“የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ”

Wednesday, 24 February 2016 14:18


ለታክሶ ላጮ የተሰጠ መልስ

ከሻመና

 

የተወለደው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ሰኔ1947 ነው። የእንግሊዝና የህንድ ዜግነት አለው። በተለያዩ የልበወለድ ድርሰቶቹ በአገረ እንግሊዝ የተለያዩ ሽልማት ያገኘ። ከሶስት ታላላቅ ድርሰቶቹ በኋላ ነበር አራተኛውንና የአረቡን ዓለም ያወዛገበውን ልበወለድ ድርሰት የፃፈው። ሴር አህመድ ሳልማን ሩሽድ ይባላል። የሳታኒክ ቬርስስ ደራሲ። መጻሕፉን የጻፈው በ1988 እንደፈረንጆች አቆጣጠር ነው። ድርሰቱ በነቢዩ መሀመድ ሕይወት ላይ የተመረኮዘ ሆኖ በዚያው ዘመን በነበሩት የራሱ የሆኑ ግምታዊ ሁኔታዎች ላይ ተሞርክዞ የጻፈው ልበወለድ አራተኛ ድርሰቱ ነበር።


ይህም ድርሰት በዓለም ላይ በተለይም በሙስሊሙ ዓለም ውስጥ ጥልቅ ውዝግብ ፈጠረ። ያሳተመው ድርጅት ላይና በደራሲው ላይ ባሉበት እንዲገደሉ እነሱን መግደል በፈጣሪ ዘንድ ጽድቅ እንደሆነ ታወጀ። በተለይም የኢራኑ ታላቅ መሪ አያቶላ ሩሆላህ ሆሚኒ ሳልማን ሩሽድን ለገደለ ብዙ ሚሊዮን ዶላር እንደሚሸለም ተሰራጨ። መጽሐፎቹም በተወሰኑ ሙስሊም አገራት ውስጥ ተሰብስቦ እንዲቃጠል ተደረገ። የእንግሊዝ መንግስትም ሩሽድን በከፍተኛ ጥበቃ ተከላከለው። በዚሁ ድርሰቱ እና በሌሎች የልበወለድ ስራዎቹ የእንግሊዝ የክብር ማዕረግ አገኘ። ሩሽድ ተጨማሪ ድርሰቶችን እየጻፈ ነገሮች ሁሉ ተረስተው ዓለም በየጊዜው በሚለዋወጥ የፖለቲካ ለውጥ ሲተረማመስ የሳታኒክ ቬርስስ ጉዳይ ተረሳ። መጽሀፉም ዛሬ በዓለም ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተሰራጭቶ ተነባቢ ሆነ።


ዛሬ የሩሽድ የሳታኒክ ቬርስስ ልበወለድ መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን ለሁለተኛው ዓለም ጦርነት መሰረት የሆነውን ስለ አራያን ዘር በዓለም ላይ ታላቅነት ይዞ የተነሳው የጀርመን ሶሻሊስት ፓርቲ ወይም የናዚ ፓርቲ ንድፈ ሃሳብ ለሃምሳ ሚልየን ሕዝብ እልቂት ምክንያት የሆነው መጽሐፍ በሌላው ዓለም ቀርቶ በራሱ በጀርመን ላይብረሪ ጭምር እንደሚገኝ ሊታወቅ ይገባል። ሰዎች የነበረውን መጥፎና እልቂት ቀስቃሽ፤ ለብዙ አይሁዳውያን ዘር መጥፋት መነሻ የሆነው ጽሁፍ እንኳን ቀጣዩ ትውልድ ወደዚህ ሁኔታ እንዳይመለስ ትምህርት እንዲያገኝ እንዲጠፋ አልተደረገም።


ይህንን ምሳሌ ያቀረብኩትና ስጠቅሳቸው የነበሩት ሁኔታዎች በመደገፍና ጥሩነታቸውን ለመግለጽ አይደለም። አንባቢ እንዲገነዘብልኝ የምፈልገው መጽሐፎች ጥሩም ይሁኑ መጥፎ የራሳቸውን ጥሩና መጥፎ አሻራ ጥለው እንደሚያልፉ ለመጪው ትውልድ ትምህርት አግኝቶ መጥፎውንና ጥሩውን በራሱ ጊዜ እንዲለይ ለማሳየት ነው።


