የሰኔ ነገር

Wednesday, 22 June 2016 12:14

 

መጣ….መጣ….ሰኔ…መጣ

ስልጠና፣ ጉዞ፣ ወርክሾፕ እንውጣ

ስቴሽነሪ፣ ማሽነሪ ገዝተን እናምጣ

ገንዘብ ተርፎ ሳይመጣብን ጣጣ

አልሰራችሁ ተብለን በአለቆች እንዳንቆጣ።……..ግጥም መሆኑ ነው?

ባለፈው ሳምንት ለስራ ጉዳይ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር የሚያስኬድ ጉዳይ ገጠመኝና በየቢሮዎቹ ጎራ እያልኩ ጉዳየን አስፈጽም ነበር። በጉደኛ ሰኔ ወር ከበጀት ማባከን፣ መበዝበር፣ መጫዎት ጋር ተያይዞ በየአመቱ ስሙን በክፉ በምናነሳው፣ በምንቦጭቀው፣ እንደክፉ መንፈስ መጣ….መጣ….መጣ… እያልን በምናማው፣ ከፊሎቹ ደግሞ በሚያወድሱት ሰኔ ወር አስረኛ ቀን ገደማ ለጉዳይ ከሄድኩባቸው ስድስት ተቋማት መካከል አራቱ የመንግስት ሲሆኑ  ሁለቱ ደግሞ የግል ተቋማት ናቸው። ታዲያ ከሄድኩባቸው የመንግስት መ/ቤቶች መካከል ሁለቱ ላይ ሰኔ ወር ያገጣጠመኝ እውነታ ነው የጽሁፌ መነሻ። አንዱ ኤጀንሲ ሌላው ደግሞ ሚኒስቴር መ/ቤት ነው። አንደኛው ተቋም በር ስደርስ የጥበቃ ሰራተኛው  የት ነው የሚል ጥያቄ አነሳ የምሄድበትን ተናገርኩ መታወቂያዬን አሳየሁ። ግን ማንም የለም እኮ አለኝ። ጆሮየ መስሎኝ …ቀኑ የስራ ቀን… ሰዓቱም የስራ ሰዓት ግራ ገባኝና እንዴት? ስለው… ሰራተኛው በሙሉ ሌላ ሀገር ሄዷል አለኝ። አይ እኔ የምፈልገው የዚህን ክፍል ባለሙያዎች ነው ስል አዎ! ማንም የለም እኔ ብቻዬን ነው ያለሁት አለኝ እና አረፈው። በግምት ተቋሙ ከመቶ በላይ ሰራተኞች እንዳሉት ባውቅም በዚያ የስራ እለት ግን የፈረደበት አንድ ጥበቃ ብቻውን ግቢውን ይጠብቃል። አሁን የፈለግሁትን ሰው እንደማላገኝ ስለተረዳሁ መግባት ከፈለግሁበት ተቋም ጎን ሌሎችም ተቋማት ስላሉ እግረ መንገዴን ጎራ ማለት ፈልጌ በቃ እገሌ ተቋም ልግባ በማለት ገባሁ። ወደሌላኛው ተቋም የማልፈው ቀድሞ ፈልጌው በመጣሁበት ተቋም ውስጥ ስለነበር እውነትም መ/ቤቱ ጭር ብሏል። እሱን አልፌ ጎረቤት ስሄድ ደግሞ በስራ ላይ ናቸው። የሁለት አለም ነዋሪዎች ማለት ይሄ ነው። አንዱ የመንግስት በጀት እየፈሰሰለት ባጀቱን ሳይጠቀምበት ወራትን አሳልፎ ለበጀት መዝጊያ ሁለት ሳምንት ሲቀረው በጉብኝት ሰበብ ተረባርቦ ገንዘብ ማጠፋፋት ዕድል የቀናው ሌላው ደግሞ በራሱ የገቢ ምንጭ የሚተዳደር የመንግስት የልማት ድርጅት በመሆናቸው ሰኔ ወር ሲመጣ ይለያያሉ። አንዱ በመንግስት ገንዘብ ይዝናናል ሌላው ደግሞ የመንግስትን ገቢ ከፍ ለማድረግ ይሯሯጣል። ወደ ገደለው ስንገባ አንድም ለታዛቢነት ለመረጃ ሰጪነት ሳያስቀምጥ ሰራተኞቹን በሙሉ ለጉብኝት ይዞ የተጓዘው ተቋም በመቶዎች የሚቆጠር ሰራተኞች ያሉት፣ በርካታ ባለጉዳይ የሚስተናገድበት የመንግስት ተቋም ነው።

