የሀገራችን ፌዴራሊዝም ለከተሞቻችን እድገት ወይስ እንቅፋት?

Wednesday, 18 May 2016 13:07

ግንቦት 2 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእሸቱ ጮሌ የመሰብሰቢያ አዳራሽ “በፌደራል አደረጃጀት የከተሞች እድገት /Urbane Region Development in a Federal Setting” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ፓርቲያችን ተጋብዞ ነበር። የዚህ ውይይት ዋና ዓላማ ተብሎ በደብዳቤው ላይ የተገለጸው የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት በማድረግ የከተሞች እድገት አፈጻጸምን በአግባቡ ከማጤን ጀምሮ በአሁኑ ግዜ በስራ ላይ የዋለውን ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የከተማ ልማት ዶክሜንቶችን በመገምገም የሌሎች ሃገሮችን ልምዶችና ተሞክሮዎችን በዋቢነት በመጠቀም ለፕሮግራሙ ተግባራዊነት የሚጠቅሙ ሃሳቦችን ለማመንጨት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ኢዴፓ እኔን ጨምሮ የፓርቲውን ፕሬዚዳንት እና የፓርቲውን ድርጅት ጉዳይ ኃላፊን የውይይት መድረኩ ተሳታፊ አድርጎ ልኮን ተገኝተን ነበር። በዚህ የውይይት መድረክ ፓርቲያችን እንዲገኝ ሲጋበዝ ከላይ በገለጽኩት ርዕስ ላይ ሃሳቡን ለመግለጽ ተዘጋጅቶ የሄደ ቢሆንም የውይይት መድረኩ በሁሉም መስኩ የጠበቅነውን ያህል ገንቢና ጥልቅ ጽሁፎች የቀረቡበት አይደለም። የሆነው ሆኖ በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ሶስት ምሁራን በተለያየ ርዕስ ጽሁፍ አቅርበው ነበር።

ፕሮፌሰር ተገኝ ገ/እግዚአብሄር በከተሞች እድገት ዙሪያ የተለያዩ የውጭ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን የዳሰሰ ጽፍ ሲያቀርቡ የሃገራችንን የከተማ እድገት ከፌደራል አደረጃጀታችን አንጻር ይዳስሳሉ ብዬ ብጠብቅም ንክች ሳያደርጓት አልፈዋል።  ንብረት ማስለቀቅ በኢትዮጵያ ከተሞች በሚል ርዕስ ህጉ፣ ተቋሙና አተገባበሩ ላይ ያለውን የህግ ጉዳይ ከልማት የዳሰሰ ሁለተኛ ጽሁፍ ዶ/ር ሙራዱ አብዶ አቅርበዋል። በዚህ ጽሁፋቸው ዶ/ር ሙራዱ ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ የህጉ አተገባበር በከተሞች እድገት ላይ ያለውን ተግዳሮት በአንጻራዊነት ከሌሎቹ በተሻለ መሬት ላይ  ያለውን ችግር እና ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ያሉትን ሊያሳዩን ሞክረዋል። የመጨረሻው ጽሁፍ ያቀረቡት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በልማት ዙሪያ የመገናኛ ብዙሃን፣ ህዝቡና መንግሰት የሚኖራቸውን ሚና ከሃገራችን አንጻር ሳይሆን ከሳይንሱ አንጻር መወያያ ሃሳብ ሳይሆን ትምህርት የሰጡበትን ጽሁፍ አቅርበዋል። በዚህ የዩኒቨርስቲው የምክክር መድረክ ላይ ጠብቀነው የነበረው ሞቅ ያለ ውይይት በቅጡ ሳይካሄድበት ተጠናቋል። ለዚህም ዋናው ችግር ከላይ እንዳልኩት ጥልቀት የሌላቸውና ሊያወያዩ የሚችሉ ጽሁፎች አለማቅረባቸው አንዱና ዋነኛው ምክንያት ነው።

