር አወጋን፤ ከዚህ በላይ መስማት ተሳነኝ። ለመሆኑ ይህን ምእመናንና ተከታዮቻቸው በማህበረ ቅዱሳን ስም የሚካሄደውን ያውቁታል አልኩ? የተመለሰልኝ መልስ ግን እሰከ ወዲያኛው የዚህን ሚስጥር ተጨባጭ ለማወቅ አስወሰነኝና እውነቱን ለማውጣት ይሄው እየቆፈርኩ ነው፡

በአንድ በኩል ማህበሩ የሚያከናውናቸውን በጎ ተግባራት ከልቤ እቀበላለሁ። ደግሞም መልካምና በስነ ጽሁፉም ሆነ በመንፈሳዊ እውቀታቸው አንቱ የተሰኙ ግለሰቦች ስብስብም እንደሆነ እረዳለሁ ..ግን የዚህ ድርጊትና በመሀከል ያለው መከፋፈል መነሻው ምን እንደሆነ ለማወቅ እቸገራለሁ። የተወሰኑ ግለሰቦችንና ከጽ/ት ቤቱ የሚወጡትን በራሪ ጽሑፎችንና ደብዳቤዎች አግኝቻለሁ። ይህንነ አደባባይ ማውጣቱ እንደ ክርስቲያን ስነ ምግባር አስፈላጊ አልመሰለኝም ደግሞስ ምን ሊራባ? ምንስ ሊፈይድ?

ቀጠልንና ስለሲኖደሱ ጽ/ት ቤት አወጋን። አማናቸው ማለት ይቀላል እሱ ፈጣሪ ይቅር ይበልን እንጂ። የተወሰኑ የአገልጋዮች ሀብት ሚስጥር፤ የጥቂት የአንድ አካባቢ ጎሳዎች አገልጋዮች ብቻ ምርጫ ጉዳይ፤ የሲኖዶሱ ሀብት በሆነው የክልል የሚገኙ የቤት ኪራይ ገቢ የት እንደሚገባና፤ ማን እንደሚጠቀምበት፤ በተለይም ከገጠር ቤተክርስቲያን የሚሰበሰብ ገንዘብ ገቢ ሁኔታ፤ የአሜሪካ ቪዛ ለማግኘት ያለውን ጣልቃ ገብነት፤ እዚሁ በሀገር ውስጥ ወደ ተሻለ ቤተክርስቲያን ለመመደብ ዝውውሩን ለሚፈጽም አካል የሚከፈል እጅ መንሻ መኖር፤ ውጭ ሀገር ባሉ ቤተክርስቲያን ለማገልገል የሚቻልበትንና ለፈቃጆች የሚከፈለውን ክፍያ በተመለከተ፤ በተለይም በአባታችን መመህር ግርማ ላይ ያለው ለመቀበልና ያለመቀበል የውስጥ መከፋፋልና በእኝህ አባታችን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ ግለሰቦችን አንስተን ተወያየን፤ ለኔ ግን መቼውንም የማላገኘው ሚስጥር ለማወቅ ተቻለኝ።

ስለመምሀር አባታችን መምህር ግርማ ሲነሳ አንድ አብሮን የነበረና ከጨዋታችን ቆጠብ ያለ ወዳጃችን ኮረኮረውና እንዲህ አለን፤

….እኔ መምህር ግርማን በጣም እጠረጥራቸው ነበር። ብዙ ጊዜም ተከታትያቸዋላሁ ጥርጣሪዬን ግን ያነሳሁት ችግሩ በራሴ ላይ ስለደረሰ ብቻ ሳይሆን የእሳቸውን ጸጋ ስጦታ ከጌታ መሆኑን በማረጋገጤ ነው። ከዛን ቀን ጀምሮ አከብራችዋለሁ ባይገርማችሁ በቤተክርስቲያን እንዳያገልግሉ የተከለከሉት በአስማት አጋንንትን ሰለሚያወጡ ሳይሆን፤ ከምእመናን የሚገባውንና የሚሰበሰበውን ገንዘብ እንዲያካፍሉ በተደጋጋሚ ተጠይቀው እምቢ ስላሉ ብቻ ነው። በአስማትማ አጋንንትን እንዲህ በቀላሉ ማውጣት የሚቻል ቢሆን በአለም ላይ የሚገኙ በርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ ቀሳውስትና ዲያቆናት፤ ፓስተሮችና ወንጌላውያን ወደ ሱዳን ኧረ እንዲያውም በመተት ወደ ምትታወቀው ህንድ ወይም ሀይቲ ሄደው መተቱን በሚገባ ችብችበውና ተቀብተው በመጡና ምድርን በሞሉና አጋንንትና መናፍስትን ባሰሩ ነበር። ደግሞም የግል ገቢያቸውን በአጭር ጊዜ ወደ ቢሊየነርነት በለወጡ። ግን ይህ ሁሉ ውሸት ነው።

