ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን በማሰርና በማንገላታት የኦሮሞ ሕዝብ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግልን መግታት አይቻልም!!

Wednesday, 13 January 2016 14:45

 

 

(ከመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ጉዳይ መምሪያ)

 

የኢህአዴግ አገዛዝ አምባገነናዊ ባሕሪውን ለመሸፋፈን ለፕሮፓጋንዳ ያህል  እየተጠቀመባቸው ቢሆንም ሰላማዊ የመቃወምና በነፃ የመደራጀት መብቶች በሀገራችን ሕገመንግሥት በአግባቡ ተደንግገው ይገኛሉ። ይሁን እንጂ አገዛዙ ከፀረ-ዴሞክራሲያዊ ባሕሪው የተነሳ በተግባር ሊያውላቸው፣ ሊያከብራቸውና ሊያስከብራቸው ፈቃደኛ ሆኖ አልተገኘም። ስለዚህም እነዚህን መብቶች ለመጠቀም የሚሞክሩትን ሰላማዊና ሕጋዊ የሕዝቦችን የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በሰበብ አስባቡ ከማፈን አልፎ በአገዛዙ ብልሹ አስተዳደር ምክንያት የተማረሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚያነሱትን ሕጋዊና ሰላማዊ ተቃውሞዎችን በተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት እንደተቀሰቀሱ በመቁጠር የአፈና እርምጃውን ብሶቱን በሚያሰማው ሕብረተሰብ ላይ ብቻ ሳይሆን በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይም ጣቱን በመቀሰርና በመወንጀል ለእስራትና ለተለያዩ እንግልቶች እየዳረጋቸው ይገኛል።
ይኼው የኢህአዴግ የተሳሳተና የአምባገነናዊ ባሕሪው መገለጫ የሆነው አካሄድ ባለፉት ሁለት ወራት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሕዝብ ላነሳው ሕገመንግሥታዊ የመብት ጥያቄም በአምባገነኖች እንደመፍትሔ እርምጃ ተወስዶ በርካታ የኦፌኮና የመድረክ አባላት የሆኑ  ሰላማዊ ተቃዋሚዎችንና ሌሎችንም ዜጎች በገፍ በማሰርና በማንገላታት ሥራ ላይ እየዋለ ይገኛል። እውነቱ ግን ይህ የኦሮሞ ሕዝብ ታሪካዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተነሳው መንግሥትን የሚቃወሙ የተወሰኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ስለቀሰቀሱ ሳይሆን የሕዝቡ መሠረታዊ መብቶችና ጥቅሞች በአምባገነን ገዢዎች ሲጣሱና ሲረገጡ በመቆየታቸው ነው። ሁሉም እንደሚያውቀው ይህ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል የተነሳው በድንገትም አይደለም።  ይልቁንም ትግሉ የተቀሰቀሰው በሕገመንግሥቱ በግልጽ የተረጋገጡት በፌደራላዊ ሥርዓት መሠረት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በነፃነት እራስን በራስ የማስተዳደር መብት በኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አምባገነናዊ አሠራርና በተጭበረበረ ምርጫ ታፍኖ በሥራ ላይ ሳይውል ላለፉት 21 ዓመታት በመቆየቱ ነው። በተለይም የሀገራችን ዋና ከተማ በኦሮሚያ ክልል መሀከል የሚትገኝ በመሆኑዋ ምክንያት ክልሉ ከከተማዋ በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ በአገልግሎት አቅርቦትና ከአስተዳደር ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መብቱ ይጠበቅለታል፣ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ሕግ ይወጣል፣ ተብሎ የተደነገገውን ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ በተግባር እንዲውል በተደጋጋሚ በሰላማዊ አግባብ ሲጠይቅ ቆይቶ ሰሚ በማጣቱ የተነሳ ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ነው። ከዚህም ሌላ የአገዛዙ የተከማቹና ተደራራቢ የሆኑ ብልሹ የአስተዳደር ችግሮች የሕዝቡን ትዕግስት ማስጨረሱ ለሕዝባዊው የተቃውሞ ትግል ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። የኢህአዴግ አገዛዝ ለዚህ የኦሮሞ ሕዝብ ሰላማዊና ሕጋዊ ጥያቄ ወቅታዊ ምላሽ በመንፈጉ በራሱ ድክመት የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ትግል ጥቅት ግለሰቦች ወይም የኦፌኮ/መድረክ አባላት ወይም ሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ እንደቀሰቀሰ በማስመሰል የሚያሰራጨው ፕሮፓጋንዳ ከአምባገነኖች የእራስን ድክመት ዞር ብሎ ለማየት ያለመቻልና በሌሎች ላይ የማላከክ አባዜ የመነጨ ነው።
የኢህአዴግ አገዛዝ ሰሞኑን ያሰራቸው የኦፌኮና የመድረክ የአመራር አባላት ማለትም፡-
1ኛ፡- አቶ በቀለ ገርባ የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር፣
2ኛ፡- አቶ በቀለ ነጋ የኦፌኮ ዋና ጸሐፊና የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፤ (በቁም አሥር ላይ የሚገኙ)
3ኛ፡- አቶ ደጀነ ጣፋ የኦፌኮ ም/ዋና ጸሐፊ፣
4ኛ፡- አቶ ደስታ ድንቃ የመድረክና የኦፌኮ የወጣቶች ሊግ ሊቀመንበርና የኦፌኮ የኦዲት  ኮሚቴ አባል፣
5ኛ፡- አቶ ጉርሜሳ አያኖ የኦፌኮ የወጣቶች ሊግ ም/ሊቀመንበርና የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ኮሚቴ አባል፣
6ኛ፡- አቶ አዲሱ ቡላላ የኦፌኮ ወጣቶች ሊግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣
