ሞኝን አንዴ ስደበው፣ ራሱን ደጋግሞ ሲሰድብ ይኖራል፣

Thursday, 24 December 2015 11:23

 

 

የመጨረሻ ክፍል

ከታክሶ ላጮ

ከጌቶ ዴሬ

የዛሬውን ክፍል ሦስት ፅሁፌን የምጀምረው በማሻሻያ ስራ ነው። ወደ ማሻሻያ (መቀነስ) ሥራ የገባሁበት ምክንያት የክፍል ሁለት ፅሑፌን ለሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ልኬ ጽሁፉ ስለበዛ ተቀንሶ ይቅረብ በሚል ምክንያት ሳይታተም ከ6 ሳምንታት በላይ ቆይቶ የግድ ቀንሼ ከላኩ በኃላ ለሕትመት ሊበቃ ችሏል። በዚህ ምክንያት በክፍል ሁለት ጽሁፍ ከነበረው ውስጥ ከየገፁ መሀል እየቀነስኩ ያወጣሁት እንዳለ ሆኖ ከመጨረሻ ላይ ቆርጨ ያስቀረሁትን 2 ገፅ ወደዚህ ፅሁፍ አምጥቻለሁ። ቀደም ሲል ያዘጋጀሁት ክፍል 3 ፅሁፍም ከ6 ገፅ በላይ ስለሆነ ቀንሼ ማዘጋጀት ግድ ስለሆነ 4 ገፅ ለመቀነስ ተገድጃለሁ። ስለዚህ ወደ አሳጠርኩት ሀሳብ ልግባ፡-

ሻመና በፅሁፉ ውስጥ ወራባ እርሻ በፃፈው መፅሀፍ ምንያት የተነሳውን አቧራ አይተናል። ጥቂት ጋሞ ነን የሚሉ ትምክተኞች በተለይ «ዶኮ»  በማለትና ጥቂት ጋሞነን ባይዎች ከማዶላ ፀሐፊ ባልተናነሰ በግል ሊጠየቁ ይገባል በማለት ስሜቱን ተንፍሰዋል። በዚህ አይነት ሻመና “ዶርዜ ጋሞ አይደለም” በሚለው አካሔድ ከልብ አያምኑም ማለት ነው። የፃፉትም በማያምኑትና ከልብ ባልተቀበሉት ጉዳይ ላይ ነው ለማለት ይቻላል። ሻመና ከልብ ሳያምኑ በተለያየ ምክንያት ሀሣቡን እያራመዱት ካሉ ክፍሎች ሊሆኑ ይችላሉ እንጂ አቋማቸው አይደለም። አቋማቸው ከሆነማ የጋሞ ሕዝብን ጥቂት ብለው ከፈረጁ የጋሞ ሕዝብ አንድ ሃምሳኛ (1/50ኛ) የሆነውን የዶርዜ ሕዝብ ምን ሊሉ ይሆን? የጋሞ ሕዝብን (ተወላጆችን) ትምክተኛ ብለው ከፈረጁ ሌላ ሌላውን ምን ሊሉ ይሆን? እኛስ ማንና ምን እንባል ይሆን? ወይስ የጋሞ ሕዝብን ሕዝባዊም ሆነ ግላዊ ባህሪን፣ እንዲሁም ባህል፣ ወግና ልማድ አያውቁም ይሆን? የጋሞ ሕዝብን  (ተወላጆችን) ሕዝባዊም ሆነ ግላዊ ባህሪን እንደዚሁም ባህል፣ ወግና ልማድ የማያውቁ ከሆነ የዶርዜ ሕዝብ ከሌላው የጋሞ ሕዝብ የተለየ ባህል፣ ወግና ልማድ አለው ብለው እንዴት ሊገልፁ ይችላሉ? የዶርዜ ሕዝብ ከጋሞ ሕዝብ የተለየ ወግ፣ ልማድና ባህል ያለው መሆኑን መግለፅ ካልቻሉስ እንዴት የተለየ ብሔረሰብ ነው ብለው ሊፅፉና ሊከራከሩ ይችላሉ? ስለዚህ ሻመና በማያምኑትና አቋማቸው ባልሆነ ሀሳብ ላይ በሌሎችና በተለያየ ምክንያት ግፊት እየፃፉና እየተከራከሩ መሆኑን መረዳት ይቻላል።

