የብአዴን/ኢሕአዴግ ታጋዮች ሆይ ለሕዝብ የገባችሁት የአደራ ቃላችሁ ወዴት አለ …?!

Wednesday, 25 November 2015 15:14

 

 

በዲ/ን ኒቆዲሞስ

…የኢትዮጵያ አምላክ ያን የአንድ እናት አብራክ ክፋይ የሆኑ የወንድማማቾችን እልቂትና ደም መፋሰስ በቃ ይል ዘንድ የቀን ተሌሊት እግዚኦታችንን፣ ጩኸታችንን የአገራችን ታቦት ይመስክረዋ! ድካማችን፣ ልፋታችን፣ መውጣት መውረዳችን፣ አዎን ልጄ ላባችንና እንባችን ከእናንተና ከእልፍ የእምዬ ኢትዮጵያ ልጆች ደም፣ እንባና ላብ ጋር ተቀላቅሎ ከአገራችን አፈር ጋር በአንድነት ተላቁጧል- ስለ ፍትሕ፣ ስለ ነጻነት …።

ያን ተስፋችን ከተስፋችሁ፣ ሕልማችሁ ከሕልማችሁ የተጋመደበትን በአንድ የተቋጠረበትን፣ ሞትን የሚተፉ- ከላይ የእልቂት መቅሰፍትን፣ የእሳት አሎሎ የሚያወርዱት የደርግ የጦር አውሮፕላኖች አስፈሪ ማጓራትና ውርጅብኝ፣ በምድር የሞት፣ የእልቂትን እሳትን የሚተፉ፣ የሚያዘንቡ የከባድ መሳሪያው ፍንዳታና ጩኸት ያልበገረው፣ መከራው፣ ረሃቡና ጥሙ የልፈታው፣ ሞት እንኳን ያላሸነፈውን፣ ያልረታውን የተሳስርንበትን ያን ጽኑ የነጻነትና የፍትሕ የቃል ኪዳን ውል የሚረሳ አንጀት ይኖራችሁ ይሆን ልጄ?! ለሕዝብ የገባችሁትስ የአደራ ቃል በቃ ይኽው ነበር እንዴ ልጄ …?!

ይህ ብርቱ ቁጭትና ኀዘን የተቀላቀለበት የሚመስል የብሶት ንግግር በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ እየኖረች ከምትገኘው የኢሕአዴን/ብአዴን ታጋይ ከሆነች ልጃቸው ዘንድ ለሕክምና መጥተው የነበሩ አንድ አዛውንት እናት ለታጋይ ልጃቸው ያሰሙት የብሶትና የወቀሳ ቃል በአንድ አጋጣሚ በወቅቱ ከውይይታቸው ውስጥ በማስታወሻዬ ካሰፈርኩት ለዚህ ጽሑፍ መንደርደሪያ ይሆነኝ ዘንድ የቀነጨብኩት ነው።

የቀድሞው ኢህዴን የአሁኑ ብአዴን የተመሠረተበትን 35ኛ የልደት በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች በማክበር ላይ ይገኛል። የመገናኛ ብዙኃንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የኢሕዴን/ብአዴን ታሪካዊ መነሻውን-ልደቱን፣ ዕድገቱንና የትናንትና አሻራውን የሚዘክሩ ከ1500 ኪሎ ሜትር በላይ የሸፈነው ጉብኝት ደግሞ የበዓሉ አንድ አካል ነው። ታዲያ ባለፈው ሰሞን በዚሁ በኢሕዴን/ብአዴን የልደት በዓል ምክንያት የተካኼደውን ታሪካዊ የሆነ ጉብኝት አስመልክቶ የሸገር 102.1 ኤፍ.ኤም ራዲዮ በእሑድ ዕለት የስንክሳር ዝግጅቱ ቁጭትና ትዝብት አከል የሆነ ሰፋ ያለ ዝግጅት አቅርቦ ነበር።