 

 

ሌላውና ሁለተኛው የሰኔ ወር በጀት መዝጊያ ጉዳይ ማሳያ ወደሆነኝ ሚኒስቴር መ/ቤት ጎራ ያልኩትም በተመሳሳይ ዕለት ከሰዓት በኋላ ነው። እዚህ ተቋም ስደርስ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ የያዘ ፌደራል ፖሊስ በር ላይ ቁጭ ብሏል። አልፌው ወደውስጥ ዘለቅሁኝ አንደኛ… ሁለተኛ… ሶስተኛ ፎቅ እያልሁ ወጣሁ ጭር ብሏል። ስለ እውነት በነገሮች ራሴንም ማመን እስኪያቅተኝ ድረስ በሚኒስቴር መ/ቤቱ እንኳን ሰው ወፍ የለም (ወፍ ደግሞ ቢሮ ምን ያደርጋል እንዳትሉኝ አንዳንዱ ቢሮ ከባለጉዳይ አልፎ ወፍ ያለምዳልና ነው)። ወደ ላይ መውጣቴን አላቆምኩም ከሆነ ክፍል ኮቴየን ሰምቶ አንድ ሰው ብቅ አለ የቢሮውን በር ስመለከት ሚኒስቴር መ/ቤቱን ሊደግፍ የተቀመጠ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ስም አየሁ። የፈለግሁትን ስነግረው ምን አለኝ መሰላችሁ “ማንንም አታገኝም ነገ ሰራተኛው በሙሉ ጉዞ ስለሚሄድና ማንም ስለማይኖር ጭር ቢልባችሁ እንዳትደናገጡ ብለው እኛንም ትናንት ነግረውናል” አለኝ። ድንቄም መልካም አስተዳደር…..ብዬ በገባሁበት በር ፌደራል ፖሊሱም ሳይጠይቀኝ የጥበቃውን ኃላፊነትም ታዝቤ ወጣሁ።

 

 

በበጀት የለንም ስም ስንት ጠቃሚ ስራዎችን ሲመልሱና ድጋፍ አናደርግም ሲሉ የሚከርሙ ተቋማት እንዲህ ሰኔ ወር ሲመጣ የጠላት ገንዘብና ንብረት ይመስል ለማደፋፋት መሯሯጥ የኢትዮጵያ መንግስት መ/ቤቶች ክህሎት ብቻ ይመስለኛል። በአለም ብቸኛዋ ወይም የመጀመሪያዋ ሀገር የምንባልበት ቀንም ሩቅ አይሆንም። በተስፋ እንጠብቃለን። የመጀመሪያ…. አንደኛ…. የምንላቸውና የምንባልባቸው ነገሮቻችን አበዛዛቸው…ደስ ይላል…….።

 

 

አንድ ተቋም የምትሰራና የአንደኛው የስራ ክፍል ኃላፊ የሆነች ሴት ደግሞ በአንድ ወቅት ያለችኝን ልንገራችሁ “ለኔ የስራ ክፍል ለተለያዩ ጉዳዮች ከተያዘው ገንዘብ ውስጥ 3መቶ ሽህ ብር ትርፍ ተገኘ። ያንን ገንዘብ በወቅቱ ጠቃሚ ስራ መስራት እየቻልን በጀት ጨርሰሻል ሲሉኝ ቆይተው የበጀት መዝጊያ ጥር ወር (እነሱ በነጮቹ አቆጣጠር በጀት ስለሚጠቀሙ ነው) ላይ ይሄን 3 መቶ ሽህ ብር በሁለት ቀን ውስጥ ማወራረድ አለብን። ስለዚህ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ አሰሪበት አሉኝ። ያሳይህ እስኪ በ2 ቀን ውስጥ እንዴት ያለ ማስታወቂያ ነው ማዘጋጀት የሚቻለው? ብቻ የተባለውን ማስፈጸም ስለነበረብኝ ቢሮዬ ውስጥ ቀድሞ የተሰራ ማስታወቂያ አፈላልጌ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲተላለፍ በመስጠት 3 መቶ ሺ ብሩ በደቂቃዎች ውስጥ እንዲወራረድ ሆኗል።” አለችኝ። ይህን የምንትነግረኝ የክፍል ኃላፊ በቁጭት ስሜት ሆና ነው።