አንዳንዴ ሌላውን ሰደብን፣ አሳነስን፣ እንኳሰስን ብለን ስንል መልሰን ራሳችንን እየሰደብን፣ እያሳነስን፣ እያንኳሰስን መሆኑ እንዴት አይሰማንም? ራሳችንን መላልሰን እየሰደብን መሆኑ ለምን አይታየንም? ለመሆኑ ሻመና ከትምክተኝነትና ከጠባብነት የቱን ይመርጣሉ? እኔ በበኩሌ ሁለቱንም አልመርጥም። ነገር ግን ከሁለቱ አንዱን የመምረጥ ግዴታ የግድ ሆኖ ቢቀርብልኝና የማይቀር ከሆነ ግን ትምክተኝነትን እመርጣለሁ። ጠባብነትን አጥብቄ እጠላለሁ። ጠባብ መሆን፣ ጠባብ አስተሳሰብን መሸከም፣ ጠባብነትን ማራመድና መመኘት ለሀገር፣ ለሕዝብ፣ ለሰፈር፣ ለመንደር ለቤተሰብም ሆነ ለግለሰብ የማይጠቅምና የማይበጅ ክፉ ነገር ነው። ስለዚህ በግሌ ጠባብነትን፣ የጠባብ አመለካከትና አስተሳሰብ ተሸካሚነትን እጅግ እጠላለሁ።

ስለአቧራ ማስነሳት ስናስብ በመሠረቱ የጋሞ ሕዝብ አቧራ አላስነሳም። የጋሞ ሕዝብ እኔና ሻመናን የሚጨምር ሕዝብ ነው። በመሆኑም የተነሳውና የተከራከረው ለጋራ ማንነታችን፣ ለጋራ ክብራችን ነው። የጋሞ ሕዝብን የሚጎዳና የሚያጠቃ ነገር ቢመጣ እኔን በመሀል ትቶኝ አያልፍም። እኔ የጋሞ ሕዝብና አገር እምብርትና ልብ በሆነ አካባቢ በዶርዜ የተፈጠርኩ ጋሞ ነኝ። የዚህ ሕዝብ መብትና ክብር ሲነካ የእኔም፣ የወገኖቼም መብት ጭምር ስለሚነካ ሰልፉ፣ ስብሰባውም ሆነ ጩኸቱ የጋራችን ነው። ጋሞ አገር የለውም ከተባለ በጋሞ መሀከልና እምብርት  ላይ ያለው ዶርዜም አገር የለውም ማለት ነው።

ስለሆነም በዚህ ምክንያት ከጋሞ ወንድሞቼ ጋር በሁለት ስብሰባዎች ተካፍያለሁ። ለሌሎቹ የዶርዜ ወንድሞቼ፣ እህቶቼ፣ እናትና አባቶቼም የምመከረው የተነካው የጋራ መብትና ክብራችን በመሆኑ፣ የተሰደብነውና አገር የላቸውም የተባልነው በጋራ ስለሆነ በጋራ እንድንሰለፍ፣ በጋራ እንድንሰበሰብ፣ በጋራ እንድንጮህ፣ በጋራ እንድንታገል ነው። ሰልፉ፣ ስብሰባውም ሆነ ጩኸቱ አቧራ የማስነሳት ጉዳይ ሳይሆን መብትን የማስከበር፣ ትግልና ጥረት ነው። ስለዚህ በጋራ ልንሰለፍና በጋራ ልንሰበሰብ ይገባል። በነገራችን ላይ ይህን አስቀድሞ የተገበሩና ዶርዜ ሆነው በጋሞነታቸው አምነው በሰልፉ፣ በስብሰባውም ሆነ በጩኸቱ በጋራ የተሳተፉ በርካታ የዶርዜ ተወላጆችን አግኝቻለሁ። ጋሞነት ለአንድ ወረዳ ሕዝብ ወይም ዶኮ ለተባለ ዴሬ ጥለንና ትተን የምንሔድ አልባሌ ነገር አይደለም። የአያት ቅድመ አያቶቻችን፣ የዘር ማንዘሮቻችን የደምና የህይወት ውህደት የፈጠረው የጋራ ማንነትና በጋራ የገነባነው መለያችን ነው። ስለዚህ ይህን ማንነታችንን ልንክድም፣ ልንሸሽም ሆነ ለማንም ትተንና ጥለን ልንሔድ አንችልም።

