በግንቦት 20 ካገኘነው ይልቅ ያጣነው ይበዛል!

Wednesday, 25 May 2016 12:54

 

ከአዳነ ታደሰ

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል

በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ የሚገኘው የኢህአዴግ መንግስት ከደርግ መንግስት በ8 ዓመት በልጦ ለ25 ዓመታት ሃገሪቱን እየመራ ይገኛል። ይኼንንም የ25ኛ ዓመት የድል በዓል ለማክበር የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ተፍ ተፍ ማለት ከጀመሩ ሠንበትበት ብለዋል። የሃገራችን መገናኛ ብዙሃንም በግንቦት 20 የተገኙ ለውጦችን ነጋ ጠባ እየነገሩን ነወ።  በዚህ የሚዲያዎቹ የዕለት ተዕለት ውትወታ የሚነገረን ግንቦት 20 ያስገኘው ድል ብቻ ነው።  እኔ ደግሞ ለምን ያገኘነውንና ያጣነውን አካትቼ አንድ ፅሁፍ አልፅፍም አልኩና ብዕሬን አነሳሁ።

ስለዚህ በእኔ እምነት በኢህአዴግ ካገኘነው ይልቅ ያጣነው ይበዛል። ለዚህ መመዘኛዬ የማደርገው ደግሞ ቁጥርን ሳይሆን የጉዳዮችን ክብደት ነው። በመሆኑም ወሳኝ በሆኑ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ አተኩሬ ያገኘነውንና ያጣነውን ለማስቀመጥ እወዳለሁ።

ኢህአዴግ በትረ ስልጣኑን ከያዘበት ከ1983 ጀምሮ ባለፉት 25 አመታት የአፈጻጸም፣ በዘላቂነት ችግሮችን የሚፈታ ፖሊሲ አለመኖር፣ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት፣ የጥራት፣ የአድሏዊነት፣ የቁርጠኝነትና ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ ያለው መረን የወጣው ሙስና  መልካም በሚባሉት የኢህአዴግ ጅምሮች ላይ እንቅፋት ሲሆኑ እያየን ነው።

በመንገድ ልማት በኩል ኢህአዴግ ባለፉት ዓመታት ያካሄደው ግንባታ በጣም አበረታች ነው። በዚህ የመንገድ ልማት ላይ የሚታየው ችግር የሀገር ውስጥ ተቋራጮችን አሳታፊ ያለማድረግ፣ የጥራት ችግር፣ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ያለው የካሳ አከፋፈል ኢ-ፍትሃዊ መሆን፣ የሀገር ሃብት ብክነትና ለሙስና ተጋላጭ መሆን ናቸው። ጤና ተቋማትን በማስፋፋት ረገድም ሰፊ ስራ የተሰራ ሲሆን ተቋማቱ ግን ከጥራት፣ ከባለሙያ እጥረት፣ ከመድሃኒት አቅርቦትና የህክምና መሳሪያዎች እጥረት፣ ከባለሙያ ስነ-ምግባር ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያሉት። የትምህርት ተቋማትን በማስፋፋትም ረገድ ከብዛት አንጻር ከፍተኛ ለውጦች መኖራቸው የሚካድ አይደለም። ነገር ግን የመምህራን ነጻነት፣ የትምህርት ጥራት፣ የመምህራኖች ደመዎዝ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተመጣጣኝ ያለመሆንና የትምህርት ስርዓቱም ለነገ ሃገር ተረካቢ የሚሆን፣ በራሱ የሚተማመንና ለሃገር ተቆርቋሪ ትውልድ የምናፈራበት እየሆነ አይደለም። ድሮ መምህርነት የሚከበር ሙያ እንዳልነበረ ዛሬ የተናቀና በትውልዱም የማይፈለግ የሙያ ዘርፍ እየሆነ ነው። 

በባቡር ሃዲድ ግንባታ አዲስ እርምጃ የተራመድንበት ምዕራፍ ላይ ነን። ሆኖም በዚህም የባቡር ግንባታ በተለይም የአዲስ አበባው የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው። ከነዚህም ውስጥ ግንባታው ከመሬት በላይ በመካሄዱ በከተሞቹ ውስጥ የተገነቡ አንዳንድ ህንጻዎች ውበታቸው እንዲደበቅ አድርጓል፣ የትራፊክ መጨናነቁን ጨምሯል። በተጨማሪም የእግረኞች መተላለፊያን ታሳቢ ያላደረገ በመሆኑ በከተማው ነዋሪ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት እየፈጠረ ነው። ይሄም ሲታይ ፕሮጀክቱ ላይ የጥድፊያ ችግር ያለበት መሆኑን ያሳብቃል።

