የፈጠራ ውንጀላ ማካሄድ፣ ሠላማዊ ዜጎችን ማፈንና መግደል ይቁም

Wednesday, 16 March 2016 12:59

 

ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረንስ የተሰጠ መግለጫ

ምንም እንኳን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንም ሆነ የኦሮሚያ ከተሞች አዲሱ አወቃቀር በገጠመዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ምክንያት ሳይተገበር እንዲቆይ በኦህዴድ/ኢህአዴግ የተወሰነ ቢሆንም፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ ንቅናቄ የመጠንና የዓይነት ለዉጥ እያስከተለ ቀጥሏል። ገዥዉ ፓርቲም የችግሩ መንስኤ የኦሮሚያ ክልል አካሉ ኦህዴድ መሆኑን በሕዝብ ዜና ማሰራጫዎች ቢገልጽም፤ ነገር ግን ለጥፋቱ ይቅርታ እንደመጠየቅ ፋንታ ባለፉት አራት ወራት ዉስጥ ዉስጥ ብቻ ከ270 በላይ የኦሮሞ ዜጎች ተገድለዋል፤ የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎችን ጨምሮ ንፁሐን ዜጎች ታስረዋል፤ ከመኖሪያ ቀዬያቸዉ እንዲሰደዱ ተደርገዋል። ይባስ ብሎም፣ ጅራፍ እራሱ ገርፎ ለራሱ ይጮሃል እንዲሉ መንግስት ሠላማዊ የመብት ጥያቄ በአቀረቡ ዜጎች ላይ ያላንዳች ርህራሄ የጭካኔ እርምጃ መዉሰዱን እንዲያቆም ደጋግመን በመጠየቃችንና የሕዝብን ሠላማዊ የመብት ጥያቄ ደግፈን በመቆማችን የአህአዴግ መንግስት ባለሥልጣናት ድርጅታችንና አባሎቻችንን መክሰስ ገፍተዉበታል።

ኦፌኮ በሠላማዊ አግባብ ታግሎ ዲሞክራሲያዊ የሕዝብ መንግስትን ለመመስረት የሚታገል ፓርቲ እንጂ በሽብር ፈጠራ ሥልጣን ለመያዝ ዓላማና ዕቅድ የለዉም። ከዚህ መሠረታዊ ዓላማችን የተነሳም በአጠቃላይ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ፣ በተለይ ደግሞ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት በማግኘታችን ሁሉንም ዜጎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ የመንግስት ሥርአትን ዕዉን ለማድረግ የሄድንበት ርቀት የድሉ ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ አመላካች ነዉ። ዲሞክራሲያዊ የመንግስት አስተዳደር ዕዉን ከሆነ ደግሞ ሙሰኛነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት እና ከሕገ መንግስታዊ አግባብ ዉጭ ሥልጣን መያዝ ብቻ ሳይሆን ከሕገ መንግስታዊ አግባብ ዉጭ ሥልጣን ላይ መቆየትም የማይታለም ይሆናል። በፖለቲካ ልዩነት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን መወንጀልም በበኢህአዴግ አገዛዝ ላይ ያበቃል።

የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብታቸዉን ለማስከበር የሚያደርጉትን መነሳሳት ከሕገ መንግስታዊ አግባብ ዉጭ ሥልጣን የያዙም ሆነ ሥልጣን ላይ የቆዩት ኃይሎች ግን፤ ኦፌኮን የመሳሰሉ ሐቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሕዝብን ዓላማ ደግፈዉ ሲሰለፉ የገዥዉ መንግስት አባላት የአሸባሪነት ታፔላ ይለጥፉባቸዋል። ከፖለቲካ ጨዋታ ዉጭም ለማድረግ የማይሰጡት መግለጫ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።

በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ዉስጥም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚነሳሱ የሕዝብ ጥያቄዎች ሠላማዊ በመሆናቸዉ መንግስት ሕጋዊና ተገቢ መልስ መስጠት ኃላፊነቱና ግዴታዉ እንደሆነ ኦፌኮ ዛሬም ያምናል። ሠላማዊ ሰልፍ በወጡና የመብት ጥያቄ በሚያቀርቡ ዜጎች ላይ የሚተኩስ መንግስት ለሕዝብ መብት መከበር ደንታ እንደሌለዉ ከዚህ የበለጠ ተጨማሪ ማስረጃ የማያስፈልግና ፓርቲያችንና አባላቱ የሕዝብን ጥያቄ ደግፈዉ የተሰለፉ እንጂ የአሸባሪነት ታፔላ ሊለጠፍባቸዉ እንደማይገባ ሚሊዮኖች የሚመሰክሩት ጉዳይ ነዉ። የሕዝብን ሠላማዊ ጥያቄ ደግፌንና ዜጎች መገደላቸዉ፣ መታሰራቸዉ፣ መሰደዳቸዉ፣ መቁሰላቸዉ፣ መደፈራቸዉ፣ መንገላታታቸዉ፣ ወዘተ እንደማይገባ መቃወማችን በምንም ዓይነት መስፈርት አሸባሪ የሚያስብል አይደለም።

አሸባሪነት በፓርቲያችንም ላይ ሆነ በአባሎቻችንን ላይ መለጠፍን አጥብቀን እንቃወማለን። በሠላማዊ አግባብ ዲሞክራሲያዊ መንግስት እንዲቋቋም የመፈለጋችን ያህል የዜጎች ሕይወት በመንግስት ሠራዊት መቀጠፉን እናወግዛለን። በተለይ እስካሁን ከሁለት መቶ ሰባ በላይ ለተገደሉ ዜጎች የኢህአዴግ መንግስት ሙሉ ኃላፊነት መዉሰድ አለበት ብለን እናምናለን።

ስለሆነም፤ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ አባላትና ደጋፊዎች ሕዝባዊ ዓላማን አንግቤን የሕዝባችንን ሠላማዊ ጥያቄ እየደገፍን፤ አንደኛ ሠላማዊ የመብት ጥያቄ ባቀረቡ ሕዝቦች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ሕፃናትና አዛዉንቶች ላይ በጦር መሳሪያ የታገዘ እርምጃ መዉሰድን እናወግዛለን። ሁለተኛ በኢህአዴግ ባለሥልጣናት ክስ ሳንሸማቀቅ ትግላችንን እንደምንቀጥል ቃል እንገባለን። በዚህ አጋጣሚ ለምናራምደዉ የተቀደሰ ዓላማ መላዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ ከጎናችን እንዲቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

ለኦሮሞ ሕዝብ የመብት ትግል መልሱ የጠመንጃ አፈሙዝ መሆን የለበትም!

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረንስ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

መጋቢት 2 ቀን 2008

ፊንፊኔ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
532 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1013 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us