ሰው የፍላጎቱ ባሪያ ነው

Wednesday, 29 June 2016 12:41

 

ወሰንሰገድ መሸሻ በላቸው / This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. /

እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ ችሎታ፣ ልማድ፣ ፍላጎት፣ ዝንባሌ፣ የአነጋገር ስልት ወዘተ… አለው። ሰው እነዚህ ግላዊ ባሕሪያት እንዳሉት ሁሉ ሰዎች የአንድ ማኅበረሰብ አባል፣ በቀለማቸው፣ በፆታቸው፣ በእድሜያቸው፣ የአንድ መደብ አባል፣ የአንድ ሐገር ዜጋ ወዘተ… በመሆናቸው ደግሞ ከሌሎች ጋር የሚዛመዱባቸው ሁለንተናዊ ባሕሪያት አሏቸው።

የባሕሪ አጀማመር ልክ እንደስውር ክር ነው። ሁል ጊዜ ግን ድርጊቱን ደጋግመን ስንፈፅመው ክሩን እናጠነክረዋለን። ጠንካራ ገመድ ሆኖ አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን እስኪቆጣጠር ወይም እስኪአስር ተጨማሪ ቀጫጭን ክሮች ባናት ባናቱ እንገምድበታለን/ኤሪሰን ስዊት ማሪየር/።

አልዱስ ሊክስሊ ልምድ ለሰው የሚሰጥ ነገር ሳይሆን ሰው በደረሰበት ወይም በሆነለት ነገር የሚሰራው ነው ማለቱና ሆራሶ ማን ደግሞ ልማድ እንደ ወፍራም ሽቦ መሆኑንና በየቀኑ በላይ በላዩ እንሸርበውና በመጨረሻም ልንበጥሰው የማንችለው ጥንካሬ ይኖረውና ይተበትበናል ብሎ አስፍሮታል። በዓለም ላይ የተከሰቱ እያንዳንዱ ታላላቅና ወሳኝ ክስተቶች የተወሰኑ ታላላቅ ፍላጎቶች ውጤት መሆናቸውን ምሁራኑ የተስማሙበት እንደሆነ መገመት ይቻላል።

ግላዊ ልዩና ሁለንተናዊ ባሕሪያት የማይነጣጠሉና እርስበርስ የተያያዙ ናቸው ብለው ምሁራኑ ያስተምራሉ። በሂደት በሚከሰቱ የተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ በውስጡ የታመቁ ፍላጎቶቹ መጀመሪያ እንደተፈጠረው፣ ባለበትና ሳይለወጥ በነበረበት እንዲቆይ አልፈቀዱለትም።

በፍላጎቶቹ አስገዳጅነት በሂደት ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ፣ ከቀላል ወደ ውስብስብ በመሸጋገር በማደግ ወይም በፍላጎቱ ቆስቋሽነት በመለወጥ ላይ በሚገኝ በማንኛውም ነገር ክንዋኔ ከእንስሳነት ወደ ሰለጠነ ፍጡርነት በረጅም የዘመናት ሂደት ለመለወጥ ችሏል።

በጥንታዊ የጋርዮሽ ስርአተ ማኅበር ኅብረተሰብ በመደብ ከመከፋፈሉ በፊት የነበሩት የአምልኮ ዓይነቶች ነፍሳዊና ሥነ ተረት ይባሉ ነበር። የሰው ልጅ በፍላጎቱ አማካይነት እራሱን ከተፈጥሮ መለየት የቻለ ቢሆንም ሰዎች ስለራሳቸውና ስለተፈጥሮ የነበራቸው እውቀት ግን እጅግ ዝቅተኛ ስለ ነበር በተፈጥሮ ላይ መጠቀምና ቁጥጥር ለማድረግ ገና አልቻሉም ነበር።

ሰው እራሱም እንደእንስሶቹ በየዱሩ እየኖረ ተፈጥሮ ከምትለግሰው ፍራፍሬና አቅማቸው ደከም ያሉትን እንስሳት እየገደለ ጥሬውን እንደአውሬ እየጋጠ፣ በዝናብ፣ በቁርና በሐሩር በዱር አውሬዎች ከሚደርስበት ስቃይና መከራ አሳልፎ በሂደት እራሱን ታድጓል።

እንዲህ አይነቱ ሁኔታዎች ናቸው ፍላጎቱን እያጦዙት የቀጠሉት። በምድር ካሉ አውሬዎች ለመዳን ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ማደርን፣ ተፈጥሮ ያዘጋጀቻቸውን ዋሻዎች ለመጠለያና ለመኖሪያነት ለመጠቀም ሞከረ። የመጀመሪያው የሰው ቡድን በወቅቱ ታላቅና ማመን የሚያስቸግር ፈጠራ ወይም እውቀት ተደርጎ በመወሰዱ ከነዚህ ያገኘውን የግንዛቤ ፍንጭ የተሻለ ጎጆ ለመቀለስና ጠንካራ አድርጎ ማዘጋጀቱ ከጥቃት መዳኑን ስለሚያረጋግጥለት፣ የሰራውን ቤት አውሬ ሲፈትሸውና የሚደፈር ሲሆን እንዳይደፈርበት እያጠበቀ ወደ ግንባታ መዳረሻ ተጠጋ።

የሰው ህልውና መሰረቱ የተገኘበት  እትብቱ የተቀበረበት አካባቢው ነው። የእድገቱና የመሻሻል ምንጩም ሆነ መነሻው አካባቢውና ገደብ የለሽ ፍላጎቱ የሚፈጥሩበት ጫናዎች ናቸው። ስለዚህ ሰውን ከአካባቢው ነጥሎ ማየት ያስቸግራል። በተፈጥሮና በክስተቶች መካከል የማያቋርጥ ትስስርና መደጋገፍ እንዳለ ሁሉ በሰውና በክስተቶች መካከልም እንዲሁ ግንኙነትና ትስስር መኖሩ ግድ ስለሆነ ነው ፍላጎቱንና ምኞቱን ያናረው።

ጥንታዊ ሰው ፍራፍሬ በመልቀም፣ አውሬ በማደንና አሳ በማስገር ሆዱን ለመሙላትና ህልውናውን ለማቆየት ሲጥር ኖሯል። እነዚህን የምግብ ፍላጎቱን በተሻለ ሁኔታ ለማሟላት ወንዶቹ የሚበላ አውሬ ፍለጋ ከሚኖሩበት ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደው ወደ ሚስቶቻቸው ለመመለስ እንዳይቸገሩ፣ አቅጣጫ እንዳይስቱና መንገዱ እንዳይጠፋባቸው በአካባቢያቸው አንዳንድ ምልክት መጠቀም ቻሉ። ይህ የምግብና የመኖር ፍላጎታቸው አንዳንድ ነገሮችን ለመፍጠርና የሚከብዳቸውንና የሚቸገሩበትን ነገር ለመፍታት መነሻቸው ሆነ።

