አካኪኖስ ደረጃ የተሰጣቸው አፍሪካዊያኑ ሰብአዊያን

Wednesday, 01 June 2016 12:25

 

ወሰንሰገድ መሸሻ በላቸው / This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. /

የሰው ልጅ ጊዜ አልፎ ጊዜ በተተካ ቁጥር በሰዎች መካከል ደረጃ እያበጀ እርከን እየሰራ መንቀሳቀስ በመሻቱና አንጎሉ ላይ በታየው የአስተሳሰብ ለውጥ:- ሰው፣ ሰባሰብ፣ አካኪኖስ የሚሉ ልዩ የሰዎች መለኪያ የደረጃ መስፈርቶችን አውጥቶ - ዋናና ምርጥ ብሎ የፈረጃቸውን ሰው፣ ከሰው በታች ናቸው ብሎ በመካከለኛ ደረጃ የሰየማቸውን ሰባሰብ፣ ተራና ከብቶች ብሎ የፈረጃቸውን ከሰው ተራ የወረዱና ከሰባሰብ ደረጃም በጣም ዝቅ ያሉ ናቸው ብሎ ያዘቀጣቸውን አካኪኖስ ብሎ ከሰውነት ተራ አውርዶ ለያይቶ አኗኗራቸውንና ስፍራቸውን ለየ።

ሰው በከሳቴ ብርሃን ተሰማ አማርኛ መዝገበ ቃላት ሰባት የተፈጥሮ ባሕርያት እንዳሉትና በሥጋ አራት በነፍስ ሶስት ባሕርያት ያሉት መሆኑን 4ቱ ሥጋ/ ነፋስ፣ እሳት፣ ውኃና መሬት 3ቱ ደግሞ ነፍስ/ ተናጋሪነት፣ ዐዋቂነትና ሕያውነት መሆናቸውንና ሰውነትን ደግሞ በሰውነት/አካልና እውቀት መገኘት፣ ሰባቱን ባሕርያት አስማምቶ ሰው መባል፣ በቂ አካልና እውቀትን ይዞ መገኘትና የሰው ልጅ መባል ነው ካለ በኋላ የሰው ልጅ ማለት ከከበርቴዎች፣ ከታላላቅ ወገኖች የተወለደ የጨዋ ልጅ የሰው ልጅ ይባላል የሚል ሌላ ፍች ሰጥቶት ይገኛል።

በማርክሳዊ ሌኒናዊ መዝገበ ቃላትም በሥነ ሕይወታዊ አመለካከት ሰው የተፈጥሮ እድገት ከፍተኛው ውጤት መሆኑን፣ ሰው ከዳበሩ እንስሳዎች የሚለየው በማሰብና በንግግር ችሎታው መሆኑን፣ እንስሶች በአካባቢያቸው ላይ ያላቸው ክንዋኔ በደመነፍስ የሚወሰን መሆኑንና የሰው ክንዋኔ ግን የሚወሰነው በስሜቶቹ፣ በፍላጎቶቹና በፈቃዱ መሆኑን እንዲሁም ሰው ስለ ተፈጥሮና ስለኅብረተሰብ ሕግጋት ባለው የእውቀት ደረጃ ነው ይለዋል። ሰብእን ደግሞ ነፍስና ሥጋ ያለው ነፍሱ ከሥጋው አንድ የሆነ ሥጋ ብቻ ወይም ነፍስ ብቻ ያልሆነ ብሎት ሰብን ተፈጥሮ ካስገኛቸው እውነታዎች ሁሉ የተለየ ቦታ ሚና ችሎታና ክብር ያለው ፍጡር ነው ብሎ ገልፆታል።

ሰው የእንሰሳ አንዱ ክፍል መሆኑን መካድ አንችልም። የሰው ልዩ ተፈጥሮ /uniqueness/ የሚመሰረተው ከማንኛውም እንስሳ ጋር በማይጋራቸው ባሕሪያቶቹ ላይ ተመስርቶ ነው። እንስሳት ሁሉ እራሳቸውን እንደ አካባቢያቸው የሚለውጡ ብቻ ሲሆኑ ሰው ግን አካባቢውን ከፍላጎቱ ጋር በሚጣጣም መንገድ እንደዕውቀቱና ችሎታው የመለወጥ ብቃት ያለው ፍጡር ነው።

አየሩን እየተንሳፈፈም እየበረረም ተቆጣጥሮታል፣ ውሃውን እንዳሻው ሰርቶበታል ጥልቅ ገብቶ ሐብቱን አሟጦታል፣ የምድርን ሆድ ዕቃ በርብሮታል። ቁልቁል ምሶ ሐብቱን አጋብሶታል፣ ጨረቃ ድረስ መጥቆ ያሻውን በማድረግ ከእግዜሩ ቀርቦ እየተቀጣጠበው ይገኛል።

ዝቅ ብለን ስለሰውና ስለምድር የምናነሳ ቢሆንም ሰው ስለደፈረው ሰማይ ጥቂት  ብንልስ። እግዚአብሔር በመጀሪያው ቀን ሰማይን እንደፈጠረ፣ ከበላያችን ከምናየው ሰማይ በላይ ሌሎች ሰማይን እንደምናገኝ፣ ከበላያችን ከምናየው ሰማይና በላይኛው ሰማይ መካከል ጣሪያ እንዳለ፣ ከጣሪያው በላይ ውሃ መልበሱ፣ የሁለቱ ሰማያት አወቃቀር እንድባለሁለት ፎቅ ቤት መሆኑን፣ ከበላያችን የምናየው የታችኛው ሰማይ የተፈጠረው በሚቀጥለው ቀን መሆኑንና እንደብርሌያማ የጓጎለ ውሃ ሆኖ ከፀሐይ ከጨረቃና ሁልቆ መሳፍርት ከሌላቸው ከዋክብት የመጣውን የእሳት ነበልባል ሳይሟሟና ሳይቃጠል የሚቋቋምና ይህ ውሃም በዓለም መጨረሻ ቀን የፀሐይን የጨረቃንና የከዋክብቱን እሳት ለማጥፋት እንዲያገለግል ሆኖ መፈጠሩን የጋባላ አቡን አቡነ ሲቨሪያንስ በአለም አፈጣጠር ላይ ስድስት ዲስኩሮች በሚለው መፀሐፋቸው ገልፀዋል። 

