የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ የቆሸሸ ገመና

Wednesday, 11 May 2016 12:08

   

ዘመኑ በሪሁን

መገናኛ ብዙሃን በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ ያላቸው ሚና የጎላ ነው። በአንዳንድ በዲሞክራሲ የጎለበቱ ሀገሮች እንዲያውም አራተኛ መንግስት  እስከ መባል የሚደርስ ህዝባዊ ፋይዳ ያለው ይህ መስክ ለግልፅትና ለተጠያቂነት ብሎም ለህግ የበላይነትና ለፍትህ መረጋገጥ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ ነው። እንዳለመታዳል ሆኖ ግን በእኛ ሃገር ግን ይህ እሳቤ እምብዛም እዉን ሆኖ አልታየም። ለማድረግ ቢሞከረም ካለዉ ነባራዊ ሁኔታና ከመንግስትም አጠቃላይ ፍልስፍና አንጻር መሰናዘር አልተቻለም።

      መገናኛ ብዙሃን የግል፣ የማህበረሰብ፣ የህዝብም ይባሉ የመንግስት የሚቆሙበት የጋራ መሠረት አላቸው። ይኸውም በጋዜጠኝነት ሙያ ስነ-ምግባርና መርሆ ላይ የተመሠረቱ የእውነትና የሚዛናዊነት መለኪያዎች ሊቀመጡላቸው ይገባል። መገናኛ ብዙሃን የሚቆሙለት የየራሳቸው ዓላማና ውግንና እንደሚኖራቸው ቢታመንም ለሀገር ብሄራዊ ጥቅም፣ ለዜጎች እኩልነትና ለዓለም አቀፍ መርሆዎች ጥበቃ የተጣለባቸው ግዴታም ሊሸራረፍ የሚችል አይደለም።

      በኢትዮጵያ ሁኔታ በሀሳብ ነፃነት ላይ የተመሠረተ የፕሬስና መገናኛ ብዙሃን ስሪት የተፈቀደው አሁን ባለው ህገ-መንግስት ነው። በአንቀፅ 29 መሠረት የዜጎችን የሀሳብ ነፃነት ለማረጋገጥ ሲባል ከቅድመ ምርመራ የተላቀቀ የመገናኛ ብዙሃን እንቅስቃሴ መተግበር ጀምሯል። ይሁንና ኢንዱስትሪው ብዙም የተሳካለት አይመስልም። የግሉ በመንግስት ጫናም ይባለ በራሱ ችግር ከመንገዳገድ መዉጣት አልቻለም። በመንግስት ስር ያሉት ደግሞ ቅድመ ምርመራ ቢነሳላቸዉም በዉስጥ የሳሳንሱር ልክፍት የተጠናዉታቸዉ በአመራር ብቃትና ገለልተኝነት ችግር የተተበተቡ ናቸዉ። ከዚያም በላይ የከፋ የሚባል ሙስና የመልካም አስተዳዳር ችግርና ብቃት ያላቸዉ ሙያተኞች እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዳከማቸዉ ይገኛል። በመሆኑም ምንም ያህል የህዝብ በጀት ቢመደብላቸው እዚህ  ግባ የሚባል ለዉጥ ሊያመጡ አልቻሉም።

      ለዛሬ በግልና በማህበረሰብ መገናኛ ብዙሀን ካለው ይልቅ በህገ መንግስቱ  “የህዝብ” ተብለው ቢቋቋሙም ጭልጥ ብለው የመንግስት ፕሮፖጋንዳ መሳሪያ ከሆኑት የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን አንዱ ላይ ለማተኮር የፈለግነዉም ለዚህ ነዉ። ቢያንስ የዘርፉን ፈተና በግልጽ ማንሳት ካልተጀመረ መንግስትም ቢሆን ሊነቃ ስለማይችል  በቀጣይም በዚሁ ጉዳይ ላይ እና ሌሎችም ተመሳሳይ ችግር ዉስጥ እየዳከሩ ባሉ መስሪያቤቶች ላይ ተጨማሪና ተከታታይ መረጃ ከቻልን እናቀርባለን።