በ6ኛውና በ4ኛው ዓመተ ዓለም በመጀመሪያ ፓታጎረስ ከዚያም አርስቶትል የሚባሉ ሁለት የግሪክ ፈላስፎች መሬት ክብ ናት ብለው አመኑ። ፓታጎረስ መሬት የምትሽከረከረው በእሳት ዙሪያ ነው ብሎ ሲያምን፣ ሔሮዶተስ የተባለው ግሪካዊ የታሪክ ምሁር በ6ኛው መቶ ዓመት ስለመሬት መንቀጥቀጥና የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ምክንያቶች የራሱን ግምታዊ ዘገባ ያቀረበና ስለታወቁት ወንዞች የጉዞ አቅጣጫና ስለናይል ጎርፍ ፅፏል። ቱሲዲዲስም እንደእሱ ፅፏል። ፍላጎት እየመጠቀና እየናረ በመምጣቱ ሄራክሊተስም ስለአለም ጂኦግራፊ የፃፈ ሲሆን ከሔሮዶተስ ቀደም ብሎ የኖረው ሔካይተስ የግሪክን የኋላና የዘመኑን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የፃፈና የዓለም ካርታን ያዘጋጀ የታሪክ አዋቂ ነበር።

ሮማውያን በጥንት ዘመን ግዛቶቻቸውን ለማስተዳደርና ወታደሮቻቸው የሚጓጓዙበትን መንገድ ለማወቅ መንገዶችን የሚያሳዩ መፃሕፍትንና የመንገድ ካርታዎችን በማፈላለግ የሀገሪቱን ፍላጎት ለማሟላት ምሁራኑ በደንብ በማጥናታቸው የተሻሉ ካርታዎችን ለመስራት በቅተዋል።

የአውሮፓ ነጋዴዎች ከአረቦች፣ ከቅርብና ከሩቅ ምስራቅ አገሮች፣ ከሕንድና ቻይና ጋር ለዘመናት የንግድ ግንኙነት ነበራቸው። ነጋዴዎቹ ሲጓዙ በአብዝሃኛው እንደ ምልክት ይጠቀሙ የነበረው የአህጉር ጠረፎች አካባቢን እንደተራራ፣ ወንዞች የመሳሰሉትን እንደነበርና ሰማይ በደመና ካልተሸፈነ ኮከቦችንና ፀሐይንም ይጠቀሙ ነበር።

ይህ የሰው ልጅ የመንቀሳቀስና ነግዶ/ከስቦ የመበልፀግ ፍላጎቱ አቅጣጫ ጠቋሚ ኮምፓስን መስራት አስችሎት ፕቶሎሚ የተባለ ግሪካዊ የጂኦግራፊና የከዋክብት ጥናት ባለሙያ እስከ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያዘጋጀው የተሻሻለ ካርታ በዓለማችን በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን አቀለለላቸው። ተጓዦች የሚያርፉበትና በየደረሱበት የሚመገቡበት ቦታ ማዘጋጀትንም ፍላጎት ጠየቀ።

ክርስቶፈር ኮሎምበስ የ40 ዓመት ሙሉ ሰው በሆነበት እድሜው ነሐሴ 7/1492 ከእስፓኝ ተነስቶ አሜሪካን ሳላሳልቫዶርና ኩባን ማግኘቱ፣ የተጓዘበትን መንገድ የሚለካባቸው 2 መሳሪያዎችን ተጠቅሟል።

ከ1497-1498 ቫስኮ ደጋማ ከፖርቱጋል ተነስቶ አፍሪካን በመዞር ወደ ህንድ መድረሱና አዲስ የባሕር መንገድና መጓጓዣነቱን አሳወቀ። ከመስከረም 20/1519-1522 ፈርዲናንድ ማጄላን ከስፓኝ ተነስቶ በደቡብ አሜሪካ በኩል አድርጎ ዓለምን በመርከብ ዞረ። መሬት ጠፍጣፋ ሳትሆን ክብ መሆኗም ተረጋገጠ። ማርቲን ቤ ሀይም የመጀመሪያውን ሉል ሰራ።

ማርኮፖሎ ከ1246-1316 የኖረ በቬነስ ከተማ የተወለደ ጣሊያናዊ ስለምስራቅ አገሮች ያስረዳ የመጀመሪያው ሰው ነው። አቡ አብዱላሂ/ኢብን ባቱታ በ1296 በታንጀር በርበር ከሚባሉ ጎሳ በፍሪካዊ መንገደኛ ነበር። ማርኮፖሎ ካያቸው ሃገሮች በበለጠ ኢብን ባቱታ ብዙ ሐገሮችን አስሷል።

ሰዎች እንደተፈጠሩ ባሉበት ተወዝፈው ባለመገኘታቸውና ሰላምና አቅል የሚያሳጣቸው ፍላጎታቸው እንዲንቀሳቀሱ ስላስገደዳቸው ታሪክ መስራትና ታሪካቸውን መመዝገብን በመማራቸው ያለፈውን የነገሮችን ምንጭ እድገትና ውድቀት በተከታታይ የሚያውቁበት ሆኖ ተቀበሉት።

ታሪክ በመረጃ ላይ በመመርኮዝ የሰው ልጅ በዚህ ዓለም ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያከናወናቸውን የስራና ማሕበራዊ ሕይወት እንቅስቃሴዎች ማለትም እንደእንስሳት እርባታ፣ እርሻ፣ ንግድ፣ እደ ጥበብ ግኝቶችን በዝርዝር የሚያቀርቡበት ሆነ።

ኅብረተሰቡ ከእራሱና ከአካባቢው ጋር የሚያደርጋቸውን ግንኙነቶች በተከታታይነትና ሥርአትን የተከተለ የሰው ልጆች ድርጊት በለውጥ መልክ ከጊዜው ጋር የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ይመዘግባል። ያለፉትንና የተከሰቱትን ድርጊቶች ለሌሎች ለተተኪ ትውልድ የሚያስተዋውቅና ያለፈውን የሰው ልጆች እድገት ማነፃፀሪያና የወደፊቱንም የሰው ልጆች እድገትና ውድቀት መተንበያ አድርገው በመጠቀም ፍላጎታቸውን አሟሉበት።

የሰው ልጅ ከቦታ ቦታ ለፍላጎቱ መሟላት ብሎ የሚያደርገው ጉዞ በድካም፣ በበሽታ፣ በተለያዩ መከራዎችና በስቃይ የተሞሉና አታካችነታቸውን መገንዘብ በመቻሉ እነዚህን ሊያቃልል የሚችልበትን ዘዴ መቀየስ ተገዶ ለዘመናዊ ትራንስፖርት መነሻው ሆነውታል። በአካባቢው የሚገኙትን የዱር እንስሳት እያላመደ ተሳፈረባቸው፣ እቃውን ጫነባቸው፣ እያረደ በላቸው፣ እያለበ ጠጣቸው።

