ግመሎቹም ይጓዛሉ፤ ውሾቹም ይጮሃሉ!!

Wednesday, 18 May 2016 13:07

ግመሎቹም ይጓዛሉ፤ ውሾቹም ይጮሃሉ!!

(የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲን አስመልክቶ ለወጡት ጽሁፎች የተሰጠ ምላሽ)

 

ሰንደቅ ጋዜጣ ግንቦት 3 ቀን 2008 ባወጣው እትሙ በፊት ገጹ ላይ “የአዲስ አበባ ከተማ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ከፍተኛ አመራሮች በሙስና፣ በብልሹ አሰራርና በፆታ ትንኮሳ ተገመገሙ” የሚል ዜና ይዞ መውጣቱ ይታወሳል። በተመሳሳይ በዚሁ ጋዜጣ በውስጥ ገጽ ላይ ደግሞ የኔ ሃሳብ በሚለው አምዱ “የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ የቆሸሸ ገመና” የሚል ጽሁፍ አውጥቷል።

‹‹ሰንደቅ›› ጋዜጣ  ዓላማው ግልፅ ባይሆንም  በተለያዩ ጊዜያት የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲን የሚመለከቱ ከእውነት የራቁና በተጨባጭ መረጃ ያልተደገፉ ምንአልባትም ለተቋሙ በጎ አመለካከት በሌላቸው ግለሰቦች አሉባልታ ላይ በመመስረት የተቋሙን መልካም ስም የሚያጎድፉ ጽሁፎችን በተደጋጋሚ ይዞ ሲወጣ ተመልክተናል።

በእርግጥ ኤጀንሲውን በተመለከተ በተደጋጋሚ የሚወጡ ፅሁፎቹ የተቋሙን መልካም ተግባርና ስም ለማጉደፍ በመሰረተ ቢስ ውንጀላዎች ላይ ተመስርተው የተፃፉ መሆናቸው ግልፅ ቢሆንም በአንድ በኩል የጋዜጣው አዘጋጆችም ሆነ አንባቢያኑ በጊዜ ሂደት እውነታውን ለመገንዘብ ይችላሉ የሚል እምነት በማሳደር በሌላ በኩል ደግሞ ትችቶቹ በአሉባልታ ላይ የተመሰረቱና መሰረተ ቢስ ቢሆኑም እንኳን ኤጀንሲው እያሳየ ያለው ለውጥ የበለጠ እንዲጎለብት ያግዙታል በሚል በትዝብት ከመመልከት ውጪ ኤጀንሲው ሌላ ትርጉምም ሆነ አፀፋዊ ምላሽ መስጠት አልፈለገም።

ይሁን እንጂ በጋዜጣው የሚወጡት ጽሁፎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመሰረታዊ ጋዜጠኛነት ስነ ምግባርና መርህዎች ብቻም ሳይሆን ሀገራችን ከምትመራባቸው የፕሬስ ህጎች ባፈነገጠና መርህ አልባ በሆነ ደረጃ በአሉባልታና በጥላቻ ላይ ያተኮሩ፣ የተቋሙን ለውጥ ሆን ተብሎ የሚያደበዝዙ፣ እንደአንድ ታዳጊ የሚዲያ ተቋም በየጊዜው ከድክመቶቹ እየተማረ መልካም ውጤቶቹን ደግሞ እያጎለበተ በመምጣት በተጨባጭ ለማስመዝገብ የቻላቸው ስር ነቀል ውጤቶችን የሚያጠለሹና ሚዛናዊነት የጎደላቸው መሰረተ-ቢስ ውንጀላዎችና ወሬዎች በጋዜጣው ላይ እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል።

ስለሆነም አሁን ላይ ‹‹ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስለናል›› በሚል አበው የሚገልፁትን ቢሂል ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ይሆናል። ከዚህ በመነጨም በተቋማችንና በአመራሩ ላይ በጋዜጣው ከጭፍን ጥላቻ በመነሳት የሚስተናገዱ የበሬ ወለደ ውንጀላዎች ምንአልባትም የጋዜጣው አንባቢያንን በተቋሙ ላይ የተሳሳተ አመለካከት ሊያሲዙ ይችሉ ይሆን? ከሚል አስተሳሰብ በመነሳትና ለጋዜጣው ተከታታዮች ክብር በማሰብ የተቋማችንን ትክክለኛው ገፅታ በሚገልፅ መልኩ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አምነናል።

