የደቡብ ሱዳን ትርምስና የጋምቤላው ፍጅት

Wednesday, 11 May 2016 12:19

 

ወሰንሰገድ መሸሻ በላቸው / This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

(ካለፈው የቀጠለ)

ደቡብ ሱዳን በሐምሌ 2003 ዓ.ም ፓውንድ የተባለ የራሷን የመገበያያ ገንዘብ ሥራ ላይ ማዋሏን የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ባንክ ገዢ አሊጃህ ማሉክ በመግለፃቸው የአቤይ ግዛት እጣ ፈንታ ሳይወሰንና ከመገንጠሏ በፊት የሰሜን ሱዳን የካርቱም መንግስት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የተበደረው 38 ቢሊየን ዶላር ይሰረዝ ወይም ይመለስ የሚለው ጥያቄ መልስ ሳያገኝ የመገበያያ ገንዘቧን ደቡብ ሱዳን መለወጧንና በግዛታቸው የሚገኘው 1.5-2 ቢሊየን የሚጠጋ የቀድሞ መገበያያ ገንዘብም መቀየሩን  በመቃወም የሰሜን/ካርቱም መንግስት ብሔራዊ ገዥ መሃመድ ከሂር አልዘብር ከደቡብ ግዛት የቀድሞውን መገበያያ ገንዘብ እንገዛችኋለን የተባለውን ስምምነት በመቀየር አንገዛችሁም አዲሱ ገንዘባችሁ ለእኛም ለእናንተም አይበጅም የሚል አቋም በማስታወቃቸው ደቡብ ሱዳን ለኪሳራ ትጋለጣለች የተባለና የወዛገበ ሌላ አጀንዳ ሆነ።

የደቡብ ሱዳን አማፅያን የያዙትን በብሉናይልና በኮርዶፋን ግዛት ላይ የካርቱም መንግስት ለ6 ወር በፈፀመው በጦር ጀት የታገዘ ጥቃት ከ200.000 በላይ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን መሰደዳቸው በኢትዮጵያ በተለይም በጋምቤላ ለደረሰው ፍጅት አጋዥም ምክንያትም ነው ብሎ መቀበል አያስቸግርም።

 

አልበሽር በአለምአቀፉ ፍርድቤት የተከሰሱት በሶስት ዋናዋና ጉዳዮች ስር በተጠቃለሉት ዘርማጥፋት፣ በሰብአዊነት ላይ የተቃጣ ወንጀልና የጦር ወንጀል ሲሆን አነዚህ ዋናዋና ጉዳዮችም በ10 ክሶች ተለይተዋል።

 

 

በዘር ማጥፋት ስር፡- ማሳሊት፣ የሰፈርና ዛግሃዋ ጎሳዎችን በመጨፍጨፍ፣ የአካልና የአእምሮ ጉዳት በማድረስ፣ የተቀነባበረ የህይወት ጥቃት በመፈፀም፣

በሰብአዊነት ስር፡- ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ግርፋት፣ አስገድዶ ማፈናቀልና የጅምላ ርሸና በማካሄድ፣

በጦር ወንጀለኝነት ስር፡- ደግሞ በዳርፉር ሲቪል ዜጎች ላይ በሩሲያ ሰራሽ አንቶኖቮችና ሄሊኮፕተሮች ጅምላ ጥቃት በማድረስና ከተሞችንና መንደሮችን በእሳት በማጋየት በተፈፀሙ ወንጀሎች ተከስሰዋል። ከአልበሽር ጋር የሱዳን መንግስት ሚንስትር የነበሩት አህመድ ሀሩንና የጃንጃዊድ መሪ አሊ ኩባይቭ አብረው የተከሰሱ ቢሆንም፣ እንኳን ሊያዙ ሀሩን በተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ የሰብአዊ ጉዳይ ባለስልጣን ሆነው እየሰሩ እንደነበር ይታወሳል።