ከዚህ ተነስቼ ስለማዶላ መጽሐፍ ቀደም ባሉት ጽሁፎቼ ውስጥ ማለት የምችለውንና ጥሩና መጥፎ ጎኑን በዚያ ላይ ያለንን አቋም ግልጽ ስላደረኩኝ እንደጋሞ ምሁር ነን ባይ መደጋገሙ አንባቢን ከማሰላቸት ውጪ አስፈላጊ አልመሰለኝም። ማዶላ ከላይ ከጠቀስኩት ምሳሌዎች ጋር በደረጃም ሆነ በታዋቂነቱ የተመጣጠነ ነው የሚል እምነት የለኝም። ሆኖም ግን ከአካባቢያችን አንጻር በተጣመመም ሆነ በቀጥታ እንደመጽሐፍ የታየ በመሆኑ የተበላሸውን በራስ ችሎታና ጥረት ለማስተካከል መሞከር አግባባዊ አካሄድ እንደሆነ ለማሳየት ነው። ታግሶ ግን መጽሐፉን በአካል አግኝተህ ያነበብክ አይመስለኝም። በመጽሐፉ ውስጥ ስለጋሞ አለመኖር የሚያወራው አንተ እንደጠቀስከው በገጽ 69 ሳይሆን በገጽ 167 እና 168 ላይ ብቻ ነው። ከግማሽ በላይ የደብዳቤ ጥርቅም የሆነው የታደለ መጽሐፍ ውስጥ በሁለቱ ገጾች ውስጥ ብቻ ስላለ ሌላውን በሙሉ ማውገዙ አስፈላጊ አይደለም። በእኛ ደረጃ ሲታይ ደግሞ ማንም ስለራሱና ስለአካባቢው ምንም ነገር በመጽሐፍ መልክ ባላወጣበት ሁኔታ በውስጡ ሰውን የሚያስቆጡ ነገሮች እንዳሉ ሆኖ ጥሩ ነገሮችም ያሉ በመሆኑ እነዚያ ስህተት የሆኑት ሁለት ገጾች እንዲታረሙ ከማድረግ ውጪ ሌላው ትርምስና ሽማግሌዎችን ማንከራተት ዋጋ አያስገኝም የሚል አስተያየት አሁንም አለኝ። ስለሆነም ከዚህ ጽሁፌ በኋላ በዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጥም። ዶርዜን የሚመለከት ስላልሆነ።


ታክሶ ስለዶርዜ ጉዳይ ያለፈውን የደገሙና በተጨማሪ አሁንም ምንም ፋይዳ የሌላቸውንና ሰውን ሊያስረዱ የማይችሉ ጽሁፍ ያወጣኸውን አይቻለሁ (ሰንደቅ ጋዜጣ ህዳር 15 2008 እና ታህሳስ 13 ቀን 2008) አንብቤያለሁ። ለመግቢያነት ብለህ የብሄር ጎሳና የዘር ሀረግ በማለት ያቀረብከው በበቂ ለመተንተን የቻልክ አልመሰለኝም። አንባቢን ለማሳመን የእንግልዝኛ ጽሁፍም አክለሀል። እንደጸሐፊ ግን ከምን መጽሐፍ ውስጥ የማን እንደሆነ የጻፍከውን ጽሁፍ ያገኘህበትን ባለቤቱን መጥቀስ ነበረብህ። ባለቤቱን አለመጥቀስ የንብረት ዝርፊያ እንደሆነ ሳታውቅ ቀርተህ አይመስለኝም።


የኢፌድሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 39/5/ ስለብሄር ብሄረሰብና ህዝብ የሚለው ነገር አለ። በሌላ በኩል ብዙ ማርክሲስት ጽሁፎች nations ብሔር, nationalities ብሄረሰብ ለሚሉት ማህበራዊ የእድገት ደረጃዎች ለመግለጽ ፈልገህ ከሆነ በሁለቱ መካከል የማህበራዊ የእድገት ልዩነት እንዳለ የተገነዘብክ አይመስለኝም። የመጀመሪያው የእድገት ደረጃ ውሰጥ ያሉ ሕዝቦች እድገቱ ከሁለተኛው የተሻለ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ደረጃው ወደ ኢንዳስትሪ ያደገና በመንግስት ደረጃም ራሱን መስርቶ መኖር የሚችል የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኝ ሕዝብ ነው። ሁለተኛው ግን በአብዛኛው የኢኮኖሚ እድገት ደረጃው ራሱን ችሎ መንግስት መስርቶ ለመኖር ያልፈቀደለት ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር ተባብሮና ተቀናጅቶ የጋራ እድገት ሊያመጡ የሚችሉ ሆኖም ግን በማህበራዊ እድገታቸው ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር በባህልና በአስተሳሰብ በስነልቦና አንድ በመሆንና በመዋዋጥ የጋራ የሆኑ እሴቶችን በመፍጠር ወደብሄር ደረጃ በማደግ ራሳቸውን ችለው መንግስት መመስረት የሚችሉ ሕዝቦች ናቸው። በአገራችን ደረጃ በመጀመሪያው የዕድገት ደረጃ ላይ የደረሰ ማን እንደሆነ የትኛው ሕዝብ እንደሆነ ለአንባብያን እተዋለሁ። በጽሑፍህ ውስጥ nationalities ብሄረሰብ ያነሳኸው ነገር ባለመኖሩ በእነዚህ የማህበራዊ የእድገት ደረጃዎች ማለትም በብሔርና በብሔረሰብ መካከል ያለውን ልዩነትና አንድነትን ልትገለጽ አልቻልክም።


