“በሀገራችን ለተፈጠረው ዘርፈ ብዙ ችግር ትክክለኛ መፍትሔ ሊፈለግና ፍትሐዊ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል!!”

Friday, 08 January 2016 12:28

 

 

ከደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች አንድነት

የተሰጠ መግለጫ

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እጅግ መጠነ-ሰፊ የሆነ የድርቅ ችግር እንደተከሰተ ይታወቃል። ይህ የድርቅ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠኑ እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። በዚህ ሁኔታ ያለመሻሻል ለ8 እና ለ9 ወራት ከባሰም ለዓመት ሊዘልቅ እንደሚችል ቅድሚያ ትንበያዎች እየወጡና በሰጋትም ጭምር እየተገለፀ ይገኛል። የተከሰተው ድርቅ ነው። ድርቅን ተከትሎ የሚመጣው ርሃብ ነው። ርሃብ ደግሞ ጊዜ የሚሰጥ ሳይሆን ሕይወትን ዋጋ የሚያከፍል አደጋ ነው። በመሆኑም በዚህ ችግር ውስጥ ለወደቀችው ሀገራችንና ለሕዝቡ መፍትሄው ችግሩን የጋራ ችግር አድርጎ መቀበልና የችግሩን መጠንና ስፋት ተገንዝቦ ከወዲሁ ለመፍትሔው በጋራ መረባረብ ነው። ይሄውም ለአንድ ወቅት ወይም ለአንድ ወገን የፕሮፓጋንዳ ወይም ለፖለቲካዊ ጠቀሜታ የሚውል የቅስቀሳና የታይታ ስራ መስራት ሳይሆን እስከ መጨረሻው ድረስ ሊዘልቅ የሚችልና የሕዝብን ሕይወት መታደግ የሚችል ተግባር ሊሆን ይገባል።

ለዚህ ዓይነቱ ተግባርና ኃላፊነት ቅድሚያውን ሊወስድ የሚገባው ደግሞ አጠቃላይ የሀገሪቱን ሀብት፣ መብትና ጥቅሞችን በሙሉ ለብቻው ተቆጣጥሮ ሀገር እየገዛ ያለው ገዥው ፓርቲ ነው። ገዥው ፓርቲ ስንል በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በፌደራል ስርዓት የምትመራ እንደመሆኑ እያንዳንዱ የፌደራል ክልሎችን እየገዛ ያለውን ፓርቲም ጭምር ነው። እያንዳንዱ የፌዴራል ክልል ገዥ ፓርቲም ሆነ የፌዴራል ክልል መስተዳድሮች በየክልላቸው ለሚከሰተው መልካምም ሆነ መጥፎ ተግባርና ክስተት ውጤት በተናጥልም ሆነ በጋራ ተመስጋኝና ተጠያቂ እንደሚሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

በእንደዚህ ዓይነት ጊዜና አጋጣሚ ለተጠያቂነት ከሚያበቁ ሁኔታዎች አንዱና ዋነኛው ግልፅነትና ቁርጠኝነት ማጣት፣ የሚከሰቱ ችግሮችንና መሬት ላይ ያለውን እውነታ መሸፋፈን፣ በሕዝብ ላይ ለሚደርስ ጉዳትና ለሚፈጠር አደጋ ትኩረት አለመስጠት፣ ከሕዝብ ለሚነሳና ለሚቀርብ ማንኛውም አይነት ጥያቄ ሰላማዊና ሚዛናዊ የሆነ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኃይልና በጉልበት መንገድ ምላሽ መስጠት፣ ችግሮችን በጊዜ እየተፈቱ መፍትሄ እንዲያገኙ ከማድረግ ይልቅ ታፍነውና ተድበስብሰው እንዲቀሩ ማድረግና የመሳሰሉት ናቸው። በዚህም ላይ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች፣ የመልካም አስተዳደር መጥፋት፣ የፍትህ መጓደል፣ የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ የመዘዋወርና በፈለጉበት ቦታ ሀብትና ንብረት አፍርተው፣ ኑሮ መስርተው የመኖር መብትና ነፃነት ማጣት ሲጨመርበት ነገሮችን እጅግ ውስብስብና ጥልቅ ወደሆነ ችግር ውስጥ ይከታል።

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለው አጠቃላይ ሁኔታም ይህንን ያሳያል። በፌዴራል መንግስትም ሆነ በክልል መስተዳድሮች በኩል በሀገሪቱ የተከሰተውን አጠቃላይ የድርቅ ችግር ደረጃውን፣ ድርቁ ያስከተለውን የጉዳት መጠን እና የድርቁን ቀጣይ ሁኔታ በተመለከተ ለሕዝብ በግልፅና በአግባቡ አሳውቆ ሕዝብ በሁሉም መንገድ ራሱን እንዲያዘጋጅና ያለውንም በአግባቡ ቆጥቦና መጥኖ እንዲጠቀም ከማድረግና ከማስተማር ይልቅ ተቆጣጥረናል፣ ከአቅማችን በላይ አይደለም፣ ችግሩ ተፈቷል በሚል የመሸፋፈን ሀሳብ እየተሰጠ ይገኛል። ይህ ሁኔታ ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያለው ሕዝብም ሆነ ድርቁ ባልደረሰበት አካባቢ ያለው ሕብረተሰብ በሙሉ እንዲዘናጋና ችግሩን የቀለለ አድርጎ እንዲመለከት እያደረገ ይገኛል። በመሆኑም ይህ ከግልፅነት ማጣት ከቁርጠኝነት ጉድለት የመነጨ ችግሩን የማድበስበስና የማዘናጋት አደጋ ነው።

