በዓሉ ግርማ- ሕይወቱና ሥራዎቹ

Wednesday, 04 May 2016 13:01

 

በዳንኤል ክብረት (www.danielkibret.com)

ደራሲ - እንዳለ ጌታ ከበደ
የሕትመት ጊዜ - የካቲት 2008 ዓ.ም
ዋጋ፡- 120 ብርእንዳለ ጌታ ከበደ በዓሉ ግርማን እንደ ጌታ ነፍስ ዘርቶ እንደደአልዓዛር ከሞት አስነሥቶታል። ከትውልድ ቀየው ጀምሮ ‹እስከ መቃብሩ› ደረስ እየተከተለ። መዛግብቱን ያገላብጣል፣ እናውቃለን የሚሉትን ይጠይቃል፣ ያውቃሉ ብሎ የገመታቸውን ያናግራል፤ ሄዶበታል፣ ውሎበታል፣ ገብቶበታል፣ ወጥቶበታል የተባለው ቦታ ድረስ እየገባ ‹ማጀት በጎረሰው፣ ደጃፍ በመለሰው› ያገኘውን ያህል ይነግረናል።


ሰው የሚያውቀውን ሲጽፍ፣ የሚጽፈውንም ሲያውቅ እንዴት የሚያጠግብ እንጀራ እንደሚጋግር በእንዳለ ጌታ መጽሐፍ ልኬቱን እናገኘዋለን። ከሱጴ እስከ ደርግ እሥር ቤት፣ ከአዲስ አበባ እስከ አሜሪካ፣ ከአሠሪ እስከ አሣሪ፣ ከወዳጅ እስከ አሳዳጅ ድረስ መረጃ ፍለጋ የኳተነው ‹ለሞተው› በዓሉ ነፍስ ሊዘራ እንጂ ለሌላ ነገር ነው ብሎ ለማመን እጅግ ጅል መሆንን ይጠይቃል።


መጽሐፉ በቀብር ላይ እንደሚነበብ የሕይወት ታሪክ ሙቀት አልባ አይደለም። ድርቀት የተለየው፣ወዝ የተዋሐደው እንጂ። እንደ አንድ የሀገራችን ታሪክ ጠገብ ሽማግሌ ሆኖ ያወጋናል። ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸውን ሰዎች እንደ አጃቢ ገጸ ባሕርይ ያስመስላቸዋል። በዓሉን ደግሞ እንደ ዋናው ገጸ ባሕርይ። ‹ተናደደ፣ ጠረጲዛ መታ፣ ፊቱን ጥቁር አደረገ፣ ሳቀ፣ ፈገግ አለ፣ ሮጠ፣ ተሹሎከሎከ› እያለ አብሮ የነበረ ያህል ነው የሚነግረን።


በዓሉ በድርሰት ሥራዎቹ ሰዎችን ሲስል ፍጹማን አያደርጋቸውም። እንደ ሁላችንም እንከን ያላቸው፤ የበዓሉ ሰዎች አንድም እንከናቸውን አሸንፈው፣ አንድም እንከናቸውን ይዘው ኑሮን ድል ለማድረግና ታሪክ ለመሥራት የሚተጉ ናቸው። የበዓሉ ሰዎች የሠፈራችን ሰዎች የሚመስሉን ለዚህ ነው። የበዓሉ ሰዎች ጀንበርና ጥላ ያላቸው ናቸው።


እንዳለ በዓሉን ሲጽፈው እርሱ ስለ ራሱ ቢጽፍ ኖሮ በሚጽፍበት መንገድ ነው። ጀንበርና ጥላ አድርጎ። በዓሉ ጎበዝ ደራሲ፣ ትኁት፣ ትጉ ሠራተኛ፣ ከሰው ጋር ተግባቢ፣ ዐዋቂ፣ ቆራጥና ጀግና ነው። ነገር ግን ደግሞ ሰው ነው። ጥላ ነበረው። እንከን ነበረው። ድካም ነበረው። ስሕተት ነበረው። ውሱንነት ነበረው። ከሻማው ሥር እንዳለው ጨለማ ያለ ነበረው። እንዳለ ይህንንም እንድናይ ያደርገናል።