የዚህ የምክክር መድረክን ክፍተት ልጠቁምና ከርዕሱ አንጻር ያለኝን ሃሳብ ላስቀምጥ። የመጀመሪያው የውይይት መድረኩ ክፍተት ከቀረበው ርዕስ ጋር ተያይዞ ከሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አያይዞ በድፍረት ጽሑፍ የማቅረብ ችግር ነው። በዚህ ረገድ እንዳየነውና እንደታዘብነው ጽሁፍ አቅራቢዎቹ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በፍፁም መንካት አልፈለጉም። እኔ በውይይት መድረኩ ላይ ለመሳተፍ ስሄድ የሃገራችን የፌደራል ስርአት በከተሞች እድገት ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ ሙሁራኑ በቅርቡ በኦሮሚያ የተቀሰቀሰውን ግጭት ምሳሌ አድርገው የመፍትሄ ሃሳብ የሚጠቁሙበት ውይይት ይሆናል ብዬ ብጠብቅም አንዳቸውም ሊነኩት አልደፈሩም። በዚህ ረገድ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ አቶ ሴኮቱሬ ጌታቸው በግልጽ የኦሮሚያው ማስተር ፕላንን ሰበብ አድርጎ የተቀሰቀሰውን ችግር ተንተርሶ ጥልቅ ሃሳቦች ይነሳሉ ብለው ቢጠብቁም ከሙሁራኑ አለመነሳቱ የውይይት መድረኩን እንዳደበዘዘው ተናግረዋል። ስለዚህ ጽሁፍ አቅራቢዎቻችን ከሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ጽሁፍ ያለማቅረብ ችግር አስተውዬበታለሁ። ይሄን ጽሁፍ ባቀርብ ይሄ ይመጣብኛል የሚል የሙሁራኖቻችን የተለመደ ፍርሃት፣ ምሁራኖቻችን በአገራችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ክንውኖች ላይ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ በማድረግ በፖሊሲ አውጪ ባለስልጣኖቻችን ላይ በጎ የሆነ ተጽዕኖ ማድረግ የሚገባቸው ቢሆንም በዚህ ረገድ ብዙም አልታደልንም። ከፊሎቹ ሙሁራኖቻችን በጽንፈኛው ጎራ ተሰልፈው የጥላቻ ፖለቲካ ሲያራምዱ ከፊሎቹ ደግሞ አልሰማንም አላየንም በሚል የአድርባይነት መንፈስ የተጠናወታቸው ናቸው።  

ሌላው እንደዚህ አይነት መድረኮች የሚዘጋጁት ለሚዲያ ፍጆታነት ብቻ አይመስለኝም። በቂ እና ለሃገር ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን ሊያቀርቡ የሚችሉ  ባለድርሻ አካላት ተሳትፈው በውይይቱ ላይ የሚገኙት የመንግስት ፖሊሲ አውጭዎች በሃገሪቱ በፖሊሲ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችንና ተግዳሮቶችን ለማየት እንዲችሉ መሆን አለባቸው ብዬ አምናለሁ። የዚህ ውይይትም ዋና አላማ የነበረው የሃገራችንን የከተሞች እድገት ለመገምገም ቢሆንም በቂ የውይይት ግዜ ደግሞ መስጠት አስፈላጊ ነው። በዚህ መድረክ ላይ ግን ጽሁፍ አቅራቢዎቹ ለአንድ ቀን የውይይት ፕሮግራም ከአንድ በላይ መሆን ያለባቸው አይመስለኝም። ሁለትና ሶስት ጽሁፎችን ማቅረብ ጉዳዮችን በጥልቀት ለመፈተሸ ዕድል የሚሰጥ አይመስለኝም። ስለዚህ ዩኒቨርስቲው ከዚህ በኃላ በሚያዘጋጃቸው የውይይት መድረኮች ጽሁፍ አቅራቢዎችን ውሱን በማድረግ ባለድርሻ አካላት የሚሰጡትን አስተያየትና ሊብራሩ ይገባሉ ብለው ሊያነሷቸው ለሚችሉ ጥቄዎች ዕድል የሚፈጥር መሆን አለበት። አለበለዚያ የሚደረጉ ውይይቶች ተደረጉ ለመባል ብቻ የሚደረጉ እንዳይሆኑ እሰጋለሁ።

