ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ ብሔራዊ ምክር ቤት የሃገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

Wednesday, 23 March 2016 12:34

 

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ መጋቢት 4 2008 ዓ.ም የብሄራዊ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል። ባካሄደው በዚህ መደበኛ ስብሰባ በሶስት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ በሁለት የሃገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚከተሉትን አቋሞች ወስዷል።


በሃገሪቱ የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ


1ኛ. መንግስት በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚሰጠውን አርዳታ የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል። በተጨማሪም በእርዳታ ስርጭቱ ላይ ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ስርጭቱና ክፍፍሉ ፍትሃዊና ከአድሎ ነጻ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። በዚህ የእርዳታ ስርጭት ላይ አድሎ ሲፈጽሙ የሚገኙ አመራሮቹ ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን።
2ኛ. መንግስት፣ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና ህዝቡ ይሄ ድርቅ የሰው ህይወት መቅጠፍ ከመጀመሩ በፊት ከምንግዜውም በበለጠ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ፣


3ኛ. ድርቁን ለፖለቲካ ፍጆታ ለመጠቀም የሚሞክሩ አንዳንድ ኃይሎች ከድርጊታቸው በመቆጠብ ህብረተሰቡ በድርቁ ዙሪያ የፖለቲካ ልዩነቱን ወደ ጎን አድርጎ የእርዳታ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችል ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።


4ኛ. በአሉታዊ ጎኑ የማንነታችን መገለጫ ተደርጎ የሚታየው ድርቅና ርሃብ በዚህ ትውልድ ሊቆም የሚችለው ኢህአዴግ በሚከተለው የኢኮኖሚ አስትራቴጂ እንዳልሆነ ኢዴፓ አጥብቆ ያምናል። ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው ላለፉት ሃያ አምስት አመታት የኢህአዴግ የኢኮኖሚ ፓሊሲና የግብርና አስትራቴጂ ገበሬውን ከተዳጋጋሚ ድርቅ፣ ከርሃብና ከተመጽዋችነት ያላወጣው ከመሆኑም በላይ በምግብ እህልም ሃገሪቷ ራሷን ሳትችል ዛሬም እንደ ትናንቱ የውጭ እርዳታ ጠባቂ ሆና እንድትቀር አድርጓታል። ስለዚህ የሃገራችን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሸግግር በማድረግ በአንድ በኩል አጠቃላዩ ኢኮኖሚያችን ከእርሻ ጥገኝነት ተላቆ ወደ ኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፍ እንዲሸጋገር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ግብርናው አሁን አንደሚታየው ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ ገበሬው የመስኖ ተጠቃሚ መሆን ይገባዋል። በተጨማሪም ገበሬው በአነስተኛ ማሳ በቂ ምርት እንደማያገኝ በመረዳት ዘመናዊና ሰፋፊ አርሻዎችን ማስፋፋት ካልተቻለ፤ ገበሬው የመሬት ባለቤትነቱ ካልተረጋገጠ የተለመደው ድርቅና ርሃብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢዴፓ ብሄራዊ ምክር ቤት ያምናል፤ በመሆኑም መንግስት አሁንም ግዜው ሳይረፍድ የሚያራምደውን የኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመመርመር የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ኢዴፓ ያሳስባል።


በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞና ግጭት አስመልክቶ፡-


1ኛ. መንግስት ችግሩን ለመፍታት በሚል የሚወስደውን የሃይል እርምጃ በአስቸኳይ በማቆም ችግሩን በዘላቂነትና በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበትን አቅጣጫ እንዲከተል እናሳስባለን። በግጭቱ ምክንያት በሰውና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ገለልተኛ አካል እንዲያቋቁም፣ ግጭቱን ተከትሎ የታሰሩ ግለሰቦች ሰብአዊ መብታቸው እንዲከበር፣ ባስቸኳይ እና ግልጽ በሆነ ሁኔታ በፍርድ እንዲዳኙ፣ በቤተሰቦቻቸው እና በጠበቆቻቸው እንዲጎበኙ እንጠይቃለን።


2ኛ. መንግስት ችግሩን የመልካም አስተዳደር እጦት የፈጠረው ነው በሚል የችግሩን ምክንያት አቅልሎ ከማቅረብ ተቆጥቦ ለግጭቶች መፈጠርና መባባስ ከአንድነት ይልቅ ለልዩነት እድል የሚከፍተውን ቋንቋን መሰረት ያደረገውን የፌደራል አወቃቀር ስርአቱን አንዲፈትሽ እናሳስባለን። ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ ሊያመጣ የሚችለውና የህዝቦችን አንድነት ሊያጠናክር የሚችለው የፌደራል አወቃቀር ስርአቱ ከቋንቋ በተጨማሪ ሌሎች መስፈርቶችንም ሲያካትት ነው ብለን እናምናለን። በዚህም መሰረት የፌደራል ስርአቱ ቋንቋን፣ የመሬት አቀማመጥን፣ የህዝብ ብዛትን፣ የህዝቡ አብሮ የመኖር ታሪካዊ ትስስርን፣ የአስተዳደራዊ አመችነትንና የኢኮኖሚ አቅምን መመዘኛ ማድረግ አለበት እንላለን። በተጨማሪም የዜጎችን ተዘዋውሮ የመንቀሳቀስና ንብረት የማፍራት ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን የሚያስጠብቅ መሆን እንዳለበት ብሄራዊ ምክር ቤቱ ለማሳሰብ ይወዳል። ባለፉት ሃያ አምስት አመታት በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች እየታየ የሚገኘው በዋናነት ብሄረሰባዊ ማንነትን መሰረት አድርጎ የሚካሄዱ ግጭቶች በመሆናቸው ዛሬ ላይ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ካልተቻለ የሀገሪቱ ህልውና ነገ ከነገወዲያ አደጋ ውስጥ እንዳይወድቅ ብሄራዊ ምክር ቤቱ ከፍተኛ ስጋት አለው። በመሆኑም መንግስት ይሄንን አሳሳቢ ችግር ለመቅረፍ የፌደራል አወቃቀር ስርአቱን ግዜው ሳይረፍድ ቆም ብሎ እንዲፈትሽ በድጋሚ እንጠይቃለን።