የጅቡቲው ፕሬዚደንት እስማኤል ኡመር ጊሌ በአለሲመት ላይ ኦማር ሀሰን አልበሽር በመገኘታቸው አለምአቀፍ ውግዘት በተሰራጨበት ሰአት የኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ የደቡቡ ሱዳን ከሰሜኑ ሱዳን መገንጠሉን በመቃወም እንደማይቀበሉት የአዋት ዶትኮም ዘገባ ገልፆ ይህ ሁኔታ ሱማሌ ላንድ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራሷን ለመቻል እያደረገችው ያለውን አላስፈላጊ እንቅስቃሴ ለማበረታት ስለሚጠቅም ደቡብ ሱዳንን እንደነፃሃገር አንቀበላትም ብለዋል አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ። /የኤርትራን መገንጠል ልብ ይሏል።/

 

ደቡብ ሱዳን የነዳጅ ክፍያው ፍትሃዊ አይደለም በማለት በካርቱም መንግስት በቱቦ የምታስተላልፈውን ነዳጅ አቅርቦቷን ካቋረጠች በኋላ ሰሜን ሱዳን 600.000 በርሚል ድፍድፍ ነዳጅ የጫነ ራታ ሾራድሃ በተባለ የኬሚካልና የማዳበሪያ አምራች ኩባንያ መርከብ ለሰሜን እስያ ነጋዴዎች በመሸጧና ጃፓን 3.5 ሚልየን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የቪቶልነ የሲኒዮፔክ መርከቦች ከፖርት ሱዳን መጫናቸውን፣ 5.4 ሚልዮን ድፍድፍ ነዳጅ ለሌሊች ሃገሮች መሸጣቸውን በጥር 2004 የአውሮፓ ህብረት የባህር ኃይል መርከቦች አስታውቀው ስለነነበር/እያንዳንዳቸው 815 ሚልዮን ዶላር ያወጣሉ/።

በህዝበ ውሳኔው የተሳተፉም ሆኑ ያልተሳተፉትም የደቡብ ሱዳን ተወላጆች በሙሉ ከሚያዝያ 2004 ጀምሮ በሰሜን ሱዳን ውስጥ እንደማንኛውም የውጭ ዜጋ እንደሚስተናገዱ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በቴሌቪዥን በማስታወቃቸው፣ በደቡብ ሱዳን በኮርዶፋን ግዛት በኮንስትራክሽን ስራ ላይ የተሰማሩ 47 ሱዳናውያን ላይ ጥቃት የሰነዘሩት 29ኙን በቁጥጥር ስር አውለው 27 ቻይናውያን አምልጠው ወደ ካርቱም የገቡና አንድ ቻይናዊ በጥቃቱ በመገደሉ ሬሳውንና 27ቱን ለቻይናዎቹ ልኡክ ማስረከቡን በሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የቻይና ጉዳዮች ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ኢሳም አዋድ ሙቱዋሊ ለሮይተርስ መግለፃቸውም አባባሽ ነገሮች ሆኑ።

 

እንግዲህ የሱዳን ትርምስን ባለፉት 2 ሳምንታት ነካነካ ያደረግነው በጋምቤላ ለተፈፀመብን ጥቃት አንባቢያን ግንዛቤ እንዲኖራቸውና አካባቢው በራሱ መነሻ እንደሚሆንም የራሱን ምልከታ እንዲያይበት በማሰብ ነው።

ከጥንት ከመሰረቱ የሱዳን ሕዝብ የጓንግ/አትባራ ወንዝን ተሻግረው ሊያልፉ ይቅርና ከወንዙ ለመጠጣት ሞክረው እንደማያውቁ የመተማ ነዋሪዎች አፋቸውን ሞልተው ነው የሚናገሩት።

 

በኢትዮጵያ ከ1914/1915 ለብሪታንያና ለሱዳን መንግስት ከባሮ ወንዝ አካባቢ ከጋምቤላ 50/60 ኪሎሜትር እርቀት ላይ 2000 ስኩየር ሜትር የሚሆን ቦታ ዳግማዊ ምኒልክ የሰጡና የንግድ ከተማ እንዲመሰርቱ ፈቀዱ።

በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የእንግሊዝ መንግስት ሱዳንን እስኪለቅ ድረስ በሱዳን አስተዳደር ስር እንዲተዳደሩም፣ እንዲዳኙም ተደረገ። ሆኖም ሙሴ ቴሲዤር የያዘው ካርታና ውል ከጋምቤላ ውጭና በጣም እርቃ በምትገኘው ኤታን ለንግድ ከተማ ምስረታ ነው የተፈቀደላቸው እነሱ ግን ጋምቤላ ገብተው ጉምሩክ ቢሮ ከፍተው የጉምሩክን ተግባር መፈፀምና ቀረጥ መቅረጥን ነው በዚያ በሩቅ ዘመን ከ90 ዓመታት በፊት የጀመሩት።

 

በደርግ ዘመን በተፈጠረ ‹አብዮት ልጆቿን ትበላለች› መርህ ኢዲዩ፣ ኢህአፓና መሰል ተቃዋሚ ቡድኖች

ጋር በተከሰተው አለመግባባት ዳሩ መሐል ወደ መሆን በመጀመሩና የጃፋር ኤል ኒሜሪን መንግስት ለመጣል ለሱዳን ተቃዋሚዎች ድንበሩ በመከፈቱ፣ የድንበር ዜጎቻችን ከዚህም ከዚያም ማምለጫ መጠጊያ ምሽጎች በመሆናቸውና ከወዲያም በኩል ለሻእቢያና ለወያኔ አማፅያን መንደርደሪያ ሆኖ ስለተዘጋጀ ከኢህአዴግ የስልጣን ዘመን ጀምሮ ማስተካከል ሳያስፈልግ ውለታ በመክፈልም የህዝቦቹን ፍላጎት ከመደገፍ አንፃር ተብሎ የሱዳን ዜጎች ያለምንም መሸማቀቅ በይፋ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደፈለጉ መግባትና መውጣት፣ የተፈጥሮ ሀብታችን የሆነውን ደናችንን በይፋ እየመነጠሩ ከሰል እያከሰሉና ግንዲላዎቹን የሱዳን ታርጋ ባላቸው የሱዳን መኪኖች እየጫኑ ሲወስዱ፣ የሱዳን ወታደሮች በጠረፉ የድንበር ቦታዎች የሚያርሱ ኢትዮጵያውያንን እያፈኑ ወደ ሱዳን ይወስዷቸውና ይደበድቧቸው፣ ያስሯቸውና ይገድሏቸው እንደነበር በወቅቱ ተወስቷል።

 

 

ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ሱዳኖቹ ያለኢትዮጵያ መንግስት ፈቃድ የጓንግን ወንዝ ተሻግረው ደለሎ በሚባለው የኢትዮጵያ መሬት ላይ ሰፋፊ ቦታዎችን ይዘው በፍፁም ነፃነት የሚያርሱት የሱዳን ሰዎች በኃይለስላሴ ዘመን ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ይዘው ያርሱበት የነበረ መሬት እንደነበርና በነዚህ ኢትዮጵያን ባለሃብቶች እርሻ ቦታ በቀን ሰራተኛነት የተቀጠሩት ሱዳናውያን ዜጎች ስለነበሩ የንጉሱ መውደቅና የደርግ ዘመን ፖለቲካዊ ሽኩቻ ታክሎበት የቀን ሰራተኞቹ ሱዳናውያን የወቅቱ ሁኔታ ባሉበት በኢትዮጵያ ምድር እንደባለይዞታ እንዲረጉና ሌሎቹን ሱዳናውያንን እንዲስቡና እንደልብ እንዲሳተፉ አድርጓቸዋል።

 

 

በጀነራል አበበ ተ/ኃይማኖት/ጆቤ/ የልኡካን ቡድን መሪነት ጀነራል መስፍን አማረ፣ አቶ መሰረት ከትግራይ ክልል፣ አቶ ተሰማ ገ/ሕይወት ከአማራ ክልል፣ ጀነራል ፓትሪስ፣ ኮሎኔል አረጋ ልባሴ/የጀነራል አበበ ተ/ኃይማኖት ልዩ አማካሪ/፣ አቶ ታረቀኝ አማኑ ከሰሜን ጎንደር፣ የሽሬ ዞን ተወካይ፣ የሁመራ አስተዳዳሪና የመተማ አስተዳዳሪ ደሳለኝ አንዳርጌ የቴክኒክ ኮሚቴ ሆነው በገዳሪፍ ሞትዊል ሆቴል በድንበሩ ጉዳይ ከሱዳን ልኡካን ጋር በአንድ ወቅት ስብሰባ አካሂደው ነበር።

