ለትብብሩ ስኬት ሰማያዊ ፓርቲ አሮጌ ካፖርቱን ያውልቅ

Wednesday, 03 February 2016 15:13

 

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ሰማያዊ ፓርቲ ከውስጥ ቁርቁስ መርዶ ጀምሮ ከመድረክ ጋር ተባብሮ ለመስራት አስቧል የሚል የምስራች የደረሱ ወሬዎች ተናፍሰውበታል። ሰማያዊ ፓርቲ በስህተት ተነስቶ በስህተት ጎዳና ተጉዞ ለዚህ የበቃ ቡድን ነውና በውስጡ ትርምስ መፈጠሩ ላያስገርም ቢችልም ፊቱን ወደ ትብብር ለማዞር ማሰቡ ግን ይበል የሚያሰኝ ነው። ሰሞኑን በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቅማንትና በሌሎች አካባቢዎች የታየው አሳሳቢ ነገር የተቃዋሚዎች አለመተባበር አገሪቱን ወደ ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ሊወስዳት እንደሚችል ፍንጭ የሚሰጥ ነው።

ከማንም ከምንም በላይ ስልጣኑን የሙጥኝ ያለው ገዥ ቡድን፣ አመጾች ሁሉ ወደ ስልጣን ይመራሉ የሚሉ ተቃዋሚዎች፣ አመጽ ሲነሳ አብረው የቆሙ መስለው ለመታየት ድራማ የሚሰሩ ተቃዋሚዎች፣ ያበጠው ይፈንዳ በሚል ፍካሬ ሁከቶች ሁሉ ጥሩ ናቸው እያሉ ወሬ የሚያስተጋቡ የስደቱ ዓለም ፖለቲከኞችና የሚዲያ ሰዎች … በዚህ ግርግርና ግጭት ማን መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ፈተናዎች መሆናቸው በጉልህ ታይቷል ማለት ይቻላል።      

ሕዝብ ‘ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ’ ሲል ያሰማው ጥሪው ተቀባይነት በማጣቱ በተቃዋሚዎች ተስፋ ባጣበት ወቅት ሰማያዊ ፓርተ በሚል ስያሜ አዲስ ፓርቲ መመስረቱ የስህተት አጀማመሩ ሲሆን ሰማያዊ ፓርቲ ዋና ከተማውን በውጭ አገር ያደረግ ያህል በስደተኛ ሰዎች የሚዘወርና የሚንደረደር መሆኑ፣ 9 ፓርቲዎችን ያቀፈ ሕብረት መሰረትኩ ብሎ በትብብር ሊያሾፍ በስህተት መጓዙን የሚያመላክቱ ፍጻሜዎቹ ናቸው። አሁን በቅርቡ ደግሞ የተለመደውንና በተቃዋሚዎች ላይ በተደጋጋሚ የታየውን የውስጥ ቁርቁስ በማስተናገድ ሌላውን ስህተት ፈጽሟል።  

ሰማያዊ ፓርቲ የፖለቲካ ቡድኖች እንደ አሸን በፈሉባት አገር የተቋቋመ አዲስ ፓርቲ ሆኖ እያለ ሕዝብ ሁሉ እሱን ብቻ መስማትና መከተል እንዳለበት ያምናል። ሰማያዊ ፓርቲ አቋሙን፣ አቅሙንና ማንነቱን ሳያገናዝብ በተደጋጋሚ ለሕዝብ ጥሪ አደረኩ ማለት ይወዳል። ከዚያም ጥሪየን የሰማ የለም ብሎ ያኮርፍና ሕዝብን ወደ መሸርደድ ያመራል። ባርነት ልብስህ ነው፣ ውርደት ቀለብህ ነው፣ ወኔ የሌለህ የአገር ሸክም ነህ የሚሉ ዘለፋዎች የተለመዱ የሰማያዊ ፓርቲ መወረፊያዎች ናቸው። የሰማያዊ ፓርቲ ሰዎች በሚያደርጓቸው ንግግሮችና ለሰልፍ ሲወጡ በሚይዟቸው የጽሑፍ መፈክሮች እነዚህ ዘለፋዎች ይስተጋባሉ። በማሕበራዊ ድረ ገጾችና የፓርቲው ልሳን በሆነው ጋዜጣ ላይም እነዚሁ ዘለፋዎች እየተስተጋቡና እየተነበቡ ኖረዋል።  