ስለነገድ /tribe/ና ጎሳ /clan/ አንስተህ ከዶርዜ ሁኔታ ጋር ወይም ዶርዜን ጋሞ እንደሆነ ለመግለጽ እንደ ማህበራዊ እድገት ትንታኔ አድርገህ ይሆን በሌላ መልክ ለመግለጽ አልገባኝም አንስተሀል። እንደዚህ ዓይነት ምደባ በአብዛኛው የሚሰራው በታደጊ አገራት ሳሆን አውሮፓውያን ከማህበራዊ ዝቅተኛ እድገት ጋር አያይዘው የሚያነሱት ነው። ጎሳ በነገድ ውስጥ የአንድ ሰፋ ያለ ቤተሰብ መሆኑን ይገልጻሉ። ነገድ ደግሞ ብዙ ቤተሰቦችን የያዘን ሕዝብ የሚገለጽ አድርገው ይመድቡታል።


ታግሶ ንድፈ ሀሳቡን ወደኛ በመሳብ ነገድን ደሬ በማለት ስትገልጽ ጎሳን ደግሞ ኦሞ በማለት ገልጸሀል። ከገለጽከው አገላለጽ ውስጥ አንድ እውነት አለ። አንድ ኦሞ የሆነ እርስበርሱ አለመጋባቱን። ታዲያ ጋዎማላ በዶርዜና በጋሞ ውስጥ ብቻነው ያለው? ሌሎች በወላይታ በጎፋና በዳውሮ ላለመኖራቸው ምንድነው ማረጋገጫህ? ወይስ በሁለቱ በዶርዜና በጋሞ ውስጥ ስለሚገኙ ሁለቱ የአንድ ጎሳ ዘሮች ስለሆኑ አንድ ናቸው ለማለት ስለፈለክ ነው? ይህም ሆነ የተለያዩ ሌሎች ኦሞዎች በአምስቱም ብሔረሰቦች ያሉ መሆናቸውም ግን እንደ አውሮፓውያን ክላን ወይም ጎሳ በአንድ አካባቢ ተሰባስበው የሚገኙ አለመሆናቸው ሲታይ የሚያስክድ ትንታኔ አይደለም። ነገድ /tribe/ን ደግሞ ደሬ ብለህ ለማቅረብ ሞክረሀል። ጎሳ በነገድ ውስጥ ያለ የአንድ ቤተሰብ ስብስብ ነው ካልክና ይሄው ጎሳ በነገድ ውስጥ ያለ ስብስብ ከሆነ በእኛ አካባቢ የህዝብ ሁኔታ ጋር ሊሄድ አያስችለውም። ሊሄድ ከቻለም ደግሞ አምስቱን ብሔረሰቦች ውስጥ እነዚህ ጎሳ ያልካቸው ተበታትነው ስለሚገኙ /ጋሞ፤ ጎፋ፤ ወላይታ፤ ዳውሮና ዶርዜ/ (ኦሞ እነዚህ የአምስቱ የጋራ እሴት ነው) ለየብቻ ብሄረሰብ ሳይሆኑ አንድ ነገድ ናቸው ማለት ነው። ለዚህም ያቀረብከው ትንታኔ የሚያሳየው ከኦሞ የጋዎማላ ሆነ የሌሎች ኦሞዎች እንደ አውሮፓውያን አንድ ቦታ ሳይሆን በተበታትነው ከመኖራቸው ጎሳ ነው ለማልት አያስችልም። ስለሆነም nations ብሔር, nationalities ብሄረሰብ በሚል የሚገለጸው ለአተናተን አመቺ በመሆኑና ጋሞም ሆነ ዶርዜ nations ብሔር ደረጃ እድገቱ ያልደረሰ ሆኖ nationalities ብሄረሰብ በሚለው ቢገለጽ የሚያስኬድ መሆኑን ነው። ከዚያ በታች ግን ሊሆን የሚችለው የእድገት ደረጃ ማህበረሰብ (community) ሆኖ ከዚያ በታች ቤተሰብ (family) በመባል ቢቀርብ የተሻለ ያስኬዳል እላለሁ። ስለሆነም ዶርዜን ብሔረሰብ ላለማድረግ የምታነሳው አገላለጽ ወደስህተት እየከተተህ ብቻ ሳይሆን አንተ ተደናግረህ አንባብንን እያደናገርክ መሆኑን ነው። ስለሆነም ጎሳና ነገድ ብሎ የማህበረሰብ የእድገት ደረጃ በአካባቢያችን በአሁኑ ጊዜ ለመግለጽ አንችልም።


