ሞኝን አንዴ ስደበው፣ ራሱን ደጋግሞ ሲሰድብ ይኖራል!

Wednesday, 25 November 2015 15:10

 

 

ክፍል ሁለት

የዛሬው የፅሁፌ ከባለፈው የቀጠለ ክፍል ነው። በባለፈው ፅሁፌ ዋና ማጠንጠኛ ያደረኩት በጋሞ ብሔር-ውስጥ የዶርዜ አካባቢ ሕዝብ (የዶርዜ ዴሬ) ጥያቄ፣ ማለትም የአካባቢው የልማትና መሰል ጥያቄዎች በውስጡ ሌላ-ሌላ ነገር ባረገዙ ሀይሎች ሲገፋ ቆይቶ በአሁኑ ወቅት በምን ደረጃ ላይ እንደደረሰና ለዶርዜ ሕዝብ መብት ቆመናል በሚሉ ክፍሎች በራሱ በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰትና ነፃነት ማሳጣት ጭምር ለማሳየት ሞክሬያለሁ። በዛሬው ፅሁፌ ደግሞ በጋዜጣው ላይ የፀሐፊው ሻመናና ሻመና ባደነቀው ታዳላ በጋሞ ሕዝብ ላይ በተሰነዘሩ የስድብ፣ የንቀትና የሽርደዳ ነጥቦች ላይ ምልከታየን ከራሴ ሀሳብና አቋም ጋር በማዛመድ አቀርባለሁ።

ከዚያ በፊት ግን ለመግቢያ ያህል ብሔር {Nation}, ነገድ ወይም ጎሳ {Tribe}, ቤተሰብ ወይም የዘር ሀረግ {Clan} በሚለው ላይ ትንሽ መነሻ ሀሳብ ጠቃቅሼ ለማለፍ እፈልጋለሁ።

አንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ የብሔረሰብ እውቅና ሊኖር የሚገባው ሕዝቡ አንድ ትልቅ የማህበረሰብ ክፍል የሆነ ሕዝብ ሲሆን፣ -በአንድ መልክአ ምድራዊ ክልል (ግዛት) ውስጥ ተሰባስቦና ተባብሮ የሚኖር ሕዝብ ሲሆን፣ -አንድ የራሱ የሆነ የተለየ መግባቢያ ቋንቋ ያለው ሕዝብ ሲሆን፣ -የራሱ የሆነ ከሌሎች የተለየ ባህልና ለረጅም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ያካበተው ወግና ልማድ ያለው ሕዝብ ሲሆን፣ -የራሱ የሆነ የፖለቲካዊ ፀባይ( ባሕሪይ) ያለው ሕዝብ ሲሆን፣ እና የራሱ የሆነ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ መሰረት ያለው ሕዝብ ሲሆን ነው። በእንግሊዘኛው ጥሬ ትርጉም (Nation- Is A Large community grohp of People, Associated With a Particular territory, Ususual Speaking a single or different language,  Have their own culture,  Political character or aspiration and  Socio economic grounds) በማለት ይገልፀዋል።

እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው ሁኔታዎች አንድን ሕዝብ ብሔረሰብ ለማስባል የሚችሉ ዋና ዋና መስፈርቶች ሲሆኑ መስፈርቶቹ ከሌሎች በኩታ ገጠም ከሚኖሩ ሕዝቦች ጋር የጋራነት (ዝምድና) ፀባይ የሌላቸው ግልጽ የሆነ ልዩነትን የሚያሳዩ መሆን እንዳለባቸው እና ከኩታ ገጠም ሕዝቦች ጋር ያለው የሕዝቡ ወይም ማህበረሰቡ የስነ ልቦና ወይም የማንነት ልዩኔታዊ አመለካኬት ልቀራረብና እርስበርሱ ልቀባበል ወይም ሊቻቻል የማይችል መሆን ሲችል ነው የተለየ ሕዝብ (ማህበረሰብ) ነው ሊባል የሚችለው። ከዚህ በመለስ ያለው የነገድ (የጎሳ)፣ ወይም ሰፋ ያለ የዘር ሀረግ አሊያም ቤተሰባዊ ስብስብ ሆኖ ሊገኝ ይችላል።

