የ“ሀጥሼ!”ን ተረት ለመተግበር አንሩጥ!!

Friday, 22 January 2016 13:06

 

 

ሀጥሼ! ማለት ማስነጠስ ነው።በባህላችን አንድ ሰው ሲያስነጥሰው እንደየፆታውና እድሜው ይመረቃል። አዋቂ ወንድ ሲያስነጥሰው “ዎዻ” ጀግና ሁን፣ ጠላት ገዳይ ሁን፣ “አልኦ ኤካ” ክበር፣ የሚልና የመሳሰሉት ምርቃት ይመረቃል። አዋቂ (ያገባች) ሴት ሲያስነጥሳት “አዴ የላ፣ ኦርዛማ” ወንድ ውለጂ፣ ትልቅ ሁኚ፣ ሃብታም ሁኚ…ወዘተ ምርቃት ትመረቃለች። ያስነጠሰው በእድሜ ልጅ ከሆነ/ከሆነች “ዲጫ” እደግ/እዴጊ የሚል ምርቃት ይመረቃሉ። ይህን ምርቃት ባስነጠሰው ሰው አከባቢ ያለ ሰው ማንም ቢሆን መመረቅ ይችላል። ለምርቃቱ ባስነጠሰው ሰው አካባቢ መኖር እንጂ ሌላ መስፈርት የለውም። ነገር ግን ይህን ለስንት ቀና ምርቃትና መልካም ምኞት የሚውለውን ማስነጠስና ምርቃቱን ተንኮልና ሴራ የሚያስቡ ሰዎች ለተንኮልና ለሴራቸው መሳካት ይገለገሉበታል።

ይሔውም በአንድ ምሳሌ ላስረዳ፡- አምስት ሌቦች ሆነው ለሊት በጨለማ የአንድን ሰው ቤት ይዘርፋሉ። ዘርፈው ሊወጡ ሲሉ ባለቤቱ ከተኛበት ስለነቃ የያዙትን ይዘው ሲጣደፉ አንደኛው ከበር መውጫ ጉበን ጋር አናቱ ይላተምና ራሱን ስቶ ይወድቃል። በዚህም የተዘረፈው ቤት ባለቤቶች ተረባርበው ይይዙታል። ለጊዜው ዘርፈው ያመለጡት አራቱ ብቻ ይሆናሉ። እነዚህ አራቱ እንዳይያዙ በጨለማው ሲሸሹ አንደኛው አደናቅፎት ገደል ውስጥ ይወድና አንድ እግሩ ይሰበራል። የቀሩት ሶስቱ ገደል ውስጥ ወድቆ እግሩ የተሰበረው ባልደረባቸው የያዘውን ንብረት ተባብረው ያወጡና እሱን በወደቀበት ገደል ውስጥ ጥለውት ይሔዳሉ።

አሁን የቀሩት ሶስት ናቸው። ሶስቱም ተያይዘው እየሸሹ ከአሁን አሁን ከአንድ አንዳቸው ወድቀው፣ ተሰብረው ወይም አንድ ነገር ሆነው እንደሚቀሩ በልባቸው ሲያስቡና ሲጠባበቁ ለሊቱ ይነጋና አንድ ጫካ ውስጥ ገብተው ይደበቃሉ። በተደበቁበት ጫካ ውስጥ ሆነው በየልባቸው ስለዘረፉት ንብረትና ስለሚደርሳቸው ድርሻ እያሰቡ እያለ ከመሀላቸው አንደኛውን ያስነጥሰዋል። ሀጥሼ! ይላል። በዚህን ጊዜ ከአጠገቡ ያለው ባልደረባው ሌባ ሀንፌ ጉፆርኮና ይላል።  “ሀንፌ ጉፆርኮና” ማለት “ከዚህችም ባነስንና” ማለት ነው። ይሔውም ከላይ እንዳየነው ለመልካም ነገር፣ ለመልካም ምኞትና ለመልካም ምርቃት ይውል የነበረው ማስነጠስ ወደሌቦች መንደር ሲመጣ ከግል ጥቅማቸው አንፃር በማየትና የዘረፉትን ንብረት ለሶስት ሆነው ከሚከፋፈሉ ለሁለት ሆነው ቢከፋፈሉ የተሻለ እንደሚደርሳቸው ስላሰቡ “ከዚህችም ባነስንና” ብለው ምርቃቱን ወደ እርግማን ቀየሩት። ከመብዛትና ከማደግ አብልጠው ማነስንና መጥፋትን ተመኙት። ይህ እንግዲህ የሴራ አስተሳሰብና የግል ጥቅም እይታ ውጤት ነው። ለመግቢያ ያህል ይህን የሀጥሼን ተረት ከገለፅኩ ወደ ዋናው ሀሳቤ ልመለስ።