የጥንቱ ሰው በድንገት ያገኘውን እሳት በመጀመሪያ የሚፈልገውን ማድረግ የሚያስችለው ማስፈራሪያውና መከላከያ መሳሪያው አድርጎ ለጊዜው እሳቱ በለላቸው ፍጥረቶች ላይ የበላይነትን ተቀዳጀበት። በታጠቀው እሳት በአዲሱ መሳሪያ ማስገበር በመቻሉና ኃይልና ጉልበት ስለሆነውም ቀስበቀስ ምግቡን እያበሰለ መመገብ ቻለ። አፈርን በእሳት ወደ ብረትነት በመቀየር መገልገያም ሆኑ ማጥቂያ መሳሪያዎችን በመስራት የማምረቻ፣ የመጓጓዣና የተሻሉ ነገሮችን በመፍጠር በለውጥ ጎዳና እንዲነጉድ አደረገው።

እሳቱን ማታ እየሞቀ እራሱን ከብርድ ከመከላከሉ ባለፈ አውሬዎችም እንዳይጠጉት ጠብቆት ቢኖርም አካባቢውን በንፋስ ግፊት ለቃጠሎ እስከመዳረግ በማድረሱና ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ እያዳፈነና ሳይጠፋበት ይዞ እየተጓዘ መገልገሉ ስጋት ፈጠረበት።  ያለ ሳይንስ በድንገት ተገኘውን እሳት በሳይንስ ድጋፍ በክብሪትነትና በላይተር መልክ እኪሱ ይዞ እስከመዞር ያስቻለው የማይበርደውና መጨረሻ የለለው ፍላጎቱ ነበር።

ሳይንስ ነባራዊውን ዓለም እና የተፈጥሮ ሕግጋትንና ክስተቶችን ለማብራራትና ለመገንዘብ የሚያስችለንን እውቀት በምልከታና በሙከራ የምናገኝበት ዘዴ ነው። መላምትና ሃሳብ እያደገ ትርጉም የሚሰጡበትን ሁኔታ ፈጠረለት።

ቴክኖሎጂ ማለት ደግሞ የአንድን ሕብረተሰብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታትና የኑሮ ደረጃውን ለማሻሻል የሚያስችል፣ የሸቀጦችና አገልግሎቶች አመራረት፣ ከአጠቃቀም ጋር የተጣመረ እውቀት፣ የድርጊት ጥበብ/ ኖውሃው/ የአሰራር ዘዴና ሥርአት ነው።

በነዚህ እየዳበሩ በመጡት ክህሎቶቹ እየታገዘ ማምረት በመቻሉ የሸቀጥ ምርት ተከሰተ። ለራስ ፍጆታ ሳይሆን ለሽያጭ ወይም ለገበያ ተብሎ የሚመረትና የሰዎችን የተለያየ ፍላጎት ለማርካት የሚችል የሰዎች የሥራ ኃይል ውጤት የሆነ እቃ፣ ነገርና የመሳሰሉት መለዋወጦችን ቀስበቀስ እያዘመነ አስኪዶታል።

ማናቸውም ሸቀጥ ሁለት ጠባዮች አሉት። እነሱም የጠቀሜታ እሴትና የልውውጥ እሴት ናቸው። የሸቀጥ በሸቀጥ ለውጥ ጥንታዊ የሆነ የሸቀጥ ልውውጥ መልክ ነው። ኅብረተሰቡ በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላይ በነበረበት ጊዜ የሸቀጥ ልውውጥ ሥርአት የያዘ አልነበረም። አንድ ሸቀጥ በሌላ ሸቀጥ/ በአገራችን እህልን በእህል፣ አሞሌ ጨውን እንደ ሸቀጥ መግዢያ መጠቀማቸውን ልብ ይሏል። አንድ እቃ በሌላ እቃ በአጋጣሚ ወይም እንዳስፈላጊነቱ ይለወጥ ነበር/አንድ በሬ በሁለት እንቅብ እህል፣ አንድ ጦር በአንድ ወይም ከዚያ በላይ ሞፈር/ ይለዋወጡ ነበር።

የገንዘብ ፍላጎቱን ያመጣው እቃ በእቃ የመቀያየር ግብይቱ ለመለዋወጫነት የሚጠቀሙባቸውን በቀላሉ ለመያዝ የማይመቹ እየሆኑ መሄዳቸው ሲሆን እንስሳትን መንዳት፣ በከረጢት እህል መሸከም፣ አንደኛው ግለሰብ ሌላኛው የያዘውን እቃ የሚፈልገው አለመሆኑ በወርቅ፣ ብርና መዳብ ባሉ ውድ ብረቶች በመጠም መገበያየት ጀመረ።

ፍላጎት እሚገዛው የሰው ልጅ ስግብግብነት ተጭኖት በገበያው የማጭበርበር ሂደትን አከለበት። ከማእድናቱ ግብይት ወጥቶ ወደ ሳንቲም መስራት የተሸጋገረው ከ700 ዓ.ዓ. ቀደም ብሎ በሊዲያ /ቱርክ እንደነበር መዛግብት ያወሳሉ።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ወደ እየሩሳሌምና ፍልስጤም የሚገቡ ሰዎች የተለያዩ ሳንቲሞችን ይዘው በመምጣታቸው በገንዘብ ለዋጮች ፍላጎት ማደግ ንግድ ቤት አቋቋሙ። የውጭ አገር ሳንቲሞችን ተቀባይነት ባለው ገንዘብ ለመለወጥ ከመጠን ያለፈ ክፍያ በመጠየቅ በሂደት የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት መስጠት፣ የቁጠባ ስርዓት ዘረጉ፣ ብድር መስጠትና በባንኩ ውስጥ ገንዘብ ለሚያስቀምጡ ሰዎች ወለድ በመክፈል የገንዘብን ስርአት አዘመኑት።

ይህ ልውውጥና ግብይት ሰዎች ገቢ እያገኙበት መሆኑን የተረዱት መንግስታት፣ መንግስት ባመቻቸው መንገድ ኢኮኖሚው ያመነጨውን ሰዎች በመጠቀማቸው ሰዎች ሁሉ ካገኙት ገንዘብ ለመንግስት እንዲያካፍሉ ግብር በመጣልና ቀረጥ በመቅረጥ ሌሎች ስርአቶችን እየተከሉ የመንግስትን ፍላጎት ለማሟላት መንቀሳቀስ ተጀመረ።

ካርል ጃንግ እንዳለው ካለ ጥልቅ ስሜት ጨለማን ወደ ብርሃን፣ ደንታ ቢስነትን ወደ እንቅስቃሴ መቀየር ፈፅሞ አይቻልምና በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በጂኦግራፊ፣ በታሪክና መሰል ዲስፕሊኖች እራሱን እያነፀ የመጣው የሰው ልጅ የፍላጎቱ ባሪያ መሆን በመጀመሩ ባቋራጭ የሚከብርበትን መላ በመቀየስ የንግድ ስርአቱንም አዘመነ።

