ከኢህአዴግ ጋር መሠረታዊ የአቋም ልዩነት የሌለው መድረክ ወይስ ኢዴፓ?

Wednesday, 13 April 2016 12:19

 

አዳነ ታደሰ

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል

ለዛሬው ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ በሰንደቅ ጋዜጣ 11ኛ አመት ቁጥር 552 ረቡዕ መጋቢት 28/2008 ዓ.ም የመድረክ አመራሮች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የሃገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት አባላትን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት ነው።የመድረክ  አመራሮች በዚህ መግለጫ ላይ በሰጡት አስተያየት የጋራ ምክር ቤቱን አባላት በጅምላ ስም አጥፍተዋል። በዛ ምክር ቤት ውስጥ በንቃት እየተሳተፉ ከሚገኙ ፓርቲዎች መካከል ደግሞ አንደኛው ኢዴፓ ነው።ስለዚህ ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል በሚል እርካሽ ፖለቲካ ማራመድን ስራ ብለው ለያዙ መድረክን ለመሰሉ ፓርቲዎች መልስ የመስጠት ፍላጎት ባይኖረኝም ሰሞኑን ግን የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉትን ውይይት አስመልክቶ የሚሰጡት አስተያየቶች መረን የወጡ ሆነው ስላገኘኋቸው እንደ ኢዴፓ አመራርነቴ የግል አስተያየቴንለመጻፍ ተገድጃለሁ።

በመድረክ ውስጥ ያሉ አመራሮች አብዛኞቹ የ1960ዎቹ ፖለቲካ ውስጥ ያለፉ በመሆናቸው አሁንም ተቀናቃኝን በሃሳብ ሳይሆን ለማሸነፍ የሚሞክሩት በለመዱት በሴራና በአሉባልታ ፖለቲካ ነው። ይሄ ትውልድ ደግሞ ይሄን የነተበና ግዜውን የማይመጥን የፖለቲካ አስተሳሰብ በድፍረት መታገል ያለበት ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቴ በሆነ የታሪክ አጋጣሚ እነዚህ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ለመንግስትነት ቢበቁና ሁሉም ነገር በእጃቸው ቢሆን ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ሳስብ አደገኝነታቸው ገዝፎ ስለሚታየኝ ነው።ይሄ ትውልድ ደግሞ የራሱን ዘመን በራሱ አስተሳሰብ ለመቃኘት ከፈለገና የስልጡን ፖለቲካ ባለቤት መሆን ካማረው ይሄን አሮጌ የፖለቲካ ባህል መታገል ግዴታው ነው የሚሆነው። ወጣቱን ለመፈክር ተሸካሚነት እና ለአዳራሽ ስብሰባ ከማድመቂያነት በዘለለ ጥቅም እንደሌለው መቁጠራቸውን እንዲያቆሙ ሃይ ባይ ትውልድ ያስፈልጋል። አቅም አለን ብለው ካሰቡ ከአሉባልታና ከሴራ ፖለቲካ ወጥተው በአጀንዳና በሃሳብ ሊሞግቱን ይገባል።

የመድረክ አመራሮች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ከሆኑ ፓርቲዎች ጋር በብሄራዊ መግባባት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። በሁለት ተከታታይ ምርጫዎች ከገዥው ፓርቲ ቀጥሎ ከፍተኛ ድምጽ ያገኘው መድረክ በውይይቱ ላይ ያልተገኘው ለምንድን ነው? የፓርቲዎቹንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን መድረክ እንዴት ያየዋል” ተብለው ከጋዜጠኞች ተጠይቀው ነበር። ለዚህ ጥያቄ ጥሩ ነው፣ ጥሩ አይደለም በሚል ከአንድ ፓርቲ የሚጠበቀውን ፖለቲካዊ ትንታኔ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ ሲገባቸው በቀጥታ የገቡት ተራ አሉባልታ ውስጥና የስም ማጥፋት ዘመቻ ውስጥ ነው።እስቲ ከላይ ለተጠየቁት የሰጡትን መልስ አንዷን ሃሳብ ነቅሼ የኔን አስተያየት ለማስቀመጥ ልሞክር።

