በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ምንነት

Wednesday, 16 March 2016 13:43

 

በህግ ጥናት፣ ማርቀቅ እና ማስረጽ ዳይሬክቶሬት

(ፍትህ ሚኒስቴር)

(….. ካለፈው የቀጠለ)

ለሽብር ተግባር የሚዉል በርካታ ገንዘብ ከወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ሊሆን እንደሚችል ይወሰዳል። ምንም እንኳን ሽብርተኝነትን በገንዘብ ለመደገፍ የገንዘቡ ምንጭ ምንም ይሁን ለሽብር ዓላማ የሚዉል ከሆነ ከላይ ባየነዉ ትርጉም መሰረት ሽብርተኛም ለመደገፍ እንደሚዉል የሚወሰድ ነዉ። ይሁንና ከተለያዩ የወንጀል ተግባራርት የሚኙ የገንዘብ ምንጮችን ህጋዊ በማስመሰል ሂደት ዉስጥ እያለፉ ለሽብር ዓላማ የሚዉሉበት በርካታ አመላካች ነገሮች እንዳሉ የሚወሰድ ሆኗል።

4ኛ ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሚጠቀሱ ዋና ዋና ጉዳዮች፣

4.1. በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን ለመከላከል ያሉ አጠቃላይ ጉዳዮች የወንጀሉ አፈጻጸም ዘዴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየረቀቀና እያደገ እንደመጣ የሚጠቀስ ነዉ። በታሪክ እንደ አዉሮፓ አቆጣጠር 1930 ዓ.ም የአሜሪካ ወንጀለኞች ከተለያዩ የወንጀል ተግባር ያገኙትን ወደ ሲዉዘርላንድ የሚገኘዉ ባንክ በመውሰድ እንደገና ከዛዉ ባንክ እንደብድር መልሶ በማምጣት የረቀቀ ተግባር መፈጸም የተጀመረዉ ህጋዊ የማስመሰል ዘዴ አሁን የፋይናንስ ተቋማትንና ሌሎች ትልቅ ገንዘብ ሊያንቀሳቅሱ የሚችሉትን ተቋማትን ጨምሮ በርካታ የኢኮኖሚ ሲስተሞች ያሉባቸዉን ሁሉ በመጠቀም ገንዘብ ወይም ንብረቱ ህጋዊ እንዲመስል ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል።

በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን ለመዋጋት በዋናነት ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች ዋንኛዉ ድርጊቱን እንደወንጀል በመፈረጅ ሊያጠፉ የሚፈልጉ ሰዎችን በማስጠንቀቅ ፈጽመዉም የተገኙ ሰዎችን ተገቢዉን ቅጣት እንዲያገኙ በማድረግ እራሳቸዉም ተምረዉ ሌሎችም እንዲማሩበት ማድረግ ነዉ። ሌላዉ ዋናዉ ቁልፍ ጉዳይ በድርጊቱ የተገኘዉን ገንዘብ ወይም ንብረት ከዛም ተያይዞ የመጣዉን የወንጀል ፍሬ ሁሉ እንዲወረስ ማድረግ ነዉ። ይህም ከወንጀል ተግባር የሚገኝ ምንም ትርፍ ሊኖር እንደማይችል በማሳየት መከላከል ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪም የፋይናንስ ስርዓት ዉስጥ ያሉ ማንኛዉም ተቋማት ለወንጀሉ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ደንበኞቻቸዉን በሚገባ የማወቅና በመለየት ህገወጥ ገንዘብ ወደ ዉስጥ እንዳይገባ መከላከል ሲሆን ጥርጣሬ ያለበት ግብይት የሚኖር ከሆነ ለሚመለከተዉ አካል ሪፖርት እንዲያደርጉ ማድረግ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪም ከፋይናንስ ዉጪ ያሉ በተለይ ከፍተኛ ገንዘብ የሚንቀሳቀስባቸዉ ተቋማት ልክ እንደፋይናንስ ተቋማት ደንበኞቻቸዉን ለይተዉ የጥንቃቄ ርምጃ ወስደዉ እነሱም ሁኔታዉን ዝግ የሚያደርጉበት እንዲሁም የሚያስጠረጥር ጉዳይ ካለ ሪፖርት የሚያደርጉበት ግልጽ አሰራር እንዲፈጥሩ ማድረግ የሚገባ መሆኑ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸዉ።

