የዎላይታ ዞን ዋና ከተማ ሶዶ የደቡብ ክልል ርዕሰ መዲና ቢሆን

Wednesday, 09 December 2015 14:10

 

ከዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ)

ከአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሌሎች ዘርፎች ሁሉ እድገት ምንጭ መሆኑ እሙን ነው። ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማህበራዊ ብልጽግናም ሆነ፣ ለፖለቲካዊ ሥርዓት ሥምረት መሠረት መሆኑ አጠያያቂ አይሆንም።

በኢኮኖሚያዊ ዕድገት የጎለበተ አገር፣ የተሟላ ጤንነት ያላቸው፤ በትምህርትም በቂ ዕውቀት የቀሰሙ፣ የልማት አራማጅ የሆኑ ጥሩ ተመራማሪዎች፣ ሳይንቲስቶችና ተፈላሳፊዎች በርከት ብለው የሚገኙበት አገር የመሆን እድሉ ሰፊ ነው።

ፍትሕ፣ ሰላምና መልካም አስተዳደር ለዘለቄታው የሰፈነበት፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ያለ እንቅፋት እያበበ የሚቀጥልበት፣ በአጠቃላይ ዜጎች ሁሉ የተሻለ ህይወት የሚመሩበት አገር ይሆናል ማት ይቻላል።

ለዚህ ዓይነት ምቾትና ድሎት የሚያበቃ የኢኮኖሚያዊ ዕድገትም በተራው የራሱ የሆነ የዕድገት ምንጮችና ሂደቶችም ይኖሩታል፤ ያስፈልጉታልም።

በማምረትና በማገልገል ሂደት የላቀ ሚና ያላቸው እንደነ ጊዜ፣ ጉልበት፣ ገንዘብ፣ ንብረትና ሌሎችም አስፈላጊ አቅርቦቶች ከብክነት መዳን አለባቸው። ይህም ሊሆን የሚችለው ከንጹህ አገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነት ስሜት ከታነፀ አዕምሮ በሚመነጭ አስተሳሰብ በሚወጣ እቅድና በሚነደፍ ስትራቴጂ መሆኑ ሊካድ አይችልም።

በሁሉም መስኮች ከሁሉም በተለየ ሁኔታ ፍፁም ተወዳዳሪ የማይገኝለት ድርሻን ለሚያበረክተው ሕዝብ፣ ለሚፈፅመው ክንዋንም ሆነ፣ ሊያገኘው የሚገባ አገልግሎት ብቃት፣ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ራሱ አንድ የዕድገት በር፣ እንደመክፈት ሊቆጠር ይችላል።

አምራችም ሆነ፣ አገልግሎት ሰጪ ሕዝብ ምቹ የመሥሪያ ሥፍራ እንዲኖረው ማድረግ ተጠቃሚም አርኪ አገልግሎትን በተፋጠነ ሁኔታ እንዲያገኝ ማስቻል፣ ምርትና ምርታማነት በላቀ ደረጃ እየጨመረ እንዲሄድ በማድረግ ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በቀላል የሚገመት አይደለም።

በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ማዕከላዊ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ አገልግሎቶች ሁሉ በተቻለ መጠን በሁሉም አቅጣጫ ለሚገኙ ሕዝቦች ያለብዙ ድካምና ውጣ ውረድ የሚደርሱብን የአሰራር ሥርዓት መዘርጋም በእድገት ሂደት ውስጥ አንዱ አጋዥና ለጥሩ ውጤትም የሚያበቃ መሆኑ ይታመናል።

የየክልል መስተዳድሮችም በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ህዝቦች የሚፈልጉን የምርት ጤትንም ሆነ፣ አገልግሎን ያለ ብዙ ውጣ ውረድና የገንዘብና የጊዜ ብክነት እንዲያገኙ ቢያደርጉ የተሻለ አሰራር ይሆናል።

ለዚህ ዓይነት ታላቅ ሕዝባዊ አገልግሎት መስጫ፣ ማምረቻና ማከፋፈያ የሚሆኑ ምቹ ሥፍራዎችን በልዩ ጥንቃቄ መምረጥ የሚጫወተው ሚና እጅግ ወሳኝነት ያለው ይሆናል።

የዎላይታ ዞን ዋና ከተማ የሆነች ሶዶ የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መስተዳድር ዋና ከተማ እንድትሆን፣ ሐዋሳም ወደ ፌዴራል ከተማነት ከፍ እንድትል ማድረግ እነዚህን ከላይ የተጠቀሱ ሕዝባዊና አገራዊ ጥቀሞችን አጉልቶ የሚያሳይ ይሆናል።

በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ዞኖችና ልዩ ልዩ ወረዳዎች ከ85 ነጥብ 7 በመቶ (ሰማንያ አምስ ነጥብ ሰባት በመቶ) ከሚሆኑ በላይ እጅግ አጭር በሆነ ጊዜና አነስተኛ በሆነ ወጪ ተፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችንም ሆነ፣ የምርት ውጤቶችን የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል። አሁን ከሚፈጅባቸው ገንዘብና ጊዜ ከፍተኛውን እንደሚቀንስላቸው ይገመታል። በብሔራዊ ኢኮኖሚም በዚያው መጠን የራሱ የሆነ አርኪ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚሄድ ግንዛቤ ማግኘት ተገቢ ይሆናል።

ይህ አገላለፅ ጉዳዩ በአገር ዕድገትና በሁሉም ሕዝቦች ጥቅም ላይ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ለማሳየት እንጂ ማንንም ያለአግባብ ለመጠቀም፣ ሆነ፣ ለመጉዳት ተብሎ እንዳይደለ በአግባቡ መረዳት ተገቢ ይሆናል።

ፍትሓዊ የሆነ፣ የህልውና ዳኝነትን በቀና አስተሳሰብና በኃላፊነት ስሜት ለመስጠት በመጀመሪያ ራሱን ያሳመነ ዜና የጠቀሜታውን ግዝፈትና ዘርፈ ብዙነት በቀላሉ ለመረዳት አያዳግተውም።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ከሚገኙ ሕዝቦች

1.  የሼካ ዞን ሕዘቦች

2.  የቤንች ማጂ ዞን ሕዝቦች

3.  የካፋ ዞን ሕዝቦች

4.  የደቡብ ኦሞ ዞን ሕዝቦች

5.  የዳውሮ ዞን ሕዝቦች

6.  የጋሞ ጎፋ ዞን ሕዝቦች

7.  የባስኬቶ ልዩ ወረዳ ሕዝቦች

8.  የደራሼ ልዩ ወረዳ ሕዝቦችና

9.  የኮንሶ ልዩ ወረዳ ሕዝቦች

የክልሉ ዋና ከተማ

አሁን ወደሚገኝበት ወደ ሃሳዋ ጉዞ ሲጀምሩ በመጀመሪያ በጣም በአጭር ጉዞ የሚረግጡት ሶዶ ከተማን ነው።

1.  የጉራጌ ዞን ሕዝቦች

2.   የሥልጤ ዞን ሕዝቦች

3.  የሐዲያ ዞን ሕዝቦች

4.  የከምባታና ጠምባሮ ዞን ሕዝቦችና

5.  የየም ልዩ ወረዳ ሕዝቦች ወደ አሁኑ ክልል ከተማ

ለመጓዝ ሲንቀሳቀሱ ዎላይታ ሶዶን እጅግ በጣም በሆነ ቅርብ ርቀት ያገኙታል። ወደ ጎን እያዩም አቋርጠው ያልፋሉ። ለአላባ ሕዝብም ዎላይታ ሶዶ እጅግ በጣም ቅርቡ ነው። እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ወደ ሶዶ በቀን ከሁለት ጊዜ በላይ መመላለስ ይችላሉ።

የሲዳማ ዞን ሕዝብም በአንድ ብቻ ሳይሆን ከአንድ በላይ በሆኑ አቋራጭ መንገዶች በአንድ ቀን በብዛት ወደ ሶዶ በመመላለስ ጉዳዮችን መፈፀም የሚችል የኩታ ገጠም ዞን ሕዝብ መሆኑ በሁሉም ዘንድ የተረጋገጠ ስለሆነ፣ ምንም ሰፊ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይሆንም። የሲዳማ ሕዝብ በተጨማሪም የነገሮችን ምንነትና ሊገኝ የሚችለውን የጋራ ጥቅም እውነተኛነትን በጥልቀት እየመረመረ የማመን ማሳመን መርህን ተጠቅሞ የሚወስን ታላቅ ሕዝብ የመሆኑ ታሪክ ሲታወስ ለጉዳዩ የሚያደርገው ዕገዛ የላቀ ያደርገዋል የሚል እምነት አሳድሮብናል።  

የጌዲዮ ዞን፣ የቡርጂ ልዩ ወረዳና የአማሮ ኬሎ ልዩ ወረዳ ሕዝቦችም ቢሆኑ ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር ትንሽ ራቅ ያለ መስሎ ቢታይም፣ የጋራ ዕድገትና ጥቅምን በሚመለከት ለሚነሱ ቁምነገሮች ከምንም በላይ ቅድሚያ መስጠት ካላቸው የሞራል ታላቅነት የመነጨ ባህልን የተላበሱ ህዝቦች ስለሆኑ ይህንን ጉዳይ በብርቱ ደግፈው እንደሚገፉ እምነታችን የፀና ነው።