ታግሶና የጋሞ ምሁር ነን ባዮች ዘንድ ያለ ችግር የተጻፉ ጽሁፎችን በስርዓት አለማንበብ እንደሆነ ከአቀራረባቸው እያየሁ ነው። ወይም ስለዶርዜ የሚጻፍ ጽሁፍ ለማንበብ ፍላጎት አለመኖር ወይም የቅናት መንፈስ እንዳለባቸሁ ይታወቃል። ዶርዜ ብሔረሰብ እንደሆነ በተለያዩ ማሳያዎች ለማሳየት ቢሞከርም ለማየት ፍላጎት የላችሁም። ዶርዜ ጋሞ አይደለም። በአገሪቱም ሕገመንግስት ከላይ በተጠቀሰው አንቀጽ መሰረትም የተጠቀሱትን አምስት መመዘኛዎች እንደሚያሟላ፤ በንጉሱ ጊዜ ከዚያም በደርግ ጊዜ በብሔረሰቦች ኢንስቲቱት ጥናት መሰረት ብሔረሰብነቱ የተረጋገጠ መሆኑን እንዲገባችሁ ፈቃደኛ አይደላችሁም። በሁለቱ ቆጠራዎች ውስጥ ያለው የዶርዜ ሕዝብ ብዛትም ጋሞን ጨምሮ ነው በማለትም ለመከራከር አልታፈረም። ጋሞ በራሱ ኮድ 74 የተቆጠረና ዶርዜ ደግሞ በራሱ 73 ኮድ መቆጠሩን በአግባቡ አለመረዳት ችግር ይመስላል። ከዚህ ቀደም በምንም አይነት ጋሞ ዶርዜ ነኝ ተብሎ ያልተቆጠረ ሆኖ ዶርዜም ቢሆን በጋሞነት የእናንተ ባለስልጣናት ባደረጉት ጭፍለቃ ምክንያት በ1999 ቆጠራ በጫና ከመቆጠሩ ውጭ በራሱ ፈቃድ አላደረገውም።


በነገራችን ላይ ስለ ሸማ ስራ ዶርዜ በአገራችን ሸማን የፈጠረና የሸማ ስራን ወደ ጥበብነት የቀየረ ሕዝብ ነው ላልኩት አገላለጽ የሰጠኸው መልስ ችግርህ ምን ላይ እንደሆነ አሳይቶኛል። ስለሸማ የዶርዜ ፈጣሪነት ጥናቱን አለማንበብህ አያስገርምም። ሁልጊዜ የምትሰጠው አስተያየት ከዜሮ ተነስተህ እንደሆነ ስለማውቅ። በአገራችን በአሁኑ ጊዜ ሸማ የሚሰራው ሕዝብ ብዙ ሊሆን ይችላል። ሸማ ስራ ከአምስት መቶ አመታት በፊት ዶርዜ ውስጥ እንደነበር እንደማስረጃነት የጋሞጎፋ ሕዝቦች ታሪክ መጽሐፍ ላይ የተገለጸው በስህተት ከሆነ ልትነግረን ይገባል። ሌሎች ሸማ በአሁኑ ጊዜ የሚሰሩትን የጋሞ ብሔረሰብ አባላትንና አካባቢውን ጠርተህልኛል። እውነት ነው። በአሁኑ ጊዜ እነዚያ የጠቀስካቸው አካባቢ ሕዝቦች በስራው ላይ በብዛት አሉ። ሆኖም ግን ዶርዜ አባቶቻቸውን ወይም በአሁኑ ጊዜ በእድሜ የገፉ የጠቀስካቸው ማህበረሰብ አባላት ውስጥ በሕይዎት ካሉ ዶርዜ በፕቀና /የድውር ልጅ/ ስም አምጥቶ ስራውን አስተምሮ በሙያው ውስጥ ተጠቃሚ ያደረጋቸው መሆኑን በእድሜ የገፉትን መጠየቅና መረዳት ይቻላል። የዶርዜ ሕዝብ ለዚህ ውለታው ሊመሰገን ይገባ ነበር።እነዚህም የጋሞ ማህበረሰብ አባላት በዚህ ሙያ ከተሰማሩ ብዙ አመት አይሆናቸውም።


በረጅም የሸማ ጥበብ ስራው በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱትና የዶርዜ ብሔረሰብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ካበረከታቸው ስጦታዎች ውስጥ ጥቂቱን ለማሳየት ያህል ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል።
ከፈጠራቸው ጥበቦች ውስጥ ደግሞ ለሚያደንቃቸውና ለሚወዳቸው ነገሮች የሚያደንቃቸውንና የሚወዳቸውን ጥበብ ስሞች ሰጥቷል።ከእነዚህም ውስጥ፡-


