“ድርቁ የኢህአዴግ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤት ነው!” ኢዴፓ

Friday, 22 January 2016 13:04

 

ሀገራችን ኢትዮጵያና ህዝቧ ለብዙ ዘመናት ድርቅና ርሃብ መገለጫቸው ሆኖ በዓለም ፊት ዘወትር ለምፅዋት መቆም አሳፋሪ የታሪካችን አንዱ አካል እንደነበር ይታወቃል። ይሄ የሀገራችንና የህዝባችን መገለጫ ሆኖ የቆየው ድርቅና ርሃብ በዚህ ትውለድም መቆም አለመቻሉ ኢዴፓን ያሳስበዋል ያስጨንቀዋል። ኢህአዴግም ላለፉት 25 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆየ ቢሆንም፣ በተጨማሪም ለግብርናው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቻለሁ ቢልም አገሪቱን ከድርቅ ብሎም ከረሃብ ለማላቀቅ የተለየ ነገር ሊፈይድ አልቻለም። ይህም ኢህአዴግ የሚከተለው ፖሊሲ አርሶ አደሩን ለተደጋጋሚ ድርቅ በማጋለጥ በየጊዜው ውድ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል። በዘንድሮው ድርቅ ዙሪያ የሚወጡ መረጃዎችን በጥልቀት ሲመረምር የቆየው የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚወጡት መረጃዎች አጥጋቢ ሆነው ለህዝቡ ተገቢ መረጃ ሊሰጡ እነደማይችሉ በመረዳቱ ከፍተኛ አመራሮቹን ድርቁ ወደተከሰተባቸው ቦታዎች ላይ የመስክ ጥናት አድርገው እንዲመጡ ለሚመለከተው አካል አስፈላጊ ትብብር ለአመራሮቹ እንዲደረግለት በደብዳቤ ቢጠይቅም ተገቢ ምላሽ ለማግኘት ሳይችል ቀርቷል። አመራሩም የጉዳዩን አስፈላጊነት ከምንም በላይ ያምን ስለነበረ ሰፊ ቦታዎችን ለመሸፈንና ጥልቅና ሰፊ ጥናት በአቅም ውስንነት ለማድረግ ባይችልም በድርቁ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባሉትን የራያና ዘቦ አካባቢዎች ላይ ሁለት የዳሰሳ ጥናት የሚያደርጉ ከፍተኛ አመራሮቹን በመላክ ሁኔታውን ለማየት ሞክሯል። በደረሰውም ሪፖርት መሰረት የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አሁን ያለውን የድርቅ ሁኔታ ገምግሞ ከዚህ የሚከተሉትን አቋሞች ይዟል፤

1ኛ. ቡድኑ በእነዚህ ቦታዎች ላይ ባደረገው የመስክ ጉብኝት በእንስሳትና በከብቱ ላይ፣ በመሬቱና በአካባቢው ያሉ ወንዞች ላይ በተጨባጭ የሚታየውና የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑ ገበሬዎችን አነጋግሮ እንዳረጋገጠው መንግሰት ድርቁን ለመቆጣጠር እርዳታ እየሰጠ ቢሆንም፤ አሁን ካለው ፍጥነት የበለጠ መፍጠን ካልቻለ በሚቀጥሉት ወራቶች ድርቁ በሰውና በእንስሳት ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ እንደሚጀምርና የድርቁ ተጽዕኖ ወደ ከተሞችም ሊዛመት እንደሚችል ኢዴፓ ያለውን ስጋት ይገልፃል።

2ኛ. አሁን ያለው የእርዳታ አሰጣጥ ከአድሎና ከወገንተኝነት በፀዳ መልኩ እየተካሄደ ያለመሆኑና ለአንድ ቤተሰብም በነፍስ ወከፍ የሚሰጠው መጠን እጅግ በጣም አንስተኛ በመሆኑ መንግስት ስርጭቱ በተገቢው መንገድ ለመዳረሱ ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግና የሚሰጠውን የእርዳታ መጠን መጨመር እንዳለበት፣

3ኛ. ኢዴፓ ላለፉት ረጅም ዓመታት ባገኛቸው መድረኮች ሁሉ የኢህአዴግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መዋቅራዊ ሽግግር ማድረግ እንዳለበት ሲወተውት ቆይቷል። ኢህአዴግ በኢኮኖሚው ላይ መዋቅራዊ ሽግግር ማድረግ ካልቻለና ግብርናውንም ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ ካልቻለ የሚመፃደቅበት የኢኮኖሚ እድገት በአንድ የመኸር ወቅት ዝናብ መቅረት ቀጥ እንደሚልና አሁንም እየታየ ያለው አንፃራዊ የኢኮኖሚ እድገት አደጋ ውስጥ ሊወድቅ የሚችል እንጂ የሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትክክለኛነት መገለጫዎች እንዳልሆኑ ሲተችና አማራጭ የሚለውን ሀሳቦች ሲያቀርብ ቆይቷል። አሁንም ጊዜው ሳይረፍድ ኢኮኖሚው ላይ መዋቅራዊ ሽግግር በማድረግ ከሌሎች ዘርፎች ማለትም ከኢንዱስትሪውና ከአገልግሎት ዘርፉ ጋር እርስ በርስ ተመጋግቦ የሚሄድ መዋቅራዊ ሽግግር ኢኮኖሚው ማድረግ ካልቻለ፣ ግብርናውንም ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ገበሬው የዝናብ ጥገኛ ሳይሆን በመስኖ ተጠቃሚ እንዲሆን ካልተደረገ፣ ገበሬው ከአነስተኛ ማሳ በቂ ምርት ሊያገኝ እንደማይችል በመረዳት ዘመናዊና ሰፋፊ እርሻዎችን ለማስፋፋት በሚያስችል የግብርና ስርዓት ውስጥ ግብርናው መግባት ካልቻለና ገበሬውን የመሬት ባለቤት ማድረግ ካልተቻለ ወደፊትም ከዚህ የባሰ የድርቅና የርሃብ አደጋ ማስተናገዳችን እንደማይቀር ኢዴፓ ያሳስባል።

4ኛ. የእርዳታ ሰጭዎችም ሆኑ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም በድርቅ ለተጐዱ ዜጐች እያደረጉ ያሉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ እየጠየቅን ከድርቁ አካባቢ ውጪ ያለው የህብረተሰብ ክፍልም ለተጐጂዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታ መንግስት እንዲፈጥር እንጠይቃለን።

የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

                                                    ጥር 5 ቀን 2008 ዓ.ም

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
580 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 108 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us