በሰማያዊ ፓርቲ ጉዳይ እውነቱን እነሆ

Wednesday, 20 April 2016 13:21ሰማያዊ ፓርቲ መታመስ የጀመረው አሁን ሳይሆን ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ይህም ድርጊት የተጀመረው በሊቀመንበሩና የስራ አስፈጻሚ አባልና የፓርቲው የሴቶች ጉዳይ በነበረችው በወ/ሮ ሃና ዋለልኝ በተፈጠረው አለመግባባት ነው።


ሰማያዊ ፓርቲን ከመመስረታችን በፊት አንድነት ከመሰረቱት ምሁራንና ወጣቶች መካከል የዛሬዎቹ ይልቃል ጌትነትና ወረታው ዋሴ ይገኙበታል።አንድነት ከተመሰረተ በኋላ ይልቃል የፓርቲው ድርጅት ጉዳይ ጸሐፊና የብሔራዊ ምክር ቤት አባል ሲሆን ወረታው ደግሞ የፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮምሽን አባል ሆነው በመስራት ላይ እያሉ የፓርቲው ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ታሰረች።ይህን ተከትሎ አንዳንድ የስራ አስፈጻሚና የም/ቤት አባላት በሊቀመንበሯ መታሰር ምክንያት የአንድነት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የወሰደውን አቋም በመቃወም የውስጥ ትግል ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜ ይልቃል ደብረወርቅ ቤተሰብ ጋ ለበዓል ሄዶ ስለነበር ሲመለስ በኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው አማካኝ ከጸሐፊነቱ ተባሮ በምትኩ አሁን የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በቃሊቲ እስር ቤት የሚገኙትን አቶ መላኩ ተፈራ ይሾማሉ። ከዚህ በኋላ የፓርቲው የውስጥ ትግል እየጠነከረ ሄደ። ስሙንም ‘መርህ ይከበር’ በማለት ተሰየመ። እንግዲህ በዚህ ወቅት ነው በኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ም/ሊቀመንበርነት የሚመራው አንድነት መሪውን እስር ቤት አስቀምጦ ከ25 በላይ የሚሆኑ ጠንካራ አባላት በሥነ-ሥርዓት እርምጃ ሰበብ ከፓርቲው ያባረረው። ከዛም የተባረርነው አባላቶችና እንዲሁም የእኛን ሐሳብ የተቀበሉ አባሎች ለሁለት ዓመት ያህል እልህ አስጨራሽ ትግል ካደረግን በኋላ አንድነትን ለማስተካከል ያደረግነው ትግል በምርጫ ቦርድ ጣልቃ ገብነት ለፍትሕ ሚኒስቴርና ለፌዴራል ፖሊስ በተጻፈ ደብዳቤ ቦርዱ የሚያውቀው የወቅቱ የአንድነት ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የሚመሩትን ስለሆነ ሌላ አንድነት ነኝ የሚለውን አካል አደብ አስገዛልኝ በሚል ትዕዛዝ አንድነትን የማስተካከሉ ትግል በዚሁ ቆሞ አዲስ ፓርቲ እንመስርት ወደሚል ሐሳብ ሲገባ አብረውን መርህ ይከበር ብለው ለሁለት ዓመታት ከእኛ ጋር የነበሩ አንጋፋ ፖለቲከኞችና ምሁራን በቃን ብለው አንዳንድ ምክር በመስጠት አሁን ምክራቸው ተግባራዊ ባይሆንም ከእኛ ተለዩ። ከዛም አዲስ ፓርቲ የማቋቋም ሂደቱ ተጀምሮ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ ተረቆ ታህሣሥ 22 ቀን 2004 ዓ.ም ሰማያዊ ፓርቲ በ122 የመስራች ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ተወለደ።


ከመስራች ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ የጉባኤው ሰነዶች ለምርጫ ቦርድ ተቀብለው ተብቀው ቢገቡም ቦርዱ ሊቀበለን ፈቃደኛ ስላልሆነ እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ውስጥ መብቱን አሳልፎ ያልሰጠውን ሰማያዊ ፓርቲ በይፋ የምርጫ አዋጁ በሚፈቅደው መሰረት ፓርቲ ሆኖ ስራ መጀመሩን የሚገልጽ ደብዳቤ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጽፎ ስራ በመጀመሩ ቦርዱ ምንም ማድረግ ስላልቻለ ሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም የምስክር ወረቀት ሊሰጠው ችሏል።