ነገድ (ጎሣ) “Tribe” በአንድ ብሔረሰብ ውስጥ ያለ የሕዝብ ክፍል ነው። ይሔው የሕዝብ ክፍል ከሌላው በተለየ እጅግ የተቀራረበ ሁኔታ የሚኖር ሕዝብ ነው። “Clan” በትልቅ ቤተሰባዊ ደረጃ ተጠጋግቶ የሚኖር የማህበረሰብ ክፍል ነው። ይሔውም {Tribe} በአማርኛ አጠራር ነገድ (ጎሳ)፣ በጋሞዎች አጠራር «ዴሬ» የምንለው የሕዝብ ክፍል ሲሆን {Clan} የምንለው ደግሞ በአማርኛው አጠራር ከአንድ የዘር ሀረግ የመጣ ቤተሰብ ብለን ብንወስድ የሚያስኬድ ይመስለኛል። ይሔውም በጋሞኛ «ኦሞ» የተባለው ክፍል ነው። ኦሞ በተለያየ የጋሞ ዴሬዎች ውስጥ ቢኖርም የአንድ እናት፣ የአንድ አባት ልጆች ናቸው፣ አንድ ደም፣ አንድ ዘር ነው ተብሎ ይታወቃል። ለምሳሌ በጋሞ ብሔር ውስጥ ባሉ በርካታ ዴሬዎች «ጋዎማላ» የተባለ ኦሞ በብዛት አለ። ይህ ጋዎ ማላ በየትኛውም የጋሞ ዴሬ ውስጥ ቢሆን እርስ በእርሱ አይጋባም። ሌላው ኦሞም እንደዚሁ ነው። ምክንያቱም እህትና ወንድም ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ነው። ለዚህ ነው በአማርኛው አጠራር ከአንድ የዘር ግንድ የመጣ ቤተሰብ ብንል ያስኬዳል ያልኩት። ለመግቢያ ያህል ይሔን ካልኩኝ ወደ ፀሐፊው ሓሳብ ልመለስ።

ፀሐፊው ሻመና በፅሁፋቸው ውስጥ አንዳንድ ቦታ ላይ ታዳላን ከተገቢው በላይ ሲያደንቁና ሲክቡት ይታያሉ። በአንዳንድ ቦታ ላይ ታዳላን ብቻ ሳይሆን ታዳላ የፃፈውን የማዶላ መፅሀፍ ጉድለቶች የሚሏቸውንና የመፅሀፉ ፀሐፊ አላዋቂነትን ጭምር አንስተው ይተቻሉ። በአንዳንዱ ቦታ ላይ በተለይም ከፅሁፋቸው ርዕስ ጀምሮ ታዳላ በመፅሃፉ ውስጥ የገለፃቸውንና የጋሞ ሕዝብን ከዳር እስከ ዳር ያስቆጣውን አባባል በማንሳት በማዶላ ፀሐፊ አባባል ብቻ ሳይሆን በራሳቸው መንገድ ጭምር በመደጋገም የራሳቸውን ፍላጎትና ስሜት ጭምር ሲገልፁና ሲሸረድዱ ይታያሉ።

በእርግጥ አንድ ሰው ማንንም ሆነ የትኛውንም ነገር ከፈለገ የማድነቅ መብቱ የተጠበቀ ነው። አግባብነት ባላቸው ነገሮችና ጉዳዮች ላይ የሌሎችን መብት፣ ክብርና ነፃነትን ሳይነካ ሀሣብ የማቅረብ፣ አስተያየት የመስጠትና ሀሳብን የመተቸት መብትም ይኖረዋል። በዚህ መንገድ ካየነው የማዶላ ፀሐፊም ሆነ የሻመናን አንዳንድ ሀሳቦችን እንደ መብት በማየት ማለፍ ይቻላል። ነገር ግን ሻመና እንገደለፁት በታዳላ የተፃፈው ስድብ ጥቂት ጋሞ ነን ባይ ግለሰቦችን…ሳይሆን መላው የጋሞ ሕዝብ መብቴ ተነካ፣ ክብሬ ተዋረደ፣ ህልውናየ ተደፈረ ብሎ ከዳር እስከ ዳር እንዲንቀሳቀስ ያደረገ ስድብ ነው። ይህን የስድብና የማንቋሸሽ ቃላትን (አባባሎችን) ሻመና እንዳለ ተጠቅሞ መልሶ እየደጋገመ በመሳደብና በመሸርደድ መፃፍ ነፃ አስተያየት ነው፣ መብት ነው ለማለት የሚቻል አይመስለኝም። በዚህ ላይ ይህ ስድብ እኛ ዶርዜዎችን አይመለከትም ለማለትም ሞክረዋል። የተሰደበው፣ መብትና ክብሩ የተነካው፣ ተበደልኩ፣ ተሰደብኩ ብሎ እየተንቀሳቀሰ ያለው እኛ ዶርዜዎችን ጭምር ያካተተ ሕዝብ መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም።

ሻመና በፅሁፋቸው ርዕስ «ዛሬ ጋሞ የሚባል ቀበሌ ሳይኖር የማንነት መገለጫና የራሱ ቋንቋ ያለው ሕዝብ ሊሆን አይችልም…»በማለት ገልፀዋል። ይህ አባባል በማዶላ መፅሀፍ በገፅ69 ላይ የተገለፀ ነው። ሻመና መፅሀፋን ሲያደንቁ ይህንን ሀሣብም ጭምር አድንቀዋል። ለመሆኑ በሀገራችን ካሉ ከ80 በላይ ብሔሮች ውስጥ የትኛው ብሔር በቀበሌ ስም እንደሚጠራ ማስረጃ ወይም ምሳሌ ይኖራቸው ይሆን? አንድ ቀበሌ የብሔር መጠሪያ የሆነበት ፀሐፊዎቹ የሚያውቁትን ዋቢ ማቅረብ ይችሉ ይሆን?  በኢትዮጵያ ትልቁን የሕዝብ ቁጥርና የቆዳ ስፋት የያዘው የኦሮሞ ብሔር ነው። በሕዝብ ብዛት 2ኛውን ደረጃ የያዘው የአመራ ብሔር ነው። ወደ ደቡብ ክልል ወረድ ካልን ደግሞ በክልሉ ትልቁን የሕዝብ ብዛት የያዘው የሲዳማ ብሔር ነው። እነዚህ ብሔሮችም ሆኑ ሌሎቹ የሀገራችን ብሔሮች ያሉባቸው አካባቢዎች የሰፈሩባቸው ቦታዎች የተጠሩትና የሚጠሩት በብሔሩ ስም ወይም በሕዝቡ አሰያየም እንጂ በቀበሌ ስም አይደለም። ብዙ ብሔሮች ባሉባቸው አካባቢዎች የብሔሩ መጠሪያ ወይም መገለጫ የሆነ ቀበሌ የለም።