በ1910ዎቹ አካባቢ "ዘውዲቱ" የሚል ስያሜ የተሰጠው ጥበብ በወቅቱ የንጉሰ ነገስቷ ዘውድቱ በተለይም ሴት በአገራችን መንገሷን በማድነቅ ለእሳቸው ክብር የተሰየመ ነበር።
ዶርዜ ገበያ ፍለጋ በወጣበት እግረ መንገዱን የሚያልፍባቸውን ቦታዎች ማድነቁን በሰራቸው ጥበቦች ገልጿል። "ሶዶ" የተባለው ጥበብ በወቅቱ በወላይታ ሶዶ ከተማ ሲያልፍ ከተማዋን ለማድነቅ የተሰራ ስጦታ ነበር።


"አዋሽ" የተባለው ጥበብ ደግሞ የአዋሽን ወንዝ የውሃ መጠንና ድልድዩን ለማድነቅ በጥበብ የገለጸው ስራ ነው።
"ቅዱስ ጊዮርጊስና ሜታ"የተባሉት ሁለት ፋብርካዎችን "ቢራ" በመባል ይጠራ የነበረው የፋብሪካዎችን አገልግሎት በማድነቅና የመጠጡን ዘመናዊነት ለመግለጽ የተሰራ ጥበብ ነበር።
"ብርዋንጫ" የተባለው ጥበብ አገራችን ኢትዮጵያ በሶስተኛው የአፍርካ እግር ኳስ በማሸነፍ ያገኘችውን ዋንጫ ለማስታወስ የተዘጋጀ ነበር።


"ስምንት ቁጥር" የተባለውን ጥበብ ታዋቂውንና ብርቅዬውን የእግር ኳስ ተጫዋች መንግስቱ ወርቁን ለማድነቅ የሚለብሰውን የማልያ ቁጥር ለማስታወስ የተፈጠረ ነበር።
“አየር መንገድ” ጥበብ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተናጋጆች የሚለብሱት የአገር ባሕል ልብስ ሆኖ ለአየር መንገዳችን ማስተዋሸናት ዶርዜ ያዘጋጀው ጥበብ ነው።
በ1960ዎቹ የአፍርካ አንድነት ድረጅት መቋቋሙን ለማስታወሻነት "አፍሪካ አዳራሽ" የሚል ስያሜ ያለውን ጥበብ ሰርተዋል።

 

"ፖስታ ቤት፣ ቴሌቪዥን" የተባሉ ጥበቦች በአገራችን አገልግሎታቸውን ለማስታወስ ዶርዜ የሰየማቸው ጥበቦች ነበሩ።
ሌሎች ከአገራችን ውጭ በዓለም ደረጃ ከፍተኛ አድናቆትን የፈጠረውን የሰው ልጅን በጨረቃ ላይ ያሳረፈን ድንቅ ስራ ለማድነቅ ዶርዜ በጥበቡ "አፖሎ" በሚል ስም ማውጣቱ ነው።


በቅርብ ጊዜ ትውስታ ደግሞ የኤርትራ መንግስት የአገራችንን መሬት በኃይል ለመያዝ ጦርነት የከፈተበትንና መንግስት ይህንን ወረራ ለመመከት ያወጣውን የዘመቻ ዕቅድ ለማስታወስ "ፀሐይ ግባት" የሚል ጥበብ ለማስታወሻነት አበርክተዋል።
ከላይ በቀረበው ጽሁፍ መሰረት ዶርዜ በአገራችን ሸማን የፈጠረ የሸማ ስራን ወደ ጥበብነት የቀየረና አገራችን በሌላው ዓለም ከምትለይባቸው መንገዶች ውሰጥ አንዱን መለያ የፈጠረ ሕዝብ ነው። ዶርዜ እንደብሔረሰብ ይህን ለአገሪቱ ያበረከተ ሕዝብ በመሆኑ ባለቤትነቱ የእሱ መሆኑና ዕሴቱ መሆኑ ይታወቃል። የጋሞ ብሔረሰብ የሸማ ስራ ጥበብ፤ (በጋሞ ጎፋ ዞን ማስታወቅያና ባህል መምሪያ ታህሳስ 2001 የተጻፈውን ገጽ 15) ላይ ተመልከት ከ500 ዓመት በፊት በዶርዜ እንደተጀመረ ይገልጻል። አለቆችህ ሳያስቡት የጻፉት አይመስለኝም። ወደገጽ 17 ስትሄድ ደግሞ በዙሪያው ያሉትን የጋሞ ብሔረሰብ አባላትን የሸማ ስራ ሙያውን ያስተማረው ዶርዜ እንደሆነ ታገኛለህ። በአገራችን ስለዶርዜ ሸማ ፈጠራነት የተለያዩ የውጭ ጻፊዎች የጻፉ መሆኑን ጭምር ይገልጻል። የእኛ ጥናት ደግሞ የሸማ ስራ ከዓመተ ዓለም ጀምሮ እንዴት እድገት እያሳየ መጥቶ በአውሮፓ ኢንዳስትሪ ሪቮሉሽን ዘመን እንዴት ወደ ኢንዳስትሪነት እንደተቀየረ ይገልጽና አገራችን በዚያ ዘመን ከውጪው ዓለምጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት በሌለበት ሁኔታ ላይ የሽማ ስራ ዶርዜ ውስጥ መኖሩ ሙያው ከውጪ አለመወረሱን የሚያስረዳ መሆኑን ጭምር በማመላከት ተብራርቷል። አሁን ሸማ የሚሰራበትን መስሪያ መሳሪያ ዶርዜ በራሱ እጅ ፈጥሮ እየሰራ የመሆኑ ተጨባጭ ማስረጃነትም ደስ ላይልህ ይችላል። መድገም ስለማያስፈልግ።