 

በዚህ ድርድር ላይ በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው የመደራደሪያ ሃሳብ የኢትዮጵያን ድንበር እያለፋችሁ እርሻ ታርሳላችሁ፣ ደን ትጨፈጭፋላችሁ፣ ዜጎቻችንን ታስራላችሁ የሚል ሲሆን በሱዳኖቹ በኩል እኛ ከይዞታችን አልፈን አልገባንም፣ የሻለቃ ጎይን መስመርን ተከትለን በራሳችን መሬት ላይ እያለማን ነው  አሉ። ጀነራል አበበ የኢትዮጵያ መንግስት ሻለቃ ጎይን ያወጣውን ካርታ ተቀብሎ ድንበር ያካለለበት ሰነድ ካለ ፊርማውንና ዲማርኬሽኑን አሳዩን ብለው በማፋጠጣቸው ሱዳኖቹ መልስ ስላልነበራቸውና አዝማሚያው ለቀጣዩ ጥሩ ስለማይሆን ተብሎ በጀነራል አበበ በቀረበ የመፍትሄ ሃሳብ የጎይን መስመርን እንተወው እና በኃይለስላሴ ጊዜ አሁን እኛ እምናርሰው መሬት የእኛ ሰዎች ይዞታ ከሆነ በሱዳናውያንና በኢትዮጵያዊያን የአካባቢው ነዋሪዎች እየተረጋገጠ የምንለቀው ይሆናል በሚለው ስምምነት ላይ ተደረሰ።

 

በዚሁ ስምምነት መሰረት የኢትዮጵያ ከነበረ ለኢትዮጵያ የሱዳን ከነበረ ለሱዳን እንዲሰጥ ተወሰኖ በሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር በአቶ ታረቀኝ እማኙ የሚመራ ቡድን ተቋቁሞ አቶ ደሴ አለሜ የአርማጭሆ ወረዳ አስተዳደር፣ አቶ ደመላሽ የማጠቢያ ወረዳ አስተዳደር፣ ደሳለኝ አንዳርጌ የመተማ አስተዳዳሪና በሱዳን በኩል ሚስተር ጋሲም የደብ አስተዳዳሪ የሚመሩት የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ከሱዳኖች ተወካዮች  በጋራ በተከናወነው የምስክር መስማት ሂደት ከአብደራፊ አካባቢ ጀምሮ የኢትዮጵያ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስተሮች ልማት ይካሄድበት እንደነበርና ሱዳኖቹ በቀን ሠራተኛነት ተቀጥረው ይሰሩ እንደነበር ስለተረጋገጠ መሬቱ የኢትዮጵያ መሆኑን በመተማመን የሁለቱም ሀገራት የቴክኒክ ኮሚቴዎች በስምምነት በፊርማቸው አረጋግጠዋል።

 

 

ሆኖም በ1987/88 የምርት ዘመን መሀመድ ሃምዛ፣ ከማል አረቢ ሀሰንና ሌሎች ሁለት ሱዳናውያን ባለሀብቶች በነዚህ የኢትዮጵያ ቦታዎች ከጓንግ ወንዝ ተሻግረው የደለሎን መሬት አርሰው አዝመራው ደርሶም ስለነበር በስምምነቱ መሰረት መልቀቅ ቢገባቸውም ምርታቸውን እስኪያነሱ እንዲጠበቁና ከምርቱ ከማሽላ 35 በመቶ፣ ከሰሊጥ 25 በመቶ ለኢትዮጵያ መንግስት እንዲከፍሉና መሬቱንም ለኢትዮጵያ እንዲያስረክቡ ተወስኖ በ1988 ከምርቱ ለኢትዮጵያ እንዲከፍሉ ታዝዞ በኮሚቴው የጋራ ውሳኔ መሰረት ከፈሉ። ሆኖም በአፍሪካ አንድነት ስብሰባ አዲስአበባ የገቡትን የግብፅ ፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ ላይ በተካሄደው የግድያ ሙከራ ሌሎቹ ተገድለው አንዱ አምልጦ ወደ ሱዳን በመሸሹ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ውጥረት በመነሳቱ የሱዳን ባለሀብቶችም ወዳገራቸው ሸሹ።

