መልዕክት ለባለአክስዮኖችና ለባለድርሻ አካላት

Wednesday, 18 November 2015 14:21

 

 

በሺፈራው ተስፋዬ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

     

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በተለይ ለባለአክስዮኖች ሲሆን ከአክስዮን ማህበራቸው ጋር የተያያዙትን የሕግና የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ መረጃ ለማቅረብና ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው።  ምክንያቱም መረጃውና ግንዛቤው ያለው ባለአክስዮን ከኩባንያው /ከአክስዮን ማህበሩ/ ጋር የተያያዙትን ጉዳዮች ለመከታተል፣ ለመረዳት፣ ለመጠየቅ፣ በችግሮቹም ላይ ለመወያየትና የመፍትሔ ሐሳቦችን ለማቅረብና ውሣኔ ለመስጠት አይቸግርምና ነው። በሌላም በኩል አክስዮን ማህበራት የሥራ ሂደትና ውጤት ተጠቃሚና ተጐጂም የሚሆኑ በርካታ ባለድርሻ አካላት ስላሉ እነሱም የበኩላቸውን አስተዋጽኦና ትብብር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

አክስዮን ማህበር በሲስተም ማዕቀፍ ውስጥ የሚመራና ከባለአክስዮኖች የተለየ ራሱን የቻለ ሕጋዊ ሰውነት ያለው የቢዝነስ ድርጅት ቢሆንም ሲስተሙ በትክክል እንዲሠራና ውጤታማ እንዲሆን ባለአክስዮኖች መተኪያ የለሽ ሚና ይኖራቸዋል።  ባለአክስዮኖች ማህበራቸው በትክክለኛው ሥርዓት እየሠራ ውጤታማ እንዲሆን መከታተልና መልካም ውጤት ሲገኝ ደግሞ የቦርዱ፣ የማኔጅሜንቱና የሠራተኛው የተቀናጀ ውጤት ስለሆነ ሁሉንም ማመስገን፣ ማበረታታትና እንደሁኔታውም መሸለም ለቀጣይ የተሻለ ውጤት መሠረት ይሆናል።

በሌላ በኩል ከውስጥና ከውጭ በሚመነጩ ችግሮች የተነሳ ሠርቶ ውጤት ማስመዝገብ ወይም ማግኘት ካልተቻለ ችግሩንና መንስኤን አጥንቶና አውቆ መተግበርም ትክክለኛው የቢዝነስ ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው። የቢዝነስ ሥራ ችግር ወይም ፈተና ሲገጥመው ብቃት ያለው ትክክለኛ አመራርና አሠራር ቦታው ላይ ካለ ችግሩን ለማደግና ጠንክሮ ለመውጣት እንደመልካም ዕድል ወይም አጋጣሚ ተጠቅሞበት ነጥሮ ወደ ተሻለ ደረጃ ለመወጣት ያስችላል። ካልሆነ ግን የኋሊት ጉዞውን መያያዙ አይቀርም። የኋሊት ጉዞ በኪሣራ፣ በጥፋትና በጉዳት የታጀበ ሲሆን፤ ይህም ባለአክስዮኑን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ባለድርሻ አካላትንም ማለትም አገርን፣ ሕዝብንና መንግሥትንም ጨምሮ የሚገባቸውን ጥቅም በማጣት ተጐጂ እንዲሆኑ ማድረጉ አይቀርም።  ይህ እንዳይሆን ባለአክስዮኖች የወከሉዋቸው የቦርድ አባላት ሥራውን በሕጉና በትክክለኛው አሠራርና አመራር በብቃት መሥራት አለመሥራታቸውን በመከታተል ሕጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ ግድ ይሆናል።  በዚሁ መሠረት ከዚህ በታች በ1952 ዓ.ም. በወጣው ንግድ ሕግ መሠረት በባለአክስዮኖች ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃዎች በአጭሩ ቀርበዋል። እነዚህን እርምጃዎች መጠቆም ያስፈለገው ቁጥራቸው በቀላሉ በማይገመቱ አክስዮን ማህበራት ውስጥ በተለይ ከቦርድና ከማኔጅሜንት በሚመነጩ ችግሮች የተነሣ መሥራት አቅቶአቸው፣ ሐብታቸውም ባክኖ ወይም ተዘርፎ፣ የሥራ ዕድል ያገኙት ሠራተኞች ተበትነው፣ ሕብረተሰቡ ያገኝ የነበረው አገልግሎት እየተዳከመ ወይም ቆሞ፣ የባለአክስዮኑ፣ የሠራተኛውና መንግሥትም /በታክስ ያገኘው የነበረው/ ገቢ ቆሞ ወይም ቀንሶ፤ በአጠቃላይ የአገር ሐብትና የዕድገት ዕድል እየባከነ ነው።  ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ ትልቅ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስና ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ፤ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚወሰዱት እርምጃዎች እንዳሉ ሆኖ፤ በተለይም የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የሆነው ባለሐብት / ባለአክስዮን ሊወሰድ የሚገባቸው ሕጋዊ እርምጃዎች በጥቂቱ ቀርበዋል። ባለአክስዮኖች ስለኩባንያቸው መረጃ እየቀረበ ግንዛቤ የሚኖራቸውና ውሣኔም የሚያስተላልፉት በባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ነው። ጉባኤ ካልተደረገ በስተቀር ስለኩባንያቸው ተገናኝተው ተወያይተው ውሣኔ ለማስተላለፍ አይችልም። ጉባኤዎቹም ሁለት ዓይነት ሲሆኑ አንዱ ደንበኛ ወይም መደበኛ ጉባኤ ሲሆን ሌላው ድንገተኛ ወይም አስቸኳይ ጉባኤ ነው። ጉባኤዎቹ የሚጠራባቸውና የሚካሄድባቸው የተለያዩ ሕጋዊ ሁኔታዎችና ጊዜያት አሉ።  በተቻለ መጠን ሁለቱን ጉባኤዎች ጐን ለጐን ማካሄድ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት ይቆጥባል።  ኢኮኖሚስቶች cost-effective እንደሚሉት ማለት ነው።