ትላንት ሌላው ወገን የሰደበን አንሶ ዛሬ እኛ ራሳችን በራሳችን እየሰደብን፣ እያዋረድን፣ እያንኳሰስን የምንሔድበት ሁኔታ፣ ዛሬም ሆነ ወደፊት በታሪክና በትውልድ ፊት  ተጠያቂና ተወቃሽ ያደርገናል እንጂ ተመስጋኝ አያደርገንም። በተለይ በአንዳንድ በእኛ ልጆች የተያዘው አካሔድና አቋም ለራሳችን ለዶርዜ ሕዝብም ሆነ ለአጠቃላዩ ለጋሞ ሕዝብ የማይጠቅም፣ ብሎም አካባቢያችን እንዳይለማ፣ እንዳያድግና እንዳይሻሻል የሚያደርግ ስለሆነ ከዚህ አካሔድና አቋም ልንወጣ ይገባል። ራሳችን የልማታችንና የዕድገታችን ፀር ሆነን እያለ በእኛው ችግር ምክንያት ባልመጣው ልማት ሌላውን ብቻ ተወቃሽ ማድረግ ትክክል አይደለም።

የልማት ሀይል ሕዝብ ነው። ለአንድ አካባቢ ልማት የዚያ አካባቢ ሕዝብ፣ ለአንድ ክልል ልማት የዚያ ክልል ሕዝብ፣ ለአንድ አገር ልማት የዚያ አገር ሕዝብ ትብብርና አንድነት ያስፈልጋል። በየትኛውም የፖለቲካ ስርዓትም ሆነ የመንግስታዊ አስተዳደር ውስጥ ተቀባይነትና ተሰሚነት የሚያገኘው አንድነቱና ሕብረቱ የጠነከረ ሕዝብና የሕብረተሰብ ክፍል  ነው። አንድነቱና ሕብረቱ የጠነከረ ሕዝብ የሚጠይቀው ማንኛውም ሕጋዊ ጥያቄ በተገቢው ጊዜ ምላሽ ያገኛል።

ስለዚህ ሁሉም የጋሞ ሕዝብ እየተነጣጠለና አንዱ አንዱን የጎሪጥ እየተመለከተ ሳይሆን አንድ ሆኖ አንድነቱንና ሕብረቱን አጠናክሮ ጥያቄያችን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ጥያቄ መሆኑን በማረጋገጥ አካባቢያችንና ሕዝባችን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ተጠቃሚ እንዲሆን በጋራ መቆም ይገባናል። የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የዴሞክራሲና የፍትህ ጥያቄው በጋሞ ጎፋ ዞን ስር ያሉ ሁሉንም የሚመለከት ስለሆነ ሁሉም በጋራ ቢቆሙ ተጠቃሚ ይሆናሉ እንጂ አይጎዱም እላለሁ።

ወደ ክፍል ሦስት ሀሳቤ ልመለስ። በክፍል ሦስት ዶርዜ የተለየ ብሔረሰብ ቢሆን የሚያገኘው ጥቅም ምንድን ነው? የሚደርስበት ጉዳትስ ምንድን ነው በሚለው ሀሣብ አቀርባለሁ ብየ ነበር።

የዶርዜ ብሔረሰብ መብት ተሟጋች ነን የሚሉ ክፍሎች ዶርዜ ከጋሞ የተለየ ብሔረሰብ ቢሆን  ጥቅም ያገኛል ብለው ለሕዝቡ ከሚቀሰቅሱት ልጀምር፡-

$1§  የዶርዜ ሕዝብ ራሱን ችሎ ብሔረሰብ በመሆን በኢትዮጵያ  ካሉ ብሄሮች ጋር እኩል መብት ያገኛል። መብቱን ሲያገኝ ስሙ፣ ከብሩና ማንነቱ ይመለስለታል። ከምኒሊክ ዘመነ-መንግስት ጀምሮ ታውቆ የኖረና በኢህአዴግ ዘመን እንዲጨፈለቅ የተደረገው ታሪክ እንደገና ይታደሳል።