 

 

ከ1988 እስከ 1994 ድረስ መሬቱ በኢትዮጵያውያን ሲታረስ ቆይቶ ከዚህ በላይ ያለውን መሬት ለሱዳኖች መልሱ መባሉን የአካባቢ ምንጮች በወቅቱ ይገልጹ ነበር /መንግስት ለሱዳን መሬት ሰጠ የሚለው በሰፊው የተነዛውን ልብ ይሏል/። ካሁን በፊት በጀነራል አበበ መሪነት ተቋቁሞ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ድርድር ሲያደርግ የነበረ ኮሚቴ እንዳልነበረ በሚያሳይ አገላለፅ መንግስት በዚህ ድንበር በ2001 አዲስ ኮሚቴ እንዳቋቋመ በቴሌቪዠን ገልፆ እንደነበርም ማስታወስ ግድ ይላል።

 

የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር ከ1800 ኪሎሜትር በላይ የሚደርስ ሲሆን አካባቢው በደንብ ባልተረጋጋበት ሁኔታ ላይ እያለ በጋምቤላ ክልል 70.000 የሚሆኑ አባዎራዎችን መንግስት በፀጥታ ኃይሎች ግፊትና ማስፈራራት ከቀያቸው እያስነሳ መሰረተ ልማት ባልተመቻቸበት ቦታ እያሰፈራቸው መሆኑን በመግለፅ በጥር ወር 2004 ዓ.ም ሂውማን ራይትስዎች በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን እየከሰሰ እንደነበርም አይረሳም።

በየካቲት 2004 በአዲስአበባ ኤግዚቪሽን ማዕከል በተከፈተው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት የሱዳን ባለሃብቶች 20 የሺሻ አይነቶችን በኢትዮጵያ ገበያ ማቅረብ የሚያስችላቸውን መረጃ በካርቱም የሚገኘው አፍራህ ቶባኮ የሚባለው የሱዳን የሲጋራ ፋብሪካ በይፋ በለቀቀው ማስታወቂያው ጥራታቸውን የጠበቁ፣ እርካታ የሚሰጡና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡ መሆናቸውን የሚገልፁ በርካታ በራሪ ወረቀቶች ጭምር በሰፊው ሲሰራጩ ባንፃሩ በአዲስአበባ ውስጥ ሺሻ የሚያስጨሱ ቤቶችን የኢትዮጵያ ፖሊሶች እያሸጉ ነበር።

 

ደቡብ ሱዳን የሰሜን ሱዳን በፈጠረበት ውዝግብ የነዳጅ ማስተላለፉን ካቋረጠ በኋላ በቀን 350.000 በርሚል ነዳጅ ውስጥ በቦቴ እየጫነች በኬንያና በጅቡቲ ወደብ በኩል ወደውጭ ለማቅረብ ሰርታለች።

 

የደቡብ ሱዳንና የሰሜን ሱዳን ሀገራት ዜጎች በደቡብ አፍሪካው ፕሬዚደንት በታምቦ ኢምቤኪ ዋና አደራዳሪነትና በቀድሞው የብሩንዲ ፕሬዚዳንት ፓብሪ ባዩያና በአፍሪካ ህብረት የሰላምና የደህንነት ኮሚሽነር ራማቲኒ ለማማራ አደራዳሪነትና ሸምጋይነት ከድንበር ማካለሉ ስራ ጋር ተያይዞ የተደረሰውን ስምምነት ሱዳናውያኑ በአካባቢያቸው እንዴት መኖር እንዳለባቸው ማለትም በሁለቱም ሀገር የመኖር፣ የመንቀሳቀስ፣ የኢኮኖሚ ጥሪት የማፍራት የንግድ እንቅስቃሴ ላይ እንዲሰማሩ የመፍቀድ ሰነድ ተዘጋጅቶ በአልበሽር ተወካይ በኢንድሪስ አብዱልቃድር አማካይነት ተቀብለውታል። መጋቢት /2004 በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ በጁባ ተገናኝተው ለ7 ቀናት የፈጀ ውይይት አካሂደው ከደቡብ ሱዳን የተወከሉት ፓጋና አሙም ናቸው የተፈራረሙት።