የመጨረሻው የውይይት መድረኩ ክፍተት የአወያዩ ችግር ነው። በዚህ ረገድ በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ተካፋይ የነበርነው የኢዴፓ አመራሮች የመድረኩን ዝግጅት አስመልክቶ፣ የቀረቡት ጽሁፎችንና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የፌደራል ስርአት በከተሞች እድገት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለማሳየትና ሃሳባችንን ለማካፈል በተደጋጋሚ ጊዜ እጃችንን ብናወጣም አወያዩ እድል ሊሠጡን አልቻሉም። እንደዚህ በጋዜጣ በጽሁፍ ሃሳባችንን መግለጻችን አይቀሬ ቢሆንም ውይይት የሚመራ ሰው ለተሰብሳቢው ሁሉ ፍትሃዊ የሆነ እድል መስጠት አለበት እላለሁ። ለዚህ ሁሉ የመድረኩ ጥበት የፈጠረው ችግር እንዳለ  ቢሆንም የፕሮፌሰር ወልደአምላክ በእውቀት የመድረክ አመራር ግን አልተመቸኝም።

በአጠቃላይ የመድረኩን ሂደት በዚህ መልኩ ለማሳየት ከሞከርኩኝ በጊዜው እድሉን አግኝቼ አስተያየት ልሰጥበት የነበረውን ሃሳብ እንደዚህ በጽሁፍ አደራጅቼ ለማቅረብ ልሞክር። የውይይቱን ርዕስ የሚገልጸውን የግብዣ ደብዳቤ ካየሁት ቀን ጀምሮ ውይይቱ ሞቅ ያለ ይሆናል ብዬ ነበር የገመትኩት። ግን ይሄና ብገምትም በጽሁፍ አቅራቢዎቹ ተገቢ ያልሆነ ፍራቻ በቂ ውይይት ሊደረግበት የሚገባው ውይይት (በኔ እምነት ምንም ገንቢ ውይይት) ሳይደረግበት ተጠናቋል።

የሃገራችን የከተሞች እድገት ኢህአዴግ በስልጣን በቆየባቸው 25ዓመታትዘላቂ የሆነ  እድገት አሳይቷል የሚል እምነት የለኝም። በተለይ አዲስ አበባ ላይ ከ1997በኋላ በተወሰነ መልኩ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ የሚታየው ለውጥ እንዳለ ሆኖ አሁንም በዘርፈ ብዙ ችግሮች ርዕሰ ከተማዋ ከህንጻዎቿ ጀርባ ያለው መልኳ እጅግ አስከፊ ነው። ለዚህ ደግሞ ዋናው ችግር ገጠርን ማዕከል ያደረገው የኢህአዴግ ስትራቴጂ ነው። በዚህ የተንሻፈፈ ስትራቴጂውና ሃገሪቱ በምትከተለው ቋንቋን ዋነኛ መስፈርት ባደረገው የፌደራል አደረጃጀት ምክንያት ከተሞቻችን የተሻለ የከተሜነት ደረጃ ላይ እንዳይደርሱ ማነቆ ሆኖባቸዋል። ከሁለቱ ማለትም ገጠርን ማዕከል ባደረገው ስትራቴጂውና በፌደራል አደረጃጀቱ ምክንያት የተፈጠሩትንና ችግሮችና መፍትሄ የምለውን ሃሳብ አቅርቤ ጽሁፌን እቋጫለሁ።

የሃገራችን የከተሜነት እድገት ከደርግ መንግስት ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ በፐርሰንት ሲቀመጥ ይሄን ያህል የሰፋ ልዩነት እንደሌላቸው የራሱ የመንግስት ዳሰሳ ያስረዳል። ለዚህ የከተሞች እድገት እንቅፋት ከሆኑት ዋነኛ የኢህአዴግ መራሹ መንግስት ችግሮች አንዱ የከተሞች አስተዳደርን ለከተማ ኑሮ ባይተዋር ለሆኑ ግለሰቦች የመስጠቱ ነው። በዚህ ረገድ አዲስ አበባን በከንቲባነት ሲመሩ የቆዩትን ግለሰቦች ብንመለከት አንዳቸውም የከተማ ኑሮ ልምድ ወይንም በውጭ ሃገር በመቆየት ከተማን ከተማ የሚያሰኘውን የውጭ ልምድ በተሞክሮ የሚያውቁ አይደሉም። ሁሉም ለከተማ ኑሮ ባዕድ የሆኑ ናቸው። ይሄ ደግሞ በከተሞች እድገት ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉ አይቀሬ ነው። ስለዚህ መንግስት ከተሞችን የማስተዳደር ኃላፊነቱን የፖለቲካ ወይም የብሄር ተዋጽዖን ብቻ ዋነኛ መስፈርት ማድረጉን መተው አለበት። ከተማ የማስተዳደር ኃላፊነት ልምድና ሙያን ያገናዘበ ሊሆን ይገባል። የከንቲባ ኃላፊነት ከተማን ለሚያውቁ መሰጠት አለበት።