$1§  የዶርዜ ብሔረሰብ በአገር አቀፍ ደረጃ በአገሪቱ የፌዴሬሽን ም/ቤት በብሔረሰብነት መቀመጫ ያገኛል። በፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በአናሳ ብሔረሰብ ደረጃ መቀመጫ ያገኛል። በተመሳሳይ በደቡብ ክልል በብሔር-ብሔረሰቦች ም/ቤት መቀመጫ ያገኛ። በደቡብ ክልል ምክር ቤትም በአናሳ ብሔረሰብነት ደረጃ እንደ ግድቾ፣ እንደ ዛይሴና ኦይዳ ብሔረሰብ መቀመጫ ያገኛል። የዞንና የወረዳ ም/ቤቶች ምርጫ በሚካሔድበት ጊዜም የዶርዜ ብሔረሰብ በዞኑም ሆነ በወረዳ ምክር ቤቶች የራሱ ወኪሎች ይኖሩታል።

$1§  በአገር አቀፍ ደረጃ በፌዴሬሽን ም/ቤትም ሆነ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወከሉ፣ በደቡብ ክልል የብሔር-ብሔረሰቦች ምክር ቤት እና በክልሉ ምክር ቤት የሚወከሉ፣ እና በዞንና ወረዳ ምክር ቤቶች የሚወከሉ ተወካዮች በየምክር ቤቶቹ የዶርዜን ብሔረሰብ መብትና ጥቅም ለማስከበር ይንቀሳቀሳሉ።  የሕዝቡን መብት ያስከብራሉ። ለሕዝቡ መብት ይቆማሉ። ይህን የማያደርጉ ተወካዮችን ሕዝቡ የመገምገም፣ የመሻር፣ ሌላ መርጦ የመወከል መብት ያገኛል፣

$1§  ዶርዜ የተለየ ብሔረሰብ ሆኖ ከተፈቀደለት መንግስት ለብሔረሰቡ በጀት ይመድባል፣ የሚመደበው በጀት በማንም አይበዘበዝም፣ ለዶርዜ አካባቢ እድገትና ልማት፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለመንገድና ለሌሎች መሠረት ልማት ሥራዎች እንዲውል ይደረጋል። በዚህም ሕዝቡና አካባቢው ተጠቃሚ ይሆናል፣ የዶርዜ ብሔረሰብ በሀገራችን የሽመናና የጥበብ ስራ የባለቤትነት መብት ያገኛል። በዚህም በአገርም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ብሔረሰቡ ልዩ ተጠቃሚ ይሆናል…ወዘተ የሚል ነው ቅስቀሳቸው።

እነዚህ ከላይ የተመለከቱ (የተገለፁ) ሁኔታዎች እውነት ለዶርዜ ሕዝብና ለአካባቢው የተባለውን የተለየ መብትና ጥቅም የሚያስገኙ ናቸው? ወይስ የሕዝቡን ስነ-ልቦና በመስረቅና ስሜት በማነሳሳት እንደተለመደው በውስጡ ሌላ የተደበቀ አጀንዳ ለማራመድ የተቀናጁ? የሚለውን እና አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የዶርዜ ሕዝብን ተጠቃሚነት በዝርዝር እንመልከት።