      ርዕሰ ጉዳዬ የሚያነጣጥረው በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ላይ ሲሆን በግሌ በጋዜጠኞች ማህበር በየዕለቱ የማገኛቸውን የመስሪያ ቤቱ ሠራተኞች ስለማገኝ መረጃዎችን ለመከተተል በመቻሌ ነው መረጃዉን ላጠናቅር የቻልኩት። ገና ከመነሻዉ ይህ ኤጀንሲ ተጠሪነቱ ለህዝብ ምክር ቤት እንደሆነ የተቋቋመበት ህግ ቢያስረዳም በተጨባጭ ግን ለአዲስ አበባ ኢህአዴግ ኮሚቴና ኮሚኒኬሽን ቢሮ ለተባለው አካላት የቅርብ ቁጥጥር ስር ያለ ነው። በዚህም ከከተማው ነዋሪዎች በተሰበሰበ ገንዘብ ሙሉ ወጭ እየተዳዳረ የከተማዉን የእዉቀት የአመለካከት የሃይማኖትና የብሔር ብዝሃነት ለማስተናገድ የማያስችል  የጎላ የሚባል የገለልተኝነት ጫና ወድቆበታል።

      ይህ መስሪያ ቤት ከ400 በላይ ጋዜጠኞችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን አሁን አዲስ ቲቪ (ቀድሞ ETV 2 የሚባለውን)፣ ኤፍ ኤም ሬዲዮ 96.3 እና አዲስ ልሳን ጋዜጣ የተባሉትን የያዘ ነዉ። ይህ  መገናኛ ብዙሃን በሬዲዮና ቴሌቭዥኑ  የስርጭት ሰዓት በመጨመሩና በአስተዳደሩ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሳተላይት ስርጭት ስለጀመረ ስር ነቀል ለውጥ ያመጣ ሊመስል ይችላል።

      ነገር ግን ሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ያውም (የህዝቦቹ) ዲሞክራሲን ያጎለብታሉ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ያደርጋሉ በምትልበት ወቅት የራሱንም ችግር መቅረፍ ያልቻለ ኤጀንሲ ነው። እንኳንስ የሀሳብ ብዝሀነትን ሊያስተናግድ ይቅርና “ተቃዋሚዎችን በሚዲያዎቻችን ማሳተፍ አይቻልም” ብለው በይፋ የሚናገሩ ካድሬዎች የሚመሩትም ነው። አለማወቃቸው እንጂ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እስከተንቀሳቀሱ ድረስ እነሱም የመገልገል ሙሉ መብት ያላቸዉ ባለመብቶች ነበሩ። ከሁሉም በላይ ኤጄንሲዉ  በውስጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያቆጠቆጠ የመጣ ሙስና፣ ብልሹ አሰራርና የህግ ጥሰት  ግን እርምትን ይፈልጋል።

      በቅርቡ በተካሄደው የኤጀንሲው ግምገማ ላይ ከተደረሰባቸው ግኝቶች በዚህ ትልቅ የመንግስት ሃብት በሚንቀሳቀስበት ተቋም ላይ ያንዣበበዉን አደጋ በመገንዘብም ነዉ እዉነቱ እንዲወጣ እንደዜጋም የፈለኩት። በዚያ ላይ ደግሞ ከዚህ ቀደምም እንደታየዉ የግምገማ ሪፖርቱንም ሆነ ሰራተኛዉ በተደጋጋሚ የሚጮኸበትን ጉዳይ ሁሉ የተነኩ የሚመስላቸዉ የስራ መሪዎቹ አዛብተዉ ያልተባለዉን ብለዉ እንደለመዱት ለምክር ቤቱም ሆነ ለሚመለከተዉ አካል እንዳቀረቡት በብዙዎቹ ሰራተኞች በመገመቱም ነዉ እዉነትን መገላለጥ ማስፈለጉ።

      የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ሠራተኞች በግልፅ እንደሚናገሩት በተቋሙ ተጨባጭ የሚባሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ። በአንድ በኩል ከደረጃ ዕድገት፣ ቅጥር፣ ዝውውርና ምደባ ጋር የሚያያዘው ነው። ለኤጀንሲው የስራ መሪዎች አድርባይ የሆኑና “እሽ እሽ” የሚሉት ሰዎች በተሻለ ቦታ ይቀመጣሉ። የመብት ጥያቄንም ሆነ ሙያዊ ብቃት ኖሯቸው በገለልተኝነት እንስራ የሚሉት ደግሞ ይገፋሉ። በዚህ ሰበብም ብዙ የለቀቁ ሙያተኞችም አሉ። አስገራሚ የሚሆነዉ ወሬ በማቀበልና በመላላክ የሚታወቁት አንዳንድ ሰዎች ህጉ እንኳን ባይፈቅድላቸዉ የቀበሌ ቤት ሁሉ እንዲያገኙ ሲደረግ በስራቸዉ የተሻለ ውጤት ያመጡት ተደብቀዉ ቀርተዋል። ሹመትና ምደባማ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል በአድርባይነትና በትዉዉቅ መሆኑን ሰራተኛዉ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የሚገልጹት ነዉ። በተመሳሳይ ስራ ከሁለት መስሪያቤት ሁለት ደመወዝ ከህግ ዉጭ እንዲበሉ የተደረጉ ጋዜጠኛ ተብዬዎችም የአስከፊው ድርጊት ጥሩ ማሳያ ናቸዉ።

