የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም

Wednesday, 09 March 2016 13:41

ሰለሞን አበበ

 

አባቶቻችን አንድን እውነት የሚገልጹበት ዘመን ተሻጋሪ ተረትና ምሳሌያቸው ዘወትር ያስደምመኛል ።
ለዚህ ማስታሻዬ ርእስ አድርጌ የተጠቀምኩበት ምሳሌያዊ መገለጫ ከአባቶቼ ተውሼ እንጂ እኔማ ምኑን አውቄው!
ለርዕሴ ዋና ምክንያት የሆነኝ የታናሽ ወንድሜ ዘወትር በስራው አለመደሰትና መማረር ሲሆን ይበልጥ ደግሞ ወንድሜ የሚሰራበት የትራንስፖርት ሴክተር አስታዋሽና ተመልካች አለመኖሩን ስረዳ በመሆኑ ይህን ሀሳቤን ከወገን ጋር መቋደሱን መርጬ ነውና አቃናብሬ ትዝብቴን የኩከት ለሀገር እድገትና ለሴክተሩ መቃናት በተለይ በሙያው ላይ የተሰማራችሁ ዜጎች አስተያየታችሁን እጠብቃለሁ ደግሞም ግዴታና ሀላፊነት አለባችሁ ብዬ በጽኑ አስባለሁ።።


ታናሽ ወንድሜ የመጀመሪያውን ዲግሪ እንዳገኘ ነበር ወደ ስራ የተሰማራው። ምንም እንኳ ቡራኬ ሰጥቼው ስራውን ባለመጀመሩ ለሚገጥመው የዘወትር ችግርና ስራው ለፈጠረበት ጭንቀት ኃላፊነቱን የሚወስደው እሱ ነውና ለዚህ ተጠያቂ አይደሁም። እንደ'ኔማ ሃሳብ በጤና ሙያ ተሰማርቶልኝ ዶክተር ሆኖልኝ የወገኖቹን ህመም ቢታመም ነበር።


በትራንስፖርት ዘርፍ ለመሰማራት ያነሳሳው ወይም የማረከውን ምክንያት አዋቂው እሱ ብቻ ነው። ሆኖም በሙያው በቆየበት አምስት አመት ሙሉ በንዴትና በብስጭት ዘወትር በሀሳብና በጭንቀት ነበር ያሳለፈው። ወይ እራሱን ችሎ ከቤት አልወጣ እኔው በሰራሁት ቤት በደባልነት ንዴቱንና ብስጭቱን እየሰማሁ አብሮኝ ይኖራል፡: ያውም ከኔ እየተበደረ ።


ታናሽ ወንድሜን ከዚህ ዘርፍ እንዲወጣ ብመክረውም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ችግሩ ተባብሶ ከአቅም በላይ ከመድረሱ በፊት ማማከር ስነበረብኝ ለተከታታይ ሰባት ቀናት ጊዜ ወስጄ ስለዘርፉ በቂ ግንዛቤ እንዳገኝ ባደረኩት ሙከራ መሰረት አስከፊነቱንና በዚህ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ መቆየት እንደሌለበት በመረዳቴ ታናሽ ወንድሜን ከዚህ እጅግ አስከፊ ዘርፍ ውስጥ ለማስወጣት የተቻለኝን ለማድረግ ወሰንኩ። እንደ አጋጣሚ የአመት የእረፍት ፈቃድ ላይ ስለነበርኩ የማውቃቸውን አምስት የማህበራት ተጠሪዎችን፤ ስድስት ትራንዚተሮችን፤ ሶስት አስመጭና ላኪ ድርጅቶችን፤ የመንገድ ትራንስፖርትንና የኢባትሎአድ ጥቂት ሠራተኞችን በሚገባ አነጋግሬያለሁ፣ የሰነድ ማስረጃም አግኝቻለሁ። ወንድሜ በዚህ ሴክተር ዋጋ ከፍሎ የሚስተካከል ቢሆን ቢቆይ ግድ አልነበረኝም፤ ግን በፍጹም ሊታሰብ እንኳ የሚቻል አልነበረም።