ዶርዜ የሸማ ስራንና ጥበብን ለመፍጠሩና በዚያ መወደሱ እንደሚከፋህና እንደሚያምህ አውቃለሁ። ሸማ ስራ እንደ ሸክላ መስራት እንደብረት ቅጥቀጣ አስነዋሪ ስራ ተደርጎ ይቆጠር በነበረ ዘመን አንተ ስድብ አስመስለህ ለመሳደብ እንደሞከርከውና ዶርዜ ቁጢት በጣሽ መባሉንና ሙያውን ፈጥሮና አሳድጎ እዚህ በማድረሱ ይኮራበታል እንጂ ተሸማቆም አያውቅም። ቀጥሎ ባወጣሔው ጽሁፍህ ውስጥ ደግመህ ሰድበሄናል ስድብ መስሎህ። ዶርዜ ዛሬም ቁጢት ይበጥሳል። በሙያው የሚገፉ ዶርዜዎች በቀጣይ ካሉም በእጁ ፈጥሮ ያሳደገውን ሙያውን ወይም ቁጢት መበጠሱን ይቀጥልበታል። እሱም አሰልጥኖ ለሸማ ስራ ያበቃቸውም ዘመዶችህም ቁጢት እየበጠሱ ናቸው። ወደፊት በሙያው የሚገፉም ከሆኑ ያልከውን ቁጢት እየበጠሱ ይኖራሉ። ዶርዜዎች ቁጢቱ እየበጠሱ ያገራችንን ባህላዊ እሴት የሆነውን ሸማ ጥበብ አሁን ወደደረሰበት ደረጃ አድርሰዋል። አንተ ዶርዜ ስላለመሆንህ አንዱ ማረጋገጫዬ ይሄው አባባል እንደስድብ መቁጠርህ ነው። ሌላው ማረጋገጫዬ ዶርዜ ስንት ቀበሌ እንደነበረና አሁን ስንት ቀበሌ መሆኑን አለማወቅህ ነው። የዶርዜ አካባቢ በፊት አማራንና ቦዶን ጨምሮ 6 ቀበሌ የነበረውን አሁን በእናንተ ድጋፍ 9 ቀበሌ መሆናችንን ገልጸሀል። ዶርዜ ነኝ እያልክ ዶርዜ ቀደም ብሎ በ15 ጭቃሹም ይተዳደር የነበረና አሁን በእናንተ ብርታት 12 ብቻ መሆኑን የማታውቅ ሰው አንባቢያንን ለማታለልና ዶርዜ ነኝ እያልክ ማምታታትህ ተጋልጧል። ለአንባቢም ዶርዜ እንዳልሆንክ በሁለቱ ማረጋገጫ ሰጥተሀል። ከዚህ በኋላ ዶርዜ ነኝ ብትል ማንም አይቀበልህም። ሌላው አሁን ዶርዜ ያለበትን የጨንቻ ወረዳ መሬት እንደማታውቅ ግልጽ አድርገሀል። ዶርዜን ጨምሮ ስምንት ደሬዎች አሉ በማለት። ማን ማን እንደሆኑ እንኳን የማታውቀውን። ስለአንድነት የኑዛዜው ፕሮፖጋንዳ ጥሩ ካድሬ ቢያስመስልህም የሚያሳምን አይደለም። በደል ያለበት አንድነት አንድነት እንደማይሆን ልገልጽልህ እወዳለሁ። ዶርዜ ባለፉት ሀያ አምስት አመታት በወረዳውና በዞኑ ተበድሎ ቆይቷል። የእድገት ደረጃው ከነበረበት እንዲያቆለቆለ የህዝቡ ኑሮ እንዳዘቀዘቀ አንተን ማስረዳት አይጠበቅብንም። ይህም በደል የደረሰብን ከአካባቢዊ የተለየን ብሔረሰቦች እንደሆንን በሂደት አረጋግጠናል። ማንነታችንን ከመጠየቃችን በፊት ያገኜነው ነገር ምንም የለም። ጥያቄችንን ካቀረብን በኋላ ግን ምን ጥቅም እንዳገኜ መግከለጽ አስፈላጊ አይደለም። ህዝባችን አንተ እንደምትለው በቁጥር አነስተኛም ቢሆን አንድ ሆኋዋል። አንድነት የጥቅም መናሻ ነውና። ዶርዜ ተጠቃሚ ነበር ላልከው ሀሳብ ማሳያ ማቅረብ አልቻልክም።