የህዳሴውን ግድብ ጨምሮ የኃይል አቅርቦቱን ለማሳደግ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ይበል የሚያሰኝ ነው። የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት እየተሰራ ያለው የኮንደሚኒየም ግንባታ ተገቢነት ላይ ምንም ጥርጥር የለኝም። ተገቢም ፕሮጀክት ነው። ሆኖም በዚህ የኮንደሚኒየም ግንባታ ደሃው የህብረተሰብ ክፍል እየተጠቀመ ነው የሚል እምነት የለኝም። የክፍያው መወደድ ድሃውን የህብረተሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረገ አይደለም። አሁንም  ቤት ሰርቶ የማስተላለፉን ኃላፊነት መንግስት ብቻዬን እወጣዋለሁ በማለቱ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ አልተቻለም። ቤት መግዛት ለማይፈልጉት ነዋሪዎችም መንግስት ቤት ሰርቶ በርካሽ የሚያከራይበትን መንገድ እንዲፈልግ ኢዴፓ በ2007 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ ያቀረበውን አማራጭ በቅርቡ የአዲስ አበባ መስተዳድር ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን በዚህ አጋጣሚ ሳላደንቅ አላልፍም።

በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ ያለውን እንቅስቃሴ ከነችግሮቹም ቢሆን እውቅና መስጠት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ነገር ግን ጥቃቅንና አነስተኛ የሁሉም ኢትዮጵያኖች መብት እንጂ የኢህአዴግ አባላት መብት ብቻ መሆን የለበትም። በአነስተኛና ጥቃቅን ለመደራጀት የኢህአዴግ አባል መስፈርትነት ሊቆም ይገባል። መንግስትም አነስተኛና ጥቃቅንን እንደ አንድ የኢህአዴግ አደረጃጀት / ወጣት ሊግ፣ ሴቶች ሊግ/ ማየቱን ትቶ ለማህበራቱ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ እድል መስጠት አለበት። በየከተሞቹም የሚታየው የኮንስትራሽን ዘርፉ መነቃቃት የሚበረታታ ነው። ፖለቲካችን ለዕውቅና ጆሮ የሚሰጥ ባይሆንም ምክንያታዊ ለሆነ ፖለቲከኛ ግን ከባድ አይደለም። ሁላችንም ከጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ ራሳችንን ካላቀቅን ከላይ የጠቀስኳቸው የኢህአዴግ ወይም የመንግስት በጎ ስራዎች መሆናቸውን የሚያስክድ አይደለም። ስልጡን ፖለቲካ ሊያድግ የሚችለው ጥሩን ጥሩ፣ መጥፎውን መጥፎ የሚሉ የፖለቲከኛ አንደበቶች ሲበዙ ነው። ያኔ የጎሪጥ መተያየታችን ያበቃና መከባበር መሃላችን ይሰፍናል። ይሄ ከላይ በበጎ ጎኑ ያነሳሁት እንዳለ ሆኖ አሁንም ለሃገራችን አንድነትና ዘላቂ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት እንቅፋት የሆኑ ኢህአዴግ በህገ-መንግሰቱ ውስጥ፣ በተለያዩ ፖሊሲና አስትራቴጂው የሚገለጹ ችግሮቹም እየታዩ የሙጥኝ ያላቸውን ጉድለቶቹን ለማሳየት ከዚህ ቀጥዬ እሞክራለሁ።

የወቅቱ የሃገራችን ሕገ-መንግስት ለሃገራችን አንድነትና ኢኮኖሚ የማይበጁ ድክመቶችና ችግሮች ያሉበትም ቢሆን እስከ አሁን ሃገሪቷ ከነበሯት ሕገ-መንግስቶች በተለይ የራሱ ጠንካራ ጐኖች ያሉት እንደሆነ አምናለሁ። የሆነው ሆኖ ሕገ-መንግስቱ ውስጥ ለሃገሪቷ አንድነትና የኢኮኖሚ እድገት እንቅፋት ናቸው የምላቸውን አንቀፆች በውስጡ በመያዙ በሕገ-መንግስታችን ላይ የተነፈግነው ይበዛል። የሕገ-መንግስቱ ንፍገት ከመግቢያው ይጀምራል። በመግቢያው ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው የሃገሪቱ ባለቤት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሣይሆን ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ተደርገዋል። ስለዚህ አንድ ዜጋ ሕገ-መንግስቱ እንዳስቀመጠው አትዮጵያዊ የሚባለው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ብሄር ወይም ብሄረሰብ አባል በመሆኑ እንጂ የሃገሪቱ አንድ ዜጋ በመሆኑ አይደለም። በሕገ-መንግስቱ የሃገር ባለቤትነት ከአንድ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ጋር ሳይሆን ከቡድን መብት ጋር የሚያያዝ ሆኗል።