4.2. ከወንጀል ተግባር ጋር የተገናኙ ንብረትን ስለመዉረስ በአጠቃላይ ከወንጀል ተግባር ተግባር ጋር ግንኙነት ያለዉን የወንጀሉ ምንጭ የሆነዉን ገንዘብ ወይም ንብረትን ስለመዉረስ /Confiscation of proceeds of crime/ ትርፍ ለማገኘት ታስበዉ በሚፈጸሙ ወንጀሎች አማካኝነት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን ለመታገል የወንጀል ህግን ዉጤታማ በሆነ መንገድ መፈጸም አንዱ አስፈላጊ ጉዳይ ነዉ። የወንጀል ህግ በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን ለመታገልና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚከተላቸዉ ሁለት ዋንኛ መሳሪያዎች ዉስጥ ተግባሩን እንደወንጀል በመፈረጅ ቅጣት እንዲያስከትል ሆኖ ተፈጽሞ ሲገኝ አስፈላጊዉንና ተመጣጣኝ ቅጣት ድጋሚ እንዳይፈጸም አቅም በማሳጣትና በማስጠንቅቅም ጭምር ሲሆን ሁለተኛዉ በወንጀል ተግባር የተገኘዉን እንዲሁም ለሽብር ዓላማ ሊዉል የሚችለዉን ገንዘብን ወይም ንብረትን በመዉረስ ከወንጀል ተግባር ምንም አይነት ትርፍ እንደማይገኝ በማድረግና ከሽብር ተግባር ጋር ሊገናኝ የሚችልን ገንንብ በመዉረስ ይሆናል። ሁለቱ የወንጀል ህግ መሳሪያዎች ወንጀሉን በመታገል እረገድ የሚፈጥሩት ለዉጥ ጉልህ እንደሆነ የሚወሰድ ነዉ።

ነገር ግን ዉጤታማ በሆነ መንገድ የሚፈለጉን ሁኔታ እንዲያመጣ የወንጀሉን ዉስብስብነት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሄድ ለዉጥ በመከታተል እንዲሁም ተገቢዉን ሁኔታ ሁሉ አጠቃሎ በመያዝ ተግባራዊ ሲደረግና ተጓዳኝ የመከላከል እርምጃዎች አንድ ላይ ተግባራዊ ሲሆን እንደሆነ ይወሰዳል። በአጠቃላይ በወንጀል ፍትሕ ስርዓት ዉስጥ ከወንጀል ጥፋት ጋር በተገናኘ ለወንጀል ተግባር መፈጸሚያ የዋሉ ነገሮችን፣ ወንጀል የተፈጸመባቸዉ ማንኛዉም ነገሮች እንዲሁም በወንጀል ተግባር የተገኙ ገንዘቦች ወይም ንብረቶች የመዉረስ ሂደት ይፈጸማል። መዉረስ ወንጀልን በመከላከል ሂደት ዉስጥ ትልቅ ቦታ ያለዉ ጉዳይ ነዉ። ለመሆኑ መዉረስ ማለት ምን ማለት ነዉ? Confiscation can be generally defined as a governmental decision through which property right can be affected as a consequence of a criminal offence.

