ሰሙነ ሕማማት

Monday, 02 May 2016 16:14

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከትንሣኤ በፊት ያለው አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት /የሕማማት ሳምንት/ በማለት ትዘክረዋለች። ሕማማት የሚለው ቃል ሐመ፣ ታመመ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማሙና ሞቱ የሚዘከርበት ሳምንት ነው። በሌላም በኩል ይህ ሳምንት ከአዳም እሰከ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ የነበሩ ነፍሳት በሲኦል የቆዩበት የአምስት ሺሕ አምስት መቶ የመከራ፣ የፍዳና የኩነኔ ዘመን መታሰቢያ ስለሆነ የሕማማት ሳምንት የሚለውን ስያሜ አግኝቷል።

 

በነቢዩ ኢሳይያስ ነስአ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ፣ በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ፣ ሕመማችንንም ተሸከመ፣ እኛ ግን እንደተመታ፣ በእግዚአብሔርም እንደተቀሰፈ፣ እንደተቸገረም ቆጠርነው። እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ፣ ስለበደላችንም ደቀቀ፣ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፣ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን። /ኢሳ.53፡4-7/ ተብሎ የተነገረው ቃል ተፈጽሞ ጌታችን ለድኅነተ ዓለም ሲል በአጭር ደረት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተቀበለው ጸዋትወ መከራ የሚዘከርበት ሳምንት ነው።
በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በአጸደ ቤተ ክርሰቲያን ተሰብስበው፣ ከሐሜት ከነገርና ከኃጢአት ርቀው፣ የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ ሲያዜሙ ግብረ ሕማም በመባል የሚታወቀውን መጽሐፍ ሲያነቡ፣ ሲሰሙ፣ ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ። ካህናትና ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፣ በሠለስት፤ በስድስት፣ በተስዓት /በዘጠኝ/፣ ሰዓት፣ በሠርክ /በዐሥራ አንድ/ሰዓት መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ።


በተለይ ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፣ ምክንያቱም ጌታችን የደረሰበትን መከራ ሥቃይንና 5ሺሕ 5መቶ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ግዞት ይኖር እንደነበር ለማዘከር ነው። ሰሙነ ሕማማት የጌታችን ሕማማት ከማሰብ ጋር በርካታ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የምናስብበት ሳምንት ነው።


ይህ ሳምንት ቅዱስ ሳምንት ይባላል። ከሌሎች ሳምንታት ሁሉ የተለየ የከበረ ነውና። ምክንያቱም በዚህ ሳምንት በእያንዳንዱ ዕለት ስለ ፍጹም ፍቅር የተከፈለ የመስዋዕትነት ሥራ ስለተሠራበት፤ የሰው ልጆች ደኅንነት ስለተፈጸመበት፣ መድኃኔዓለም ስለ እኛ ቤዛ ሆኖ ለመስቀል ሞት ታዛዥ ሆኖ ነፍሱን ስለካሠልን ቅዱስ ሳምንት ተብሏል። በተጨማሪም የመጨረሻ ሳምንት ተብሎ ይጠራል። ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሙዓለ ሥጋዌው ለፈጸማቸው የቤዛነትና የአርአያነት ተግባራት ፍጻሜ በመሆኑ ነው።


በዚህ ልዩ በሆነ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠልስት፣ በቀትር በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርሰቲያን በመጓዝ ስለጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ያዘክራሉ። ቅዱስ ያሬድ በመጨረሻው ሳምንት በየዕለቱ በጌታን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን ነገረ መስቀል በተመለከተ ያዘጋጀውን መዝሙር ይዘምራሉ፣ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ።


ሰሙነ ሕማማትን ከሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ልዩ የሚያደርገው ሥርዓት አለ። በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ደንብ መሠረት በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፣ ስብሐተ ነግህ አይደርስም፣ ሥርዓተ ማኅሌት፣ ሥርዓተ ተክሊል፣ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፣ ጸሎተ አስተሰርዮም አይደረግም፣ ጥምቀተ ክርስትና አይፈጸምም፣ በመስቀል መባረክ፣ ኑዛዜ መስጠትና መቀበል፣ እግዚአብሔር ይፍታህ ማለት አይኖርም። ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሳዕና ይከናወናሉ።


በአጠቃላይ ከዓመት እስከ ዓመት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ለምእመናን ይሰጡ የነበሩ መንፈሳዊያት አገልግሎቶች አቁመው ጌታችን መከሰሱን፣ መያዙን፣ ልብሱን መገፈፉን፣ በጲላጦስ ዐደባባይ መቆሙን፣ ሕማሙን፣ መከራውን፣ መስቀል ላይ መዋሉን፣ ሐሞት መጠጣቱን እና ሌሎችንም ለኃጢአተኛው የሰው ልጅ ሲባል የተከፈለውን ዕዳ በሚያስታውሱ አገልግሎቶች ይተካሉ። በተጨማሪም ማንኛውም ክብረ በዓል በዚህ ሳምንት ቢውል ከትንሣኤ በኋላ እንዲከበር ይተላለፋል። ይህ ብያኔ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የጸና ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት ነው።


ሕማምና ሞት የማይገባው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የኛን ሕማምና ሞት ለራሱ በማድረግ በዚህ ሳምንት ለእኛ ቤዛ ሆኗል። ደዌያችንን ተቀበለ፣ ሕማማችንንም ተሸከመ፣ ከዓመጸኞችም ጋር ተቆጠረ። እርሱ ግን ግፍን አላደረገም ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም። /ኢሳ.53፡4-12/ ተብሎ እንደ ተጻፈ። ምእመናን ክርሰቶስ የተቀበለው የእኛን ሕማም መሆኑን በማዘከር በሰሙነ ሕማማት ከማንኛውም የሥጋ ሥራ መታቀብ፣ በዋዛ በፈዛዛ ባለመነጋገር በኀዘን ልናከብረው ይገባል። ብድራትን የማያሰቀረው አምላክም መተላለፋችንና በደላችንን በመደምሰስ የመንግሥቱ ወራሽ ያደርገናልና።


ሰሙነ ሕማማት እስከ ዐራተኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ከጾሙ ተለይቶ ለብቻው ይከበር ነበር። በኋላ ግን በባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት ጾሙም፣ ሕማማቱም፣ ትንሣኤውም ተያይዘው እንዲከበሩ ተደረገ። ምዕራባውያን ከዐርባ ጾም ውስጥ የመጨረሻውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ያደርጉታል። የምሥራቃውያን /ኦርየንታል/ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ግን አርባውን ጾም ጨርሰን ከኒቆዲሞስ በኋላ ያለውን ተከታዩን አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት አድርገን እናከብራለን።

 

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጋዜጣ፣ ከመጋቢት 20-24 ቀን 2002 ዓ.ም፤ ልዩ እትም፡
ሐመር ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ መጋቢት/ሚያዝያ 1996 ዓ.ም

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
757 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 830 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us