 

በሚያዝያ 2004 የገዳሪፍ አስተዳዳሪዎች ቡድን  በካሲም አላአባስ መሪነት ወደ ኢትዮጵያ አማራ ክልል ፕሬዚደንት አያሌው ጎበዜ ጋር ለመወያየት በተያዘ ቀጠሮ በኮንቮይ ይጓዙ በነበረበት ወቅት በሁለቱ ሐገሮች አዋሳኝ የኢትዮጵያ መሬት በኡምባጋሎ አካባቢ አቡሳንዳ ሲደርሱ የገዳሪፍ አስተዳዳሪዎቹ የኢትዮጵያውያን ገበሬዎችን በማሳቸው ላይ እየሰሩ ባሉበት ወቅት ከመኪናቸው ወርደው መጎብኘት በመጀመራቸውና አላአባስ ገበሬዎቹን እያረሳችሁት ያለው መሬት የሱዳን እንጂ የኢትዮጵያ መሬት ስላልሆነ ለምን መሬታችንን ታርሳላችሁ ብለዋቸው ክርክር የተገጠመና አለመግባባቱን አላአባስ አጭረው

ጉዟቸውን በሰላም እንደቀጠሉና ከትንሽ ጉዞ በኋላ ባልታወቁ ታጣቂዎች የሩምታ ተኩስ በቡድኑ ላይ ተከፍቶ ጉዳት ባይደርስም የአላአባስ ቡድን ግን ሸሽቶ ወደ ገዳሪፍ ተመልሶ ባደረገው አሰሳ 12 ተጠርጣሪዎችን የያዘ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ግን ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጠውም ክትትል አላደረገበትም ብሎ የሱዳኑ የልኡካን ቡድኑ ወቅሶ ነበር።

 

 

ሱዳን ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ስደተኞችን በኃይል እያስገደደች ማስወጣቷንና ለኢትዮጵያ መንግስት አሳልፋ መስጠቷን ሶሊዳሪቲ ኮሚቴ ፎር ኢትዮጵያን ፖለቲካል ፕሪዝነር የተባለው የሰብአዊ መብት ቡድን በተቃወመ ጊዜና እንዲሁም በግንቦት 2004 በጋምቤላ በአኝዋክ ጎሳዎችና በኢትዮጵያ መንግስት ሰራዊት መካከል በተፈጠረ ግጭት 200 የሚደርሱ የአኝዋክ ተወላጆች ከአቦቦና ጀር ከተባሉ ቦታዎች ወደ ደቡብ ሱዳን ጀንግሊ ግዛት መሰደዳቸው የወቅቱ የመነጋገሪያ ርእስ እንደነበረና በአዲስአበባ የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ቢሮ ተወካይ ፕሮኮፕቹክ የአኝዋክ ጎሳዎች መሰደዳቸውን አዲስ አበባ ላለው ቢሮአችን የደረሰ መረጃ የለም ያሉና አቶ ሽመልስ ከማል የመንግስት ጉዳዮች ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ በቀጠናው ምንም አይነት ግጭት አልተፈጠረም፣ ግጭት የሚፈጥር አማፂ ወይም ታጣቂ ቡድን የለም፣ ቀጠናው አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት ነው ካሉ በኋላ በደቡብ ሱዳንና በኢትዮጵያ ድንበር የሚኖሩ ህዝቦች በንግድና በአንዳንድ ጉዳዮች አንዱ የሌላውን ድንበር አልፎ መሄድ የተለመደ መሆኑን፣ በጎረቤት ሃገሮች መካከል ወንጀል ፈፅሞ ወደሌላ ሃገር የሄደን ሰው መጠለያ ያለመስጠት፣ የሚፈለግበት ሃገር አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ኤክስትራዲሽን ትሪቲ ከአለም አቀፍ የጀኔቫ ህግ ጋር የሚጣረስ አለመሆኑንና በብዙ ሃገሮች መካከል በሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያደርጉት እንደሆነ በወቅቱ ለአልአፍሪካ ገልፀው እንደነበር  ይታወሳል። 

