“ዓሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል”

Monday, 02 May 2016 16:14

ያለፈው ሣምንት ፅሑፌን እንደመንደርደሪያ የተጠቀምኩበት ሲሆን በቀጠሮዬ መሰረት ወደ ዋናው ጉዳይ እገባለሁ። የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት ወረታው ለአስር ወራት የፓርቲው ገንዘብ ሲቦጠቡጥበት ከነበረበት የፋይናንስ ኃላፊነት ላይ ድጋሚ እንደማያስቀምጠው ሲያውቅ ስራ ፈልጎ ለመግባት የአንድ ወር ጊዜ እንኳን አልፈጀበትም። ይህን ስራ ከጀመረ በኋላ ደግሞ የምክር ቤቱ ስብሰባ በተጠራ ቁጥር ቂም ቋጥሮ ስብሰባውን በተደጋጋሚ በመበጥበጡ በም/ቤቱ ሰብሳቢ አማካኝነት የሥነ-ሥርዓት ክስ ተመስርቶበት መቀጣቱ ይታወቃል። የተወሰነበትን ቅጣት ባይከፍልም። ይህ አልበቃ ብሎት እንደገና ም/ቤቱ በሚሰበሰብበት ወቅት እሱ የም/ቤት አባል መሆኑን ረስቶ የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴው ሪፖርት ሲያቀርብና በሪፖርቱም ላይ ትችት ሲቀርብ ሊቀመንበሩ ወይም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መልስ መመለስ ሲገባቸው ስለ ሥራ አስፈጻሚው የሚከራከረው እሱ ነው። ታዲያ ይሄን ሰው ምን እንበለው? ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያበቅላል የሚባለው ተረት ለእሱ ይሆን­?

አሁን ደግሞ ወደ ይልቃል ልመለስ። ይልቃል ከደንብና መመሪያ ውጪ ምንም ቃለጉባኤ ባልተያዘበት የፓርቲ አመራር አባላት ደሞዝተኛ ናቸው በማይልበት ፓርቲው ውስጥ ላለፉት ሶስት ዓመታትና አሁንም ድረስ በወር የአምስት ሺህ ብር ደመወዝ ተከፋይ ነው። እንደውም በዚህ ዓመት ለዋናው ጽ/ቤት ኪራይ የሚከፈል በም/ሊቀመንበሩ በአቶ ነገሰ ተፋረደኝ ጠያቂነት ከውጭ ደጋፊዎቻችን ከተላከው አንድ መቶ ሺህ ብር ላይ አርባ ሺህ ብሩን በደሞዝ መልክ የወሰደው እሱ ነው።

ወደ ሰነድ ማስረጃዬ ልግባ። ከሀምሌ 2006 ዓ.ም ጀምሮ አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ፣ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ እና ሌሎችም ለእስር ይዳረጋሉ። በዚሁ ዓመት ነሀሴ መጨረሻ ላይ ደግሞ በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አባላት ወይም ደጋፊ አይደሉም ተቆርቋሪዎች ናቸው ለአብርሃ ደስታ አንድ ሺህ ዶላር እና ለሌሎች እስረኞች ደግሞ አንድ ሺህ አራት መቶ ዶላር በድምሩ ሁለት ሺህ አራት መቶ ዶላር በአንድ ደጋፊያችን በሆኑ ግለሰብ በኩል ይመጣል። ይህን ኃላፊነት ወስዶ ለእነዚህ እስረኞች ማን ያድርስ የሚል ሃሳብ ሲቀርብ ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ ትከሻ ላይ ያርፋል።