የዚህን መልክት ከያዝነዉ ጉዳይ ጋር ስንመለከት መዉረስ በወንጀል ጥፋት ምክንያት በንብረት መብት ላይ የሚወሰድ እርምጃ እንደሆነ ያስገነዝበናል። በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያስችለዉ ሁኔታ ላይ ከተቀመጡት ትርጉሞች ስንመለከት አስቀድመን ካየነዉ ትርጉም በተለየ መልኩ በቬና እና በፓሌሬሞ ኮንቬንሽን እንደተመለከተዉ confiscation which includes forfeiture where applicable means of permanent deprivation of property by order of a court or other competent authority. የዚህንም መልዕክት ስናየዉ መዉረስ ማለት መንጠቅን የሚጨምር ሲሆን ተፈጻሚነት በሚኖረዉ አኳኋን በፍርድ ቤት ወይም ስልጣን ባለዉ አካል በሚሰጥ ትዕዛዝ ንብረትን በቋሚነት ማሳጣት ነዉ። የቬና ኮንቬንሽን አደንዛዥ እጽ ዝዉዉርን ለመከላከል የወጣ ኮንቬንሽን ሲሆን ከወንጀሉ የሚገኘዉን ገንዘብ ወይም ንብረት ጥቅም ላይ እዳይዉል ለመከላከል እንዲያስችልም ጭምር የታሰበ ነዉ።

የፓሌሬሞ ኮንቬንሽን ድንበር ዘለል የተደራጁ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል ሲሆን ከወንጀሎቹ ጋር የሚገናኙ ወንጀል መፈጸሚያ መሳሪያዎችን ለወንጀሉ መፈጸም ምክንያት የሆኑትንና ከወንጀሉ ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸዉ ንብረቶችና ገንዘቦች እንዲወረሱ የሚያስችል ህግ ነዉ። በነዚህ ኮንቬንሽን ለመዉረስ የተሰጠዉ ትርጉም ተመሳሳይ ሆኖ ንብረትን በቋሚነት መንጠቅን የሚመለከት ሲሆን ይህም መከላከልን መሰረት ያደረገ ቅጣትን የሚያመለከት ለመሆኑ አጠቃላይ ከህጉም ይዘት መረዳት ይቻላል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሌላዉን ትርጉም ሰጪ ህግ ስንመለከት የአዉሮፓ በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ኮንቬንሽን አንቀጽ 1(d) የተመለከተዉን ሲሆን፤ ይህም፡- confiscation is a penalty or measures ordered by a court following proceedings in relation to a criminal offence or criminal offences resulting in the final deprivation of property.

የዚህንም መልእክት ስንመለከት ፍርድ ቤቶች የክስ ሂደትን ተከትለዉ ከወንጀል ወይም በወንጀል ተግባር ጋር የተገናኘ ንብረትን ለመንጠቅ የሚያስተላልፉት ትዕዛዝ ወይም እርምጃ ነዉ በሚል ተቀምጧል። በዚህ ኮንቬንሽን የመዉረስ ተግባር የሚፈጸመዉን አካል ፍርድ ቤት ብቻ እንዲሆን ያደረገ ሲሆን አስተዳደራዊ የመዉረስ እርምጃን የማይፈቅድ መሆኑን የሚያመለክት ነዉ። በሀገራችን በወንጀል ተግባር የተገኘ ንብረትን ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 2(15) ላይ እንደተመለከተዉ መዉረስ ማለት በፍርድ ቤት ዉሳኔ መሰረት የገንዘብ ወይም የንብረት ባለኔትነትን በቋሚነት ማሳጣት ነዉ በሚል ተቀምጧል።

የሚወረሰዉ ምንድ ነዉ?

የመዉረስ ተግባር የንብረት ባለቤትነትን በቋሚነት ማሳጣት ስለሆነ የግለሰቦች የንብረት ባለቤትነት እንዳይነካ ጥንቃቄ በማድረግ በቅድሚያ የሚወረሰዉ ነገርን በምን ሁኔታ እንደሆነ አስቀድሞ ማወቅ አስፈላጊ ይሆናል። በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እነዲቻል የመዉረስ ተግባር እንዲፈጸም ጠንካራ የህግ ማእቀፍና ድጋፍ ያለዉ ጉዳይ ሊሆን ይገባል። ይህንን በአግባቡ መፈጸምና የሚፈለገዉን ዉጤት ማምጣት ይገባል። በወንጀል ተግባር የተገኘ ንብረትን ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲያስችል ከወንጀሉ ጋር በተገናኘ በሶስት መልኩ የሚከፈል የሚወረስ ነግር ይኖራል።