ቤንጃሚን ፍራንክሊን አንድ ወቅት ሰው መሳሪያን የሚፈጥር እንሰሳ ነው ብሎ ነበር። በእርግጥም ንቁ ሆኖ መሳሪያዎችን መጠቀምና ለዓላማው እንዲያመቹ አድርጎ መሳሪያዎቹን መፍጠር ብቸኛ የሰው ልጅ ዋና ፀባዩ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል።

ሆኖም የተፈጥሮ ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት ቺምፓንዚ በመርፌ ቀዳዳ ውስጥ ክር ሲያስገባ መታየቱን፣ እንዳይደረስበት ተደርጎ የተሰቀለን ሙዝ ዱላን በመጠቀም ሙዙን አውርዶ መብላቱን፣ ጋሻና ጦርን በአደጋ ጊዜ እራሱን ለመከላከል መጠቀሙን፣ ቀለቡን በመያዣ ውስጥ ከትቶ ወደፈለገበት ማጓጓዙን፣ በአለንጋ መሳይ እንጨት በመጠቀም ከኩይሳ ውስጥ ጉንዳኖችን እያወጣ መመገቡን፣ በድንጋይ ጠጣር ፍሬዎችን በመስበር መመገቡን በማስረጃ አስደግፈው ስላቀረቡ የሰው ችሎታ ብቻ አይደለም ለማለት ዳድተዋል።

በሌላ በኩል በሰውና በእንስሳት መካከል ካሉት ልዩነቶች አንዱ እንስሳት መሳሪያዎችን የሚጠቀሙት መሳሪያው አጠገባቸው እስካለ ብቻ መሆኑንና መሳሪያው ካጠገባቸው ከተወገደ ግንዛቤው ፈፅሞ የሌላቸውና መሳሪያው ከእይታቸው ውጭ ከሆነ ልምዱና ሐሳቡ ስለማይኖራቸውና ነገሩ ከአእምሮአቸው ውጭ እንደሚሆን  አረጋግጠው ሰው ግን መሳሪያው ባጠገቡ ባይኖር እንኳን ልምዱና ሐሳቡ ከእርሱ ጋር ስላሉ የነኝህ ነገሮች ምስል በአእምሮው ይቀረፃል ብለው ንፅፅሩን አጉልተው አመላክተዋል።

ይህንንም በምሳሌ ሲያስረዱ አንድ እንስሳ የልጁ እሬሳ አጠገቡ እስካለ ድረስ ሐዘኑ ይታይበታል እንጅ ሬሳው ካጠገቡ ከተወገደ በኋላ ሀዘኑም ሐሳቡም ከበድኑ ጋር አብሮ ይሄዳል ወይም የጠፋበታል ትዝታ አይኖረውም ብለዋል። ሰው ግን ከቀበረም በኋላ በየጊዜው እለቱን ሰዓቱን ሳይቀር እያሰበ ሲዘክርና ከሟቹ ጋር ንክኪ ያላቸው አንዳንድ ነገሮች፣ ኩነቶችና ቦታዎችን ባየና በሰማ ቁጥር ለብዙ ዓመታት እያሰበና በትዝታ እያስታወሰ ይታያል ብለው አነፃፅረው ገልፀውታል።

የጥንት ሰው ታሪክ ጥናት በሁለት አብይ ክፍሎች ማለትም በፕራይማቶሎጂና በፖሊዮአንትሮፖሎጂ ተመድቦ ተፈትlል። ፕራይማቶሎጂ በአሁኑ ጊዜ የሚገኙ የሰው የቅርብ ዝርያዎች ላይ ሲሆን ፖሊዮአንትሮፖሎጂ ደግሞ የእነኝሁ የሰው የቅርብ ዝርያዎችንና የሰውንም ጭምር አመጣጣቸውን በተጨባጭ በሚያስረዳን በቅሪተ አካል/ በፎሲል/ ጥናት ላይ ተመስርቶ የሚካሄድ ነው።

ሰው ከ24ቱ የተለያዩ የአጥቢ እንስሳት/ማማልስ/ ክፍሎች ውስጥ አንዱ በሆነው ፕራይሜትስ በተባለው የእንስሳት ክፍል የሚመደብ ነው። ከፕራይሜትስ መሃል በተለይ ለሰው የሚቀርቡት ሆሞኖይዲዩ የተባለው ክፍል ውስጥ የሚገኙት ጎሬላ፣ ቺምፓንዚና ኦራንጉታን በተለይ በሰው መሰል አቋማቸው ይመሳሰላሉ። እነዚህ ፕራይሜትስ ዝርያዎች  በምድር ወገብ አካባቢ የነበሩ የጥንት ደኖች ይኖሩ የነበሩ እንስሳት ሲሆኑ ቀስ በቀስ ወደ ገላጣ መሬት እያመሩ የኖሩ በመሆናቸው የእነዚህን ፕራይሜቶች ፀባይ በሁለት ዋናዋና ክፍሎች አጠቃለዋቸዋል።

