ፓርላማው አይሰበሰብም! ለምን? የ“ደረቅና እርጥብ” ኮሚቴዎች አባዜ ዛሬም ዘልቋል

Wednesday, 25 November 2015 15:14

 

 

ወልኬሳ /ከሰባራ ባቡር/

የኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት በአንቀጽ 45 ስለ ስርዓተ መንግስት እንደተደነገገው “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓተ መንግስት ፓርላመንታዊ ነው። ይህም ባለ ሁለት ቤት ፓርላማ (Bicameral) የሚባለው ዓይነት ሲሆን፤ ሁለት ምክርቤቶች አሉት። እነዚህም የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ናቸው። የእነዚህ ምክርቤቶች የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ነው። በዚህ መሠረት እነዚህ ምክርቤቶች ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ አራት የፓርላማ ዘመን ማለትም ሃያ አመታትን አሳልፈው መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም በተካሄደው የጋራና የተናጠል፣ መስራች እና መክፈቻ ጉባኤ፡- መንግስት በመመስረት አምስተኛው የፓርላማ ዘመን አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን ከጀመሩ ከአንድ ወር በላይ ሆኗል። ምክርቤቶቹ ሃያ ዓመታትን ዘልቀው ሃያ አንደኛውን ዓመት መጀመራቸው ሲገለፅ እነዚህን ዓመታት ሁሉ አብረው የዘለቁ የፓርላማ አባላትም ፓርላማውን በርስትነት የያዙ እስኪመስል ድረስ አሁንም እንዳሉ አሉ።

እነዚህ የፓርላማው የዕድሜ ባለፀጐች በፓርላማ ታሪክ ለሃያ ዓመታት አሳልፈው አሁን ደግሞ ሃያ አንደኛውን ዓመት በአባልነት ሲቀጥሉ ዓመታትን ከመቁጠር በቀር በአቅም ብስለትና በችሎታ የወጡበት ጊዜ የለም። አስተያየት በመስጠት እንኳ አይታወቁም። እንኳን በሌላው ሕዝብ በመረጣቸው (በወከላቸው) ሕዝብ ዘንድም ቢሆን እውቅና የሌላቸው ስለመኖራቸው የሚያስታውሳቸው የለም። ለውጥ ያለ ቢሆንም እነዚህ ግን እዚያው ባሉበት ያሉ መሆናቸው እጅግ አሳፋሪ ነው። ሃያ ዓመታት ሙሉ ሰው እንዴት አይለወጥም? ይህ ብቻ አይደለም አንዳንዶቹ እንደውም ከስላሴ ቤተክርስቲያን ጋር በማመሳሰል ‘ስላሴን ከአራት ኪሎ፣ እገሌን ከፓርላማ የሚነቅለው የለም?’ ይሏቸዋል።

እነሱም ቢሆኑ ማንም ከፓርላማ እንደማይነቅላቸው፣ እንደማይነቀንቃቸው ሲናገሩ በኩራት ነው። “ዛፍ በሌለበት….” እንዲሉ ሆኖ እንጂ ድርጅቱስ ቢሆን የተሻለ ሰው ማብቃት አቅቶት ነው፤ ለሃያ አንድ ዓመታት እነዚህን ያቀረበው? ብቻ ለእጅ ቆጠራ ይጠቅማሉ። በደርግ ጊዜ ለውክልና ከተላኩት የደርግ አባላት መካከል “እስቲ የሚሉትን ሰምታችሁ ተመለሱ!” የተባሉ የበታች መኮንኖች ደርግ ሆነው እንደዘለቁ ሁሉ እነዚህ የፓርላማ ዕድሜ ባለፀጐችም ከእነዚያኞቹ በምን ይለያሉ? ወደ ዋናው ርዕሴ ልመለስ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት እና የፌዴሬሽን ምክርቤት የተለያየ ሥልጣንና ተግባር ያላቸው ሲሆን፤ በአንድ የምክርቤት የሥራ ዘመን ማለትም በአምስት ዓመታት የስራ ጊዜያት ውስጥ መደበኛ ጉባኤ እንደሚያካሂዱ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 67 የፌዴሬሽን ምክርቤት በፌዴራል መንግስት አባል ክልሎች የሚገኙት ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚልኳቸው አባላትም የሚወከሉበት ምክርቤት እንደሆነና ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚሰበሰብና እንደአስፈላጊነቱ ልዩ ወይም አስቸኳይ ጉባኤ እንደሚያካሂድ ይታወቃል። አምስተኛ የፌዴሬሽን ምክርቤት በመስራች ጉባኤው አዲስ አፈጉባኤ በመምረጥና ሦስት ቋሚ ኮሚቴዎችን በማደራጀት የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ጉባኤውን አካሂዷል። ልዩና አስቸኳይ ጉባኤ ከሌለ በስተቀር አንድ ጉባኤ ብቻ ይቀረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤትን በተመለከተም በሕገመንግስቱ አንቀፅ 58 መሠረት “የምክርቤቱ የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻው ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ 30 መሆኑ” ተደንግጓል። በዚህ መሠረት “መደበኛ ጉባኤ የማይካሄድ መሆኑ” ካልተገለፀ በስተቀር በየሳምንቱ ማክሰኞ እና ሐሙስ መደበኛ ጉባኤውን ያካሂዳል። ባለፈው የፓርላማ ዘመን የመጨረሻው ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች መደበኛ ጉባኤውን አልፎ አልፎ ባለማካሄዱ በመጨረሻው ሰዓት አጣዳፊ ስብሰባዎች ማባሄድ ግድ የሆነበት የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ዘንድሮ ደግሞ ገና ከአሁኑ “በዓለማችን የማይሰበሰበው ፓርላማ” በሚያስብል ሁኔታ ለተከታታይ ማክሰኞ እና ሐሙሶች መደበኛ ጉባኤውን አላካሄደም።