 

 

አሁንም 208 ሰዎቻችንን ሲገደሉ፣ 100ዎች ሲቆስሉ ብዙ ሕፃናትና ሴቶችን እንደበግ እየነዱ መውሰዳቸውና ከ2000 የማያንሱ ከብቶች ጨምረው ባደባባይ አቧራ ወደ ሰማይ እያስነሱ ሲነዱ ለአፍሪካ እንኳን ለእኛ ለአፍሪካ ሰላም አስከባሪነት ሞልቶ የተረፈው ታላቅና የሰለጠነ ዘመናዊ ጦር እያለን፣ በሕዋ ምርምር አየራችንን ከዳር እስከዳር ከጫፍ እስከጫፍ አዋሳኝ ሐገራትንም በልዩ ሳተላይት የእይታና የይዞታ ቀለበት ስር ከተን ቁልቁል እያዩ መሬት ላይ ምን እየተከወነ እንዳለ የሚያውቁ ልሂቃንን ይዘን፣ ለአሰሳም ለአጥቂነትም የሚተክሩ ድሮንስ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን የሚያመርት በክህሎት የረቀቀ ሰራዊት እያለን እንደናይጀሪያው ቦኮሃራም በታጠቁ ዜጎቹ እንደተከወነው አፈና ይፋ ውግዘት ያልተካሄደበት፣ ድንበር በተሻገረ የታጠቀ ኃይል ዜጎቻችንን ለባርነት አግቶ ሲወስድ ዝምታችንና መዘግየታችንን ከዚህ አንፃርም ልናየው የሚገባ ይሆናል።

 

በሱዳን ኦምዱርማን ግዛት በሚገኙ የኢትዮጵያ ስደተኞች ላይ የሱዳን ፖሊስ በመጋቢት 2004 ዓ.ም መኖሪያ ቤታቸውን በመውረር በቁጥጥር ስር በማድረግና በጭነት መኪና ጭነው ወደኢትዮጵያ ሊያስተላልፉአቸው ሲያጓጉዙዋቸው በተጓዦቹና በሱዳን ፖሊሶች መካከል በተፈጠረ ግጭት መኪና ተገልብጦ 242 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችና 2 የሱዳን ፖሊሶች ህይወት ተቀጥፏል። ኢትዮጵያና የሱዳን መንግስት ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመሰጣጠትም በዚያው ሳምንት ነበር በይፋ የተፈራረሙት።

 

በግንቦት 2004 ኤርትራ ከእናት ሐገሯ ከኢትዮጵያ የተገነጠለችበትን 21ኛ ዓመት ስታከብር አልበሽር አጋርነታቸውን ለማረጋገጥ አስመራ ድረስ ሄደው በጋራ ለመስራት ከኢሳያስ ጋር ስምምነት አድርገዋል።

በጋምቤላ ሳዑዲ እስታር በአንድ አመት 2 ጊዜ የሚያለማው የሩዝ እርሻ በሄክታር 4.5 ሜትሪክ ቶን የሩዝ ምርት የሚያመርትና ከምርቱ 45 በመቶውን ወደሳዑዲ ይልካል።

 