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝም ይህ በሸገር ራዲዮ የስንክሳር ዝግጅት ክፍል የቀረበው የኢሕዴን/ብአዴን ታሪካዊ ጉዞ የተመለከተው ዝግጅት አንዱናና ዋንኛው ነው። በተጨማሪም ባለፈው ሰሞንም የኢሕዴን/ብአዴን ታጋይ፣ አባልና ከፍተኛ አመራር በአሁን ወቅት ደግሞ በሀገረ እስራኤል የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የኾኑት አቶ ህላዊ ዮሴፍ በፋና ራዲዮ ያደረጉት እጅግ መሳጭ የሆነ ቃለ መጠይቃቸው ይህን ጽሑፍ እንዳዘጋጅ በውስጤ ትልቅ የሆነ ቁጭትን አጫረብኝ።

አቶ ህላዊ ስለ ትግል ሕይወታቸውና ገና በአፍላ የልጅነት ዘመናቸው ከትግል ጓዶቻቸው ጋራ የከፈሉትን ታላቅ መሥዋዕትነት የተረኩበትና ያን የእምዬ ኢትዮጵያን እልፍ ልጆች እምባ፣ ላብና ደም ያስገበረውን የትግል ዘመናቸውን ከትዝታ ማሕደራቸው ያካፈሉን ታሪክ በዚች አገር የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ምን ያህል ወገኖቻችን ክቡር ሕይወታቸውን መሥዋዕት እንዳደረጉ ቆም ብዬ ያን የ60ዎቹን ቆራጥና ፋኖ ትውልድ ዛሬም ዳግመኛ እንዳስበው፣ እንድዘክረው አስገደደኝ።

የአገራቸው የሺ ዘመናት ግዙፍ ታሪክና ገናና ሥልጣኔ በወቅቱ አገሪቱ ካለችበት የከፋ ድህነትና ጉስቁልና፣ የመብት ረገጣና ጭቆና ጋራ ሲያንጻጽሩት እጅጉን ብሶት ያጫረባቸውና ቁጭት ያንገበገባቸው የዛ ትውልድ አባላት “ዱር ቤቴ ብለው” የከተሙበት የትግል ዘመን አብቅቶ ዛሬ ያን ግዙፍ የሆነ መሥዋዕትነት የተከፈለበትን ታሪካቸውን እየተረኩና በጽሑፍ ሰንደው ለትውልድ እያቀረቡ ያለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ምንም እንኳን ዛሬም በቂምና በበቀል ዓይን የሚተያዩና የትናንት እያመረቀዘ ያስቸገራቸውን የዘመናት ቁስላቸውን በይቅርታ ልብ ሽረው በበጎ ዓይን ለመተያየትና በፍቅር ለመቀባበል ዳገትን የመውጣት ያህል የከበደው የትናንትናው ፋኖ ትውልድ አባላት በቃልና በጽሑፍ ትዝታቸውን እያካፈሉን ነውና በእውነት ይበል የሚያሰኝ ነው።

ኢሕዴን/ብአዴንም የተመሰረተበትን 35ኛ ዓመቱን ይኸው ሞቅ ደመቅ አድርጎ በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው። የፓርቲው ገድልና ታሪኩም በቀድሞው ታጋዮቹ አንደበት እየተተረከልን ነው። የመገናኛ ብዙኃንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የሰሜን ኢትዮጵያ ጉብኝትም የበዓሉ አካል ሆኖ ሰፊ ሽፋን አግኝቷል። ግና የዚህ ታሪካዊ ጉብኝት አካል የሆነው የሸገር ራዲዮ የስንክሳር ዝግጅት ክፍል ስለ ኢሕዴን/ብአዴን የ35ኛ ዓመት ምስረታ በዓሉ ያቀረበው ትርክት ግን ያዛን ትውልድ ግዙፍ መሥዋዕትነት ጥያቄ እንዲነሳበት ያደረገና ፓርቲው ለሕዝብ የገባውን የአደራ ቃሉን መፈጸሙን ዳግመኛ ቆም ብሎ ማሰብ እንዳለበት ያስገነዘበ ነበር ማለት ይቻላል።

በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴና የፖለቲካ ትግል ውስጥ ግዙፍ ስምና ክብር ካለው ከኢሕአፓ ማኅፀን የተገኘው ኢሕዴን/ብአዴን ህልውናው ባገኘበት በበለሳና በዙሪያ በሚገኙ ቀበሌዎች በተደረገው ጉብኝት የሸገር ስንክሳር ራዲዮ ያቀረበው የሕዝብ ብሶት፣ እሮሮና ዋይታ በእጅጉ ቁጭትን የሚያጭር ነው። በበለሳ ዐርባ ፀጓር በተባለች ቀበሌ አስተያየታቸውን ሲያቀርቡ የነበሩት የትግሉ ዘመን አጋር የነበሩ እናቶችና አባቶች ዛሬም ከትጥቅ ትግሉ ማብቃት ሃያ ዓመታት በኋላ እንኳን ውኃ፣ ሕክምና፣ መንገድ የመሳሰሉት መሠረት ልማቶች ጥያቄ ሆነው የቀረቡበት የሕዝብ ብሶት በእውነትም ፓርቲው ቆም ብሎ ለሕዝብ ገባውን የአደራ ቃሉንና የትግል ጓዶቹን ግዙፍ መሥዋዕትነት መለስ ብሎ በማየት ራሱን መፈተሽ እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው።

በዚህ የሸገር የስንክሳር ዝግጅት ባልደረባ ለሆነ ጋዜጠኛ አስተያየታቸውን ያቀረቡ እናት ሲናገሩም፣ የረባ ሕክምና የሌለ መሆኑን፣ በቀበሌያቸው ከፍተኛ የሆነ ውኃ እጥረት መከሰቱንና በዚህ ዓመት ደግሞ የክረምቱ ዝናብ አነስተኛ መሆኑ በአካባቢው የተጋረጠው የድርቅ አደጋ ልጆቻቸውን ለስደት እንደዳረገባቸውና ነገን አስፈሪ እንዳደረገባቸው የገለጹበት የሞት ጥላ ያንዣበበት የሚመስለው ፍርሃታቸው የእነዚህን ወገኖቻችንን ብሶታቸውን፣ ኀዘናቸውንና ቁጭታቸውን እንድንካፈል የሚያስገድደን ነው ብዬ አስባለሁ።

ኢሕዴን/ብአዴን የምስረታ በዓሉን አስመልክቶ እያደረገ ያለውን ሽር ጉድ አስመልክቶ በሶሻል ሚዲያ ትዝብቱን ያካፈለኝ አንድ ብርቱ ብዕረኛ የሆነ ወዳጄ ያነሳውን አሳቡን እዚህ ጋራ ላነሳው ወደድኹ። እኔ በበኩሌ አለ ይህ ወዳጄ፣ “… እኔ በበኩሌ የአማራ ሕዝብ ለምግብ እህል እጥረት ስለተጋለጠና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ለአስከፊ ረሃብ ተጋልጠው የሚገኙ በመሆኑም ጭምር የዚህ ዓመት የኢሕዴን/ብአዴን በዓል ቢያንስ ረሃቡ እስኪያልፍ ፓርቲው ባጋጠመው አሳፋሪ ምክንያት የዘንድሮ በዓል ላልተወሰነ ጊዜ ተላልፏል በሚል በዓሉ ቢዘለል የሚል አሳብ ነበረኝ።”

እናም ይህ ወዳጄ ትዝቡትን ሲቀጥልም ኢሕዴን/ብአዴን ሆነ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ሜዳ ባመኑበትና ይሆናል ባሉት መንገድ ለሕዝባቸው፣ ለወገናቸው ካላቸው ፍቅርና መቆርቆር የተነሣ ክቡር ሕይወታቸውን መሥዋዕት አድርገው ያቀረቡ የእናት ኢትዮጵያ ልጆች ግዙፍ የሆነ መሥዋዕትነት ዛሬ በአገራችን መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋራ አልገጥም ያለው ይህ ወዳጄ ትዝብቱን/አሳቡን ሲያጠናክርም፡-

“… የሚያሳዝነው ለዚሁ ውድ ዓላማ ሲሉ ውድ ሕይወታቸውን የገበሩትና ፓርቲው በአሰልቺው ማስታወቂያው ላይ የሚዘክራቸውን የብአዴንና የመላው ኢትዮጵያ የዛን ዘመን ውድ ልጆች ሕይወታቸውን የሠዉበት ዓላማ ተሳክቶ አካላዊ ሞታቸው በዓላማቸው መሳካት ድል የሚነሳበት ቀን መቼ ይሆን…?! ሲል በናፍቆትና በቁጭት ይጠይቃል።” እርግጥ ነው ብአዴን በትግሉ ያሳካው ዓላማ መኖሩን መካድ አይቻልም። ነገር ግን በዓሉን አስመልክቶ እየተነገረ ካለው ማስታወቂያው ውስጥ ቢያንስ “ስለ መልካም አስተዳደርና ስለ ምግብ እህል ራስን ስለመቻል” እያደረገ ያለውን ዲስኩሩን ቢያቆም መልካም ነው። ምክንያቱም ወሬውና በተግባር መሬት ላይ እየታየው ያለው እውነታ የየቅል ናቸውና።

