የጠ/ሚ ኃ/ማርያም አዲሱ የአመራር ዘይቤ እንደሞዴል

Wednesday, 13 April 2016 12:17

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተገኝተው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ የመልካም አስተዳደር እጦቱ በመላ ሀገሪየከፋ ሁኔታ ላይ በመድረሱ ህብረተሰቡ እያማረረ መቆየቱን ጠቅሰው ችግሩን ለመቅረፍና እርምጃ ለመውሰድ ባለመቻሉኃላፊነቱን መንግስት እንደሚወስድ ጠቁመዋል። የመልካም አስተዳደር ችግሩ የመንግስት መሆኑንና ጣትን ወደሌላው ከመቀሰር ይልቅ ውስጣቸውን ማፅዳት ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ በመግለፅ ስለተፈጠረው አጠቃላይ ሁኔታ እምብዛም ባልተለመደ መልኩ ይፋዊ ይቅርታ ጠይቀዋል።

በዚህ አባባላቸው አንዳንድ ወገኖች አቶ ኃይለማርያም ስህተት የሰሩ አስመስለው የተረዱ ሲሆን በሌላ በኩል ከደረሰው ጉዳትና ከሰው ህይወት መጥፋት አንጻር ይቅርታ መጠየቃቸው የታላቅነታቸው ምልክት መሆኑን በመረዳት አክብሮታቸውን የለገሱዋቸው ወገኖች አሉ።

ለመሆኑ የአንድ ሀገር መሪ ይቅርታ መጠየቁ ምንን ያመለክታል? ግብረ መልሱስ ምን ሊሆን ይችላል?ይህ ሀገር ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ‘ንጉሥ አይከሰስም፣ ሰማይ አይታረስም’ በሚባል አስተሳሰብ ተሸፋፍኖለኖረ ማህበረሰብ መንግስታዊ ይቅርታ እንግዳ ነገር ሊመስልና ግርታን ሊፈጥር ይችላል።

ሕዝቡ ንጉሡ በመንገድ በሚያልፉበት በማንኛውም አጋጣሚ እጅ የሚነሳ ሳይሆን ወድቆ የሚሰግድበት ዘመን ነበር። በንጉሡ ዘመን የንጉሥን ተክለቁመና ለማግዘፍና ከፈጣሪ የተሰጠ ልዩ መለኮታዊ ኃይል ያለው ለማስመሰል ጭምር ጥረት የሚያደርግ እና በርካታ አስገዳጅ ሁኔታዎች ውስጥ የኖረ ማህበረሰብ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ።

በንጉሱ ዘመን ለንጉሡ መስገድ ግዴታ የነበረ ሲሆን የደርጉ ሊቀመንበር ጓድ ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ወደ ሥልጣን ሲመጡ ስግደቱን በፍርሃት ተኩት። ለጓድ መንግስቱ ስግደቱ የማይደረግላቸው ቢሆንም ህዝቡ እንዲያከብራቸውና እንዲፈራቸው የሚያደርጉት በሚወስዱት ርህራሄ በሌለው ጨካኝ አብዮታዊ እርምጃ ነበር። እንደእሳቸውአነጋገር መቀመጫውን በሳንጃ መውጋት. . .ለእራት ያሰቡዋቸውን ለቁርስ ማድረግ አንዱ የሽብር መንገድ ነበር። እንዲሁም ንግግራቸውን ኃይለቃል የታከለበት በማድረግ ከፍተኛ የሆነ የፍራቻ ድባብ በህዝቡ ላይ እንዲሰርጽ በማድረግ በፈላጭ ቆራጭ የአመራር ዘይቤ ህዝቡን መውጫ መግቢያ በማሳጣት አስተዳደረዋል፣ መርተዋል። ይሁንና ሁለቱም ሥርዓቶች በህዝብ አመፅና በጠመንጃ ኃይል ስልጣናቸውን አጥተዋል።