እንግዲህ ሀ ብሎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቤዛ ለመሆን የተመሰረተው ሰማያዊ ፓርቲ በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር ለስምንት ዓመታት ተከልክሎ የነበረውን የተቃውሞ የአደባባይ ሰልፍ ግንቦት 25/2005 ዓ.ም ሲያደርግና አመራሩም በወጣቶች የተገነባ መሆኑን ሕዝቡ ሲያይ ተቀባይነቱ እየናረ መጣ። ከግንቦት 25 በኋላም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን በምክር፣ በጽሑፍ፣ በማቴሪያልና በገንዘብ ያዥጎደጉዱት ጀመር። የፓርቲው አመራርና አባላትም ይህን በመጠቀም ትግሉን ወደ ፊት ማራመድ ጀመሩ። ተደጋጋሚ ሰልፎችንም በመጥራት ገዢውን ፓርቲ ማስጨነቅ ተጀመረ። በዚህ ጊዜ ግን አባላት ላይ ውክቢያውና እስሩ እየበረታ መጣ። ከዛን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በእስር ላይ ያሉ አባላት አሉ። ስለ አመሰራረቱና ስለትግል እንቅስቃሴው ይህንን ያህል ካልኩ ወደ ወቅቱ የሰማያዊ ፓርቲ ችግር ልግባ።


የዛሬ ጽሑፌ የሚያተኩረው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ከሆነው ይልቃል ጌትነትና የቀድሞው የፓርቲው ፋይናንስ ኃላፊ ስለነበረው ወረታው ዋሴ ነው። ይልቃል የፓርቲው ሊቀመንበር በነበረበት ጊዜ ላለፉት ሶስት ዓመታት ከጠቅላላ ጉባኤው በፊት በነበሩት የስራ አስፈጻሚዎች ድክመቱ ተሸፍኖ ወደር የሌለው መሪ መስሎ ታይቷል። ይህም የሆነው በወቅቱ ፓርቲው ሲመሰረት በቁጭትና በስሜት ስለነበር ሁሉም ስለስራ እንጂ ስለድክመት የሚያወራበት ጊዜ ስላልነበር በደቦ ስራ የይልቃል ችግር ሊታይ አልቻለም። ይህ የደቦም ስራም ወይም ትግል የግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም ሰልፍን ምክንያት በማድረግ ለፓርቲው የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ እየጨመረ ሲመጣ የፓርቲው የፋይናንስ አቅም ሲጎለብት ሚዲያውም ሰማያዊ ሰማያዊ ማለት ይጀምራል። በተለምዶ ገንዘብ ሲጠፋ ተመዘበረና ባከነ ይባላል፤ ጉዳዩ ግን ሌላ ነው። ይህን የደቦ ስራ ተከልሎ ነው እንግዲህ ይልቃል ጌትነት እጁን ወደ ሌብነት የዘረጋው። ይህ ለሶስት ዓመት የቀጠለ ሌብነት የ2007 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ምርጫና የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ውጥረት ውስጥ ከቶ እንዳያልፍ የለ ሁለቱም ጉዳዮች አለፉ። ከዛም አዲሱ የፓርቲው ም/ቤትና ስራ አስፈጻሚ በከፊልም ቢሆን ስራ ጀመሩ። ስራ እንደጀመሩም በፊት ሲነሳ የነበረው ገንዘብ ተሰርቋል የሚለው ክስ እንደገና ሲያገረሽ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ሶስት አባላት ያሉት አጣሪ ኮሚቴ አቋቁሞ እንዲያጣራ ያደርጋል። አጣሪ ኮሚቴውም መጠኑ ያልታወቀ (አሁን ኦዲት እያጣራው ነው) ተሰርቋል ሲልና የሥነ-ሥርዓት ክስ ተመስርቶ ገንዘብ መሰረቁ ሲረጋገጥ ይልቃል ጌትነት ውሎውን አራት ኪሎ ሻይ ቤቶች አድርጎ ፓርቲውን እያመሰ ትግሉን ወደ ፌስቡክ ትግል አሸጋግረው። ይህም አልበቃ ብሎት አባላትን በወያኔነት መክሰስ ጀመረ። ይህ ከቀድሞ የተቃዋሚ ፓርቲ አንዳንድ አመራሮች የወረሰው አንዱ የትግል ልምዱ ነው። ይልቃል ላለፉት አምስት ወራት በሀገራችን በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል በተነሳውን ግጭት የብዙ ወገኖቻችን ሕይወት እየጠፋ እያለ አንድም ቀን እንኳን ስራ አስፈጻሚውን ሰብስቦ መግለጫ ለመስጠት አልሞከረም። ይህን የተረዳው የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤትም ግራ ሲገባው መግለጫ አውጥቷል። ይልቃል ግን ‘ሰርቀሃል’ ሲባል አንድ ጊዜ አውሮፓ ህብረት፣ ዶቼቬሌ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የአሜሪካ ሬዲዮ ጣቢያ በመሮጥ ሌብነቱን ሊያስተባብል ይሞክራል። የፖለቲካ ዕድገቱ ሁል ጊዜ እንደ ካሮት ወደ ታች የሆነው የይልቃል ስርቆት ከአባላትና ከሕዝብ ተደብቆ መኖር ስለሌለበት እውነቱ መገለጽ ስላለበት እቺን ታህል ለመግለጽ ሞክሬያለሁ። ሌላውን ወደፊት ከሰነዶች ጋር በማስደገፍ ይፋ ለማድረግ እሞክራለሁ።


