በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቆጣጠር የኅብረተሰቡ ድጋፍ ወሳኝ ነው

Wednesday, 17 February 2016 14:39

 

 

- ከሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ግብረ-ኃይል

በታደሰ ካሳ

(ፍትህ ሚኒስቴር ኮሙኒኬሽን ማስተባበሪያ)

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ የማሻገር ወንጀል የዓለም ሀገራትን ማኅበረሰብ በር እያንኳኳ የመጣ የዘመኑ የእግር እሳት መሆኑን ተከትሎ ሁሉም ዜጋ በሔደበት፣ በተቀመጠበትና በሚኖርበት ቦታ ሁሉ በዚሁ አደጋ ምክንያት ስለቆሰሉ፣ በውቅያኖስ ላይ ስለተጣሉ፣ ከፎቅ ወደ መሬት ስለተወረወሩ፣ በዱር እንስሳት ስለተበሉ ሲቀጥልም የሔዱበት የውሃ ሽታ ስለሆኑ ሰዎች ሲያወራ ይደመጣል። ጉዳዩ አይነትና ይዘቱን እየቀያየረ የመጣ አሳሳቢነቱ ለዓለም ማኅበረሰብ ብሎም ለምዕራባውያን ብዙሀን መገናኛዎች መነጋገሪያ ከመሆን ባለፈ እያስከተለው ስላለው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መዘገብ ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል። ወንጀሉን ለማስቆም ሲታሰብ ወንጀሉ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለውና ውስብስብ ከመሆኑ አኳያ የዓለም ሀገራት መንግስታትን ጥምረትና የጋራ ጥረትን የሚጠይቅና ፈጣን ማስታገሻ የሚሻ ነው።

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የሕገ-ወጥ ሰዎች ዝውውር ተከላካይ ግብረ-ኃይል ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ እንደ አቶ ይበልጣል ዋለልኝ ገለፃ ይህ ድርጊት ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት አንዱ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ አደገኛ እፅን በሕገ-ወጥ መንገድ ከማዘዋወር ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አስችሎታል። በብዙ ቢሊዮን ዶላር ብር በጀት ከፍተኛ እንቆቅልሽ እየተጫወተ፣ በሰዎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ላይ ከፍተኛ ጥሰትን እያስከተለ የመጣው ይህ ወንጀል፣ በሀገራችንም ስር ከሰደደና ከጊዜ ወደ ጊዜ የአፈፃፀም ስልቱን እየቀያየረ ከመጣ አመታትን አስቆጥሯል።

እንደ አቶ ይበልጣል ገለፃ ይህን ለመግታትም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እስከ ቀበሌ ድረስ ባሉ አመራሮች፣ የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም በብዙሃን መገናኛ አውታሮች ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ስለሚያስከትለው ዘርፈ-ብዙ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲነገር ቆይቷል። ይሁንና በሕገ-ወጥ ደላሎች በሚደረጉ የማጭበርበሪያ ስልቶች በተለይ በአርሶ አደሩ ማኅበረሰብ ዘንድ በነበረው የተዛባ አመለካከት ምክንያት ችግሩን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት አርሶ አደሩ ኅብረተሰብ አለመሳተፉ አደጋው እንዲባባስ አድርጎት ቆይቷል ይላሉ።

ወንጀሉ በተለይም የሰዎች ውስጣዊ አካል ወጥቶ እንዲሸጥ፣ ሴቶች ለወሲባዊ ባርነት፣ ወንዶችም ለጉልበት ብዝበዛና ለመሳሰሉ አስከፊ መልክ ያላቸው የወንጀል ድርጊቶች እንዲጋለጡ እያደረገ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ አንፃርም ይላሉ ብሔራዊ የሕገ-ወጥ ሰዎች ዝውውር ተከላካይ ግብረ-ኃይል ጽ/ቤት አስተባባሪው፤ የወንጀል ድርጊቱ ዘመናዊ ባርነት እንደገና እንዲያቆጠቁጥና እንዲንሰራፋ በር እየከፈተ ያለ ነው። ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ የማሻገር ወንጀል በአሁኑ ሰዓት መልኩን ቀይሮ በተለያየ መልኩ ነው እየተካሔደ የሚገኘው። ኢትዮጵያም ይህ ችግር የሚስተዋልባትና የተለያዩ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ ደላሎች እንደ መተላለፊያ መንገድ ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት በመኖሩ ብሎም የወንጀል ድርጊቱ ሰለባ ከሆኑት አንዷ በመሆኗ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሰረት አድርጋ ከሀገራችን ሕገ-መንግስት ጋር ተስማሚ አዋጅ አውጥታለች።