ይዞ መገኘትና ከሁሉም የበለጠ ሃብታም የመሆን ራእይ ሰንቆ ሕገወጥ ንግድንና ሕጋዊውን እያጣቀሰ ገንዘብና የግል ጥቅም መጋበስና ማግበስበስን መርሁ ማድረግ ጀመረ። በመንፈሳዊው ዓለምም ራሱን በማስገባት ከፈጣሪው/ ከአምላኩ ጋር የሚተሳሰርበትን መንገድም አመቻቸ። ሰዎች ግዑዝ ነገሮችን ሁሉ ሕይወትና አእምሮ ያላቸው አድርገው በመገመት ለሚገጥሟቸው የተለያዩ ችግሮችና ጉዳዮች የተለያዩ ጣዖቶችን እየሰሩና ንግርት ወይም ተረት እየፈጠሩላቸው መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ይመሩ ነበር። ለውሃ ሙላት፣ ለጦርነት፣ ለሰላም፣ ለፍትሕ ወዘተ…የተለያዩ ጣዖቶችና ንግርት ስለ ነበሯቸው ጣዖቶቻቸው እንዲታደጓቸው ይማፀኗቸው ነበር።

ከረጅም ጊዜ በኋላ የሰው ልጅ ስለራሱና ስለተፈጥሮ ቀስበቀስ የሚረዳበት አጋጣሚዎች እየተፈጠሩ በመምጣታቸው ፍላጎቶቹ እያነሳሱት በተለያየ አቅጣጫ በተፈጥሮ ላይ ቁጥጥሩን እያሳደገና እያሰፋ መጣ። በልዩ ልዩ የአምልኮ ጣዖቶች ላይ የተመሰረተው እምነቱና እውቀቱ በአንድ ረቂቅ አምላክ/ፈጣሪ በአዳዲስ ኃይማኖት አስተምህሮ ላይ ወደ መመስረት አዘነበሉ።

ሰው በከሳቴ ብርሃን ተሰማ አማርኛ መዝገበ ቃላት ሰባት የተፈጥሮ ባሕርያት በሥጋ አራት በነፍስ ሶስት ባሕርያት አሉት። 4ቱ ሥጋ/ ነፋስ፣ እሳት፣ ውኃና መሬት 3ቱ ደግሞ ነፍስ/ ተናጋሪነት፣ ዐዋቂነትና ሕያውነት ናቸው። ሰውነትን ደግሞ በሰውነት/አካልና እውቀት መገኘት ሰባቱን ባሕርያት አስማምቶ ሰው መባል በቂ አካልና እውቀትን ይዞ መገኘትና የሰው ልጅ መባል ነው ብሎታል።

በማርክሳዊ ሌኒናዊ መዝገበ ቃላት በሥነ ሕይወታዊ አመለካከት ሰው የተፈጥሮ እድገት ከፍተኛው ውጤት ነው። ሰው ከዳበሩ እንስሳዎች የሚለየው በማሰብና በንግግር ችሎታው ነው። እንስሶች በአካባቢያቸው ላይ ያላቸው ክንዋኔ በደመነፍስ የሚወሰን ሲሆን የሰው ክንዋኔ ግን የሚወሰነው በስሜቶቹ፣ በፍላጎቶቹና በፈቃዱ ነው። ሰው ስለ ተፈጥሮና ስለኅብረተሰብ ሕግጋት ባለው የእውቀት ደረጃ እንደሆነና ሰብእ ነፍስና ሥጋ ያለው፣ ነፍሱ ከሥጋው አንድ የሆነ ሥጋ ብቻ ወይም ነፍስ ብቻ ያልሆነ ብሎ ሰብን ተፈጥሮ ካስገኛቸው እውነታዎች ሁሉ የተለየ ቦታ፣ ሚና፣ ችሎታ፣ ፍላጎትና  ክብር ያለው ፍጡር ነው ብሎ አስፍሮታል።

ይህ ሰው ከጣዖት አምልኮ እየወጣ በሂደት በአምላኩ/በፈጣሪው በሚያመልክበት ሃይማኖት ላይ ተመስርቶ ዓለምን በማናቸውም ረገድ በመምራትና በመተንተን፣ እራሱን ሰውን ጨምሮ ተፈጥሮ ከሷ በላይ በሆነ ታላቅ መለኮታዊ ኃይል የምትገዛና የምትመራ እንደሆነች መገንዘብና በፅኑ ማመን ቻለ።

የሰው ልጅ ኑሮ የሚወሰነው ከሱ ውጭ በሆኑ ምክንያቶች መሆኑን አመነበት፣ እናም በአምላኩ/ በፈጣሪው ፍቃድና ይሁንታ ላይ ህልውናውን ቢመሰርትም ፍላጎቱ ግን እነዚህን ፅኑ እምነቱን ሳይቀር እየተፈታተኑት አምላክ የለም፣ እኔ ራሴ አምላክ ነኝ ወደሚል ግብዝነት መለወጥና ኃይማኖታዊ ሕልውናነትና ኢእምነታዊ ህልውናነት በሚል የልዩነት መስመርን አበጅቶ መራቀቅ ጀመረ።

የሰው ልጅ በኅብረተሰብ ውስጥ ሲኖር ስለአካባቢው የሚኖረው ግንዛቤና በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ኃላፊነት የሚያውቅበት፣ ግለሰቡም ስለራሱ ድርጊትና ጠባይ የሚያጤንበት ልዩ ልዩ መልክ ያለው ክስተታዊ ስሜት የሚሰጠው ኅሊና አለው።

የሰው ልጅ አንጎል/አእምሮ የማሰቢያ ኅሊናውን መግዢያ፣ የእውቀት ማኅደሩ/ቋቱ ነው። ለሰው ልጅ አንጎል ማለት እራሱ፣ እራሱ ማለት ደግሞ አእምሮው ነው። የዚህ የአንጎሉ መብሰል፣ መበልፀግና የመገንዘቡ ልክ በወሰን አልባው ፍላጎቱ መራሽነት የሚመኛቸውን፣ የሚፈልጋቸውን፣ ያያቸውንና የደረሰባቸውን ሁሉ ለራሱ ለማድረግ ያነሳሳዋል። ሰው ካለ አንጎሉ የሕይወትን ጣእም ጨርሶ አያውቀውም። ስሜት አልባ ይሆናል። አስቦ ስራ ሊሰራና ሊኖር አይችልም። አንጎል የደስታ፣ የፍቅር፣ የጉጉት ስሜት ህሊናንና ባሕሪን የሚያዝዝ፣ ጉዳትንና እርካታን የሚገነዘብ ዋናው የሰው ልጅ አካል ነው።