ሰማያዊ ፓርቲ ለሕዝብ መንግስት እንመስርት የሚል ጥሪ ያቀረበበት ጊዜ አለ። ይህን መሰሉ ጥሪ ሰሞኑን በአገሪቱ ውስጥ የተቀሰቀሱ ግጭቶችን ተከትሎም ተስተጋብቷል። ይህ ጥሪ ይሳካል ተብሎ ታምኖበት ወይም ለማሳካት ምክክርና ዝግጅት ተደርጎበት የቀረበ ሳይሆን የተለመደውን በስደተኛ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ትልቅ ተደርጎ ለመታየትና የጭብጨባ ትርፍ ለማግበስበስ የተሰራ ድራማ ነው። ያላደራጀኸውን ሕዝብ፣ ያላመነብህን ሕዝብ፣ የማታውቀንና የማያውቅህን ሕዝብ ለዚህ ትልቅ ነገር ተነስ ብሎ ጥሪ ማድርግ፣ ለዚያውም በቅጡ ዝግጅት ያልደረገበት ጥሪ የፓርቲውን ቀልደኛነት የሚያጋልጥ ነው። አሳዛኙ ነገር ፓርቲው የዚህ ዓይነቱ ጥሪዎቹ ውጤት አልባ መሆናቸውን ሲያይ ሕዝቡ ፈርቶ ጥሪየን አልተቀበለም፣ ሕዝብ ከነጻነት ባርነትን መረጠ፣ ሕዝብ ከነጻነት ውርደትን መረጠ የሚሉ ዘለፋዎችን ለመደርደር የሚነሳሳው።

ሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብን “ተባበሩ” የሚል ጥሪ አፍንጫህን ላስ ብሎ የራሱን የጉልት ፖለቲካ የፈጠረ ፓርቲ ስለሆነ ሕዝቡም በተራው አፍንጫህን ላስ ቢለው ሊያኮርፍ አይገባውም።

ሰማያዊ ፓርቲ የአገሪቱ የተቃውሞ ችግር ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመጥን አቋም ያለውና የገዥውን ቡድን ሁለገብ እርግጫ መቋቋም የሚችል ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ አለመፈጠሩ መሆኑን ሊያውቅ ይገባል። ካልሆነ ግን 90 ፓርቲ ባለበት አገር 91ኛው ፓርቲ ሲጨመር አማራጩም 91 መሆኑ መዘንጋት የለበትም። በፓርቲዎች እንደ ጫጩት መፈልፈል አላምን ላለ ሕዝብ ደግሞ አማራጩ ዜሮ ሊሆን ይችላል። ሰማያዊ ይህን ማየት ሳይችል የኖረ ፓርቲ ነው። ፓርቲው ማስተዋል በማጣቱ ሕዝብን የሚጠላ ስብስብ እያደረገው ነው። ፓርቲው በዚህ ከቀጠለ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን የአገር መክሽፍ መርዶ ነጋሪ፣ የአገር ሕልውና ማክተም ሟርት አሟራች፣ በሕዝብ ላይ ቅጡን ያጣ ዘለፋ አዥጎድጓጅ ከመሆን አያልፍም። ይኸ ደግሞ አቅም ያጣ አምባገነን የመሆን ምልክት ነው። በጥርስህ መንከስ ሲያስፈራህ በምላስህ መርዝ ማጥቃት።

ሰማያዊ ፓርቲ ከመድረክ ጋር ለመስራት ማሰቡ ጥሩ ቢሆንም ፓርቲው ይህን መሰሪ አመለካከቱን ከወዲሁ እርግፍ አድርጎ ትቶ፣ ማንነቱንና ዓቅሙን አውቆ ከመድረክ ጋር መቀራረቡ ተገቢ መሆኑን ሊያውቅ ይገባል። ሰማያዊ ፓርቲ እንዲሁ በሜዳ ትልቅ ነኝ የሚል አመለካከቱን መተው ካልቻለ መድረክ ውስጥ የነበረው አንድነት ፓርቲ በተጓዘበት የውድቀት ጎዳና እሱም መጓዙ የማይቀር ይሆናል።

ሰማያዊ ፓርቲ ከመድረክ ጋር አብሮ መስራትን ሲያስብ ሊያርመው የሚገባ ሌላ ነገርም አለ። ይኸ ሊያርመው የሚገባ ጉዳይ መንፈሱን በውጭ አድርጎ ኢትዮጵያ ውስጥ በበድኑ መኖርን ማቆም ነው።   