1ኛ. የእጅና የእግር ጣቶች ዞሮ መግጠም፣ ይህም በተለይ በሰው ደረጃ ቁሳቁሱን በእጅ ለማገላበጥና እጅም የማራመጃ ብልትነቱ እየቀረ እንደመጣ፣ ከማሽተት ይልቅ የማየት ሕዋስ እንደዳበረ፣  የአንጎል መጠን ከሌሎች እንስሳት ሲወዳደር የጨመረ መሆኑ፣

2ኛ. ፕራይሜቶች በተለይ የሚያሳዩት በሰውና በመሰሎች የዳበረ ፀባይ የልጅ አወላለድ ፀባያቸው  መሆኑንና የልጆችን ቁጥር ለመቀነስና ሕፃኑም በወላጅ ላይ ተደጋፊነት የሚሆንበት ዘመን መርዘሙ፣ ሕፃኑ ሙሉ ዕድሜ ከመሆኑ በፊት ማከማቸት ካለበት የሶሻል መረጃዎች ጋር መያያዙ፣  ፕራይሜቶችና በተለይም ሰው በኅብረት የሚኖሩ እንስሳት መሆናቸው ነው።

የፕራይሜትስ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ፕሮሲይሚን አይጥ መሰሎቹን፣ አንትሮፖይዲዩ ደግሞ ሰው መሰሎቹን የለየበት ሲሆን አንትሮፖይዲዩ በአሜሪካ ክ/ዓለም የሚገኙትን ፕላተሪኒን፣ በአፍሪካና በእስያ የሚገኙትን ደግሞ ካተሪንን በሚል አጠቃሏቸዋል።

እ.ኤ.አ. በ1859 ቻርለስ ዳርዊንም ለሥነ ሕይወት ጥናት ካደረገው ታላቅ አስተዋፅኦ ከአዝጋሚ ለውጥ ፅንሰ ሐሳብ ሌላ የሰው ልጅ በአፍሪካ ከሚገኙት ፕራይሜትስ ዝርያዎች የቅርብ ግንኙነት እንዳለውና ስለጥንት ሰውም ታሪክ ለማረጋገጥ አፍሪካ ውስጥ መረጃን መሻት እንደሚገባ ጠቁሞ ሰው የሚመደበው ከአፍሪካዎቹ ካተሪን መሐል እንደሆነም በትንበያው አስገንዘቧል።

በተፈጥሮ ኬሚካሎች ጥናት የሰውንና የቺምፓንዚን ኬሚካሎች በማወዳደር ሰውና ፓንጊዴ ከ8-6 ሚሊዮን ዓመት በፊት የጋራ ዘር እንደነበራቸው ያረጋገጡና ቺምፓንዚዎች የደን እንስሳት ሆነው ሲቀሩ ሰዎች ግን ወደ ገላጣ ስፍራ መንቀሳቀሳቸውን የጥናት ሰነዶች ያብራራሉ። የደን ምንጠራ መነሻውም ከዚህ እንደሚመነጭ ልብ ይበሉ።

ፕራይማቶሎጂ ፖሊዮ አንትሮፖሎጂ፣ የመጀመሪያው የተረጋገጠ ሰው መሰል አውስትራሎፒቲክስ፣ የአውስትራሎፒቲሰን የሰውነት ቅርፅና የኑሮ ዘዴ፣ የሰው የቅርብ ዝርያዎች ጂንስ ሆሞ አባሎች፣ የድንጋይ መሣሪያዎችን መጠቀም - የሥራ ክፍፍል በማኅበራዊ ኑሮ- የቋንቋ ችሎታ- ለአካባቢው የሰውን ባሕርይ የሚያረኩ ትርጉሞች ለመስጠት የሚደረጉ አምልኮ መሰል ባሕርዮች-፣ የጂንስ ሆሞ አባሎች የሰውነት ቅርፅ፣ ዘመናዊው ሰው በሚል እየተለዩ በጥናቱ በዝርዝር ተፈትሸዋል፣ ተተንትነዋል።

የጥንት ሰዎች በአካባቢያቸው ከሚገኙት እንስሳትና አራዊት ጋር ባላቸው ጉልበት መጠን ሲወዳደሩ በጣም ደካሞች ነበሩ። የጥንት ሰዎች ኑሮአቸውን ያሸንፉ የነበሩት ተፈጥሮ ያደለቻቸውን ፍራፍሬዎች በመልቀምና በአካባቢያቸው የሚገኙትን አንዳንድ የዱር እንስሳት በማደን የእለት ጉርሳቸውን፣ ልብሳቸውን መጠለያቸውን፣ የቁሳቁሶቹ ምንጮቻቸው አድርገው የተጠቀሙት የተፈጥሮ ኃይላቸውን የሚያጎሉላቸው መሳሪያዎችና ሌሎች መከወኛዎችን በመስራት ነበር።

የጥንት ታሪክ በሰዎች የአኗኗር ሁኔታና በቴክኖሎጂ እድገት ደረጃ በሶስት ክፍላተ ዘመን ሲከፈል ቀደምት የድንጋይ ዘመን፣ መካከለኛው የድንጋይ ዘመን፣ አዲሱ የድንጋይ ዘመንና የግብርና መጀመር ተብለው ነው።