ሌላው የሃገራችን ፌዴራሊዝም ነው። ይኼ የሃገራችን የፌዴራሊዝም አወቃቀር ላይ ያለኝ ልዩነነት የመስፈርቱ ብቻ ነው። አሃዳዊ አደረጃጀት ለኢትዮጵያ አለማስፈለጉ ላይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን ልዩነት ያላቸው አይመስለኝም። አሁን ያለውን የፌዴራሊዝም አወቃቀር የምንቃወም ኃይሎች የብዙዎቻችን መከራከሪያም ቋንቋንና ብሄረሰባዊ ማንነትን ብቻ መስፈርት በማድረጉ ነው። በዚህም የሃገራችን ቀጣይ ሕልውና አደጋ ላይ ወድቋል ነው የምንለው። ይኼ የቋንቋ ፌዴራሊዝም ከአንድነት ይልቅ ለልዩነት በር የሚከፍት በመሆኑ አንድነታችን አደጋ ላይ ነው። ዛሬ በሃገራችን የአንዱ ክልል ነዋሪ ወደ ሌላኛው ክልል በነፃነት ተንቀሳቅሶ ሃብት የማፍራት ጉዳይ የማይታሰብ እየሆነ ነው። ሁሉም የየራሱን ጐጆ ቀልሶ አትደረሱብኝ አልደርስባችሁም በሚል ዘረኝነት ታጥሮ ግለኝነት በአብሮነታችን ላይ ነግሷል። ስለዚህ ለኢትዮጵያ ቁመና፣ አንድነት፣ ህልውናና ለአብሮነታችን የሚሆን የተለያዩ ጠቃሚ መስፈርቶችን ታሳቢ ያደረገ አከላለል ይኑር እያልን ነው። አሁን ያለው ፌደራሊዝም አገራዊ የጋራ ጥቅምን ዘንግቶ ክልላዊ ጥቅም የበላይነትን እንዲይዝ እያደረገ ነው። በቅርቡ የኦሮሚያው ቀውስ የነገረን/ያሳየን ይሄንኑ ነው። የአንድ ሃገር ልጆች በልማት መግባባት እያቀተን ነው። በዚህ 25 ዓመት ለቁጥር የሚታክቱ ዜጐቻችን በፌዴራሊዝሙ ጦስ ተገለዋል፣ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል፣ መጤ በሚል ከአንዳንድ ክልሎች ተባረዋል። ዛሬ ባቡር በኔ ደጅ አያልፍም የሚል ዜጋ ተፈጥሮ በአደባባይ ልዩነቱን እየነገረን ነው። ይኼ ነገ ከነገ ወዲያ በሃገራችን አንድነትና የኢኮኖሚ እድገት የተጋረጠው አደጋ የተፈጠረው የግንቦት 20 ፍሬ እየተባለ በሚወደሰው ቋንቋን ብቻ ዋነኛ መስፈርት ባደረገው የሃገራችን የፌዴራል ስርዓት ውስጥ ነው።

