ፍትሕ የተነፈገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል

Wednesday, 16 December 2015 13:14

 

 

ከማዕከሉ ሰራተኞች አንዱ፤

ተመርቄ ስራ ለመጀመር ደፋ ቀና ስል የመጀመሪያ ስራ የቀናኝ የኢትዮጵያ ባህል ማዕከል ነበር። ስሙ ግዙፍ ስለነበር ከምኞቴ ጋር በመገጣጠሙ እድሌን ወደድኩት። ብዙ አልቆየሁም ምናልባትም በጣት የሚቆጠሩ ወራት፤ የምሰማው ነገር ሁሉ ድጋሚ የስራ ማስታወቂያዎችን እንዳሳድድ አደረገኝ። በአዋጅ የተቋቋመው ብሔራዊ መስሪያ ቤት ውስጡ የተተራመሰ፣ ፍትሕ የጎደለበት፣ እሮሮ የሚያቀርበው ሰው ስፍር ቁጥር የሌለው ሆነብኝ። በመ/ቤቱ ብዙም ሳልቆይ አንዱ የሮሮ አሰሚ ሆኜ አረፍኩት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ቀድሞ የኢትዮጵያ ስብሰባ ማዕከል የሚባለው ነው። አሁንም ቢሆን ከአዲሱ ስሙ ጋር የሚስተካከል ስራ ስላልሰራ ብዙዎች የሚያውቁት በዚሁ የቀድሞ ስሙ ነው። ማዕከሉ በፍትሕ እጦት የሚሰቃዩ ሠራተኞች የሞላንበት መሆኑ እውነት ይህ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው? እንድንል አስገድዶናል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ግለሰብ ማዕከሉ በአዋጅ የተቋቋመ ሳይሆን የግል ንብረታቸው ሆኗል። የማዕከሉ ተሽከርካሪዎች ግለሰቧን ብቻ ያገለግላሉ። ግዢና ፋይናንስ የሚመራው በሕግና በሥርዓት ሳይሆን በግለሰቧ ውሳኔ ነው። የስራ ኃላፊዎችና የማኔጅመንት አባላቱ አንዳች የሚያገባቸው ነገር የለም። ማቀድና ያቀዱትን መስራት እኛ ጋር የውሃ ሽታ ነው። በዚህ ሁኔታ መንግስት የ75 ብሔረሰቦች የባህል አስተዋዋቂ አድርጎ ከእኛ ብዙ ስራ ይፈልጋል። እኛም ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በአንድ ሰው በሚመራ ተቋም የምንሰራ የግለሰብ አሽከሮች ሆነን ኖረናል። በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገንዘቦች ለገንዘብ ሚኒስቴር ሳይሰራባቸው ተመላሽ ይሆናሉ።

መስሪያ ቤቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህል እንዲያስተዋውቅ ቢቋቋምም ይህንን መስራት የሚችልበት አቅም እንዲፈጠር የሚያስችል አቅም ያለው መሪ አላገኘም። ብሔራዊ ተቋም ማዕከል መሆኑ ቀርቶ የወረዳና የዞን ዕቅዶችን በገንዘብ እየደገፈ አብረን ሰራን የሚል ሪፖርት የሚያቀርብ ሆኗል። የሸካ፣ የቤንች ማጂና የዳውሮ ዞን ፌስቲቫሎች በዚህ መልኩ የተከናወኑ ጣልቃ ገብነቶችና የሪፖርት ማሟያዎች ናቸው። በእርግጥ ተቋሙ ሙሉ ለሙሉ በሰው ኃይልም የተደራጀ አይደለም። ከሚፈልገው የሰው ኃይል 70 በመቶው የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አሻፈረኝ በማለታቸው ሳይሟላ አምስት ዓመታት ቆይቷል።

በተደጋጋሚ የመብት ጥያቄ ያነሱ የመስሪያ ቤቱ ባልደረቦች በህገወጥ አሰራር እየተሰቃዩ ነው። የመስሪያ ቤት ክበብ ሳይቀር በርካሽ ምግብ መመገብ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው ተብሎ እንዲዘጋ ተደርጓል። ምናልባትም አዲስ አበባ ውስጥ ካሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ክበብ የሌለው ተቋም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ብቻ ይመስለኛል።

ብዙ ጊዜ አቤቱታ አቅርበን ሰሚ አጥተናል፤ ተሰናባቹን ሚኒስትር ጨምሮ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታዎች ጭምር አወያይተውን ምላሽ አጥተናል። ግለሰቧ የተቋሙን የመንግስት ቤት በስማቸው አዙረዋል። ተደጋጋሚ አበል በመብላት በኪራይ ሰብሳቢነት ተጠምደዋል፤ ብለን ለፌዴራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና  ኮሚሽን ብናመለከትም ምላሽ አላገኘንም። ሌላው ይቅርና ዶክተር ነኝ የሚሉት የግለሰቧ የትምህርት ማስረጃ የፒኤችዲ ማረጋገጫ ሰነድ አለመያያዙ በተደጋጋሚ ጥያቄ አስነስቶ አሁንም ምላሽ አላገኘም። በመንግስት ወጪ የትምህርት ማስረጃዬን ላምጣ ብለው ራሺያ ድረስ በመሄድ ሳይዙ ተመልሰዋል። ይህንን ሁሉ ጉድ መንግስት እያወቀ በሠራተኛው እንባ መገረሙን ቀጥሏል።

የመንግስትም ሆነ የግል ሚዲያዎች ማዕከሉን ችላ ብለዋል። በእርግጥ የግል ፕሬስ ደጃፌን አይረግጥም የሚል አባባል ስላላቸው የትኛውም የግል ሚዲያ የምንሰራውን ተጠግቶ የማየት እድል አልገጠመውም። የመስሪያ ቤታችን ኩነቶች መንግስት ኮሙኒኬሽን ፈጽሞ አያውቃቸውም።

አሁን አዲስ መንግስት መጣ ስንል ለእኛ አሮጌ አስተሳሰብ ይዘን የሀገሪቱን የህዳሴ ጉዞ ከተጣለብን ኃላፊነት ጋር እንደማንወጣው በማረጋገጥ ነው። ለምሳሌ የኮሬ ብሔረሰብ ላይ የሚያተኩር የባህል ህግ ታትሞ ግለሰቧ ስላልተመቻቸው ከሁለት ዓመት በላይ መሰራጨት አልቻለም። ብል እየበላው መጋዘን ያጣብባል። የእኛ ፋይናንስ በግለሰቧ መልካም ፍቃድ ብቻ የሚንቀሳቀስ ነው። የሰሞኑ ሹም ሽር እልባት ይሰጠዋል ብለን ተስፋ ስናደርግ ጭራሽ “አዲሷ ሚኒስትር ጓደኛዬ ናት” እየተባልን ተሸማቀን ልንሞት ነው። በእውነት እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ነን? ኢትዮጵያስ ተራ ግለሰቦች ብሔራዊ ተቋምን እንደፈለጉ እንዲያደርጉ የምትፈቅድ ሀገር ናት? የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር መሪ ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን እባክዎትን ይድረሱልን? ያኔ ኢህአዴግ የእውነት ለውጥ ላይ እንደሆነ እናምናለን። ይሄ የግለሰብ ጽሑፍ ይሁን እንጂ የመስሪያ ቤቱ ሠራተኛ መቶ በመቶ የሚያምንበት ነው። የመንግስት ያለህ!….

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
651 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 70 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us