አእምሮ ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍንበት ከተደረገ /ሌላ ፍላጎቱ ካልተጫነበት በስተቀር/ የተስተካከለና ሚዛናዊ የሆነ የአካልና የአእምሮ ጤንነት እንዲኖር ያደርጋል። 3 ፓውንድ የሚመዝነው አንጎላችን 13 ቢሊዮን ሕዋሳት አሉት። ከዚህ ውስጥ በቀን 50.000 የሚያክሉት ሕዋሳት ይሞታሉ። የሰው ልጅ በሕይወቱ 10 በመቶውን ብቻ ስለሚጠቀምባቸውና ብዙ ተቀማጭ/ተጠባባቂ ህዋሳት ስላሉት አይጎዳም። ሰዎች 90 በመቶ የሚሆነውን የሚማሩትን ይረሱታል። ሁሉም አይነት መድኃኒት በአንጎል ላይ አንድ አይነት ውጤት አለው። ምክንያቱም ልብ ለአካል ከሚያሰራጨው ደም አንድ አምስተኛው ያህሉ ወደ አንጎላችን ስለሚሄድ ወደ ደም የሚገባ ነገር ሁሉ ወደ አንጎል ይሄዳል። ጥልቅ አገልግሎት ያለው አንጎል ለፍላጎት ማበጥ ታላቁ የጀርባ አጥንት ስለሆነም ዛሬ በዳሰሳ አነሳናው። በአንድ ሰው ጭንቅላት ውስጥ ያለው አንጎል በአንድ ሐገር ተብሎ ከተዘረጋው የቴሌ መረብ የበለጠ መስመሮችን የያዘ የተወሳሰበ መዋቅር ይዟል።

ጥሩ ስሜቶች ለክፉ ነገር መነሻ ይሆናሉ። ጥያቄዎችን የሚጠይቅ ሰው መልሶችን ማስወገድ አይችልም። አዶልፍ ሂትለር የጀርመን ሕዝብ ጦረኛ አይደለም ግን ጀግና ነው። ማለትም ጦርነትን አይፈልግም እንጂ ከመጣ ግን ወደኋላ አይልም። እጅግ ሰላም ወዳድ፣ ነገር ግን በክብሩ እና በነፃነቱ ቀልድ የማያውቅ ሕዝብ ነው ብሎ የተናገረ ሰው ነው። በተገላቢጦሹ ግን ማንም ሳይነካው በራሱ ፍላጎት ተገፋፍቶ የዓለምን ሕዝብ ሰላም የነሳ፣ ያወከና በጅምላ የፈጀ፣ ሰዎችን እንደ አይጥ የቤተ ሙከራ እንስሳ አደርጎ የዘለዘለና የከተፈ እኩይ አንጎልን የያዘ እቡይ ሰው ነበር።

ሰይጣናዊ መንፈስ መላ አካሉን የወረረውና በደሙ ውስጥ የሰረፀበት ግለሰብ ነው። ሂትለርን ለዚህ ሰይጣናዊ ተግባሩ ያነሳሳው ምርጦቹ ሰዎች እኛ ጀርመኖች ብቻ ነን የሚለው መናጢ ፍላጎቱ ሁለንተናውን ስለገዛውና የስልጣን ጥሙ ማየሉ መሆኑን መገመት ተችሏል።

ፍላጎት የሚለው የአማርኛ ቃል በእንግሊዝኛው ብዙ አቻ ፍቺዎችን፣ ትርጉሞችንና ገላጭ ቃላቶችን ይዞ ይገለገሉበታል። ዊሽ፣ ዲዛየር፣ ዋንት፣ ኒድ፣ ዊል/ኢንተረስትና ኢንክሊኔሽን በሚሉ እንደአገባባቸውና እንደየስሜታቸው ፍላጎትን እንዲገልፁ አድርገው ይሰሩባቸዋል። ለማንኛውም ጠቅለል አድርገን ስናየው ፈለገ አሰበ፣ የሰውን ሊቀማ ሊሰርቅ ከጀለ፣ ፍለጋ የጠፋውን መሻት ለማግኘት መጣርን ይገልፃል። የሰውን ሚስት ወይም ባል መመኘት/ መፈለግ/ መሻት አንዱ የፍላጎት ደርዝ ነው።

ፍላጎት ወደ ንቁና አስቀድሞ ወደተወሰነ ክንዋኔ የተመራ ተግባርና አንድ ነገር መሆን አለበት ወይም መደረግ አለበት የሚል ግምት ወይም ውሳኔ ነው። ባጭሩ የተወሰነ ክንዋኔ ወይም ክንዋኔዎችን ለማካሄድ ሰዎች የሚኖራቸውን ንቁና ቁርጠኛ ውሳኔን የሚገልፅ ፅንሰ ሃሳብ ነው።

ሰው ደረጃ በደረጃ ከእንስሳነት አሁን ወደአለበት ከፍተኛ እድገት ደረጃ መድረሱና መለወጡ ይታወቃል። ስለነገሮች ልናውቅ የምንችለው ከህውሰታችን በመነሳት በመሆኑና አንድ ነገር በእርግጥ ይህ አይነት ጠባይ አለው ብለን ለመናገር የምንችለው በተደጋጋሚ ሲገለፅልን በመሆኑ ልምድ የእውቀት ብቸኛ ምንጭ መሆኑን ብዙዎቹ ይስማሙበታል።

እያንዳንዱ አካል ወይም ክስተት በጠባይ፣ በጊዜና በቦታ ከሌላው የሚለይበት ባሕሪ ልዩ ጠባዮች  ይባላል። በተፈጥሮ ነገሮች በተናጥል የሚኖሩ ቢሆኑም እርስ በርሳቸው የማይገናኙ ግን አይደሉም። እያንዳንዱ ነገር ከሌሎች ጋር የሚያመሳስለው ሁኔታ አለ። ከሌሎች ጋር የወል ባሕሪያትን ይጋራል። ይህ በነገሮች መካከል ያለ ተመሳሳይነት በአንድ አካል ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ክፍሎች ወይም በሁለት አካሎች መካከል ያለ ግንኙነትና ተመሳሳይነት የክስተቶች ሁለንታዊ ባሕሪ ነው።

እኛ ሰዎች ባለንበት ሥርአተ ፀሐይ ውስጥ የሚገኙት ፀሐይ፣ ዘጠኙ ፕላኔቶችና ጨረቃዎቻቸው ብቻ አይደሉም። ጅራታም ኮከቦች /ከበረዶና ከአቧራ የተሠሩ አካላት/፣ ንዑሳን ፕላኔቶች /ትንንሽ ወይም አነስተኛ ፕላኔቶች/ እና ሰማይ ወረዶች /አብዛኞቹ የንዑሳን ፕላኔቶች ስብርባሪዎች ናቸው/ እኛ ባለንበት ሥርአተ ፀሐይ ውስጥ ይዞራሉ።