ይሄ እስኪሆን ድረስ ግን አሁን ሀገር ውስጥ የለም የም/ቤታችን ፀሀፊ ሳሙኤል አበበ ከግለሰቦችና ከም/ቤት አባላት ገንዘብ እንዲዋጣ እያደረገ ማዕከላዊ እስር ቤት ለነበሩ እስረኞች ስንቅ ያመላልሳል። እንደውም በአንድ ወቅት ከአባላት አንድ ሺህ ብር እና ከጓደኞቹ አንድ ሺህ ብር አሰባስቦ የአብርሃ ደስታን እህትን ሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ድረስ እንድትመጣ ካደረገ በኋላ የተወሰኑ የም/ቤት አባላት በተገኙበት የሁለት ሺህ ብር እርዳታ አድርጎላታል። ይህንን ለአብርሃ ደስታ ነግራው ምስጋና አቅርቧል። የኋላ የኋላ ሳሙኤል ሰው መለመኑ ይሰለቸውና ይልቃልን ከፓርቲው አካውንት የተወሰነ ብር ይውጣና ለእስረኞች ስንቅ እናድርሰበት ፍቀድልኝ ሲለው ይልቃልም ሳሚ አታስብ ከውጪ ደጋፊዎቻችን አስር ሺህ የኢትዮጵያ ብር ተልኳልና በእሱ ስንቅ እናደርሳለን ይለዋል። በዛን ወቅት ም/ቤቱ በየሳምንቱ አስቸኳይ ስብሰባ ያደርግ ስለነበር ስብሰባው ከመጠናቀቁ በፊት አንድ የም/ቤት አባል ደግሞ እባካችሁ ለእስረኞች ስንቅ የሚሆን ገንዘብ እናዋጣ ሲል ሳሚም አሁን ምንም ችግር የለም ከውጪ ሀገር አስር ሺህ ብር ይልቃል መጥቷል ብሎኛል ስለዚህ በእሱ ስንቅ እናመላልሳለን ይላል።

ከዚህ በኋላ ያን ዶላር ያመጡትና መምጣቱን የሚያውቁ አባላት እኔን ጨምሮ ጉዳዩን ለፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮምሽን ሪፖርት እናደርጋለን። በዚህ ጊዜ ሪፖርት የቀረበለት ኦዲት ይልቃልን ስለገንዘቡ ይጠይቀዋል። እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ይሸመጥጣል። ዶላሩን ግን እኔ በፅ/ቤት ኃላፊነቴ፣ ወረታው በፋይናንስ ኃላፊነቱ ይልቃል በሊቀመንበርነቱ ስለሚመለከተን አንድ ሁለት ብለን ቆጥረን ለእስረኞቹ እስከሚሰጥ ድረስ ቢሮ ባለው የፓርቲው ካዝና ውስጥ ለጊዜው እንዲቀመጥ ይደረጋል። ከዛ በኋላ ግን ወይንሸት ሞላ በመጀመሪያ ቀን አምስት መቶ ዶላር አውጥታ አንዱን ዶላር በሃያ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ዘርዝራ ታመጣለች። በእዛን ወቅት እኔ ለእስረኞቹ የሚላክ ነበር  የመሰለኝ።

ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ደግሞ አሁንም የተወሰነ ዶላር ልትዘረዝር ስትሄድ በወቅት በተደጋጋሚ ትታሰርና ትፈታ ነበርና እባክሽን አንቺ ልጅ እነዚህ ሰዎች ያውቁሻልና አሁን ደግሞ በህገወጥ ገንዘብ ዝውውር እንዳያስሩሽ ብዬ ብመክር ሰሚ አጣሁ ያሁሉ ዶላር እየተዘረዘረ አሁን በየፌስቡኩ የሚንጫጩትን ግለሰብ አምላኪ ወጣቶች አፈሩበት ገንዘቡም አለቀ። እስረኞቹም ምንም ሳይደርሳቸው ሳሚም በሁኔታው ተስፋ ቆርጦ አገር ጥሎ ተሰደደ። አሁን ኬንያ ይገኛል። ተጨማሪ መረጃም የሚፈልግ ካለ ከእሱ ማግኘት ይቻላል። ከእዛ በኋላ እኔም ከወረታው፣ ከይልቃል፣ ከወይንሸትና ከስለሺ ጋር በአይነ ቁራኛ መተያየት ጀመርኩ። እንግዲህ ዶላሩ የመጣው ከላይ እንደገለጽኩት ነሀሴ መጨረሻ ላይ ነው። ይልቃል ግራ ሲገባው ፓርቲው በወቅቱ ብር ስላልነበረው ዘርዝረን ለፓርቲው ስራ ተጠቅመንበታል አለ። በዛን ጊዜ ግን ፓርቲው ብር ነበረው የእስረኛ ብር አይፈልግም። ዶላሩ ለፓርቲው ስራ እንኳን ቢውል የገቢ ደረሰኝ በዶላር ወይም በኢትዮጵያ ብር ይሄን ያህል ገንዘብ ገብቷል ተብሎ ደረሰኝ መቆረጥ ነበረበት። ይህ ሁሉ ሳይደረግ ኦዲት የዚህን ዶላር መድረሻ አሳውቁኝ ብሎ የጊዜ ገደብ ሲያስቀምጥባቸው ዶላሩ በመጣ በሶስተኛ ወሩ ህዳር 10/2007 ዓ.ም አንድ ደጋፊያችን ጋ ስለሺ ፈይሳ ይደውልና እባክሆትን ለአስቸኳይ ስራ ጉዳይ ገንዘብ ስለምንፈልገው ሰላሳ ሺህ ብር አበድሩን ብሎ ያስጨንቃቸዋል በማግስቱም ግለሰቡ ገንዘቡን ይዘው ይመጣሉ እኔ ቢሮ ነበርኩ ይልቃልም በእዛን እለት የዘጠኙ ፓርቲዎች ስብሰባ ስለነበር በጠዋት መጥቶ ስብሰባ ላይ ነው አበዳሪያችንም ምን ሆናችሁ ነው እንዲህ ያጣደፋችሁኝ ሲሉኝ እኔ ምንም ስለማላውቅ እስቲ ወይንሸትን አናግሯት አልኩኝ ይልቃል የሰውየውን ድምጽ ሲሰማ ስብሰባውን አቋርጦ በመውጣት ሰውየውን ወደፋይናንስ ቢሮ ይዞት ሄደ። በማግስቱም ከሶስት ወር በኋላ የአብርሃ ደስታ አንድ ሺህ ዶላር በሃያ የኢትዮጵያ ብር ታስቦ አዋሽ ባንክ ገባ የሚል ሰነድ በወረታው በኩል እኔና ኦዲቶች ባለንበት አሳዩን።