ለዚህ ፅሁፌ መነሻ የሆኑኝ እጅግ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩኝም በዋናነት ግን ታደለ ቱፋ በተባለ ሰው “ማዶላ” በሚል ሲያሜ የተፃፈ መጽሀፍ ላይ ስለ ጋሞ ብሔር የተፃፈው የተሳሳተ ጽሁፍ እና በተለያዩ ግለሰቦች አማካይነት በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ ስለዶርዜ ሕዝብ በተደጋጋሚ የወጡ ጽሁፎች ናቸው። በተለይም በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ ከወጡ ጽሁፎች ውስጥ በቆንጆ መጽሔትና በሰንደቅ ጋዜጣ የወጡ የተለያዩ ይዘትና መልእክት የነበራቸው ጽሁፎችና መግለጫዎችን መጥቀስ ይቻላል። ከቅርብ ጊዜዲህ ደግሞ በሰንደቅ ጋዜጣ ሲወጡ የነበሩ ጽሁፎችም ለዚህ ጽሁፌ ምክንያቶች ናቸው። በእነዚህ ጽሁፎች ውስጥ አንዳንድ ፀሀፊዎች የጋሞ ሕዝብን እርስ በርሱ ለያይተውና ገነጣጥለው ለማሳየት ሞክሯል። ሲመቻቸው ደግሞ ሲሰድቡና እንዲህ የሚባል ሕዝብ፣ ብሔር፣ ቀበሌ የለም እስከ ማለት ደርሰዋል። በጣም ዋልጌ የሆኑት ደግሞ ብሔሩን በድጋፍና በእርዳታ ተሰብስቦ የተቋቋመ ብሔር እስከ ማለት ድረስ ደርሰዋል።

አንዳንዶቹ በጽሁፋቸው ስለዶርዜ ሕዝብ ማንነት ለማሳየት የሚሞክሩ እየመሰሉ ነገር ግን በሕዝቡ መሀከል ተገቢ ያልሆነ ግጭትና ፀብ እስከ መኮርኮር ድረስ እየሔዱ ነው። የተወሰኑት ደግሞ እውነታውን ከማሳየት ይልቅ በፈጠራና በውሸት የተጀቦኑ ሃሣቦችን ይዘው ሲፅፉ ይታያሉ። ይህን ስል ከዚህ በፊት በወጡ ጽሁፎች ውስጥ እውነትን የተመረኮዙ የሉም እያልኩ አይደለም። የሕዝቡን ነባራዊ እውነታ ለማሳየት የሞከሩ መኖራቸውም ሳይዘነጋ ማለት ነው።

በአንድ ነገር ላይ ከእውነት በራቀና በተዛባ መንገድ የሚፃፉ ክፍሎችን በተመለከተ ለምን ብሎ መጠየቅና መጠርጠር፣ ከፍ ሲልም መተቸትና እውነታውን እያሳዩ ማጋለጥ መብት ቢሆንም ሁሉም ይህን መብት በአንድ ጊዜ ተነስቶ ሊጠቀም እንደማይችል ይታወቃል። ሁኔታው የተሰማቸውና የሚሰማቸው ካሉ እንደየስሜታቸውና እንደየተሰማቸው ሁኔታ ሃሳባቸውን እስከሚገልፁ ድረስ እኔ የተሰማኝን ሀሳብ ገልጨ ማለፍ ፈልጌያለሁ። ይሔውም ቀደም ሲል በወጡ ጽሁፎችና በነበረው እውነታ ላይ ተመርኩዤ ጥቂት ሃሣብ ቢሰጥ ስለእውነታው ከእኔ የበለጠ የሚያውቁና የጠለቀ ግንዛቤ ያላቸው የተሻለ ሀሣብ ሊያክሉበት ይችላሉና ነው።