አመራሮቹ እያልኩ በጽሁፌ የምገልጸው መልስ ሰጭው በስም በጋዜጣው ላይ ስላልተጠቀሰ እንደሆነ በቅድሚያ ይታወቅልኝ። አመራሮቹ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ያደረግነውን አጠቃላይ የምክር ቤቱን አባላት “ከኢህአዴግ ጋር መሰረታዊ የአቋም ልዩነት የሌላቸው ”በማለት ተችተዋል። ይሄን አይነት አስተያየት ሲሰጡ አንድ ሁለቴ ቢያስቡ ጥሩ ነበር። እውነት ለኢህአዴግ በአቋም ደረጃ የሚቀርበው መድረክ ነው ወይስ ኢዴፓ?ይሄን ጥያቄ በአሉባልታ ላይ ተመስርቼ ሳይሆን በበቂ መረጃ የማቅረብ ነው የዚህ ጽሁፌ ዋና አላማ። ያውም በጥቂቱ።

በተለያዩ በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች ላይ መድረክና ኢህአዴግ ምን ያህል ተመሳሳይ አቋም እንደሚያራምዱ የተወሰኑትንና ዋና ዋና የሚባሉ ጉዳዮችን በማንሳት እውነታውን ለማሳየት ልሞክር። በመጨረሻ ደግሞ ኢዴፓ በጋራ ምክር ቤቱ የሚያደርገው ተሳትፎ ከምን መነሻ እንደሆነ አስቀምጬ ጽሁፌን እቋጫለሁ።

1ኛ. በሃገራችን አከራካሪ ከሆኑ ፖሊሲዎች አንዱ ኢህአዴግ የሚከተለው የመሬት ፖሊሲ ነው። በመሬት ፖሊሲ ላይ በሃገራችን ሶስት አይነት አቋሞች ይራመዳሉ። አንደኛው አቋም መሬት መሸጥ መለወጥ አለበት  የሚለው ነው። ይሄን አቋም መኢአድን ጨምሮ ብዙ ፓርቲዎች አቋማቸው አድርገው በተለያዩ የምርጫ ክርክሮች ላይ አንስተዋል። ሁለተኛው አቋም ኢህአዴግና በብሄር የተደራጁ መድረክ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችን ጨምሮ መሬት የመንግስት መሆን አለበት በማለት የሚያራምዱት አቋም ነው። ከነዚህ መሬት የመንግስት ወይም ይሸጥ፣ ይለወጥ በሚል በሃገር ደረጃ አንድ አይነት የመሬት ስሪት ይኑር ከሚሉት የፖለቲካ ኃይሎች በተለየ ሶስተኛ አማራጭ ያለው ኢዴፓ ብቻ ነው። ኢዴፓ ሶስት አይነት የመሬት ስሪት እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ሊኖር ይገባል የሚል አቋም ያራምዳል። በዚህም መሰረት የመንግስት፣ የወልና የግል የመሬት ይዞታን የሚፈቅድ የመሬት ፖሊሲ በሃገራችን ሊኖር ይገባል እንላለን። ታዲያ በዚህ ትልቅ ሃገራዊ ጉዳይ ላይ ከኢህአዴግ ጋር የበለጠ የሚቀርብ አቋም ያለው መድረክ ነው ኢዴፓ?