ታዲያ የጋሞ ብሔርን በተመለከተ ጋሞ የሚባል ቀበሌ ሳይኖር ብሔር ሊኖር አይችልም የሚል መደምደሚያ ተሰጥቶ በታዳላም ሆነ በሻመና ሊፃፍ የቻለው ከምን መነሻ ይሆን? ሻመና ታዳላ ሲሳሳት አብሬ ልሳሳት ካላሉ በስተቀር ለጽሁፋቸው ይህን የተሳሳተ ርዕስ ሰጥተውና አድንቀው ባልፃፉ ነበር።

ጋሞ የሚባል ቀበሌ ሳይኖር የማንነት መገለጫና የራሱ ቋንቋ ያለው ሕብዝ ሊሆን አይችልም፣ በሚለው ርዕስ ውስጥ ታዳላም ሆኑ የታዳላን ጽሁፍ ያደነቁት ሰው የአንድ ሕዝብ የማንነት መገላጫ አንድ ቀበሌ ወይም አንድ በስሙ የሚጠራ ቀበሌ መኖር እንደሆነ አድርገው የወሰዱት ስለብሔር ባላቸው ግንዛቤ መጠን ይመስለኛል። ምክንያቱም ታዳላ ከቀበሌም ወርደው በግላቸው «እኔ የኡማ ብሔር ነኝ….» ብለው ለራስ ብሔርነትን የሰጡ  ሰው ናቸው። ይህን ሀሳባቸውን ለማጠናከር ማንም ሰው ወይም አካል እኔ የዚህ ብሔር ነኝ ካለ ማንነቱ ቢረጋገጥና ቢሰጥ ምን ችግር አለው? በማለት የሚጠይቁ ናቸው። ሻመናም ይህን አባባል አጠንክረው ይደግሙታል። በዚህ አባባላቸው እኔ የዚህ ብሔር ነኝ ብያለሁና ማረጋገጫ ይሰጠኝ አሊያም እነ እገሌ ብሔር ነኝ ብለው የጠየቁ ስለሆነ ለምን ብሔርነት ማረጋገጫ አይሰጥም? ቢሰጥ ምን ችግር አለው? የሚል ነው። ይህቺ ጎንበስ-ጎንበስ ለምን ትመቻለች እንዲሉት ተረት ሀሣባቸው በጥልቀት ሲታይ አካሔዳቸውን በቀላሉ ማወቅና ማረጋገጥ ይቻላል።

የማዶላ ፀሐፊ ጋሞ...የራሱ ቋንቋ ያለው ሕዝብ ሊሆን አይችልም ብለዋል። ሻመናም ይህን ይጋሩታል። መጋራት ብቻ ሳይሆን በፅሁፋቸው ውስጥ በቆሞ በዶርዜኛ (ኦሞ) በማለት የገለፁበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ይህ ማለት ያው እንደተለመደው ዶርዜ ለብቻው ቋንቋ አለው ለማለት ነው። የማዶላ ፀሐፊ የጋሞን ቋንቋ  ለማን ሊሰጡት ፈልገው እንደሆነ ባይገባኝም በዶርዜ ተወላጆች ስብሰባ ላይ በተለያየ ጊዜ መጥተው እንደነበርና ምክር ሲሰጡ እንደነበር አውቃለሁ። ከአዲስ አበባ ተነስተው ዶርዜ ድረስ ሔደው ሲመክሩ እንደነበርም በአንደበታቸው ሲናገሩ ሰምተናል። ግለሰቡ ስብሰባዎች ላይ መጥተው ሲናገሩ የነበሩት በጋሞኛ ቋንቋ መሆኑን እንዴት ዘነጉት? ወይስ ጋሞኛን አዲስ ወደ ፈጠሩት ኡማ ብሔር ቋንቋነት ለመቀየር ፈልገው ይሆን?