ሌላው በግንቦት 20 ድል ማግስት የተነጠቅነው ሃገር እና ወደብ ነው። ኢህአዴግና ሻዕብያ በግዜው በነበራቸው የተለየ ፍቅር ኢህአዴግ ኤርትራን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከእናት ሀገሯ እንድትገነጠል አድርጓል። በዚህም ምክንያት አስከ ዛሬ ኢህአዴግ በጊዜው ባራመደው አቋም ለሃገር አንድነትና ለዳር ድንበር ግዴለሽ ተደርጎ እንዲታይ ያደረገውን ስህተት ሰርቶ አልፏል። በዚህም ታሪካዊ የኢህአዴግ ስህተት ሃገራችን ለወደብ ኪራይ በየዓመቱ ከፍተኛ ብር ወጪ እንድታወጣ የዳረጋትን የሃሰብ ወደብ አሳጥቷታል። ነፃነት ወይስ ባርነት በሚል የፌዝ ምርጫ ከኤርትራ ህዝብ ጋር ለመለያየት በቅተናል። ይሄም አልበቃ ብሎ ለዳግም ብተና ስጋት ውስጥ ሊከተን የሚችልና በዓለም ብቸኛዋ ሃገር ያደረጋትን የመገንጠል መብትን በሕገ-መንግስቷ ያካተተች ሃገር የሆነችው በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ነው። ይኼ የመገንጠል መብት ተግባራዊ ቢሆን (የሠይጣን ጆሮ ይደፈንና) ውጤቱ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገርን ማጣት ነው የሚሆነው።  ይኼን ቦንብ ይዘን እንድንኖር የተደረገው በግንቦት 20 በተገኘ ድል ነው። ስለዚህ ሃገር ወደብ አልባ የሆነችውና  የሆነ ወቅት ሊፈነዳ የሚችል አንቀፅ 39 የሚባል ቦንብ የተቀበረው በግንቦት 20 ነው።

ኢህአዴግ ባለፉት 25 ዓመታት የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓቱን ከማጠናከር ይልቅ እያዳከመው የመጣበት ሁኔታ ይታያል። ኢህአዴግ የስልጣኑ የመጀመሪያው ዓመታት ማለትም በሽግግሩ ወቅት በአንፃራዊነት የተሻለ የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ሰርዓት የተስተዋለበትን ሂደት ያሳየበት ነበር። በዚያ በሽግግር መንግስቱ ግዜ ም/ፕሬዘዳንት እና ትምህርት ሚኒስቴርን የመሳሰሉ ተቋማትን ለተቃዋሚ ፓርቲ ያጋራበት ወቅት ነበር። ከዚህ በ1987 በተደረገው ምርጫ የተቃዋሚው ቁጥር እየቀነሰ የመጣበት ሁኔታ ተፈጠረ። በ1997 የተሻለ የፖለቲካ መነቃቃት የተፈጠረበትና በግዜው የነበረው ቅንጅትም ከ170 በላይ የፓርላማ መቀመጫ በምርጫ ያገኘበት እና አዲስ አበባን ያሸነፈበት ታሪካዊ አጋጣሚ ተፈጥሮ የነበረበት ነው።  ሆኖም በቅንጅቱ መሪዎች ታሪካዊ ስህተት ያንን ታሪካዊ አጋጣሚ ሳንጠቀምበት አልፎናል። በዚህም በአጠቃላይ እንደ ትውልድ የወደቅንበት ፈተና ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።

ይኸው ከዛ በኋላ የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓቱ መገለጫ የሆነው የምርጫ ስርዓታችን በኢህአዴግ የ2007 ምርጫ የ100% አሸናፊነት ደረጃ ደርሶ በግንቦት 20 ማግስት የአንድ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ ወድቀናል። በዚህም በአፍ ብቻ እንጂ በተግባር የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት በ25ኛ ዓመት የግንቦት 20 ድል ዋዜማ ላይ የውሃ ሽታ ሆኗል። ዛሬም የፖለቲካ ፓርቲዎች ይዋከባሉ፣ በተለያዩ አፋኝ ሕጐች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ ይታሰራሉ፣ ዛሬም ሃሣብን በነፃነት የመግለፅ መብት እየተሸራረፈ ይገኛል። ስለዚህ ያጣነው ነገር ለኔ በዝቶብኛል ካገኘነው ይልቅ።

ሌላው ኢኮኖሚው አሁንም መዋቅራዊ ለውጥ ስላላደረገ የአለም ጭራ እንደሆንን ነው። ዛሬም የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ዜጐች በሕገ-ወጥ መንገድ እየተሰደዱ ውሃ እየበላቸው ነው። በከተሞች አካባቢ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ትንሽ መነቃቃት እንዳለ እሙን ቢሆንም በከተሞች የኑሮ ውድነቱ ጣራ ነክቷል። አሁንም የውሃ የመብራት አቅርቦት እጥረት ከፍተኛ በመሆኑ ኢኮኖሚው ላይ የራሱን ተፅዕኖ እያሳረፈ ነው። ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር ሳያደርግ አሁንም የመንግስት አስትራቴጂ ግብርናና ገጠርን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ ዘላቂና አስተማማኝ ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም።