የብረታ ብረት ሥራ መጀመር፣ ማረሻ ጋሪና የጭነት ማቀናጃ፣ የመጀመሪያዎቹ የስልጣኔ ዘመናት፣ ማኅበራዊ ለውጥ፣ የነሐስ ዘመን ስልጣኔ፣ የብረት ዘመን ስልጣኔ፣ የአቴና ዲሞክራሲና የግሪክ ስልጣኔ፣ ጦርነትና ባርነት፣ መካከለኛው ክፍለ ዘመን፣ የተፈጥሮን የኃይል ምንጭን ስራ ላይ ማዋል፣ የውሃ ሽክርክር፣ የነፋስ ኃይል አሽከርካሪ፣ የተሻሻሉ የእንስሳት ማቀናጃዎች፣ የትራንስፖርት መሻሻል፣ ግብርናና የጨርቃጨርቅ ስራ፣ ወረቀትና የሕትመት ስራ፣ ልዩ ልዩ የፈጠራ ስራዎች ሜካኒካዊ እቃዎች መከወኛዎችና መቀላጠፊያዎች፣ የኢንዱስትሪ አብዮት ዋዜማና ኩነቱ፣ የሽመና ቴክኖሎጂ መሻሻልና መስፋፋት፣ ማዕድን ሜታለርጂና ከባድ የምህንድስና ስራዎች፣ አዳዲስ የኃይል ምንጮችን መፈለግ፣ የልኬት መሳሪያዎች፣ የእንፋሎት ሞተርና የእንፋሎት ኃይል ስራ ላይ በማዋል መኪና ባቡር መርከብ፣ በውስጠ ቃጠሎ ሞተር ነገሮችን ማሻሻል፣ በአየር ላይ መጓጓዣ መፍጠር የኤሌክትሪክ ኃይልና የኤሌክትሪክ መሳሪያዎችን ማምረትና መብራት ማግኘት፣ ቴሌግራፍና ቴሌፎን፣ የራድዮ መገናኛና ሌሎች ኑሮን የሚያግዙ ድካምን የሚያቃልሉ ጊዜን የሚቆጥቡ ወደተሻለ የአኗኗር ሁኔታ የሚቀይሩ ክንውኖችን በየፈርጁ ማስተናገድ በመቻሉ በሰዎች መካከል ክፍተትና ሰፊ ልዩነት በመፈጠሩ ሰዎች ለራሳቸው በራሳቸው ደረጃ ተበጀላቸው።

ያንን ሰው ሰራሽ ደረጃ በቀላሉ የሚወጡትን ሰብ፣ እየተንገዳገዱም ሆነ እየተቸገሩ ተንፏቀውም ቢሆን ደረጃው ላይ የወጡትን ሰባሰብ በሚል በመካከለኛ ሰብእ ሲፈረጁ፣ የተዘጋጀው ደረጃ ላይ መውጣት ያልቻሉትንና ደረጃውን ባሉበት ተጎልተው ሽቅብ የሚያዩትን ሰነፎች ደደቦች ዳተኞችና ልምዝምዞች በሚል ፈርጀው አካኪኖስ /ተራ ሰብእ/ ከእንስሳቶቹ የማይለዩ ከብቶች ተብለው ከሰው ተራ አስወጧቸው። እኒህ አካኪኖስ ተብለው የተፈረጁት አፍሪካውያኑ በሙሉና አፍሪካውያኑ ናቸው።

እንስሳት ግንዛቤ እንደለላቸው ከላይ ገልፀናል እውቀት ልምድና ችሎታንም ከትውልድ ወደ ትውልድ የማስተላለፍ ብቃትም የላቸውም ሆኖም አስመስሎ የማድረግ /ኢሚቴሽን/ እውቀት ነው ያላቸው። ቢሆንም የራሳቸው በናኝ ግንዛቤ የተግባር ውጤታቸው አይደለም። በመስተዋት ፊት ሲኮን ብቻ እንደሚታይ ምስል ወይም እንደገደል ማሚቱ ያለውን መልሰው የሚሉ እንጅ የተቀበሉትን አሻሽለውና ሕይወት ሰጥተው የሚገለገሉ አይደሉምና አካኪኖሳውያኑ አፍሪካውያን በጥንተ ሰው ዘመን ባለው እንስሳነታቸው ከቺንፓዚዎቹ እንኳን ሳይበልጡ ለዝንተዓለም የኖሩና ለዘለዓለምም በዚሁ ሁኔታቸው የሚኖሩ ናቸው ብለው ፈርጀውን ደምድመዋል።

በእርግጥም ከነሱ የተሰጠንን መርዝም ቢሆን በመሻመት እየተስገበገብን ከለኩልን መጠን በላይ በብዙ አብልጠን  እየተጋትን እንገኛለን። እንስሳት ሥነ ምግባር ኃይማኖት የኃላፊነት ስሜትና ሥልጣኔ የላቸውም። ይህ ሁኔታም ባብዝሃኛው በአፍሪካውያን ላይ በገሃድ እየታየ ነው። እያጣሉን  ተጣዮቹ እኛ በሁለት ወገን እርስበርሳችን ተፋጠን ለምንተጋተግበት መሳሪያ በገፍ እየሸጡልን መልሰን እነሱው እንዲዳኙን እንዲፈርዱብንና ፍትሕ እንዲሰጡን እንንበረክላቸዋለን።

ከእንስሳት ምድብ የተሰፈረው ሰው በቆዳ በቀለምና በልዩ ልዩ ዘሮች/ሬስስ/ በአንዳንድ አካላዊ ገፅታዎች የሚለያይ ቢሆንም አሁን እየኖረ ያለው የሰው ዘር ሆሞ ሳፒያንስ በተባለ አንድ ዝርያ ስር ተጠቃሎ የተጠና ነው።