በፍላጎት የሚነዱ ሰዎች ጠቢብ/ሊቅ ሆነዋል። ራስህን ብቁ አድርገህ ስትገኝ ስትፈልገው ያጣሃው ሲፈልግህ ታገኘዋለህ ብለው ይንቀሳቀሳሉ። ፍላጎታቸው የማይበርድና ማለቂያ የለለው በመሆኑ ሳይንቲስቶች ምድር ላይና በከርሰ ምድር ውስጥ/በምድር ሆድ እቃ/ ያለው ሃብት አልበቃቸው ብሎ ሌላውን ሁሉ ሊገለገሉበት ያስሳሉ። ሊቆቹ ምድር ከጠፈር ለሚወረወሩ አካላት የተጋለጠች እንደሆነች ከተረዱ ረጅም ጊዜ ሆኗቸዋል። በተደጋጋሚ የተደበደበውን የጨረቃ ገፅታ በመመልከት ብቻ ዝብርቅ ባለበት አካባቢ እንደምንኖር መገንዘብም ችለዋል።

ከባቢ አየር እንዲሁም በስፍሃን ቴክቶኒካ /plate tectonics/ እና በመሬት መሸርሸር አማካይነት በምድር ገፅ ላይ የሚካሄደው የማያቋርጥ ድግመ ኡደት ባይኖር ኖሮ የፕላኔታችን ገፅ ልክ እንደ ጨረቃ ገፅ በስርጉደ መሬት የተሞላ ይሆን ነበር ይላሉ።

በመሬት ከባቢ አየር ውስጥ በየእለቱ እስከ 200 ሚልዮን የሚደርሱ ተወርዋሪ ኮከቦች እንደሚታዩ ሳይንቲስቶች ይገምታሉ። ወደ ከባቢ አየር ከሚገቡት አካላት መካከል ብዙዎቹ ትንንሾች ከመሆናቸውም በላይ ማንም ልብ ሳይላቸው እንደ ጧፍ ቀልጠው ይጠፋሉ። ይሁን እንጅ ከእነዚህ አካላት መካከል አንዳንዶቹ የማቃጠል ኃይል ያለውን ከፍተኛ ሙቀት አልፈው ወደ ከባቢ አየር ዘልቀው በመግባት ከአየር ግፊት ጋር በሚፈጥሩት ሰበቃ ፍጥነታቸው በሰአት ወደ 320 ኪሎሜትር ዝቅ ይላል። የተረፈው አካላቸው ዱቤ በረቅ/meteorites/ ሆኖ ምድርን ይመታል። አብዝሃኞቹ የሚወድቁት ውቅያኖሶች ላይ ወይም ሰው በማይኖርባቸው የምድር ክፍሎች በመሆኑ እምብዛም በሰው ላይ ጉዳት አላደረሱም። ወደከባቢ አየራችን የሚገቡት አካላት በየእለቱ የመሬትን ክብደት በመቶዎች በሚቆጠር ቶን እንደሚያሳድጉት ይገመታል።

በተጨማሪም የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች ከመሬት ምህዋር ጋር የሚሳበሩ ወይም ወደ መሬት ምህዋር የተጠጉ ከአንድ ኪሎ ሜትር ስድስት አስረኛ በላይ የሆነ ዲያሜትር ያላቸው 2.000 ገደማ የሚሆኑ ንኡሳን ፕላኔቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገምታሉ። ሳይንቲስቶቹ ያገኟቸውና የእንቅስቃሴያቸውን አቅጣጫ መከላከል የቻሉት 200 የሚሆኑትን ብቻ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ከ50 ሜትር የሚበልጥ ዲያሜትር ያላቸውና ወደ መሬት ምህዋር በአደገኛ ሁኔታ የተጠጉ አንድ ሚሊዮን ንዑሳን ፕላኔቶች እንዳሉ ይገመታል። ይህን የሚያክል መጠን ያላቸው ንዑሳን ፕላኔቶች መሬት ሊደርሱና ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ የሚባለው እንዲህ አይነቱ አረር አስር ሜጋቶን ገደማ የሚሆን ጉልበት ያለው ሲሆን ይህም ከአንድ የኑክሊየር ቦምብ ጋር የሚተካከል ነው።

የመሬት ከባቢ አየር አነስተኛ ከሆኑ ልተማዎች ሊጠብቀን ቢችልም እንኳ አስር ሜጋቶን ወይም ከዚያ በላይ ጉልበት ያላቸውን ግን ሊያቆማቸው አይችልም። በአንዳንድ ተመራማሪዎች ከአሃዛዊ መረጃዎች አንፃር ሲታይ በአንድ መቶ ዘመን ውስጥ በአማካይ አስር ሜጋቶን ጉልበት ያለው አንድ ልተማ ሊከሰት ይችላል ብለው ያምናሉ። አንዳንድ ግምታዊ አሃዞች እንደሚያሳዩት ከሆነ አንድ ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆን ዲያሜትር ያላቸው አካላት በ100.000 ዓመታት ጊዜ ውስጥ መሬትን አንድ ጊዜ ይለትማሉ።

በቀደምት ዘመናት ፕላኔታችን ከሰማይ በዘነቡ ትልልቅ አካላት ተመትታ እንደነበረና ከ150 በላይ የተሰረጎዱ ቦታዎች ማግኘታቸውን ሰነዶች ላይ ሰፍሯል።

ሹማከር ሌቪ 9 የተባለችው ጅራታም ኮከብ ስብርባሪዎች በጁፒተር ላይ የተፈጠሩት ጊዜያዊ ስርጉዶች በብዙ ሰዎች የታየ የቅርብ አመታት ክስተት ስለነበር አስረጂ ናቸው።

በሳይንቲስቶቹ ግኝት መጀመሪያ ፈንጅ የሆነ የአለትና የአቧራ ሙቅ ዘለቅ /plume/ እንደ ሚከሰት፣ ወደታች የሚዘንበው ግባሶ ሰማዩን ፍም የሚያስመስልና ደኖችንና የሳር መሬቶችን እሳት በማያያዝ አብዛኛውን የየብስ ሕይወት የሚያጠፋ የተወርዋሪ ኮከብ ክፈት /meteor shower/ ፈጥሮ ከባቢ አየሩ ተንጠልጥሎ ለረጅም ጊዜ የሚቆየው አቧራ የፀሐይ ብርሃንን በመጋረድ የሙቀት መጠን ወዲያውኑ እንዲያሽቆለቁልና በጨለመው የምድር ገፅ ላይ የሚያካሂደው ብርሃን አስተፃምሮ/ፎቶሲንተሲስ/ እንዲስተጓጎል ያደርጋል ይላሉ።