እዚህ ላይ የዛሬው ጽሁፌ ዋና ዓላማ የየትኛውንም ወገን ሀሳብ ወይም ከዚህ በፊት የተፃፉትን ቃል በቃል ወይም ቀንና ቁጥር እየጠቀስኩ መኮነን ወይም መተቸት አይደለም። ዓላማዬ የጋሞ በሉት የዶርዜ ህዝብን አጠቃላይ ነባርና ተጨባጭ እውነታውን እኔ የማውቀውንና በተጨማሪም ከብሔሩ አካባቢያዊ (ደሬዎችና) ከታላላቅ አባቶች ያገኘሁትን መረጃ መሰረት አድርጌ ለሌላው ለጉዳዩ እሩቅ ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብና ለመገናኛ ብዙሃን ትክክለኛውን ነገር ማሳየትና ማካፈል ብቻ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ስለጋሞ ብሔር ሃቁን ደብቀው፣ እውነቱን ክደው፣ በመሰላቸው መንገድ የሚጽፉ ወገኖች ምን እየሰሩ እንደሆነ እራሳቸውን ዞር ብለው እንዲመለከቱ የሚያደርግ ሃሳብ መስጠት ነው። ከዚያም ማመዛዘኑንና ፍርዱን ለሕዝብ እንተዋለን።

ነገር ግን ከሁሉም በፊት በሕዝብ መካከል ተገቢ ያልሆነ ውዝግብ የመፍጠር አዝማሚያ ይዘው የሚፅፉት ወገኖች ሁሉ ይህ ነገር አድሮ ውሎ ወንድማማችና አንድ በሆነው ሕዝብ መካከል ሊያስከትል የሚችለውን አደገኛ ውጤት እያሰቡ ቢጽፉ ጥሩ ነው እላለሁ። በጋዜጣ፣ በመጽሔት፣ በኢንተርነትም ሆነ በፌስቡክ የምንጽፍ ሰዎች እኔ ምን ቸገረኝ በወጣ ያውጣው በሚል ግድየለሽነት የምንፅፋቸው ነገሮች በእህትና በወንድም፣ በታላቅና በታናሽ መካከል ሊፈጥር የሚችለውን የነገውን አደጋ ትንሽም ቢሆን ቆም ብለንና ደጋግመን ብናስብበት የተሻለ ይሆናል የሚል ሃሣብ አለኝ።

ይህን ስል ሰዎች በጋዜጣ ላይ ጹሁፍ ለምን ይፅፋሉ ማለት አይቻልም። ምክንያቱም መፃፍ መብት ስለሆነና መብትን መጠቀም በራሱ መብት ስለሆነ። እንደዚሁም መፃፍ በራሱ የመናገርና ሀሣብን በነፃ የመግለፅ ዲሞክራሲያዊ መብት አካል ስለሆነ ነው። ስለዚህ መፃፍ እንችላለን። መብት አለን። ምናልባት የምንፅፈውን ነገር የፕሬስ ሕጉ እስካልገደበንና እስካልወነጀለን ድረስ፣ የሌላውን መብትና ነፃነት ያለአግባብ እስካልነካን ድረስ፣ የምንጽፈው ለባህል፣ ለእውነት፣ ለሞራልና ለህሊና ተቃራኒ እስካልሆነ ድረስ በአግባቡ መፃፍ እንችላለን። ብንፅፍም ጥሩ ይሆናል።

እዚህ ላይ ወደ ዋናው ሀሳቤ ስገባ በመጀመሪያ በማዶላ መጽሀፍ ውስጥ “ጋሞ ብሔር አይደለም፣ ጋሞ የሚባል ሀገርም የለም፣ ጋሞ ሕዝብ ካኦ የለውም” ስለተባለው በጥቂቱ እንመልከት። ጋሞ የራሱ ሀገር ያለው ብሔር ስለመሆኑ ምንም ክርክርና ንትርክ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም። ምክንያቱም የብሔሩ መሰረት በሆነው በደቡብ ክልል ካሉት 56 ብሔሮች ውስጥ በሕዝብ ብዛት 4ኛውን ደረጃ የያዘ፣ በቀድሞ መንግስታት ዘመን በራሱ ጠ/ግዛትና ክ/ሀገር ሆኖ የታወቀ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ ከ250 እስከ 300 ሺህ የሚደርስ ሕዝብ እንዳለው የታወቀውን ብሔር የለም ብሎ መፃፍ ከጭፍን ጥላቻ አመለካከት የመነጨ ችግር ሊሆን ከሚችል በስተቀር ሌላ ሊሆን አይችልም። እንዲሁም “ጋሞ” የሚባል ሀገር የለም ብሎ መፃፍም በቂመኝነት አስተሳሰብ ተነሳስቶ ተሳድቤ ይውጣልኝ በማለት፣ አሊያም እድሜዬንና ዘመኔን አንድ የሚረባ ነገር ሳልሰራ ጨርሻለሁና አንድ የሚያወዛግብ ነገር ጽፌ በዚህም ልታወቅ ከሚል ከንቱ አስተሳሰብ የመነጨ አፃፃፍ ካልሆነ በስተቀር ትርጉም ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደለም።

