“ዓሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል”

Wednesday, 18 May 2016 12:52

“ዓሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል”

ክፍል ሁለት

እንዳሻው እምሻው

የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤትና አስተዳደር ኃላፊ

 

የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ በፋይናንስ ሪፖርቱ ላይ የወሰነውን ውሳኔ ይልቃል ችግር እንደሌለበት አድርጎ ነው የሚጠቅሰው። ነገር ግን ጉባኤው የኦዲትን የፋይናንስ ሪፖርት ካዳመጠ በኋላ የፋይናንስ አወጣጥና አጠቃቀማችን የፓርቲያችንን መተዳደሪያ ደንብ እና እንዲሁም የፋይናንስ መመሪያውን ያላገናዘበ በመሆኑ ወደፊት የሚመረጠው አዲሱ ብሔራዊ ምክር ቤት እና ኦዲትና ምርመራ ኮምሽን በተብራራ መልኩ ሂሳቡን እንዲሰሩት ነው የወሰነው። ይልቃልንም ባለፈው ሰኔ 8/2007 ዓ.ም በግፍ በተገደለው ወጣት ሳሙኤል አወቀ ፎቶግራፍ ፊትለፊት አቁሞ ይህንን የመሳሰሉ ድርጊቶች ከአሁን በኋላ እንዳይፈጸሙ ቃል አስገብቶና የአቋም መግለጫ አውጥቶ ነበር የተጠናቀቀው። ከዛ በኋላ ግን ያንኑ ለመድገምና የግል ስልጣኑን ለማስጠበቅ በመፈለግ የሆነ ያልሆነ ነገር መዘላበድ ጀምሯል እንደማያዋጣው ግን ማወቅ አለበት ሰማያዊ የህዝብ ንብረት ነውና። አሁን ወደ ዛሬው ጽሁፌ ልግባ፡-

የፓርቲያችን የፋይናንስ መመሪያ እንዲወጣ በተደጋጋሚ ም/ቤቱ ቢያሳስብምና ስራ አስፈጻሚውም ቢሰበሰብም አጀንዳ በዝቷል እየተባለ በይደር እየታለፈ ሳይጸድቅ ቆይቷል። በተለይ ከስራ አስፈጻሚ አባላት መካከል ሃና ዋለልኝ፣ ሰለሞን ተሰማ እና ይድነቃቸው ከበደ በተደጋጋሚ ለሚያነሱት የገንዘብ አወጣጣችን ጉዳይ ላይ የሚሰጣቸው መልስ ምን ፓርቲው ብዙ ገንዘብ ያለው ይመስል ስለገንዘብ ታነሳላችሁ የሚል ነበር በተለይ በይልቃል በኩል የሚሰጠው መልስ። ይህ በእንዲህ እያለ ግን ም/ቤቱ በግድ የፋይናንስ መመሪያው እንዲወጣ ሲያስገድድ መመሪያው ከመውጣቱና አንዳንድ ቀዳዳዎች ከመደፈናቸው በፊት  በገንዘብ ያዥ አቀጣጠር የሚያወያይ አጀንዳ የካቲት 19/2006 ዓ.ም በተደረገ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ አጀንዳ ሆኖ በይልቃል በኩል ይቀርባል። ከስራ አስፈጻሚው አባላት ውስጥም የተወሰኑት እሰከዛሬ ድረስ እንዲጸድቅ የተጠየቀው የፋይናንስ መመሪያ ሳይጸድቅ እንዴት ሆኖ ነው ስለገንዘብ ያዥ አቀጣጠር የምንወያየው በማለት አጀንዳው እንዲያድር ይደረጋል። ከአምስት ቀን በኋላ የካቲት 23/2006 ዓ.ም በተደረገ የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ደግሞ ይህ አጀንዳ በድጋሚ ይቀርብና ውይይት ይደረግበታል አሁንም መመሪያው ሳይጸድቅ እንዴት ይህ ይሆናል የሚል ጥያቄ ከቤቱ ሲነሳ እሱን በሚቀጥለው አጀንዳ ላይ እናየዋለን በማለት ቀጥታ ወደ አጀንዳው ይገባል። ከዛም ማንን እንቅጠር በሚለው ጉዳይ ላይም ብርቱ ክርክር ከተደረገ በኋላ በይልቃል በኩል አሁን ስምንት ሰዓት የሚያሰራ ስራ በፓርቲው ውስጥ ስለሌለ ሰራተኛ ከምንቀጥር ወይንሸት ሞላ የዛን ጊዜ በፓርቲው ውስጥ ተቀጣሪ ሰራተኛ ነች ደርባ ትስራ የሚል ሃሳብ ያቀርባል። በሌላ በኩል ደግሞ የለም ምንም ቢሆን ገንዘብ እያንቀሳቀስን ስለሆነ ሰራተኛ መቅጠር እንችላለን የሚል ሃሳብ ይቀርባል። ይህ ሁሉ ጭቅጭቅ ግን መመሪያ ሳይጸድቅ ነው። በመጨረሻም ስምምነት ላይ ባለመደረሱ በድምጽ እንዲወሰን ይደረግና በመጀመሪያ ይልቃል ያቀረበው ሞሽን የገንዘብ ያዥነቱን ቦታ ወይንሸት ደርባ ትስራ ለዚህም በፊት ሲከፈላት በነበረው አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ላይ ተጨማሪ አምስት መቶ ብር ይጨመርላት የሚል ሃሳብ ተካትቶበት በ3 ድምፅ ተቃውሞና በ6 ድምፅ ድጋፍ አስከትሎ ተወሰነ። ከዚያም ከመመሪያ ውጪ ለሚደረግ ዘረፋ ፓርቲው ተጋለጠ። የዚህን ስብሰባ ውሳኔ ቃለ ጉባኤ ማየት ይቻላል።