ሁለተኛው ሰው ደግሞ ወረታው ዋሴ ነው። ወረታው እኛ አንድነት ውስጥ ሆነን ‘መርህ ይከበር’ ስንል እሱም ይል ነበር። ነገር ግን መርህ ሳይገባው መርህ ይከበር ማለቱ አሁንም አልገባውም። በዛን ወቅት ወረታው የአንድነት ፓርቲ ኦዲትና ምርመራ ኮምሽን አባል ነበር ከእሱ ጋርም አቶ ፀጋዬ አላምረው ሻ/ል አየለና አሁን በሕይወት የሉም ሌሎችም ነበሩ። ታዲያ ወረታውን ለኦዲትና ምርመራ ኮምሽን የመረጠው የአንድነት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ነበር። እንደ አቶ ፀጋዬ እና እንደ ሻ/ል አየለ ገለልተኛ ሆኖ ችግሩን መፍታት ወይም ለመፍታት መሞከር ሲኖርበት ያንን ሳያደርግ ቀረ። ሌሎቹ ግን የገለልተኛ ስራቸውን ሰርተው ሁለቱም ያመኑበትን ለመከተል ወስነዋል። ፀጋዬ እዛው አንድነት ውስጥ ሲቀር ሻ/ል አየለ ግን ሰማያዊን ተቀላቅለው እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ የምክር ቤት አባል በመሆን ለመርህ መገዛታቸውን አስመስክረው አልፈዋል። ለመርህ መገዛት ማለት ይሄ ነው።


ወረታው በተፈጥሮው ከእሱ በላይ አዋቂ ያለ አይመስለውም። የፓርቲያችንን መተዳደሪያ ደንብ የመተርጎም ብቸኛ ስልጣን የተሰጠው ለፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮምሽን መሆኑ እየታወቀ ወረታው ግን ደንባችንን ሁልጊዜ እሱ በፈለገው መንገድ ተርጉሞ ለመፈጸም ሲሞክር ይታያል። አንድ ምሳሌ ላንሳላችሁ ላለፉት አስራ ሁለት አመታት ይሰራበት የነበረው መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያባርረዋል። ይህን ተከትሎም በይልቃል በኩል ወረታው በፖለቲካ አመለካከቱ ከስራው ተባረረ እያለ አስወራለት። ወረታውም ሚስጥሩን በሆዱ ይዞ መኮፈስ ጀመረ። በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰራተኛ ማህበር መተዳደሪያ ደንብ መሰረት አንድ የአስተዳደር ሰራተኛ በስሩ ያሉ ሰራተኞች ሲያጠፉ የመቅጣት ግዴታ አለበት። ይህንን ካላደረገ እንደጥፋቱ ታይቶ ኃላፊው ይቀጣል። አቶ ወረታውም ከአስራ ሁለት ዓመት በላይ የሰራበትን መስሪያ ቤት መተዳደሪያ ደንብ አንድም ቀን ዞር ብሎ አይቶት ስለማያውቅ በደንቡ መሰረት ከህዳር 2007 ዓ.ም ጀምሮ ድርጅቱ ከስራ ያሰናብተዋል። አዋቂ ነኝ ማለት ትርፉ ይሄ ነው ሳያውቁ። ሰውየውም ይህን የራሱን ጥፋት ለፖለቲካ ትርፍ መጠቀሚያ ያውለዋል።


