ሜ/ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት፤ የደርግን ምንነት ሳያውቁ ነበር እንዴ ደርግን የታገሉት?

Wednesday, 15 June 2016 12:46

ከአለሙ ታፈሰ

“ደርግነት እያቆጠቆጠ - ዴሞክራሲው እየጨላለመ ነው - ህዝቦች ጠንቀቅ በሉ!” በሚል ርዕስ በቅርቡ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች የለቀቁትን ፅሁፍ ካነበብኩ በኋላ የተሰማኝን ስሜት እኔም እንደ እርስዎ ሃሳቤን በነፃነት የመግለፅ ዴሞክራሲያዊ መብቴን ተጠቅሜ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

ደርግን ለመጣል በተደረገው የትጥቅ ትግል ውስጥ በመሳተፍ ከተገኘው አንፀባራቂ ድል በኋላ በልዩ ወታደራዊ ስልጣን እርከን በማገልገል እስከ ሜ/ጄኔራልነት ለመድረስ የቻሉትና በህወሓት የፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ ባሳዩት ግልፅና ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የተነሳ ከስልጣንዎ ለመሰናበት ከበቁ ከአመታት በኋላ የያዙትን ያልሰከነ ፅሁፍ የማስነበብ አብሾ ለመወጣት የሞከሩበትን አንድ ፅሁፍ ለማንበብ ጊዜ አልፈጀብኝም።

“ደርግነት እያቆጠቆጠ - ዴሞክራሲው እየጨላለመ ነው - ህዝቦች ጠንቀቅ በሉ!” የሚለውን ፅሁፍዎን ካነበብኩ በኋላ አቋምዎን በነፃነት የማራመድ ዴሞክራሲያዊ መብትዎን ሳይሸራርፉ አሟጠው እንዲጠቀሙበት እድሉን ያመቻቸልዎትን ስርአት “ወደ ደርጋዊ አምባገነንነት እየተለወጠ ነው” በማለት የሞገቱበትን አቋምዎን በዴሞክራሲያዊ መብቴ በመጠቀም ልታዘበው ዘንድ ወደድኩኝ።

ከህወሓት ጋር ይሁን ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጋር በመሆን ለከፍተኛ አመራርነት ደረጃ የደረሱ እንዲሁም እንደ እርስዎ ሁሉ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከድርጅትዎ አለያም ከሰራዊቱ ውስጥ አብረው በመሆን ረጅም ርቀት የተጓዙ “ቆመንለታል፣ መስዋእትነት ለመክፈል ቆርጠን ስንታገልለት ነበር” ከሚሉለት መስመር እጅግ በተፃራሪ ቆመው ሲራመዱ ሳይ የተለያዩ ጥያቄዎችን ማንሳቴ አልቀረም።

እነዚህ የቀድሞ የድርጅቱ አመራር እና አባላት ከነበሩበት ቦታ ሲርቁ በዚህ መሰል የተገላቢጦሽ መስመር የሚቆሙት ለምንድነው? ታግለንለታል የሚሉትን ድርጅትም ሆነ የፖለቲካ መስመር የምር ያውቁት ነበር? አምነውበትና ቆርጠውለት ሲታገሉስ ነበር? ወይም የትግል ጎርፍ አንከባሎ እንዳመጣው ድንጋይ (ጠጠር) ተንከባለው የመጡ አለያም ቀድሞ ከነበሩበት የትግል መስመር የሚፃረር አቋም ይዘው በመደበቅ ቀን እየቆጠሩ ይጠብቁ የነበሩ ናቸው እንዴ?” ብዬ ለአንድ የኢህአዴግ አባል የሆነ ወዳጄ ጥያቄ አቀረብኩለት። እሱም ጥቂት ከሳቀ በኋላ “እነዚህ ሰዎች ቀድሞ ከነበሩበት መስመር ለምን ወጡ ብለህ ከጠየክ መልሱን ታገኘዋለህ” አለኝ።