የዶርዜ ሕዝብ ራሱን ችሎ ብሔረሰብ በመሆን አሁን ካለው የተለየ የብሔረሰብ እኩልነት መብት ሊያገኝም ሆነ ሊጎናፀፍ የሚችልበት ሁኔታ የለም። ዛሬ ከሌሎች የጋሞ ብሔር አባል ከሆኑ ዴሬዎች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የብሔሮች ዕኩልነት መብት አግኝቷል። ነገር ግን ዶርዜ ተብሎ በመንደርና በጎሣ በመከፋፈል የተለየ እኩልነት ልናገኝ የምንችልበት ሁኔታ የለም። የዶርዜ ሕዝብ ከምንሊክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ታውቆ የኖረውና በኢህአዲግ ዘመን እንዲጨፈለቅ የተደረገ የተለየ የብቻው ክብር፣ ማንነትና ታሪክ የለውም። የለውም እንጂ ቢኖር እንኳን ከሌላው የጋሞ ሕዝብ ጋር አንድ ላይ ነው የሚኖረው። ከምኒሊክ ዘመን ጀምሮ እስከ ደርግ መንግስት የነበረን ስምና ታሪክ ምን እንደነበረ እናውቃለን። እውነትና ሀቅ እንነጋገር ከተባለ የነበረን የስድብ፣ የንቀት፣ የማንቋሸሽና የማዋረድ ስምና ታሪክ ብቻ ነበር። ስማችን ብቻ ሳይሆን ሙያው ሳይቀር ይሰደብ፣ ይናቅ እንደነበር፣ እኛም በሙያችን እንሰደብ፣ እንናቅ እንዋረድ የነበረ መሆኑን ነው የማውቀው። ይመለስልን የምትሉት ይሔው ስም፣ የውርደትና የስድብ ታሪክ ከሆነ እጅግ ያሳዝናል። በኢትዮጵያ የሽመና ሙያ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የዕደጥበብ ሙያዎች የተናቁ እንደነበረ፣ ሙያተኞቹም ይናቁ፣ ይገለሉና ይዋረዱ እንደነበር እንዴት ተዘነጋን? አው ከምኒሊክ ዘመን ጀምሮ የነበረን ያለፈው ስም፣ ማንነትና ታሪካችን ይሔው ነው።

በነዚያ ጊዜያት የዶርዜ ሕዝብ ብቻ አይደለም የዶርዜ ዴሬ ወንድምና አካል የሆነው መላው የጋሞ ዴሬ ሕዝቦች ሁሉ ተሸማቀው፣ ተዋርደው፣ ተንቀውና አንገት ደፍተው የኖሩበት ዘመን መሆኑን ነው የማውቀው። በተለይም በሽመና ሙያ የሚተዳደሩ ክፍሎች በሌሎች ብሔሮች ውስጥ ያሉም ጭምር ማለት ነው። አያቶቻችን፣ አባቶቻችን ከሰው በታች ሆነው የታዩበት፣ የተረገጡበት፣ የተዋረዱበት ዘመን መሆኑን እንጂ የተለየ እንዲመለስልን የምንፈልገው ምኒሊክ ወይም የፊውዳሉ ስርዓት ያስቀመጠልን የክብር ስም፣ ማንነትና ታሪክ የለም።

የደርግ መንግስት በጊዜው ለዜጎች መብት ምንም ግድ የሌለው ቢሆንም የዕደጥበብ ሙያውም ሆነ ሙያተኞች እንዲከበሩ በማድረግ ለሙያውና ለሙተኞች ከፍተኛ ድጋፍ ያደረገ መንግስት እንደሆነ አይዘነጋም። ያም ቢሆን በጊዜው የነበረው ንቀቱና ስድቡ ሳይቀረፍ ማለት ነው። በዘመነ ኢህአዴግ ግን የዶርዜ ብቻ ሳይሆን የመላው ጋሞ ሕዝብ ክብር፣ ማንነትና ታሪክ ወደ ከፍተኛ ደረጃ መሸጋገሩን፣ የዶርዜ ዴሬም ሆነ አጠቃላይ የጋሞ ብሔር ሕዝብ ታሪክ ከተቀበረበት ጉድጓድ መውጣቱን፣ ሕዝባችን እንደሕዝብ መታየት መቻሉን፣ ወገኖቻችን በግለሰብ ደረጃም ቢሆን እንደሰው መታየት መቻላቸውን ነው የማውቀው። ኢህአዴግን በብዙ ነገር መውቀስና መኮነን የሚቻል ቢሆንም በብሔር /በሕዝብ/ መብት ከሌሎች ካለፉት መንግስታት ሁሉ የተሻለ መሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል። ስለዚህ በኢህአዴግ የተቀበረ ማንነትም ሆነ የተጨፈለቀ ነገር የለም። ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኮርተን፣ ተከብረንና መብት አግኝተን ያለነው አሁን ነው። በመሆኑም ተጠቃሚዎች ሆነናል እንጂ አልተጎዳንም።