7ኛ፡- አቶ ደረጀ መርጋ የኦፌኮ የወጣቶች ሊግ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣
8ኛ፡- አቶ ዓለሙ አብዲሳ የኦፌኮ ወጣቶች ሊግ ዋና ጸሐፊ፣
9ኛ፡- አቶ ጣሕር -------- የኦፌኮ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣
10ኛ፡- አቶ እስማኤል ----- በኢሉባቦር ዞን የዳርሞ ወረዳ የኦፌኮ ተጠሪ እና ሌሎችም በርካታ የኦፌኮ/መድረክ አባላትና በሰላማዊ ትግሉ በመሳተፋቸው ከመቶ በላይ የተገደሉትና በሺዎች የታሰሩት ወገኖቻችን ጥያቄዎቻቸውና ትግላቸው ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌን መሠረት ያደረገና በሰላማዊ አግባብ የተጀመረ መሆኑን እኛ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳንሆን መላው ዓለምም የሚያውቀው እውነት ነው።
በተለይም ኦፌኮና መድረክ በተለያዩ ወቅቶች በጻፉዋቸው ደብዳቤዎችና ባወጡዋቸው መግለጫዎች ጉዳዩ ወደ አስከፊ ሁኔታ ከመድረሱ በፊት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ለዚህ ሕገመንግሥታዊ የሕዝብ ጥያቄ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ ጋር በመወያየት ወቅታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ሲጠይቁ ቆይተዋል። ኢህአዴግ ይህንን ሰላማዊና ሕጋዊ የመብት ጥያቄዎችን ሕገመንግሥቱ ከጸደቀ በኋላ ባሉት 21 ዓመታት አፍኖ ይዞ ሳይመልስ መቆየቱ ብቻ ኃላፊነት የሚሰማውና ኃላፊነትን መውሰድ የሚያውቅ ድርጅት ቢሆን ኖሮ ራሱን ተጠያቂ አድርጎ ከሥልጣኑ እንዲወርድ ሊያደርገው በቻለ ነበር። በተቀራኒው ግን ሥራውን በሕጉ አግባቢ እንዲሠራና በሕዝቡ የመብት ጥያቄ ላይ እየፈጸመ ያለውን አፈና እንዲያቆም የጠየቁትን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ለመብቱ የሚታገለውን ሕዝብ በማሰር በመግደልና በማሰቃየት አፍኖ በመግዛት አምባገነናዊ እርምጃውን ቀጥሎበታል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ይህ የኢህአዴግ የተሳሳተ አምባገነናዊ አካሄድ የሕዝቡን ትክክለኛና ሕጋዊ ትግል በፍጽም ሊገታው የማይችል መሆኑንና በአስቸኳይ የኃይል እርምጃው ቆሞ ሰላማዊና ሕጋዊ መፍትሔ ካልተሰጠው ይበልጥ እየተወሳሰበ ሀገራችንንም ለአስቸጋሪ ሁኔታ ሊዳርጋት እንደሚችል ይገነዘባል። ስለዚህም መድረክና ኦፌኮ በተደጋጋሚ ባወጡዋቸው መግለጫዎች በጠየቁት መሠረት፡-
1ኛ፡- የሕዝቡ ሰላማዊ ጥያቄዎች በሚነሱባቸው አከባቢዎች ጥያቄዎቹን በኃይል ለማፈን ተሰማርቶ የሚገኘው የጸጥታ ኃይል እየፈጸማቸው የሚገኙት የግዲያ፣ የእስራትና የማንገላታት እርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣
2ኛ፡- በዚሁ ሰላማዊ የሕዝብ ትግል ምክንያት ሕዝቡን ቀስቅሳችኋል በምል ሰበብ ለእስራት የተዳረጉት ከዚህ በላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም የኦፌኮ/መድረክ አባላትና በሰላማዊ ትግሉ በመሳተፉቸው ምክንያት ለእስራት የተዳረጉት ዜጎቻችን በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣
3ኛ፡- በሰላማዊ የመብት ጥያቄ በመሳተፋቸው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ወገኖቻችን ቤተሰቦች ተገቢው ካሳ በመንግሥት እንዲከፈላቸው፣
4ኛ፡- በሰላማዊ ዜጎች ላይ የግዲያና የማንገላታት ተግባራትን የፈጸሙ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ፤
5ኛ፡- ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መንግሥት ከኦፌኮ/ መድረክና ከሌሎችም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ካለአንዳች ቅድመሁኔታ በመወያየትና በመደራደር ለሕዝቡ ፍትሀዊና ሕጋዊ ጥያቄ በአስቸኳይ ሕገመንግሥታዊ ምላሽ መስጠት ጊዜ ሳይሰጠው ተግባራዊ መሆን የሚገባቸውና አማራጭ የሌላቸው የችግሩ መፍትሔዎች ስለሆኑ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረጉ አጥብቀን እንጠይቃለን። ተመሳሳይ ጭቆናና አፈና እየተፈጸመበት የሚገኘው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ወንድሙ የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ባነሳቸው ሕጋዊ ጥያቄዎች ምክንያት እየተፈጸመበት ያለውን ግፍና በደል ሊያወግዘውና የትግል አጋርነቱን ሊያረጋግጥለት ይገባል እንላላን።

                                              ድል ለሕዝባዊ ትግላችን!!
                                         የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ጉዳይ መምሪያ
                                                  ታህሳስ 30 ቀን 2008 ዓ ም
                                                               አዲስ አበባn

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
515 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 104 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us