ከዚህ ታሪክ ቀጥለው ወደ ስልጣን የመጡት አቶ መለስ እጅግ አንደበተርቱዕ መሆናቸው የተመሰከረላቸው በመሆኑ በሃሳብ የበላይነትን በማመንጨት በውይይትና በክርክር መንፈስ ሀገሪቷን በሀሳቦች የበላይነት በመምራት ወደር አልተገኘላቸውም። በተለይ እስከ 1993 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ውስጥ ከድርጅታቸው ከፍተኛ የሆነ ቁጥጥርና ጫና የነበረባቸው አቶ መለስ ባላመኑበት የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት መርተው በአሸናፊነት ከተወጡ በኋላ በፓርቲያቸው ውስጥ ስርነቀል የሆነ የፖሊሲና የስትራቴጂ ዝግጅት በማድረግ የሃሳብ ልዕልና በመጎናጸፍ በፓርቲያቸው ውስጥ የመሪነት ሚናን በመቆናጠጥ ሀገሪቱም ወደ ትክክለኛና ተከታታይ የእድገት ምህዋር ውስጥ እንድትገባ አስችለዋል። የሥነ-ልቦና የበላይነታቸውን እየተጠቀሙ ህብረተሰቡን በማሳመን፣ በማስፈራራትና አለፍ ሲልም ይቅርታ መጠየቅ እንደአስፈላጊነቱ የግል ተሰጦአቸውን በመጠቀም በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነትንና ታማኝነትን እያተረፉ ሀገሪቷን አስተዳድረዋል። በአጠቃላይ በመለስ የአመራር ዘይቤ ህብረተሰቡ የተናበበና መግባባት የቻለ በመሆኑ ቀድሞ ከነበሩት ሥርዓተ መንግሥታት መሪዎች ባህሪ በእጅጉ የተለየ ነበር።

ወደ አቶ ኃይለማርያም የመሪነት ደረጃ ስንመለስ ከአስተዳደጋቸው የሚነሳ ባህርይ እናገኛለን። የካቶሊክ እምነት ተከታይ በሆኑ ቤተሰቦቻቸው አማካይነት በቤተክርስቲያን ስርዓት ያደጉ በመሆኑ ገራገርነትና የዋህነት ያጠቃቸው ይሆናል የሚል ስጋት በአንዳንድ ወገኖች ተደጋግሞ ይነሳል። ቁጡ ለመሆን የሚያበቃ አስተዳደግና ጭካኔ ሊኖራቸው እንደማይችል ስለሚታመን የመንግስት ሥርዓቱ በንቃት ሊታይ እና ሕግና ስርዓት ማስከበርን አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችል ይሆን ወይ ብለው ይሰጋሉ።

 የእሳቸው ግለስብዕና ሕገ ወጥነትንና ተገቢ ያልሆነ የአድሎ አሰራርይጠየፋል። እንዲሁም ሙስናና አጠቃላይ ብልሹነትን ሲመለከቱ የእሳቸውን የቁጣ ፊት ከማየት መሬት ተሰንጥቃ ብትውጣቸው የሚመርጡ ወዳጆቻቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ።በሥራቸው ሁሉ ንፅህናን የሚወዱ በመሆናቸው ምንም አይነት የህዝብ ሮሮና እርካታ መታጣትን መስማት አይፈልጉም። ከስርመሰረታቸው ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ያልተለማመዱት አቶ ኃይለማርያም በእሳቸው አመራር እንደ ሲቪል መሪነታቸው ለህዝቡን እርካታ ቀን ከሌት ሰርተው ማለፍ ያስደስታቸዋል።

በቅርቡ በአንዳንድ አካባቢዎች የተነሱ ሁከቶችን ለመቆጣጠር በተወሰደ እርምጃና ከዚያ ጋር ተያይዞ በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ለጉዳቱ መንስዔ ሆኖ የተገኘው ህዝብ በመልካም አስተዳደር እጦት በመማረሩ የተነሳ እንደሆነ በመረጋገጡ በፍጥነትየማስተካከያ እርምጃ አለመውሰዱ ስህተት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነቱን መንግስታቸው እንደሚወስድ ይግለፁ እንጂ ከ2007 ምርጫ በኋላ በተሟላ ሁኔታ ስልጣን በእጃቸው ከገባና አዲሱን ካቢኔ ካቋቋሙ ገና የ6 ወራትዕድሜ ብቻ መቆጠሩ ነው።ይህን ተከትሎም አብዛኛዎቹ የመንግስት መዋቅሮች በእሳቸው አዲስ የአመራር ዘይቤ እንዲዋቀሩ የተደረጉ ሲሆኑ አንዳንዶቹ እስካሁንም ድረስ አዲሱን አደረጃጀት ጨርሰው ገና ወደ ሙሉ ሥራ አልገቡም ማለት ይቻላል። አቶ ኃይለማርያም ዘመናዊ አሰራር የተገነባበት አዲስ የአሰራር ስርዓት ዘርግተው የኪራይ ሰብሳቢነትንና የሙስና ችግሮችን በማቃለል የህዝቡን እርካታ ለማግኘት ያስችለኛል ያሉትን በተለይም ከመዋቅሮች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን እያከናወኑ የሚገኙት እጅግ የተለጠጠ እና በቀጣይ ጊዜያት ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር የምታደርገውን ፈርጀ ብዙ ሩጫ ለማስጀመር የሚያስችል እቅድም አውጥተው በየደረጃው ለመተግበር እየታተሩ እንደሚገኙ ነጋሪ አያሻውም። ምንም እንኳን መንግስታቸውና ሀገሪቱ ገና ስልጣን በተረከቡ ማግስት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ከ10 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለምግብእጥረት ችግርየተዳረገባቸው ቢሆንም በአንድ በኩል በድርቁ ህዝቡ ጉዳት እንዳይደርስበት እየተከላከሉ በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ ህዝብ ላይ ከተከማቸ የመልካም አስተዳደር እጦት ጋርመዋጋት ላይያሉት አቶ ኃይለማርያም፣በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆነው በእሳቸው ቁርጠኛ አመራር ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋትና ከስር መሠረቱ መንግለው ለመጣል የጀመሩት ጥረት ለአፍታ አላቋረጡም።