ይህ ጉዳይ በማንኛውም በትክክልና በቀናነት በሚስብ በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ፤ በሌላው የአገሪቱ ሕዝብ ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ የሚታንበትና የሚደግፍም ስለሆነ፤ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶት ተግባራዊነቱ እንዲረጋገጥ ቢደርግ የሚበረክተው አገራዊ ጥቅም የገዘፈ ይሆናል እንላለን።

የዚህና የዚህ ዓይነቶቹ ሃሳቦች ተግባራዊነት መረጋገጥ ድህይትን ከአገራችን ለማሰናበት፤ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማስወገድ ተብሎ የሚደረግ፣ ተጋድሎ ጥሩ ማሳያ መሆኑ በቂ ግንዛቤ ማግኘት ይገባል።

የዎላይታ ዞን ከላይ ከተዘረዘሩ ነጥቦችም በተጨማሪ፣ ያለውን መልካዓ ምድራዊ አቀማመጥንና የአየር ጠባይ ምቹነትን መሰረት በማድረግ ዞኑ የኢንዱስትሪ ማዕከል እንዲሆን የሚያበቃ አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስድ ደጋግመን ማሳሰባችን ይታወሳል።

የዎላይታ ዞን የኢንዱስትሪ ዞን የመሆን ጥያቄ አንገብጋቢና ወቅታዊ ጥያቄ እንዲሆን ካስገደዱ ሁኔታዎች ጥቂቶቹ 1. የዞኑ የእርሻ መሬት እጅግ እየተበበ ከመምጣቱም በላይ ለረዥም ጊዜ የታረሰ በመሆኑ ምርታነቱን እየቀነሰ መምጣቱ 2. የሕዝብ ብዛትም እጅግ በጣም እየጨመረ የመጣ በመሆኑ የተመረተ ያህልም ቢሆን ለአንድ አባወራ ገበሬ ራሱንና ቤተሰቡን ለማስተዳደር የሚያስችል ሆኖ አለመገኘቱና 3. የዎላይታ ወጣት ትውልድ ትምህርት በመቅሰሚያው ጊዜ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ላይ ተጠምዶ በመላ አገሪቱ ተበትኖ መገኘቱና የመሳሰሉ ናቸው። ይህ ሁኔታ በስፋት ተገልፆ በአንደኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ውስጥ ተካቶ እንዲፈፀም አሳስበን ነበር። ይሁን እንጂ እንኳን የተፈፀመና የተሞከረም የለም። ያ ዞን አሁን ባለበት ከቀጠለ በሂደት በአጭር ጊዜ ውስጥ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት የሚሳነው ይኖራል ብለን አንጠብቅም። ያንን በመሰለ ጥሩ ጆኦግራፊያዊ አቀማመጥ ላይ ባለ ስፍራ በዘርፍ ከዘርፉ በኢንቨስትመንት የሚመቹ ሁኔታዎችን ሳቢ በሆነ ሁኔታ በማዘጋት የውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችን በመጋበዝ ሲያወያዩና ሲያበረታቱ አይታይም።

ለአገራዊ ዕድገትና ለሕዝባዊ ጥቅም ፍፁም ወደር የማይገኝላቸው ድርጊቶችን ለመፈፀም ችላ እየተባለ (እየተለገመ) ኪራይ ሰብሳቢነት መወገድ አለበት፤ መልካም አስተዳደርም መስፈን አለበት እያሉ በቃል ብቻ ማውራት ለታሪክ ወቀሳና በትዝብትም የሚጋለጡ አይቀሬ ይሆናል። ሐዋሳ ወደ ፌዴራል ከተማነት አድጎ ሶዶ የክልሉ ዋና ከተማ መሆን ዞኑም የኢንዱስትሪ ዞን እንዲሆን ማድረግ ለሁሉም ተመጋጋቢ የምርት እንቅስቃሴ ለሚያደርጉ አጎራባች ሕዝቦች የሚሰጠው ጠቀሜታ ወደር የሌለው መሆኑ በከፍተኛ ትኩረት ተጢኖ ተፈፃሚ መሆን ይገባል እንላለን።

-    ድህነትና ኪራይ ሰብሳቢነት የተወገደበት፤

-    መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲዊ ሥርዓት የሰፈነብ ኢትዮጵያን እንረገነባለን።

የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር

(ዎሕዴግ)

ሕዳር 23 ቀን 2008 ዓ.ም

አዲስ አበባ

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
2070 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us