መፍትሔ ያጣው የመልካም አስተዳደር እጦት መዳረሻው ሠራተኞች በህግ ያገኙትን ደመወዝ መከልከል ሆነ

Wednesday, 09 December 2015 14:13

 

 

በዮሴፍ ጌታቸው

የመንግስት መ/ቤቶች የሚተዳደሩት መንግስት በዘረጋው መዋቅራዊ አደረጃጀት ግልጽ የሆነ መንግስታዊ አሰራር በመዘርጋት እንደሆነ በኢ.ፌ.ድ.ሪ. ህገ መንግስት በግልጽ የተደነገገ ጉዳይ እንደሆነ ያታወቃል። ቅጥ ያጣው የመልካም አስተዳደር ችግር ደግሞ ዛሬ ዛሬ የመንግስት ቁንጮ የሆነውን የኢ.ፌ.ድ.ሪ  ጠቅላይ  ሚኒስቴር  ጽ/ቤት የሰጠውን ትእዛዝ ባለመቀበል የህግ የበላይነትን በሚጻረር መልኩ ከጠቅላይ ሚኒስቴር  ጽ/ቤት የተላከውን ደብዳቤ በመሰወር የሠራተኞችን ህጋዊ ደሞዝ ለሶስት ዓመት እንዳይከፈል እስከማድረግ ዘልቋል። የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊ ለሦስት ዓመታት የተደበቀው ደብዳቤ በያዝነው ዓመት ጥቅምት 2008 ዓ.ም ተገኝቷል። ባለስልጣኑም ችግሩን አምኖ የተቀበለ ይሁን እንጂ ድርጊቱ በተቋሙ የመልካም አስተዳደር ችግር ጣሪያ የደረሰ ሰሚ ያጣ ጉዳይ እንደሆነ አሳይቷል።

የፌዴራል ንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥብቃ ባለስልጣን የደሞዝ ማስተካከያውን እንዲደረግለት የጠየቀው እና ይህ የደሞዝ ማስተካከያ ከተደረገለት በኋላ ደግሞ ለሚፈልገው አካል የደሞዝ ማስተካከያውን ተግባራዊ በማድረግ ለማይፈልገው አካል ደግሞ ደብዳቤውን በመሰወር ተግባራዊ እንዳይሆን በማድረግ፣ ግልጽ ከሆነው የመንግስት አሰራር ውጭ በሀገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መንግስት የፈቀደውን ደሞዝ ለ3 (ሦስት) ዓመታት በመደበቅ ሰራተኞች በህግ የተፈቀደላቸውን ደሞዝ በመከልከል ጥቅማቸውን በእጅጉ ሲጎዳ ቆይቷል። ይህ ደግሞ የህግ የበላይነትን በመጣስ የተፈጸመ በሀገሪቱ የወንጀል ህግም የሚያስጠይቅ ተግባር ነው። ምክንያቱም በሀገሪቱ ህግ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ማንም አካል ያለ በቂ ህጋዊ ምክንያት የሰራተኛን ደሞዝ መቁረጥ አይችልም።

የኢ.ፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ለለፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር፤ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ለኢ.ፌ.ድ.ሪ. ንግድ ሚኒስቴር፤ የኢ.ፌ.ድ.ሪ ንገድ ሚኒስቴር የደሞዝ ስኬል ማስተካከያውን ባለስልጣኑ ተግባራዊ እንዲያደርግ ለባለስልጣኑ የላከውን ደብዳቤ ስልጣንን አለአግባብ በመጠቀም ደብዳቤውን በመሰወር ግልጽ ባልሆነ የመንግስት አሰራር የባለስልጣኑን ፋይናንስ ዳይሬክቶሬት በከፊል ለዳኞች ብቻ የደሞዝ ማስተካከያውን እንዲፈጽም ህገወጥ ትእዛዝ በመስጠት በተቋሙ የመልካም አስተዳደር ችግር ለሚታገሉ ዓቃቤ ህጎች የደሞዝ ማስተካከያው ተግባራዊ እንዳይሆን በማድረግ እና አገር አቀፍ ደሞዝ ጭማሪም ከቀድሞ የደሞዝ እስኬል ላይ ተነስቶ እንዲሰራ በማድረግ ለዳኞች ግን በከፊል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ካጸደቀው እና ፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ለንግድ ሚኒስቴር አውርዶ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለባለስልጣኑ እንዲፈጽም ከላከው የተሻሻለ የደሞዝ ስኬል ላይ እንዲሰራ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ዋና ዳይሬክተሩ ፈጽመው ይህንንም ለሚዲያ አካላት አምነው ችግሩ የሚመሩት አንድ ክፍል እንጂ የእርሳቸው እንዳልሆነ አድበስብሰው መረጃ ለመስጠት ሞክረዋል።   

