የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአመራር ሽግሽግ ቀጣዩን የህዳሴ መድረክ ታሳቢ ያደረገ ነው!

Wednesday, 17 February 2016 14:31

 

በየሳምንቱ እሮብ ጧት ሰንደቅ ጋዜጣን ከቁርሴ ማወራረጃ ቡና ጋር ማጣጣም ከጀመርኩ ሰነባብቻለው። ሚዛናዊ ዘገባዎቿ፣ ምክንያታዊ የሆኑ ግሳጼዎቿና በሳል የሆኑ ትንታኔዎቿ እንደእኛ ባለ ታዳጊ አገር ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ባህልን በመገንባት ረገድ አንድ ሚዲያ ሊጫወት የሚገባውን ሚና የምትጫወት ሚዲያ እንደሆነች ይመሰክራሉ። እናም እሮብ የካቲት 02  ቀን 2008 ዓ.ም  የወጣችውን ሰንደቅ ሳገላብጥ አይነገብ የሆነ ርእስ ተመለከትኩ። “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያባረራቸው አመራሮች እነማን ናቸው?” ይላል ለጹሁፉ የተሰጠው ርእስ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አኳያ  ለህዝቡ የገባውን ቃል በተግባር ለመተርጎም የሚወስዳቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች የተመለከተ ትንታኔ በፖለቲካ አምዷ ላይ አስፍራለች። ከአንድ ገጽ ዘለግ ብሎ የተሰናዳውን መጣጥፍ ስጨርስ ሀሳቡን ባደንቅም ሰፊ የሆነ ብዥታ ያለበት እንደሆነ ለመረዳት ግን ጹሁፉን መጨረስ አላስፈለገኝም።

ዛሬ ከሰንደቅ አንባቢነት ወደተሳታፊነት ያሸጋገረኝም ይህ የተሳሳተ ምልከታ መስተካከል አለበት የሚል እምነት ስላለኝ ምላሽ ለመስጠት ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ትርጉም ባለው መልኩ ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየተጋ ባለበት ባሁኑ ወቅት የሚያከናውናቸውን ሰፊ የልማት መርሀግብሮችና የሚወስዳቸውን የአመራር ማስተካከያ እርምጃዎች የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ሆነ አንባቢዎች ሊረዱት ስለሚገባ የራሴን ድርሻ ለመወጣት አንድ ብያለው። በነገራችን ላይ ይህ ምላሽ እኔ በግሌ እንደአንድ አንባቢ የምሰጠው ምላሽ እንጂ ኢህአዴግን ወይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ወክዬ የማቀርበው ሀሳብ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ።

ወደ ሀሳቤ ስገባ ጋዜጣዋ ላይ ለወጣው ጹሁፍ አንድ በአንድ ምላሽ መስጠት አስቸጋሪ በመሆኑ የአዲስ አበበባ ከተማ አስተዳደር የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመፍታት እያከናወነ ያለውን የአመራር ማስተካከያ አጠር አድርጎ ማቅረብ ብዥታን ለማጥራት የተሻለ እንደሆነ ይሰማኛል። እግረመንገዴን ሰንደቅ ላይ የተንጸባረቁ ህጸጾችን ለማመላከት እሞክራለው።

በአዲስ አበባ ከተማ እየተሰሩ ያሉ ሰፋፊ የልማት ስራዎችን ነዋሪዎቿ ሁሉ  የሚመሰክሩት፣ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የሚፈልጉት መሆኑ አሌ የሚባል አይደለም። በአዲስ አበባ ፈጣን እድገት ነዋሪዎቿ ተሳታፊም ተጠቃሚም ስለመሆናቸው ክርክር ይነሳል ብዬ አላስብም። መልካም አስተዳደር ማለት በአንድ መልኩ ህዝብን በልማት አጀንዳ ላይ ማሳተፍና ሁሉም በተሳተፈው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ በመሆኑ በዚህ ረገድ መልካም አፈጻጸም ተመዝግቧል። ከቅርብ አመታት ወዲህ የእያንዳንዱን ነዋሪ ደጅ ማንኳኳት ከጀመሩት የአዲስ አበባ  ሰፋፊ የመሰረተልማት አውታሮች ተጠቃሚዎቹ ህዝቦቿ ናቸውና ይበል የሚያሰኝ ነው።