በፈደራል የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በደቡብ ክልል የብሔረሰቦች ም/ቤት፣ በፓርላማ፣ በደቡብ ክልል መስተዳደር ምክር ቤት፣ በጋሞ ጎፋ ዞንና በጨንቻ ወረዳ ም/ቤት መቀመጫ ማግኘት ለዶርዜ ልጆች አዲስ አይደለም። በደርግ ዘመን የኢህዲሪ መንግስት ሲመሰረት «የሱራ አውራጃን» ወክሎ የብሔራዊ ሸንጎ አባል የሆነው የዶርዜ ተወላጅ ነው። የያኔው ሱራ አውራጃ የአሁኑን ጨንቻ ወረዳን፣ ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ደጋ አቾሎን፣ ከቦሮዳ የተወሰነ ከምዕራብ አባያ የተወሰኑ ቀበሌዎችን ይዞ በጠቅላላ ከ75 በላይ ቀበሌዎችን ያቀፈ ነበር። በዚህ ውስጥ ያኔ ዶርዜ 6 ቀበሌ ብቻ ነበር። ይህም ሆኖ ዕድሉን አልተነፈገም። በሰሜን ኦሞ አስተዳደር አካባቢ ምክር ቤትም ከሌሎች የሱራ አውራጃ ተወላጆች ጋር የዶርዜ ልጆች ነበሩ። ይህ የሚሆነው የዶርዜ ወይም የጋሞ ብሔር በሚል ሳይሆን ሡራ አውራጃን መሠረት ያደረገ ውክልና ነበር። በኢህአዴግ ዘመንም የጨንቻ ወረዳን ወክለው የፓርላማ፣ የደቡብ ክልል መስተዳደር ምክር ቤት፣ የጋሞ ጎፋ ዞን ምክር ቤት፣ የጨንቻ ወረዳ ምክር ቤት አባል በመሆን የዶርዜ ተወላጆች በቂ ውክልና ሲያገኙ ቆይተዋል። አሁንም እየተወከሉ ይገኛሉ። ከመወከልም አልፎ የጨንቻ ወረዳን በዋና አስተዳዳሪነት አስተዳድረዋል። በካቢኔ አባልነት አገልግለዋል። እያገለገሉም ይገኛሉ። የዶርዜ ልጆች ከደርግ ዘመን ጀምሮ በተለያየ ጊዜ የወረዳውን የገበሬዎች ማህበርን የወረዳውን የሴቶች ማህበርን፣ የወረዳውን  የወጣቶች ማህበርን በኃላፊነት የመምራት መብትና ዕድሉ ተሰጥቶን መርተናል። በዚህ ሁሉ ከሌላው የተሻለ የዶርዜ ተወላጆች ቅድሚያ የተሰጣቸውና ተጠቃሚዎች ሆነዋል እንጂ ተጎጂዎች አይደሉም።

የዶርዜ ብሔረሰብ መብት ተሟጋቾች ነን የሚሉ ክፍሎች ግን ይህን ውክልናም ሆነ የመብት ተጠቃሚነት አይቀበሉትም። ሕዝቡ «…እነ እገሌ፣ እነ እገሌ የእኛ ልጆች አይደሉም ወይ? በዚህ ቦታ የተወከሉ፣ በዚህ ኃላፊነት የተቀመጡ፣ ይህን ወረዳ ያስተዳደሩ የእኛ ልጆች አይደሉም ወይ?...» የሚል ጥያቄ ሲነሳ የሚከራከሩትና የሚሟገቱት «እነሱ የጋሞ ብሔርን ወክለው በጋሞ ስም የተመረጡ እንጂ በዶርዜ ስም አይደለም። ዶርዜን ወክለው አይደለም…» በሚል ነው። ለፌደራል ፓርላማ፣ ለክልል ም/ቤትና ለዞን ምክር ቤት ተመራጮች የሚመረጡት በብሔር ስምና ውክልና ሳይሆን የአካባቢን የሕዝብ ብዛት መሠረት በማድረግ እንደሆነ ለሕዝቡ አይገልፁም። ለወረዳው ም/ቤት የሚወከሉ ተወካዮች የሚመረጡት ቀበሌን መሠረት ባደረገ መሆኑን እያወቁ ለሕዝቡ አያሳውቁም።

