“አለባብሶ ቢያርሱ በአረም ይመለሱ”

Wednesday, 09 December 2015 14:17

የኢትዮ-ሱዳን ድንበር የማካለል እንቅስቃሴ በተመለከተ

ከኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ /ኢራፓ/ የተሰጠ መግለጫ

የዛሬ ዘንድ ዓመት ተኩል አካባቢ የኢትዮ- ሱዳን ድንበር የማካለል እንቅስቃሴ በተሟሟቀበት ወቅት የነበረው የህብረተሰባችን የተቃውሞ ትኩሳት ጫፍ በመድረሱ የማካለሉ ተግባር አለመፈፀሙን በከፍተኛ የመንግስት አካላቱ አማካይነት ተደጋግሞ ለህዝባችን መግለፁ ቢታወቅም በወቅቱ ሙከራዎቹ እንደነበሩ ማካለሉ የሚከናወንበት አመቺ ወቅት የኢትዮጵያና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲወሰኑ በመሪዎች መካከል ስምምነት እንደነበረ መዘገቡ ይታወቃል። ይህም የህዝባችንን ቁጣና ግፊት ለማስተንፈስ ታቅዶ ጊዜ የመግዣ ታክቲክ እንደሆነ ተቆጥሯል።

አሁን የተጠበቀው ጊዜ በመድረሱ ይመስለናል። የሱዳን መንግስት የይገባኛል ጥያቄ አቅርቦ በይደር የቆየውን አወዛጋቢ 250 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሆን የኢትዮጵያ ግዛት በመሬት ላይ የማካለል (Demarcation) ተግባር በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተጀምሮ ሊጠናቀቅ እንደሚችል በሀገር ውስጥና (እንደ ሪፖርተር ጋዜጣ)፤ ከሀገር ውጭ እንደ ሱዳን ትሪቡን ሌሎችም ድረ-ገፆች እና ማህበራዊ ሚዲያዎች ዜናውን ከተለያዩ ምንጮች እየፈለፈሉ በማውጣት ከዓለም የወቅቱ ትኩስ ዜናዎች አንዱ እንዲሆን አድርገውታል። በቅርቡ ህዳር 13 ቀን 2008 ዓም የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሱዳን 2ኛ ም/ፕሬዝዳንት ሃሳቦ መሐመድ አብዱሰራሃምን ጋር አዲስ አበባ ላይ ያካሄዱት የውይይት ርዕሶች ማለትም ነፃ የኢኮኖሚ ዞን ስለመፍጠር አመቺ ነፃ የንግድ ስርዓትና የባንክ ትብብር አለማድረግ መካከል የጋራ ድንበር ለማካለል የደረሱበት ስምምነት ስለመኖሩ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን መግለፅ ባይፈልግም/ ባይፈቀድለትም ከውጭ የሚዲያ ተቋማት ወዲያውኑ መዘገቡና መሰራጨቱ የአደባባይ ሚስጢር አስብሎታል።

የሱዳን የመንግስት ባለስልጣትና የሚዲያ ተቋማት መንግሥታቸው በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በህዝባቸው ስም ያከናወኑአችን አብይት ሀገራዊ ተግባራት ከእነምንጮቻቸው ወዲያውኑ በአደባባይ እንደወረደ ሲገልፁና ሲያስረዱ ለህዝባቸው ቅርብ የመሆናቸውና የግልጽነት ዲሞክራሲያዊ ባህሪቸው ከእኛዎቹ ልዩ እንደሚያደርጋቸው በማመልከቱ ያስቀኑናል።

አሁንም የኢትዮጵያ መንግስት ቀጥሎ የተመለከቱትንና ሌሎች ተጓዳኝ ከታሪካዊ ስህተት፣ ጥፋትና ተጠያቂነት ሊታደጉ የሚችሉ ዲሞክራሲዊና ሕገ-መንግስታዊ የጥንቃቄ እርምጃዎች በአስቸኳይ መውሰድ እንዳለበት የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ያምናል።

$11.  በ1987 ሕገ-መንግስታችን አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 በተደነገገው ድንጋጌ መሠረት ይህ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር የመከለል አጀንዳ እና የተያዘለትም ቀነ ቀጠሮ ለባለቤቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽና ግልፅ ይሁንለት። ይህንንም ባላደረጉት ወይንም  ማድረግ በማይፈልጉት የመንግስት ኃላፊዎች ላይ ሕገ-መንግስቱ ተጠያቂ ማድረጉ ለህብረተሰባችን ይረጋገጥ።

$12.  በዚሁ ሕገ-መንግስታችን አንቀጽ 29/ን/ አንቀጽ 3(ለ) ላይ የተረጋገጠው “የህዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት ዕድልን” ማሳጣት በራሱ ኢ-ሕገመንግስታዊ ድርጊት ሆኖ መቆጠሩ ስለማይቀር የእርምትና የማስተካከያ እርምጃዎች በጊዜና በቦታው መወሰዳቸው ይረጋገጥ፤