በንግድ ሕጉ ቁ. 418/1 መሠረት የሒሳቡ ማጠቃለያ ከተዘጋበት ቀን ጀምሮ በአራት ወራት ውስጥ በአስተዳዳሪዎች /በቦርዱ/ ጥሪ በየዓመቱ አንድ ደንበኛ የሆነ ጠቅላላ ጉባዔ ይደረጋል በማለት ተደንግጓል። ይህ ማለት ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ጥቅምት 30 ድረስ ጠቅላላ ጉባዔ ይደረጋል ማለት ነው። ቢሆንም ይህ የጊዜ ገደብ እስከ ስድስት ወር ድረስ፤ ማለትም እስከ ታኅሣሥ 30 ቀን ድረስ፤ በመተዳደሪያ ደንብ ሊራዘም እንደሚችል ንዑስ ቁጥር 2 ይገልፃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙ ባለአክስዮን ከአንድ መደበኛ ወይም ደንበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ውጭ እንደሚደረግ የሚያውቅ አይመስልም። ሕጉ ግን በንዑስ ቁ. 3 ላይ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሌላ ደንበኛ/መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ሊደረግ ይችላል በማለት ደንግጓል። ይህ ጉባዔ ከድንገተኛ ወይም ከአስቸኳይ ጉባዔ የተለየ መሆኑ መጤን አለበት። በሁለቱ ጉባኤዎች የሚቀርቡት አጀንዳዎችና የአወሳሰን ሥርዓታቸውም የተለያዩ መሆኑም መታወቅ አለበት።  ወደ አጀንዳ ዝርዝር ሳንገባ ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ታኅሣሥ 30 ቀን ድረስ ያሉት የአክስዮን ማህበራት የጉባኤ ወራት ናቸው ማለት ነው። ታዲያ በነዚህ ወራት እና በተለይም በጉባኤው ቀን በባለአክስዮኖች ዘንድ ተገቢውን ማስተዋል ወይም ትኩረት የሚፈልጉ የሕግና ሌሎች የተያያዙ ጉዳዮችን ማስታወስ ይጠቅማል።

በሌላ በኩል የባለአክስዮኖች መብትና ሚና ምንድነው? የሚለውን ጉዳይ በአጭሩ እንመልከት።  የባለአክስዮኖች መብቶች በን.ሕ.ቁ. 389 መሠረት ከሕግ፣ ከደንብና ከመመሥረቻ ጽሑፍ እንዲሁም ከጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊነት የሚመነጩ ሲሆኑ እነሱም በማህበርተኛነት ድምጽ የማግኘትና የመስጠት፣ የማህበሩን ውሣኔ የመቃወም መብት፤ የትርፍ ድርሻና ማህበሩ ሲፈርስ ድርሻን የመካፈል መብት ናቸው። ከመብቶቹ ውስጥ የማህበሩን ውሣኔ የመቃወም መብት የሚለው ሊሰመርበት የሚገባ ነው። ይህ መብት ከሌሎች መሠረታዊ የባለአክስዮኖች መብቶች ጋር በእኩልነት የተቀመጠ ነው። ሕጉ በሚደነግገውና በአካሄድም ተቀባይነት ያለውም ቢሆን እንኳን አንድ ባለአክስዮን ወይም ሃያ በመቶ የሚሆኑ ባለአክስዮኖች በጉባዔው ላይ ብቻ ሳይሆን በፍ/ቤትም አቤቱታ ሊያቀርቡ ይችላሉ። ነገር ግን ሕገወጥ የሆኑ የቦርድና የማኔጅመንት ውሣኔዎችን እና አሠራሮችን መቃወም የኩባንያውን ውሣኔና ሥራ እንደመቃወም ሊቆጠር አይችልም።