በሃገራችን ከተሞች አደጉ የሚባልበት የመንግስት መስፈርት ራሱ የተሳሳተ  ነው። ከተሞች እድገት የሚለካው መስታዋት በለበሱ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች፣ በረዣዥም የቀለበት መንገዶችና በተለያዩ ቁሳዊ ነገሮች በሚሳዩት እድገት መሆን የለበትም። በዋናነት የከተሞች እድገት ታሳቢ ማድረግ ያለበት የከተሜው ኑሮ ምን ያህል ተለውጧል፣ የመኖሪያ ቤት፣ የትራንስፖርት፣ የኑሮ ውድነቱ፣ የስራ አጥነት፣ የውሃ አቅርቦት፣ የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የስልክ ኔትወርክ፣ የመዝናኛ ቦታዎች፣ የልጆች መጫወቻ ቦታዎች፣ የቄራ አገልግሎት መስጫ፣ ሌላው ቢቀር በከተማችን ያለው አስታዲዮም አንድ ለናቱ ነው። ይሄ ሁሉ ዘርፈ ብዙ ችግር በከተሞች እየታየ ቁሳዊው ነገር ቢበዛ ውጤቱን በዜሮ የሚያባዛ ነው። ይሄ ስር የሰደደ ማህበራዊ ችግር እያለ እድገት አለ ማለት ፌዝ ነው የሚሆነው። ስለዚህ እነዚህን ችግሮች የሚፈታ ስትራቴጂክ ፕላን መንደፍ የግድ ነው የሚሆነው። ያለበለዚያ እነዚህ ችግሮች ተባብሰው የሚቀጥሉ ከሆነ አደጋው ለራሱ ለኢህአዴግ ነው የሚሆነው።

በኢህአዴግ የከተማ ፖሊሲ ከተሞችን በአንድ አይነት ሁኔታ እንዲድጉ የማድረግ አባዜ ደግሞ ሌላው ችግር ነው። በሌሎች ባደጉት ሃገሮች እንደሚታየው ከተሞች በራሳቸው ለየት በሚሉበት አከታተማቸው እንዲታወቁ እና እንዲያድጉ የማድረግ መንግስታት የፖሊሲ አቅጣጫ ያስቀምጣሉ። በኛም ሃገር እንደዚህ ሁሉም ከተሞች አንድ አይነት ባህሪ ያላቸው ከተሞች እንዲሆኑ ከማድረግ ከአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ከተሞችን ለየት ባለ ሁኔታ እንዲያድጉና እንዲመሰረቱ ቢደረግ መልካም ነው እላለሁ። ለምሳሌ አንዱን ከተማ የቱሪዝም፣ ሌላውን ከተማ የኢንዱስትሪ የፋይናንስ፣ የመንግስት መቀመጫ በማድረግ የከተሞቹን ታዋቂነትና እድገት መጨመር ይቻላል። አለበለዚያ ሁሉንም ከተሞች የኢንዱስትሪም፣ የባህልም፣ የንግድም፣ የቢሮና የመዝናኛ ማድረግ ነገ ከነገ ወዲያ የምናገኛቸውና የምንፈጥራቸው ከተሞች ልዩነት የሌላቸው አሰልቺ እንዳይሆኑ ስጋት አለኝ። በተጨማሪም አዲስ አበባ ላይ የሚፈጠረውን ጫና ማባባስ ነው ሚሆነው፤፡ ስለዚህ ከአዲስ አበባ በህዝብ ብዛት ተመጣጣኝ የሆኑ ሁለትና ሶስት የሚሆኑ ከተሞች እንዲፈጠሩ የፖሊሲ አቅጣጫ አስቀምጦ መስራትና በአንድ ነገር ስፔሻላይዝድ የሆኑ ከተሞችን ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ የከተማ የፖሊሲ አቅጣጫ ማስቀመጥ ለዛሬ ለነገ የማይባል የቤት ስራ ሊሆን ይገባል።