የግብፅ ሰራዊት በ2010 ሀይላንድ ትሪያንግል የሚባለውን የሱዳን ግዛት በኃይል ሰፍሮበታል በሚል ከሱዳን መንግስት ጋር አለመግባባት ፈጥረው የነበረ ቢሆንም በምእራብ የሱዳን ዳርፉር ግዛት ኩርሲ በተባለ ቦታ ለግብፅ አየር ኃይል ጣቢያ የጦር ቤዝ እንድትገነባ አልበሽር እንደሚሰጧት በ2005 መጀመሪያ በኛ አቆጣጠር ተገልፆ የነበረ ሲሆን ዓላማውም በዲፕሎማሲው ሂደት ግብፅ ካልተሳካላት ለሱዳን ዋነኛዋ ጠላት የሆነችው ኢትዮጵያን ወዳጇ ግብፅ በጦር ኃይሏ የአባይ ግድብን እንድታፈርስ የተጠነሰሰ ሴራ ነበር።

 

የሱዳን መሐዲስቶች ንጉሠ ነገሥታችን አፄ ዮሐንስን አንገት ቆርጠው የወሰዱበትን የጣሊያንን ወደ መሐል ሐገራችን በወረራ የመስፋፋትና የመግፋት አጋጣሚን በመጠቀም እንደነበር ዘላለም በቁጭት የምናስበው መሆኑም ታሪክ የማይዘነጋው የመላው ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ሆኗል።

 

 

በቅርቡ በሰንደቅ 11ኛ ዓመት ቁጥር 555 ሚያዝያ 19/2008 ዓ.ም በፋኑኤል ክንፉ የቀረበው ‹ግብፅ ኢትዮጵያን በወታደራዊ የከበባ ቀለበት ውስጥ ለማስገባት የነደፈችው ስትራቴጅ መክሸፉ አነጋገረ› የሚለው ፅሁፍ ለረጅም ዓመታት እየተሴረብን መኖሩ እየታወቀ ግድ ሳይሰጠው አውቆ የተኛውን መንግስታችንን ሊያነቃው የሚያስችል ጥሩ ደወል ይመስለኛል።

መስከረም 2005 አለምአቀፍ የገንዘብ ድርጅት አይኤምኤፍ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ እንድታቀዘቅዝ ማሳሰቡን በብሉምበርግ የዜና አውታር ማሰራጨቱን ተከትሎ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የቀድሞ ቃል አቀባይ የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በውጭ ተፅእኖ ፈፅሞ እንደማይቋረጥ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የአለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት በበኩላቸው በብሉምበርግ የተሰራጨው ዜና የተሳሰተ መሆኑንና አይኤምኤፍ ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብም ሆነ ማንኛውንም አይነት ግንባታ እንድታቀዘቅዝ አሳስቦ እንደማያውቅና ሊያሳስብም አይችልም ብለው የህዳሴው ግድብ በኢትዮጵያ ሕዝብ ወጪ የሚሰራ በመሆኑም አይ ኤም ኤፍ በፍፁም በማይመለከተው ገብቶ ወጪ በማያወጣበት ሥራ አቁሙ፣ አቀዝቅዙ ለማለት የሚያስችለው ምክንያት የለም ብለዋል።

 

ደቡብ ሱዳን ከዋና ከተማዋ ከጁባ በስተደቡብ የበደን ግዛትን አቋርጦ የሚያልፈው የነጭ አባይ ወንዝ ላይ 500 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ግድብ ልትገነባ መዘጋጀቷን ያስታወቀችው  በመስከረም 2005 ሲሆን በሰሜን ሱዳን በኩል እያለፈ ትሸጠው የነበረውን ነዳጅ ካቋረጠች በኋላ ከውጭ እየገዛች 15 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ኃይል የሚለግሳትን ጀነሬተር በውጭ ምንዛሬ እጥረት ስራው   እንደሚቋረጥ ስለሰጋች የነበረ ሲሆን ከቻይና በሚሰጥ 300 ሚልዮን ዶላር 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ መስመር ለመዘርጋት ተነስታለች። ከጎረቤቶቻችን ጋር የሚያነካካን ልናስወግዳቸው የማንችላቸው ብዙ እጅግ ብዙ ጉዳዮች እንዳሉን ይገባኛል። በተለይም ብዙ ድንበሮችን ከምትጋራን ሱዳን፣ ሶማሊያና ኤርትራ ጋር ግን ከፍተኛ ጥንቃቄና ከውስጥም ከውጭም በጥልቀት ቀርበን ልናየው ያስፈልጋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
608 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 885 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us