ሻዕቢያ፣ በኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያቤት ላይ ለምን አነጣጠረ?

Wednesday, 22 June 2016 11:41

በሳምሶን ደሳለኝ

የሻዕቢያ መገናኛ ብዙሃን ሰሞኑን ለየት ያለ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ እንደሚጀምሩ እየደለቁ ይገኛሉ። ባልተለመደ መልኩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያቤትን ለይተው ለመምታት እያሰሉ ናቸው። ከሁሉ በላይ የሚገርመው የኢትዮጵያ ተቋማት የኢትዮጵያን ሕዝብ እያጠቁ በመሆናቸው በመቆጨቱ ሻዕቢያ ኃላፊነት በመውሰድ ነፃ ለማድረግ እንደሚሰራ ማስነገሩ ነው።

የሻዕቢያ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት “የኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያቤት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየፈፀመ ያለውን ግፍ እና በደል ለህዝብ እናቀርባለን” የሚሉት ይገኙበታል። ለየትኛው ሕዝብ እንደሚያቀርቡት ግን ግራ የሚያጋባ ነው። ይህም ሲባል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነው? ወይንስ ለኤርትራ ሕዝብ? የሚለውን መመለስ ነበረባቸው። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ከተባለ፣ የአዛኝ ቅቤ አንጓች ..ነው የሚሆነው። ለኤርትራ ሕዝብም ከተባለ የኤርትራ ሕዝብ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ባለቤት አይደለም። ቢያንስ ደግሞ የኤርትራ ሕዝብ የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት ሊመለከተው አይችሉም። ምክንያም የኤርትራ ሕዝብ በራሱ ጊዜ መጨረስ ያለበት ብዙ የቤት ሥራዎች በአገዛዙ ላይ ያሉበት በመሆኑ ነው።

ከኤርትራ ብዙሃን መገናኛ ጋር በመመጋገብ መረጃ የሚያጠናክረው የኢሳት ቴሌቪዥን ጣቢያ በበኩሉ “የኢትዮጵያ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት የስልጣን ደረጃ እና የመኖሪያ ቤታቸውን አድራሻ የተመለከተ ያገኘነውን መረጃ በቅርቡ እናቀርባለን” የሚል ማስታወቂያ ሲያስተላልፍ ስሰማ ግራ የሚያጋባ ስሜት ውስጥ ነው የጨመረኝ። በአንድ በኩል ኢሳት የግንቦት ሰባት የአርበኞች ግንባርን የሚዲያ ዘርፍ የሚመራ አካል መሆኑን ብረዳም ከሻዕቢያ ጋር በዚህ ደረጃ የተቀነባበረ መረጃ ልውውጥ ውስጥ ይገባል ብዬ አልጠበኩም።

ዳሩ ግን  የሰሜኑ የሀገሪቱን ክፍል ተደጋጋሚ የማወክ ተግባራት ያልተሳካለት ሻዕቢያ የደቡብ ኢትዮጵያን አቅጣጫ እንደ ሌላ አማራጭ በመጠቀም የሽብር ተግባር ለመፈፀም ሞክሮ ውርዴ እንደሆነበት የሚታወቅ ነው። ይህንን የማተራመስ ተልዕኮ የግንቦት ሰባት የአርበኞች ግንባር ኃላፊነት መውሰዱን በይፋ ማስታወቁን ተከትሎ ብዙ ባለድርሻ አካሎችን ያነጋገረ ነበር። ምክንያቱም ባልተለመደ መልኩ ለሻዕቢያ የሽብር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የግንቦት ሰባት የአርበኞች ግንባር ሽፋን ለመስጠት መንቀሳቀሱ ነበር። ሁለቱም የሽብር ኃይሎች ተደርገው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰየሙ አካሎች ቢሆኑም፤ ዋናው የሽብር አባት ሻዕቢያ ሲሆን የሽብር ባሕሪው ተጋሪው የግንቦት ሰባት የአርበኞች ግንባር መሆኑን ራሱ ግንባሩ ይፋ ማድረጉ ነው። የሁለቱንም ተልዕኮ ያመከነው ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት ተቋም መሆኑን አከራካሪ አይደለም። ቢያንስ አሸባሪዎቹ አይክዱም።

በተቋም ደረጃም ከተመለከትነው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያቤት ሀገር የመጠበቅ አቅሙ የትድረስ እንደሚሰርግ ሻዕቢያም ግንዛቤ የወሰደበት ጥሩ አጋጣሚ ነበር። በተለይ በቅርቡ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሲተላለፉ ከነበሩ ዘገባዎች በተጨባጭ መረዳት የቻልኩት የአርባ ምንጭ አካባቢን ለማተራመስ እቅድ ይዘው የነበሩ የሽብሩ ቡድን አባላት የሽብር ተልዕኮዋቸውን ለመፈጸም ከአስመራ ከተማ ጀምሮ ሲሰናዱ በኢትዮጵያ የደህንነት ኃይሎች ክትትል ስር መሆናቸውን ስሰማ የደህንነት መስሪያቤቱ የስርገት (Infiltration) አቅምን ለመገንዘብ ችያለሁ።