በመልክአምድራዊ፣ በቀለም፣ በማኅበራዊ፣ በኃይማኖትና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች በተለያዩ የሰው ዘሮችና ጎሳዎች ተሰነጣጥሮ እንዳሰፋፈሩና ለዘመናት እንዳኗኗሩ ልይይት ቢፈጥርም ሰው በአንድ ዝርያ ውስጥ የሚጠቃለልበት ምክንያት አንዱ ዘር ከሌላው ዘር ፆታዊ ግንኙነት እንዳይፈፅምና እንዳይራባ የሚያደርግ አንድም ስነሕይወታዊ የሆነ አጋጅ ነገር ባለመኖሩ ነው። /ባሕል ኃይማኖትና ሌሎች እምነቶች ከጎሳቸው ውጭ ፆታዊ ግንኙነት እንዳይፈጥሩ ከማገዳቸው ውጭ/

ተፈጥሮአዊና ነፃ በሆነ መንገድ ምንም ዓይነት ሥነ ሕይወታዊ የመርቦ እገዳ በመካከላቸው ሳይኖር እርስበርስ የሚራቡ ወይም ዓይነታቸውን የሚወልዱ የእንስሳት ወይም የእፅዋት ስብስብ /ቡድን/ ዝርያ ስለሚባል በዚህም አተያይ ማየት እንችላለን።

ከ3.7 ቢሊዮን ዓመታት በፊትና ከዚያም በኋላ ለጥቂት አመታት የነበረው አየር /አትሞስፌር/ ያዘላቸው ዋና ዋና ጋዞች ናይትሮጂንና ካርበንዳይኦክሳይድን ነበር። አየቆየ በብዛት ሲፈነዱ በኖሩት እሳተ ገሞራዎች/ቮልካኖስ/ የሚወጡት ጋዞች የናይትሮጂንና የካርበንዳይኦክሳይድን ይዘት በብዛት ጨመሩት፣ ከእነዚህ ጋዞች ጋር የተፈጠረው እንፋሎት ወደውሃነት እየተለወጠ ውቅያኖሶች ስፋትና ጥልቀታቸው ሲጨምር ካርበንዳይኦክሳይድ በአየር ግንባታ በማገልገል ከድንጋዮች አፈሮችና ማእድናት ጋር በመዋሃድ ከአየር ውስጥ ብዛቱን ቀነሰ።

በዚህ ሳቢያም ከጊዜ ወደጊዜ የናይትሮጂን መጠኑ እየጨመረ የካርበንዳይኦክሳይዱ መጠን በብዛት እየቀነሰ በመሄዱ ከ3.2 ቢሊዮን ዓመት በፊት ጀምሮ እስከ 1.8 ቢሊዮን ዓመት በፊት ድረስ በውቅያኖስ ውስጥ በብዛት ይኖሩ የነበሩ ሕዋሳት ካርበንዳይኦክሳይድንና የፀሐይን ጨረር በመጠቀም እንደ ስኳር ያሉ ነገሮችን በመሥራት ኦክስጂን ማመንጨትና በውቅያኖሶችና በሌሎች የውሃ ጥርቅሞች ውስጥ በብዛት መድረስ ጀመረ። በዚህም ሳቢያ እፅዋትና እንስሳት ከውሃ ውጭም በመሬት ላይ መስፋፋት ቻሉ። የሰው ዝርያም የሚስበው ኦክስጅን በማግኘቱ ምድሪቱን ሞላት።

ምድር አንድ መቶ ሚሊዮን ከሚሆኑ /የፍኖተ ሀሊብ ጋላሲ/ ከዋክብት መካከል በአንደኛዋ ዙሪያ የምትሽከረከር አንድ ፈለክ ናት። ምድር ሕይወታዊ እስትንፋስ ሰጪ ከሆነው የአየሯ ይዘትና ፀባይ ሌላ የቅርብ ጊዜ የሳይንስ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ሰዎች በብዛትና ሙሉ በሙሉ ማለት  በሚቻልበት ሁኔታ ምድራዊ ሐብትንና የደረሰባቸውን ሌሎች የፍኖተ ሀሊብ ጋላሲ ሐብትን ጭምር  ተቆጣጥሮ ለራሱ ጥቅም እያዋለውና በልጦ ለመገኘት እየተጣደፈ ይገኛል።

በየጎሳቸው ከሚያደርጉት ሐብትን የመቆጣጠር ቅጥ የለሽ እንቅስቃሴያቸው ባሻገር ግለሰቦች ከጎሳቸው ከጎረቤቶቻቸው ከዘመድ አዝማዶቻቸው ልቀው ለመገኘት ሐብትንና ኃይልን ሊያካብቱ ሲፍጨረጨሩ ደረጃ አበጅተው ሌላውን የበታቻቸው በማድረግ ባሪያ አድርጎ እስከመግዛትና እንደከብት እስከመንዳት ዘልቀው አበላልጠውበታል። መንግስታት ከመንግስታት ጋር በሐብትና ጥቅም ፍለጋ በተናጥል ጦርነት አካሂደዋል። የተወሰኑ መንግስታትም በሚያስተሳስራቸው የጋራ ጥቅም ባንድ ወገን ሆነው ሌሎች መንግስታትን ተቧድነው ወግተዋል።

ከ2.5 ሚሊዮን አመታት በፊት ስለታም ድንጋይን በማዘጋጀት እንስሳትን ለማረድና ለመያዝ አመቺ የሆነ መጥረቢያ የሚመስል የሰራው የድንጋይ ቴክኖሎጂ ከተጀመረ አንድ ሚሊዮን ዓመት በኋላ ቢሆንም የበላይነትን ለመቀዳጃነት ተገልግሎበታል። እሳት በተገኘበት ዘመንም ለሰው ዝርያ ታላቅና አዲስ ግኝት ከመሆኑም በላይ ከተቀናቃኝ እንስሶች የበላይነቱን ስላቀዳጀው በመንጋ ሊጎዱት የመጡትን ሁሩ አባሮበታል፣ እያስፈራራ እንደፈለገ ሊነዳቸው አስችሎታል። የሰው ልጅ እሳትን የፈጠረው ቀጥ ብሎ መሄድ ባልጀመረበትና እንሰሳነቱ ባመዘነበት በጥንት ዘመን ስለነበርም ለስልጣኔው በር ከፋች ክስተት ሆኖለታል።