ጋሞ የሚባል ሀገር ከሌለ ጋሞጎፋ ጠቅላይ ግዛት የሚል ስያሜ ባልኖረ፣ ጋሞ የሚባል ሀገር ከሌለ ጋሞጎፋ የሚባል ክፍለ ሀገር ባለተሰየመ፣ ጋሞ የሚባል ሀገር ከሌለ ጋሞጎፋ ዞን የሚባል ሲያሜ ባልተሰጠ ነበር። ጋሞ የሚባል ብሔርና ሕዝብ ከሌለ ደግሞ በስሙ የሚጠሩ ጠ/ግዛት፣ ክ/ሀገር፣ ዞን ባልኖረ ነበር። ከዚህም በላይ የማዶላ ፀሀፊ በአንድ ቦታ ሳት ብሎአቸው በገጽ 69 ላይ የምንሊክ ጦር ሻለቃ ሕዝቡን ይሔ ምንድነው? ብሎ ሲጠይቅ የጋሞ ካኦ” የአንበሳው ንጉስ ብለው እንደመለሱለት ይገልፃል። በዚያውም ይቀጥልና ጋሞ የሚባል አገር የለም የሚለውን መልሶ አፍርሶ…ወደ ዛላ ሲሻገር ጋሞና አማዶ ዛላ ስለሚባል፣ ማዜንም ሲሻገር በአንበሳው ንጉስ በዴሙሳ ሰዎች ስለሚያመልኩ …በማለት ጋሞ የሚባል ሀገር መኖሩንና በዚያውም በራሱ ንጉስ የሚያመልክ ሕዝብ እንዳለ ያረጋግጣል። በመሆኑም ፀሀፊው ጋሞ የሚባል ሀገርም ሆነ ብሔር የለም ብሎ የተነሳው ከእውነት ሳይሆን ከተሳሳተ መነሻ በመሆኑና ድብቅ ዓላማ ሌላ በመሆኑ አካሔዱም ሆነ አፃፃፉ በራሱ ጊዜ ተመልሶ ከሸፈበት።

ጋሞ የሚባል ሀገር ስለመኖሩና ጋሞ ሀገር ያለው ሕዝብ ስለመሆኑ ምንም አያከራክርም ብያለሁ። ነገር ግን በራሳችን በጋሞዎች ችግር ይሁን ወይም በሌላ ወገን ተፅዕኖ ብዙም ሊታወቅ ስላልቻለውና ተቀብሮ ስለቀረው ስለጋሞ «ካኦ» ንጉስ በጥቂቱ እንመልከት።

በጋሞ ብሔር ውስጥ ሶስት የተለያዩ የካኦ (የንጉስ) ደረጃዎች አሉ። ይሔውም “አፋ ካኦ” የበላይ ንጉስ፣ “ጋሞ ካኦ” የጋሞ ንጉስ፣ እና “ዴሬ ካኦ” የአካባቢ ንጉስ (የጎሳ ንጉስ) በሌላ አጠራር (ባላባት) በሚል ይታወቃሉ። እነዚህ የካኦ (ንጉስ) ደረጃዎችን እና ስልጣንና ተግባራቸውን በጥልቀትና በትክክል ሊያውቅ የሚችል የብሔሩ አባቶች እና በብሔሩ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የኖሩ ሰዎች ናቸው። የማዶላ ፀሐፊ እነዚህ እውኔታዎችን በጥልቀትና በስፋት ባለማወቁና ስለ አካባቢውም ሆነ ስለ ሕዝቡ ባህል ሰፋ ያለ ዕውቀት ስለሌለው ወይም እያወቀ ሆን ብሎ ከአስተማሪነትና እውነትን መሠረት ከማድረግ ይልቅ ብሔሩን በማጥላላትና በስድብ የተሞላ፣ ብሎም አከባቢውን የሰው ልጆች መኖር የማይችሉበት ሲኦል አስመስሎ በመቅረፅ ለቃችሁ ውጡ፣ ተሰደዱ በማለት ጽፈዋል። ሌሎችም ይህን መነሻ አገኘን በሚል መሰለኝ በጥልቀት በማያውቁት ጉዳይ ላይ እየፃፉ ይበልጥ የመቆሳሰል ስራ ሲሰሩ ይታያሉ።