ማህበረ ቅዱሳንም በእኝህ ሰው አገልግሎት መጠቀም ይፈልጋል። እሳቸው የማይነጥፍ ገቢ ነበሩ። የሚገርማችሁ እስጢፋኖስ በማገለግልበት ወቅት እሳቸው (ያኔ አብረን ነበርን) በእሳቸው አገልግሎት ሳቢያ ዘወትር የሚገባውና የሚሰበሰው መባ በማናቸውም ክብረ በአል ከሚገባው ገንዘብ በላይ ነበር። በዶላር፤ በብር፤ በዩሮ ምንዛሪ ሳይቀር። ደምዎዝና ሌላም ጥቅም የእስጢፋኖስ አገልገይ ያገኘው በእሳቸው ነው።

በግላቸው የገንዘብ ስጦታ ሲሰጣቸው እንኳ ለቤተክርስቲያኗ ነበር የሚሰጡት፤ የሚገርመኝ ከውጭ ሀገር በግላቸው የተላከላቸውን ገንዘብ መባ በሚሰበስብበት ሳጥን ሲያስገቡ አይቻለሁ። ምንም እንኳ በአጠገባቸው ጥቂት ችግር ያለባቸው ሰዎች ቢኖሩም የተቻላቸውን ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር።

ግን ይህን ሚስጥር ለምን በአደባባይ እንደማያወጡ አላውቅም። ለምን እንደሚፈሩም አይገባኝም። ብቻ በጣም ጠለቅ ያለ ሚስጥር ያውቃሉ ብዬ እገምታለሁ። የፈሩበትም ምክንያት ይኖራል ሞትን እንኳ ባይፈሩ፤ የሰው ህይወት እንዳይበላሽ የቤተክርስቲያን ሚስጥር አደባባይ እንዳይወጣ ተጠንቅቀውና አስበው ይሆናል። ብሎ የሚያውቀውን ዘረገፈልን ለመሆኑ አገልጋይ ነበርክ አልኩት..አዎ የተከለከልኩ አገልጋይ እንጂ አለኝ።

አዘንኩ አይ አንቺ ቤተክርስቲያን ..በስምሽ ስንት ግፍ ተሰራ አልኩ

ወደ ጽሁፌ ማገባደጃ ደርሻለሁ። ህዝበ ክርስቲያንን የምማጸነው ቢኖር ክፉውን በክፉ ለመመለስ እንዳይሞክር ነው። በርካታ ሚስጥሮች አሉ አውቀን ዝም ያልንባቸው፤ ተጎልጉለው የማያልቁ በመሆናቸው። በቤተክርስቲያናችና በእምነታችን ላይ አደጋ የሚሆኑና ለእምነታችን ተቃዋሚ በቂ ማስረጃ ማቀበል ስለሆነ መተውን መርጫለሁ። እባካችሁ እናንተም ሁሉን ተውና ጌታ አምላካችንን እናስቀድም። ቃሉንም እናክበር።

አባታችን መምህር ግርማና ሌሎች ብዙ አባቶቻችን ለአገልግሎት ተመርጣችኋልና ክርስቶስን ምሰሉ። ቢያሳድዷችሁ፤ ቢገርፉአችሁ፤ ቢያስሯችሁ፤ ቢቃወሙአችሁ፤ አትርገሙ እነሱ የተፈጠሩት ለዚህ ነውና።

ኑ እንዋቀስ ይላል የሰራዊት ጌታ   

ሻሎም ሻሎም   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1230 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us