በአክስዮን ማህበራት ጠቅላላ ጉባዔ /ጠቅላላ ባለሐብቶች/ እና በቦርድና በማኔጅሜንት መካከል ያለው ግንኙነት፤ በንግድ ሕጉ እና በፍትሐብሔር የውክልና ሕግ ላይ ተመሥርቶ፤ በመመሥረቻ ጽሑፍና በመተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም በጠቅላላ ጉባኤ ውሣኔዎችና በመደበኛው አሠራር ላይ የተመሠረተ ይሆናል።  በዚሁ መሠረትም ጠቅላላ ጉበኤ በተለይ በቦርዱ ላይ ሁለት መሠረታዊ ውሣኔዎችን ሊያስተላልፍ ይችላል። ይህም የቦርድ አባላትን መሻርና በሌላ መተካት ሲሆን ሌላው እርምጃ ወይም ውሣኔ ግዴታቸውን በአግባቡ ባልተወጡትና ጉዳት ባደረሱት ላይ ለደረሰው ጉዳት በአንድነት ኃላፊ ማድረግን ይመለከታል።

በዚሁ መሠረት በሁለት የንግድ ሕግ ድንጋጌዎች ሥር የተደነገጉትን እርምጃዎች በአጭሩ እንመለከታለን። የንግድ ሕግ ቁ. 354 ስለአስተዳዳሪዎች ማለትም ስለቦርዱ መሻር ሲገልጽ “ከዚህ ጉባኤ ተቃራኒ ቃል ቢኖርም በማናቸው ጊዜ አስተዳዳሪዎች በጠቅላላ ጉባኤ ሊሻሩ ይችላል” በማለት ሲገልጽ በተመሳሳይ ሁኔታ የን.ሕ.ቁ. 397/2 የቦርዱ አባላቱን የመሻር ጉዳይ በዕለቱ አጀንዳ ባይያዝ እንኳን በሰበር አጀንዳ ማለትም “በማናቸውም ጊዜ አንድ ወይም ብዙ አስተዳዳሪችን ለመሻርና በምትካቸው ሌላ ለመሾም ይችላል” በማለት የጠቅላላ ባለሐብቱን ያልተገደበ መብት በድጋሚ ያረጋግጣል።

በሌላ በኩል የቦርድ አባላትን መሻርና ማሰናበት ብቻ ሳይሆን በኃላፊነት የሚጠየቁበትም የሕግ አግባብ አለ።  በን.ሕ.ቁ. 364/2 መሠረት “አስተዳዳሪዎቹ ግዴታቸውን ያጓደሉ እንደሆነ ለደረሰው ጉዳት በማህበሩ ዘንድ በአንድነት ሳይከፋፈል ኃላፊዎች ይሆናሉ” በማለት ይደነግጋል። በኃላፊነት የሚጠየቁትም በን.ሕ.ቁ. 364/3 እና 4 መሠረት ኃላፊዎች የሆኑበትን ጠቅላላ ሥራ አመራርና ለማህበሩ ጉዳት የሚያመጡ ሥራዎች መኖራቸውን እያወቁ ለመከላከል ወይም የጉዳቶቹን ምክንያቶች ለማቃለል የሚቻላቸውን ያላደረጉ እንደሆነ በኃላፊነት እንደሚጠየቁ ተደንግጓል። ከዚህ በላይ ከተገለፁት ተጠያቂነት ለመዳን አስተዳዳሪዎች በቅን ሕሊናና በትጋት ለመሥራታቸው ማስረዳት አለባቸው። ከዚህ በላይ የተገለጠው በንግድ ሕግና በፍትሐብሔር የውክልና ሕግ መሠረት ለፍ/ቤት የሚቀርቡ ጉዳዮች ናቸው።  ከዚህ ውጭ ሌሎችም አማራጮች አሉ። 