ሜ/ጄኔራል አበበ በርግጥ ደርግን በጥልቀት አውቀውት ነው በቲዮሪ ደረጃ ስለ ደርግ ለመተንተን የባዘኑት? ደርግን በህዝብ ጨፍጫፊነት ለመግለፅ ለምን እንደተሳነዎ አልገባኝም፣ ከ25 አመታት በኋላስ የምን ደርግ አመጡብን? በደርግ ስርአት አይደለም የመናገር እና የመፃፍ መብት ሊከበር ቀርቶ በግል የማሰብ ተግባር ‘እንዲህ ስታስብ ደረስኩብህ’ አስብሎ የሚያሳስር እና የሚያስገድል መሆኑን ምነው ዘነጉት? በደርግ ዘመን እንኳንስ በከፍተኛ የስልጣን ደረጃ ላይ የሚገኘውን የመካላከያ ኢታማዦር ሹም ማብጠልጠል ይቅርና የቀበሌ አመራርን መተቸት ይቻል ነበር ወይ? እርስዎ ያን የአፈና ስርአት መሆኑ የተረጋገጠለትን ደርግ ነው የታገሉት ወይንስ እኛ የማናውቀው ደርግ ነው የታገሉት? በበኩሌ በፍፁም አልገባኝም። ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ማለት እንደዚህ ነው።

በፅሁፍዎ ላይ “የአገራችን መንግስት እና የገዢው ፓርቲ አጠቃላይ ችግር ውስጥ በመግባታቸው ምክንያት እዚህ እና እዚያ የሚታዩ ችግሮች እየተስተዋሉ ነው። ሰሞኑን እንኳ ብናይ ከኦሮሚያው ህዝባዊ አመፅ፣ ሜቴክ እና ስኳር ፋብሪካ፣ ከጋምቤላ ጠለፋ እና ግድያ፣ ከኤርትራ በኩል የሚመጣ ተከታታይነት ያለው ትንኮሳ እየተስተዋለ ነው፣ የድርቁ እና በየክልሉ የሚታዩ የህዝቦች መነሳሳት ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ የሚፈጠሩ ነገሮች ህገመንግስታዊ ማእቀፍ እና ከህዝቦች ፍላጎት አንፃር ማየት አለብን” በማለት በተጠቀሱ ችግሮች የተነሳ የኢህአዴግ አመራር አደጋ ላይ እንዳለ ለማስመሰል የሞከሩት ሜ/ጄኔራል በተጠቀሰው ርእስ ስር መፃፍ ስለፈለጉት አንድ ነጥብ ለማወቅ ዝግጅት አለማድረጋቸውን ማረጋገጥ ይቻላል። ለምሳሌ የጋምቤላውን ብንወስድ ለአገራችን እና ለጎረቤት አገሮች የተከሰቱ ችግሮች ስርአቱ አስተማማኝ የሆነ ምላሽ መፍትሄ ይሰጣቸውና ከጎረቤት አገሮች ጋር በመተባበር ሊያስተካክላቸው የቻላቸውን እንዲሁም በወሰዳቸው የተጠናከረ እርምጃ አለማቀፍ ምስጋናዎችን የተቸረባቸው መሆናቸው እየታወቀ ሜጀር ጀነራሉ “አይኔን በጨው” ብለው አደጋዎቹ አሁንም አሳሳቢ እንደሆኑ ለማራገብ መብቃታቸው ግራ የሚያጋባ ነው።