ይህን ማስታወሻ የምታነቡ በዘርፉ የተሰማራችሁት ሁሉ ሃሰት አስተላልፌ ከሆነ ልትወቀሱኝ ይገባል። ያስቀረሁት እውነት ካለ ጉድለቴን ልትሞሉ የግድ ይላችኋል ምክንያቱም ከኔ የተሻለ እውነቱ እናንተ ጋር ስላለ፡፤


ወንድሜ የተሰማራበት የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ትራንስፖርት ዘርፍ በመሆኑ የዚህ ዘርፍ አደራጅ በስም እንጂ በአካል መኖሩ የሚያጠራጥረው የመንገድ ትራንስፖርት በላስልጣን በትራንስፖርት ማህበራት ላይ የሚደርስውን በደልና ስቃይ እንኳን ሊመክት ሌላው ተጨማሪ ስቃይ መሆኑን ከደረስኩበትና በተለይም ከህዝብ ማመላለሻ ላይ ያለውን የህዝብ መከራ በመረዳቴ ሌላ ተጨማሪ ማስረጃ አላስፈለገኝም።


…….በአንድ ወቅት ለስብሰባ ከአንድ ባለስልጣን ጋር ወደ ውጭ ሀገር የመሄድ እድሉ ገጥሞኝ ስለነበር ይህንን የትራንስፖርት ዘርፍ ችግር አወያይቻቸው አሳዛኝ መልስ ነበር የመለሱልኝ…. እንዲህ አሉኝ …. በደርግ ጊዜ የትራንስፖርት ዘርፉ ጠንካራና በሙያው የበሰለና የስራ ልምድና በቂ የሰው ኃይል ያለበት ነበር። ሆኖም የተሻለ አድርገን እናደራጃለን ስንል ብዙ አፍርሰን ስለነበር ያፈረስነውን ዳግም መገንባት አቃተን:: አማካሪዎቻችን አሳሳቱን ዛሬም እያሳሳቱን ተቸግረናል:: የዚህን የትራንስፖርት ዘርፍ ችግር በሚገባ መንግስት ያውቀዋል። ይህን የባህርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት በመልካም አስተዳደር ችግር እንደተዘፈቀ የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ ሰብስበናል ግን የሚያስከትለውን የተወሰነ ጊዜ ችግር የምንቋቋምበት ስልት ስላላዘጋጀን ለጊዜው አለመንካቱና እያዩ ዝም ብሎ ማለፉ ግን ከሀሉም ባለይ የተሻለ ሆኖ አግኝተናዋል።


ይህ ድርጅት የመንግስት የገቢ ምንጭ ስለሆነ ቅድሚያ የምንሰጠው ደግሞ በመንግሰት ገቢ ላይ ነውና የሚያደርሰውን ችግርና በደል ላለመናገር ዝምታ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ አግኝተነዋል። ስለዚህ በዚህ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማራው በተለይም የተሸከርካሪ ባለንብረቶች ችግሩና ስቃዩን በሚገባ ስለተላመዱት ማህበራት ስለችግራችው ከመጩህ ሌላ የተሻለ አማራጭ እንደሌላቸው ስለምናውቅ hኃላፊዎቻቸውም ይህን ያህል የጠነከረ አቋም ስለሌላቸውና አንድነታቸው የተሸረሸረ መሆኑን ስለምንረዳ በመንግስት ህልውን ላይ ችግር ያመጣሉ ብለን ስጋትና ፍርሀት የለብንም። ግን ከዚህ የባሰ አታምጣ ብለን ነው ዝም ያልነው።


ማህበራትን እንዲያደራጅ የሰጠነውን ኃላፊነት በብቃት ያልተወጣውን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን መ/ቤትም መንጋጋ የሌላው አንበሳ አድርገን ያደራጀንበት በቂ ምክንያት አለን የተጠናከረ የትራንስፖርት ዘርፍና የተደራጀ የትራንስፖርት ማህበራት መኖር የሚያስከትለውን የፖለቲካ ጫና ከፈረንሳይና ከደበብ አፍሪካ ከኬንያ እና ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ስላለን ማጠናከሩ አስፈላጊ መሆኑን ብናምንበትም ጊዜው አሁን አይደለምና ዘርፉን ከነችግሩ ከነመከራው እያየን ማለፍ እንጂ ለማንካት ቢሞከር ተሳስቦ ፖለቲካውን በቀጥታ ስለሚነካ ዝምታን መርጠናል ብለው መለሱልኝ…..