ቦርድና ማኔጅመንት በሚሠሩዋቸው ሕገወጥ ሥራዎች ዓይነት በወንጀል ሕግ ሊሸፈኑ የሚችሉ ጉዳዮች ይኖራሉ።  እንዲሁም በአዲሱ የፀረ-ሙስና የተሻሻሉ ሕጐች ሥር የሚወድቁ ጉዳዮች ይኖራሉ። እነዚህን ሁለት ጉዳዮች በተመለከተ ባለአክስዮኖች ጉዳዩን ለፖሊስና ለዐቃቤ ሕግ እንዲሁም ለፀረ-ሙስና ኮሚሽን በተሻሻለው አዋጅ መሠረት በመረጃ አስደግፎ በማቅረብ ጉዳዩን መከታተል ይጠበቅባቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የሕግ አስፈፃሚው አካል ለሆነው ለንግድ ሚኒስቴር በንግድ ሕግ ቁጥሮች 381፣ 382፣ 383፣ 384 እና 386 ሥር የሚወድቁትን ጉዳዮች እንዲጣራ በማድረግ የሕግ ወይም ሲጣሩ የምርመራውን ውጤት ለፍ/ቤት ማቅረብ ሌላኛው አማራጭ ነው። በርግጥ መሠረታዊ የሕግ አፈፃፀምና የአሠራር ለውጥ ካልተደረገ በስተቀር በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሱትን እርምጃዎች በሌላው ቀርቶ በአክስዮን ማህበር ደረጃ መተግበር ቀላል እንዳልሆነ በተግባር ታየቷል። ይህም ባለአክስዮኑ በሕግና በሥርዓት ተማምሮ እርምጃ እንዳይወስድ ያደርገዋል።

ባለአክስዮኖች ስለማህበራቸው የሚወያዩበትና የሚወስኑበት መድረክ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሆነ ቀደም ሲል የተጠቀሰ ሲሆን አንዳንድ ቦርዶች ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት ፈቃደኛ የማይሆኑበት ጊዜ አለ። ይህም ሲያጋጥም በን.ሕ.ቁ. 377 መሠረት የማህበሩ ኦዲተር ቦርዱን ተክቶ እንዲጠራ ማድረግ ይቻላል።  ሌላው አማራጭ ጉዳዩን ለፍ/ቤት በማቅረብ ፍ/ቤት ጉባኤውን የሚጠራ አካል እንዲወሰን ማድረግ ይቻላል። ጉባኤውን የሚመራው ስብሰባውን የሚጠራው አካል ነው።  ጉባኤው ከመደረጉ ከ15 ቀናት በፊት የጉባኤው ጥሪ መተላለፍ እንዳለበት ሕጉ ይደነግጋል።  ጥሪ የሚደረግባቸው ሁኔታዎች ከዛሬ 55 ዓመታት በፊት በተደነገገው አካኋን ሳይሆን ዛሬ የቴክኖሎጂው ዕድገት በፈቀደበት ዓይነት ለባለአክስዮኑ ሁሉ ጥሪውን ተደራሽ ማድረግ ይገባል።  ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ አስገራሚ ሁኔታ አጋጥሟል። ይኸውም ሁለት የሕግ ጠበቆች በነበሩበት የአልፋ ቦርድ ውስጥ የጉባኤውን ጥሪ የምናደርገው በ1952 ዓ.ም. በወጣው የንግድ ሕግ ድንጋጌ መሠረት ብቻ ነው የሚል ክርክር ነበር። የሕጉ ዓላማና ግብ ጥሪው ደርሶ ባለአክስዮኑ በጉባኤው ላይ እንዲገኝ በመሆኑ ብዙ አክስዮኖች በእጅ ስልክ፣ በኢሜይል፣ በፖስታ፣ በጋዜጣ፣ በረዲዮና በቴሌቪዥን በመጠቀም የጥሪውን መልዕክት ለመላው ባለአክስዮን እንዲደርስ ማድረግ የተለመደና ተገቢ አሠራር ሆኗል።

ጉባኤው ተጠርቶ በሚካሄድበት ወቅት ከቦርዱ ሪፖርትና ከኦዲት ሪፖርቱ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮችን ማስተዋል ያስፈልጋል። ሥራቸውን በትክክል የሚሠሩና ትክክለኛ ሪፖርት የሚያቀርቡ ቦርዶች እንዳ ሁሉ፤ ሆነ ብለው አስልተው እውነቱንና ድክመታቸውን በመሸፋፈን የሚያቀርቡ እንዳሉም ይታወቃል።  ሪፖርቱ ከጉባኤው ጥሪ ጋር ቢላክ ነገሮችን በሚገባ ለመመርመር ጊዜ ለማግኘት የሚረዳ በመሆኑና የሕጉም መንፈስ ወደዚህ አሠራር ያዘነበለ ሰለሆነ በዚህ ረገድ ማሻሻያ ያስፈልጋል። በተለይ ችግር ያለባቸው ቦርዶች ሪፖርቱን ስለማይልኩ በደንቡ ውስጥ ወይም መንግሥት በሚወጣው የአፈፃፀም መመሪያ ወስጥ ይህ ጉዳይ ቢካተት እጅግ ጠቃሚ ይሆናል።