በኦሮሚያ ክልል የተነሳው ችግር በተወሰዱ ተደጋጋሚ እርምጃዎች እና ውሳኔዎች እየተፈታ ነው። በጋምቤላ የተፈጠረው የዜጎች የጠለፋ ችግር መነሻውና እንቅስቃሴው በአመራሩ ልልነት የተደረጉ ካለመሆናቸው በላይ አህጉሪቱን ባስደመመና ልጃገረዶቻቸው ለአመታት ተጠልፈው ለቆዩባቸው ሌሎች አገራት ትምህርት በሚሰጥ ወታደራዊ ሀይል መራሹ የሰላም ተግባር መልስ ማግኘቱ እየታየ፣ ሰው ሰራሽ ባልሆነ መልኩ የተፈጠረ የድርቅ አደጋ ህዝብን ያማከለ እንቅስቃሴ ለማድረግ ቆርጦ አቋሙን በማሳየት ይህንን አስደንጋጭ አደጋ የመቀልበስ አቅሙ እንዳለው ያረጋገጠውን የኢህአዴግ አመራር አለም ባደነቀ መልኩ ለመግታት መቻሉ በተጨባጭ እየታየ ሜ/ጄኔራል አበበ መሰረት አልባ ትንታኔ ለማቅረብ መድፈራቸውን አሳፋሪ ያደርገዋል።

አሁን ያለው ስርአት ወደ ደርጋዊነት እየተሸጋገረ በመምጣት ላይ መሆኑን ለመተንተን የሞከሩት ሜጀር ጀነራሉ “የዴሞክራሲ እጥረት ወይም ምህዳር መጥበብ ማለት ደርግነት መንገስ ማለት ነው” ብለው መፃፋቸው አንገት የሚያስደፋ አሸማቃቂ አቋም መሆኑን አልክድም። በአንድ ስርአት ውስጥ የነበረ ዴሞክራሲ ከነበረበት ስፋት አንፃር ሲሰላ መጥበቡ አለያም ወደ አነሰ ምህዳር መንሸራተቱ በፍፁማዊ አምባገነናዊ መዳፍ ውስጥ ሆኖ በሰብአዊ መብት ጨለማ ተከርችሞ ከነበረው የለየለት ጨፍጫፊ ስርአት ጋር ለማነፃፀር የሚበቃ አለመሆኑን ሜጀር ጀነራሉ አሁን ቁጭ ብለው ሲያስቡት ይረዱታል ብየ አምናለሁ። ቢያንስ ወደ በረሃ የወረዱበት የለየለት ሰው በላ ስርአት ዛሬ “ምህዳሩ ጠቧል” ካሉትና አቋማቸውን የሰብአዊ መብቶች ሀሁ ከሆነው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ጋር ያነፃፀሩበትን አግባብ ለመፈተሽ ይረዳቸዋልና።

በኢህአዴግ አመራር ውስጥ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንደተፈፀመ በማስመሰል ወታደሩ የአመራሩን በትር ለመንጠቅ አይነተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ በፅሁፋቸው ያስነበቡት ሜ/ጄኔራል አበበ ኢህአዴግ ከ15 አመታት በፊት የውስጥ አደጋ አለኝ በማለት የስርአቱን መዳከም በገለፀበት ወቅት እርሳቸውን ከመሰሉ ደጋፊዎቻቸው ጋር በመሆን “ምንም አይነት የውስጥ አደጋ የለም፣ ዴሞክራሲ እና ልማት ከበቂ በላይ አለ፣ ያለብን ችግር የሉአላዊነት ችግር ብቻ ነው” በማለት ደረታቸውን ነፍተው ሲከራከሩ እንደነበረ ማስታወሱ አስፈላጊ ነው።

በአሁኑ ወቅት በተደረገው ከፍተኛ ትግልና መስዋእትነት ያገኘነውን ዴሞክራሲ በመጠቀም እርስዎም ሆኑ ከእርስዎ በላይ የነበሩ ያለገደብ በተሰጣቸው ዴሞክራሲ የፈለጉትን ሲፅፉ ማን ነካቸው? በርግጥ በኢትዮጵያ ያለው ዴሞክራሲ በማደግ ላይ ያለ ዴሞክራሲ ከመሆኑ አንፃር ስህተት የለውም ብሎ በትምክህት ለመናገር የሚቻልበት ደረጃ ላይ አለመድረሱን ጠንቅቀን ስለምንረዳው ኢህአዴግን ወደ ደርጋዊ ክፉ መንፈስ ለመጎተት የተፈለገውን የእርስዎን ፅሁፍ ለማንበብ አያስፈልገንም።

የመከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም “የኔ አመለካከት፣ እኔ እንደሚመስለኝ” በማለት በግላቸው ያስቀመጡትን አስተያየትና ትንተና መነሻ በማድረግ በአስተማማኝ መሰረት ላይ የቆመውን እና በህዝቦች አንድነት የተገነባውን ታላቅ ስርአት ወደ ደርጋዊ አምባገነንነት መለዮ የመገልበጥ ስትራቴጂ ለምን ዓላማ ታስቦ የተሰነዘረ ስለመሆኑ መግለፅ ግራ ቢያጋባም ፀሃፊው ከኢታማዦር ሹሙ ጋር የኮከብ ውድድር ውስጥ ገብተው ከሆኑ በአጭር አማርኛ ማለት የሚቻለው “ተበልጠዋል” ብቻ ነው። የአንድ ሰራዊት አዛዥም ሆነ ወታደር ዜጎች እንደመሆናቸው በአገራቸው ላይ ሃሳባቸውን የማስተላለፍ ህገመንግስታዊ መብት አላቸው። በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን ማቅረብ የፖሊሲ ትንታኔዎች መስጠትም ሆነ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ መነሻዎችን በማቅረብና ግንዛቤ በመፍጠር ለተቋማት የሚሰጡት ፋይዳ የላቀ ነው። ከዚህ አንፃር ኢታማዦር ሹሙ “በእኔ አመለካከት” ብለው የሰጡት አስተያየት ሃሳብን በነፃነት የማንፀባረቅ ህገመንግስታዊ መብታቸው ነው። ሰራዊቱ የመምረጥ መብቱ በህግ በተቀመጠለት በዚህ ወቅት ጠመንጃ ይዞ የማስገደድና ሃይልን ተጠቅሞ መንግስታዊ አስተዳደርን የመለወጥ ምልክቶች ካልታዩበት በቀር አመራሩ ሆነ ተራው ወታደር የሰለጠነ የሰው ሃይል እንደመሆኑ ጭምር አመለካከቶቹና አቋሞቹን ቢያንፀባርቅ ታዲያ ምኑ ላይ ነው ችግሩ?

ሜ/ጄኔራል ሆይ ምን አልባት ኢታማዦር ሹሙ የቃላት ወለምታ ችግር ተፈጥሮባቸው ሊሆን ስለሚችል በአገላለፅ ተሳስተዋል ልንል የምንችልበት ነጥብ እንኳ ቢኖር ከዚህ ችግር በመነሳት “ደርግ መጣ” የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የቻሉበት አካሄድ ከምን የመነጨ ነው? ለልጅ “ጅብ መጣ” ብሎ እንደማስፈራራት የሚቆጠር የልጅ ጨዋታ አይነት አያስመስልብዎትም?