እውነትም የባሰ አታምጣ። ይህ የትራንስፖርት ዘርፍ የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት ነው። የእድገታችን መሰረት ነው። መንግስት በተደጋጋሚ የሚያወጣቸው የትራንስፎርሜሽን እቅዶች ዋናው መሰረት የትራንስፖርት ዘርፍ ነው። ግን እውነቱ ይህ ሆኖ እያለ በተግባር እየታየ ያለው ግን ሌላ ነበር። ብለው እኛ የመንግሰት ባለስልጣን መመለሳቸውም ትዝ ይለኛል።


በርካታ የተሸከርካሪ ባለንብረቶች በስምሪት ወቅት የጫኑትን ጭነት ለማራገፍና ለመጫን የሚደርስባቸውን ስቃይና መከራ ለመግለጽ አስቸጋሪ ነው።በትራንስፖርት ማህበራት ላይ ዘወትር የሚያጋጥመው ችግር በራሱ የሴክተሩን ብልሹነት ማሳያ ነው። በትራንስፖርቱ ዘርፍ ተጠቃሚ የሚሆኑት ጥቂት በኮንትሮባንድ ስራ ላይ የተሰማሩት ካልሆኑ በስተቀር አሁን ባለው የጭነት ታሪፍና የገበያ ውድድር አሸናፊ ሆኖ ለመወጣት በራሱ አስቸጋሪ ነው። በዚህም የተነሳ እንደ ወንድሜ ያሉ ኃላፊዎች አበሳቸውን የሚያዩበት በጭንቀት ተወጥረው ኑሮአቸውን በሚገባ መምራት አቅቷአቸው ለዘመድና ለቤተሰብ መከራ የሆኑ በርካቶች ናቸው። በዚህ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት የሚያስብ ካለ ታሪኩን የማያውቅና ወደ ጅቡቲ ወደብ ተመድቦ በመሄድ የደላላ ስራ ለመስረት የወሰነ ብቻ ነው።


ይበልጥ አሳዛኙ ደግሞ በሞኖፖል ሥራውን ከያዘው የባህር ትራንስፖርት ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት ከትራንስፖርት ማህበራት ጋር ያለው የሻከረ ግንኙነት ነው። ከእሾህ የተጠጋ ቁልቋል ዘወትር ያለቅሳል እንዲሉ ማህበራት የውዴታ ግዴታ ስላለባቸው ከዚህ ድርጅት ጋር የመስራት ውስጣዊ ፍርሀት ስለሸበባቸው አበሳቸውን ያዩበታል። ደግሞም እውነትነት አላቸው። ምክንያቱም በዚህ ድርጅት ያልተመዘገበ ተሸከርካሪ ሰሌዳ ወደፊት ከጅቡቲ ማንኛውንም ጭነት መጫን አይችልም የሚል በገሀድ የተነገረ እውነት አለ።


ድርጅቱ የባእድ ሀገር ድርጅት ወይም ማህበራትን ለማሰቃየት የተቀቋቋመ እስኪመስል መንግስት የዚህን ድርጅት በደል እያወቀ ዝም ያለው ድርጅት መሆኑ ነው።
አጠቃላይ የሀገሪቱ ነጋዴዎች ጭነታቸውን ከውጭ ማስመጣት የሚችሉት በዚህ ድርጅት መርከብና ተሸከርካሪ ብቻ ነው። ስለጭነታቸው የሰነድ ክትትል መጠቀም የሚችሉት በሌሎች የግል ትራንዚተሮች ሳይሆን በዚህ እራሱን ባገዘፈ ድርጅት ብቻ ነው። ስለዚህም ይህ ድርጅት ነጋዴውንና ትራንስፖርተሩን አስገድዶ ማሰራት ከቻለ፤እጅ ሲጠመዝዝ ማንም ከልካይ ከሌለው ወደፊት ደግሞ የግል ተሽከርካሪዎችን ንብረት መውረስ እችላለሁ እንደሚል ጥርጣሬ አያስገባም። ምክንያቱም የመንግስት ድርጅት ነዋ። በወንድሜ ንዴትና ብሥጭት እናደድ የነበርኩት ወንድሜ መናደዱ ትክክል ሆኖ አገኘሁት። እኔንም ድርጊቱ አባሳጨኝ። የማህበራት አባላትንና የማህበሩ ኃላፊዎችን ከልብ ያደነቀኩት ይህ ሁሉ መከራና በደል ሲደርስባቸው አድማ ሳይመቱ፤ ስራ ሳያቆሙ፤ አመጽ ሳያስቡ፤ ይህን የህል ዘመን በትእግስትና በዘዴ መቆየታቸው ነው።