በሌላ በኩል ሻመና “በዶርዘኛ ኦሞ” ሲሉ የገለፁት ዶርዘኛ ከጋሞኛ የተለየ  ቋንቋ ነው ለማለት እንደፈለጉ ግልፅ ነው። ዞሮ ዞሮ የሁለቱም ግለሰቦች መንገድና ፍላጎት አንድ ነው። ቋንቋው ዶርዘኛ ነው። ጋሞ የራሱ ቋንቋ የለውም ለማለት ነው። ታዳላም ሆነ ሻመና አይናቸውን ከፈት አድርገው ቢመለከቱ ጥሩ ነው። እኛ ዶርዜዎች ዙሪያችንን የተከበብነው በዶኮ፣ በጨንቻ፣ በአቾሎ፣ በሻማ፣ በጋንታ፣ በዜጌቴ ዴሬዎች ነው። እነዚህ ዴሬዎች ሁሉ የጋሞ ብሔር አካል ናቸው። የሚናገሩት ቋንቋ ጋሞኛ እንጂ ዶርዝኛ አይደለም።

የጋሞ ሕዝብ ዶርዜን ጨምሮ በዘጠኝ ወረዳዎችና ዶርዜን በመሳሰሉ ከሀምሳ (50) በላይ ዴሬ ውሰጥ ያለ ሕዝብ ነው። ዶርዜ ከጋሞ ዘጠኝ (9) ወረዳዎች በአንዱ በጨንጫ ወረዳ ውስጥ የሚኖር ሕዝብ ነው። በጨንቻ ወረዳ ውስጥ ብቻ ዶርዜን ጨምሮ 8 ዴሬዎች አሉ። እነዚህ ስምንቱ ዴሬዎች ጋሞኛን ይናገራሉ። ከ50 በላይ የጋሞ ዴሬዎችም ጋሞኛን ይናገራሉ።

የዶርዜ አካባቢ በፊት አማራና ቦዶን ጨምሮ 6 ቀበሌ የነበረ ሲሆን አሁን ወደ 9 ቀበሌ ከፍ ብሏል። ይህ ማለት በጨንቻ ወረዳ ውስጥ ካለው ከ53 በላይ ቀበሌዎች ውስጥ 9 ቀበሌ ማለት ነው። ይታያችሁ ከ50 በላይ ከሆኑ የጋሞ ዴሬዎች ውስጥ ዶርዜ አንድ ዴሬ ብቻ ነው። ከ53ቱ የጨንቻ ወረዳ ቀበሌዎች ውስጥ ዶርዜ 9 ቀበሌ ብቻ ነው። በጨንቻ ወረዳ ዶኮ የተባለው ዴሬ ብቻውን ወደ 14 ቀበሌ አለው። ኤዞ ዴሬ ወደ 12 ቀበሌ አለው። እነዚህ ዴሬዎች ደግሞ እያንዳንዳቸው አሁን ዶርዜ አለኝ የሚለውንና አሟላለሁ የሚለውን ነገር ሁሉ የሚያሟሉ ናቸው። እያንዳንዳቸው ካኦ፣ ዳና፣ ሁዱጋ፣ ሀለቃ፣ ደቡሻ፣ ገበያ፣ ባሌ፣ ሌላም ሌላም አላቸው። ታዲያ ዶርዜ ከእነዚህ በምን ተለየ?።

የዶርዜ ሕዝብ ብዛት ብንመለከት በገጠር ቀበሌ የሚኖር የሕዝብ ግምት በአንድ ቀበሌ ከ1500 እስከ 2000 ቢሆን ነው። እጅግ ብዙ ሕዝብ ይኖራል በተባለ ቀበሌ ደግሞ ከ2500-3000 ሕዝብ ሊኖር ይችላል። ይህ ማለት በ9 ቀበሌ ቢሰላ በአማካይ ሊኖር የሚችለው የሕዝብ ግምት ይታወቃል። ከዚህ ከገጠር ቀበሌ ውጭ በተለያየ የንግድ ስራና በሽመና ስራ በሀገሪቱ ከተሞች ተበታትኖ የሚኖር የዶርዜ ተወላጅ አለ።

አሁን ባለው አንዳንድ መረጃ መሠረት ዶርዜን ጨምሮ እስከ 2 ሚሊየን እንደሚደርስ የሚገመት ሕዝብ ያለው የጋሞ ብሔር ቋንቋ የለውም ማለት እውነት ከቅን ህልና የሚመጣ (የሚመነጭ) አስተሳሰብ ነው? ወይስ በጋሞኛና በዶርዜኛ መሀከል ልዩነት ስለአለ ዶርዜ ራሱን የቻለ ቋንቋ ያለው ሕዝብ ነው ለማለት ነው?። አሁን አሁን የዶርዜ ሕዝብም እውነቱን እየተረዳ መጥቷል። ስለዚህ እባካችሁ ይህን የምታደርጉ ወንድሞቼ ሆይ ያለፈው ይብቃና ወደ ቅን ልቦና ተመለሱ።

