ገብሬ ወደኢጣልያ፣ ኢህአዴግ ወደምስራቅ እስያ፣ ግን ለምን ይሆን?

Wednesday, 30 March 2016 12:16

 

በተስፋዬ ሀቢሶ

ለዚህች አጭር የውይይት እድል በር ከፋች የሆነው አቶ ገብሬ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ጀርባ ገዳም ሰፈር የሚኖር የከምባታ ተወላጅ ነበር፣ ጊዜውም በደርግ ዘመነመንግስት በ1969 ዓ.ም ገደማ ሲሆን ገብሬን ከቅርብ ጉዋደኛዬ ጋር ያገኘነው በዚሁ ጉዋደኛዬ አማት ቤት ነበር። ጠላ የሚጠመቅበትና ጠጅ የሚጣልበት ቤት ስለነበር የጉዋደኛዬ አማት ጎጆ፣ ገብሬን ያገኘነው ጠላውን ሲጨልጥ ነበር። ጉዋደኛዬ ጠብያለሽ በዳቦ አይነት ባህርይ የነበረው የህግ ባለሙያ ስለነበር (ዛሬ የተከበረው የዳያስፖራ አባል ሆኖ በአሜሪካ ይኖራል) ገብሬን ይጣራውና ምን እንደሚሰራ ይጠይቀዋል። ገብሬም ጠዋት ጠዋት የሰዎችን ልብስ አጥቦና ተኩሶ ለየባለቤቶቹ ካስረከበ በኋላ ከሰአት በኋላ ደግሞ ጠላ እንደሚጠጣ፣ ወደማታ ደግሞ ጣልያን ትምህርት ቤት እየሄደ ጣልያንኛ እንደሚማር ገለፀለት። ጉደኛው ጉዋደኛዬ ቀበል ያደርግና ምነው ገብሬ፣ አማርኛ እንኳ በደንብ ሳትማር ወደጣልያንኛ ምን አንጠራራህ? ሲል ጠየቀው። ገብሬም እንዲህ ሲል መለሰለት፣ አማርኛን ለመማር ሞክሬ ነበር፣ ግን አልቻልኩም። ለምን ካልከኝ፣ አማራዎች እኛ በቀላሉ እንዳይገባንና ባጭር ጊዜ እንዳንማር፣ አንዱን ፊደል ብቻ ሁለት፣ ሦስት፣ አራት ቅርፅ እንዲኖረው አድርገው አወሳሰቡት፣ ስለዚህም በደንብ ለመጨበጥ አልተቻለኝም። ለምሳሌ፣ 1) ዐ፣ አ፣ 2) ሰ፣ሠ፣ 3) ሀ፣ ሐ፣ ኀ፣ ኸ 4) ፀ፣ ጸ፣ ወዘተ። ከነዚህ ውስጥ የትኛውን ይዤ የትኛውን ልተው? ስለዚህ ጣልያንኛ ለመማር ወሰንኩና ትምህርቱን እያቀላጠፍኩ ነው ብሎ መለሰለት፣ ጣልያንኛ ለማንበብም ሆነ ለመማር ቀላል መሆኑን እያስረዳ። ገብሬ በጠላው ኃይል የተነሳ ሞቅ ብሎት ነው መሰለኝ ያልተጠየቀውን መቀባጠር ጀመረ፣ የገብርኤልን ስሌት ዛሬ ለጊዮርጊስ ሰጥቼ መጣሁ አለ። ምነው ሲባል፣ እነርሱ አንድ ናቸው፣ ይተዋወቃሉ፣ ካዝናቸዉም አንድ ነው ሲል መለሰ። ይህ ዛሬ ለኔ ቁምነገር ያዘለ ጨዋታ ሆኖ ያገኘሁት የገብሬ ትረካ ነበር።