አፋ ካኦ፡-በጋሞ ብሔር (አፋ ካኦ) ማለት በአማርኛ (የበላይ ንጉስ) እንደማለት ሲሆን ተግባሩም በድሮ ጊዜ ከሰው አቅም፣ ከሰው ቁጥጥርና ዳኝነት ውጪ ወይም በላይ ለሆኑ ነገሮች ለፀሀይ፣ ለዝናብ፣ ለጨረቃ፣ ለጎርፍ፣ ለናዳ- - -ወዘተ በተለይም ተፈጥሮነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የመለመንና የሚፈለገውን ሁኔታ የማምጣት ስልጣን አለው ተብሎ የሚታመን ንጉስ (ካኦ) ነው። ፀሐይ በበረታና ዝናብ በጠፋ ጊዜ ዝናብ እንዲመጣ የሚለምንና ባህላዊ ስርዓት የሚፈፅም፣ ዝናብ ከሚገባው በላይ በዝቶ ጎርፍ፣ ናዳና የመሳሰሉ አደጋዎችን በሚያስከትልበት ጊዜ ዝናብ እንዲቀንስና የሚፈለገው ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመጣ የሚለምንና የተለያዩ ስርዓቶችን የሚፈፅም ነው። ለዚህ ተግባር ከሕዝቡ የበሬ፣ የፍየል፣ የበግ፣ የእህል፣ የቅቤ፣ የወተት፣ የማር ግብር ይሰጠዋል።

ከየትኛውም የጋሞ አካባቢ ዝናብ የበዛበት ወይም ፀሀይ የበረታበት አካባቢ (ዴሬ) ዳና፣ ሁዱጋ እና የሀገር ሽማግሌዎች ወደዚህ የአፋ ካኦ ቤት በመሔድ በአካባቢያቸው የተፈጠረውን በማስረዳት እንዲፈፀምላቸው የሚፈልጉትን ይጠይቁታል። ለዚህም በአካባቢያቸው ሕዝብ ተወክለው መምጣታቸውን ያስረዳሉ። ለስርዓቱ መፈፀሚያ የሚያስፈልገውን ግብርም ያቀርባሉ። አፋ ካኦው ከፈለገ ረዳቶችን ይዞ ችግሩ ወደተፈጠረበት አካባቢ (ዴሬ) ይሔዳል። አለዚያም ባለበት ሆኖ ስርዓቱን ሊፈፅም ይችላል። የአፋ ካኦነት ሹመት በዘር የሚተላለፍ ነው። አፉ ካኦ በባህሉ በጣም ይከበራል። ነገር ግን በፖለቲካውና በሕዝባዊ የአስተዳደር ስራ ማለትም በባላባቱ (ዴሬ ካኦ) ተግባር ውስጥ አይገባም።

የአፋ ካኦው ጥንት መሠረቱ አሁን ባለበት ሻሌ አካባቢ አይደለም። ሻሌ የሚባለው አካባቢ ያለው ጨንጫ ወረዳ ውስጥ ነው። የአፋ ካኦው ጥንት መሠረቱ ከጋሞ ዴሬዎች አንዱ ከሆነ አካባቢ እንደ ሆነ ይነገራል። አፋ ካኦው ወደ «ሻሌ» የመጣው (ጋሞ ካኦ ዳዌ) በሚባለው የካኦነት ዘመን እንደሆነ ታሪኩን በሚነግሩን አባቶች ይነገራል። በዚያን ጊዜ ሲመጣ ለአፋ ካኦው በራዕይ ወይም በራሱ መንፈስ እንደተነገረው «እኔ የጋሞ ካኦ ባለበት ዴሬ እንዲኖር ተነግሮኛል» በማት ከራሱ አገር ጓዙንና ተከታዮችን ይዞ እንደመጣና ከጋሞ ካኦ ዘንድ እንደደረሰ አመጣጡን አስረድቶ «መሬት ሰጠኝ፣ ቤት አሰራልኝ፣ አገልጋዮችን ስጠኝ፣ ግብርና ስርዓቴን እዚሁ እዘዝልኝ» ብሎ ጋሞ ካኦውን ይጠይቃል። የጋሞ ካኦው ሀሳቡን ከሰማ በኃላ “እኔ እዚሁ ነኝ፣ አንተ ደግሞ ከወንዝ ማዶ ሂድና የመረጥከው ዴሬ ላይ ሁን። ሁለታችን በአንድ ወንዝ ከምንሆን አንተም ከወንዝ ማዶ፣ እኔም ከወንዝ ማዶ ብንሆን ይሻላል” ይለዋል።