ነገር ግን መልካም አስተዳደር ሌላም ገጽታ አለው። ህዝብ ከመንግስት ተቋማት ሊያገኝ የሚገባውን አገልግሎት ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ መንገድ በማቅረብ የነዋሪውን ጊዜና ወጪ በመቀነስ የአገልግሎት እርካታን ማረጋገጥ ሁለተኛውና ወሳኝ የመልካም አስተዳደር ገጽታ ነው። ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ ሲመዘን በልማት ቱርፋቶች የህዝቡን ተስፋ መፈንጠቅ የተቻለውን ያክል በአገልግሎት አሰጣጣጡ  እርካታን ማረጋገጥ እንዳልተቻለ ኢህአዴግ ነጋሪ አላስፈለገውም። የመልካም አስተዳደር ሪከርዳችን ያስመዘገብነውን የልማት ውጤት የሚመጥን አይደለም የሚለው ግምገማ  የኢህአዴግ ግምገማ ነው። ግምገማ በመሰረቱ ለመማር፣ ለመሻሻልና የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የምትንደረደርበት ነውና እንዲህ አይነቶቹ በሳል ግምገማዎች የኢህአዴግ መለያ መሆናቸው የሚታወቅ ነው።

ባሳለፍነው ክረምት መቀሌ ላይ በተካሄደው 10ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር ተብትቦ ይዞኛል፣ ይህን ችግር በተሀድሶ መንፈስ ታግዬ ካላስተካከልኩ በቀር ለአገርም ለድርጅቱም አይበጅም ብሎ ምንም ሳይሸፋፍን በይፋ ለህዝቡ ማቅረቡም የሚታወስ ነው። ከጉባኤው በኃላ ደግሞ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን መሰረት በማድረግ በስራ አስፈጻሚ ደረጃ ብዙዎችን ያስደመመ የውስጠድርጅት ትግል የታየበት ውይይት ከህዝብ ጆሮና አይን ደርሷል። ይህንን ተከትሎም የህዝብ ንቅናቄ መድረኮች እየተካሄዱ ነው። ኢህአዴግ ይህን የሚያደርገው ወትሮም ቢሆን  ህዝባዊ መስመሩ ፈተና ሲጋረጥበት ባለቤቱ ለሆነው ለህዝቡ ማቅረብ ነባር ኢህአዴጋዊ ባህል በመሆኑ ነው። ኢህአዴግ ዛሬም ቢሆን እራሱን በራሱ የመቆጣጠር ፍላጎቱም ሆነ አቅሙ እንዳለው በአደባባይ ያስመሰከረበት አጋጣሚ ነው።

10ኛውን የኢህአዴግ ጉባኤ ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባደረገው ጠለቅ ያለ  ግምገማ መሰረት አሁን በከተማችን የሚታየው የመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያቶች ሁለት ናቸው። የመጀመሪያውና ዋነኛው ምንጩ የአመለካከት ችግር ነው። አመራሩም ሆነ ፈጻሚው የተሟላ የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ አለመላበሳቸውና የህዝብ ውግንና የማጣት ችግር አሁን በከተማችን ለሚስተዋለው የመልካም አስተዳደር ችግር የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀላል የማይባለው አመራር ህዝብን የማገልገል ቅን አመለካከትና ቁርጠኝነቱ እያለው ከከተማዋ እድገት ጋር እየተወሳሰበ የመጣውን የፖለቲካል ኢኮኖሚ ባህሪይ ተረድቶ የመምራት ክህሎት ወይም እውቀት የሚያንሳቸው መሆናቸውም ተገምግሟል።

