“አቻ ለአቻ ትምህርት”

Wednesday, 02 December 2015 14:49

 

ክፍል አንድ

አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ1970ዎቹ ጀምሮ የትምህርትም ሆነ የጥናት ጥራት በእጅጉ እየቀነሰ መምጣቱን ብዙዎች ምሁራን ይስማማሉ። ከአንጋፋዎቹ የትምህርት ክፍል አንዱ ደግሞ የታሪክ ትምህርት ነው። ይህ የትምህርት ክፍል በሰው ሀይልም ሆነ በቁሳቁስ በጣም የተደራጀና ታዋቂ ክፍል ነበር። በሂደትም ይህ ክፍል ሌሎች ተዛማጅ የትምህርት ክፍሎችንም ደርቦ ያስተባብር ነበር። ከእነዚህም ክፍሎች የአርኪዮሎጂ ዩኒት አንዱ ነው። በአሁኑ ወቅት የአርኪዮሎጂና የቅርስ አስተዳደር የትምህርት ክፍል በመባል የራሱን የቻለ ዲፓርትመንት መሆንም ችሏል። ይህ የትምህርት ክፍል ራሱን የቻለው በ2002 ዓ.ም ነው። በመጀመሪያ ዲግሪ ከዚያም በሁለተኛ ዲግሪ ማስመረቅ ጀምሯል። የዚሁ የትምህርት ክፍል ውጤት አንዱም እኔ ነኝ። በእነዚያ የዩኒቨርስቲው ወርቃማ ጊዚያት የመጀመሪያ ዲግሪ ለማስተማርና ጥናትና ምርምሩን ለመደገፍ ብዙ ዶክተሮችና ከአምስት ያላነሱ ፕሮፌሰሮች ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ግን የመጀመሪያ ዲግሪ በመጀመሪያ ዲግሪ ባላቸው መምህራን፣ ሁለተኛ ዲግሪ ሁለተኛ ዲግሪ ባላቸው መምህራን፣ እንዲሁም ሶስተኛ ዲግሪ ወይም ፒኤችዲ ዲግሪ ትምህርት ፒኤችዲ ዲግሪ ባላቸው መምህራን ትምህርቱ ይሰጣል። በአጠቃላይ የትምህርት ስርዓቱ የአቻ ለአቻ ትምህርት አሰጣጥ ነው ወደሚል ድምዳሜ ያደርሰናል።

በእርግጥ አቻ ለአቻ ለጋብቻ ቢሆን ስንቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመቅረፍ የስንቱን ስቃይ ማቃለል በቻለ ነበር።  አቻ ለአቻ በሴቶች ጉዳይ ዘንድ የሚወደድ አስተምህሮ ቢሆንም በትምህርት ገበታ ግን መሪ ለመሆን አያስችልም። ምንም መደበቅ የማይቻለው ሀቅ በአሁኑ ወቅት ቢኖር ብርቅዬ የነበሩት ሁለት ዩኒቨርስቲዎች ብዙ ጊዜ ተባዝተዋል። በዛ ላይ በአንዴ ብዙ ተማሪዎችን የመቀበል አቅምም ዕድገት አሳይቷል። ትምህርትን ለሁሉም ማዳረስ ቀዳሚ ተግባር ቢሆንም ጎን ለጎን መሰራት ያለባቸው ስራዎች አልተሰሩም። በዚህም ምክንያት የአቻ ለአቻ ትምህርት አሰጣጥ ደረጃ ላይ ደርሰናል። ይህ አይነቱ ትምህርት አሰጣጥ ደግሞ ከቁጥር የዘለለ ፋይዳ የለውም። በዛ ላይ ብዙ ችግሮችን ማስከተሉ አልቀረም። ለአብነት ለማሳየት ያክልም የእኔው የትምህርት ክፍል ልውሰዳችሁና እንየው።

እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2006 ዓ.ም ሁለተኛ ዲግሪ ለመማር የአርኪዮሎጅና የቅርስ አስተዳደር የትምህርት ክፍል በተቋሜ ዕድሉን አግኝቼ ተመዘገብኩ። በዚሁ የትምህርት ክፍል በቀደመ ጊዜ እኔን በቀጠረኝ መስሪያ ቤት ባልደረባ የነበሩ በአሁኑ ወቅት ግን በዚሁ የትምህርት ክፍል አስተማሪዎች ይገኛሉ። እነዚህ መምህራን የአንድ ትምህርት ክፍል አስተማሪ ቢሆኑም የትምህርት ክፍሉ ሞተር በሆነው የቅርስ ትርጓሜ ግን ምንም ስምምነት የላቸውም። እነሱ ሳይስማሙም ተማሪው እንዲስማማ ጫና ያደርጋሉ። አንደኛው መምህር ቅርስ አንተነትህ ነው ሲል ሌላው ቅርስ የአንተ ምርጫ ነው ብለው ያስተምሩናል። ይህ የሚያሳየን ስለ ቅርስ አስተምራለሁ ብሎ ከመንግስት ኃላፊነቱን የወሰደው አካል ምን ያክል ዝግጅት አድርጎ ወደ ስርዓት ትምህርት ቀረጻ እንደገባ መገመት አይከብድም። በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተጨማሪ  የትምህርት ክፍል ሲቀረጽ ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ። በመጀመሪያ ደረጃ ግን የሚቀረጸው የትምህርት ክፍል ለሀገሪቱ ያለው ፋይዳ ግምት ውስጥ መግባት አለበት ምክንቱም የሚመረቀው ተማሪ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ በገበያው ተፈላጊ ሁኖ ወይ በራሱ ካልሆነም የሥራ ቅጥር የሚያገኝበት ዕድል ሊኖር ይገባል ያለበለዚያ ግን የተማረ ቦዘኔ ከማፍርት አይተናነስም። በአሁኑ ወቅት የምናየው ግን የትምህርት ክፍል ከመጀመሪያ ዲግሪ ወደ ሁለተኛ ዲግሪ ሲያድግ ስለ ሀገራችን ምንም እውቀት በሌላቸው ህንዶች አማካኝነት ከአንዳንድ ኢትዮጵያን ጋር በመመሳጠር ተጨማሪ ኮርሶችን ለማግኘት ሲባል የሰው ሀይልንና የትምህርቱ አስፈላጊነት እንዲሁም የሚመረቁ ተማሪዎች የስራ ዕድል የሚገኝበት ቅድመ ሁኔታ ሳይመቻች ዝም ብሎ በአንድና በሁለት መምህራን ይከፈታል። በእንደዚህ ሁኔታ የተከፈተ የትምህርት ክፍል ደግሞ አይደለም ከህብረተሰቡ ጋር፣ አይደለም ከተማሪው ጋር ርስ በርስም ለመግባባት እንኳ በማይቻልበት ሁኔታ ላይ ተደርሷል። እንደ እኔ ግን ለማስተማር በከፈቱት የትምህርት አይነት ላይ መሰረታዊ ልዩነት መኖር የትምህርት ክፍሉ ሲከፈት የህብረተሰቡን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ሳይሆን የተወሰነ አካላትን ፍላጎት ለማሟላት ይመስለኛል። ስለሆነም ስለ ቅርስ ከማስተማራቸው በፊት ቅርስ የሆነውን የትምህርት ክፍሉን ታሪክ በአግባቡ መርምረው ቢያስተካክሉ የሚል ሀሳብ አለኝ ሲቀጥል ደግሞ ሶስተኛ ዲግሪ ለመክፈት ከመሯሯጥ በፊት የመምህራንን አቅም ወደ ሶስተኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ ማልማት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ያለበለዚያ ግን የአቻ ለአቻ ትምህርት ብዙ ውድቀቶችን ያስከትላል።

የአቻ ለአቻ ትምህርት ውጤቱም መጠላለፍ ሁኗል። አንድ እውነት ለአብነት ላሳያችሁ በሁለተኛ ዲግሪ መረሀ ግብር ማስተርስ ፕሮግራም መመረቂያ ጹሁፍ ለቀጣይ ትምህርት ወሳኝ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን በጥናትና ምርምር የምታበረክተውን አስተዋጸኦ ሁሉ ገደል በመክተት ለራስህም ለሀገርህም ሳትሆን በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ አቅምህን ሳታወጣ ተደብቀህ የጡረታ ጊዜ እንድትጠባበቅ የሚያደርግ በመሆኑ አልደግፈውም ብቻ ሳይሆን አምርሬ እጠላዋለሁ። ይህንን እንዳይማር ለማድረግ በእጅ ያላቸው መሳሪያ ጉድ በመስጠት ከቀጣይ ትምህርት ማሰናበት ነው። ቀጣይ ትምህርት ፒኤችዲ ለመማር ደግም ቬሪ ጉድና ከዚያ በላይ ማግኘት አለብህ።  ይህ የሚደረገው ደግም ከአለማወቅ የተነሳ ብቻ አይደለም። የአቻ ለአቻ ትምህርት መጠላለፍ ውጤት ነው። ይህ የአቻ ለአቻ ትምህርት መሪ ቅናት ከእነሱ በላይ እንዳትሆን ሁለትም ዕድሉን አግኝተህ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር እንዳትችል ሞራልህን መግደል ነው። ይህ ድርጊት ደግሞ ሀገሪቱን ከመግደልና በአሁኑ ወቅት ብቃት ያለውን ጥናትና ምርምር የሚሰራና የሚያማክር ፕሮፌሰሮችን ለማፍራት ያልተቻለበትን ሁኔታ ማጤን ብቻ በቂ ነው።