በጣም የሚያስገርመው ሻመና “ጋሞነት የዶርዜ ብሔረሰብን የማይመለከት ሆኖ… “ገሙ ጎፋ” ሲባል “ገሙ” የሚለው ቃል ጋሞ ለማለት ነው? ጋሞን አንድ የሚያደርጉ እሴቶች ምንድ ናቸው?..... ወዘተ በማለት ጠይቀዋል። ሞኝን አንዴ ስደበው ደጋግሞ ራሱን ሲሰድብ ይኖራል፣ የሚለው አባባል ይሔው ነው። ትላንት በነበሩ አስከፊ የፊውዳል ስርዓቶችና በነዚያ ስርዓቶች ወቅት በነበረው አመለካከት የተሰደብነውና የተናቅነው አንሶ ዛሬ እኛው ራሳችንን መልሰን መላልሰን የምንሳደብበት አንደበትና ሕሊና ባለቤቶች ሆነናል እንዴ? ለስድብ ለስድቡማ ከገሙ ይልቅ የእኛ የዴሬ ዶርዜዎች ስም የመሰደቢያ፣ የመዋረጃ፣ የመሸማቀቂያ ስያሜና መጠሪያ አልነበረም እንዴ? አያቶቻችን ቁጭት በጣሽ፣ አባቶቻችን የቁጭት በጣሽ ልጅ እየተባሉ ሲሰደቡ አልኖሩም ነበር? በአባቶቻችንና በታላላቆቻችን ዘመን ዶርዜ በሚለው የአከባቢያዊ ስያሜ ከመጠራት ብለው ተሸማቅቀው ራሳቸውን ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ከንባታ… ወዘተ እያሉ በትምህርት ቤት ያስመዘገቡ የዶርዜ ተወላጆች እንደነበሩ ሻመና አያወቁትም? ሌላው ቢቀር ከአያቶቻችንና ከአባቶቻችን ይህንን እውነታ ሻመና አልሰሙም ይሆን? ያላወቁና ያልሰሙ ከሆነ ዛሬም እውነቱን ለማወቅ አልመሸም። ወደ አዲስ አበባ ሽሮሜዳ፣ ጉለሌ፣ ኮልፌ አካባቢ ያሉ የዶርዜ ሽማግሌዎች ዘንድ ይሂዱና ያነጋግሯቸው። እውነቱን ያገኛሉ።

እዚህ ላይ ሻመናም ሆነ የሻመና መሰል አስተሳሰብ ያለው የዶርዜ ተወላጅ ሁሉ አንድ ነገር ልብ ብሎ እንዲገነዘብ ልጠቁም። ይሔውም በአዲስ አበባ በሸማ ስራ የሚተዳደረው የዶርዜ፣ የዶኮ፣ የጨንቻ፣ የኤዞ፣ የሻማ፣ የወበራ፣ የዶቃማ፣ የቦንኬ፣ የባልታ፣ የዲታ፣ የዛራ፣ የኦቾሎ፣ የጋንታ፣ የዘጌቴ፣ የብርብራ፣ የቦሮዳ፣ የቁጫ፣ የዳራማሎ፣ የጌረሴ… ወዘተ ሕዝብ ሁሉ ዶርዜ ተብሎ እንደሚጠራና ዶርዜ በመባሉም የተለየ ቅሬታ እንደሌለው፣ ጋሞ ተብሎ ሲጠራም የተለየ ሁኔታ እንደማይሰማው፣ ይሔ ሁሉ ሕዝብ ዶርዜነትንም ሆነ ጋሞነትን አሜን ብሎ ተቀብሎ እንደ ሚኖር ልንረዳ ይገባል።

አንዳንድ ራሳቸውን የዶርዜ ሕዝብ ተጠሪና ተሟጋች አድርገው ያስቀመጡ አፈ ጮሌዎች የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ማስረጃ እያሉ በእጃቸው አንጠልጥለው የሚሮጡት ሁለት ገፅ ወረቀት የዚህ ሁሉ ሕዝብ የጋራ ቆጠራ ውጤት መሆኑንም ልንረዳ ይገባል። ያም ሆኖ በዚህ መልኩ የተቆጠረውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽኑ የአሰራር ስህተት መሆኑን አምኖ፣ የደቡብ ክልል መንግስትም ስህተት መሆኑን አምኖ በአሁኑ ወቅት ስህተታቸውን በማረም ዶርዜ ከጋሞ ዴሬዎች አንዱ እንጂ የተለየ ብሔር አለመሆኑን ወስኗል። ሻመና እንዳሉት ጉዳዩ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በደቡብ ክልል እየታሸ ሳይሆን በግልፅ ተወስኖ እልባት አግኝቷል።