ኢህአዴግ ባለፉት 10 ዓመታት ገበሬው የተሻለ ዝናብ በማግኘቱ በኢኮኖሚው ላይ ትንሽ መነቃቃት ታይቶ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ግብርናው የተሻለ ዝናብ በማግኘቱ የታየው የኢኮኖሚ ዕድገት ዝናቡ ቀጥ ሲል ተረት ከመሆን አያልፍም። በቅርቡ የተከሰተውም የዝናብ እጥረት የሚያሳየን ይሄን ነው። ግብርናው እና ገበሬው አሁንም የዝናብ ጠባቂ በመሆኑ ከ13ሚሊዩን ሕዝብ በላይ በረሃብ ተጠቅቷል። ዛሬም መንግስታችን እንዳለፉት መሪዎች አቁማዳ ይዞ ምዕራባውያንን ስንዴ በመለመን ላይ ነው። ዛሬም በግቦት 20 ድል ዋዜማ የልመና አሳፋሪ ታሪካችን ቀጣይ ሆኗል።

ኢህአዴግ መሬት የመንግስትና የህዝብ የሚለው ድርጅታዊ አቋሙን ህገ-መንግስታዊ ያደረገበት ተገቢ ያልሆነ እርምጃ ነው። ይሄንን በሃገራችን የፖለቲካ ልሂቃን ከፍተኛ የልዩነት ምንጭ  የሆነው መሬት ህገ መንግስታዊ መሆኑ ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው። መንግስት መሬት የመንግስትና የህዝብ ብሎ ደንግጎ አሱ ግን በጨረታ በብዙ ሚሊዮን ብር እየቆነጠረ ሲቸበችብ ይታያል። መሬት በመንግስት እጅ በመሆኑ በኢኮኖሚውና በገበሬው ምርታማነት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖም ቀላል አይደለም። በተጨማሪም በሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ መሬትን የመንግስትም የግልም ብቻ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ የለም የሚል እምነት ነው ያለኝ። አርብቶ አደሩ ጋር መሬትን የመንግስትም የግልም አድርጎ ማህበራዊም ፖለቲካዊም መረጋጋት ማምጣት አይቻልም። በከተማው ነዋሪና በገበሬው እጅ የሚገኘውን መሬትም እንደዚሁ የመንግስት ማድረግ ተገቢነት የለውም። እንደዚሁም ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የማዕድንና ቦታዎችንና ጠፍ መሬቶችን በመንግስት ከማስተዳደር ውጭ የተሻለ አማራጭ ያለ አይመስለኝም። ስለዚህ ለሃገራችን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት መሬት ከመንግስት እጅ ወጥቶ በአዲስ  አይነት ስሪት መከፋፈል አለበት። ማለትም በመንግስት፣ በግልና በወል በሚል። ይሄም ለሃገራችን ዘላቂ እድገት ቁልፍ የመሬት ፖሊሲ ነው የሚል እምነት አለኝ። እንግዲህ የኢህአዴግ 25ኛአመት የሚከበረው መሬትን እንደ ደርግ ከህዝብ ሃብትነት አላቆ የመንግስት ጭሰኛ ባደረገ ስርዓት ውስጥ ሆነን ነው።    

ሌላው በኢኮኖሚው ውስጥ ያለ ችግር የነፃ ገበያ ስርዓቱ በመንግስቱ ገደብ የለሽ ጣልቃ ገብነት አደጋ ውስጥ መውደቁ ነው። መንግስት የግሉ ዘርፍ በቂ ተሳትፎ ማድረግ በሚችልበት ዘርፍ ውስጥ ሳይቀር እየገባ ኢኮኖሚው ላይ ተሳትፎ እያደረገ ነው። በተለይም በአሁኑ ወቅት የመከላከያው ለከት የለሽ ጣልቃ ገብነት የግል ባለሃብቱን ስጋት ውስጥ እየጣለው ነው። መከላከያ የመኪና ቦዲ ቅጥቀጣ፣ የእርሻ፣ የመንገድ ሥራ፣ የሆቴል ንግድ ውስጥ ሁሉ ያለ ጨረታ እና በጨረታ እየገባ የግል ባለሃብቱና ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ስጋት እንደደቀነ ነው ግንቦት 20 የሚከበረው። የዚህ የመከላከያ በኢኮኖሚው ያለው ጣልቃ ገብነት ኢኮኖሚያዊ ችግር ብቻ ሆኖ የሚቀር ሳይሆን ፖለቲካዊም ይሆናል የሚል ስጋት አለኝ። ከዚህ ከኢኮኖሚው ጉዳይ ሳንወጣ በኢህአዴግ ጉዳዬ ያልተባለ ነገር ግን ከፍተኛ እድገት እያሳያ ያለው የህዝብ ብዛት ነው። የቤተሰብ ምጣኔ ተገቢ ትኩረት የተነፈገው ጉዳይ በመሆኑ ኢኮኖሚው ላይ የራሱን ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።