የኦዲት ሪፖርቱን በተመለከተ ያሉት የአሠራር ችግሮች በሚገባ መጤን አለባቸው። ይህም ክፍተቶችን ተረድቶ መፍሔውን ለማዘጋጀት ይጠቅማል።  በንግድ ሕጉ ውስጥ ስለአክስዮን ማህበራት ቁጥጥር የተደነገገውና በተግባር በኦዲተሮች እየተሠራ ያለው የሚጣጣም አይመስልም። በተለምዶ አሠራር ኦዲተሮች እንደመስቀል ወፍ በዓመት አንድ ጊዜ እየመጡ በማኔጅሜንት የተዘጋጀውን ሪፖርት ትክክለኛነት ከማረጋገጥ ያለፈ ሥራ እየሠሩ አይደለም። ይህም ሥራቸውንና ሚናቸውን ወደ ማረጋገጫ ማህተምነት (Rubber stamp) የወረደ ነው የሚል ትችት አስከትሏል። ችግሮች እንዳሉ በገሃድ እየታየና እየተጠቆመ እንኳን ያቺኑ የተለመደችዋን አስተያየታቸውን በመስጠታቸው ከባለአክስዮኖች ከፍተኛ ተቃውሞ የቀረበባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም ምንም ለውጥ ሳይታይ አሠራሩ ቀጥሏል።  ጉዳዩን በአንድ ተጨባጭ አብነት አይተን እንለፈው። ለአልፋ አክስዮን ማህበር አምናና ካቻምና የቀረበው የኦዲት ሪፖርት /ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ቀርቦ ሊሆን ይችላል።/ በባለአክስዮን ዘንድ በገሀድ የታወቁ መረጃዎችንና አሠራሮችን ያላካተተ ነበር። ይኸውም በኩባንያው ላይ የስምንት ሚሊዮን ብር ዕዳ እንዳለ ቢገለጽም ዕዳው በፋይናንሽያል እስቴትመንት ላይ ሳይታይ የኩባንያው ሐብት፣ እንዲሁም ትርፍና ኪሣራ የቀረበበት አሠራር ትክክል አልነበረም።  በተጨማሪም የኩባንያው ባንክ እስቴትመንት ሳይመሳከር (Bank Reconciliation ሳይሰራ) በመቅረቡ ተቃውሞ ቢቀርብም ውጤት አልተገኘም።  የሁለቱም ዓመት ሪፖርቶች ሲቀርቡ የንግድ ሚኒስቴር ተወካዮች እዚያው ነበሩ። ከጉባኤውም በኋላ ጉዳዩ በማመልከቻ ለንግድ ሚኒስቴር ቢቀርብም ውጤት የለም። ሌላው ቀርቶ ኦዲተሩ የጻፈው አስተያየት እንኳን ለባለአክስዮኑ እንዲደርስ አልተደረገም ነበር። ኦዲተሩ እነዚህ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሪፖርቱን ማቅረብ ከሙያው ሥነ-ምግባር አንፃር ተገቢ ነው ቢባሉ “እኔ መረጃው ካልቀረበልኝ ምን ማድረግ እችላለሁ” የሚል መልስ ሰጥተው ነበር። የዚህ ዓይነት አሠራሮች ጀርባቸው በሐቀኛ ኦዲተር ቢመረመር ጉድ የሚያሰኝ ነገር ሊወጣው ይችል ይሆናል።  ትክክለኛ ላልሆነ አሠራር እያወቁ ሕጋዊ ሽፋን የሚሰጡ ኦዲተሮችን የሚከታተልና አጣርቶም እርምጃ የሚወስድ አካል መኖር አለበት ብዬ አስባለሁ።  በሌላ በኩል በራሳቸው በአክስዮኑ ማህበራት ውስጥ ያለው ውስጣዊ የቁጥጥር ሥርዓት በሚገባ መጠናከር ያለበት ነው።  አልፋ ውስጥ አስተማማኝ የቁጥጥር ሥርዓት እንዲኖር፤ በደንቡ ወስጥ በማሻሻያነት እንዲታከል፤ በባለአክስዮኖች አስተባባሪ ኮሚቴ የቀረበው ሐሳብ ለባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ እንኳን ሳይቀርብ እንዲቀጭ ተደርጓል። ስለሆነም ውጪያዊና ውስጣዊ የአክስዮን ማህበራት ቁጥጥሮችን በተመለከተ በርካታ የሚሠሩ ሥራዎች ስለሚኖሩ እና ወሳኝም ስለሆኑ ባለአክስዮኖችና የንግድ ሚኒስቴር ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