ስለዚህ እየገፋ የመጣውን የአዲስ አበባ ነዋሪ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ከምንም በፊት ይህን ቋጠሮ መፍታት ያስፈልጋል የሚለው  ሁላችንንም የሚያስማማን ይመስለኛል። በመሆኑም ኢህአዴግ ቆራጥ አቋም ወሰደ። በቂ የትምህርት ደረጃ እያላቸው በስነመግባር ተጨማልቀው  የህዝብንና የመንግስትን አደራ የዘነጉትን  ሁሌም እንደሚያደርገው የውስጠድርጅት ትግሉ አንገዋሎ ተፍቷቸዋል። ከኢህአዴግ የአመራር ፑል እንዲወጡም ተደርጓል። ባስ ያለባቸውን ደግሞ በህግ እንዲጠየቁም እያደረገ ነው። በሌላ ጎኑ ህዝብን የማገልገል ፍላጎት እያላቸው አቅም ያነሳቸውን ደግሞ አቅማቸውን ለመገንባት የሚያስችል የከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተሉ ወስኖ በማስተማር ላይ ነው።

እንዲህ ግልጽ በሆነ የግምገማ መስፈርት መልክ የያዘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  የአመራር ማስተካከያ ውሳኔ ሰንደቅ ጋር ሲደርስ ተበርዞና ተደልዞ መድረሱን አንብቢያለው። ከኃላፊነታቸው የተነሱ አመራሮች በሶስት ምክንያት እንደሆነ ሰንደቅ ጋዜጣ አለኝ የምትለውን መረጃ ጠቃቅሳ ለማቅረብ ሞክራለች። በሰንደቅ መረጃ መሰረት ከኃላፊነታቸው የተነሱ አመራሮች በሶስት መስፈርት የሚታዩ ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ከአስረኛ ክፍል በታች የሆኑ ሲሆኑ በጥቃቅን እንዲደራጁ፣ ሁለተኛዎቹ በድሮ አስራሁለተኛና በአሁኑ አስረኛ ክፍል ያጠናቀቁትን ዲፕሎማ እንዲማሩ፣ በሶስተኛ ደረጃ ዲፕሎማ ያላቸውን ዲግሪ እንዲማሩ ተወስኗል  ይላል። እንዲህ አይነቱን የተሳሳተ መረጃ ነው መታረም አለበት የምለው። ደግነቱ መረጃው የተሳሳተ ከሆነ ለመታረም ዝግጁ ነኝ ስላለች ይክው ታረሚ የተሳሳተ መረጃ ነው ለማለት እወዳለው።

ምክንያቱም ሲጀመር በጥቃቅን የሚደራጁት ያልተማሩ ሰዎች ናቸው የሚል አተያይ ኢህአዴግ የለውም። በመሰረቱ ጥቃቅን የካፒታል መጠንን እንጂ የትምህርት ደረጃን የሚያመላክት የስራ ዘርፍ አይደለም። እንደማንኛውም ዜጋ ከኃላፊነት የተቀነሱ አመራሮች ተደራጅተው የመስራት መብት ስላላቸው በጥቃቅን የተደራጁ አሉ። ይህ የነርሱ ምርጫ እንጂ አንተ ትማራለህ አንተ በጥቃቅን ትደራጃለህ ብሎ የከተማ አስተዳደሩ ማንንም ወክሎ አልወሰነም።

ሌላው ስህተት አንድ ክፍለከተማን ማሳያ አድርጎ ማቅረቡ ነው። በሰንደቅ እይታ የዚህ ክፍለከተማ ኮር አመራሮች ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ተብሎ ተገምግሟል ይላል። ይቀጥልና ትምህርት የገቡትን፣ የስራ ቦታ የቀየሩትን ይጠቅሳል። መጨረሻ ላይ ውሳኔው ትክክል አይደለም ብሎ ይሞግታል። ለነገሩ አመራሮቹ የተነሱበትን ምክንያት “ኃላፊነታቸውን አልተወጡም” በሚል አድበስበሶ አለፋት እንጂ እንዲህ አይነት ጥቅል ግምገማ ሲጀመር ኢህአዴግ ቤት ውስጥ የለም። ምክንያቱም ኢህአዴግ ያንገዋለላቸውን አመራሮችም ሆነ ወደትምህርት ቤት የላካቸውን አመራሮች ግምገማ በግልጽ አስቀምጧል። ግምገማ ማለት ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ ማቅረብ ሳይሆን ለምን መወጣት እንዳልቻለ ትክክለኛውን ምክንያት ማወቅ ማለት ነው። ምክንያቱም ትግል ለማድረግም ሆነ የግንባታ ስራ ለመስራት የችግሮችን ምንጭ ማወቅ የግድ ያስፈልጋልና።