2ኛ. ሌላው በአገራችን የፖለቲካ መድረክ አከራካሪ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ አገራችን ምን አይነት ፌደራሊዝም ያስፈልጋታል የሚለው ነው። በጉዳዩ ዙሪያ የሚነሳው ክርክር ፌደራሊዝም ያስፈልጋል፣ አያስፈልግም ሳይሆን አገራችን ምን አይነት የፌደራል አደረጃጀት ነው የሚያስፈልጋት የሚል ነው።በፌደራሊዝም ዙሪያ ኢህአዴግና መድረክ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ማንነትን ዋነኛ መስፈርቱ ያደረገውን የፌደራል አደረጃጀት የሚደግፉ ናቸው።ሌሎች ፓርቲዎች ደግሞ የቋንቋ ፌደራሊዝምን ቢቃወሙም በግልጽ ይሄ አማራጭ አለኝ ሲሉ አይሰሙም። ኢዴፓ ደግሞ የፌደራል አደረጃጀት ለኢትዮጵያ ጠቃሚና አስፈላጊ አደረጃጀት መሆኑን ያምናል።ነገር ግን የኢህአዴግና የመድረክ የፌደራል አደረጃጀት ከአንድነት ይልቅ ለልዩነት በር የሚከፍት ነው የሚል አቋም አለው። ስለዚህ ከቋንቋ ወይም ከብሄረሰባዊ ማንነት በተጨማሪ የመሬት አቀማመጥ፣ የህዝብ ብዛት፣ የህብረተሰቡ አብሮ የመኖር ታሪካዊ ትስስር፣ የአስተዳደራዊ አመችነትና የኢኮኖሚ አቅም የመሳሰሉት ጉዳዮች የፌደራል አከላለል መመዘኛዎች ሊሆኑ ይገባል እንላለን። ታዲያ በዚህ በአሁኑ ወቅት ሃገሪቱን ስጋት ውስጥ የከተተውንና የግጭት መንስኤ የሆነውን የፌደራል አደረጃጀት ኢዴፓ አጥብቆ የሚቃወመውም ለዚህ ነው። ታዲያ ማንኛው ነው በአቋም ደረጃ ለኢህአዴግ የሚቀርብ ኢዴፓ ወይስ መድረክ?

3ኛ. ሌላው በኢትዮጵያ ፖለቲካ አከራካሪ የሆነው ጉዳይ  የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል የሚለው የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 39 ነው። ኢህአዴግ በብሄር ከተደራጁት የመድረክ አባል ፓርቲዎች ጋር መሠረታዊ ልዩነት የለውም።ለኢዴፓም የዚህ የመገንጠል መብት በህገ መንግስቱ መስፈር በቀጥታ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ አጥብቆ ይቃወመዋል። ለምሳሌ የኦሮሚያ መገንጠል በቀጥታ ውጤቱ የኢትዮጵያ መፍረስ ነውና።ከኢትዮጵያ ውጭ ይሄንን የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል ድረስ የሚል መብት በህገ-መንግስታቸው ያሰፈሩ ሶቭዬት ህብረትን ዩጎዝላቪያ የደረሰባቸውን ለሚረዳ ፖለቲከኛ አንቀጽ 39 ስጋት ቢፈጥርበት ጤነኝነት ነው።ይሄ ህገ-መንግስት ሲጸድቅ እንደ አንድ አባት ተነስተው ባይጨፍሩም አሁን የመድረክ ፕሬዘዳንት የሆኑት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ግን በግዜው ፓርላማ ውስጥ ተገኝተው ደግፈው አጨብጭበው እንዲጸድቅ አድርገዋል።ሌሎች እነ አረናን የመሰሉ ፓርቲ መሪዎች ደግሞ ይሄ አንቀጽ በህገ-መንግስቱ እንዲካተት ከማድረጋቸውም በላይ የኤርትራን ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው በሚል ከሻዕቢያ ጋር ተስማምተው ኤርትራን ከኢትዮጵያ አስገንጥለዋል። አገራችንንም ወደብ አልባ አድርገዋታል።ታድያ ማነው ለኢህአዴግ የሚቀርበው ኢዴፓ ወይስ መድረክ?