በወረዳው የፓርላማ ተወካይ ምርጫ እንደ ወረዳው ስፋት ሁሌም ከአንድ አካባቢ ላይሆን ይችላል። ለክልል ምክር ቤትና ለዞን ምክር ቤት ግን በየጊዜው የዶርዜ ተወላጆች በበቂ ሁኔታ ሲወከሉ ነው የምናውቀው። ለወረዳ ም/ቤትም እያንዳንዱ የዶርዜ ቀበሌ ከሦስት ያላነሰ ተወካይ ሲወከል ነው የማውቀው። ዶርዜ ራሱን የቻለ ብሔረሰብ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የተለየ ምን አይነት ውክልና እናገኝ ነበር? በእኔ እይታ ጭራሽ አሁን ያለውን ሰፊ የውክልና ዕድልና መብት እናጣለን ብየ አምናለሁ። ይህ ማለት አሁን ያለንን መብትና ጥቅም ማጣት ማለት ነው።

በፌደራል ፓርላማ ዶርዜ መቀመጫ ያገኛ የሚለው የማይሆን ከንቱ ቅስቀሳ ካልሆነ በስተቀር በየትኛውም መስፈርት ሊሆን የሚችል አይደለም። ምክንያቱም በጨንቻ ወረዳ ያለው የጋሞ ሕዝብ ድጋፍ ካልሰጠ ዶርዜ ለብቻው የፓርላማ መቀመጫ ምርጫ ውድድርን አሸንፎ ወንበር ለማግኘት የሚያስችል የሕዝብ ብዛት የለውም። በአናሳ ብሔረሰብ ሂሳብ አንድ የፓርላማ መቀመጫ እናገኛለን ቢባል እንኳን አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት ካልተሻሻለ በስተቀር ሊሆን የሚችል አይደለም። በፌደራል ፓርላማ ለአናሳ ብሔረሰቦች የተመደበው የፓርላማ ወንበር ተይዟል። በደቡብ ክልል መስተዳደር ምክር ቤትም ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ ህገ-መንግስቶቹ ካልተሻሻሉ አዲስ ወንበር ሊሰጥ አይችልም።

በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በደቡብ ክልል የብሄረሰቦች ምክር ቤት በብሔረሰብነት ስም አንዳንድ መቀመጫ ቢገኝ እንኳን ሁለት መቀመጫ ምናልባት የመብት ታጋይ ነን ለሚሉ ሁለት ግለሰቦች የፖለቲካ ጥቅም ካልሆነ በስተቀር ለዶርዜ ሕዝብ የሚያስገኘው ምንም አይነት የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥቅምም ሆነ የማንነት ግንባታ ፋይዳ አይኖርም። ለዚህ ማስረጃው ሻመና በምሳሌነት ያቀረባቸው እነ ግድቾ፣ ዛይሴ፣ ኦይዳ ብሔረሰቦች (ሕዝቦች) ምን የተለየ ጥቅም አገኙ? ምን ተጠቀሙ? ምን ተረፈላቸው? የሚለውን ማየት በቂ ነው። ከእነዚህ ብሔረሰቦች በፌዴሬሽን ም/ቤትና በደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት የሚወከሉ ሁለት ተወካዮች በአመት ሁለት ጊዜ ስብሰባ እየተጠሩ ይቀመጣሉ። ከዚህ ውጪ ለየብሔረሰቡ ሕዝብ ምንም ጥቅም አልተገኘም። ምንም የተረፈ ነገር የለም። ሁሉም እኛ ዶርዜዎች እንደምንኖረው ይኖራሉ። ከእኛ ከዶርዜዎች የተለየ ያገኙት ነገር የለም። ይህን ስል ግድቾ፣ ዛይሴ፣ ኦይዳ ለምን ብሔረሰብ ሆኑ እያልኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። ብሔረሰብ የሆኑት የሚገባቸው መስፈርት ታይቶና ተረጋግጦ ሊሆን ስለሚችል በዚህ ላይ ለጊዜው ክርክር የለኝም። በፀሐፊው ምሳሌ ተደርገው ስለቀረቡ ሕዝቡ የተለየ ጥቅም ምን አገኘ ነው ዓላማው።