የዚሁ ስብሰባ ሁለተኛ አጀንዳ የሆነው የፋይናንስ መመሪያን ረቂቅ ማየት ሲሆን ገንዘብ ያዥነቱን ወይንሸት ፋይናንሱን ወረታው ቼክ ላይ ፈራሚዎቹ ደግሞ ይልቃልና ስለሺ ሆነው ቦታውን መቆጣጠራቸውን ካረጋገጡ በኋላ ወደ ውይይት ተገባ። በዚህ አጀንዳ ላይ ከተወሰኑ የስራ አስፈጻሚ አባላት ውጪ ትኩረት ሰጥቶ የሚወያይ ጠፋ በኋላም ዝም ከማለት ተብሎ አንዳንድ አንቀጾችን ማየት ተጀመረ በተለይ ቼክ ላይ የሚፈርሙ ኃላፊዎችን በተመለከተ ሊቀመንበሩ፣ የፋይናንስ ኃላፊው እና የጽሕፈት ቤትና አስተዳደር ኃላፊው ይሁኑ የሚል አንቀጽ በመመሪያው ላይ በግልጽ ይስፈርና ም/ሊቀመንበሩ ደግሞ ቼክ ላይ መፈረም የሚኖርበት ሊቀመንበሩ በማይኖርበት ጊዜ ብቻ ነው የሚል እንዲካተትበትና የቼክ ፈራሚዎቹ ግን ከሶስቱ ሁለቱ ከተገኙ እንደሚቻል የሚል ታክሎበት ሌሎች የሚስተካከሉ አንቀጾች ካሉም ከስራ አስፈጻሚ የተወከሉ ይድነቃቸው ከበደ፣ ወረታው ዋሴ፣ ስለሺ ፈይሳና ከም/ቤት ደግሞ ሰብሳቢው ሰይድ ኢብራሂም እንዲያዩትና የመጨረሻ ረቂቁን ጨርሰው ለም/ቤቱ አቅርበው ያጸድቁ በማለት ውሳኔ ላይ ተደረሰ። የሰማያዊ ፓርቲ የንብረትና ፋይናንስ አስተዳደር መመሪያም መጋቢት 28/2006 ዓ.ም በም/ቤቱ ሁለተኛ ዓመት አራተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርቦ ጸደቀ። እስካሁን ድረስ ግን በመመሪያው መሰረት ለመስራት ፈቃደኛ የሆነ ሊቀመንበርም ሆነ ፋይናንስ ኃላፊ ባይገኝም። በነገራችን ላይ ፓርቲያችን አሁን ድረስ የፋይናንስ ኃላፊ የለውም እንዳለፈው አሰራር ይልቃልና አቶ ነገሰ ናቸው ያለውን ብር ቼክ ላይ እየፈረሙ የሚያወጡት። እስቲ ተመልከቱ እንዴት ሆኖ ነው ዋና እና ምክትል ቼክ ላይ የሚፈርሙት?