እንግዲህ ተመልከቱ የመጀመሪያው አምስት መቶ ዶላር የተዘረዘረው በሃያ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ነው ብያለሁ አንድ ሺህ ዶላሩ በዚሁ ሂሳብ እንኳን ቢዘረዘር ለአብርሃ ደስታ ይደርሰው የነበረው ሃያ አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ነው። ባንክ ገቢ የሆነው ግን ሃያ ሺህ ብር ብቻ ነው። በኋላም ላይ በፓርቲው ውስጥ እንዴት የእስረኛ ብር ይበላል በማለት ጭቅጭቅ ይፈጠራል። ይልቃልና ወረታው ግን ገንዘቡ የመጣው በፓርቲው ስም አይደለም በይልቃል በግሉ ስለሆነ አያገባችሁም ማለት ጀመሩ። ያልገባቸው ግን እነሱ ነበሩ። ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ይልቃልን ማንም ሰው አያውቀውም ነበር። የታወቀው ግን የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ስለሆነ ብቻ ነው። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን ከፊታችን የ2007 አገር ዓቀፍ ምርጫ እና የፓርቲያችን ጠቅላላ ጉባኤ አለ እነዚህን ሁለት ጉዳዮች እንዴት እንለፋቸው በሚል አባላት ውስጥ ለውስጥ መነጋገር ጀመሩ። በተቻለ መጠን  ሁሉም ስራውን እየሰራ ምርጫውም አለፈ። ጉባኤውም ተደርጎ ጠንካራ ውሳኔዎችን አሳልፎ ተጠናቀቀ።