እሳትን የታጠቀው የሰው ልጅ ብቻ ስለነበር አቅልጦ መሣሪያ መስራትንና በሂደት ሳይንስን አፍልቆ እሳትን በኪሱ በክብሪትና በላይተር እስከመያዝ አደረሰው። የመጀመሪያ መሳሪያው ጎራዴም የኢኮኖሚ የበላይነትን አቀዳጅቶታል። ሁሉም ሰው ጎራዴን ማግኘት ባለመቻሉ ጎራዴውን ለማግኘት በሌሎች ቁሶች በመቀየር የዘመናዊ ንግድንና የጦር መሳሪያ አስፈላጊነትን መስርቶ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ቀዳሚ ታሪክን ፈጥሯል። በርካታ የጦር መሳሪያ ያገኙት መሳሪያ የለላቸውን በቁጥጥራቸው ስር በማድረግ በጦርነት በማስገደድ የመሳሪያዎቹ ባለቤቶች ባለስልጣን እየሆኑ ከ3000 ዓ.ዓ ጀምሮ አስተዳደር ነክ ስራዎችን መስርተዋል።

በሕግ ፊት ሁሉም እኩል ነው የሚል ስምምነት በመፍጠር ግለሰብን ከግለሰብ የማያበላልጥ አስተሳሰብ እንዲሆን ሞክረዋል። በአሜሪካ ሕገ መንግስት ግለሰብ በኑሮው በነፃነቱ ወይም በንብረቱ ላይ ያለው መብት ያለመደበኛ ፍርድ ቤት ብያኔ ሊደፈር አይችልም ይላል። ይህ ግን በአካኪኖስ ደረጃ ላሉ አፍሪካውያን አያስፈልጋቸውም ብለው ያምናሉ። ምክንያቱም የሚያወሩት ስለሰው እንጅ ስለተራዎቹ አፍሪካውያን አካኪኖሶች/ከብቶች/ አይደለምና። ነፃነት ማለት ደግሞ የሰው ነፃነትን የሚያሳይ ስለሆነ ነፃነት ግለሰብ ከግለሰብ ግለሰብ ከኅብረተሰብ ያላቸው ግንኙነት በኅብረተሰቡ የፖለቲካ የኢኮኖሚ ማኅበራዊና ባሕላዊ ኑሮ ውስጥ የሕዝቡ ጥቅምና ዕድገት በሥርአት የሚጠቀምበት መብት ነው የሚል ትርጉም ቢኖረውም ለአካኪኖሶቹ ሰው አይደሉም ተብለዋልና ይህ አይመለከታቸውም።

በፊውዳሊዝም ከሱ ኋላ በየምክንያቱ በቀጠሉት ስርዓትም ይህው ደረጃ ቀጥሎና ይበልጥ ገንኖ ተንፀባርቋል። ፊውዳሊዝም ፊዩዱም ከሚለው የላቲን ቃል የመጣ ሲሆን ንጉሡ ወታደራዊ ታማኝነት ላላቸው ባለሟሎቹ ለሚያከፋፍለው መሬት የተሰጠ ስም መሆኑንና ከ3ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በመካከለኛው ዓመታት በእርሻ ኢኮኖሚ ላይ የተመሰረተ ስርአት ስለነበር ይህ ስርዓት በራሱ አካኪኖስን እንደከብት እንጅ እንደሰው አላያቸውም።

አካኪኖሶቹ አፍሪካውያን ብዙ ተባዙ ውለዱ ተዋለዱ በሚለው መርህ ዘራቸውን ያለገደብ በማባዛታቸው ሰው ነን ብለው እራሳቸውን የለዩት ወገኖች የምድርን ሐብት የሚሻማቸውን አካኪኖስ ትውልድ ማጥፋትን እነደ ጥሩ መላ ሊጠቀሙበት ፈለጉ።

አሜሪካ በበኩሏ በፖሊሲ ደረጃ የአንዳንድ ሐገራት ሕዝብ ቁጥር መጨመር ሀገራቱ አቅም እንዲኖራቸው በማድረግ በዓለም ፖለቲካ ላይ ተፅእኖ ይፈጥራሉ የምትል ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ያስቀመጠችው አሜሪካም ሆነች ምእራባውያኑ ካላደጉት ሀገሮች ወደፊት በሚጠቀሙት ተፈጥሯዊ አንጡራ ሐብት ላይ የአፍሪካና መሰል ያልሰለጠኑ ሐገራት የሕዝብ ቁጥር ማሻቀብ ትልቅ ጋሬጣ ይሆንብናል ብለው ሰጉ።

የአሜሪካ መንግስት በዓለም ላይ በተለይም አፍሪካውያኑ የሕዝባቸውን ቁጥር መቀነስ ባለመቻላቸውና በየቀኑ በመፈልፈል የሕዝባቸው ቁጥር ማመን በሚያስቸግር ፍጥነት መጨመሩ የአፍሪካውያኑ በስፋት መዋለድና መራባት በአሜሪካ ላይ የምግብ እጥረት በመፍጠር የማንወጣው ችግር ስለሚሆንብን እንደተባበሩት መንግስታት እና የዓለም ባንክ መሰል ድርጅቶችን በመጠቀም በመራባታቸው ሳቢያ ሐብት መሻማታቸውን ለማስቆም ሄንሪ ኪሲንጀር በነደፉት ፖሊሲ በአሜሪካውያኑ ላይ ሊከሰት የሚችለውን የምግብና የፍላጎት እጥረትን ለመታደግ በቆራጥነት ታጠቁ።