በተጨማሪም ብርሃን አስተፃምሮው ሲስተጓጎል በውቅያኖስ ውስጥ ያለው የምግብ ሰንሰለት ይቆረጥና በባሕር ውስጥ ያሉት አብዝሃኞቹ ፍጥረታት ይሞታሉ። በዚህ ንድፈ ሐሳብ መሰረት ለአካባቢያዊ  አደጋ ዓለም አቀፋዊ በሆነ አሲድ ዝናብና በኦዞን ንብር ላይ በሚደርስ ጥፋት ይደመደማል ማለት ነው። እንዲህ ያለ ንዑስ ፕላኔት ውቅያኖስን ቢመታ ከፍተኛ ውድመት ሊያስከትል የሚችል መውጃዊ ሞገድ ይፈጥራል። መውጃዊ ሞገዶች በመጀመሪያ ላይ ከሚከሰተው ክውታዊ ሞገድ /ሾክ ዌቭ/ የበለጠ ረጅም ርቀት መጓዝ የሚችሉ በመሆናቸው በሽህ የሚቆጠሩ ኪሎሜትሮች ርቀው የሚገኙ የባሕር ዳርቻዎችን ያወድማሉ። የስነፈለክ ተመራማሪ የሆኑት ጃክ ሂልስ ቀደም ሲል ከተሞች የነበሩባቸው ቦታዎች ሁሉ ጭቃ የተቆለለባቸው ባድማዎች ይሆናሉ ያሉ ቢሆንም የሰው ልጅ ግን መውደም ቢኖርም ቀልቡ አላርፍ ብላ ትኩረቱና ፍላጎቱን በዚህም ላይ ቀሰረ።

ይህው አይበርዴ ፍላጎቱ በሌላውም ነገር ተሳበ። በውቅያኖስ ወለል ላይ በሚገኝ አንድ ሞለኪውል ውሃው በፀሐይ ሲተን ሞለኪዩሉ ተነስቶ ከመሬት ብዙ ሽህ ጫማ እርቆ ይሄዳል። ከዚያም ከሌሎች የውሃ ሞለኪዩሎች ጋር ይደባለቅና አንድ ትንሽ ጠብታ ውሃ ይሰራል። ጠብታው በንፋስ እየተገፋ በመቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ይጓዛል። ከጊዜ በኋላ ጠብታው ይተንና ሞለኪውሉ እንደገና ወደ ላይ ተነስቶ ወደ መሬት ለመውደቅ የሚያስችል መጠን ካለው ከአንድ የዝናብ ጠብታ ጋር ይገናኛል።

የዝናብ ጠብታው በቢሊዮን ከሚቆጠሩ ሌሎች የዝናብ ጠብታዎች ጋር በአንድ ኮረብታ አጠገብ ይወድቃል። ውሃው ወደ አንድ ዥረት ይወርዳል። ከዚያም አንድ እንስሳ ከጅረቱ ውሃ ሲጠጣ ሞለኪውሉን ወደ ሰውነቱ ያስገባል። ከሰአታት በኋላ እንስሳው ሲሸና ሞለኪውሉ ከመሬት ጋር ይደባለቅና አጠገቡ ያሉ የዛፍ ስሮች ይወስዱታል። ከዚያም ሞለኪውሉ ወደ ዛፉ አናት ይጓዝና በመጨረሻ ከቅጠሉ ላይ ወደ አየር ይተናል/ይህ በየቦታው በየትኛውም አቅጣጫ የሚከወን መሆኑን ልብ ይሏል/። ልክ እንደበፊቱ አሁንም አንዲት ሌላ ትንሽ ጠብታ ለመስራት ወደላይ ይወጣል።  

ጠብታውም በጣም ከጠቆረ ከባድ የዝናብ ደመና ጋር እስኪገናኝ ድረስ በንፋስ ኃይል ይጓዛል። ሞለኪውሉ እንደገና ከዝናብ ጋር አብሮ ይወርዳል። ሆኖም በዚህ ጊዜ ወደ አንድ ወንዝ ይገባና ከውቅያኖስ ጋር ይደባለቃል። እዚያ ከገባ በኋላ ወደ ውቅያኖሱ ወለል እስኪወጣ፣ እስኪተንና እንደገና አየር ወለድ እስኪሆን ድረስ ለብዙ ሽህ አመታት ሊወስድበት ይችላል። ዑደቱ ማብቂያ የለውም። ውሃ ከባሕር ይተናል፣ ከምድር በላይ ይጓዝና ዝናብ ሆኖ ይወርዳል። ከዚያም ተመልሶ ከባሕሩ ጋር ይደባለቃል። በዚህ መንገድ ውሃ በምድር ላይ ያለውን ሕይወት ሁሉ ጠብቆ እንደሚያቆይ የሰው ልጅ ተረድቷል። ፍላጎቱንም እዚህም ላይ በስርዓት መስርቶታል።

ቀለም፣ ሽታ፣ ወይም ጣእም የለለውና ካሎሪ አልባ የሆነው ውሃ በምድር ላይ ለሚገኝ ሕይወት ላለው ነገር ሁሉ እጅግ አስፈላጊ ነው። ማንኛውም ሰው፣ እንስሳም፣ ሆነ እፅዋት ያለ ውሃ መኖር አይችሉም። ከዝሆን አንስቶ እስከ ትንl ህያው ነፍስ ድረስ ያሉት ፍጥረታት ውሃ የግድ ያስፈልጋቸዋል። ውሃን የሚተካ ምንም ነገር የለም። ሰዎች በየቀኑ በፈሳሽም ሆነ በምግባቸው ሁለት ተኩል ገደማ የሚሆን ውሃ መውሰድ አለባቸው። ውሃ ከሌለ ሕይወት የለም። ውሃ ከለለ ምግብ የለም ምግብ ከለለ ሕይወት የለምና።

በዓለም ላይ ካለው ውሃ ውስጥ ጨዋማ ያልሆነው ውሃ 3 በመቶው ብቻ ነው። ከዚህ ውስጥ 99 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው በግግር በረዶና በበረዶ ንጣፍ መልክ ወይም በጥልቅ  መሬት ውስጥ ነው። የሰው ልጅ በቀላሉ ሊያገኘው የሚችለው 1 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ነው።

ይህ 1 በመቶ የሚሆነው ውሃ በዓለም ዙሪያ ለሁሉም በእኩል ደረጃ እንዲደርስና በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ቢደረግ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የዓለማችን ነዋሪ ሁለት ወይም ሶስት እጥፍ የሚሆን ሕዝብ ማኖር ይቻላል። በዓለም ዙሪያ ያለው ውሃ ያለማቋረጥ ስለሚሽከረከር ከውቅያኖሶች ወደ ከባቢ አየር ከዚያም ወደ ምድር ቀጥሎ ደግሞ ወደ ወንዞች ይገባና ተመልሶ ከውቅያኖሶች ጋር ይቀላቀላል።

የደን ምንጠራና መሬቱ ከሚገባው በላይ ለእርሻና ለግጦሽ መዋሉ አፈሩን ራቁቱን ያስቀረዋል። እንዲህ አይነቱ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ የምድር ገፅ ተጨማሪ የፀሐይ ብርሃን ወደ ከባቢ አየር መልሶ ያንፀባርቃል። በውጤቱም ከባቢ አየሩ ይሞቅና ደመናዎች ይበተናሉ። የዝናቡም መጠን ይቀንሳል።