የሸገር የስንክሳር ዝግጅት እንዳረዳን ደግሞ በበለሳና በዙሪያዋ፣ በተከዜ፣ በሰቆጣና ኢሕዴን/ብአዴን የትጥቅ ትግል ባካሄደባቸው አካባቢዎች ያሉ የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ሕዝቦች ዛሬም በመንገድ ችግር፣ በሕክምና እጦት፣ በትምህርት ቤቶች አለመኖር፣ በመልካም አስተዳደር እጦትና በሙስና በተተበተበ አሠራር ምክንያት ፍዳውን እያየ ያለ ሕዝብ መሆኑንና ዛሬም ብሶቱን በቅጡ የሚሰማው እንደሌለ ነበር ሲገልጹ የነበሩት።

በትግሉ ዘመን ለራሳቸውና ለሕዝባቸው ነገ ብሩሕ ተስፋ እንደሚፈነጥቅ በማሰብ አፍላ ዕድሜያቸውን በበረሃ የፈጁና ያለ ምንም አገልግሎትና ጡረታ ከፓርቲው የተሰናበቱ የ80 ዓመት የዕድሜ ባለጠጋዎችና አዛውንቶች ያ ሁሉ ለሕዝቦች ነጻነት፣ ለአገራችን ልማት፣ ዕድገትና ዲሞክራሲ ማበብ የከፈልነው መሥዋዕትነት ውለታችን ይህ ሆነ እንዴ ብለው ምሬታቸውንና ብሶታቸውም ሲያሰሙ መስማት በእውነት በእጅጉ ስሜትን የሚፈትንና ልብን በኀዘን ጦር የሚወጋ ነው።

ዛሬ በቅንጦትና በተንደላቀቀ ሕይወት ያሉ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና አባላትስ የትናንትና የተጋድሎ ታሪካቸውን ከመተረክ ውጪ ይህን የሕዝባቸውን ብሶትና ዋይታ የሚያዳምጡበት ሰሚ ጆሮ ይኖራቸው ይሆንን?! ከአንድ ሰሞን ከበዓል ግርግርና ኹካታ ውጪስ ይሄን በዛ ክፉ ዘመን አጋራቸውና አካላቸው የሆነውን ምስኪንና ድኻ ሕዝባቸውን በቅጡ አይተውትና ጎብኝተውት ያውቁ ኖሯል፣ እንደው ብሶቱንና እሮሮውንስ ለመስማትና ለመካፈል ምን ያህል ሰፊና ቅን ልብ አላቸው…?!

ለመሆኑ በየዓመቱ ብአዴን ለፓርቲው ምስረታ ልደት፣ ለተለያዩ ዝግጅቶችና ስብሰባዎች በሚል ለኮፍያ፣ ለቲሸርት፣ ለምግብና ለመጠጥ፣ ለውሉ ዓበል ክፍያ፣ ለሆቴልና ለአዳራሽ ኪራይ በሚል የሚያወጣው ከፍተኛ የሆነ ወጪ፣ አላግባብ የሆነ የገንዘብና የጊዜ ብክነት፣ የተንዛዛ ድግስና ፈንጠዝያስ በተለይ በዚህ ሰዓት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ለአስከፊ ረሃብ በተጋለጡበት ወቅት በእውኑ ይህ ሁሉ ሽርጉድና ወጪስ ተገቢ ነውን …?! እንደ እኔ እንደ እኔ ብአዴን ለ35ኛ ዓመት ምስረታ በዓሉ የመደበውን ገንዘብ ለረሃብ ለተጋለጡት ወገኖቻችን በማዋል ታሪኩን ቢያድስ መልካም ነበር እላለሁ።