ከዚሁ ጋር የሰሞኑ አቢይ ርዕስ ሆኖ የቆየው እና በተከበሩ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ-ጉባኤ በአቶ አባዱላ በሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተመራውን ስለመረጃ አሰጣጥ አቀባበልና አተገባበር የተቀየሰው አዲስ እና በጎ የተሀድሶ መስመር በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጭምር መተግበሩ ይረጋገጥ፣

$13.  በዚሁ የበላይ የሕግ ሰነድ አንቀጽ 29 /ን/አንቀጽ 5 የተገለፀው “በመንግስት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አስተያየቶች ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ያደርጋል” የሚለው ድንጋጌ ያለመከልከል ተግባራዊ እንዲሆን እና በዚሁ አንቀጽ ን/አንቀጽ 4 እንደተመለከተው ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ሃሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሰራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖው የህግ ጥበቃ ይደረግለታል የሚለው ድንጋጌ ጭምር በዚህ ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ ጭምር በሙሉ ኃይሉ ስራ ላይ እንዲውል፤

$14.  የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳንም ሆነ ከተቀሩት ጎረቤትና አጎራባች ሀገራትና መንግስታት ጋር የሚኖረው ግንኙነትና የውጭ ፖሊሲው ወጥነትና ዘላቂነት ያለው ሆኖ የቀደምት የጥንት የጠዋቱ ጀግኖቻችንና አርበኞቻችን መስዋዕትነት ቀይ መስመር ድንበር ላይ በመቆም የሀገራችንን ሁለንተናዊ (ዳር ድንበርን ጨምሮ) ህልውናና ማንነት አስከብሮና ጠብቆ ወደ ከፍታ ከማሸጋገር ውጭ በሕገ-መንግስቱ ባልተሰጠና ባልተፈቀደለት ስልጣን ተጠቅሞ ሀገርን ቆርሶ የመስጠት አባዜ፣ ቢፈፀም እንኳ የሁለቱ ህዝቦች የእስካሁኑን ጤናማና ታሪካዊ ግንኙነት የሚጎዳና የሚፈታተን ብቻ ሳይሆን የማይሽር የታሪክ ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ ድርጊት በመሆኑ መንግስት ደግሞ ደጋግሞ ሊያስብበት ይገባል እንላለን።

$15.  ምን አልባት የኢትዮጵያ መንግስት በአንዳንድ ሁኔታዎች ምክንያት ይህ ወሳኝ ሀገራዊ የወሰን አካለል አጀንዳ ከአቅሙ በላይ የሚሆንበት ከሆነ የሉዓላዊነቱ ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሆነ ጉዳዩን ለህዝበ - ውሳኔ የማቅረብ ኃላፊነትን ሊወጣ ይገባል እንላለን። ከዚሁ ጋር በርዕሰ-ጉዳዩ ላይ ሕዝብንና የሀገሪቷን ተፎካካሪ (ተቃዋሚ) ፓርቲዎችን ለግልፅና ለዲሞክራሲዊ ውይይቶች ሁኔታዎችን በአስቸኳይ  ማመቻቸት ይጠበቅበታል። 

$16.  ከዚሁ የተለየ የተሻለና ለአሁኑም ሆነ ለመጭዎቹ ትውልዶች ጤናማ ውጤታማና አትራፊ ሊሆን የሚችል ቋሚ ወይም ዘላቂ ሀገራዊና ሕዝባዊ ጥቅም የማስገኘት የተለየ ሕዝባዊ ራዕይ መንግስት ካለው ለህዝባችን በቅንነትና ግልፅነት አሳማኝ ምክንያት ከማስረገጥ አኳያ የዜጎቻችንን አስተያየቶችና የህዝብ ድምፅ መስማትና ማክበር ይጠበቅበታል።

በመጨረሻም የኢትዮ-ሱዳንን ወሰን የማካለል ተግባር በመንግስት በኩል ብቻ የሚወሰድ የተናጠል እርምጃ ያለ ህዝባችን ሙሉ ይሁንታና ፈቃድ፣ ከሀገራችን ጠቅላላ የግዛትና የቆዳ ስፋት 22 በመቶ የሚሆነውን ለጎረቤት ወዳጅ መንግስት ገጸ-በረከት የማቅረብ እንቅስቃሴ በምንም መመዘኛ ሕገ-መንግስታዊና ፍትሃዊ ብሎም ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ የመሆን ሕጋዊ መሠረት ስለመኖሩ መንግስት በትክክል ግልጽነትና ቅንነት በተላበሰ ሕዝባዊ ውይይት ማሳመን ባልፈለገበትና መላው ዜጎቻችን በሀገራቸው አንኳር ጉዳይ ብሎም በህልውናው ላይ በመጣበት አደጋ ድምፃቸውን የሚያሰሙበት ዕድል ባልተሰጠበት በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ያለው ወይንም ሊደረግ የታቀደው የኢትዮ-ሱዳን ድንበር የማካለል መርሃ-ግብር “አለባብሶ ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንዳይሆን፣ እንዲቋረጥ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ድምፁን ከፍ አድርጎ ለማሰማት ይገደዳል።

                                 እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

                                 ህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
707 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 66 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us