አክስዮን ማህበራት አንድ ዓይነት አይደሉም። የሚመሳሰሉባቸው ጉዳዮች ቢኖራቸውም በብዙ ጉዳዮች ደግሞ ይለያያሉ። ልዩነቱ በአክስዮን ማህበራት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት መካከልም መሠረታዊ ልዩነት እንዳለና፤ ይህም በኩባንያው ላይ ያስከተለውንና የሚያስከትለውን ተጽእኖና እንድምታ ቀላል ላይሆን ይችላል። ስለሆነም ችግሮችና መፍትሔዎቹ ከልዩነታቸውም አንፃር መታየት አለባቸው። ይህ ማለት አንድ ዓይነት መድኃኒት ለሁሉም ማዘዝ አይቻልም ማለት ነው። ስለሆነም አክስዮን ማህበራት እንዳሉበት ሁኔታና እንደችግራቸው ደረጃ ተለያይተው መፍትሔዎች መቅረብ አለባቸው ማለት ነው።    ስለ አክስዮን ማህበራት ዝርዝር ጥናት ተደርጐ ባይገኝም በውስን የግል ዳሰሳ መሠረት በሚከተሉት ዓይነት ከፋፍሎ ማየት ይቻላል።  በመጀመሪያ ደረጃ ችግር የሌለባቸውና ሥራቸውን በአግባቡ የሚሠሩ የተወሰኑ አክስዮን ማህበራት ይኖራሉ።  እነዚህ ማህበራት በዚሁ መቀጠልና ችግሮች እንዳይፈጠሩ አስፈላጊዎቹን ጥንቃቄዎች ማድረግ ይገባቸዋል።  በሌላ በኩል ግን ብዙ አክስዮን ማህበራት ችግር ውስጥ ያሉ ስለሆነ “ነግ በኔ” ነውና በአገር አቀፍ ደረጃ ችግሮች የሚፈቱበት ሥርዓት እንዲኖር አስተዋጽኦና ድጋፍ ከማድረግ መቆጠብ የለባቸውም።

በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚመደቡት ገና ከባድ ችግር ውስጥ ያልገቡ ነገር ግን ሠርተው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ አቅቷቸው በማሽቆልቆል ሂደት ላይ የሚገኙ ናቸው። እነዚህ ማህበራት በአፋጣኝ ችግሮቹን ማወቅና ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ ጉዳት እንዳይከተል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ከባድ ችግር ውስጥ የገቡና መሥራትም ስላልቻሉ ወደ ኪሣራ (bankruptcy) እያዘገሙ ያሉና አንዳንዶቹም ኪሣራ ወስጥ የገቡ ናቸው። እነዚህ ማህበራት አጣብቂኝ ውስጥ ስለገቡ ወደፊትም ለመሄድ፣ ወደኋላም ለመመለስ አስቸጋሪ በሆነ አጣብቂኝ ውስጥ ናቸው። ሁኔታውን በጥልቀት በማጥናት የማይድኑ ከሆነ ሐብት ሳይባክን በጊዜ መግደል፤ የሚድኑ ከሆነ ደግሞ ባለአክስዮኑ ተስማምቶ መስዋዕትነት ከፍሎ ለማዳን ጥረት ማድረግ የባለአክስዮኑና የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ኃላፊነት ነው።  በአራተኛ ደረጃ የተመደቡት ደግሞ ምንም ዕዳ የሌለባቸውና በቂ ቋሚ ሐብት ያላቸው ቢሆንም በተለይ በቦርዱና በማኔጅሜንቱ ድክመት እና ችግር የተነሣ መሥራት አቅቷቸው ቢዝነሱና ተቋሙ /ድርጅቱ/ እየፈረሰና እድላቸውና ሐብታቸው እየባከነ የሚገኙ ናቸው። ቢሆንም ለጊዜው የወድቀት ኪሣራ (bankruptcy) ስጋት ባይኖርባቸውም ያለውን ሐብት ወደውጤት ለመቀየር ባለመቻላቸው በሠራተኞች፣ በደምበኛው፣ በባለአክስዮኑና በባለድርሻ አካላትም ጭምር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ያለበት ሁኔታ ላይ የሚገኙ አሉ። ይህን በቀላሉ ለመፍታት የሚያስችል ዘዴና ሥርዓት ከውስጥም ከውጭም ባለመኖሩ ችግሩን መፍታት አልተቻለም።