አፋ ካኦው እሲ ብሎ ቢወጣም ከጋሞ ካኦው ላለመራቅ ስለፈለገ ከአካባቢው ሳይርቅ አንድ ወንዝ ተሻግሮ ከወንዝ ማዶ ተሻግሬያለሁና ይህን መሬት ስጡኝ፣ ቤት ስሩልኝ ብሎ ያዛል። የአካባቢው ሕዝብ ሁኔታውን ከጋሞ ካኦ ለማጣራት መልዕክተኛ ስልክ የጋሞ ካኦው ለማለት የፈለገው ወደ ሌላ ባላባት (ዴሬ) እንዲሔድና መሬት አግኝቶ እንዲኖር ነበር አፋ ካኦው ግን ከአካባቢው ላለመራቅ በያዘው አቋም ለመኖር የመረጠውን ቦታ ከተከለከለ ሊመጣ የሚችለውን የከፋ ችግር የጋሞ ካኦው በመገንዘብና መቃቃርና መጣላት እንደማያዋጣ በማሰብ “የሚፈልገውን አድርጉለት፣ ለዴሬው ካኦ (ለጎሳው ንጉስ) ሔዳችሁ፣ ታላቅ እንግዳ እንደመጣና ለታላቀ እንግዳ የሚደረገው ሁሉ እንዲደረግለት ንገሩት ብሎ . . . “ ያዛል። በዚህ ምክንያት የአፋ ካኦው መኖሪያ ሻሌ ሆነ። እርሱም በምርጫው ሻሌ ተባለ። በአሁኑ ጊዜ የአፋ ካኦ ዘሮች በሻሌ ውስጥ ይኖራሉ።

ጋሞ ካኦ፡- በጋሞ ብሔር ውስጥ አጠቃላይ ብሄሩን ከሚወክሉ ካኦዎች (ንጉሶች) ውስጥ አንዱ (የጋሞ ካኦ) ነው። ጋሞ ካኦ በብሔሩ ባህል እጅግ ታላቅ ቦታ ያለው አካል ነው። በጥንቱ ጊዜ ለጋሞ ሕዝብ በሙሉ ኃላፊነት አለበት ተብሎ እንደሚታሰብ ይነገራል። በጋሞ ዴሬዎች ያሉ (የዴሬ ካኦዎች) ባላባቶች አዲስ ሲሾሙና ወደ ስልጣን ሲመጡ የመጨረሻ ሹመታቸውን ከመቀበላቸው በፊት ለጋሞ ካኦ ግብርና የመታያ (የመተዋወቂያ) ስጦታ ይዘው ሔደው አባቴ፣ አያቴ፣ ቅድመ አያቴ፣ ዘር መንዘሬ ሲያስተዳድር፣ ሲመራ የኖረውን ሀገርና ሕዝብ ለመምራትና ለማስተዳደር ተሹሜያለሁና በሹመት በዓል ላይ ተገኝተው ሹመቱን መርቁልኝ በማለት ጥያቄ ያቀርባሉ። በዚህን ጊዜ የጋሞ ካኦው በዴሬ ካኦው (በጎሳው ንጉስ) ወይም በባላባቱ ሲመት በዓል ላይ ተገኝተው ይመርቃሉ። በሲመት በዓሉ ላይ ለመገኘት የማይመቻቸው ወይም የማይችሉ ከሆነ በእርሱ ምትክ ሆነው በዓለ ሲመቱን የሚመርቅ (ካኦ አቱማ) የሚባል ሹመት ያለው ሰው ይልካሉ። አቱማ ማለት የታወቀ የጋሞ ካኦው ወኪል ነው። በአንድ ጉዳይ ቦታ አቱማው ተገኘ ማለት ጋሞ ካኦው እንደተገኘ ይቆጠራል።