የመጀመሪያዉ ለወንጀሉ መፈጸሚያነትና ለወንጀሉ መፈጸም ምክንያት የሆነዉ፣ ሁለተኛዉ ከወንጀሉ ጋር በተገናኘ የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት እና ሶስተኛ ለወንጀል መፈጸሚያነት ሊዉል የሚችል ገንዘብ ወይም ንብረት ይሆናል በዝርዝር እንመለከታለን፡-

 ለወንጀሉ መፈጸሚያነትና ለወንጀሉ መፈጸም ምክንያት የሆነዉን መዉረስ (confiscation the instrumentalities and the subject of crime) ንብረትን መዉረስ የራሱ የሆነ አላማ ያለዉ በመሆኑ ለመዉረስ ትክክለኛ ምክንያትና አካሄድ ሊኖረዉ ይገባል በዚህ ሁኔታ ላይ የሚወረሰዉ ነገር ከምክንያት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ይህንን መሰረት በማድረግ ከፍሎ ማየት ይገባል። ለወንጀሉ መፈጸሚያነት የዋለ ማንኛዉም ነገርና ለወንጀሉ መፈጸም ምክንያት የሆነዉን መዉረስ በወንጀል ተግባር የተገኘ ንብረትን ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ማንኛዉንም ወንጀል በመከላከል ሁኔታም የሚፈጸም ነዉ።

ለወንጀሉ መፈጸሚያነት የዋሉ ነገሮች ማለት ከተፈጸመዉ ወንጀል ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለዉና ለወንጀል መፈጸሚያነት ያገለገለ መሳሪያ ሲሆን ለወንጀሉ መፈጸም ምክንያት የሆነዉ ነገር ደግሞ ወንጀሉ ሲፈጸም ከመነሻዉ ያነጣጠረበትን ነገር የሚመለከት ነዉ:: ለወንጀሉ መፈጸሚያነት የዋሉ ንብረቶችን መዉረስ በዋናነት የሚፈጸመዉ መከላከልን መሰረት ያደረገ ሲሆን፤ ህብረተሰቡን በአግባቡ ጥቅም ላይ ከማይዉሉ አደገኛ መሳሪያዎች የመጠበቅና ድጋሚም ለወንጀል መፈጸሚያነት እንዳይወሉ የማድረግ አላማ ይኖረዋል። ለወንጀል መፈጸሚያነት የዋሉ መሳሪያዎችን አስመልክቶ እና ለወንጀሉ መፈጸም ምክንያት ሆኑትን ማንኛዉም ነገሮች በሚመለከት ያሉ አለም አቀፍ ህጎችንና የሀገራችንን ህግን ስንመለከት በመጀመሪያ የምናገኘዉ United Nation Convention Against Illicit Drug and Psychotropic substance ሲሆን በአንቀጽ 12/b/ Property, equipment or other instrumentalities used in or destined for use in offences covered by this Convention.

በዚህ ኮንቬንሽን ሽፋን ለተሰጠዉ ወንጀል መፈጸሚያነት የዋሉ ወይም እንዲዉሉ የታሰቡ መሳሪያዎችና መገልገያችን በሚመለከት እንደሆነ አስቀምጧል። ከዚህ ኮንቬንሽን የምንረዳዉ አንድ ለመዉረስ የሚያበቃዉ ምክንያት ወይም የሚወረሰዉ ነገር ከተመለከተዉ ወንጀል ጋር ግንኙነት የሚኖረዉ መሳሪያ ወይም መገልገያ ሆኖ ኮንቬንሽኑ ሽፋን የሰጠዉ ወንጀል የአደገኛ እጾችንንና የሳኮትሮፒክ ሰብሰታንሶችን ብቻ በሚመለከት በመሆኑ የሚወረሰዉም ንብረት የዚህን ወንጀልና ከወንጀሉ የሚገኘዉን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ለማቅረብ ጥቅም ላይ የሚዉል ወይም ለመዋል የታሰበ ማንኛዉም መሳሪያ ወይም መገልገያ እንደሆነ ተቀምጧል። ይህ ኮንቬንሽን ለወንጀል መፈጸሚያነት የዋሉና ሊዉሉ የታሰቡ ነገሮችን ሲያመለክት (instrumentalities) ለወንጀሉ መፈጸም ምክንያት የሆነዉን (subject of crime) ያካተተ አይደለም።

ከወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት አንድ የወንጀል ተግባር ከተፈጸመ በኋላ ተጨማሪ ድርጊት ተፈጽሞ ሊሆንም፣ ላይሆንም ይችላል ገንዘብ ወይም ንብረት የሚገኝበት ሁኔታ ይኖራል። ይህ ማለት አንዴ ወንጀሉ ተፈጽሞ የሚገኘዉን ገንዘብ ወይም ንብረት ብቻ ሳይሆን የሚመለከተዉ በሂደት ወደ በተለያዩ ተግባራት መነሻዉ ወንጀል ሆኖ የተፈጠረዉን ገንዘብ ሁሉ የሚጨር ነዉ። የተደራጁ ወንጀሎችን ለመከላከል በወጣዉ የፓሬሌሞ ኮንቬንሽን ከወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ምን ማለት እንደሆነ በትርጉም ክፍል ሲያስቀምጥ “Proceeds of crime” shall mean any property derived from or obtained, directly or indirectly, through the commission of an offence; የዚህም ትርጉም ዋንኛ ጉዳይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የወንጀል ተግባር በመፈጸም የተገኘ ማንኛዉም ንብረት ነዉ በሚል ያስቀምጣል። የንብረቱ ምንጭ ወይም መሰረት ወንጀል ሆኖ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከወንጀሉ ጋር መገናኘቱ ንብረቱን በአጠቃላይ የወንጀል ፍሬ እንዲሆን ያደረገ ህግ እንደሆነ የሚያስገነዝበን ይሆናል።

4.3 በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ስለመዉረስ በሀገራችን ያለዉ የህግ ማዕቀፍ በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል ከሚያስፈልጉ ዋንኛ ጉዳዮች አንዱ ንብረትን ማገድና መያዝ በኋላም መዉረስ እንደሆነ የሚታመንበት ጉዳይ ነዉ።

በተለይ በወንጀል ተግባር የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብን አንዴ የወንጀል ምንጭ ሆኖ ለረጅም ጊዜ የተቀላቀለ ንብረት ህጋዊ የመምሰል ሂደቱ ተጠናክሮ የቀጠለ ቢሆንም የሚወረስበት ሁኔታ ካለ ወንጀሉ በመከላከልና በመቆጣጠር ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነዉ። ከዚህ አንጻር ንብረትን መዉረስ በሚመለከት የአገራችን ህግ ማእቀፍ በቂ ነዉ፣ አይደለም የሚባለዉ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ በወንጀል ተግባር የተገኘዉን ገንዘብ ለመዉረስ የሚያስችል የህግ ማእቀፍ እንዲኖር ጥረት የተደረገበትን ሁኔታ እንመለከታለን። አዋጅ ቁጥር 780/2005 የሚወረሱት ጉዳዮች ምን ምን እንደሆነ ጨምሮ በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን እንደሚወረስ በዝርዝር የሚያስረዳን ሲሆን ይህም የወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚቻልበት ሁኔታ ዉስጥ ያስገባን ነዉ።