3ኛ. ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማው ባቀረቡት የስድስት ወር ረፖርት ላይ መንግስት በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ለተፈጠሩት ችግሮች ከዚህ በፊት ከሚሰጠው ምክንያት በተለየ ሁኔታ ለችግሮቹ መፈጠር በዋናነት ተጠያቂዎቹ እኛው ነን ማለታቸውን የኢዴፓ ብሄራዊ ምክር ቤት በበጎ ጎን ተመልክቶታል። ነገር ግን በቀጣይ መንግስት በአጭር ግዜ ውስጥ ተጠያቂዎቹን ለፍርድ ሲያቀርብና እርምጃ ሲወስድ ማየት እንፈልጋለን።


4ኛ. ህብረተሰቡ ማንኛውንም ጥያቄ የማቅረብ ህገ-መንግስታዊ መብት አለው። ሆኖም ጥያቄውን ማቅረብ ያለበት ፍጹም ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ መሆን እንዳለበት ብሄራዊ ምክር ቤቱ ያምናል። ስለዚህ ተቃውሞውን የሚገልጸው የህብረተሰብ ክፍል ጥያቄውን በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ብቻ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን። ህብረተሰቡ የሚያነሳውን የመብት ጥያቄ ተገን አድርገው ግጭቱን ለማባባስና ያልተገባ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክሩ አንዳንድ ሃይሎችንም ሊከላከል ይገባል እንላለን። ይሄ ግጭት ተባብሶ የሚቀጥል ከሆነ ሃገራችን ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ከዚህ አደገኛ አዝማሚያ ራሱንም ሃገሪቱንም እንዲጠብቅ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።


5ኛ. በማንኛውም ወገን ድርጊቱ ይፈጸም ዘርንና ሃይማኖትን ኢላማ ያደረገ ጥቃትን፣ በግል ባለሃብቶች እና በህዝብ ንብረት ላይ የሚፈጸምን ጥቃት የኢዴፓ ብሄራዊ ምክር ቤት አጥብቆ ይቃወማል ድርጊቱንም ይኮንናል።


6ኛ. የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው የሚል የዜሮ ድምር ፖለቲካ የሚያራምዱ አንዳንድ ሀይሎች ግጭቱን ከሚያባብስ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ብሄራዊ ምክር ቤቱ ያሳስባል። በሃይል፣ በአመጽና በአብዮት የሚመጣ ለውጥ የስልጣን እንጂ የስርአት ለውጥ እንዳማያመጣ ጠንቅቆ የሚረዳው የኢዴፓ ብሄራዊ ምክር ቤት የሃይል አማራጭን አጥብቆ ያወግዛል።


7ኛ. የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ችግሩ የተፈታ በማስመሰል የሚያስተላልፉትን ተራ ፕሮፖጋንዳን በማቆም ቀውሱን ሊፈታ የሚያስችል መፍትሄ ጠቋሚ ስራ በመስራት ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ በሃገር ውስጥ የሚሰራጩ የግል የመገናኛ ብዙሃንና የህትመት ውጤቶች የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ቀውሱን ለማርገብ የሚያስችል ስራ እንዲሰሩ እንጠይቃለን። በተጨማሪም በውጭ ሃገር የሚተላለፉ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ይሄ ግጭት ተባብሶ በሀገሪቱ ህልውና ላይ የሚያስከትለውን አደጋ በመገንዘብ ግጭቱን ከሚያባብሱና የህዝቡን አንድነት ከሚያናጉ ዘገባዎች እንዲቆጠቡ ብሄራዊ ምክር ቤቱ አጥብቆ ያሳስባል።


በመጨረሻም የኢዴፓ ብሄራዊ ምክር ቤት የሀገራችን ወቅታዊ ጉዳይ እጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ተረድቷል። በመሆኑም ግጭቱ ተባብሶ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት ሁሉም ወገን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እናሳስባለን። በተጨማሪም መንግስት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የውይይት መድረክ እንዲያዘጋጅ እንጠይቃለን። በሌላም በኩል መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል በሃቀኝነት ላይ የተመሰረተ ግልጽ መድረክ በተከታታይ በመክፈት ህብረተሰቡን በችግሮቹ ዙሪያ በማወያየት በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝና የመፍትሄው አካል እንዲሆን የማድረግ ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ እንጠይቃለን።


ብሄራዊ ምክር ቤቱ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በተቀሰቀሰው ግጭት ህይወታቸውን ላጡ፣ አካል ጉዳት ለደረሰባቸው እና ንብረታቸው ለወደመባቸው ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን በመላው የኢዴፓ አባላት ስም ይገልጻል።
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)
ብሄራዊ ምክር ቤት
መጋቢት 8 /2008/ ዓ.ም
አዲስ አበባn

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
664 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 930 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us