የዶርዜ ተወላጆች በተለያየ ምክር ቤቶች በጋሞ ብሔር ስም ስለሚወከሉ ለዶርዜ መብትና ጥቅም አይቆሙም፣ ስለዶርዜ ሕዝብ መብትና ጥቅም አይከራከሩም የሚለው ቅስቀሳ መነሻና እይታም ትክክለኛ ያልሆነ ነው። ምክንያቱም ጨንቻ ወረዳን ወክሎ ለፓርላማም ሆነ ለክልል ወይም ለዞን ምክር ቤት የተመረጠ የዶርዜ ተወላጅም እንበል ሌላ መቆም ያለበት የዶርዜ ሕዝብን ጨምሮ እሱን ለወከለው ጠቅላላ ለወረዳው ሕዝብ መብትና ጥቅም ነው። ስለዚህ ጥቅሙ የሁሉም ሕዝብ ስለሆነ ልንቃወም አይገባም።

በሀገራችን ለአንድ ብሔረሰብ… ተለይቶ የሚመደብ መንግስታዊ በጀትም ሆነ የሚዋቀር መንግስታዊ የስራ መዋቅር የለም። በጀት ለፌደራል፣ ለክልል፣ ለዞን፣ ለወረዳና ለቀበሌ የስራ መዋቅሮች ይመደባል። ይህ ደግሞ አሁንም በተገቢው ሁኔታ እየተካሔደ ነው ያለው። ወደፊት ብሔረሰብ ስለሆኑ የሚመጣ ወይም የሚጨመርና የሚሻሻል በጀት የለም። ስለዚህ ሊጠቅመን የሚችለው አሁን የሚመደበው በጀት በአግባቡ በስራ ላይ እንዲውል ማድረግ ነው።

ዶርዜ የሽመናና የጥበብ ስራ ባለቤትነት መብትን በሚመለከት በአገር አቀፍና በአለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ተጠቃሚ እንሆናለን የሚለው አስተሳሰብም በተመሳሳይ ሊተገበር የማይችል ፕሮፓጋንዳ ነው። የሩቁንና በአለም አቀፍ ደረጃ ያለውን እንተውና በሀገራችን ብቻ በተለያዩ ከአራትና ከአምስት ባላነሱ ብሔረሰቦች ውስጥ በሽመና ስራ የሚተዳደሩ ማህበረሰቦች እንዳሉ ግልፅ ነው። እነዚህ የሕዝብ ክፍሎች ነገ የቀደምትነት መብት ባለቤት ማነው የሚለው ጥያቄ ቢነሳ ሁሉም እኛ ነን እንደሚሉ ጥርጥር የለም። በመሆኑም ባልተረጋገጠና ባልሆነ ተስፋ ሕዝብን መሸወድና በሕዝብ ስነ-ልቦና ከመጫወት በዘለለ ቅስቀሳው የሚያስገኝልን ፋይዳ የለም።

በአጠቃላይ ከላይ በዝርዝር በተመለከትነው ሁኔታ የዶርዜ ሕዝብ ወንድም ከሆነው የጋሞ ሕዝብ ጋር አንድ ላይ በመሆኑና በጋሞ ዴሬነት በመኖሩ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊም ሆነ በማህበራዊ  ዘርፍ ሁሉ ከሌላው የጋሞ ዴሬ ሕዝብ ጋር፣ እንዲሁም በተሻለ ተጠቃሚ ሆኗል። እጅግ የተሻለ ተሰሚነትን፣ ተቀባይነትን፣ ከብርና ሞገስን አግኝቷል እንጂ አልተጎዳም። ብቻውን ቢሆን ኖሮ መወከልና መደመጥ በማይችላቸው ቦታዎች ሁሉ ተወክሏል፣ ተደምጧል። ከጥንት ጀምሮ በአብሮነት፣ በአንድነት ሲገነባ የመጣውን ባህል፣ ወግ፣ ልማድ፣ ማንነት፣ ክብርና ታሪክ የበለጠ የሚያጠናክርበትና የሚያሳድግበትን ዕድል አግኝቷል። ስለዚህ ከጥንት እስከ ዛሬ ተያይዞ፣ አብሮ አድጎና አዳብሮ በኖረውና በመጣው አንድነትም ሆነ አሁን ባለው የአንድነት ተጨባጭ ሁኔታ ተጠቃሚዎች ነን። ወደፊትም ካለን አብሮነትና አንድነት የበለጠ ተጠቃሚ እንሆናለን እንጂ አንጎዳም።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
819 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 67 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us