የጋሞ ካኦ ከፓለቲካዊ ወይም ከሕዝብ የአስተዳደርና የመምራት ስራ ይልቅ ወደ ሀይማኖታዊ አባትነት ያደላ ነው። ምክንያቱም የአስታራቂነት፣ የአስማሚነትና የገላጋይነት ሚና በመጫወት ይታወቃልና ነው። በተለያዩ የጋሞ አካባቢዎች በሕዝቡ ወይም በባላባቶች ወይም (በዴሬዎች) መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ፀብ ወይም ግጭትና ከፍ ያለ ችግር ከተፈጠረ ሁለቱም ወገን ግጭቱን አቁመው ወደ ሰላም እንዲመጡ፣ እርቅ እንዲያደርጉ ጋሞ ካኦ ያዛል። ጉዳዩ የከፋና አስቸጋሪ ሆኗል በሚባልበት ወቅት አንድም ተጋብዞ አሊያም በራሱ ተነሳሽነት በጉዳዩ ውስጥ በመግባት ችግሩ እንዲፈታ የማስማማት፣ የማግባባት፣ ስራ ይሰራል። በዚህ ካልተሳካ ፍርድ (ዳኝነት) በመስጠት ይታወቃል። ትዕዛዙን ጥሶና አሻፈረኝ ብሎ ወደ ከፋ ግጭት ወይም ውጊያ የገባ ካለ ጋሞ ካኦ ያወግዛል፣ ይገዝታል፣ ይረግማል። ሌላው አካባቢ ሕዝብ ወይም (ዴሬዎች) የጋሞ ካኦ ትዕዛዝን ከጣሰው አካባቢ ሕዝብና ባላባት ጋር እንዳይገናኝ ያዛል። እንደዚህ አይነት ውግዘት፣ እርግማንና ከሌላው ሕዝብ እንዳይገናኝ ትዕዛዝ የደረሰው አካባቢ (ዴሬ) አስቀድሞ በተፈጠረው ጉዳይ ላይ እርቅ እስኪሆን ድረስ ከሌላው ሕዝብ ተገልሎ ይቆያል።

አስቀድሞ በተፈጠረው ችግር ላይ እርቀሰላም የሚወርደው በአገሬው አጠራር (ካሬ ወይም አጌሳ) የሚባሉ ወክሎችን በማነጋገርና በእነሱ አማካይነት በመላላክ ነው። (ካሬ ወይም አጌሳ) ማለት በእያንዳንዱ አካባቢ (ዴሬ) ውስጥ ያሉና እንደዚህ አይነት ችግር ወይም ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ የአንዱ አካባቢ ባላባት (ዴሬ ካኦ) ከሌላው አካባቢ ባላት ወይም (ዴሬ ካኦ) ጋር ተገናኝቶ እንዲነጋገር፣ የአንዱ አካባቢ ሕዝብ ከሌላው አካባቢ ሕዝብ ጋር ተገናኝቶ እንዲመክር ቅድሚያ ሁኔታዎችን የሚያመቻች፣ በአጠቃላይ የዲፕሎማሲያዊ ስራ የሚሰራ፣ አንዳንዴም እንደ ውጪ ግንኙነት አይነት የሚሰራ አካል ነው።

እነዚህ ካሬ ወይም አጌሳዎች እርስ በእርስ እየተገናኙ ሁኔታዎችን ካመቻቹ በኃላ ከተለያዩ ገለልተኛ አካባቢዎች የተሻለ ተሰሚነት ያላቸው ባላባቶችን፣ ዳናዎችን፣ ሁዱጋዎችን፣ ኤቃዎችን በመሰብሰብ ግጭቱ በተፈጠረበት አካባቢ ሕዝቦች (ዴሬዎች) መካከል የተፈጠረውን ችግር እንዲፈቱ ያደርጋሉ። በዚህን ጊዜ የጋሞ ካኦው በጉዳዩ ሊገኝ ወይም ወኪሉን (አቱማውን) በመላክ ጉዳዩን እንዲጨርስ ሊያደርግ ይችላል። እንደዚህ አይነት ፀብና ግጭት የተፈጠረበት ጉዳይ በእርቅ ሲታይ እርቁ የሚካሔደው በሁለቱ አካባቢ ሕዝብ (ዴሬዎች) መካከል ባለ (ጫቆ ዱቡሻ) በሚባል ቦታ ነው።