4ኛ. በሃገራችን ያሉ ተቃዋሚዎች ሁለት አይነት አደረጃጀት ነውያላቸው። ብሄርን ወይም ብሄረሰባዊ ማንነትን መሰረት አድርገው የተደራጁና ህብረ ብሄራዊ ወይንም ሃገር አቀፍ ፓርቲ የሆኑ ማለት ነው። በዚህ አደረጃጀት ብሄርን መሰረት አድርገው የተደራጁት በተለይም መድረክ ውስጥ ያሉ አባል ድርጅቶች ተቃዋሚ ከመሆናቸው በስተቀር በአደረጃጀት ቅርጽ ከገዥው ፓርቲ የተለዩ አይደለም። ሌሎቹ ደግሞ ኢዴፓን ጨምሮ በሃገር አቀፍ ፓርቲነት ተደራጅተን ሃገራዊ አላማና ራዕይ ሰንቀን እየታገልን እንገኛለን። በብሄር ተደራጅቶ መታገል ህገ-መንግስታዊ መብት መሆኑን ኢዴፓ ጠንቅቆ ይረዳል።ሆኖም በብሄር ተደራጅቶ ታግሎ ግን ሃገራዊ ጥቅምም ሆነ ለህዝቡ ጠብ የሚል ነገር ይኖራል ብለን ስለማናምን የብሄር አደረጃጀትን አንደግፍም።የሚያስገርመው ደግሞ በተግባርም በብሄር የተደራጁት በተለይ የመድረክ አባል ፓርቲዎች በአደረጃጀት ቅርጽ ብቻ ሳይሆን ከኢህአዴግ ጋር የሚመሳሰሉት ከአገራዊ አጀንዳ አንጻርም ብዙም ልዩነት የላቸውም። ታድያ መድረክ በምን መመዘኛ ነው የጋራ ምክር ቤት ውስጥ ያሉትን ፓርቲዎች በተለይም ኢዴፓን ከኢህአዴግ ጋርመሰረታዊ የአቋም ልዩነት የሌላቸው ናቸው የሚለው? ይሄ ውስጥን በደንብ አድርጎ ያለማየት ችግር ነው።

5ኛ. በመድረክ ውስጥ የመሪነቱን ሚና እየተፈራረቁ የሚይዙትን አመራሮች ስናይ ሁለት ግለሰቦች ሆነው እናገኛቸዋለን። እነዚህ ሁለት ግለሰቦች በድርጅታቸው ያለውንም የመሪነት ስልጣን ለረዥም ግዜ በመቆጣጠር ወደር የማይገኝላቸው ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች ፓርቲያቸውን ይዘው በህዝቡ ውስጥ የሚጨበጥ ስራ መስራት ስለማይችሉ ደግሞ በሃገሪቱ ፖለቲካ ተሰሚነት ለማግኘት የሚፈጥሩት ዘዴ በህብረት ስም በሚቋቋም ስብስብ ውስጥ አመራርነት ላይ መንጠላጠልን ነው። እነዚህ መድረክን የሚመሩ ግለሰቦች በአንድ ህብረት ወይም መድረክ ውስጥ ገብተው ትልቅ የሚሰሩት ፖለቲካ ቢኖር ኢህአዴግ አደጋ ውስጥ ነው ብለው ሲያስቡ የሽግግር መንግስት ወይንም የአንድነት መንግስት ምስረታ ጥያቄን ማቅረብ ነው። በሃገራችን እስከ ዛሬ የተፈጠሩት ህብረቶችና መድረኮች የትም ሲደርሱ የማናያቸውም ህብረቱ የነዚህ የብልጣብልጦች እና የስልጣን ጥመኞች  መሸሸጊያ በመሆኑ ነው። እንደ ፕሮፌሰር በየነ አይነት የፖለቲካ መሪዎች ኢዴሃቅን፣ ደኢህዴህን፣ አማራጭ ሃይሎችን፣ ጋፓመን፣ ኢተፖድህን፣ ኢዴሓህን የመሳሰሉ ህብረቶችን መርተው፣ አፍርሰው ዛሬም መድረክን እየመሩ ነው። እነዚህን ሰዎች ይሄን ሲያደርጉ የሚጠይቃቸው አካል ስለሌለ ዛሬም የሌላውን ፓርቲ ስም ጥላሸት በመቀባትና በሴራ ፖለቲካቸው የትውልዱን ስልጡን ፖለቲካ የማየት ህልም እያጨለሙ ይገኛሉ። በፓርቲያቸው ውስጥ ድርጅታዊ መዋቅር እንኳን በቅጡ የሌላቸው ኢዴፓ ላይ አሉባልታ ለመንዛት ያለ የሌለ ጉልበታቸውን ሲጠቀሙ ሳይ የሴራንና የጥላቻን ፖለቲካ ዋነኛ የትግል ስልት አድርገው መያዛቸውን ለመረዳት አያዳግትም። ፓርቲን እንደ ግል ርስት በመያዝና በስልጣን ጥመኝነት ከኢህአዴግ ጋር ካልሆነ እነዚህ ግለሰቦች የሚወዳደሩት ከየትኛው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጋር ነው። እንደ እነሱ ተቃዋሚ ሆኖ ከ20 አመት በላይ በመሪነት የቆየ አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ማግኘት አይቻልም። ኢዴፓ ከተመሰረቱ ረዥም እድሜ ካስቆጠሩ ፓርቲዎች አንዱ ነው። ለምሳሌኢዴፓ ባሳለፋቸው 16 አመታት ውሰጥ ዶ/ር አድማሱ ገበየሁን፣ አቶ ልደቱ አያሌውን፣ አቶ ሙሼ ሰሙን እና በአሁኑ ወቅት ደግሞ ዶ/ር ጫኔ ከበደን ፓርቲውን እንዲመሩ መርጧል። ታድያ ዴሞክራሲያዊ ባህልን ተቃዋሚም ሆኖ እየተገበረው ያለው ማነው? ታድያ ማነው ከአንባገነናዊ አቋምና ከስልጣን ጥመኝነት አንጻር ከኢህአዴግ ጋር የበለጠ የሚቀርበው ኢዴፓ ወይስ መድረክ?