የሚወረሱት ጉዳዮችን ምን ምን እንደሆኑ ስንመለከት በአንቀጽ 35 ሲያስቀምጥ ይህም የመጀመሪያዉ ጥፋተኛነት መሰረት ያደረገ /conviction base/ ሲሆን በዝርዝርም፡- የወንጀሉ ፍሬ የሆነዉን ገንዘብ ወይም ንብረት፣ ተቀላቅሎት ወይም ተለዉጦበት የተገኘ ንብረት፤ ከወንጀሉ ፍሬ የተገኘ ገቢና ሌሎች ጥቅሞች የሚመለከት ገንዘብ ወይም ንብረት፤ ለወንጀሉ መፈጸሚያነት የዋለ ንብረት፤ ባለቤትነቱ የተላለፈለት ምንጩ ሕገወጥ መሆኑን ሳያዉቅና ተገቢ የሆነ ዋጋ ከፍሎበት ወይም ለሰጠዉ ተመጣጣኝ አገልግሎት ታስቦለት ወይም በሌላ ሕጋዊ ምክንያት መሆኑን ፍርድ ቤቱ ካላመነ በስተቀር ከላይ የተከለጹትን ለማንኛዉም ወገን የተላለፈ ገንዘብ ወይም ንብረት፤ ከወንጀሉ ፍሬ ጋር ተመጣጣኝ ግምት ያለዉ የወንጀል ፈጻሚዉ ንብረት ሊወረስ እንደሚችል ህጉ በግልጽ ያስገነዝባል።

ይህ እንዳለ ሆኖ የጥፋትኛነት ዉሳኔ ባይሰጥም ነገር ግን የወንጀሉ ፈጻሚ ሳይታወቅ ቀርቶ እንደሆነ፣ የተሰወረ እንደሆነ፣ የሞተ የሆነ እንደሆነ በመሆኑ ምክንያት ከሆነ ፍርድ ቤቱ በወንጀል ድርጊት የተገኘ በንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወይም የየአመንጪዉ ወንጀል ወይም የሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል መፈጸሙን ካረጋገጠና የተያዘዉ ንብረት የወንጀል ፍሬ ወይም የወንጀል መፈጸሚያ መሆኑን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ ከቀረበለት እንዲወረስ ሊወሰን ይችላል። በአጠቃላይ ሲታይ የሀገራችን ህግ ያሰቀመጣቸዉ ጉዳዮች ከሞላ ጎደል ጥሩ ቢሆንም በአፈጻጸም ደረጃ የተሄደበት ርቀት ሲታይ ገና ብዙ የሚቀረዉ ጉዳይ ነዉ።

ማጠቃለያ

በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያሉትን አንዳንድ ጉዳዮች ተመልክተናል። ወንጀሉ ለሌሎች ወንጀሎች መበራከት ከፍተኛ ድርሻ ያለዉ ከመሆኑም በላይ በሀገር ላይ የሚያስከትለዉ ቀዉስ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ተገንዝበናል። ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በዋናነት ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች እያንዳንዷን ተግባር በወንጀልነት ፈረጆ ክትትል በማድረግ የሚከላከል ተግባር መፈጸምና ድርጊት ተከስቶም ሲገኝ አጸፋ ወይም ምላሽ በመስጠት ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም የማድረግ ሂደት እንዲኖር ከማድረግ ባለፈ ከወንጀሉ ጋር የተገናኘ ገንዘብ ወይም ንብረት እንዲወረስ ማድረግ ትልቅ ቦታ ያለዉ ጉዳይ ነዉ። በወንጀል ተግባር የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አገራችን እስከ አሁን የሄደችበት ርቀት ጥሩ ቢሆንም በህግ አፈጻጸም ረገድ ገና ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለባት የሚታመን ነዉ። በመሆኑም ህብረተሰቡ በዋናነት በጉዳዩ ላይ ከፍትህ አካላት ጋር ተባብሮ በመስራት በወንጀል ተግባር የተገኘዉን ማንኛዉም ንብረት በመጠቆም ተገቢዉ የህግ እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ኃላፊነትን ይዞ መንቀሳቀስ ያለበት ሲሆን የፍትህ አካላትም ሆኑ ሌሎች በወንጀል ተግባር የተገኘ ንብረትን በመከላከልና በመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጣቸዉ ድርጅቶች ወንጀሉን በመከላከልና በመቆጣጠር እንዲሁም በመከታተልና ምላሽ በመስጠት ረገድ ጠንክሮ መስራት ይገባቸዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
804 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 828 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us