ምንም እንኳን አቶ ኃይለማርያም ይህንን አስቸጋሪ ወቅት ያለምንም መንገራገጭ በቀላሉ እየተወጡት ያሉት አንዳንድ ምሁራን እንደሚናገሩት በአመራር ዘይቤያቸው የህዝቡን ታዓማኒነት በቀላሉ ለማግኘት በመቻላቸው ነው።

በመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ጋር በሚሊኒየም አዳራሽና በጽ/ቤታቸው አዳራሽ ያለምንም መሰልቸት በተከታታይ ጊዜ ሕዝብን በማወያየትሕዝቡ የመንግስትን ቁርጠኛ አቋም ተረድቶ በመንግስት ውስጥ የተሰገሰጉ ሌቦችን እንዲያጋልጥ በማደፋፈር በሀገሪቱ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ በብሔራዊ የተሌቭዥን ጣቢያ ጭምር ጉዳዩ ለህዝብ ፍርጥርጡ ወጥቶ ወደ መፍትሔው ለማምራት እንዲቻል ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል። ብዙዎቹ ጠ/ሚኒስትሩ ይህንን ያደረጉት በየዋህነታቸው ነው እንጂ ማድረግ አልነበረባቸውም በማለት ሲከራከሩየተሰማውም ካረጀውና ካፈጀው ግልጽነት ከጎደለው የመንግስት አሠራር ልማድ ውስጥ ታስረው በመኖራቸው እንደሆነ ይታመናል።

በሚኒስትሮች ደረጃ የተደረገውን ውይይት ለህዝብ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ በየተዋረዱ እልህ አስጨራሽ የሆኑ ተከታታይ ውይይቶችን ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር አደረጉ። ከተለያዩ የህዝብ አደረጃጀቶች ጋር የመከሩት አቶ ኃይለማርያም በተለይም በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንዳያደርጉ ከተነፈጉትና ትኩረት ካልተሰጣቸው የሀገሪቱ ምሁራንም ጋር ጭምር መክረዋል። ይህም ሳያንስ በሀገሪቱ የሚገኙ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል። ከኦሮሞ አባገዳዎችና እንደ አስፈላጊነቱ ከተገኘው አደረጃጀትና መዋቅር ሁሉ ጋር ያለ መታከት መክረዋል።ምክረ ሀሳብ ተቀብለዋል፣ በቅረዋልም።

አቶ ኃይለማርያም ይህንን ሁሉ ስብሰባ ሲያደርጉ ለተናጋሪዎች ከፍተኛ ነፃነት በመስጠት ራሳቸውንም እንደ ፈላጭ ቆራጭ የሀገር መሪ ሳይሆን የህዝቦችን ፍላጎትና አመለካከት አስፈፃሚ አካል በማየት በአገልጋይነት መንፈስ ተንቀሳቅሰዋል።ይህ የአገልጋይነት መንፈስ (ስሜት) ቀደም ሲል በሀገሪቱ በመሪ ደረጃ ከነበሩ ግለ ባህሪያት ሁሉ የተለየና የአቶ ኃይለማርያም የግል ስብዕና ውጤታቸው እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።

አቶ ኃይለማርያም ባመኑበት ጉዳይ ላይ ቆራጥ እርምጃ ከመውሰድ ቦዝነው አያውቁም። በሚኒስትሮች ደረጃ የተደረገውን ውይይት ተከትለው ሥርነቀል ለውጥ ለማምጣት ቀን ከሌሊት እየሰሩ ለመሆናቸው ምስክሩ ከዚሁ ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር በተያያዘ በሁሉም ክልሎች በየደረጃው የሚገኙ የፖለቲካ ሹመኞችና የሲቪል ሰርቪስ ተቀጣሪዎች በሥርዓቱ እየተገመገሙ የሚቀጥሉበት፣ ችግር ፈጣሪዎች እንደየጥፋታቸው አግባብ በሕግ የሚጠየቁበት፣ ከሥራ የሚሰናበቱበት፣ በምክር የሚታለፉበት፣ አቅማቸውን ወደሚመጥን ሥራ የሚዘዋወሩበት እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑ ነው።

እንደዚህ አይነት እርምጃዎች በአንድ ጊዜ በመላ ሀገሪቱ በዘመቻ ሲወስዱ ይህ ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ ጠንካራና የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ የተቻለው ምንም ማስፈራራትና የስድብ ቃላቶችን መጠቀም ሳያስፈልግ መሆኑ የዘመናዊ አመራር ቁርጠኝነትና አሰራር በድንፋታና በማቅራራት ላይ ሳይመሰረት በዕውቀትና በክህሎት ታግዞ በሚሰጥ አመራር ሥርዓት በመሆኑ አቶ ኃይለማርያም በእስካሁኑ ጉዞአቸው እጅግ ስኬታማ፣ በህዝብ ዘንድም ተወዳጅነትን እንዲያገኙ ረድቷቸዋል። ይህ ዘይቤአቸው በህዝብ ዘንድ እምነት የተጣለበት መሆኑ ደግሞ የሚወሰዱ እርምጃዎች ህዝባዊ ድጋፍ እንዲኖራቸው የሚረዳ በመሆኑ የቀጣዩ ጉዞአቸውን ስኬት ከወዲሁ አመላካች ሆኗል።

የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት የሆነን ህዝብ በአገልጋይነት መንፈስ በመምራት ለሌሎች የመንግስት ኃላፊዎችም አርአያነት ያለውን ተግባር እየተወጡ ነው ብሎ መግለፅ ይቻላል።

በቀጣይ ጊዜያት አቶ ኃይለማርያም ምን አይነት ተክለቁመናና ስብዕና ይኖራቸዋል በሚለው ላይ ለውጥ ሊኖራቸው እንደማይችል ብዙ ምሁራን ቢተነትኑም ብቃታቸውንና የመተንተን አቅማቸውን እንደዚሁም አስልተው የሚፈልጉትን ዓላማ ለማሳካት የሚከተሉት ስትራቴጂ ማንም በቀላሉ ከሚገምታቸውና ከሚያስበውምበላይ መሆኑ ብዙ ዓለም አቀፍ መሪዎች ከወዲሁ በምሳሌነት እንዲመለከቷቸው እያደረገ ነው።

ምንም እንኳን በሀገራችን የመሪ ስብዕና መለኪያው የቁጣ ንግግርና ነቆራ ወይም ስድብ፣ ማስፈራራትና ዘለፋ ቢሆንም የአቶ ኃ/ማርያም አካሄድ ለየት ያለ የአመራር ጥበብን ለማሳየት አስችሏል። ይህም ተጋግሎ ፈጦ የመጣን ችግር በቀላሉ ለማስወገድና እልባት ለመስጠት የሚከተሉት ዘዴ ህዝብን በማስፈራራት ከሚደረገው የተለየ እና የራስ ጥበብ የተሞላበት በመሆኑ ብዙዎች ያወድሱታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ወጣቶች ማንም ስልጣንን ስለማይሰጣችሁ ነጥቃችሁ ለመውሰድ መዘጋጀት አለባችሁ በማለትየተናገሩት ትክክል ሲሆን ይህ አስተሳሰብ በመላውም አለም የተተገበረና የሚተገበር ነው። ስልጣንን መውሰድ የቻለ ምን ማድረግ እንዳለበት ይጠፋዋል ተብሎ አይታሰብም።ሥልጣንን በአግባቡ ለሕዝብ ጥቅም በማዋልና ባለማዋል መካከልያለው ልዩነት የሚወሰነውበመልካም አስተዳደግ ከመኖርናጥሩ ስብዕናን ከመላበስ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ሥነ-ምግባር የተላበሰ አመራር ማግኘት፣ የአንድ ታላቅ ህዝብ ምኞቱና የዘወትር ፀሎቱ ነው።እንደሞዴል እየተጠቀሱያሉት የጠ/ሚ ኃይለማርያም ባህርያት መካከል ሰዎችን በአክብሮት ተቀብሎ ማነጋገር፣ ሰዎችን ማዳመጥ፣ በውይይትና በመግባባት ላይ የተመሰረተ መፍትሔ መስጠት በአጠቃላይ አሳታፊነትን የተከተለ የአመራር ዘይቤ እንደእሴት ሊታይ የሚገባው ነው።አበቃሁ። ረጅም ዕድሜና ጤና ለጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ!!

ሮሪሳ ቡርመጂ - ከፊንፊኔ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
759 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1051 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us