አንዳንድ መምህራን ብንመለከት ሀገራችን በውድ ዋጋ ኦክስፎርድና በመሳሰሉት ዩኒቨርሲቲዎች አስተምራቸው የሰሩት መመረቂያ ግን አሁንም የውጭ ሀገራትን አስተዋጸኦ አጉልቶ የሚያሳይና የሚደግፍ ጥናት ሰርተው ይመረቃሉ። ይህ ቅኝት በእነሱ ላይ ቢያበቃ ጥሩ ነበር። ግን አመለካከታቸውን በተማሪዎቻቸው ለማሳረፍ ላይ የሚያደርሱት ጫና ቀላል አይደለም። ተማሪውን ሀገራዊ ይዘት ባለው ጥናት እንዲሰሩ ከማበረታት ይልቅ አንዳንድ የውጭ ምሁራን የጻፉትን ደግፈን እንድንመረቅ እንገደዳለን። ችግራችንን ለመቅረፍ የተቋቋሙ የቅሬታ አቀራረብ አሰራር ቢኖርም የአንድ መምህር ውሳኔን ማስቀየር የሚችል ግን አይደለም። ይህች ሀገር ችግር ፈቺ ተቋም እንጅ የሚያስፈልጋት የጥቅምን መረብ የሚያጠናክር ሌላ ደመወዝ ተከፋይ ቢሮ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ተማሪዎች የመምህራንን ፍላጎት በማሟላት እንዴት መመረቅ እንደሚችሉ በማግባባት ላይ የሚሰራ ተቋም ነው። ይህን የምልበት ምክንያትም ተማሪዎች ተበድለናል ብለን በምንሄድበት ጊዜ አስተማሪህ ጋር አትጋጭ፣ ያለህን እሺ በለውና ሌሎችም ምክሮች እንጅ አንድ እርምጃ ወደፊት ብለው አያውቁምናና ነው። ስለዚህ ይህ ተቋም በህጋዊ መንገድ የራሳቸውን ፍላጎት ማስፈጸሚያ እንጅ ምንም ለተማሪው የሚፈይድ እንዳልሆነ ለአንድ ጉዳይ ቢሮው ድረስ ጎራ ማለት በቂ ነው።  የቅሬታ አፈታት ተቋም ወይስ የቅሬታ ማለስለሻ ተቋም እንበለው። የትውልድን ችግር ለመረዳት መማር አይጠበቅብኝም። የዩኒቨርሲተውን ማህበረሰብ ችግር ለመረዳት ተማሪ ሁኖ ማለፍ አይጠበቅበትም። ስለሆነም ትውልድ አድን ስራ በሚታየው በሚሰማው ነገር ላይ አጋርነትህን ማሳየት መቻልም ጭምር ነው። ፓርላማ ስር ባለው አዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ የተፈጸመው በደል በሌሎች ዪኒቨርሲቲዎች በምን ያክል የጨመረ መሆኑን መገንዘብ ቀላል አይደለም። ይህን ጸሑፍ መሰል የግል ስሜትና ያገባኛል ባይነት አጋርነት ለማሳየት በምጽፍበት ወቅት በአራት ኪሎና በስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ያውም የህይወትን መንገድ ለመሸከም ምንም አይነት ልምድና ተሞክሮ በሌላቸው ጮርቃ ጭንቅላት ተማሪው መሸከም የማይችለውን የመምህራንን ግለሰባዊ ፍላጎት ከመጡበት ማህበረሰብ ትውፊትና እሴት ጋር የማይሄድ ጥያቄ ለማሟላት ባለመቻላቸውና በመፈጸማቸው በሁለቱም ድርጊት ከህሊና ጸጸት ራሳቸውን  ለማዳን ሲባል የአደንዛዥ እጽ፣ ብሎም ራስን የማጥፋት ወሳኔ በቅርቡ በአራት ኪሎና በስድስት ኪሎ የታየውና የተሰማው ድርጊት ህያው ምስክር ነው።

 በመጨረሻም ህሊናን ለጊዜው በማሸሽ ለመመረቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ ነገ በእህት ወንድሞችህ ላይ ብሎም በልጆችህ ላይ ጠንከር ያለ ክንድ ማውረስ ነው። ስለዚህም ትውልድ ይዳን እኔ አልመረቅ በሚል መንፈስ ችግሩን ማስወገድ አይቻልም ብዬ ራሴን ደካማ ማድረግ አልፈልግምና ባለንበት የተማሪዎችን ችግር እንታገል። ማን ያውቃል በመምህራን ግለሰባዊ ፍላጎት ከሚባረሩት ተማሪዎች አንዱ ታሪክ ሰሪ ይሆናል!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
913 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us