ስለዚህ ይህን በውሳኔ የተደመደመ ጉዳይ ለሕዝቡ ለምን በግልፅ አትነግሩትም። ለነገሩ ይህን ዕውነታ ለሕዝብ ከገለፁ የጥቅምና የእንጀራ ገመዳቸው የሚቆረጥባቸው ክፍሎች ስላአሉ ደፍረው ይህን ሊያደርጉ አይችሉም። ምክንያቱም አላማቸው ሕዝቡን እያወናበዱ ጥቅማቸውን ማሳደድ ስለሆነ አሁንም እያጭበረበሩ መቀጠል ይፈልጋሉና። ሌላው በኢትዮጵያ በስያሜው ላይ ማሻሻያ ያደረገ የጋሞ ብሔር ብቻ አይደለም። በፊውዳሉ ስርዓት የነበራቸውን ወይም ይጠሩ የነበሩበትን ስያሜ ያሻሻሉ በርካታ ብሔሮች እንዳሉ ይታወቃል። ለምሳሌ ያህል፡- የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የወላይታ፣ የኮንታ፣……ወዘተ መጥቀስ ይቻላል። በስያሜያቸው ላይ ማሻሻያ ወይም ለውጥ ያደረጉ ብሔሮች በፊውዳሉ ስርዓት ይጠሩ የነበሩበት መጠሪያ አንዴም ለንቀት አሊያም ለስድብ ወይም በጥላቻ የተሰጣቸው በመሆኑ ይህን አስቀርተው ወደ ትክክለኛ የሕዝቡና የአካባቢው መጠሪያ ወይም ስያሜ ቀይረውታል  ማለት ነው። ታዲያ የጋሞ ብሔር ስያሜ ለስድብና ለማሸማቀቅ ከሚጠቀሙበት ወጥቶ ወደ ጥንታዊው ትክክለኛ የብሔሩ ስያሜ መመለሱ ለምን ጥያቄ ሊያስነሳ ቻለ?

ሻመና በጽሁፋቸው ውስጥ «ቦንኬ፣ ባልታ፣ ዘጌቴ፣ ዲታ…..ወዘተ ካኦዎችና ሕዝብ መኖሩን፣ ዶርዜ የሚባል ብሔረሰብና በሀገራችን የሸማ ስራን የፈጠረና የሸማ ስራን ወደ ጥበብነት የቀየረ ዝነኛ ህዝብ መኖሩን ሳያውቁ ቀርተው አይመስለኝም» በማለት የማዶላ ደራሲን ይወቅሳሉ። ከዚያም ወረድ ሲል « የቦንኬ ባለስልጣን ለቦንኬና ለተነሳበት አካባቢ እንጂ ጋሞነትን መሠረት አድርጎ ዶኮን ወይም ሌላውን ለጥቅም ማስጠጋት የመጣውን የመንግስት ድጋፍ ወደ ራሳቸው ቤት ከመሳብ የሚያድን አይደለም» በማለት ያጣጥሉታል። ይህ ከላይ የተቀመጠው አባባል በክፍል አንድ ፅሁፌ እንደገለፅኩት የተልዕኮ ሰጪዎችና የተላኩ ዶርዜዎች ዓላማና ፍላጎትን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ምክንያቱም የእነሱ ዓላማና ተልዕኮ የጋሞን ብሔር ሕዝብ ከተቻለ በየዴሬው (በየጎሳው) እንዲከፋፈል ማድረግ፣ ይህም ካልሆነ በየወረዳው እንዲከፋፈል በማድረግ መበታተንና አንድነት እንዳይኖረው ማድረግ ነው። አንድነት የሌለውና እርስበርሱ የተከፋፈለ ሕዝብ መተማመን ስለማይኖረው እርስበርሱ እየተበጣበጠና እየተጋጨ እንደሚኖር የታወቀ ነው። ይህን እውን ለማድረግም ቦንኬ፣ ባልታ፣ ዜጌቴ፣ ዲታ… ወዘተ ጋሞ አይደለም እያሉ እየዞሩ ነገርና ፀብ መቀስቀስ ነው አላማቸው። በሻመና ብዕርና አንደበት የተገለፀውም ይሔው የተልዕኮ ሰጪዎች ዓላማ ነው።

በጋሞ ብሔረሰብ ውስጥ ካሉት ከ50 በላይ ዴሬዎች (ጎሣዎች) ውስጥ ከ40 የሚበልጠው የየራሱ አካባቢያዊ ካኦ (ባላባት) የነበረው ሕዝብ ነው። የዴሬዎች ብዛት ከ50 በላይ ሆኖ የካኦዎች ብዛት ወደ 40 ሊወርድ ይችላል ያልኩበት ምክንያት በአንዳንድ አካባቢ ሁለትና ሦስት ዴሬዎች (ጎሣዎች) በአንድ አካባቢያዊ ባላባት (ካኦ) ስለሚተዳደሩ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የዶርዜ ሕዝብ የሸማ ስራን ፈጥሯል የሚል ምንም የተለየ መረጃ እስከ አሁን አልተገኘም። የሸማ ስራ በሀገራችን በብዙ ቦታዎች ይካሔዳል። ከአጠቃላዩ የጋሞ ሕዝብ ከ40-50 ከመቶው የሸማ ስራን ይችላል። ጥበብ ይሰራል። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በሸማ ስራ የሚተዳደሩ አማራዎች፣ ወደ ትግራይ ራያዎች፣ በጉራጌ ብሔርም ሸማ ሰሪዎች እንዳሉ ይታወቃል። ከኢትዮጵያ ውጪም ጥንታዊ ቻይናዊያን፣ ግብፃዊያን፣ ሶሪያዊያን፣ እስራኤላዊያን፣ ህንዳዊያንና ሌሎችም ሸማን በመስራት እንደሚታወቁ ታሪካቸው ይገልፃል። ታዲያ ዶርዜ የሸማ ስራ ፈጣሪ ለመሆኑ እንዴት ተማመኑ? በእርግጥ የጋሞ ብሔር አባላትና ሕዝብ ውብ የሆነ ሸማና ጥበብ ይሰራሉ። ተደናቂ ሙያም አላቸው። እኔን፣ አባቴንና አያቴን ጨምሮ ምርጥ ጥበብ ሰሪዎች ነን። ግን የሸማ ስራ ፈጣሪዎች እኛ ነን ለማለት አልደፍርም፣ አያስችልም።