በቅድሚያ ግን ግንቦት 3 ቀን 2008 የወጣውንና ሚዛናዊነት እና ኃላፊነት የጎደለውን ክብረ-ነክ ጽሁፍ እንዴት የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንዲታተም እንደፈቀደ ጥያቄያችንን ማቅረብ እንወዳለን፤ የሚመራበት ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ቅኝቱ ምን እንደሆነም ለመጠየቅ እንገደዳለን። ምክንያቱም የጋዜጠኛነት ሙያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረና የራሱ የሆኑ የስነ ምግባር መርሆዎች ያሉት ቢሆንም ከሙያው ስነ-ምግባር ባፈነገጠ ደረጃ በአንድ ተቋም ላይ ያነጣጠረ የማጠልሸት ዘመቻ ዓላማው ምን ይሆን የሚለው ጊዜ የሚፈታው ቢሆንም ዓላማው ምንም ይሁን ምን ኤጀንሲው በተለያዩ ጊዜያት ሆን ተብለው የሌለ ስም በመስጠት ለተፈፀሙበት የስም ማጥፋት ወንጀሎች በህግ የሚጠይቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለጊዜው ትክክለኛና ተጨባጭ ተቋማዊ እውነታውንና ገፅታውን  ማስረዳትና ማሳወቅ ግን የሚገባ ይሆናል።

ከዚህ አኳያም ኤጀንሲውን አስመልክቶ በጋዜጣው ግንቦት 3 ቀን 2008 በፊት ለፊት ገጽ ላይ የወጣው ዜና በጋዜጣው ሪፖርተር እንደተዘገበ በግልጽ አስቀምጧል። የጋዜጣው ሪፖርተር ከሰራተኞቻችን ጋር በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ስንወያይ ፈፅሞ በቦታው ሳይገኝ ጭራሽ በውይይቱ ላይ ያልተነሱ ጉዳዮች ዜና ተደርገው ቀርበዋል። በሌላ መልኩ ደግሞ በገጽ 13 “በዚህ ዓምድ ስር የሚወጡ ጽሁፎች የጸሐፊውን እንጂ የኤዲቶሪያሉን አቋም አያንጸባርቅም” በሚል በውጭ ጸኃፊ በብር ስም የተፃፈ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ጽሁፍ ይዞ ወጥቷል። ይሄ እውነታ ብቻ የጋዜጣውን የመረጃ ምንጭ ተአማኒነትና ሚዛናዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑን መመልከት ይቻላል። ስለሆነም የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ የጋዜጣው ኤዲቶሪያል ቦርድ አምኖበትም ሆነ ሳያምንበት የወጣውን ጽሁፍ በሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በኩል ቶሎ እርምት ሊወሰድበት እንደሚገባ ያምናል።

እንደሚታወቀው ጋዜጠኝነት እውነት ላይ ተመስርቶ መረጃን የማቀበል፤ ሚዛናዊ ሆኖ ሃሳብን የማንሸራሸርና ከሃሜት ይልቅ በተጨባጭ ሃቆች ላይ ተመስርቶ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስን የሚጠይቅ ትልቅና የተከበረ ሙያ ነው። ይህ እውነታ ግን የሙያውን ስነ-ምግባር አውቀውና ጠብቀው ለሚኖሩትን እንዲሁም ለሙያውና ለራሳቸው ክብር የሚሰጡትን ብቻ የሚመለከት ነው። ሙያውንና እራሳቸውን አቅልለውና ቀለው የሚኖሩትና በጋዜጠኛነት ስም ለመነገድ የሚሹ ግለሰቦችን ግን ይህ አይመለከታቸውም።

ግንቦት 3 ቀን 2008 በወጣው ጋዜጣ የውስጥ ገጽ ላይ “የእኔ ሃሳብ” በሚል አምድ ስር ዘመኑ በሪሁን በሚል የብእር ስም የሰፈረውን ጽሁፍ ያነበበ ሰው የሚገባውም ይህንኑ ነው። የብዕር ስም በሚል ታፔላ ውሸት እንዲጽፉ የተፈቀደላቸው “ብዕረኞች” ሳይወጡና ሳይወርዱ አንድ ስርቻ ውስጥ ተወሽቀው የግለሰቦችንና የተቋማትን ስም በአሉባልታና በሃሜት ማጥፋት የተፈቀደ ሙያ መስሎ የሚታያቸው ናቸውና።