አዲሱም ም/ቤት ስራ ሲጀምር የመጀመሪያው ስራው በጠቅላላ ጉባኤው የተሰጠውን ስራ በተለይም ፋይናንስን በተመለከተ መስራት ነበር። ይህን ሲያደርግ ደግሞ ህጉን ተከትሎ ነው። ይልቃል አሁን በአንዳንድ ሚዲያና ጋዜጦች ላይ እየወጣ እንደሚያወራው ጠቅላላ ጉባኤው የፋይናንስ ሪፖርት ቀርቦለት ያንን ተቀብሎ ምንም ችግር እንደሌለበት ወስኖ ለምርጫ ቦርድ ሰነዱ ገብቷል ይለናል። በዛን ወቅት ለጠቅላላ ጉባኤ የቀረበው የፋይናንስ ሪፖርት ግን የሚለው ሂሳቡ የተዝረከረከ እንደሆነና በኦዲት ሪፖርት በናሙና ከታዩት የወጪ ሰነዶች ውስጥ ከሃምሳ ከመቶው በላይ የሚሆነው በደጋፊ ሰነድ ወይም በህጋዊ ደረሰኝ ያልተደገፈ መሆኑ ነው ሪፖርት መደረጉ የሚታወቀው የስብሰባውን ካሴት ማየት ይቻላል። እንደውም ወደፊት የሂሳብ አሰራሩ ለአዲሱ ብሔራዊ ምክር ቤት ቀርቦ በሂሳብ ባለሙያ እንዲታይ ነው ጉባኤው ውሳኔ ያሳለፈው። በዚህም ውሳኔ መሰረት ነው ፓርቲው የፋይናንስ አሰራሩን እንደገና መመርመር የጀመረው። በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 573/2000 መሰረት ማንኛውም ፓርቲ እስከ አስር ዓመት ድረስ ያለውን የፋይናንስ ሰነድ ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር በስርዓት መያዝ አለበት ይላል። አሰራርና ሂደቱ ተመልሶ እንዴት እንደነበር የመመርመርና በዛን ወቅት የነበሩ ኃላፊዎችን የመጠየቅ መብት አለው። ኃላፊዎቹ ካልሞቱ በቀር። ስለዚህ ይልቃልና ወረታው ደግሞ በህይወት አላችሁ አይደል እንዴ? ሰማያዊ ደግሞ ከተመሰረተ ገና አራት ዓመቱ ነው ታዲያ ምን ያግደዋል። ም/ቤቱም ይሄን ግንዛቤ ውስጥ በመክተት ነው እንግዲህ የፓርቲው የፋይናንስ ሰነዶች እንደገና እንዲታዩ ጥቅምት 7/2008 ዓ.ም ባደረገው አራተኛ ዓመት አንደኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ሶስት አባላት ያሉት አጣሪ ኮሚቴ ያቋቁማል ኮሚቴውም የፓርቲውን የፋይናንስ ሰነዶች መመርመር ይጀምራል።

በመጀመሪያም የሚመለከታቸውን ኃላፊዎችና ሰነዶችን እየመረመረ ጥሩ ጥሩ ማስረጃዎችን ማግኘት ሲጀምር መጨረሻው ያላማራቸው ወረታው፣ይልቃልና ወይንሸት አንዳንድ አባላትን መጎነታተል ይጀምራሉ ”ዓሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” እንደተባለው በተለይ ከላይ ለእነ አብርሃ ደስታ ለመክፈል በፓርቲው ስም የተበደሩትን ሰላሳ ሺህ ብር ከፋይናንስ መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ በሰነድ ላይ ወይንሸት ሞላ ጠያቂ፣ ወረታው ዋሴ አረጋጋጭ ይልቃል ጌትነት አጽዳቂና እንደገናም ወይንሸት ከፋይ፣ ወረታው ተቀባይ፣ ይልቃል አረጋጋጭ፣ በመሆን ፓርቲውን ሲዘርፉ እንደነበር ሰነድ የተገኘው። የፈረሙበትም ሰነድ ከዚህ ጽሑፍ ጋር ተያይዞ የቀረበው ነው። በዚህ አጋጣሚም አጣሪ ኮሚቴው ለሰማያዊ ፓርቲ ብድር የሰጡትን የተለያዩ ግለሰቦች ፓርቲው ቢሮ ድረስ ጠርቶ በእማኞች ፊት ላደረገላቸው ጥያቄ ሰላሳ ሺህ ብሩ እንዳልተመለሰላቸውና ብድሩን ስላልከፈላችሁኝ ነው መሰለኝ ብድርም መጠየቅ አቆማችሁ በማለት ማረጋገጫ ከሰጡን በኋላ ለሌላ ጥያቄ ኮሚቴው ሲጠራቸው ደግሞ ሃሳባቸውን ቀይረው ይልቃል እግራቸው ስር ስለወደቀባቸው ብቻ ማረጋገጫ እንኳን ሳያቀርቡ እረስቼው ሳይሆን አይቀርም ተከፍሎኛል መሰለኝ ይላሉ። እንግዲህ እንደነዚህ አይነት ሰዎች ናቸው ጥሩ የሰሩ እየመሰላቸው በተደጋጋሚ የፓርቲ መሪዎች ነን በሚሉ ግለሰቦች አማካኝነት ሕዝብ ተስፋ የጣለባቸው ፓርቲዎች እንዲፈርሱ ምክንያት የሚሆኑት።

እንደሻው እምሻው

የሰማያዊ ፓርቲ ፅ/ቤትና አስተዳደር ኃላፊn

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
649 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 826 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us