ለመሆኑ የአንድ አካባቢ ሕዝብ አንድ የሸማ ስራን ፈጠረ ብንልና ምርጥና ውብ ጥበብ ይሠራል ቢባል ሸማ መስራት የብሔረሰብነት መስፈርት ነው እንዴ? የአንድ ሙያ ባለቤት (ፈጣሪ) መሆን በምን መንገድና መለኪያ ነው የአንድ ብሔር መስፈርት ሊሆን የሚችለው። ይህ አባባል ብዙውን ጊዜ ሕዝቡ ለብቻው በሚሰበሰብበት ወቅት የሕዝቡን ሞራል ከፍ ለማድረግ ሲባል የሸማ ስራን ከመፍጠርና ጥበብ ከመስራት የበለጠ ሙያም ሆነ እውቀት በዓለም ላይ እንደሌለ ተደርጎ በእናንተ አንደበት ሲሰበክ ቆይቷል። ይሕ ስብከት ግን ሕዝቡ ከአንድ ነገር ውጪ ሌላ እንዳያስብና እንዳይረዳ የሚያደርግና የማደንቆር ስብከት ነው።

ለሕዝቡ በየእድሩ፣ በየዕቁቡ፣ በየዱቡሻና በየስብሰባ ቦታው የሸማ ጥበብ ሙያ አቻ የለሽነትን በመስበክ፣ የጃፓን፣ የአሜሪካ፣ የጀርመን፣ የሩሲያ፣ የቻይና ሳይንቲስቶች፣ ቴክኖሎጂስቶች እና የእነዚህ አገሮች ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች መስራት ያልቻሉት የልዩ ሙያ ባለቤት እንደሆነን በማራገብ ዛሬ ሕዝባችን ከጊዜ፣ ከዘመንና ከእውነት ጋር እንዳይጓዝና ወደ ኋላ እንዲያስብ እየተደረገ ነው። ዛሬ የጃፓን፣ የአሜሪካ፣ የጀርመን፣ የሩሲያ፣ የቻይና ሳይንቲስቶችና ቴክኖሎጂስቶች ከምድር አልፈው ጨረቃን ከጨረቃ አልፈው ማርስን፣ ከማርስ አልፈው ሌሎች ፕላነቶችን ለሰው ልጆች ጥቅም ለማዋል እስከ መመራመር ደርሰዋል። በእነዚህ ፕላነቶች ላይ ምርምር የሚያካሔዱ መሳሪያዎችን፣ ቴክኖሎጂዎችን ፈጥረዋል። ወደ እነዚህ ፕላኔቶች የሚያጓጉዙ መንኩራኩር ወይም ሮኬቶችንና የሮኬት ሳይንስን ፈጥረዋል።

እነዚህ አገሮችና በየአገሮቻቸው ያሉ ሳይንቲስቶች፣ ቴክኖሎጂስቶች እኛ በእጅ ጣቶቻችን እየበጠስን የምንቋጥረውንና መወርወሪያ ይዘን ከቀኝ ወደ ግራ፣ ከግራ ወደ ቀኝ እየወረወርን የምንሰራውን ሸማና ጥበብ ይቅርና በእያንዳንዱ የሰው ልጅና እንስሳት አካል ውስጥ ያለው የደም ሴል፣ የነርብ አይነት፣ጂን (ቅንጣቴ ባህሪይ) ሳይቀር ዘርዝሮ የሚነግረንን የሳይንስ ግኝት ፈጥረዋል። በስራ ላይ አውለዋል።  የሰው ልጅን አንጎልና ልብን ቀደው ሲሰፉ እያየን ነው። ዓለምን በአንዴ ሊያጠፋ ከሚችለው የጦር መሳሪያ ጀምሮ አንድ ሰው እቤቱ ቁጭ ብሎ አለምን በሙሉ ማየትና መቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ፈጥረዋል። በስራ ላይ አውለዋል። ታዲያ እነ ሻመና እና መሰሎቹ የእነዚህ ሳይንስቶችንና አገሮችን ስራና ተግባር ከአባቶቻችንና ከእኛ የሽመና ጥበብ ስራ አሳንሶ ለሕዝቡ በማሳየት ሕዝቡ ከጊዜና ከዘመን ተራርቆ፣ ከእውነት ተለይቶ ወደ ኃላ እያሰበ ወደኃላ እንዲሔድ ማድረግ የፈለጉት ለምን ይሆን? የዚህ ቅስቀሳ ተገቢነቱስ የቱጋ ነው ብለው ያስባሉ?