እኛም ዛሬ ሊበራል ዴሞክራሲ የምንመኘው የነፃነት ጎዳና መሆኑን በቲዎሪ ደረጃ ብንገነዘብም ባጭር ጊዜ ለመማርና ለሃገራችንም ሆነ ለህዝባችን የአስተዳደር እና የሕይወት ዘይቤ እንዲሆን ለማድረግ አልቻልንም፤ ከዘመናት ጉጉት በሁዋላ። ምክንያቱም ዛሬ በኢኮኖሚ ልማትና በዴሞክራሲ እሴቶች የዳበሩ ምእራባውያን አገሮች እነርሱ "የወጡበትን መሰላል በተመሳሳይ ሁኔታ እኛም እንዳንወጣበት አሽቀንጥረው በመጣል" ("Kicking Away the Ladder of democratic and economic development") ለዘመናት ከተዘፈቅንበት የአምባገነንነት የፖለቲካ ስርአት እና የኢኮኖሚ ድህነት አረንቋ እንዳንወጣ መንገዱን አወሳሰቡብን፣ እነዚህን እሴቶች ለመማር እንዳንችልም አያሌ መሰናክሎች ተጋርጠውብናል፣ ልክ እንደገብሬው አማርኛ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ አያሌ ብሄረሰቦችና ቋንቋዎች ባሉበት አገር ሊበራል ዴሞክራሲ ሊያብብ አይችልም ይላሉ ምእራባውያን የፖለቲካ ተመራማሪዎች። በሁለተኛ ደረጃ፣ የተማረና በሃብት የደረጀ ህብረተሰብ በሌለበትና አብዛኛው ህዝብ ያልተማረ አርሶአደር በሆነበት አገር ዴሞክራሲን እውን ማድረግ ዘበት ነው የሚል ጠንካራ የምእራባውያን ልሂቃን ትችት አለ። በሦስተኛ ደረጃ፣ ከተሜነት፣ ኢንዱስትሪ፣ ዘመናዊ ትምህርት፣ የከበርቴ መደብ ወዘተ ባልተስፋፋበት የሊበራል ዴሞክራሲ እሴቶችን ማስረፅ አይቻልም የሚል ክርክር ይቀርባል ከነዚሁ ወገኖች። በአራተኛ ደረጃ፣ በኢትዮጵያ ለዘመናት የተንሰራፋው የፖለቲካ ባህላችን የሥልጣን ተቀናቃኝን ሁሉ በጠላትነት የሚፈርጅና ያንንም ጠላት ከመግደል በመለስ ሌላ አማራጭ እንደሌለ በፅኑ የሚያምን ባህል በመሆኑና ከዚህ ኋላቀር ባህል ለመላቀቅ ባለመቻሉ ነው። ሌሎችም ለዴሞክራሲ ግንባታ ደንቃራ የሆኑ ምክንያቶች ተብለው የሚጠቀሱ በርካታ ናቸው። በዚህም የተነሳ የሩቅ ግባችን ሊበራል ዴሞክራሲ ቢሆንም ወደዚያው ለመጓዝ አሁን ለሃገራችን ተስፋ የሚሆነው የሩቅ ምስራቅ እስያ(ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን) አገሮች የተከተሉት የእድገት ሞዴል እንደሆነ የኢህአዴግ ልሂቃን የማያወላዳ አቋም ጨብጠዋል። ይህም የልማታዊ መንግሥት ሞዴል ተብሎ ይታወቃል፣ አገዛዙ ከረር፣ የሰብአዊ መብቶች አከባበር ላላ የሚሆንበት ስርአት ነው። እንደኢትዮጵያ ያሉ ደሃ አገራት ይህንን የእድገት ሞዴል ለአገሪቱ በሚበጅ ሁኔታ በመቅረጽና ወደተግባር በመተርጎም በቅድሚያ ከድህነት አረንቋ በአፋጣኝ ካልወጡና ዘመናዊ ኢንዱስትሪ ፣ ትምህርት ፣ቴክኖሎጂ ካላስፋፉ እና የአገር ውስጥ የከበርቴ መደብ ወሳኝ ሚና በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲጫወት ካልተደረገ በስተቀር ሊበራል ዴሞክራሲ የህልም እንጀራ ከመሆን አያልፍም የሚል አስተሳሰብ ነው።እንግዲህ አገራችን በእርግጥ ከድህነት አረንቋ በፍጥነት እንድትወጣ የሁላችንም የተባበረ ተጋድሎ አማራጭ አይኖረውም፣ የሞት ወይ የሽረት ትግል ነውና። ነገር ግን፣ ይህ መንገድ ወደአራት ኪሎ ቤተመንግሥት በምርጫ ሳጥን ድምፅ አማካኝነት በሰላም ይመራን እንደሆነ ወይም አምባገነናዊ አገዛዝ ይንሰራፋ እንደሆነ ጊዜ ያሳየናል። ጊዜ ኃይል ነውና።