ሲቀጥል ኃላፊነትን አለመወጣት ማለት የግድ የስነምግባር ችግር ነው ማለት አይደለም። የተጠቀሰውን ክፍለከተማ ምክንያት ይህ ነው ብሎ ማቅረብ ተገቢ ባይሆንም አንድ ነገር ግን በርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። በመላው የከተማው አስተዳደር እርከን  የስነምግባር ችግር ያለበት አመራር የስራ ቦታ ቅያሪም ሆነ የትምህርት እድል ያልተሰጠው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ለመታረም ዝግጁ ነን የሚለው የሰንደቅ አባባል ከልብ ከሆነ ይህም መታረም አለበት። ከአቅም ማነስ የሚያጋጥም የስራ ሽግሽግ ግን ትላንትም የነበረ፣ ነገም የሚቀጥል የአመራር ምደባ ስልት ነው።

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ሲነሳ ከመሪ ድርጅቱ ህዝባዊ ባህሪይው ተነስቶ የወሰነው እንጂ ሌላ ምንም አይነት መንደርደሪያ የለውም። የከተማ፣ የክፍለከተማና የወረዳ አመራሩ በዚህ የመልካም አስተዳደር ሚዛን ተመዝኗል፣ ውሳኔም አግኝቷል። የስልጣን እርከን ወይም ደረጃ፣ የሚሰራበት ተቋም ወይም ቦታ፣ እድሜ ወይም ጾታ፣ የድርጅት ቆይታ ወይም ያለፈ ታሪክ፣ ከዚህ ውሳኔ በስተጅርባ ቅንጣት ታክል ቦታ የላቸውም። እውነታው ይህ ነው።    

አገር ያወቀው ጸሀይ የሞቀው እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ ሰንደቅ የካቲት 02 ይዛ በወጣችው የፖለቲካ አምድ ላይ ነገሩን የተገላቢጦች አድርጋ ነው የተመለከትኳት። “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያባረራቸው አመራሮች እነማን ናቸው?” በሚል  ጥያቄ  ጹሁፉን ይጀምርና ከእውነታ የራቀ አንድ ረዥም ልበወለድ ታሪክን በምሳሌነት በማንሳት የተባረሩት አመራሮች ዝቅተኛ የአመራር እርከን ላይ ያሉት ናቸው ብሎ ይደመድማል። እዚህ ጋር አንድ ጥያቄ አለኝ።

 ሰንደቅ ጋዜጣ የበታች አመራሩ እርምጃ እንደተወሰደበት መረጃ ካገኘች የሌላውን እንደምን አጣችው? ደግሞስ አመራር ማለት ምን ማለት ነው? ጥያቄው ለዝግጅት ክፍሉ የቤት ስራ ይሁን። ኢህአዴግ ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ ቆራጥ አቋም ወስዶ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ለማሳየት የግድ ከንቲባው ወይም ምክትል ከንቲባው ላይ እርምጃ ይውሰድ ከሆነ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሆናል። እርምጃም ሆነ ግምግማ በኢህአዴግ ቤት ችግርን ለመሻገር ነውና ችግርን ለይቶ እርምጃ መውሰድ ሊወደስ የሚገባው መሆን አለበት።

ባጠቃላይ የኢህአዴግ አልፋና ኦሜጋ የህዝብ ተጠቃሚነት ነውና የዚህ ውሳኔ መነሻውም ሆነ መድረሻው ህዝብ ነው። የህዝቡን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄ ለመፍታት ብስለት በተሞላበትና የድርጅቱን የውስጥ ዴሞክራሲ በሚያጎለብት መልኩ በትግል የተወሰነ ውሳኔ ነው። ለዚህም ነው የአመራር ማስተካከያው ቀጣዩን የህዳዜ ጉዞ ታሳቢ ያደረገ ነው የሚባለው። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች  በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ስር ነቀል ለውጥ እንዲመዘገብ ስትጎተጉቱ በመቆየታችሁ ይህ ውሳኔ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የእናንተም የትግል ውጤት ነውና ተሳትፎአችሁን አጠናክራችሁ ልትቀጥሉ ይገባል እላለሁ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
682 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 101 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us