ስለሆነም የአክስዮን ማህበራትን ችግር ለመፍታት አጠቃላይ የሆነ ጥረት የሚያስፈልግ ሲሆን ችግር የሌለባቸውም ባለአክስዮኖች ‹‹ነግ በኔ›› በሚለው መርሕና፤ እንደየደረጃቸው ችግር ያለባቸው ባለአክስዮኖች ደግሞ አክስዮን ማህበራትን ያጋጠሙ ችግሮችን፤ ከአገር አቀፍ ውጭያዊ ችግሮች ጀምሮ እስከ ውስጣዊ ችግሮች ድረስ በጋራ በሚፈቱበት አቅጣጫ ላይ ፖሊሲ፣ መመሪያ፣ ደንብና ሕግም እንዲወጣ መተባበርና መረባረብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ባለአክስዮኑ ሳይንቀሳቀስ ሌላ አካል መጥቶ ችግሩን የሚፈታበት ሁኔታና ዕድል በቅርብ ስለማይታይ ነው። በእያንዳንዱ አክስዮን ውስጥ ያጋጠሙትን ችግሮች በቀላሉ ለመፍታት እንዲቻል በመጀመሪያ ደረጃ በአገር አቀፍ ደረጃ ችግሮች የሚፈቱበት የመንግሥት ፖሊሲ አቅጣጫ፣ የአፈፃፀም መመሪያ፣ የአስፈፃሚው አካል ዝግጅትና ድርጅት፣ ባለአክስዮኖች ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት ውስጣዊ የሲስተም ማዕቀፍ እንዲኖር የሚያስፈልገውን ሁሉ በአንድነት ቆሞ መጠየቅና ምቹ ሁኔታዎችንም ለመፍጠር ድጋፍና ትብብር ያስፈልጋል። ከዚያም ባለአክስዮኑ በውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ አክስዮኑን ማጽዳትና ማስተካከል ይጠበቅበታል።

በርግጥ ቀደም ሲል የአክስዮን ማህበራት ጉዳይ ባለቤት ስላልነበረውና የንግድ ሕጉ የአፈጻጸም መመሪያ አሁንም ባለመኖሩና ከንግድ ሚ/ርም፣ ከንግድ ሕጉ ቁ. 381 ጀምሮ በተደነገጉት ቁጥሮች መሠረት በቂና ተገቢውን መፍትሔ ለማግኘት አልተቻለም ነበር። በርካታ ባለአክስዮኖች ለኩባንያቸው መፍትሔ ፍለጋ በተመሳሳይ ሁኔታ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበረ ይታወቃል። ቢሆንም ጥረቱ በየኩባንያው የተበታተነና ያልተቀናጀ በመሆኑ ባለአክስዮኖች በግል ለየአክስዮኖቻችን መፍትሔ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት በቂና አርኪ ውጤት አላስገኘም። በርግጥ ቆይቶም ቢሆን ለአክስዮን ማህበራት ድጋፍ የሚሰጥ ዳይሬክቶሬት መቋቋሙ በራሱ በጎና አዎንታዊ እርምጃ ቢሆንም የተከማቹና ውስብስብ ችግሮችን ለማቃለል በርካታ ሥራዎች፣ ዝግጅትና ድርጅት እንዲሁም ተመጣጣኝ አቅምና በጥናት ላይ የመተሠረተ እርምጃ ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት በርካታ አክስዮን ማህበራት ከደረሱበት የችግሮች ደረጃ አንፃር ባሉበት ቆመው መፍትሔ መጠበቅ አይችሉም።  ወደ መፍትሔው ሥርዓት በጋራ በመሄድና የመፍትሔውን አቅጣጫ በተሳትፎ እየቀየሱ እና እያሣዩ ችግሮች እንዲፈቱ አስተዋጽኦ በማድረግ፤ የችግሮች ገፈት ቀማሽ ብቻ ሳይሆኑ የመፍትሔውም አካልና ተጠቃሚ መሆን፤ ለአክስዮን ማህበራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኖ ቀርቧል። ምክንያቱም የአክስዮን ጉዳይ ያገባናል፣ መብትና ጥቅም አለንና። ጥቅሙ በቀጥታ የባለአክስዮኖች ብቻ ሳይሆን ከበስተጀርባቸው በቀጥታ ለቤተሰብና ቀጥታም ባልሆነ ሁኔታ ተጠቃሚዎችና ተጐጂዎች ይኖራሉ። ጥቅሙ የባለአክስዮኑ ብቻ ሳይሆን መንግሥትም በታክስ መልክ ገቢ ያገኛል።  ዜጐች ሥራና ገቢ በማግኘታቸውም ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ብቻ ሳይሆን ለመንግሥትም ፖለቲካ ጥሩ ነው።  ሕብረተሰቡም በልዩ ልዩ መልክ የጥቅሙና የጉዳቱ ተቋዳሽ ይሆናል። በሌላ አንፃር ከሕግና ከመብት አንፃርም ከታየ ዜጐች ቆጥበው ኢንቨስት ያደረጉትን ሐብት ሕግና መንግሥት ባለበት አገር ማጣት የለባቸውም። መንግሥትም ለዜጐች መብትና ጥቅም ጥበቃ ማድረግ ይጠበቅበታል።  ሕጋዊ ሥርዓቱ መሥራት አለበት።  ለዚህ ደግሞ ችግሩ የደረሰባቸው ባለአክስዮኖች ብቻ ሳይሆኑ ያልደረሰባቸው ነግ በኔ ነውና ተባብረው አብረው መቆም አለባቸው።  በዚህ ረገድ ዜጐችም ግዴታቸውን መወጣትና መብታቸውን ለማስከበር ሚናቸውን መጫወት አለባቸው።