ኢንጅነር ይልቃልና ፓርቲያቸው በአስቸጋሪ ጊዜ በአገርህ ላይ መኖር፣ ልጆችህ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ሳይተው (ሳይክዱ) በሙያቸው በጽናት እዲያገለግሉ መምከር፣ ዜግነትን አለማቃለልና እክብሮ መያዝ ወዘተ የሰላማዊ ትግል ክፍሎች መሆናቸውን ሊረዱ ይገባል።

አንዱ የሌላውን ሰው ዜግነትና የሚኖርበትን አገር የሚመለከቱ ጉዳዮችን የመወሰን መብት ባይኖረውም ፓርቲንና ሕዝብን እመራለሁ የሚል ሰው ግን እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች እንዳሻው የሚወስን መሆን እንደሌለበት ሊታወቅ ይገባዋል። በሰማያዊ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ዜግነትን፣ አገርን ማክበርን፣ ከራስ ጥቅም እና ደህንነት የአገርን ጥቅምና ደህንነት ማስቀደምን የሚመለከት ሕግ እና መመሪያ ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን በአሜሪካው ኃይት ሃውስ ውስጥ፣ በእንግሊዙ ባኪንግሃም ፓላስ ውስጥ ወዘተ በነዚህ አገራት መኖር ስትጀምር ወይም የነዚህን አገራት ዜግነት ከወሰድክ በኋላ ልትገዛበት ግድ የሚልህ መሕግ እና ልትከተለው የሚገባህ መመሪያ ያለ መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል። በተለይ ደግሞ ዜግነትህን ስትቀይር የቀድሞውን ዜግነትን ችላ ማለትና ለኢትዮጵያ ያለህን ታማኝነት በሙሉ በውዴታ እርግፍ አድርገህ መተውህን በፊርማህ አረጋግጠህ መቀመጥ እንዳለብህ የሚያስገድድ ሕግ አለ።

ስለዚህ ዜግነታቸውን የቀየሩ ስደተኞች ‘ጥሩ የቢዝነስ ሸሪክ’ እንጅ ጥሩ የትግል ጓድ ማድረግ አይቻልም። የተቻለ ቢመስልም በፈረንጅ ጉዳናዎች ላይ ከመውረግረግ ያለፈ አይሆንም። አንዳንዶች ከዚህ አልፈው ሄደው ተመልሰው አሜሪካን ይቅርታ ሲጠይቁና ‘አርፈህ ተቀመጥ ወይም ውጣ’ ተብለው አሜሪካን ሲሰናበቱ ታዝበናል። እነዚህ መሰል ሰዎች የባዕዳንን ዓላማ ተሸክመው፣ አገራቸውን የሚጠቅሙ መስለው ተሰማርትው አገራቸውን ለማውድም መሳሪያ ሲሆኑ በተደጋጋሚ በብዙ አገራት ተሞክሮ ተስተውሏል። ኢትዮጵያችንም የዚህ ገፈት ቀማሽ ከመሆን አላመለጠችም። የሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስና እሱ ያስተባበራቸውን የቀድሞው ጦር መኮንኖች ድርጊት መርሳት ወይም ያላዩ መስሎ ማለፍ አይገባም። ይህን አውዳሚ ታረክ አላውቀውም የሚል ፖለቲከኛ ካለም አንብቦና ተመራምሮ ሊያውቀው ይገባል።

ሰማያዊ ፓርቲ በጣሊያንና በኢትዮጵያ ጦርነት ዘመን የንጉሱን ስልጣን የሚመኙ ራሶች፣ ንጉሶች፣ ደጃዝማቾችና ሌሎች የአካባቢ ገዥዎች ተከታዮቻቸውን (ሰራዊታቸውን) ይዘው ለጣሊያን አድረው አገራቸውንና ወገኖቻቸውን የወጉት ራስ ወዳድነታቸው አሳፋሪ አድርባይ ባንዳ ስላደረጋቸው መሆኑን ልብ ሊል ይገባል። በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ የሕወሐት፣ የሻእቢያ፣ የኢሕአፓ፣ የኢዲዩ፣ የኦሮሞ እስላማዊ ግንባር፣ የኦጋዴን ግንባሮች ወዘተ ከሶማሊያው ዚያድ ባሬ ጋር ግንባር የገጠሙትና አገራቸውንና ወገኖቻቸውን የወጉት፣ የኢትዮጵያን መወረር እንደ መልካም አጋጣሚ ያዩት ከኢትዮጵያና ከሕዝቦቿ ደህንነት ይልቅ ተልካሻ ዓላማቸውን ስላስቀደሙ መሆኑም መረሳት የለበትም። ጭንቅላቱን በውጭ ያስቀመጠው ሰማያዊ ፓርቲ ትክክለኛ አድራሻውን በጊዜ ሊወስን ይገባል።          