ከዛ በኋላ ከስራው እንደተባረረ ውሎውን በፓርቲው ጽ/ቤት ማድረግ ይጀምራል። እንግዲህ አንድ የስራ አስፈጻሚ አባል ያውም የፓርቲው የፋይናንስ ኃላፊ ጠዋት ሁለት ሰዓት እንደ ቋሚ ሰራተኛ ቢሮ ይገባል፤ ለምሳ ስድስት ሰዓት ይወጣል፤ ስምንት ሰዓት ተመልሶ ይገባል። የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ካለ እስከማታ ሁለትና ሶስት ሰዓት ድረስ ያመሻል። አንድ ከስራ የተባረረ ሰው ምንም ገቢ የሌለው ቀን ለምሳ በትንሹ ሰላሳ ብር፣ ትኩስ ነገር ከወሰደ ስምንት ብር፣ መኖሪያውም አዲሱ ገበያ ስለሆነ በትንሹ ደርሶ መልስ የትራንስፖርት አስራ ሁለት ብር ወጪ ያወጣል። እንግዲህ ይህን ወጪ በወር ደምሩት፤ ተጨማሪ የቤት ኪራይ እንዳለበትና ቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደሆነ ይናገራል። ታዲያ ወረታው ላለፉት አስር ወራቶች ያለምንም ክፍያ ቢሮ መዋሉን አላቋረጠም። እንግዲህ ይህ እየሆነበት ባለበት ወቅት ነው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ የተደረገውና የፓርቲው የፋይናንስ አወጣጥ ሂደት ሃምሳ ከመቶው የሆነው ደጋፊ ሰነድ የለውም የሚል ሪፖርት በኦዲትና ምርመራ ኮምሽን በኩል ቀርቦ ጉባኤው ከተወያየበት በኋላ ሂሳቡ በደንብ እንዲጣራ ውሳኔ አሳልፎ የተበተነው። እንግዲህ ይታያችሁ ከጉባኤ በኋላ ይልቃል ስራ አስፈጻሚውን መልምሎ በም/ቤቱ ማጸደቅ ስላለበት ካመጣቸው አስር የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እጩዎች ውስጥ በሌብነት የሚጠረጠረውን ወረታውን በራሱ ፈቃድ አልፈልግም ያለውን ስለሺን ይዞ የመጣው። በዚህ ጊዜም ም/ቤቱ ሰባቱን እጩዎች ተቀብሎ እያስጴድን በብቃት ማነስ፣ ወረታውን በእምነት ማጉደል እንደሚጠይቀው አሳውቆ ስብሰባው ይጠናቀቃል። ከዚህ በኋላ ለመርህ የማይገዛው ወረታው እኔ የፋይናንስ ኃላፊ ሆኜ ካልሰራሁ፣ ያለፈ የፋይናንስ ሰነድ ካልደለዝኩና የበፊቱን ሌብነቴን ካልቀጠልኩ በማለት ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ይጀምራል። ም/ቤቱም በያዘው አቋም ይፀናል። በነገራችን ላይ ይልቃልና ወረታው ም/ቤቱን ያልተረዱት ም/ቤቱ ያለው ወረታው ፋይናንስ ኃላፊ አይሆንም አለ እንጂ በሌላ ቦታ ላይ አይቀመጥ አላለም ነበር። እነዚህ ከላይ ስማቸውን የጠቀስኳቸው ሁለት ሰዎች በአሁኑ ወቅት ሌብነታቸውን ለመሸፈን አንዱ በፌስቡክ፣ አንዱ ደግሞ በሚዲያ የሚያደርጉት ከእኛ በላይ ማን ታጋይ አለ የማለት አባዜያችው አመራር በነበሩበት ወቅት የዚህን ያህል ግማሹን እንኳን ለፓርቲው ስራ ቢያውሉት ኖሮ ይህ ሁሉ ችግር ባልተፈጠረ ነበር። በነገራችን ላይ ፅሑፌ ሁለት ሰዎች ላይ ብቻ ያተኮረው ይልቃል ሊቀመንበር፣ ወረታው ደግሞ በወቅቱ የፋይናንስ ኃላፊ ስለነበረ ነው። ሁለቱ ደግሞ ተላላኪና ፈጻሚዎች ስለሆኑ ነው። ስለእነሱ ደግሞ ወደፊት እመለስበታለሁ። አንባቢያንን ይቅርታ የምጠይቀው አንዳንድ ቃላቶች ፅሑፉ ውስጥ በግልጽ የተቀመጡት ባለማወቅ ሳይሆን እስከዛሬ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ያበላሸው አካፋን አካፋ ባለማለታችን መሆኑን በመረዳቴ ነው። ስለዚህ የዛሬ ፅሑፌን እዚህ ላይ ላብቃና በሚቀጥለው ፅሑፌ ሰነዶችን እያያያዝኩና የፓርቲያችንን መተዳደሪያ ደንብ እየጠቀስኩ የምመለስ መሆኑን እገልጻለሁ።


እንደሻው እምሻው
የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤትና አስተዳደር ኃላፊ
ሚያዝያ 2008 ዓ.ምn

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
621 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1047 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us