በተጨማሪም በደኖች ላይ የሚዘንበው አብዝሃኛው ዝናብ መጀመሪያ ከእፅዋት ማለትም ከዛፎች ቅጠሎችና ከቁጥቋጦ የተነነው ውሃ በመሆኑ ጠፍ የሆነ ምድር ለዝናብ መቀነስ ምክንያት ሊሆን ችሏል። እፅዋት ዝናብን መጥጦ እንደሚይዝ ግዙፍ እስፖንጅ ናቸው። ዛፎቹና ቁጥቋጦዎቹ ከተወገዱ የሚተነውና ዝናብ የያዙ ደመናዎችን የሚሰራው ውሃ ደግሞ በጣም አነስተኛ ይሆናል። ሰዎች ከዚህም ገንዘብ ለማግኘት ፍላጎታቸው መርቷቸው የካርበን እመቃ በሚል የካርበን ፋይናንስን ዘየዱ።

የሰው ልጅ ፍላጎት ማለቂያ ስለለውና ገደብ ባለመኖሩ ለነዚህ መሰል ጥፋቶች በጣልቃ ገብነቱና ተፈጥሮ የሰጠችውን ገፀ በረከት ለራሱ እንደሚመቸው ለማዋል ባደረገው ጥፋት አምክኗቸዋል። የተፈጥሮን ዑደት ባጠቃላይ አዛብቶታል። የተፈጥሮ ሰንሰለታቸው ውስጥ እጁን አስገብቶ አበለሻሽቶታል።

እንዲህ እንደሚሆንና ዓለምን የራሱ ለማድረግ የሚጣደፈውና የሚገነዘበው የሰው ልጅ የመሬትን ሆድ እቃ ደረማምሶና በርብሮ መሬት ላይ ያለውን ሁሉ ሸጦ አልበቃው ስላለ የሰዎችን ልብ፣ ደም፣ ኩላሊትና የአካል ብልት ለመሸጥ ሰውን ያህል ክቡር ፍጥረት እየገደለ የመጣው፣ መብረጃና ማቆሚያ የለለው ፍላጎቱን ለማርካት ሲል ነው።

በቆሻሻነት የተፈረጀውን ሽንቱን መልሶ እስከ መጠጣትና ዩሪን ቴራፒ በሚል ፈዋሽ ስም እያሞካሸ የመድኃኒቱ አንዱ ክፍል አድርጎታል። ሽንትን በተለየ ማጓጓዣ በመውሰድና ለብቻው ከአይነምድሩ ለይቶ በማጠራቀም ከውሃ ጋር አደባልቆ ማሳንና የጓሮ አትክልትን ለማልማት እየጣረ መሆኑ ሰው ምን ያህል ለፍላጎቱ ባሪያ መሆኑን አንዱ ማሳያ ነው።

ሐሽሽ እያልን እኛ የምንጠራው ባጠቃላይ የዚህ ዝርያ የሆኑት አደንዛዥ እፆች የሰው ልጅ ማባሪያ የለለው ፍላጎቱ የከሰታቸው አነቃቂና አጉል ባሕሪ አመንጭና አባባሽ ነገሮች በታሪክ የኦፒየም ጦርነትን እስከማስነሳት የቻለ የከንቱ ፍላጎቶች ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል።

ቻይና በሕንድ እየተመረተ ለግሬት ብሪቴይን የገንዘብ ፍላጎት እርካታ ሲባል ድንበሯን ጥሶ ይወርራትና ዜጎቿን ይጎዳ የነበረውን አደንዛዥ እፅ ወደ ግዛቷ እንዳይገባ በመከልከል፣ ያለመፈለግ ፍላጎቷን በይፋ በማሳየቷ የብሪቲሾችን የገንዘብ ፍላጎት ገዳቢ በመሆኑ በሁለቱ የማይጣጣሙ ፍላጎቶቻቸው ነበር የኦፒየሙ ጦርነት የተካሄደው።

በአሸባሪነት የሚፈረጁትና አሸባሪ ብለው የሚፈርጁት ሁለቱም ወገኖች የየራሳቸው ፍላጎት ተገዢ ስለሆኑ ወደ ሚያስማሟቸውና ወደ ሚያግባቧቸው መስመር በጭራሽ ሊደርሱ እንዳይችሉ የየራሳቸው ፍላጎቶች ገድቧቸው ለመተላለቅ ተሰላልፈዋል።

የሰው ልጆች የማይቻላቸውን የዝንብ ጠንጋራን አበጥረው ማወቅ የሚችሉት መለስ ዜናዊ አንድ ወቅት እኛ ኢህአዴጎች የመላእክት ስብስብ ስላይደለን ሕዝቤ ሆይ ፍላጎታችሁ መረን የለቀቀ በመሆኑ ብዙ ከኛ አትጠብቁ እንደማለት የነገሩንን ስናስብ፣ የመላእክት አለቃ የነበረው ሉሱፌር የፈጣሪን ቦታ በመፈለጉ/በመሻቱ የፈጣሪን ስም ለማጥፋት በመሞከሩ ዲያብሎስ የሚል ስያሜ ተሰጥቶ ወድ ምድር መባረሩን አያውቁትም ነበር ለማለት ያስቸግራል።

ይህ መላእከ የነበረ በኋላ የተባረረ ሰይጣን ፍላጎቱ የማይጨበጥ ሆኖ በኤደን ገነት ውስጥ በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን ስላሳታት የቀደመው እባብ ተብሎም ተጠርቷል። ባይሳካለትም እየሱስን በፈተና አሳስቶ እንዲሰግድለት ሞክሯል። የፈጣሪ አገዛዝ በፅድቅ ላይ የተመሰረተና ትክክል የመሆኑን/የዴሞክራትነቱን ጉዳይ ጥያቄ ያነሳ መልአክ ስለነበር ከሰባተኛው ሰማይ ወደ ምድር ተወረወረ እንጂ የመላእክትን ለምድ ለብሶ የአምላክን መንግስት ለማስቸገር የታጠቀ የኃጢአት ምንጭ በሆነ  ነበር።

ፓን የተባለው የግሪካውያን አምላክ ምስልና ኢጣሊያዊው ባለ ቅኔ ዳንቴ አሊገፌሪ በፃፈው ኢንፌርኖ በተባለው መፅሐፍ የመካከለኛው ዘመን ሰዓሊዎች አእምሮ የመነጨው ባለ ቀንድ የሚያቃጥል እሳት ብለው የሰየሙት መልአክ እያለ እኒህ ሁሉን አዋቂ መሪያችን መላእክትነት ፍፁምነት አድርገው ነበር የገለፁልን።

ገፆቹ ባይገድቡን ኖሮ በዚህ አጀንዳ ብዙ ነገሮችን ማንሳትና በጥቅሉም ቢሆን መተንተን በታቻለ ነበር።

መልካም ሳምንት ይሁንልን!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
851 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 826 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us