የፓርቲያችን የፋይናንስ መመሪያ አንቀጽ 6/6 የግዢ አፈቃቀድ/ ውሳኔ አሰጣጥን በተመለከተ ከብር አንድ ሺህ እስከ አስር ሺህ ብር ድረስ የሚፈቅደው የጽ/ቤት ኃላፊው፣ ከአስር ሺህ አንድ እስከ ሰላሳ ሺህ ብር ድረስ ሊቀመንበሩ ሲሆን ከአላሳ ሺህ አንድ ብር እስከ ሃምሳ ሺህ ብር ደግሞ የስራ አስፈጻሚ ውሳኔ ሲያገኝ ነው እነዚህ ከላይ የተገለጹትን ወጪዎች አንዱም አካል አስፈጽሞት አያውቅም። ለምን ቢባል በገንዘብ ጉዳይ ላይ የሚወስኑት አራቱ ሰዎች ይልቃል፣ ወረታው፣ ወይንሸትና ስለሺ ናቸውና። ይህን ጉዳይ በሚመለከት የፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮምሽን በተደጋጋሚ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይም ሆነ እንዲሁም ስራ አስፈጻሚውን እየቀረበ የፋይናንስ አወጣጡ ትክክል አይደለም አስተካክሉ እያለ ቢያሳስብም ሰሚ ባለማግኘቱ ለጠቅላላ ጉባኤው ባቀረበው አጠቃላይ የፋይናንስ ሪፖርት ላይ የገንዘብ አወጣጡ የተዝረከረከና ሃምሳ በመቶው የሚሆነው በህጋዊ ደረሰኝ ያልተደገፈ ነው ያለው። አንድ ሰነድ ላሳያችሁ ፓርቲው ህዳር 2007 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የአዳር ሰልፍ በመስቀል አደባባይ ይጠራል ይህን ተከትሎም በረካታ አባላት ለእስር ይዳረጋሉ በዚህ ጊዜ በስለሺ ፈይሳ ስም ከውጪ ደጋፊዎቻችን መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ ይላካል። ያን ገንዘብ ካመጣ በኋላ ገንዘቡን ለተለያዩ ስራዎች ወጪ ሆነዋል ይለናል አብዛኛዎቹ ወጪዎች ግን ህጋዊ ደረሰኝ የሚሰራላቸው ሲሆኑ ደረሰኝም የነበራቸው ነበሩ። ደረሰኞቹን ግን ስለሺ እየቀዳደደ በየመሳቢያው ውስጥ ይጥል ስለነበር ለማስረጃ ያህል በስቴፕለር የተጠገነውን የ253፡ከ86 ሳንቲም (የሁለት መቶ ሃምሳ ሶስት ሺህ ከሰማኒያ ስድስት ሳንቲም) ደረሰኝ ይሄ ነው። እንግዲህ ባለፈው ጽሑፌ ሶስቱ ሰዎች ከፋይ፣ አረጋጋጭና አጽዳቂ እንደነበሩ ሁሉ አሁንም በዚህ ሰነድ ላይ ወረታውና ይልቃል በዛን ወቅት እስር ላይ የነበሩ ሆነው ምንም በማያውቁት ወጪ ላይ ስለሺ ጠያቂ፣ ወረታው አረጋጋጭ ይልቃል አጽዳቂ በመሆን ነው መመሪያ የሚጥሱት። ግርግር ለሌባ ይመቻል የሚሉት ተረት እዚህ ላይ ነው የሚሰራው። ታዲያ እነዚህን ሰዎች ምን ትሏቸዋላችሁ? እንግዲህ የፓርቲያችንን ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ግለሰቦች እንደፈለጉት ከባንክ ሲያወጡና ሲመነዝሩ እንደነበር በተደጋጋሚ ጽፌያለሁ አንድም ሰው እኔ ተጠያቂ ነኝ አላለም እንደውም ይህንን ጉዳይ ወይም የገንዘብ ዘረፋን የሚያነሳ ሰው በይልቃልና በወረታው በኩል የሚሰጠው ስም ሌላ ነው ይህ ደግሞ ላለፉት ሃያ አራት ዓመታት የለመድነው ስለሆነ አይደንቀኝም። መጀመሪያ ነበር………………….እጅን መሰብሰብ።n         

                  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
555 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 917 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us