ሁለቱ ምክርቤቶች መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም መስራች ጉባኤያቸውን በማካሄድ ሥራ መጀመራቸው ይታወቃል። በፕሬዝደንቱ ንግግር የተጀመረው የምክርቤቶቹ ሥራ በይፋ ፓርላማው ስራ መጀመሩ የተበሰረበት ነው። በሕገመንግስቱና በአባላት የሥነምግባር መመሪያና ደንብ መሠረት ዘወትር ማክሰኞ እና ሐሙስ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ የሚጠበቅበት “ፓርላማችን!” እስከ ህዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ ያለመሰብሰቡ አባላቱን ጭምር ግራ አጋብቷል። በዚህ ረገድ ምክርቤቱ መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም መስራችና የጋራ ጉባኤውን ካካሄደበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሕዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ ቢያንስ አስራ አራት መደበኛ ጉባኤዎች መካሄድ ነበረባቸው። ከአነዚህ ውስጥ የተካሄዱት አራት አይደርሱም። ዘንድሮ ላይሰበሰብ የተጀመረው ፓርላማችን ምን ሆኖ ይሆን? እያሰኘ ነው። ፓርላማው የማን ነው? የተጣለበትን ሕዝባዊ ውክልና እና አደራ የሚወጣው መደበኛ! ጉባኤዎቹን በመሰረዝ (ባለማካሄድ) ከሆነ ምን እየሰራ እንደሆነ ለሕዝቡ ሊገለፅለት ይገባል።

ባለፈው ዓመትም እንደዚሁ ጉባኤዎች ሳይካሄዱ ቀርተው በመጨረሻው የሰኔ ወር የነበረው ጥድፊያና በጉባኤው ሂደት የታየው ወከባ ሳይረሳ፤ ዘንድሮ ከአሁኑ ጉባኤዎች አለመካሄዳቸው (በተከታታይ ለወር ያህል ምክርቤቱ አለመሰብሰቡ የሚመክርበት አገራዊ አጀንዳ የለውም ማለት ይሆን? ምናልባትም “የአንድ ፓርቲ ውክልና ያለበት ፓርላማ ነው ስጋት አይግባችሁ” የሚሉና “ቢሰበሰብም ባይሰበሰብም ምንም ለውጥ አይመጣም” የሚል ካለ እንደዜጋ ይህ ተቀባይነት አይኖረውም እላለሁ። ይህ ከሆነም በአገርና በፓርላማው ገፅታ ላይ ጥላ ያጠላበታል የሚለ ስጋት አለኝ። በአገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን አካል ነው የሚባለው ፓርላማችን ከአባላቱ ዕውቀት፣ አቅም፣ ችሎታና የህዝብ አደራን በአግባቡ የመወጣት ተልዕኮ አንፃር ጥያቄ መነሳቱ እንዳለ ሆኖ መደበኛ ጉባኤውን በተከታታይ ያለማካሄዱ ጉዳይ እንደአገርና ሕዝብ ሌላ ጥያቄ ያስነሳል! ገዥው ፓርቲም ቢሆን እውነታውን በሚገባ መመርመር ይኖርበታል።