ዛሬ ዓለማችን በቴክኖሎጂ መጥቆ ባለበት ዘመን አንተ ሸማ ስራ ፈጣሪ ነን ትላለህ ብለኸናል። ልክነህ። ዓለም ከፍተኛ እድገት እያሳየ እንደሆነ እንግባባለን። ነገር ግን ቴክኖሎጂው ያፈራውን የአውሮፓ ወይም የህንድ ጨርቅ መልበስ የአገራችን የኢትዮጵያ ባህላችን ሊሆን እንደማይችል የግንዛቤ ጉድለት አለብህ እላለሁ። የሸማ ስራና ጥበቡ ውበቱና ማማሩ በቴክኖሎጂ ታግዞ መሰራቱ ሳይሆን እንደ ስዕልና ቅርጻቅርጽ ጥበብ በእጅ መሰራቱ እንደሆነ አልተገነዘብክም። ዶርዜዎች የሸማ ስራና የሸማ ጥበብ ፈጣሪ መሆናችን እሴታችን ነው ማለት የዓለምን ቴክኖሎጂ ወጣቱ እንዳይገነዘብ የሚያደርግ ወይም ሕዝቡን ወደኋላ የሚያስቀር እንደማይሆን አጥተኸው አይደለም።


"የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ" ይላል ተረቱ። ባለፈው የደቡብ ክልል የሰጠውን መልስ ጉዳይ ለጠየከኝ ጥያቄ "የብሄረሰባዊ መብትን መንግስት ወይም ሌላ አካል በችሮታ መልክ የሚሰጥ ጉዳይ ወይም የችሮታ ዕቃ አይደለም። ሕዝቦች ከቤተሰብ ጀምሮ በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ በጋራ ባሕላዊና ፖለቲካዊ ዕሴታቸው አንድነት ኖሯቸው በዚሁ ከሌሎች ጋር ያለውን ልዩነትና አንድነት አውቀው ራሳቸው ሕዝቦች ብሔር ወይም ብሔረሰብ ነኝ ብለው የሚወስኑት እንጂ። የዶርዜ ሕዝብ ለጠየቀው ጥያቄ ምክር ቤቱ እውቅና ሰጠ አልሰጠ በምንም አይነት ሁኔታ ዶርዜ እራሱን የቻለ ብሄረሰብነቱን ጠብቆ ይኖራል።" በሚል መልስ ሰጥቼህ ነበር ። አሁንም ይሄውነው መልሴ። ክልሉን የጠየቅነው በጽሁፍ ነው። ክልሉ መልሱን በጽሁፍ እስኪሰጠን ትግላችን አይቆምም።


ጥቁሩን ነጭ ነጩን ጥቁር ብሎ በቃል መዋሸት ችግር የለውም ምንም የሚጨበጥ ነገር ስለሌለው። ወረቀት ላይ ያለን ግን መዋሸት አይቻልም። ታደለ "በዶርዜ ተወላጆች ስብሰባ ላይ በተለያየ ጊዜ መጥተው እንደነበረና ምክር ይሰጡ እንደነበረ አውቃለው።ከአዲስ አበባ ተነስተው ዶርዜ ድረስ ሔደው ሲመክሩ እንደነበር በአንደበታቸው ሲናገሩ ሰምተናል።" በማለት በጽሁፍህ ውስጥ የሚረባ ውሸት ባኖርም የማረባ ውሸት ዋሽተሀል። ዶርዜ ለሚያደርጋቸው ድርጊቶች ምንም መካሪ እንደማያስፈልገው ቀደም ብሎ ሌላውን ሲያማክር እንደነበር ገልጫለሁ። በምትላቸው ወይም አንተ ብቻ በምታውቀውና የዶርዜ ሕዝብ በማያውቀው ስብሰባዎች መጥተው ሊሆን ይችላል። ማንም ዶርዜ ታደለን አይቶት አያውቅም። ዶርዜ ድረስ ሔዶም ለመምከር ዶርዜ የእሱ ምክር አያስፈልገውም። መጥቶም አያውቅም። ዘመኑ የውሸት ዘመን ቢሆንም እንደዚህ አይኑን ያወጣ ውሸት ከአንተ አይጠበቅም።