የብሔራዊ ደኅንነት ሜሞራንደም 200 በሚል እቅድ የአለምን ሕዝብ በተለይም በየቀኑ የሚፈላፈሉትን አፍሪካውያንን በብዛት ለመቀነስ በአፍሪካውያኑ መካከል ትናንሽ ጦርነቶች መፍጠርና ለተዋጊዎቹ ሁለቱም ወገኖች መሳሪያ በማቅረብ እርስበርሳቸው እንዲጫረሱ ማድረጉ አንዱ መፍትሄ ነው ብለው ስላመኑ በጎሳ፣ በእምነትና በደረጃ እየለያዩ በማናቆር መሳሪያ እያቀረቡ አፋጇቸው።

በካርተር ዘመን ኪሲንጀርን የተኩት ዘብኘብ በርዝንስኪም የአሜሪካ ብሔራዊ ሜሞራንደም 46 ላይ ኤፍቢአይና ሲአይኤ በመሳሰሉ ድርጅቶች በሕዝብ ቁጥር መቀነስ ላይ ጠንክረው እንዲሰሩ መብት ያሰጡና አፍሪካውያንና ጥቁር አሜሪካኖች መሰባሰባቸው ለአሜሪካ ደኅንነት የከፋ ስጋት መሆናቸውን አስምረው እነሱን ለማጥፋት በተግባር ተንቀሳቅሰዋል።

በርዝንስኪም የአሜሪካ መንግስትም አፍሪካውያን አላስፈላጊ በላተኞች ናቸው ያሉና የወደፊቷን አሜሪካ ለመጠበቅ እነዚህን አካኪኖስ አላስፈላጊ በላተኛ የሆኑ አፍሪካውያንን ደረጃ በደረጃ መቀነስን እንደመርህ ተያያዙት። አንድ ኪሎ ሜትር በአንድ ኪሎ ሜትር በሆነ ክልል ውስጥ የሚኖሩ አፍሪካውያን ሕዝቦችን ለመቀነስ በሌሎች የመሣሪያ አይነቶች 2000 የአሜሪካን ዶላር ስለሚፈጅ በባዮሎጂካል በኒውክሊየር መሣሪያ ነጥለንና ለይተን ብናጠፋቸው የሚፈጅብን 800 የአሜሪካን ዶላር ብቻ መሆኑንና 1200 ዶላር መቆጠብ እንደሚቻል ዶ/ር አላን ካንትዌል ያቀረቡት ጥናት በማስረጃነት መጠቀስ የሚችል ነው።

ፕሬዚደንት ኒክሰንም በተራቸው የሕዝብ ቁጥር ማሻቀብ ለአሜሪካውያን አደገኛ በመሆኑ ለኮንግረሱ አቅርበውና ፐብሊክ ሎው 91-213ን አፀድቀው ኤችአይቪን በላብራቶሪ ለመስራት በአሜሪካ ሕጋዊ ድጋፍ አገኘ። የተመረጠና የተወሰነ ዘርን ብቻ ለይቶ የሚያጠፋ ኤትኒክ ዌፐን መሳሪያ በተለያየ ሙከራ ተሰራ። ወደ 400 የሚደርሱ በአልባማ የሚኖሩ ጥቁሮች ላይ ለቂጥኝ በሽታ ሳይንሳዊ ጥናት ሙከራ ተደርጎባቸው ፈጅተዋቸዋል። ሳይንሳዊ ሙከራ የተደረገባቸው ጥቁሮች እየተሞከረባቸው ሆን ተብሎ  በበሽታው እንዲያዙ መደረጋቸውንና የሙከራ አይጥ መሆናቸውን ፈፅሞ አያውቁም ነበር። ሕመሙ ሲጠናባቸው መፍትሄ ለማግኘት አቅራቢያቸው ወደሚገኙ የሕክምና ማእከላት ቢሄዱም አንቲባዮቲክስ ሕክምና ለእነዚህ ጥቁሮች እንዳይሰጥ ትእዛዝ በመተላለፉ መታከምም አልቻሉም። ምርምሩ ጥቁሮችን ቂጥኝ ማስያዝና ምን ያህሉን በምን ያህል ጊዜ እንደሚገድል ማወቅን መሰረት ያደረገ ነበር።

ከባርነቱ ዘመን በኋላም በሰለጠነው በበቅርቡ ዘመን ስለጥቁር ስነዘር /ጀነቲክ/፣ የስነዘር ልዩነት /ጀነቲክ ዲፈረንስ/ ምርምር ተካሂዶ ኤችአይቪ በካንሰር ምርምር ስም በላብራቶር ተፈብርኮ ከአፍሪካ የመጣና የተሰራጨ በሽታ እንደሆነ ሲነግሩን፣ በሉ ያሉንን እኛ አስመስሎ አቅራቢ አካኪኖስ አፍሪካውያንም ከአፍሪካ የመጣና የተሰራጨ ብለን አወጋን፣ መንግስታቶቻችንም በዜና ማሰራጫዎቻቸው ይህንኑ እያስተጋቡ አደመቁት። እንዳውም ይህን ያሉንን በሬ ወለደ ወሬ በማስተጋባታችን አዋቂ ምሁራን ሆነን ተፎከስን።