በመሆኑም ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከዚህ በፊት የነበረውን የሕግ ክፍተት መሙላትና ማስተካከል እንዲቻል አዋጅ የማሻሻልና የማርቀቅ ኃላፊነት የተሰጠው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አዲስ አዋጅ በሳለፍነው ነሀሴ ወር 2007 ዓ.ም ማውጣት የተቻለ መሆኑን አስተባባሪው ገልፀዋል። በዚህም አዋጁ ወንጀሉን የፈፀሙ አዘዋዋሪዎች (ጥፋተኞች) ላይ ሊያስተምር የሚችል ቅጣት እንዲኖር፣ ተጎጂዎችን መልሶ ማቋቋም በሚያስችል ሁኔታ እንዲሁም ወደፊት የሚደረገውን ወንጀልን የመከላከል ስራ ውጤታማ ለማድረግ የሚሉ አብይ ዓላማዎችን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው ሲሉ አክለው ተናግረዋል።

አቶ ሰለሞን እምሩ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ-ሕግና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ አርቃቂ ኮሚቴ አባል በበኩላቸው፤ የአዋጁ ፍሬ ነገር ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ማዕከል ያደረገ ነው። በተለይም ደግሞ ወንጀሉ ውስብስብና ዓለም አቀፍ ትኩረትን እየሳበ የመጣ በመሆኑ ኢትዮጵያም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀለኞችን ለመከላከል ከሀገራት ጋር ባላት ስምምነት መሰረት ሕግ አውጥታ እየሰራች መሆኗን የሚያሳይ ነው። ይህን ለማስፈፀም ስትልም በተለይ ሁለት ፕሮቶኮሎችን አውጥታ ተግባራዊ አድርጋለች።

አንደኛው ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን (Human Trafficking) ለመከላከል የሚረዳ ፕሮቶኮል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር (Human Smuggling) ወንጀልን የሚያመለክት ነው። አዋጁ ወንጀሉን መከላከል፣ ተጎጅዎችን መጠበቅ፣ ወንጀለኞችን ማስቀጣትና ከባለድርሻ አካላት ጋር የስራ ትብብርን ማጠናከር የሚሉ ፍሬ ነገሮችንም የያዘ ነው። ይህን አዋጅ ተፈፃሚ ለማድረግም ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ከሃይማኖት ተቋማትና መሰል ድርጅቶች የተውጣጣ ግብረ-ኃይል ተዋቅሮ ስራውን መጀመሩንም አስረድተዋል።

የግበረ-ኃይሉ አስተባባሪ አቶ ይበልጣል ዋለልኝ እንደሚሉት ግብረ-ኃይሉን እየመሩትና እየሰበሰቡት ያሉት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ጌታቸው አምባዬ ሲሆኑ፤ በዚሁ አግባብ አዋጁ ከፀደቀበትና ግብረ-ኃይሉ ከተዋቀረበት ካለፉት ወራት ወዲህ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተደርገው ወደ ስራ ተገብቷል።