ማህበራትን ያደራጀው የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ከሚደርስባቸው በደል ሊያድናቸው አለመቻሉ ሳይሆን ሊከራከርላቸው አለመቻሉ አሳዛኝ ነው። የአህያ ባል ከጀብ አያስጥልም እንደሚባለው ይህም ባለስልጣን መ/ቤት ማህበራትን አደራጅቶ ህልውናቸው እንዳይናጋ የመጠበቅ ግዴታ ነበረበት። ሆኖም አንድ ድርጀት የፈለገውን ያህል በደል ሲያደርስ እንኳ ሊከላከል አለመቻሉ ግርምትን ይፈጥራል ።


ይህንን የሀገሬ ጉድ ለፓርላማ ምክር ቤት በሚገባ ከነማስረጃው ለማቅረብ ተዘጋጅቻለሁና እናንተ በዚህ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የምትገኙ ወገኖች አስፈላጊውን ማስረጃ በማቅረብ ትተባበሩኝ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ


የዚህ ድርጅት ጥቂት ኃላፊዎች የትራንስፖርት ኃላፊዎችን ከመናቃቸው በላይ የሚጋፈጣቸውን ኃላፊ ማህበሩን ከስምሪት ፕሮግራማቸው በማገድ ከስራ እንዲባረር ለማድረግ እንደሚችሉ በተግባር አሳይታዋል። በስብሰባ ላይ ስለእነሱ ድክመት የሚያነሳ ኃላፊ እንዳይኖር አኮላሽተውታል። ማህበሩን በማገድ ተሽከርካሪዎች ከስምሪት ፕሮግራም ዝርዝር እንዲወጡ ብላክ ሊስት በማስገባት አስመርረውት ማሩኝ ብሎ እንዲበረከክ ያደርጉታል። የሚገርመው እንደ አሽን ከፈላው የማህበራት ኃላፊዎች ሶስት የኢ.ባ.ት.ሎ.አ. ድርጅት ኃላፊዎች አምባገነንነት ደምቆ ይታያል።


የድርጅቱ ጥቂት ኃላፊዎች ማንንም አይፈሩም። አንድ ማህበር ስሙ ወይም የደረጃው ጥንካሬ ካስፈራቸው ወይም አካሄዱ ከደበራቸው ሰበብ ፈለገው ያግዱታል።በስብሰባው መድረክ እነሱ ተናጋሪ፤ እነሱ ደረጃ ሰጪ፤ እነሱ ተበዳይ፤ እነሱ የመልካም ስራ ተምሳሌት ሆነው ይቀርባሉ። መድረኩን በብቸኝነት ስለሚመሩት ይህንን የማህበራት ኃላፊ በባዶ ያንጫጩታል። ይዝናኑበታል። ማህበራት ስለገጠማቸው ችግርና መብታቸው እንዲጠበቅ ስለሚያቀርቡት ጥያቄ ሰሚ አያገኙም።


ታዲያ በዚህ ዘርፍ ከመስራት ቦዘኔነት በስንት ጠአሙ። የወንድሜ ቁስል ዛሬ ተሰማኝ ይህንን ጉዳይ በቀላሉ ላለመተው ከራሴ ጋር ቃል ገባሁ። በበሰለና በትእግሰት ጉዳዩን በመከታተል በሚኒስትሮች ምክር ቤት አማካይነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጉዳዩ እንዲደርስ በበኩሌ ጥረት አደርጋለሁ፤ እናንተም ተባበሩኝ።
ሰላም ለሀገሬ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
786 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 891 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us