ማንም የማንንም ሕዝብ መብት መንካት አይችልም።ጋሞ ቋንቋ የለውም ያልኩበትን ቦታ በጽሁፌ ውስጥ ልታሳየኝ አትችልም። ዶርዜ የራሱ ቋንቋ እንዳለው ጋሞም የራሱ ቋንቋ አለው ብያለሁ። ስለሁለቱ ቋንቋዎች ልዩነትና አንድነትም ገልጫለሁ። ዶኮ ዶርዜን በድሏል ያልኩበትም በጻፍኳቸው ጽሁፎች ውስጥ የለም። የአካባቢ ወሬ እየቀዳሕ መንዘት ምንም ጥቅም አይሰጥህም። "ዛሬ ጋሞ የሚባል ቀበሌ ሳይኖር የማንነት መገለጫና የራሱ ቋንቋ ያለው ሕዝብ ሊሆን አይችልም።" ካለው ለታደለ መልስ መስጠት ሲያቅት የአንባብያን አስተሳሰብ ወደሌላ ሰው ለማላከክ አትሞክር። በውቅቱ የነበረኝን አቋም ገልጫለሁ። አንብበህ መረዳት ካልቻልክ የሻመና ችግር አይደለም። ስለጠባብነትና ስለመስፋት ስለትምክተኛና ስለማይመካ ያለከው ነገር አለ። ይህንን ለሌላ ጊዜ እበትህ አቆየው። ከጋሞ ውስጥ ለምሳለ ሻማ ምሔረሰብ ነኝ ብሎ ቢነሳ ጠባብ ሊባል ይቻላል ምንም መነሻ ስለሌው። እኛ ግን ባለመረጃዎችና ባለማስረጃዎች ነን።


በማጠቃለያነት ዶርዜ ለጠየቀው ጥያቄ ምን ጥቅምና ጉዳት እንዳለ ለይቶ የተነሳበት ጉዳይ ነው። እስከ 1999 የክልሉ መስተዳደር ከአቶ ሽፈራው ቢሮ የጭፍለቃ ደብዳቤ እስኪወጣ ድረስ ዶርዜዎች በብሔረሰብ ደረጃ ነበርን። አንተ እንደምትልው እንደብሔረሰብነት በነበረ ጊዜ ስለምትለው የስልጣን ወንበር አስቦም አያውቅም። ወደፊትም መብትን ከመጠየቅና ከማግኜት ውጪ አንተ ያተትከው ወንበር ለዶርዜ ምኑም አይደለም። ይህ ተራ ፕሮፖጋንዳህ ዶርዜ ቀደም ያውቀዋል። የእናንተ ጩኸትና ጫጫታ ሁልጊዜ ከስልጣንና ከወንበር መያዝ ጋር የተያያዜ መሆኑ ያሳዝናል። በዶርዜ ሕዝብና በጋሞ ምሁራን ነን ባዩች መካከል ያለው ልዩነት አንድና አንድ ነው። እናንተ ዶርዜን ጋሞ አድርጋችሁ የዶርዜን መለያ እሴቶቹን የጋሞ ለማድረግ ነው። የዶርዜ ህዝብ ደግሞ እኔ ጋሞ አይደለሁም ራሴን የቻልኩኝ ብሔረሰብ ነኝ እያለ ነው። ስለሆነም የእኔ የዶርዜ እሴቶቼ የራሴ ናቸው፤ ጋሞ የራሱ ብሔረሰባዊ እሴት አለው እያለ ነው። ለዚህ ሂሳብ ሲባል በምንም ዓይነት ሁኔታ ዶርዜ ተጨፍልቆ የጋሞ ብሔረሰብ አካል አይሆንም። አሁንም በተጨባጭ ዶርዜን ጋሞ የሚያደርጉ ምክንያቶችን ይዛችሁ ቅረቡ እላለሁ። በጉልበትና በተደጋጋሚ "ዶርዜን ጋሞ ነህ" በማለት ዶርዜ ጋሞ አይሆንም። በጋሞ ሕዝብና በዶርዜ ሕዝብ መካከል በብሔረሰባዊ ማንነቱ ዙሪያ የሚተዋወቁ ስለሆነና ዶርዜም የነበረውን መብቱን እንደጠየቀ ያውቃሉ። ይህን መብት መጠየቅ ደግሞ ሕገመንግስታዊ ነው። ይህ ጥያቄ በህዝቦቹ መካከል የነበረውን ቅርበት የሚጎዳ አድርጋችሁ መንዛታችሁ ለስልጣናችሁ እንጂ ለሕዝቦቹ አይጠቅምም። ዶርዜና ጋሞ ቀድሞም አብረው እንደኖሩ ወደፊትም አብረው ጎን ለጎን እየተተጋገዙ ይኖራሉ።n

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1604 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 154 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us