የካንሰር ምርምር ማእከሎቹ ኤችአይቪን አምርተው ሲጨርሱ ምስጢሩ እንዳይገለጥ ያልተሳካ ፕሮጀክቶች ተብለው ከነድብቅ ምስጢራዊ ታሪካቸው እንዲፈርሱ ቢደረግም የአሜሪካ ባዮሎጂካል መሳሪያ ተመራማሪዎች በ1969 10 ሚሊዮን ዶላር ከአሜሪካ ኮንግረስ ተቀብለው በቪስና ቫይረስ ላይ ከፍተኛ ምርምር ተደርጎ ዶ/ር ሮበርት ጋሎ ያወጡት HL-23 ተብሎ ከተሰየመው ቫይረስ ጋር በማዳቀል ኤችአይቪ ቫይረስን አምርተው ነው እንዲፈርሱ  የተደረጉት።

ይህንን ምስጢር ለማጥፋት ነበር በጀት መድበው ኤችአይቪ አፍሪካ አመጣችብን የሚል የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፍተው በመንግስታቶቻችንና በልኂቃን ኤሊቶቻችን እየተመሰከረና በሰጧቸውና ባስታጠቋቸው ፅንሰ ሐሳብ ላይ እየተመሰረቱና የራሳቸውንም አዋቂነት እያከሉበት አውርተው ያስወሩን።

እናም የሰሩትን ቫይረስ ያወቁ የሚመስላቸው ሆኖም ባላወቁት በራሳችን መሪዎችና ምሁራን እገዛና ሙሉ ድጋፍ አካኪኖስ አፍሪካውያንን አላስፈላጊ በላተኞች ብለው ለመፍጀት ተጠቀሙበት። ወሲባዊ ፍላጎታቸውን ለመገደብ ጨርሶም ለማስቆምና ዝርያው እንዳይቀጥል ሞከሩበት። በዘመቻ በክትባት አፍሪካውያንን በግልፅ ከተቡበት፣ በየሰው ላይ በስፋትና በጥድፊያ አሰራጩበት። መንግስታቶቻችንም በይፋ ዘመቻውን አውጀው ስንከተብ እንዳንንፈራገጥ ጠብደሎችን መድበው እጅና እግራችንን እያስያዙ አስከተቡን። ቫይረሱን አስከትበው ሕዝባቸውን በጅምላ አስፈጁት፣ በደስታው ላይ የሐዘን ማቅ ቸለሱበት።

አንድ ጥቁር ሰው የሰው ሲሶ ነው ብለው የሚያምኑት እነዚህ ምርጥና እውነተኛ ሰው እኛ ብቻ ነን ብለው የሚያምኑ ግብዞች፣ በአፍሪካ ምድር በተለይም በኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኘቱንና እነሱም ከዚህ ሕዝብና ምድር የመፍለሳቸውን ዝንጋታ ተጭኗቸው በሐብት ማከማቸት፣ በጥቅምና በስግብግብነት የሕዝብ ቁጥርን በመቀነስ የራሳቸውን ተጠቃሚነት ለማስፋት ሲሰሩ እኛም ለውድመታችን እንዲጠቀሙብን ተሰልፈን ለማራገቡና ለአፈፃፀሙ እንጣደፋለን።

አካኪኖስ ተራ ዝርያዎች ተብለን ሰው ነን ብለው እራሳቸውን በመደቡት ወገኖች እንደከብት የተፈረጅነው አፍሪካውያን አካኪኖስነታችንን አምነን መቀበላችንን ማረጋገጫዎቹ እራሳችንን ፈረንጆቹን ለማስመሰልና በምንም መመዘኛ ላንመስላቸው ግን መስለን ለመገኘት ጨንጓራችንን አስገልብጠን እንታገላለን። የነሱ ዘፈን፣ የነሱ ልብስ፣ የነሱ ቋንቋ፣ የነሱ ማንነት የኛ እንደሆነ አድርገን በብብታችን የያዝነውን የራሳችንን ማንነት ጥለን እነሱን ለመሆን እንቋምጣለን።

የቂጡን አንድ ጎን ሙሉ ለሙሉ ባዶ ያደረገ ሱሪን ያለውስጥ ሱሪ /ፓንት/  ሰው ነን የሚሉት ቢለብሱ እኛም እነሱን የሆንን መስሎን ተሸቀዳድመን እንለብሳለን። ይልቁንም ሁለቱም ቂጣችንን ባዶ አድርገን አሻሽለን የሱሪውን ሌላውን ጎን ቀደን በመልበስ ድጋፋችንን በታማኝነት በፍፁም የበታችነት ስሜት እናረጋግጥላቸዋለን።

ፈረንጅ ወይም ሌላ ዜጋ በሌለበት አዳራሽ ስለህዝባችንና ስላገራችን ችግርና መፍትሄው ለመመካከር በሚካሄድ ስብሰባ በስውር ቅኝ ተገዥነት ባለሟልነታችን በእንግሊዝኛ እንደሰኩራለን። አገር በቀል የላቀ እውቀትና ክህሎት እያለንና እነሱም ከሰው መገኛ አገር ከአፍሪካ በየምክንያቱ በዘመናት ብዛት እየፈለሱ መበተናቸውንና የሰው ዘር መነሻዎቹ ኦርጅናሎቹ እኛ፣ የስልጣኔ ምንጮቹ እኛ፣ እናንተ እንዳላችሁን አካኪኖስ ነን ብለን በመቀበል የነሱን ዘፈንና እብደት ሳይቀር እየኮረጅን አካኪኖስ አይደለንም እናንተ ነን ለማለት ያዙኝ ልቀቁኝ ብለን እነሱኑ ለእብድ ገላጋይነት ከመካከላችን እንስጋቸዋለን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
574 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 918 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us