እስከአሁን መደበኛ ጉባኤውን ያላካሄደው ፓርላማችን ችግሩ ምን እንደሆነ ባይታወቅም፤ በዚህ ዓመት ባሉት ቀሪ 2 ጊዜያትም ቢሆን የማያካሂዳቸው ጉባኤዎች መኖራቸው እንደሚኖሩ ሲታሰብ በዕቅድ የመመራቱና በአገራዊና ሕዝባዊ ጉዳይ ትኩረት ስለመስጠቱ ስጋት አለኝ። በዚህ ረገድ ለየቋሚ ኮሚቴዎች የሚመሩ አጀንዳዎችና ጉዳዮች እንደገናም ኮሚቴዎቹ የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች በፓርላማው አባላት (በተወካዮቻችን) በወቅቱ ካልፀደቁ አሁንም አገሪዊ ጉዳዮችን ለመተግበር ከፍተኛ ችግር እንደሚፈጠር አይካድም። በእርግጥም ህዝቡ የሰለቸው ነገር እጅግ የተንዛዙ ስብሰባዎች በመብዛታቸው ፓርላማውም ስብሰባ ቀንሶ ከሆነም ምኑን ፓርላማ ሆነ? ፓርላማ እኮ ሰፊ የሀሳብ መንሸራሸርና ፍጭት የሚታይበት ሕዝባዊና አገራዊ ጉዳይ ወቅታዊ ውሳኔ እንዲያገኝ በማድረግ ሕግ የሚወጣበት የሚደነገግበት ነው።

አቤት! የሕንድን ፓርላማ፣ የእንግሊዝን ኸረ! እንደውም የደቡብ አፍሪካንና የሌሎች አገራትን ፓርላማዎች ባያችሁ! እንደነሱ ባንሆንም በአቅማችንም ቢሆን “ፓርላማችን” ነፍስ ዘርቶ ሕዝቡም የሚናፍቀው በሆነ! ነፍሳቸውን ይማረው አቶ መለስ ዛሬም ድረስ የፓርላማ ውሎአቸው ትዝታው አልጠፋም። ስንት የሚያወያይና ውሳኔ የሚጠይቅ አገራዊ አጀንዳ ሞልቶ ፓርላማችን “…. ቀን ይካሄድ የነበረው መደበኛ ስብሰባ የማይካሄድ መሆኑን እንገልፃለን” በሚል ማስታወቂያ የማይሰበሰበው ፓርላማችን እስካሁን ያደረገው እረፍት ይብቃው። ወደ መደበኛ ሥራው (ጉባኤው) ይመለስ ሲባል በቀጣይነትም ድርጅታዊ በዓላማትን ጨምሮ በብሔራዊ በዓላት ሰበብ ጉባኤው የማይካሄድ ከሆነ የፓርላማችን ፓርላማነት ጥያቄሪ ያስነሳል።

በዚህ ረገድ በአገራችን ድርቅ ስጋት በሆነበት ሰዓት ቀጥሎ ረሃብ እንዳይከሰት፣ ሰው ከሚኖርበት እንዳይፈናቀል፣ በቀዳሚነት የመፍትሄ አማራጮች ላይ ፓርላማው መምከር ይኖርበታል። ወደየአካባቢዎቹም በመንቀሳቀስ ቀዳሚ መሆን ይጠበቅበታል። ድርቅ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች የተወከሉ የምክርቤት አባላትም የጉዳዩን አሳሳቢነት በቅርብ የሚያውቁትን ያህል ለወከላቸው ሕዝብ አለማሰባቸው እጅግ አሳፋሪ ነው። እንደወከልናቸው በምክርቤቱ አጀንዳ አስይዘው ውሳኔ ላይ መድረስና ኢትዮጵያውያን በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በእውቀትና በጉልበት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ በማስተባበር ከሞት ጋር የተፋጠጡ ወገኖችን የመታደግ ኃላፊነት አለባቸው። መንግስትም በግልፅነትና በተጠያቂነት መንፈስ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት በአፅንኦት ውይይት ሊደረግ ይገባል። በዚህ ረገድ በኋላ የታሪክ ተጠያቂነት እንዳይመጣ ፓርላማችን መላ መዘየድ ይኖርበታል እላለሁ።