በባለስልጣኑ የምንገኝ ዐቃቤ ህጎች እና የምርመራ እና ዐቃቤ ህግ ዳይሬክተር እንደማንኛውም ዜጋ ግልጽ በሆነ ማስታወቂያ የሚፈለገውን የትምህርት ዝግጅት እና የስራ ልምድ በሟሟላት ተወዳድረን በገባንበት የስራ መደብ ለመደቡ የተፈቀደው መነሻ ደሞዝ በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ትእዛዝ ተግባራዊ እንዳይደረግ በመደረጉ እንዲፈጸም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በቁጥር መ/20-3/813/1 በቀን ህዳር 10/2005 ዓ.ም. ለኢ.ፌ.ድ.ሪ. ንግድ ሚኒስቴር የተሰጠውን መመሪያ የኢ.ፌ.ድ.ሪ. ንግድ ሚኒስቴር በቁጥር 01.89/14 በቀን ህዳር 17/2005 ዓ.ም. ለባለስልጣን መ/ቤቱ በተፈቀደው ስኬል መሰረት ተግባራዊ እንዲደረግ የደሞዝ ስኬል የላከ ቢሆንም ባለስልጣን መ/ቤቱ በዋና ዳይሬክተሩ አመራር  የተለያየ የደሞዝ እስኬል ከተፈቀደው ውጭ ለህግ ባለሙያዎች መጠቀም እንደሚችል ለራሱ ስልጣን በመስጠት በባለስልጣኑ ለሚገኙ ዳኞች የደሞዝ እስኬሉን ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲያደርግ ለአቃቤ ህጎች እና ለክፍሉ ዳይሬክተር የደሞዝ ስኬሉ በትክክል እንደሚመለከተን እየታወቀ ዋና ዳይሬክተሩ ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ ከህግ አግባብ ውጭ ደብዳቤው እንዲሰወር በማድረግ እንዳይከፈለን አድርገዋል።

መንግስት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በፈቀደው መጠን የመንግስት ሠራተኛው ኑሮው መቋቋም እንዲችል የሰራተኛውን ጥቅም የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች ሲያስተላልፍ አንዳንድ የመንግስት መ/ቤቶች መጠነኛ የሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር ቢኖርባቸውም የመልካም አስተዳደር ችግሩ ግን ገፍቶ የህግ በላይነትን በሚጻረር መልኩ የሀገሪቱ የስልጣን ቁንጮ የሆነው የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የሰጠውን ትእዛዝ ሽሮ በህግ የተፈቀደን የሠራተኞች ጥቅም በመንፈግ ለሚፈልገው እየከፈለ፣ ለማይፈልገው የማይከፍልበት የስርዓት አልበኝነት ላይ ተደርሷል። በመሆኑም  መንግሥት እንዲህ ዓይነቱን ዓይን ያወጣ ሥርዓት አልበኝነትና የመልካም አስተዳደር ችግር የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ኃለፊዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት እናሳስባለን። ይህ ጽሁፍ ለአንባቢ ሲደርስ አሳታሚ ድርጅቱ ወይም የጋዜጣው አዘጋጅ ሳይሆኑ ኃላፊነቱን የሚወስዱት ጽሁፉን አዘጋጅቼ የላኩት የጽሑፉን አቅራቢ የሚመለከት እንደሆነ አረጋግጣለሁ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1523 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us