በዚህ ደረጃና መጠን ተሰርጎ የሚገባበት የሻዕቢያ አገዛዝ ከምን መነሻ እንደሆነ ሊገባ የማይችል ነጭ ፕሮፖጋንዳ የራሱን  የአፍራሽነት አጀንዳውን ሚስጥር አድርጎ ማሳካት ያቃተው አገዛዝ፣ የኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት የስልጣን ደረጃ እና የመኖሪያ ቤታቸውን አድራሻ የተመለከተ መረጃ አውቃለሁ ጠብቁኝ ሲል በኢሳት መደመጡ አነጋጋሪ አድርጎታል። ሻዕቢያ “ሀገራዊ ድሕነት” እያለ የሚጠራው የኤርትራ መረጃ ተቋም በኢትዮጵያ ላይ አቅዷቸው የነበሩ በርካታ የሽብር ተልዕኮዎች በተደጋጋሚ ሲከሽፉ ለተመለከተ ወይም ለሚያውቅ ማንኛውም አካል ሚስጥር አውቃለሁ ለሚለው ለኤርትራ መረጃ ተቋም ጥያቄዎችን ማንሳቱ አይቀርም። ይኸውም እንኳን ሚስጥር ማወቅ፤ ሚስጥር መያዝ መች ቻላችሁና ሚስጥር ለመንገር በቃችሁ የሚል ጥያቄ ማስቀመጡ አይቀርም። ከዚህ ውጪ የሻዕቢያ ሚስጥር ነጋሪነት በዓመቱ መገባደጃ ታላቅ ፋርስ ተደርጎ እንደሚወሰድ ወደ ፊት የምናየው ነው።

ቁም ነገሩ ግን ከሻዕቢያ አገዛዝ ጋር ስትራቴጂክ የሆነ ግብ የሌላቸው መሣሪያ ያነገቡ ኃይሎች፣ ሰላማዊ አየር መተንፈስ ብርቅ በሆነባት ዓለም ውስጥ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ከሌላው በጣም የተሻለ አንፃራዊ ሰላምንን ለማደፍረስ ሌት ተቀን ሲተጉ መመልከት በጣም አሳዛኝ ነው። በየትኛውም መመዘኛም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው። በተለይ ደግሞ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር ፈጽሞ በተቃርኖ ከቆመ ነብሰ በላ አገዛዝ ጋር ማበር የጊዜ ጉዳይ እንጂ ከተጠያቂነት የሚያስጥል ተግባር ተደርጐ የሚወሰድ አይደለም። ከዚህም በላይ በሰው ልጆች ላይ በሚፈጸም ወንጀል ከተወንጀለ አገዛዝ ጋር ማበር ቀርቶ፣ የሞራል ድጋፍ እንኳን መስጠት በዓለም ማሕበረሰብ ዘንድ የሚያስከትለውን መገለል ለማየት የወራት እድሜዎችን መጠበቅ በቂ ነው። ያን ግዜ ሁሉም ነገር ፀሐይ ይሞቃል።

የሆነው ሆኖ ከኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች መኖራቸውን መገንዘብ ግን ተገቢ ነው። እነሱም የሻዕቢያ አገዛዝ በአንድም በሌላ መልኩ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚከተለውን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እስከመቼ ድረስ ተግባራዊ እያደረገው እንዲቀጥል ይፈቀድለታል? የኢትዮጵያ መንግስትስ ይህንን ሁኔታ በዝምታ የሚከታተለው እስከ መቼ ነው? ከሻዕቢያ ጎን የተሰለፉ ኃይሎች ከበለጸጉ ሀገሮች የሚሰበስቡትን ገንዘብ የንፁሃን ኢትዮጵያውያን ደም ለማፍሰስ እና ህይወታቸውን ለማጥፋት አቅዶ ከተነሳ አገዛዝ ጋር ማበራቸው እንዴት ነው የሚታየው? የኢትዮጵያን መንግስት ልንወጋ ነው እየተባለ ውጪ ከሚገኘው ማሕበረሰብ ገንዘብ እየሰበሰቡ ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ኢንቨስትመንት ውስጥ ተሰማርተው ለሚገኙ ሃሰተኛ ፖለቲከኞችስ የኢትዮጵያ መንግስት ከለላ የሚሆናቸው እስከመቼስ ነው? ለእነዚህ እና ለሌሎች ጥያቄዎች መንግስት ተገቢውን ምላሽ ማዘጋጀት ያለበት ጊዜ ላይ ነን ቢባል ብዙ የተጋነነ መደምደሚያ አይሆንም።

ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያቤትን ሰርገው ለመግባትም ሆነ የተቋሙን ቅቡልነት ለመንሳት የሚደረጉ ሩጫዎች በተራ የፖለቲካ ጨዋታ የሚታይ ሳይሆን ከአጠቃላይ ከሀገሪቷ ሰላምና ደህንነት አንፃር ምላሽ የሚሹ ናቸው። ደግነቱ ተቋሙ አሁን ባለበት ቁመና በቁልቅለት ላይ የቆመውን የሻብዕያ አገዛዝ ሴራ ከማክሸፍ በላይ፣ ለቀጠናው ሰላም እያደረገ ያለው አስተዋፅዖ እውቅና ሊቸረው በሚገባ ደረጃ ላይ ተቀምጦ መገኘቱ ነው። ይህ ማለት ግን ተቋሙን ለሶስተኛ ወገኖች አሳልፈው ሊሰጡ የሚችሉ አፍራሽ ኃይሎች አይኖሩም ከሚል አጠቃላይ መደምደሚያ ላይ የሚያደርስ አይደለም።   

በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያቤት እና በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ላይ እየተበተኑ ያሉ አፍራሽ መረጃዎች በሶስተኛ ወገኖች እና እምቅ ፍላጎቶች ባሏቸው ወገኖች አለመረጋጋት ለመፍጠር ሆን ተብለው የተዘየዱ መሆናቸው ግልፅ ነው። የየትኛውም ወገን ፍላጎት ግን፣ ከሰላም በላይ ሊታይ አይችልም። መጨበጥ እስከምንችለው ድረስ ተጉዘን ሰላማችን ለመጨበጥ መስራት ምርጫ አልባ ምርጫችን መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።¢

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
633 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 893 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us