እንደ አስተባባሪው ገለፃ ከሆነ የግብረ-ኃይሉ ተቀዳሚ አላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወንጀልን የመከላከል፣ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር፣ ተጎጅዎችን መልሶ የማቋቋምና በስነ-ልቦናም ይሁን ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮችን ድጋፍ ለማድረግ ብሎም የወጡ ሕጎችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ እንዲቻልና ቁጥጥር በማድረግ ዘላቂ ስትራቴጂያዊ ጥናቶችን ማውጣትና ማፅደቅ ነው። በመሆኑም ይህንና መሰል ጉዳዮችን ለመተግበር የሚያስችሉ አራት ግብረ-ኃይሎች ተዋቅረው እየሰሩ መሆኑን የገለፁት አስተባባሪው አንደኛው በሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የሚመራ ቡድን ሲሆን፤ ይህም ወንጀልን የመከላከል ስራ የሚያከናውን ቡድን ነው። ሁለተኛው ግብረ-ኃይል መልሶ የማቋቋም (አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ኤጀንሲ) የሚመራው ቡድን ነው። ሦስተኛውም የሕግ ማስከበር ቡድን ሲሆን፤ ይህም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሚመራ ቡደን ነው። አራተኛው ግብረ-ኃይል ደግሞ የጥናት ክትትልና ግምገማ ቡድን ሲሆን፤ ይህም በትምህርት ሚኒስቴር የሚመራ ቡድን ነው ብለዋል። በዚህ አግባብም እያንዳንዱ ቡድን በበኩሉ መስራት የሚገባውን ዕቅድ አውጥቶ ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

የወጣውን አዋጅ መሬት ላይ በማውረድ ለውጥ ማምጣት እንዲቻልም በተለያየ ጊዜና ቦታ የተለያዩ አጋር አካላትንና የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማወያየት ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በተለይ ደግሞ በጉዳዩ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከሚሰሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም በቀጣይም የበለጠ ለመስራት እየተሔደበት ያለ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የነበረውና ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት የሆኑት ድህነት፣ ሰዎች ውጭ ሀገር በመሄድ በአጭር ጊዜ እንከበራለን የሚል አጉል ተስፋ፣ በፍትሕ ሴክተሩ በኩልም ቢሆን ወንጀለኞችን በሕግ አግባብ አስቀርቦ ተገቢውን የሕግ ውሳኔ እንዲያገኙ አለማድረግ የሚሉ ድክመቶች የራሱ ተፅዕኖዎች የነበሩት ሲሆን፤ በሌላ በኩልም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በራሱ የተደራጁ ወንጀለኞች የሚሳተፉበት ትልቅና ፈታኝ ይዘት ያለው መሆኑ ፈጣንና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት አስቸጋሪ አድርጎት እንደቆየም አስረድተዋል። ይኸውም ሆኖ ይላሉ አስተባባሪው ይህን በተገቢው መልኩ ለመቆጣጠርም ሆነ ለመከላከል ከዚህ በፊት የነበረው የሕግ ማዕቀፍ የዘመቻ ስራ ነው ብሎ መውሰድ እንደሚቻልና ችግሩ ከደረሰ በኋላ መፍትሔ ለመውሰድ የሚደረግ የአንድ ወቅት ሩጫና ግብግብ ነው። ለአብነትም በሳዑዲዓረቢያ በነበረው ችግር ምክንያት ወደ 350 ሺህ ስደተኞችን ወደ ሀገር ለመመለስና ከአደጋው ለማዳን የተደረገው ዘመቻ ሊጠቀስ ይችላል። ስለዚህ ችግር ሲፈጠር ከመሮጥ ይልቅ ቀድሞ መዘጋጀትና ለችግሩ ቀድሞ መልስ መስጠት የሚያስችል ስትራቴጂ መቀየስ እንደሚያስፈልግ ተረጋግጦ ለስደትና ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መንስኤ የሚሆኑ ምክንያቶችንና መፍትሔዎችን ግብረ-ኃይሉ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ሲሉም አብራርተዋል።