በእርግጥ በውስጣችን ሊኖር ከሚችል የጥላቻ አስተሳሰብ አኳያ ለሙያውና ለእራሳቸው ክብር የሌላቸው ግለሰቦች ለሌላው ክብር ይሰጣሉ ተብሎ ባይጠበቅም በዚህ ደረጃ ዘቅጠው ወደ ለየለት ዘለፋና ስም ማጥፋት ይገባሉ ብሎ መጠበቅ ግን ይከብዳል።

ይሁንና ደግሞ በሰሚ ሰሚና የውስጥ ምንጮች እንደዘገቡት በሚል የተለመደ መሸፈኛ በዘመቻ መልክ የኤጀንሲውን ስም የሚያጎድፉ፣ የኤጀንሲውን አመራሮችና ሰራተኞች የሚያንቋሽሹ፣ ኤጀንሲው የተሰጠውን ህጋዊ ኃላፊነቶችንና መብቶችን የሚክዱ ሃሰተኛ መረጃዎች በጋዜጣው ላይ እንዲታተሙ መደረጉ ኃላፊነት እንዳለበት ከሚገልፅ የጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የሚጠበቅ አይደለም።

የጋዜጣው ሪፖርተር ለመፃፍ ሲነሳሳ ኤጀንሲው እየሰራቸው ያሉትን መልካም ተግባራት ለመመልከት ለምን አልደፈረም? የጋዜጠኝነት ‹‹ሀ ሁ›› ሚዛናዊነትን መረዳት ነውና ችግር ናቸው ብሎ ባስቀመጣቸው ነጥቦች ዙሪያስ የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች ለማነጋገር ለምን ድፍረት አጣ? በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ ዜናውን ማዘጋጀት ሲገባው ሃሜትና አሉባልታን እንዴት የዜናው ምንጭ ለማድረግ ደፈረ? በተለይ ደግሞ በድፍረት ኤጀንሲውን፣ አመራሮች እና ሰራተኞቹን ለማጣጣል ለምን ፈለገ? የሚሉትን ማንሳት እንፈልጋለን። እኛ እንደምረዳው ጋዜጠኝነት በእውነት መረጃ ላይ በመመስረት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ህዝብን ለማገልገል የሚያስችል የተከበረ ሙያ እንጂ በጥላቻና በማጥቃት ሂሳብ የሚወራረድበት ሙያ አይደለም።

በስማ በለው እገሌ እንደነገረኝ፣ የውስጥ ምንጮች፣ ታማኝ ምንጮች፣ እነ እገሌን በየስብሰባው ባገኘኋቸው ቁጥር ስለ ኤጀንሲው መጥፎነት ስለሚነግሩኝ  በሚል በተጨባጭ መረጃ ያልተደገፈ፣ በትውውቅና በዝምድና የአንድን ተቋም ስም ማጠልሸት ተራ ውንጀላ እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል።

የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ በሩ ለማንም ክፍት ነው። የኤጀንሲውን ስም ባገኙት አጋጣሚ ለማብጠልጠልና ለማጠልሸት ለሚፈልጉት ግን ዘወትር ክፍት የሆነውን በር ከመጠቀም ይልቅ ለስውር ዓላማቸው የሚጠቅማቸውን ሃሜትና አሉባልታን ከመሰሎቻቸው መቃረምን ይመርጣሉ።

በጋዜጣው ላይ በድፍረት እንደተፃፈው የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ‹‹የቆሸሸ ገመና›› ያለው ሳይሆን ሁል ጊዜ እራሱን እያደሰ የሚሄድ ጠንካራ አመራሮችና ታታሪ ባለሙያዎች በውስጡ አቅፎ የያዘ ተወዳጅና ተመራጪ የከተማችን የሚዲያ ተቋም ነው። ኤጀንሲው የራሱን ማሰራጫ ተክሎና አዳዲስ አደረጃጀቶችን አጥንቶ በራሱ አቅም ፕሮግራሞችን ማሰራጨት ከጀመረ እንኳ ከአንድ ዓመት ብዙ የዘለለ ዕድሜ ባይኖረውም በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በከተማ፣ በሃገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ልዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ተደራሽ በማድረግ በብዙ ተመልካቾች ዘንድ ተመራጭ ለመሆን በቅቷል።

የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ስራዎቹን በየዕለቱ በአዲስ ቴቪ፣ በኤፍ.ኤም. 96.3፣ በአዲስ ልሳን ጋዜጣና በአዲስ ሜትሮፖሌታን መጽሄት መረጃዎችን ለህዝብ አይንና ጆሮ የሚያደርስ የሚዲያ ተቋም ነው። በየእለቱ በሚያስተላልፋቸው ወቅታዊ ጉዳዮች፣ ትምህርታዊ መረጃዎችና አዝናኝ ርዕሰ ጉዳዮች በአጭር ጊዜ ውስጥ የብዙዎችን ቀልብ መሳብ ችሏል። የህዝብን ጉዳይ ጉዳዩ ያደረገ በከተማዋ ነዋሪዎች የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ የሚያወጣ እና በህዝብ ላይ በደል የሚያደርሱ ኃላፊዎችን የሚያጋልጥ የህዝብ ሚዲያ ነው። ቅን ልቦና ላለውና በጥላቻ ላልታወረ የሚገባውም ይኽው ሃቅ ነው።

ኤጀንሲው ሰራተኞቹ ሃብቶቼ ናቸው ብሎ የሚያምንና ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ የሚሰጣቸው በመሆኑ በሰራተኞች የሚነሱ ጥቃቅን ችግሮችን  ትኩረት ሰጥቶ የሚፈትሽ ተቋም ነው። ከስራተኞቹ ጋር በሚያደርገው ግልጽ ውይይትም የግልጽነትንና የተጠያቂነትን ባህል እያሰፈነ የመጣ ተቋም ነው። ለዚህም ነው በቅርቡ ከሰራተኞቹ ጋር ባደረገው ውይይት ባልተገባ ጥቅም እና ብልሹ  አሰራርውስጥ አግኝቼዋለሁ ብሎ ያመነበትን አመራር ከስራ አሰናብቶ ለፍርድ ማቅረብ የቻለው።ይህ የግልጽነት አሰራር ለበርካቶች በአርአያነት መጠቀስ ሲገባው ሃቁ  ተዛብቶ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ሁሉንም አመራሮች በሙስናና በብልሹ አሰራር ለመወንጀል ተሞክሯል።

ከዚህም በባሰ መልኩ የተቋሙ ጋዜጠኞች “አይደለም ከሌላ ሚዲያ ጋዜጠኞች ጋር ሊወዳደሩ በራሳቸው ውስጥም አርአያ ነው የሚባል ጋዜጠኛ እና ኤዲተር አለ ለማለት አይቻልም” የሚል በድፍረትና በማን አለብኝነት የተፃፈ ጅምላ ጭፍጨፋ እናገኛለን። የአንድን ተቋም ባለሙያዎች በሙሉ ሞያዊ አቅም የላቸውም ብሎ መፈረጅ ደፋርና ባለጌ ከመሆን ውጭ ሌላ ምን ይባላል። በድፍረት እና በማን አለብኝነት እንደተፃፈው ሳይሆን የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ተቋማቸውን የሚወዱ፣ ስራቸውን የሚያፈቅሩ፣ ያመኑበትን ነገር ያለምንም ፍራቻ ፊት ለፊት የሚናገሩ፣ ዘውትር ሙያዊ አቅማቸውን ለማዳበር የሚተጉ እና ለብዙ ጋዜጠኞች በመልካም ስነምግባራቸው አርአያ የሚሆኑ ናቸው። እነዚህ ባለሙያዎች የተቋሙ ሃብቶች በመሆናቸው ነው ኤጀንሲው በአጭር ግዜ  ውስጥ በህዝብ ዘንድ አመኔታን በማትረፍ ተመራጭ እየሆነ መምጣት የጀመረው።

የኤጀንሲው አመራሮችና ሰራተኞች በወሰዱት የጋራ አቋምም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን፣ ብልሹ አሰራሮችንና ከስነ-ምግባር ውጭ የሆኑ ተግባራትን በተባበረ ክንድ ለማስወገድ ትግል ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ከየትኛውም ተቋም የሚሰጥ የትራንስፖርት አበልም ሆነ ሌሎች ምልጃዎችን መቀበል የተቋማችንን ስም ያጎድፋል በማለት እራሳቸውን አስከብረው ተቋሙንም አስከብረዋል። ጋዜጠኞቻችን በተሰማሩባቸው ቦታዎች ህዝቡ በየአዳራሹ በትራንስፖርት ስም የሚሰጡ ብሮችንና ሌሎች አበሎችን አይገባንም በማለት  ለሙያቸውና እና ለህሊናቸው ተገዢ መሆን ችለዋል።

በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ተቋሙን ለመወንጀል ቆርጦ የተነሳው “ብዕረኛ” ግን ከሙያው ብዙ የራቀ በመሆኑ ጋዜጠኞቻችን ምልጃና ጉቦ እንዲቀበሉ ለመማጸን ሞክሯል። ይህንኑ ከጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር ውጭ የሆነን ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ ጥቂት ጋዜጠኞች ቢገኙ  “ብዕረኛው” አይኑን በጨው አጥቦ እንዳሰፈረው ከስራ የሚባረሩ ሳይሆን በተግሳጽና በምክር እንዲታለፉ ነው የሚደረገው። “ብዕረኛው” ግን ከአዲስ አበባ ምክር ቤት 50 ብር አበል የወሰዱ ጋዜጠኞች ከሰራ እንደተባረሩ ነግሮናል። ሌላውን ማደናገር ቢቻል እንኳን እውነታውን የሚያውቁት የተቋሙ ሰራተኞች ይታዘቡኛል አይባልም ወይ?

ሌላው ተራ ውንጀላ ደግሞ የሚከተለው ነው። “አዲስ አበባ የሁሉም ህዝብ ከተማ ብቻ ሳትሆን አህጉራዊ መዲና ሆና ሳለ ደረጃዋን የማይመጥኑ መንግስታዊ ተቋማት የታጎሩባት ናት። ከእነዚህ ዓይነቶቹ መስሪያ ቤቶች ቀዳሚ ተጠቃሹ ደግሞ ይህ ኤጀንሲ ነው ብል ማጋነን አይሆንም” የሚል ፍረጃ እናገኛለን። ለመሆኑ ጸሐፊው የትኛውን ጥናት አገላብጦ ወይንም አጥንቶ ነው አዲስ አበባ ደረጃዋን የማይመጥኑ መንግስታዊ ተቋማት የታጎሩባት መሆንዋን በድፍረት ለመፃፍ የሞከረው? ይባሱኑ ደግሞ ለከተማዋ ነዋሪዎች አንደበት ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኘውንና  ህጋዊ ሰውነት ያለውን የሚዲያ ተቋም ከመረጃ ውጭ ለመዝለፍ ለምን ተጣደፈ? ፍርዱን ለጋዜጣው አንባቢ መተው የተሻለ ነው።

በአጠቃላይ ረቡዕ ግንቦት 3 ቀን 2008 በሰንደቅ ጋዜጣ የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲን አስመልከተው በፊት እና በውስጥ ገፆች የሰፈሩት መረጃዎች ሚዛናዊነት የጎደላቸው፣ ተራ አሉባልታና ሃሜት ላይ የተመሰረቱ፣ የተቋሙን ኃላፊዎችና ሰራተኞች ስም እና ክብር የሚያጎድፉ ናቸው። ኤጀንሲው በጋዜጣው ላይ ለወጡት ሃሰተኛ መረጃዎች ሁሉ ምላሽ ለመስጠት ከመሞከር ይልቅ በተወሰኑት ላይ ብቻ ለማተኮር ሞክሯል። በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው በሃሰት የጎደፈው ስሙን ለማደስ ግን ጉዳዩን ለህግ በማቅረብ ይፋረዳል።

በየትኛውም ጋዜጣ ላይ ሃቅን መሰረት ያደረገ ፅሁፍ ወይም ትችት ተቋምንም ሆነ ሃገር እንደሚያሳድግ የታመነ ነው። በተቃራኒው በጥላቻ፣ በአሉባልታና በማፍረስ ሂሳብ የሚሰነዘር ትችት ከተራ ውንጀላና እንደማይጠቅም ተራ ወረቀት ተቀዶ ከመጣል የዘለለ ፋይዳ ይኖረዋል የሚል እምነት የለንም ። ስለሆነም በርዕሳችን እንዳሰፈርነው  “ግመሎቹም ይጓዛሉ፤ ውሾቹም ይጮሃሉ” ነውና ብሂሉ የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ዘወትር እራሱን እያደሰና እያዘመነ ለመዲናችን ነዋሪዎች ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ መሆኑን ይቀጥላል።n

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
798 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 916 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us