አንድ ከተማ በሁለንተናዊ መልኩ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ሰለማዊና ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት መሆን አለባት። በነዚህ መመዘኛዎች ከተሞቻችንን ያየን እንደሆነ ብዙ የሚቀሩን ነገሮች እንዳሉ ማየት ይቻላል። ምሳሌ አዲስ አበባን ብንወስድ ብዙ ማህበራዊ ችግሮችን በሆዷ የያዘች ከተማ ነች። የአስራ ሁለትና የአስራ ሶስት አመት ህጻናት ከምሽቱ ሶስት ሰዓት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ስጋቸውን ለመሸጥ አደባባይ የሚወጡባት፣ የአስራ ሁለትና አሰራ ሶስት አመት ህጻናት ወንዶች በግልጽ በአደባባይ በጫት፣ በሃሽሽ፣ በሲጋራ፣ በቤንዚን፣ በማስቲሽ የሚደነዝዙባት፤ መንደሮች የሃብታምና የደሃ ተብለው የተለዩበትና ሰፈሮች በዘርና በሃይማኖት አጥር ተከልለው የሚኖሩባት ከተማ እየሆነች ነው። ሌላው በአዲሱ የኮንደምኒየም ልማት ሰበብ ብዙ ነባር ሰፈሮች እየፈረሱ ነው። እነዚህ ነባር ሰፈሮች ፈርሰው ወደ ሌሎች ቦታዎች ነዋሪው ሲሄድ ጠቃሚ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶቹ አብረው እየፈረሱ ነው። እድር፣ እቁብና ማህበሮች እየፈረሱ የህብረተሰቡን አብሮነት፣ ማህበራዊ ትስስር እየተናጋ ነው።  ይሄን መንግስት አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ እየሆነ ነው። ይሄን በቅርበት ለምንከታተል ደግሞ ነገ ከነገ ወዲያ ይሄ ከፍተኛ ማህበራዊ ችግር እንደሚፈጥር ስለምናስብ የነገዎቹ ከተሞቻችን ያሰጉናል። ያስጨንቁናል። ስለዚህ መንግስት አብሮነታችንን እና አንድነታችንን አደጋ ውስጥ የሚከቱ የነገ ችግሮቻችንን መንግስት ቢያስብበት። ይሄ ችግር ነገ ከነገ ወዲያ የስርአቱም የሃገርም አደጋ ይሆናልና። ገጠርን ማዕከል ያደረገው የኢህአዴግ አስትራጠየጂ ከተሞችን የዘነጋ በመሆኑ ኢህአዴግ አስትራቴጂውን ጀንበር ሳትጠልቅ ቢፈትሸው ለራሱም ለሃገራችን ከተሞች ትንሳኤ ይሆናል።