 

 

እንዲህ ነች ሀገሬ! ሰኔ ሲመጣ ዝናሩን ታጥቆ…ወጭ ፍለጋ…..ሰኔ የወራት መቁጠሪያ እኛው ሰዎች ለኑሮአችን እንዲመቸን የፈጠርነው ጊዜ መለኪያችን ነው። ታዲያ ምን በወጣው ነው ሰኔን ቁም ስቅሉን የምናሳየው? እኛው ቁም ስቅላችንን እንይ እንጅ ስሩበት ተብሎ የተሰጣቸውን ገንዘብ ዜጋው ሳይጠቀምበት ለባለቤቱ ሳያተርፉበት በሰኔ ወር ጥቂት ቀናት በማባከናቸው ምክንያት ለምንሰቃይ…. ከዓመት አመት ኑሯችን እንደግመል ሽንት ወደ ኋላ ለሚለው ምስኪን ዜጎች። ሙሾስ ለኛ…. ደረት መድቃትስ ለኛ ነው እንጅ ለምን ለሰኔ?

 

 

ድንቄም መልካም አስተዳደር…..ደግሞ ሰሞኑን እኮ መንግስታችንን ይፋዊ ይቅርታ እስከሚያስጠይቅ ድረስ የደረሰው የመልካም አስተዳደር ዘፈን የሚያስተጋባው (የገደል ማሚቶ) ድምፁ ገና ከጆሯችን አልጠፋም። ሙሉ ተቋም እየዘጉ ጉብኝት መሄድን ከመልካም አስተዳደር ጋር ምን አገናኘው ብትሉኝ እውነት ነው በኛ ሀገር አይገናኝም……እናስ ምንይጠበስ ለምትሉም አልቃወምም ምክንያቱም ኩይኒን እንደሚባለውና በአንድ ወቅት ለወባ በሽታ ፍቱን መድሀኒት የነበረ በኋላ ላይ በሰው የአጠቃቀም ስህተት ተላምዶት ከፈዋሽነት ወደ ምግብነት እንደተለወጠው መድሀኒት ነገሮችን ሁሉ ተላምደን …ተላምደን ….ተለማምደን……ተመስገን እያልን የምንኖር ዜጎች ሆነናል።

 

 

በነገራችን ላይ የተቋማቱ ሰራተኞች ጉዞ መሄድ የለባቸውም የሚል ሀሳብም እምነትም የለኝም። በእቅድና በፕሮግራም ይሁን ባይ ነኝ። የምን ሰኔ ላይ መዝፈን ነው። ሰራተኛው በጋራ ሆኖ መደሰቱማ ተግባብቶ ለመስራት እርስ በርስ ለመተዋወቅ በጥቅሉ ለኢንዱስትሪ ሰላም እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ታዲያ ዓላማውና ግቡ ይህ ከሆነ ለጉብኝትማ ከሰኔ ወር መስከረምና ጥቅምት አይሻሉንም። ሰራተኛውን ማኖ አስነክቶ በህዝብ ገንዘብ መነገድ፣ በድሆች ላብ ጮቤ መርገጥ….. ቤቱን ቆላልፎ የመስክ ስራ እንደሚወጣ ወንደላጤ አይነት መረጃ ሰጭ ባለሙያ እንኳን አንድ ሰው ሳያስቀምጡ ውልቅ ማለት ግን መታረም ይኖርበታል።  

                     

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
545 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 883 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us