የጫቆ ዱቡሻ ማለት መሀላ የሚካሔድበት ቦታ ነው። እርቁ ከተጠናቀቀ በኃላ ለወደፊትም ሁለተኛ እንደዚህ አይነት ነገር አንፈጽምም፣ ወንድማማቾች ነንና እርስ በእርስ ደም አናፈስም፣ ችግር ቢፈጠር እንኳን በሰላም እንፈታለን በማለት ከሁለቱ ችግሩ ከተፈጠረባቸው አከባቢዎች (ዴሬዎች) በወቅቱ በሹመትና ሕዝባቸውን በማገልገል ላይ የሚገኙ ዳናዎች፣ ሀዱጋዎች፣ ኤቃዎችና ተወካዩች ተሰብስበው መሀላ ያደርጋሉ። መሀላውን የሚያስፈጽሙት የጋሞ ካኦ ወይም ወኪሎችና በየአካባቢው ያሉ ካሬ ወይም አጌሳ ተብሎ የሚወከሉ ተወካዮች ናቸው። መሀላው ሲፈፀም በመሀላው ቦታ የበሬ፣ የፊየል የበግ ኮርማ እርድ ይፈፀማል። በቦታው በሬውን፣ ፍየሉንም ሆነ በጉን የሚያርደው እንደየ አካባቢው ሁኔታ የስልጣን ተዋረድ ደረጃ ያለው አካል ነው።

የእርቅ እርድ ከተፈፀመ በኃላ ከሁለቱም ግጭቱ ከተፈጠረው አካባቢ መሀላውን የሚፈፅሙ፣ የሚያስፈፅሙ እና ከየአካባቢው በአስታራቂነት የተሰበሰቡ ክፍሎች ሁሉ ተራ በተራ ከታረደው እንስሳ ደም በካኦው ወይም በአቱማው በእጅ ጣት እየተነካ በየግንባራቸው ላይ እንዲቀባ ይደረጋል። በሁለቱ አካባቢዎች መካከል ውጊያ ተካሕዶ የሰው ይህወት የጠፋ ከሆነም ሌላ የደም ካሳ ሳያስፈልግ በዚህ እርቀሰላምና የደም መቀባት ስነ-ስርዓት ውስጥ ተካትቶ እርቅ ሆኖ ያልቃል። ሁለቱ በውጊያው የተሳተፉ አካባቢዎች ባላባቶች (ካኦዎች) እና የእነሱ የጦር ረዳቶች ሁሉ ጦር ጋሻ እና ጎራዴዎቻቸውን አምጥተው ከታረዱት እንሰሳት ደምና ፈረስ እንዲያስነኩ ይደረጋል። ከዚያም በአንድ ቦታ ላይ ሰብስበው ቀላቅለው እንዲያስቀምጡ ይደረጋል። ቀጥሎም ሁሉም በፀቡ የተሳተፉ ወገኖች የእንሰሳት ደምና ፈርስ በነኩ ጦር፣ ጋሻና ጎራዴ ላይ ከቀኝ ወደ ግራ፣ ከግራ ወደ ቀኝ እየተሸጋገሩ አንድ መሆናቸውንና ሰላምና እርቅ ተፈጥሮ የተቀላቀሉ መሆናቸውን፣ ለወደፊትም ከሰላም ውጪ ሌላ መንገድ የማይከተሉ መሆናቸውን እያረጋገጡ መሀላ ያደርጋሉ።

ከዚህ በኃላ በካኦው ወይም በአቱማው የሰላም ምርቃት ተደርጎ ሁሉም ወደየአካባቢውና ወደየቤቱ ይመለሳል። ለዚህም ነው የጋሞ ካኦው ስልጣንና ሀላፊነት ከፖለቲካዊነት ይልቅ ወደ ሀይማኖታዊ አባትነት ያደላል ያልኩት። ሆኖም የጋሞ ካኦው በጋሞ አካባቢ ያሉ ሁሉንም (የዴሬ ካኦዎችን) የሚያዝ፣ ሲሾሙ የሚመርቅና ሲያጠፉ የሚገስፅ በመሆኑ የሁሉም ካኦዎች ካኦ (የሁሉም ባላባቶች) የበላይ የሆነ ንጉስ ነው።

                                             የ« ሀጥሼን » ተረት ለመተግበር አንሩጥ!! 

                             

                                                                         ገሣቶ ዳዴ

                                                             ከፋንጎn

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
828 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 90 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us