እርስዎ ከ15 አመታት በፊት በህወሓት ውስጥ ተፈጥሮ በነበረው የመከፋፈል አደጋ ወቅት ምን አግብቶዎት ነበር በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ ገብተው አንዱን ወገን በመደገፍ ሌላውን ሲያብጠለጥሉ እና ሲያጠቁ የነበሩት? በወቅቱ ያንፀባረቁት ፖለቲካዊ ወገንተኝነት አሁን ኢታማዦር ሹሙ በግላቸው “እኔ እንደሚመስለኝ” በማለት ካንፀባረቁት አቋም የተለየና የተቃርኖ ሃሳብ ያራመዱ አካላትን በቡድን ተደራጅቶ እስከማጥቃት ለመድረስ በሚያስችል አርበኝነት አክርሮ እስከ መጓዝ የደረሰ የነበረ መሆኑ እንደምን ይዘነጋል? እርግጥ በወቅቱ ባደረጋችሁት አደገኛ እንቅስቃሴ ህገመንግስቱን በግላጭ ጥሰው ስለነበረ አይደለም ከአመራርነት የተባረሩት? በኢትዮ - ኤርትራ የድንበር ጦርነት ወቅት ሳምሶናይት ተይዞ የነበረውን የገበያ ሩጫ እግዚአብሄር እና የሚያውቀው ብቻ ያውቀዋል። ማስረጃ ስላልነበረ እንጅ ጉዳዩ ከህግ ተጠያቂነት የሚያድንዎ አልነበረም። ቤት እየሸጡና እየለወጡ ከመኖር በላይ ከየት እንደመጣ ባልታወቀ ገንዘብ አሜሪከን አገር ሄደው እንደተማሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይህንን ሁሉ አድርገውም “ወደ ደርጋዊነት ተለወጠ” የሚሉት ስርአት በሰጠዎት መብት ተጠቅመው አፍራሽ አቋምዎን በፅሁፍ እያራመዱ ነው። በእርግጥ የሚፅፉት ፅሁፍ ቁም ነገር አለው የለውም የሚለውን የመከራከሪያ ነጥብ ለጊዜው በመተው ቢያንስ የፈለጉትን መፃፍ የቻሉት የዴሞክራሲ ስርአት ስላለ መሆኑን ሊረዱት ይገባል። በተረፈ አቋምዎ የስልጣን ወንበር ላይ ቁጭ ካላልኩ በስተቀር ዴሞክራሲ የለም የሚል ከሆነ ግን ስልጣን የሚታሰብዎ ሊሆን አይገባም፣ አያገኙትምና!!

ሜ/ጄኔራል አበበ “ዴሞክራሲያዊ ነኝ” እያሉ የአገሪቱ የዴሞክራሲ ማገር የሆነውን ህገመንግስታዊ የህዝቦች መዋደድ በቅጡ አለማወቅዎ ያሳፍራል። በተንሻፈፈው በዚህ ፅሁፍዎ እንኳን የኦሮሞ ህዝብን “የኦሮሞ ህዝቦች”፣ የቅማንት ህዝብን “የቅማንት ህዝቦች”፣ የኮንሶ ህዝብን “የኮንሶ ህዝቦች” እያሉ መፃፍዎ በህግ ት/ቤት ፊደል ለቆጠረ እና “word - careful” ሊሆን ለሚገባው እንዲሁም እራሱን እንደ አንበሳ ምሁር ለሚቆጥረው ሰው እጅግ ቀላል ተደርጎ የሚታይ ነበር። በመሆኑም በህዝብ እና በህዝቦች መካከል ስለሚኖር ፅንሰ ሃሳባዊ ፍቺ ልዩነት አለመረዳትዎን ያሳያል።

ኢህአዴግ የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት እስካስጠበቀ ድረስ ህዝባዊ መሰረቱን ማንም አይነቀንቀውም። እርስዎ ኢህአዴግ በአጠቃላይ ችግር ውስጥ እንደገባ አድርገው በመግለፅዎ ምን ለማለት ፈልገው እንደሆነ ግልፅ አይደለም። ወደ ችግር እንዲገባ ካለዎት ምኞች በመነሳት አስበው ከሆነ ይህም የሚሳካ አይደለም። ኢህአዴግ በተደጋጋሚ ጊዜ ችግሮቹን አንድ ሁለት ብሎ በግልፅ እና በድፍረት በማንሳት እየተወያየ መፍትሄ የሚሰጥ ድርጅት ነው። ኢህአዴግ “ችግሮቼ” ያላቸውን ችግሮቹን ለመፍታት ውስጣዊ ትግሉን በማቀጣጠል እና ህዝቡን በማሳተፍ መፍታት የቻለ ፓርቲ ነው። ይህም ባህል ጥንካሬው እንጂ እርስዎ እንደሚመኙት ውስጣዊ ችግሩን የሚያሳይ አይደለም። ውስጣዊ ችግር አደጋ ሊያስከትል የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ በማስመሰል በእሳት ላይ ቤንዚን የሚያርከፈክፉ እንደ እርስዎ የመሳሰሉ ግለሰቦች ቢኖሩም ኢህአዴግ ግን የሚፈጠሩ ችግሮችን በቁርጠኝነት ከህዝብ ጋር ይፈታዋል።