በዚህ በተፈጠረውና በተከሰተው ችግር ዙሪያ ሀገርና ሕዝብ በጋራ በመቆም መረዳዳት፣ ያለበት፣ ወገን ለወገኑ መድረስ ያለበት፣ ያልተጎዳው አካባቢና ሕብረተሰብ ጉዳቱ ለደረሰበት አካባቢና ሕዝብ አጋርነቱን ማሳየትና መግለፅ ያለበት ጊዜና ወቅት እና የሀገሪቱ ባለሀብቶች፣ የልማት ድርጅቶች፣ የሃይማኖትና ልዩ ልዩ ድርጅቶችና ተቋማት፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሁሉ ከሚሊኒየም ድግስም ሆነ ከህዳሴ ግድብ በላይ ለወገን ደራሽ ወገን ነው ብለው መነሳትና መዘመር ያለባቸው ጊዜ አሁን ሆኖ እያለ ዝምታን በመምረጥ ከዳር ሆነው እንዲታዘቡ ሆኗል። ለዚህ ዓይነቱ መልካምና በጎ አድራጎት ተግባርም ቢሆን የመንግስትንና የገዥውን ፓርቲ የይሁንታ ፈቃድ ሳያገኙ መንቀሳቀስ የማይቻል መሆኑ እየታወቀ መንግስትና ገዥው ፓርቲ ለዚህ አይነቱ ተግባር ሕዝብን ለማንቀሳቀስ ቁርጠኝነትና ወኔ ማጣታቸው ሌላው ትልቅ ስህተትና ችግር ነው።

በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ሕዝብ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ፣ የዴሞክራሲ ጥያቄን ከማንሳት አልፎ የአትዝረፉን፣ አትግፉን፣ አትጨቁኑን፣ አታንገላቱን፣ አትከፋፋፍሉን በማለት ተቃውሞን እያቀረበ ይገኛል። ሰሞኑን በአብዛኛው በኦሮሚያ አካባቢ፣ በከፊል የአማራ ክልል የተነሳውና የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ እና በአንዳንድ የደቡብ አካባቢዎች እየተነሳ ያለው የሕዝብ ጥያቄ የዚሁ እውነታ ገላጭ ነው። እነዚህ ጥያቄዎችን በዴሞክራሲያዊ አግባብ ከመመለስና ከመፍታት ይልቅ በኃይል በማፈን ለማስቀረት እየተወሰደ ያለው እርምጃ፣ ለተቃውሞ አደባባይ የወጣውን ዜጋ ሕይወት ማጥፋት፣ ደም ማፍሰስ፣ አካል ማጉደል ከአንድ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጫለሁ ከሚል መንግስት የማይጠበቅ ሌላው አስከፊ ስህተትና ወንጀልም ጭምር ነው።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የድንበር ማካለል ስራ ለማከናወን ሁለቱ መንግስታት ከጫፍ ላይ ደርሰው ባሉበትና በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ ከወትሮው የተለየ እንቅስቃሴና ውጥረት በነገሰበት ሁኔታ ላይ ሆነን መንግስት ስለሁኔታው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልፅ መረጃ ለመስጠት አልቻለም። ይህም ከመንግስትና ከገዥው ፓርቲ የማይጠበቅ ተግባር ከመሆኑም በላይ የግልፅነት፣ የቁርጠኝነትና የታማኝነት ማጣት ችግር አንዱና ዋነኛ ማሳያ ነው። ስለዚህ፡-

1.  በሀገሪቱ የተከሰተው የድርቅ ችግር በሁሉም አካባቢ ከአቅም በላይ ሆኖ የከፋ አደጋ ከማድረሱ በፊት መንግስት በግልፅነትና በቁርጠኝነት ዘላቂ የሆነ መፍትሄ እንዲፈልግና ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ የማቋቋም ስራ እንዲሰራ፤

2.  የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግሩ የጋራ መሆኑን ተገንዝቦ እርስ በእርሱ እንዲረዳዳና እንዲደጋገፍ ለማድረግ የማያስችል የብሔራዊ ንቅናቄ መድረክ እንዲፈጠርና ለመድረኩ መፈጠር ቅድመ ሁኔታዎችን በማመቻቸትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣

3.  በአየካባቢው የሚነሳውን የሕዝብ ጥያቄና ተቃውሞ መንግስት በኃይል ከማፈንና በጥቃት ከማስቆም ይልቅ በሆደ ሰፊነትና በፍትሃዊ መንገድ እንዲያዳምጥና በዴሞክራሲያዊ አግባብ እንዲፈታ፣

4.  በሁሉም ደረጃ ያሉ የመንግስት የታጠቁ ኃይሎች የመብት ጥያቄ በሚያነሱ ዜጎችና የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚተኩሱትን እንዲያቆሙ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራና በሌሎችም የሀገሪቱ ክልሎች በታጠቁ የመንግስት ኃይሎች አማካይነት በሕይወት በአካልና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት መጠን በአስቸኳይ እንዲጣራና ጉዳት አድራሾችም ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲደረግ፣

5.  በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ስለሚካሄደው የድንበር ማካለል ጉዳይ፣ በአሁኑ ወቅት የድንበሩ መካለል ለሀገራችን የሚያስገኘውን ፋይዳ፣ ባለመካለሉ ሀገራችን ልታጣ የምትችለው ጥቅም ወይም ሊመጣ የሚችል ጉዳት ምን እንደሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ጉዳዩ ያገባናል ለሚሉ ወገኖች ሁሉ መንግስት ግልፅ ማብራሪያና መረጃ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን

 

የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች አንድነት /ደኢዴኃአ/

የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ታህሳስ 21 ቀን 2008 ዓ.ም

አዲስ አበባ¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
464 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 134 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us