የአክስዮኖች ጉዳይ የአገር፣ የሕብረተሰብ፣ የመንግሥትና የዜጐችም ልማት በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት ማግኘት ይኖርበታል።  ዛሬ ችግሩ ባለመፈታቱ ወይም ካልተፈታ ጉዳቱ የሚደርሰው ዛሬ ላይ ብቻ ሳይሆን ነገም ላይ ጐጂ ተጽእኖ የሚፈጥር መሆኑ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል። ዜጐች እስከዛሬ ቆጥበው ኢንቬስት ያደረጉት ገንዘብ ውጤት ካላመጣና ከወደመ ነገ ኢንቨስት ለማድረግ አይበረታቱም።በአገራችን ዛሬ 809 የተቋቋሙና ምናልባትም በሂደት ላይ ያሉ 41 አክስዮኖች ይኖራሉ ብንል በጠቅላላው 850 አክስዮን ማህበራት፤ ከ90 አስከ 100 ሚሊዮን ለሚገመት ሕዝብ እጅግ ትንሽ ነው። ወደፊት በብዙ መቶ ሺ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አክስዮኖች ያስፈልጉናል።  ከአክስዮኖች ተፈጥሮ፣ ከአመራርና ከአሠራር የሚከሰቱትን ድክመቶችና ችግሮች በሥርዓት መቋቋምና ማስወገድ ከተቻለ ከሁሉም የተሻለ ለብዙሀን የሐብት ክፍፍልና ጥቅም ለማዳረስ ያስችላል የተባለው የአክስዮን ማህበር አደረጃጀት ውጤት አልባ ሆኖ ይቀራል።  ይህን የልማት መሣሪያ የሆነ ተቋም በአግባቡ ገንብቶ፣ ተንከባክቦ በአግባቡና ውጤታማ በሆነ ሁኔታ መጠቀም ለሁሉም ይበጃል፣ ከብዙ አማራጮችም የተሻለ ነው። ምክንያቱም በጠቅላላው የኩባንያው ሥራ በዋነኛነት ሦስት ወገኖችን በቀጥታ ይጠቅማል።  በመጀመሪያ ደረጃ ገንዘብ በመቆጠቡና ኢንቨስት በመደረጉ ከፍተኛ ካፒታል ይፈጠርና በሚገኘውም ትርፍ ቆጣቢ ዜጐች ይጠቀማሉ። እነዚህም ሙያና ሌላ ሥራ የሌላቸው ወይም ያላቸው፤ ደካሞች ሆነው ለመሥራት የማይችሉ፣ እየሠሩ ቆጥበው ለወደፊት መጦሪያቸው ኢንቨስት የሚያደርጉ፣ ወዘተ በሚገዙት አክስዮን አማካይነት ከፍተኛና ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ካፒታል፤ ለሥራ ዝግጁ በማድረግ አገር እየለማች፣ ዜጐችም ይጠቀማሉ። በሌላ አንፃር የሥራ ዕድል በማግኘት ጉልበታቸውን፣ ሙያቸውንና ክህሎታቸውን በመሸጥ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ገቢ የሚያስገኙና በሥራ ልምድም ችሎታቸውንና ሙያቸውን የሚያሳድጉና፤ ከገቢያቸውም ለመንግሥት ግብር የሚከፍሉ ተጠቃሚዎች ናቸው።  በሦስት ደረጃ የሚጠቀሱት ቀደም ሲልም እንደተጠቀሰው መንግሥት በልዩ ልዩ መልኩ ተጠቃሚ ሲሆን እንደሰንሰለት በተያያዙ ሁኔታዎች ሕብረተሰቡ ይጠቀማል፣ አገርም ትለማለች። ይህን ሁለንተናዊ ጠቃሜታ ያለውን የልማት መሣሪያ ችግሮቹና ድክመቶች ተወግደው ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት በሙሉ የራሳቸውን ድርሻ መወጣት ወይም መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ባለአክስዮኖች አሁን የደረሰባቸው ችግር ብቻ ሳይሆን፤ ለወደፊትም ዘለቄታ ያለው መፍትሔ እንዲቀየስና፤ አክስዮኖች ጠቃሚ የልማት መሣሪያ እንዲሆኑ መስዋዕትነት የመክፈል ኃላፊነታቸው በመወጣት፣ መብታቸውን አስከብረው የሚገባቸውን ጥቅም አግኝተው በውጤቱም የልማት አሻራቸውን በሚገባ በሥርዓት መሬት ላይ ማሳረፍ ታሪካዊ የልማት አስተዋጽኦ መሆኑን መዘንጋት አይገባቸውም። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
922 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us