በመጨረሻ ግን ኢዴፓ በጋራ ምክር ቤቱ ላይ ያለውን አቋም ተናግሬ የዛሬውን ጽሁፌን ልቋጭ። የአገራችን የቆየ የፖለቲካ ባህልበተለይም የ1960ዎቹ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለሃገርም ለወገንም እንደማይበጅና እየቆየና ስር እየሰደደ ከሄደ ደግሞ በሃገር ህልውና ላይ የራሱን ተጽዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። አብዛኞቹ የዛ ትውልድ ግለሰቦች አሁንም በገዥውም ፓርቲ ሆነ በተቃዋሚው ፓርቲ መሪነት ላይ በብዛት መታየታቸው ዘመኑን የሚመጥን ፖለቲካ የማየት እድላችንን አጥብቦታል። ያ ትውልድ በጎ ተሞክሮ ጭራሽ የለውም ማለቴ እንዳልሆነ ይሰመርበት።

የሃቀኝነትንና እውነቱን ተናግሮ የመሸበት የማደርን ፖለቲካ ገፍተን በሴራ ፖለቲካ፣ በጥላቻ ፖለቲካና በፍጥጫ ፖለቲካ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለማምጣት ማሰብም ቅዠት ነው የሚሆነው። እንደውም የጥላቻ፣ የሴራ፣ የፍጥጫና የአሉባልታ ፖለቲካ በተራው ጥላቻን፣ ሴራን፣ ፍጥጫንና አሉባልታን ስለሚዘራ ሁኔታው በዚህ ትውልድ መገታት ካልቻለ በሂደት ሃገሪቱን ወደ እርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ሊያስገባት ይችላል። እንዲህ አይነቱ የፓርቲዎቹና የመሪዎቻቸው የፖለቲካ ስብዕና የማይቀየር ከሆነ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ተስፋችንን የሚያጠወልግ ብቻ ሳይሆን እንደዚህ በጋዜጣሃሳባችንን የመግለጽ እድላችንንም ነው የሚነጥቀን።

አንዳንዶቹ ፓርቲዎች የሚያራምዱት የጥላቻ ፖለቲካ የሚያመጣው ውጤት ሳይገባቸው ቀርቶ ሳይሆን የእወደድ ባይነት ፖለቲካ እስረኛ በመሆናቸው የመጣ በሽታ ነው።ለዚህ ነውይሄን ስልጡን የፖለቲካ ባህል ተቀብለው የእውቅና ፖለቲካ፣ የመቻቻል ፖለቲካ፣ የመከባበር ፖለቲካ አቀንቃኝ ሆነው ወደ ጋራ ምክር ቤቱ ብቅ ቢሉ ከሃዲ፣ ቅጥረኛ፣ ተለጣፊ፣ ከፋፋይ፣ አሻንጉሊትና አጨብጫቢ መባልን ፈርተው የማያምኑበትን ግን ጎጂ የሆነውን አቋም ማራመድን የመረጡት።መድረክም በግልጽ የዚህን መድረክ አስፈላጊነት ሲተች ሰምቼ አላውቅም።በፊት የጋራ ምክር ቤቱ ምስረታ አካባቢ ኢዴፓ ያለበት መድረክ ላይ መገኘት አልፈልግም የሚል ነበር አቋሙ። ዛሬ ደግሞ እኔን ስለማይመጥኑኝ ነው ወደሚል ራስን በቅጡ አለማወቅ ትምክህት ውስጥ ገብቷል። ምን ያህል የያዘው አቋም እንደሚያዋጣው ወደፊት የምናየው ነው የሚሆነው።