ሜ/ጄኔራል ሆይ! አውሮፓዊቷን ፈረንሳይ እና አገራችን ኢትዮጵያ ያሉበትን አንፃራዊ ውሎ እና አዳር ይረዱታል። ይህንን ሃቅ አገራችን ያለችበትን ታላቅ ጉዞ ለማሳየት ስል እንደመልካም አብነት ላነሳው እወዳለሁ። በፈረንሳይ አገር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች አሳሳቢ እየሆኑ በመጡበት በዚህ ወቅት የእርስዎ አይነት የአመለካከት ግራቀኝ መጋባት ያጋጠመው የፈረንሳይ ጄኔራል ቢሆን ኖሮ “ችግሩ ወደ ደርጋዊ ስርአት ከማምራት የመነጨ ነው” ለማለት ሳይደፍር እንደማይቀር እገምታለሁ።

ከቀን ወደ ቀን ወደ ተሻለ እድገት እያመራች ባለችው አገራችን የድርቅ እና የጎርፍ አደጋ እንዳጋጠመን ሁሉ በፈረንሳይም ከባድ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ ጉዳት አስከትሏል። በዚህች አውሮፓዊት አገር በተደጋጋሚ ጊዜ የሽብርተኝነት ጥቃት ተፈፅሞ በርካታ ሰዎች ሞተዋል። አሁንም ተከታታይ የሆነ የህዝብ ተቃውሞ እና አመፅ እየተካሄደ ነው። ከቀን ወደ ቀን ወደ ተሻለ እድገት እየተጓዘች ባለችው አገራችን በተደጋጋሚ ጊዜ የተቃጣብን የሽብርተኝነት ሴራዎች በፅናት ከሽፈዋል። እነዚህ አይነት ጥንካሬዎች ስርአቱ ወደ አጠቃላይ ችግር ውስጥ ገብቷል ሊያስብል የሚችልበት አግባብ እንዴት ነው? “ክቡር” ሜ/ጄኔራል ባልተፈጠሩበት የስነ ፅሁፍ አለም ውስጥ ገብተው በትግርኛም በአማርኛም ለመፃፍ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እከታተላለሁ። በርግጥ ዴሞክራሲ ስላለ ይቀጥሉበት።

በመጨረሻም ሜ/ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት በፅሁፍዎ ወጣት ወጣት እያሉ መደጋገምዎ አስደንቆኛል። የጠቀሷት አንዲት ወጣት ያሳየችው ቁርጠኝነት ግን እርስዎ እንዳሉት የስርአቱን ደርጋዊነት የሚያንፀባርቅ አልነበረም። የህዝቦች መስዋእትነት የተከፈለው የዴሞክራሲ ስርአት ለመገንባት በተደረገ ትግል እንደሆነ ያረጋገጠ እንጂ!! ወጣቱ በተሰጠው ዴሞክራሲያዊ መብት በመጠቀም ሃሳቡንና አቋሙን በግልፅና በነፃነት በማራመድ ትውልዱ በቀደሙት ጀግኖች መስዋእትነት በተዘረጋው የዴሞክራሲ መስመር መጠቀም መጀመሩን ያልተረዱበትን ጭፍንተኝነት ያሳያል። ወደ ደርጋዊነት እየተለወጠ ነው ያሉት ስርአት የዴሞክራሲ መብታቸውን ጠንቅቀው የተረዱና በከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ አቋማቸውን ማንፀባረቅ እና መብቶቻቸውን መጠየቅ የጀመሩ ወጣቶች እያፈራ መምጣቱ ሊያስደስት እንጅ ሊያበሳጭ አይገባም። በጀግኖች ትግል እና መስዋእትነት የተገነባው ዴሞክራሲያዊ ስርአት ወደ ደርጋዊነት የመቀልበስ አደጋ ውስጥ ወድቆ ቢሆን ኖሮ “የፍየል ወጠጤ” በተዘፈነባቸው ነበር።n

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
699 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1028 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us