ከደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች አንድነት (ደኢዴኃአ) የተሰጠ መግለጫ

Wednesday, 02 December 2015 14:50

 

የታጋዮች መታሠር ትግልን አያስቆምም!!

በደቡብ ክልል በዳውሮ ዞን መስተዳደር በ2005 ዓ.ም በተፈጠረው የዞኑ ሕዝብ የመብት ጥያቄ ምክንያት ከአስር በላይ የሆኑ የዞኑ ተወላጆች እስከ ዛሬ ድረስ በእስር በመንገላታት ላይ ይገኛሉ። የመታሰራቸው ዋና ምክንያት የዳውሮ ዞን መስተዳደር በዞኑ ውስጥ ያሉ ነባር ወረዳዎችን ያለሕዝብ ፈቃድና ስምምነት በማጠፉ የተነሳ የሕዝቡ የመብት ጥያቄ ነው። በወቅቱ ሕዝቡ የመብት ጥያቄ ማንሳቱ አግባብነት ያለው መሆኑ ታምኖና የክልሉና የዞኑ መስተዳደር ስህተት መፈፀማቸውን አምነው በጊዜው ሕዝቡን ይቅርታ በመጠየቅ ታጥፎ የነበረው የማረቃ ወረዳ መስተዳደር ወደ ነበረበት እንዲመለስ መደረጉ ይታወቃል።

ነገር ግን በዚህ የወረዳ መታጠፍ ምክንያት ሕዝቡ የመብት ጥያቄ ባነሳበት ወቅት በቦታው ተገኝተው በሰላማዊ ሰልፍ የተሳተፉም ሆነ በወቅቱ በስራ ምክንያት በዞኑም ሆነ በክልሉ ውስጥ ያልነበሩ የዞኑ ተወላጆች ከያሉበት እየተለቀሙ ለእስር ተዳርገዋል። አብዛኞቹ ባልነበሩበት በተካሔደ ሰላማዊ ሰልፍ ምክንያት ለእስር የተዳረጉት በፖለቲካ አመለካከታቸው፣ አቋማቸውና እምነታቸው ምክንያት ነው። በዚህም ተገቢ ያልሆነ ስም እየተሰጣቸውና የፈጠራ ወንጀል እየተለጠፈባቸው በፍትህ ስምና በሕግ ሽፋን እስከ ዛሬ ድረስ የእንግልትና የስቃይ ሰለባ ሆነዋል።

የዳውሮ ዞን መስተዳደር በሰራው ጥፋትና ስህተት ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቆ ወረዳውን ወደነበረበት ከመለሰ በኋላ በዚህ ምክንያት የተነሳውን ሰላማዊና ሕጋዊ የመብት ጥያቄ አነሳሳችሁ፣ አቀነባበራችሁ፣ መስፍን መሸሻና አባተ ኡቃን ጨምሮ 12 ሰላማዊ ሰዎች መስተዳደሩና የመንግሥት ባለስልጣናት በሕዝቡ ላይ ለፈፀሙት ወንጀልና በደል ያለተግባራቸው መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ታጋዮች ናቸው እንጂ ወንጀለኞች ወይም አሸባሪዎች አይደሉም። በመሆኑም ሰላማዊ ታጋዮችን በማሰር፣ በማንገላታትና በማሰቃየት ትግሉን ማስቆም አይቻልም።

በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙት እነ አቶ ዱባለ ገበየሁ፣ መስፍን መሸሻ፣ አባተ ኡቃ እና ሌሎችም ታሳሪዎች ወንጀለኛ ናቸው ከተባሉ ወንጀላቸው አንድም የዳውሮ ዞን ተወላጅ መሆናቸውን አለም ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅም አላማና የፖለቲካ አቋም ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰላማዊ ታጋይ መሆናቸው ነው። ከዚህ ውጪ እስረኞቹ በዞኑ ውስጥም ሆነ በዞኑ ሕዝብ ላይ ምንም አይነት ችግር አልፈጠሩም። በዳውሮ ዞን መስተዳደር እንደተቀነባበረው ክስ ሁኔታ ወንጀለኞችም፣ አሸባሪዎችም ሳይሆኑ ሰላማዊ ታጋዮችና ሕጋዊ የመብት ጥያቄ የሚያነሱ፣ በዚህም ምክንያት ሰላማዊ ትግላቸውን ለማስቆምና የመብት ጥያቄዎችን ለማፈን ሲባል የተከሰሱና የታሰሩ የፖለቲካ የህሊና እስረኞች ናቸው።

በሀገራችን መልካም አስተዳደርና እውነተኛ የፍትህ ስርዓት ቢኖር ኖሮ በጊዜው የነበሩ የዳውሮ ዞን መስተዳደር ባለስልጣናት እና የዞኑ ፖሊስና ለሎችም የፍትህ አካላት ለራሳቸው ስህተትና ጥፋት መሸፈኛ ሲሉ ባቀነባበሩት የፈጠራ ወንጀል በተመሰረተ ክስ ታሳሪዎች እስከ አሁን ድረስ መጉላላት አይገባቸውም ነበር። ሆኖም ጉዳዩ በአግባቡ ፍትህ ያገኛል በሚል ግምትና ተስፋ እስከ ዛሬ ድረስ ብንጠባበቅም ፍትሃዊ መፍትሔ ሳያገኝ ቆይቷል። ተከሳሾች በፍርድ ሂደቱ ላይ ያቀረቡት የይግባኝ ጉዳይም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራዘመ መሔዱ ጉዳዩ የሕግና የፍትህ ጉዳይ ሳይሆን በሕግና በፍትህ ሽፋን እየተወሰደ ያለ የፖለቲካ እርምጃ መሆኑን በግልፅ አሳይቷል። ስለዚህ፡-

$11.  የፌዴራል መንግሥት፣ የደቡብ ክልል መንግሥትም ሆነ የዳውሮ ዞን መስተዳደር እስረኞን በሕግ ሽፋንና በፍትህ ስም ከማንገላታትና ከማሰቃየት ይልቅ የታሰሩት በፖለቲካ አመለካከታቸው፣ አቋማቸውና እምነታቸው ምክንያት ስለሆነ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጥና ነፃነታቸው እንዲጠበቅ እንጠይቃለን።

$12.  በሰላማዊ ታጋይነታቸው ምክንያት የታሰሩ የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን ጉዳይ አገራዊና አለም አቀፋዊ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፣ አገራዊና አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እንዲከታተሉ፣ እንዲጠይቁና ያሉበትን ሁኔተ ለሕዝቡ እንዲያሳውቁ እንጠይቃለን።

$13.  የደቡብ ክልል መንግስትና በስሩ ያሉ የዞንና የወረዳ መስተዳድሮች የፖሊስና የፀጥታ ኃይሎች በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በሕዝብ የሚነሱ የመብት ጥያቄዎችን አግባብ ባለው መንገድና በሰላማዊ ሁኔታ መፍታት ሲቻል በተቃራኒው ጥያቄ በሚያነሱ ክፍሎች ላይ የሚወስደውን የእስር፣ የማሰቃየትና ልዩልዩ የቅጣት ዕርምጃዎችን እንዲያቆሙ እንጠይቃለን።

ሰላም፣ ፍትህና አንድነት ለኢትዮጵያ!!

የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች አንድነት (ደኢዴኃአ)

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ሕዳር 17 ቀን 2008 ዓ.ምn

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
535 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us