በመጨረሻም ብአዴን ትናንትና በርካታ የትግል ጓዶቹ ግዙፍ መሥዋዕትነት የከፈሉበትን የአደራ ቃላቸውን ዘንግቶ፣ የታሪክ አሻራውንና ተጋድሎውን የሚዘክሩትን ታሪካዊ ቦታዎችንና ቅርሶቹን ሁሉ እንደአልባሌ ነገር ቆጥሮ ያለምንም ማስታወሻ እንዲቀሩ ለምን እንደፈለገ ግልጽ አይደለም። የበዓሉ ተካፋይ የሆኑ የመገናኛ ብዙኃን በዘገባቸው የነገሩን እውነታም ቢኖር ፓርቲው ታሪኩንና ቅርሶቹን በመጠበቅ ረገድ ያለው ክፍተትና ቸልተኝነት ሰፊ መሆኑን ያጋለጠ ነው ማለት ይቻላል።

ለነገሩ እንነጋገር ከተባለ ይህ በአጠቃላይ በኢትዮጵያችን በሰፊው የምናስተውለው እውነታ ነው። መቼም በአብዛኛው እኛ ኢትዮጵውያን ታሪካችንን በሚገባ፣ ሳይንሳዊና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መዘገብ፣ መጻፍና ሰንዶ ለቀጣዩ ትውልድ ተጠብቆ እንዲሻገር፣ እንዲተላለፍ በማድረግ ረገድ ገና ብዙ መሥራት ይቀረናል ብዬ አምናለሁ። ዛሬ ዛሬ ለታሪክ እውቀትና ለቅርሶቻችን ያለን ግንዛቤና ክብርም ጥያቄ ውስጥ እየወደቀ እየመጣ ያለ ነው የሚመስለው። በዚህ ሂደት ደግሞ ከቀጠልን የትናንትና ማንነቱ መሠረት የሆነውን ታሪኩንና ቅርሱን የጣለ ሀገር፣ ሕዝብና ትውልድ ዕጣ ፈንታው ምን ሊሆን እንደሚችል ደግሞ ግልጽ ይመስለኛል።

በአንድ ወቅት የታሪክ ምሁሩ ፕ/ር ላጲስ ጌዴልቦ “የታሪክ ትምህርትና እውቀት የአገርና የኅብረተሰብ ግንባታ መሳሪያ ነው።” ብለው ነበር። ስለሆነም የትናንትናው ትውልድ ታሪክና ቅርሶች በሚገባ ተሰንደውና ተጠብቀው ቀጣዩ ትውልድ የሚማርበትና ለአገር ዕድገትና ብልጽግና መሠረት እንዲሆን በማድረግ ረገድ የትናንትናው ትውልድ አባላቶች ታሪካዊ አደራቸውንና ሓላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባቸዋል።

ብአዴንም ሆነ ሌሎች በርካታዎች- ለሕዝቦች መብት መከበር፣ ለፍትሕ፣ ለአገራችን ኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማበብ መሥዋዕትነት የከፈሉ፣ ሥልጣን ላይ ያለውም ሆነ ተሸንፎ የሸሸውም በአንድነት ሁሉም በጠላትነት የሚተያዩበትንና ለቂም የሚፈላለጉበትን እኩይ መንፈስ አስወግደው ታሪካቸውንና ቅርሶቻቸውን በቅን ልብና በመልካም ሕሊና ከትበው ለትውልድ የሚተላለፍበትን መንገድ በቅጡ ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባቸዋል።

ሁሉም ለሰው ልጆች ነጻነትና መብት ነው መሥዋዕትነት የከፈልነው፣ ወይም እየከፈልን ያለነው የሚሉ ታጋዮቻችን ሁሉ ለሕዝባቸው የገቡት የአደራ ቃል ተግባራዊ ሆኖ ተፈጻሚነት አግኝቶ እናየው ዘንድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትና ተቀራርበው ሊነጋገሩበት የሚችሉበት ከጥላቻና ከጽንፈኝነት መንፈስ የጸዳ ነጻና ግልጽ የሆነ መድረክ ይፈጠር ዘንድ በማድረግ ረገድ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ መንግሥት ያለ መታከት በርትቶ ሊሠራ ያስፈልገዋል። አበቃሁ!! ሰላም!!n

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
613 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us