በቀብር ላይ እንደምናነበው ታሪክ ‹ትጉ፣ቅን፣ሰው ወዳጅ፣ ታታሪ፣ ታማኝ፣ እግዜርን የሚፈሩ ነበሩ› ብሎ አይደመድምም። በዓሉ ሰው ነበረ። ሰው ሆኖ ሠርቶ ሰው ሆኖ ነው የሞተው ይለናል። እንድናደንቀው ብቻ ሳይሆን እንድንበሳጭበት፣ እንድንወደው ብቻ ሳይሆን ‹ለምን ይህን ያደርጋል› እንድንለው፣ እንድናከብረው ብቻ ሳይሆን እንድንተቸው፣ ‹እንኳን አደረገ› እንድንል ብቻ ሳይሆን ‹ምን ነካው› እንድንል አድርጎ ነው የሳለው።


በዓሉና እንዳለ ልብ ለልብ ተናበዋል። ይል ነበር በሚባለው የጎጃም ልቅሶ ላይ ስለ ወዳጃቸው አሣምረው እየገጠሙ የዋሉ አንድ ሰው ነበሩ አሉ። በዚህ በጎንጅ ጽላሎ። ሁኔታውን የታዘበች አልቃሽ


እርሳቸው እርሳቸው እርስዎም እርስዎ
እንዴው የወዳጅ ልብ ምን አሰረቀዎ
ብላቸዋለች አሉ። የወዳጅዎን ልብ ሰርቀው ቢወስዱት እንጂ እንዲህ አድርገው የልቡን እንዴት ዐወቁት ማለቷ ነው። የቅጅ መብትን ባልፈራ ለእንዳለ እለው ነበር።


በዓሉን የሚወድ፣ የሚያደንቅና ስለ በዓሉ ማወቅ የሚፈልግ ሰው አሁን የእንዳለን መጽሐፍ ከማንበብ የተሻለ አማራጭ የለውም። በመጽሐፉ ውስጥ በዓሉ ብቻ ሳይሆን እንዳለም ተጽፏል። ሲወጣና ሲወርድ፣ ተሥፋ ሲያደርግና ሲቆርጥ፣ ሲያገኝና ሲያጣ፣ ሲያዝንና ሲደሰት፣ እናየዋለን።


ተራራ ቁልቁለት ወጥቼ ወርጄ
ስሙ የማይታወቅ ሩቅ ሀገር ሄጄ


እንዳለቺው የከበደ ሚካኤል የአይጥ ግልገል የተደበቀውን ለመግለጥ ‹ስሙ የማይታወቅ ሩቅ ሀገር› ድረስ ሲተጋ እናየዋለን። እኛም አብረነው እየተጓዝን ‹እንዘ ሥውር እምኔነ፣ ይእዜሰ ክሡተ ኮነ› እንላለን።


የእንዳለ አጻጻፍ የታላላቆቻችን ታሪኮች እንዲህ በፍቅርና በትጋት ተሠርተው፣ ሰው ሰው ሸተው፣ በደረቅ እንጀራ ሳይሆን በአዋዜ ቢቀርቡ እንደ ወግ ተደምጠው፣ እንደ ፊልምም እንደሚታዩ ማንጸሪያ ነው። የእንዳለ መጽሐፍ በዓሉን አግኝቶ ከማነጋገር ቀጥሎ ስለ በዓሉ ሊነግረን የሚችል ሁለተኛው መዝገብ ይመስለኛል። ምናልባትም ደግሞ ከራሱም ከበዓሉም በላይ።
እናም
በድግሱ የተደሰተ የቆሎ ተማሪ የወረበውን ማኅሌተ ገንቦ እንወርብለታለን።
ዝ ጠላ ከመ ወይን ጣዕሙ
እስኩ ድግሙ ድግሙ፣ እስኩ ድግሙ፤

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
705 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1098 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us