      ሌላው የኤጀንሲው አስከፊ ገፅታ በአንዳንድ የሥራ መሪዎች ላይ ያለው የስነ-ምግባር ጉድለት ነው። የተቋሙ አንዳንድ ሴት ጋዜጠኞች ሁሉም ሠራተኛ በተሰበሰበበት እንደተናገሩት በሴትነታቸው ፆታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ካለፍላጎታቸው ለኢሞራላዊ ተግባር ይጋበዛሉ፣ ይህን አልፈቅደም በማለታቸውም ከሽልማት፣ ከስራ ስምሪት ምደባና ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞች ይከላከላሉ። ደረጃ ዕድገትና የውስጥ ዝውውርም አይታሰብም። በዚህ ችግር ለረጅም ጊዜ የዘለቀ አስከፊ የስነ ምግባር ጥሰት በቢሮ ዉስጥ እንደሚፈጸም ቢታወቅም አንድም ከልካይና ተቆጪ በመጥፋቱ ችግሩ እየሰፋ ሄዶ አደባባይ ላይ ወጥቷል።

      በኤጀንሲው አንዳንድ አመራሮች የተጀመሩ የምርመራ ዘገባዎችና የሙስና ማጋለጥ ሙከራዎች መከልከላቸውም የኤጀንሲውን ዝቅጠት የሚያሳይ ነው። በተለይ የአንድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆን ብሎ ያለቀለት ስራን አየር ላይ እንዳይውልና የህዝብ ጥቅም እንዳይከበር እያደረሰ ያለው በደል ብዙዎችን ጋዜጠኞች ያሳዘነ ድርጊት ነው። ይህ ሰዉና ግብረ አበሮቹ ባህርዳር ዉስጥ ካለ አንድ ትልቅ ሆቴል (ለጊዜዉ ስሙን መጥቀስ አያስፈልግም) ባለቤት የመሬት ጉዳይ አስፈጽምላችኋለሁ ብለዉ በመቶሺ ብር የሚቆጠር ገንዘብ ተቀብለዋል በሚል ክስ ጸረ ሙስና ጉዳዩን እያጣራ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በቁጥጥር ስር መዋል የጀመሩ የመንግስት ሌቦችም የተገኙት በዚሁ የህዝብ በተባለ ተቋም ነዉ። (እዚህ ላይ ግን ገና መጣራት ያለባቸዉ ጉዳዮች እንዳሉ ሳይካድ ማለት ነዉ።) ለነገሩ ይህ ሰዉ ከዚህ ቀደም በኢ.ት.ቪ እና በየካ ክፍለ ከተማ በሚሰራበት ጊዜም ቢሆን የሚነሱበት ችግሮች እንደነበሩ እየታወቀ ወደ ኤጀንሲዉ ያዉም ቁልፍ በሆነ ቦታ ላይ እንዲመጣ ያደረጉት ኃላፊዎችም እንዴትና ለምን እንደወሰኑ ሊጠየቁም ይገባል። ይህ ከልካይና አሰራር የማያዘዉ በመንገሱ በቦርድ ሰብሳቢ በነበሩት ኃላፊ በኩል ሳይቀር ዉሳኔዉ መተላለፉም ብዙ ነገር የሚያስጠረጥር ሆኗል ነዉ የሚሉት ሰራተኞቹ።

    በአንዳንድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የግል ኩባንያዎች በኩል “ቢጫዋ ፖስታ” ለአለቃችሁ ተልኳል፣ እናንተ ዘግባችሁ ብቻ ሂዱ መባላቸው ያስቆጫቸው ጋዜጠኞችም በእንባ እየታጀቡ ነው በመስሪያቤቱ ዉስጥ ያለዉን የተጨመላለቀ አሰራር ያጋለጡት። በሀዘን የተናገሩትም። ይህ ሁኔታም ለሌሎች ጋዜጠኞች የሚሰጠውን የትራንስፖርት እየተነፈጉ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከከተማዉ ምክር ቤት 50 ብር አበል ወሰዳችሁ ተብለዉ ከስራ እስከመባረር የደረሱ ጭቁን ሰራተኞችም ሰለነበሩ እንደሆነ ይነገራል። ይሄ ጉዳይ ከሰሞኑ በከንቲባ ጽህፈት ቤት በኩል በተወከሉ አጣሪዎች በጥብቅ እየተገመገመ ሲሆን ገና መቋጫም አልተሰጠዉም።

      የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ በቅርቡ ለሰራተኞች ከፍተኛ የሚባል የደመወዝ ጭማሪ አድርጓል። ይሁንና ሠራተኛው ላይ መውጫና መግቢያ የሚያሳጣ ግምገማ፣ በሙያው ውስጥ ከሚፈቀደው በላይ የስራ ጫናና ማጨናነቅ ተፈጥሯል። ከሁሉ በላይ ከሥራ አመራር ምዘና ጋር የማይጣጣም የሥራ መለኪያ ለመተግበር በመሞከሩ ጥራት ያለውንና ተፈላጊ ዘገባ ከማቅረብ ይልቅ ውሃ ቅዳና ውሃ መልስ ላይ ኤጀንሲው ለመውደቅ ተገዷል። ተደማጭነትና ተነባቢነትን ማግኘትም አልተቻለም የሚለዉ የብዙዎቹ ወቀሳም ብዙሃኑን ሰራተኛ ያላሰተፈ አሰራር ዉጤት ተደርጎ ይወሰዳል።

      ለዚህም ነው ዛሬ ኤጀንሲው የመጣበትን ከፍተኛ የአስተዳደሩ ኢንቨስትመንት ያህል ተመልካችን የሚስብ ስራ የሌለው። ማንም እንደሚያውቀው አዲስ ቲቪ በአንዳንድ ሥራዎቹ ቢሻሻልም አሁንም “አይጠየፍ” የሚባል አሰስ ገሰስ አቅራቢ ነው። የአዲስ አበባ ኤፍ.ኤም ሬዲዮም ዝቅተኛ ተደማጭነት ያለው ጣቢያ እንደሆነ ራሱ ብሮድካስት ባለስልጣን ባደረገው የቅርብ ጊዜ ጥናት አረጋግጦታል። አዲስ ልሳን ጋዜጣና በየወሩ የምትታተመው መፅሄትም ሶስት ሺ ኮፒ እየታተሙ የሚሠራጩት ከ400 አይበልጥም። በዚህም ህትመቱ ለብክነት ተዳርጓል። ከሁሉ በላይ በዘልማድ እየተሰራ ባለዉ የማስታወቂያ አሰራር ግለሰቦች እየበለጸጉበት ይገኛሉ። ለዚህ አብነት የሚሆነዉ ያለምንም አይነት አሰራር በየሆቴሉ የሚካሄደዉ የቴሊቭዥን የበአል ቀረጻ ነዉ።

      ከነዚህና መሰል ችግሮች አንጻር የዚህ መስሪያ ቤት ዋነኛው ችግር የአመራር ነው።  ተቋሙን ከላይ እስከ ታች እየመሩ ያሉት ከሙያዊ ብቃትና የህዝብ ተቆርቋሪነት ይልቅ በመወዳጀትና ቅርርብ የተሰባሰቡ ናቸው። ስለሆነም መማማርና መተጋገል  ብሎ ነገር የለም። ይልቁንም አንዱ አጥፍቶ ገደል ሊገባ ጫፍ ላይ እንኳን ቢደርስ “ቁም!” ወይም ተመለስ የሚለው ሌላ አካል የለም። ተያይዞ ገደል እንዲሉ። ከዚህ ቀደም መስሪያ ቤቱን በቦርድ መሪነት ያስተዳዳሩት የነበሩ የከተማዉ ከንቲባና ከፍተኛ ባለስልጣንን ጨምሮ ትንሽ ቁጥር የሌላቸዉ ያተኛና የስራ ኃላፊ የመንግስት ንብረትን ሳያስረክቡ የጠፉበትና የተሰወሩበት አጄንሲ እንደሆነም ይታወቃል። በሚልዮን ብሮች በሚቆጠር ገንዘብ ተገዝተዉ ለብልሽት የተጋለጡና የሰረቋቸዉና የሰበሯቸዉ ሰዎች የማይጠየቁበት አሰራርም ብዙዎችን እያሳዘነ ይገኛል።