የፌደራሊዝሙን ችግሮች ያየን እንደሆነ ቋንቋን ብቻ መስፈርት ማድረጉ ከተሞች እንዳይለሙ እንቅፋት እየፈጠረ ነው። በቅርቡ በኦሮሚያ የተከሰተውን ግጭት እንደማሳያ ብንቀስድ የቋንቋ ፌደራሊዝም የወለደው ችግር መሆኑን እንገነዘባለን። ግጭቱ የተለያየ ምክንያት በኋላ ቢሠጠውም መነሻው ግን የአዲስ አበባና ኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተፈጠረ ነው። ይሄ ማለት የኢህአዴግ ፌደራሊዝም ለአስተዳደርና ለልማት አመቺ የሆኑ ከተሞችን ታሳቢ ያደረገ የፌደራል ስርአት ቢከተል ኖሮ ያ ሁሉ ቀውስ አይፈጠርም ማለት ነው። አሁን አሁንማ በዚህ የተሳሳተ የፌደራል አወቃቀር ዜጎች በነጻነት የፈለጉበት ክልል ሄደው ኑሮ የመመስረትና ሃብት ንብረት የማፍራት ስጋት ውስጥ እየወደቁ ነው። በተጨባጭም እንደታየው ይሄን ስጋት የሚያባብሱ ድርጊቶችን በኦሮሚያው ግጭት ታዝበናል አይተናል። የሌላ ዘር መጤ ተብለው ተባረዋል፣ የግል ባለሃብቶች በዘር ልዩነት ሃብታቸው ወድሟል በተጨማሪም የሃይማኖት ተቋማት ተቃጥለዋል። ስለዚህ በዚህ ፌደራሊዝሙ ከአንድነት ይልቅ ለልዩነት በር የከፈተ በመሆኑ ግለኝነትን እያነገሰ ነው። አንድ ዜጋ ከኖረበት ከተማ ወጥቶ ሌላ ክልል ሄዶ ለመኖር ከምንግዜውም በላይ እየፈራ ነው። የሁላችንም የሚሆኑ ከተሞችን የኢህአዴግ ፌደራሊዝም ሊፈጥርልን አልቻለም። ስለዚህ የፌደራል ስርዓቱ ከምንግዜውም በበለጠ ለኢትየጵያ ቁመና የሚመጥን አይደለምና የሚመጥነንን፣ አንድ የሚያደርገንን፣ የሚያፋቅረንን፣ ባይተዋር የማያደርገን ፌደራሊዝም ስርአት  ያስፈልጋል።

ሌላው ከተሞቻችን እድገት ማነቆ የኢህአዴግ የመሬት ፖሊሲ ነው። የመሬት ፖሊሲው መሬትን በብቸኝነት መንግስት እንዲያስተዳድረው በመደረጉ ዜጎች የመሬት ዋጋ በጣም በመወደዱ እየተሰቃዩ ነው። መንግስት መሬትን በፈለገው ግዜ በአነስተኛ ካሳ ከነዋሪዎች እየወሰደ እሱ በብዙ በዕጥፍ ዋጋ እየቸበቸበ ነው። ዛሬ ከተሞቻችን ላይ የመሬት ዋጋ ጣራ በመንካቱ ዜጎች የቤት ባለቤት የሚሆኑበት እድል እየጠፋ ነው። ባለፈው አመት እንደሰማነውን በጋዜጣም እንዳነበብነው  በመርካቶ የአንድ ካሬ ቦታ ዋጋ እስከ 350ሺህብር የሚሸጥበት ሃገር ነው። ይሄ ደግሞ የመንግስትን ስግብግብነት የሚያሳይ እንጂ ለህዝብ ተቆርቋሪነት የሚያረጋግጥ አይደለም። ስለዚህ የከተማው ነዋሪ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኝበትን መንገድ የየከተሞቹ አስተዳደሮች ሊያስቡበት ይገባል። በተጨማሪም የኮንደሚኒየም ቤቶች ግንባታን በብቸኝነት መንግስት መቆጣጠሩን ትቶ ለግል አልሚዎች መሬትን በነጻ በመስጠት አልምተው ለነዋሪው በርካሽ ዋጋ የሚተላለፉበትን መንገድ መፈጠር አለበት። ቤት ገዝተው መኖር ለማይፈልጉ ዜጎችም በርካሽ የሚከራዩበትን ቤት መንግስት መገንባት አለበት። ለህዝብ የሚያስብ መንግስት መሬትን ለብቻው ተቆጣጥሮ እየቸበቸበ መኖር አይገባውምና መሬትን እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ለማስተዳደር የሚያስችል ፖሊሲ መንደፍ ካልተቻለ በስተቀር ሀዝቡ በመኖሪያ ቤት ችግር የሚሰቃይባቸው ከተሞች እያሉ ከተሞች አደጉ ማለት አያስችልም።  እድሉን በዚያ የውይይት መድረክ አግኝቼ ቢሆን ይሄን ያህል የሰፋ እድል አይኖረኝም ነበርና በውይይቱ አጋጣሚ ይሄን በከተሞቻችን ላይ ያሉ ከእድገቱ በስተጀርባ የሚታዩ ስጋቶቼን በመተንፈሴ በአጋጣሚው ተደስቻለሁ። ቸር እንሰንብት። (ይህ ጽሁፍ የግል አቋሜን የሚያሳይ ነው።)n

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
720 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 945 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us