በመጨረሻ በዚህ 25 አመታት ከዕለት ወደ ዕለት እያደገና አስፈሪ እየሆነ የመጣው ሙስና ነው። የሃገራችን ሙስና ከቢሮክራሲው ጋር አንድ አካል አንድ አምሳል የመሆን ደረጃ ላይ ደርሷል። በብዙ ቦታዎች ሙስና የሚፈጸመው ሰው አየኝ አላየኝ ተብሎ መሆኑ ቀርቶ ተመን ወጥቶለት በአደባባይና በጠራራ ጸሃይ እየሆነ ነው። ህብረተሳባችንም ሙስናን የሚጠየፍ ሳይሆን “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” እያለ ልጆቹ ከዩንቨርሲቲ ተመርቀው ጉምሩክና ገቢዎች ሲመደቡ ጮቤ የሚረግጥ አስተማሪና ጉቦ ሊበላ የማይችልበት ቦታ ሲመደቡ የሚያለቅስና የሚያዝንበት ዘመን የፈጠረው ግንቦት 20 ነው። ግለሰቦች በአንድ ጀንበር ሚሊየነር የሚሆኑባት የጉድ ሃገር እየሆነች ነው። አዲስ አበባ ቁጭ ብለው የአውሮፓና የአሜሪካ  ኑሮ የሚኖሩ በተለየ ስርአቱ የፈጠራቸው ግለሰቦች የሚኖሩባት ሀገር እየፈጠርን ነው። ይሄ የሙስና አደጋ በባለፉት ስርአቶች አሳፋሪ ተግባር የነበረ ቢሆንም በኢህአዴግ መንግስት ግን የስርአቱ መገለጫ እየሆነ ነው። ስለዚህ በግንቦት 20 ድል በ10 ሺዎች የነበረው ሙስና ወደ ሚሊዮኖች ያደገበት ነው።  

በአጠቃላይ 25ኛ ዓመት የግንቦት 20 ድል እየተከበረ ያለው በኔ እምነት አንድ ዜጋ በሕገ-መንግስቱ በቡድን ካልሆነ በግሉ ኢትዮጵያዊነቱን ያላረጋገጠበት፣ የሃገራችን ፌዴራሊዝም አሁንም ልዩነታችን እየተራገበ ለህልውናችን ስጋት የሆነበት፣ የመገንጠል መብት በሕገ-መንግስቱ ሠፍሮ ከዛሬ ነገ የመገንጠል አደጋ ላለመፈጠሩ እርግጠኛ ያልሆንበት፣ አሁንም ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር ማድረግ ባለመቻሉ በድህነትና በርሃብ የምትታወቅ ሃገር ይዘን የቀጠልንበት፣ መድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአትና የምርጫ ስርአቱ አደጋ ውስጥ የወደቁበት፣ ሙስና መረን የወጣበትና በመሬት ፖሊሲው ምክንያት ሕዝቡ የመንግስት ጭሰኛ ሆኖ የቀጠለበት ወቅት ላይ ሆነን ነው ግንቦት 20 እየተከበረ ያለው። ስለዚህ የግንቦት 20 ድል ዛሬም 25ኛ ዓመቱን የሚያከብረው ከነብዙ እንከኖቹ ነው። ኢህአዴግ ከዚህ በላይ ሊጠቀሱ የሚችሉ እንደስርአት ብዙ ችግሮች ያሉበት ፓርቲ ነው። ያ ሁሉ ቢጻፍ መጽሃፍ ነው የሚወጣው። ግን ዋና ዋናውን ለመጥቀስ ነው የሞከርኩት። ቸር እንሰንብት። ይህ ፅሁፍ የግል አቋሜን የሚያንፀባርቅ ነው።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
602 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 841 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us