ነገር ግን ይላሉ የአዋጁ አርቃቂ ኮሚቴ አባል አቶ ሰለሞን እምሩ ዝርዝር ተግባራት በአዋጁ የተገለፁ ሲሆን በዋናነት ግን በኅብረተሰቡ ላይ ጥልቅ የሆነ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መስራትን ይጠይቃል። በተለይም በሕገ-ወጥ ደላሎች አማካኝነት የሚደረጉ የማታለልና የማማለል ተግባራትን ህዝቡ እንዲያውቀው ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ገልፀዋል። ከሕግ አንፃርም ፍትህ ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው አካላት፣ ብዙሀን መገናኛ ድርጅቶችን ጨምሮ በተደራጀና በተቀናጀ አካሔድ ኅብረተሰቡን የማሳወቅ ሰፊ ስራ መስራት አለባቸው።

አቶ ሳምሶን ተገኔ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት የማስረፅ ቡድን ዐቃቤ-ሕግ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉትም አሁን በስራ ላይ የዋለው አዋጅ የሀገራችንና ዓለም አቀፍ ሕጎችን ተንተርሶ የወጣ ሲሆን፤ የወንጀሎችን ባህሪ መሰረት ያደረገና ዜጎች ከሚደርስባቸውና ሊደርስባቸው የሚችለውን እንግልት ለማዳን የወጣ ነው። በዋናነትም በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ወንጀለኞች እንዲቀጡ ሳይሆን ይህ ተግባር በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ስቃይ፣ እንግልት፣ ሞት በተለይ ደግሞ በሴቶችና ህፃናት ላይ ጥቃት እንዲደርስ እያደረጉ በመሆናቸው በዚህ ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት ቆም ብለው እንዲያስቡና ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የማስጠንቀቅ ተግባር ለማከናወን ነው። ይህን አዋጅ ቸል በማለት ወይም ደግሞ በዚህ የወንጀል ድርጊት የሚቀጥል አካል ካለ በሕግ እንዲቆነጠጥ ማድረግ የሚያስችል ነው። በመሆኑም አሁን የወጣው አዋጅ ከምንጊዜውም በተለየ ጠበቅና ጠንከር ያለ ነው። ፍትሕ ሚኒስቴር አዋጁን ከማርቀቅ እስከ ማስፀደቅ ድረስ ከፍተኛ ስራ ሰርቷል።

ይሁንና አዲስ አዋጅ በፍጥነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የማያስችሉ ተፈጥሮአዊ ባህሪ ያላቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች በመኖራቸው ይህን መቅረፍ የሚያስችል ሰፊ የስርፀት ስራ እየተሰራ ነው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።

በተለይም ብዙሀን መገናኛዎች ከፍትህ ተቋማት ጋር በመተባበር የሕግ ባለሙያዎችንና ሌሎች አካላትን በመጋበዝ አዋጁን አጉልቶ በማሳየት ኅብረተሰቡ በራሱ የትግበራ ኃላፊነቱ አንዱ አካል የማድረግ ሰፊ ስራ ቢሰራ መልካም ነው እንደ አቶ ሳምሶን ተገኔ መልዕክት።

የፍትህ አካላትም ቢሆኑ የማስፈጸም ኃላፊነት ያለባቸው እንደመሆኑ መጠን አዋጁን የሚጣረስ ሰራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ከተደበቁበት ጉድጓድ በማውጣት ይዞ በሕግ አደባባይ ላይ በማቅረብ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጣቸው ማድረግ ይጠበቅበታል።

አዋጁን የማስከበር ከፍተኛና ቀዳሚው ኃላፊነት በፖሊስ ላይ የተጣለ በመሆኑ የወንጀል አፈፃፀም ሒደቱን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ኅብረተሰቡን አጋርና አሳታፊ ባደረገ መልኩ መረጃዎችን ሰብስቦና አጣርቶ ለዐቃቤ ሕግ ማቅረብ አለበት። ዐቃቤ ሕግ በበኩሉም ከዚህ በፊት ከፖሊስ ጋር እንደሚያከናውነው ሁሉ ከፖሊስ ጋር ያለውን የስራ ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር አጥፊዎች ተገቢውን የፍርድ ውሳኔ እንዲያገኙ የማድረግ ኃላፊነታቸውን በመወጣት የዜጎቻችንን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ልናረጋግጥ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
513 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 83 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us