ኢንጅነር ይልቃል በቅርቡ የታየውን የፓርቲያቸው አባላት ለእስር መዳረግ ተከትሎ ኢትዮጵያ እውነትን የሚናገር ሰው መኖር የማይችልባት አገር መሆኗ እየታየ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ይች አባባል በአንድ ሰሞን አንዱ የፋና ጋዜጠኛ ወደ እስራል፣ አንዷ የኢቲቪ ቤተኛ ወደ አሜሪካ መጓዛቸውን ተከትሎ “ትግልን ተቀላቃሉ” ተብሎ በኢሳት ቴሌቪዥንና በበርካታ ማሕበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተናፈሰውን ወሬ የሚያስታውስ ነው። አሜሪካ ወይም አውሮፓ ሄጀ እታገላሉ የሚል መንፈስ እየተስፋፋ እያየን ነው። አንድ እግራቸውን በውጭየተከሉ ወይም በውጭ አገራት ካሉ ሰዎች ጋር ተሻርከው የሚሰሩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ከእለታት አንድ ቀን ወደ ውጭ መጓዛቸው የማይቀር መሆኑ በተደጋጋመ ታይትል። እነዚህን ሰዎች የውጭ ጓዶቻቸው ‘ያበጠውን አፈንዳውና፣ አተረማምሰውና አልሆን ካለ ወደ ውጭ ጠርተን አንደላቀን እናኖርሃለን’ የሚለው ማበረታቻ ለዚህ እንደሚያበቃቸው ይታወቃል። በትርምሱ ያነካኩት ሌላው ሰውስ ምን ይዋጠው? የራሱ ጉዳይ ሊባል ነው? ትግል እንመራለን የሚሉ ሰዎች ይህን በቅጡ ሊያስቡበት ይገባል? የሆነ ነገር ኮሽ ሲል አውራዎች ሁሉንም ነገር ሜዳ ላይ በትነው ወደ ውጭ የሚሮጡበት ትግል ሕዝቡን ተስፋ እያስቆረጠ ብቻ ሳይሆን አንገቱን እያስደፋው መሆኑም ሊታወቅ ይገባል።   

አንበሶቼ ተበሉብኝ የሚለው ሰማያዊ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ተቃዋሚ ቡድኖች አውራዎች ከፍልስጥኤማውያን ህጻናት ድንጋይ ውርወራ ሊማሩት የሚገባ ትልቅ ቁም ነገር አለ። እውነተኛው አንበሳም ተነጥሎ መኖርን ከወደደ በጅቦች ከመዘነጣጠል የሚያድነው ዓቅም እንደሌለው መታወቅ አለበት። ፍልስጥኤማውያን ከነ ከተሞቻቸው በእስራኤል ኤፍ-16 ጀቶች እየተደበደቡና እና መርከባህ ከተባለው የተራቀቀ ታንክ ጋር ተፋጥጠው በእሳት ውስጥ የሚኖሩት በአገርህ ላይ መኖር አንዱ የአገርህን ሕልውና የማስቀጠል የትግል ስልት ስለሆነ መሆኑን ሰማያዊ ፓርቲ ሊያውቀው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ቪኦኤንና ዶቸቨለን የመሳሰሉ ሚዲያዎች ሃማስ እና ኢራን የእስራኤልን ሀገርነት አይቀበሉም እያሉ ደጋግመው ነግረውናል። እስራኤል ብቻ ሳትሆን አሜሪካና ብዙ ሸሪኮቿ የፍልስጥኤምን አገርነት እንደማይቀበሉ ግን ብዙም አይነግሩንም። ከሶስትና ከአራት ዓመታት በፊት የፍልስጥኤም አስተዳዳሪዎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፍልስጥኤምን እንደ አንድ አገር አድርጎ እውቅና እንዲሰጣት ጥያቄ ለማቅረብ ሲነሳሱ የባራክ ኦባማ መንግስት ለፍልስጥኤም የሚሰጠውን ዕርዳታ ሁሉ እንደሚያቆም በመዛት ጥያቄውን ለማሰናከል ማስፈራራቱ ይታወሳል። ጥያቄው ግን ቀርቧል። ይህን ተከትሎ ከአውሮፓ ስዊዲን ፍልስጥኤምን እንደ አንድ አገር አድርጋ ተቀብላታለች። ድንጋይ ወርዋሪ ፍልስጥኤማውያንም ወደ 60 ለሚጠጉ ዓመታት ያደረጉት ትግል ቀጥሏል። ታንክ አየሁ እያሉ  አገራቸውን ጥለው ከሮጡ ፍልስጤም የምትባል አገር አትኖርም። አባቶቻችንና አያቶቻችን የጣሊያንን ታንኮች አይተው ቢፈረጥጡ ኖሮ ኢትዮጵያችንም አትኖርም ነበረ። 