አንዳንድ የዶርዜ ሕዝብ መብት ታጋይ ነን የሚሉ ወንድሞቼ የሸማ ጥበብን ከሰው የእጅ ጥበብ፣ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጥበብ አስበልጠው ከሌላ ጥበብ ጋር ለማወዳደር ሲሞክሩ ሳይ አፍራለሁ። ዝናና ዝነኝነትም ከእውነትና ከተገቢ ተግባር ጋር የተያያዘ ሲሆን ጥሩ ነው። አለዚያ ውድቀቱም ቅርብ፣ ውርደቱም ከባድ ነው። ስለዚህ ሕዝቡን ከጊዜ፣ ከዘመንና ከእውነት አለያይታችሁ፣ እራሳችሁ በፈጠራችሁት አስተሳሰብና በእናንተ አመለካከት ውስጥ አስራችሁ ለማኖር የምትፈልጉ፣ ለእኛ ሳይሆን ለራሳችሁ ጥቅም እየሮጣችሁ ያላችሁ ወንድሞቼ ሆይ እባካችሁ አደብ ግዙ። ሕዝቡን በባዶ ተስፋ እያስጨበጨባችሁ፣ ራሳችሁን በጭብጨባው ሙቀት ውስጥ ደብቃችሁ ሕዝቡን ወደ አልሆነ መንገድ አትግፉት። ሻመና «የምጣዱ እያለ የሰፌዱ ተንጣጣ» በሚል ምሣሌ ስለዶርዜ ሕዝብ መብት መረገጥ  ገልፀሃል። በመሠረቱ የዶርዜ ሕዝብን ከሌሎች የአካባቢው ዴሬዎች (ሕዝብ) ለይቶ መብቱን የሚረግጥም ሆነ የሚጥስ አካል የለም። የዶርዜ ሕዝብ መብት ከተረገጠና ከተጣሰ የሻማ፣ የወበራ፣ የዙቴ፣ የጋንታ፣ የዘጌቴ፣ የሻራ የአቾሎ፣ የጨንቻ፣ የሱልእ ሕዝብ መብት በሙሉ ይጣሳል፣ ይረገጣል።

ፀሐፊው በአንድ ቦታ ላይ “በተለይ ዶኮ” በሚል ጠቀስ አድርገው እንዳለፉት ከሆነ ይህ ችግር ከዚህ በፊትም የደኮ፣ የጨንቻ፣ የኤዞ ዴሬ ልጆች እኛን ይበድሉናል በሚል በአንዳንድ ካድሬዎችና ባለስልጣናት ወይም በአዲስና ተጨማሪ ስልጣን ፈላጊዎች የሚቀርብ የዘወትር ለቅሶ መሆኑን እናውቃለን። በዚህ አስታክከው የጀመሩት ሴራ ምን ደረጃ እንደደረሰም አይተናል። ችግሩ የዶኮ፣ የኤዞ ወይም የጨንቻ ችግር ብቻ አይደለም። አጠቃላይ የሀገሪቱ የመልካም አስተዳደር ችግር አካል ነው። ይህን አጠቃላይ የሀገሪቱ ችግር የሆነውን የመልካም አስተዳደር ችግር መፍታትና ማስተካከል ያለበት ሕዝቡና መንግስት በመተባበር ነው። ስለዚህ ችግሩን የሌሎች ችግር ብቻ በማድረግ እኛ ዶርዜዎች ራሳችንን ከደሙ ንፁህ አድርገን ልንቀመጥ አንችልም። ምክንያቱም እኛም ሆንን ከእኛ የወጡት በርካታዎች የችግሩ አካልና ፈጣሪም ጭምር በመሆናችን ነው።

የዶርዜ ሕዝብ በሌሎች የጋሞ ወንድሞቹ ወይም ዴሬዎች ተሰድቦ አያውቅም። እንዲያው እንሰደብ የሚል ምኞትና ፍላጎት ካለ አላውቅም። አንዳንድ ካድሬዎች እርስበርሳቸው የተሰዳደቡትንና የተበዳደሉትን የሕዝብ  አጀንዳ አድርገው ወደ ሕዝብ ለማምጣት ከሆነ በከዚህ ቀደሙ ይብቃ። ከዚህ በኃላ ካድሬዎች ለግል ፍላጎታቸውና ጥቅማቸው ማሳኪያ ሕዝቡን ጫማና መሰላል አድርገው ሊጠቀሙ አይችሉም። በእኔና በመሰሎቼ አስተሳሰብ ዶርዜ የጋሞ ብሔር አካል ነው፣ የተለየ ብሔር አይደለም ብሎ መናገር ስድብም፣ መብት መርገጥም አይደለም። እውነትን መናገር ስድብም፣ መብት መርገጥም ሊሆን አይችልምና። እነ ግጁቾ፣ ዛይሴ፣ ኦይዳ… ወዘተ ብሔረሰብ ሆኖ ሲወጡ ዶርዜ ተሞኝቶ ነበር ስለተባለው በክፍል ሶስት ፅሁፌ እመጣበታለሁ።

                                                                                                    ታክሶ ላጮ

                                                                                                                       ከጌቶ ዴሬ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1020 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us