ሌላው ደግሞ ቀደም ብዬ እንዳልኩት አብዛኞቹ በ1960ዎቹ ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ስለሆኑ አስከ ደም ማፋሰስ የደረሰ የፖለቲካ ሽኩቻ ውስጥ የቆዩ በመሆናቸው ዛሬ ላይ የሚያደርጉት የፖለቲካ ትግል የትናንቱን ቂም በቀል ማወራረጃ እንጂ ለዛሬው ትውልድና ለነገዋ ኢትዮጵያ የማይበጅ ሲሆን እያየን ነው።ነገር ግን ይሄን የሃገራችንን ካለመከባበርና ከመናናቅ የሚመነጭ የፖለቲካ ባህል ቀይረን በመከባበርና በመደማመጥ አዲስና ስልጡን የፖለቲካ ባህል መትከል ካልቻልን የትም እንደርሳለን ብዬ አላምንም።

ኢዴፓ ይሄ የቆየ ፖለቲካ ባህላችን ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ከምስረታው ጀምሮ የተረዳና ይሄንን ለመታገል የቆረጠ ፓርቲ ነው። ኢዴፓ ለሃገር ይበጃል በሚለው አዲስ ባህል ውስጥ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች የመደማመጥ፣ የመከባበርና ሰጥቶ የመቀበል ፖለቲካ ሲጀምሩ አንዳችን የሌላችን ስጋት መሆናችን ይቀራል ይላል። እንደውም በተቃራኒው አንደኛችን ለሌላኛው ህልውና ዋስትና ሰጪ እንሆናለን። ስለዚህ የአብሮ መስራት፣ የመደማመጥ፣ የመከባበር በአጠቃላይ የመቻቻል ፖለቲካ ባህል እንዲሆን ኢዴፓ ትውልዱ የሚከፈለውን መስዋዕትነት መክፈል አለበት ይላል። ትውልዱ የራሱን ዘመን በራሱ መቃኘት ግድ ይለዋልና።

ይሄ የሴራ የሻጥርና የአሉባልታ ፖለቲካ አሁንም በዚህ ዘመን የሃገራችን ፖለቲካ ስልጡን እንዳይሆን ማነቆ ሆኖ ይገኛል። ኢዴፓ ግን ይሄን የነተበ የፖለቲካ ባህላችንን ፊት ለፊት በመዋጋት የሚመጣውንም ፈተና እየተጋፈጠ ፋና ወጊ በመሆን የሚከፈለውን ዋጋ እየከፈለ ነው። ወደፊትም ብዙ ትግስት አስጨራሽ ሁኔታዎች እየገጠሙትም ቢሆን እጁን ሳይሰጥ መቀጠል እንዳለበት እምነቴ ጽኑ ነው። ኢዴፓ ይሄ የያዘው ስልጡን ፖለቲካ የሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችና የህዝቡ እንዲሆን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።ስለዚህ በጋራ ምክር ቤቱ ያለን ተሳትፎ ይሄን ያረጀና ያፈጀ ያለመደማመጥና ያለመከባበር የፖለቲካ ባህል ለመትከል የተሻለ መድረክ እንደሆነ በማመን ነው። የጋራ ምክር ቤቱ የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የጋራ መድረክ ሆኖ የጥላቻና የፍጥጫ ፖለቲካ ቦታ እንዳይኖረው እስከምናደርግ ድረስ ትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥላል። ብሄራዊ መግባባት የሚጀምረው ተቀራርቦ በመነጋገርና በመወያየት እንደሆነ ጠንቅቀን እንረዳለን። ጽንፍና ጽንፍ ሆኖ ድንጋይ በመወራወር ዴሞክራሲያዊ ስርአት አይገነባም። ይሄ ጽሁፍ የግሌን አቋም ነው የሚያንጸባርቀው። ቸር ይግጠመን።

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
930 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 827 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us