       እስከአሁን የነበሩት የአጀንሲው ሥራ አመራር ቦርድ አባላትም ቢሆኑ ሰራተኛውን ከመስማት ችግሩን አዳምጦ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በኃላፊዎች የውሸት ሪፖርት የተደበቁ ናቸው። ከዚህ ቀደም ቦርዱን የመሩትና አሁን በኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታነት የሄዱት ኃላፊ የተሻለ ክትትል ሊያደርጉ ቢሞክሩም ችግሩን ሳይፈቱ መሄዳቸዉን በመቆጨት የሚያነሱት አንዳንድ ሙያተኞች እንዳዉም ዛሬ በሌብነት እየተጠየቁ ያሉትም ሆኑ አንዳንዶቹ የእርሳቸዉን ስም ደጋጋሞ በመጥራት ተሸፍነዉ የኖሩ ናቸዉ። እንዲያውም ባለፈው አመት ለቀናት በዘለቀ ስብሰባ ሰራተኛዉን  ካስለፈለፉ በኋላ ምንም አይነት እርምት ሳይወሰድ ጉዳዩን አዳፍነዉት በመሄዳቸዉ ያላዘነ ሰራተኛ አልነበረም።

      ሰራተኛው በአግባቡ ሳይመዘን መሸላለም የኤጄንሲው መገለጫ ነው። ይሁን አይደለም ከሌላሚዲያ ጋዜጠኞች ጋር ሊወዳደሩና በራሳችን ውስጥም አርዐያ ነው የሚባል ጋዜጠኛና ኤዲተር አለ ለማለት አይቻልም። ኃላፊዎችም ሠራተኛውን አዳምጠው፣ የሚታረመውን አስተካክለው ከመሄድ ይልቅ ማስፈሪራትና «ፀጥ በሉ» ማለትን ስራ አድርገውታል። የሚገርመው ነገር እርስ በርስ ደግሞ ሊማማሩ አለመቻላቸው የችግሩን ዉስብስብነት ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ ነው።

      ኤጀንሲው የተለያዩ የቪዲዮና ኦዲዮ መረጃችን አያያዝ ላይ፣ የሙዚቃ ክሊፕ አጠቃቀምና የቴሊቪዥን ዶክመንቶች ባለቤትነት ላይም  ለሙስና የተጋለጠ ነው። ለዚህ አብነት የሚሆነው ከዚህ ቀደም እስከ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ድረስ የማጣራት ስራ እየተሰራባቸው ያሉ ጉዳዮች ያለበቂ ምላሽ መዳፈናቸው ነው። በበዓላት ቀን በገንዘብ (በጉቦ) በየሆቴሉ የቴሌቭዥን ዝግጅት የሰሩ ጋዜጠኞች መቼ ታረሙ፣ የጣቢያው ባለቤትነት ያላቸው ድራማዎችና ዶክመንተሪዎች ውጭ ሀገር ድረስ ሲሸጡ ማን ከለከላቸው፣ ንብረት ሳያስረክቡ የጠፉ ሙያተኞችና አመራሮች ስንት ናቸው? ከዚህ ቀደም ጸረ ሙስና ምርመራ ጀምሮባቸዉ የተዳፈኑ ጉዳዮችስ የማን ዕዳ ናቸዉ። መልስ የሚሰጥ የለም።

      አዲስ አበባ የሁሉም ህዝብ ከተማ ብቻ ሳትሆን አህጉራዊ መዲና ሆና ሳለ ደረጃዋን የማይመጥኑ መንግስታዊ ተቋማት የታጎሩባት ናት። ከእነዚህ ግይነቶቹ መስሪያ ቤቶች ቀዳሚ ተጠቃሹ ደግሞ ይህ ኤጄንሲ ነው ብል ማጋነን አይመስለኝም። ለዚህም ሠራተኛዉን ማናገር ብቻ በቂ ይመስለኛል።

      እንግዲህ ይህን መስሪያ ቤት ለመልካም አስተዳደርም ሆነ ለዲሞክራሲ የሚረዳ መገናኛ ብዙሃን ለማድረግ ውስጡ ይፈተሽ። የሚመራው ቦርድም ሆነ ራሱ የከተማው ምክር ቤት ጉዳዩን አጣርቶ ካላረመው የከፋ ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦትን እየታገልን ነው ለማለት ሞራል አይኖረውም። በኤጀንሲው ውስጥ የታጎሩ ሙሰኛ ዋልጌና አቅም ብቻ ሳይሆን ህዝባዊ ተቆርቋሪነት የሌላቸው ግን የንግግር ጀግኖችን ማበረታታት ይሆናል። የብዙሃኑን ሠራተኞች ሞራልና ተነሳሽነትም እንደማድቀቅ ይቆጠራል። ስለዚህ ተመልካች ለአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲና በዉስጡ ላሉት ትጉ ሰራተኞች  ለማለት እንወዳለን።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
511 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 980 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us