ሰማያዊ ፓርቲን በውጭ ሆነው ከሚመሩት አንዱ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም የተባሉ ሰው ናቸው። እኝህ ሰው በደርግ ዘመን ከአሜሪካ ትምህርቴን ጨርሼ ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ አዲስ አበባ ውስጥ ታንክ አየሁ ብለው በቀናት ዕድሜ ውስጥ ወደ አሜሪካ ተመልሰው የሄዱ ሰው ናቸው። ከደርግ በኋላም ወያኔ ታንክ ይዞ አዲስ አበባ ስለገባ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለመታገል ወይም በሙያቸው አገሪቱንና ሕዝቦቿን ለማገልገል ሳይችሉ ቀርተዋል። ፕሮፌሰሩ በዚህ ዓይነት በውጭ አገር እየኖሩ የስደታቸውን 40ኛ ዓመት በቅርበት እያማተሩ ቢሆንም ሰማያዊ ፓርቲን ከሚመሩት ሰዎች አንዱ እኝህ ሰው ናቸው። ፕሮፌሰር አለማየሁ የፕሮፌሰር መስፍንን መጽሐፍ ሸምድደው የአሁኑን ትውልድ፣ አያቶቻችንን እና አባቶቻችንን ኃላፊነት የማይሰማቸው፣ ፈሪዎች ወዘተ እያሉ ዘልፈዋል።* ሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብን ፈሪ፣ ውርደት ቀለቡ፣ ባርነት ልብሱ እያለ የሚዘልፈው ስለ እነ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም ቀለብ፣ ወኔ እና ክብር ምንም ሳያጤን ነው። ሰማያዊ ፓርቲ ከመድረክ ጋር ተባብሮ መስራት የሚችለው ይህን መሰሉን አንድ እግርን ወይም ልብንና ጭንቅላትን በውጭ አገር አድርጎ በበድኑ አገር ውስጥ መኖሩን ሲያቆም መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ምክንያቱን መድረክ ውስጥ ያሉት መሪዎች ለስደተኛ ፖለቲከኞች አጉራ ዘለል ትእዛዝ የማይንበረኩ ናቸው። በስደቱ ዓለም ያለው ፖለቲከኛም እነሱን አያርባቸውም።

ሰማያዊ ፓርቲ ከነ አቶ ግርማ ሰይፉ አንድነት ፓርቲ ጋር በብዙ መንገድ የሚመሳሰል መሆኑ ይታወቃልና አንድነት ከመድረክ የወጣበትና ብሎም ለመፈራረስ የበቃበትን እውነታ በመረዳት ሰማያዊ ፓርቲ ከወዲሁ ሊያስተካክላቸው የሚገቡ ነገሮች መኖራቸው ሊታሰብበት ይገባል። በውጭ ያሉት አውራዎች አንድነትን ከመድረክ እንዲወጣ እንዳደረጉትና ፓርቲው ያካሄደውን የአመራር ምርጫ በአሳፋሪ አምባገንናዊ ግርግር በመለወጥ መፈንቅለ ስልጣን በማካሄድ ለመፈራረስና ለመናቆር እንደዳረጉት ሁሉ ሰማያዊ ፓርቲም በውጭ ያሉት መሪዎቹ በተመሳሳይ መንገድ እንደማያስጉዙት መረጋገጥ አለበት።  

(* ኢትዮ-ምሕዳር ጋዜጣ- ቅጽ 03፣ ቁጥር 126፣ ህዳር 4/2008 ዓም ‘ኢትዮጵያውያንን ከእራሳቸው መጠበቅ’)

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1029 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 91 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us