ይህ በዚህ እንዳለ ቢሆንም፣ በየተወሰኑ አመታት በሚካሄዱ አገርአቀፍ፣ ሠላማዊ እና ነፃ ምርጫዎች አማካኝነት ሊበራል ዴሞክራሲን ከጊዜ በኋላ ለማስፈን ይቻላል ብለው የሚያምኑ አያሌ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገራችን የፖለቲካ መድረክ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ እንዳሉ መካድ አይቻልም። ለነዚህ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሠላማዊ እንቅስቃሴ የፖለቲካ ምህዳሩ/መድረኩ ክፍትና አመቺ እንዲሆን ማድረግ የገዥው ፓርቲ እና መንግሥት የዉዴታ ግዴታ ነው፣ የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት ድንጋጌ ነውና። ይህን በሚቃረን አቋም በአንዳንድ የገዢው መንግሥት እና ፓርቲ አመራሮችና ካድሬዎች ዘወትር እንደሚነገረው እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች "የጥፋት ሃይሎች" አይደሉም በጭራሽ፣ የተለያዩ አይዲዎሎችን የሚያቀነቅኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና አጋር የአገር ገንቢዎች እንጂ። የርእዮተአለም ልዩነቶች የ"ጥፋት ኃይሎች" ተብለው እንዲወገዙ አያስደርግም፣ በየትኛውም መስፈርት። የእንግሊዘኛ ቋንቋ እና የፖለቲካ ፍልስፍና የሚተነትናቸው "የጥፋት ሃይሎች" ሁለት ናቸው፣ እነዚህም ድንቁርና እና ድህነት ናቸው። ሌሎች "The Forces of Evil" ተብለው የሚጠሩ የተለያዩ ማህበራዊ ክበባት በአሜሪካ አገር እንዳሉ ይታወቃል። ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ሐረግ የሚፈረጁባት ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ እንዳትሆን ያሰጋል። ከዚህ አስፀያፊ ነገር እግዚአብሔር አትዮጵያን ይጠብቃት። ምናልባት በ21ኛው መቶ ክፍለዘመን ሌሎችም የ"ጥፋት ሃይሎች" ተብለው ሊወገዙ የሚገባቸው 1ኛ/ መንግሥታዊ ያልሆኑ ሽብርተኛ ቡድኖች (Al-Qeda, ISIS, Taliban, Islamic Jihad, Al-Shabab, Boko Haram, Daesh, etc) እና 2ኛ/ ሽብርተኛ መንግስታትና የእነዚህ የስለላና የሽብር ተቋማት ናቸው። እስቲ ቆም ብለን እናሰላስል፣ በመላው አለም ከNATO የሚከፋ አሸባሪ ድርጅት ይገኛል? You be the judge!

 

በመጨረሻም፣ ከሁሉም በላይ ለህዝባችን ሠላም፣ ብልፅግና፣ ነጻነት፣ የሕግ የበላይነት የሚያጎናፅፍ ሊበራል ዴሞክራሲ እውን ለማድረግ በኢፌዴሪ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት መሰረት ሁላችንም እንንቀሳቀስ። እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
741 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 889 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us