በዚሁ ርዕስ ስር በፓርላማችን ዙሪያ ሌላው የማነሳው የቋሚ ኮሚቴዎችን የድልድል ሂደት በተመለከተ “ደረቅ” እና “እርጥብ” ኮሚቴዎች መኖራቸውን የተገለፀበትን እውነተኛ ጉዳይ በተመለከተ በጥቂቱ ላቅርብ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጥቅምት ወር ባካሄደው አንድ ጉባኤው በምክርቤቱ የቋሚ ኮሚቴዎችን አመራሮችንና አባላትን ደልድሏል። ምክርቤቱ የቋሚ ኮሚቴዎችን አመራሮችንና አባላትን በደለደለበት በዚህ ጉባኤው የኮሚቴዎቹን “ደረቅ እና እርጥብነት” ይፋ ያወጣበት ሁኔታ የአደባባይ ምስጢርነቱ እጅግ አስገራሚ ቢሆንም፤ ምክርቤቱ በቀጣይነት በአሉባልታ ብቻ ሳይሆን በአባላቱ ዘንድ ያለውን “የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት” ከወዲሁ መቅረፍ ያለበት ትልቅ ችግር በመሆኑ ከአመለካከት ጀምሮ በሂደትም ችግሩን ማስወገድ ያስፈልጋል።

በዚህ ረገድ በምክርቤቱ የቋሚ ኮሚቴዎች ድልድል ሂደት ወቅት የተንፀባረቀውና ከልዩነትም ባለፈ ስጋት መሆኑ የተገለፀበት ይህ “የደረቅና እርጥብነት” ጉዳይ በአባላቱ ጭምር የሚታወቅ መሆኑና የተወሰኑ የኮሚቴ አባላት ተጠቃሚ መሆናቸው በአሳሳቢነቱ መወገድ ይኖርበታል። በተለይም በፓርላማው የመንግስት ተጠሪ ሚኒስቴርና የካቢኔ አባል በሰጡት ማስጠንቀቂያ ጭምር የቋሚ ኮሚቴ አባላት ድልድል “ደረቅና እርጥብ” የመባሉ መንስኤ ቀደም ሲል ከነበረው ተሞክሮ የመነጨ መሆኑ በግልፅ ተንፀባርቋል። በምክርቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ዓይነት “የደረቅ እና እርጥብ” አባዜ መኖሩን በአፅንኦት የገለፁት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ይህን በተመለከተ እንደተናገሩት፤ “የኢኮኖሚ ጥቅም ወይም የወጭ አገር የጉዞ ዕድል በሚያስገኙ ቋሚ ኮሚቴዎች ላይ ለመመደብ ያለፍላጎትና ለዚህ ዕድል የሚያስገኙ ቋሚ ኮሚቴዎችን እርጥብ አድርጎ ሌሎችን ደረቅ ብሎ የመፈረጅ አባዜ መኖሩን ይህን አስተሳሰብ ማስወገድ ይገባል ብለው በጥብቅ አሳስበዋል። ይሄ የአመለካከት ችግር ያለባችሁ ችግሩን አስወግዱ ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

በየትም አገር የሚገኝ ፓርላማ ያለ ኮሚቴ እንደማይሰራ ይታወቃል። “ደረቅና እርጥብ” የሚባል ኮሚቴ ግን የለም። የእኛ ግን ችግራችን ድህነታችን የፈጠረውና ከባለፈው ተሞክሮ ይዘነው የመጣነው በመሆኑ ለዘለቄታውም ጭምር ይህንን ለልዩነት ምክንያት የሆነ የኮሚቴ ምደባ የሚወገድበትን መፍትሄ መፈለግ ይገባል።

የኮሚቴነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል የነበሩ የምክርቤት ተወካዮች የውክልና ጊዜያቸው ሲያበቃም ቢሆን ቀጣዩን የዘለቄታ ህይወት ወይም አኗኗር በተሻለ ሁኔታ መምራት እንዲችሉ የተመቻቸ ነገር የለም። በመሆኑም በውክልናቸው ዘመን በየሚሰማሩበት የሥራ ግንኙነት በኮሚቴ ደረጃ የሚከታተሉትን ተቋም ወይም ድርጅት በመጠበቅና የተሻለ ግንኙነት በመፍጠር ምቹ ሁኔታ አንደሚፈጥሩ ሁሉ ይታወቃል። ይህ “የውክልና ዘመኔ ሲያበቃ ምን እሆናለሁ? የት እገባለሁ?” የሚለው ስጋት ሁሉ ከወዲሁ በውክልናው ዘመን የተሻሉ አማራጮችን ማደላደል ወይም በትምህርት ዘርፍ ራስን ማብቃት ግድ ይላል። ለመሆኑ የኬንያ ፓርላማ አባላት ደመወዝ ስንት ነው? ታድያ የእኛዎቹ በእርጥብ ኮሚቴነት ቢመደቡ ምን ይገርማል። ፓርላማው ባይሰበሰብም የደረቅና እርጥብ አባዜ ዛሬም ዘልቋል። ድልድሉ በዙር ቢሆንስ?  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
715 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us