ተላላፊ በሽታዎችና መዘዛቸው

Thursday, 14 July 2016 16:09

ወሰንሰገድ መሸሻ በላቸው/ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. /

በሐገራችን በአዲስ መልኩ የተቀሰቀሰው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ብዙ ነገሮችን እያነቃነቀና እያወከ የመጣ ብሔራዊ አጀንዳ ከሆነ ሰነባበተ። ሰንደቅ ጋዜጣን ጨምሮ የመገናኛ ብዙሃን የፊት ገፆችንና የአየር ሰዓት ከፍተኛ ትኩረትን እየሳበ የመጣና ስነልቡናዊ ሽብርን ባገሬው ላይ የፈጠረ ህዝባዊ ጉዳይና ከአይሲኤስ የአሸባሪ ቡድን በጦር የታገዘ ጥቃት የበለጠ ስውር ገዳይና ቀውስ ፈጣሪ ችግርም ሆኗል።

ሰንደቅ 11ኛ ዓመት ቁጥር 563 ረቡዕ ሰኔ 15 2008 በመስከረም አያሌው <አፋጣኝ ህክምና የሚያስፈልገው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት> በሚል ርእስ የቀረበውን ፅሁፍና በሰኔ 07/2008 ዓ.ም የተለቀቀውን መንግስታዊ ማስታወቂያ መነሻ በማድረግ የነበረውንና ሊሆን የሚችል የሚመስለንን ከተለያዩ ተዛማጅ መረጃዎችና ጥናታዊ ፅሁፎች ጋር በማሰናሰን በዚህ ፅሁፍም በመጠኑ ለማየት እንሞክራለን።

ውሃ ወለድ በሽታዎች በሰፊው በተንሰራፋባት ሐገራችን፣ ንፁሕ ውኃ ማዳረስ ያልተቻለና የተሻለ መፀዳጃ ያልተመቻቸላቸው ብዙ ዜጎች በሚኖሩባት ሐገር፣ የሚሊኒየሙን የሳኒቴሽን ዓለም ዓቀፍ ግብ ማሳካት ያልቻለች ሐገር፣ የውሃ ማማ ተብላ በተሞካሸች ሃገር፣ ዜጎቿ በውሃ እጥረትና በድርቅ የሚያልቁባት ሐገር ይህን መሰል አጣዳፊና በፍጥነት ጨራሽ ችግርና ከፍተኛ አደጋን ንቆ ማለፍ አለመቻሉ ለዚህ ለዛሬው ፅሁፍ አስገዳጅ ሁኔታን ፈጥሯል።

የሐገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር በየጤና ጣቢያዎቹ አማካይነት ለሕዝቡ የእናድናችሁ ተባበሩን ጥብቅ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ በር ለበር እያዳረሰ ይገኛል። የሚኒስቴሩ የአንድ ጤና ጣቢያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት/አተት/ ምን ማለት እንደሆነ ሲገልፅ በተለያዩ በጥቃቅንና በዓይን በማይታዩ ጎጂ ተህዋስያን አማካኝነት ሊመጣ የሚችል ተላላፊ የሆነ በሽታ መሆኑንና መገለጫውም አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት መሆኑንና በወቅቱ አስቸኳይ ህክምና ካላገኙ ለሞት የሚዳርግ በሽታ እንደሆነ መንግስት በፅሁፉ ህዝቡን በጥብቅ አስጠንቅቋል።

በኤልኒኖ ሳቢያ ቀደም ሲል በድርቅ አሁን ደግሞ በጎርፍና ባልተጠበቀ አደገኛ ዝናብ አገር እየታወከ በመምጣቱ ተላላፊ በሽታዎችን የሚቆጣጠር አቅም ያልተፈጠረ መሆኑን መገንዘብ አይቸግርም። ፍሳሽ ቆሻሻ ማለት ለቤት ውስጥ አገልግሎት፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለንግድና ለመሳሰሉት አገልግሎት ከዋለ በኋላ የሚፈጠረው ተረፈ ውሃ ማለት ነው። ፍሳሽ ቆሻሻ ውስብስብ የሆነ የኦርጋኒክና የኢንኦርጋኒክ ይዘት ያለው በአነስተኛ መጠን ሰው ሰራሽ ብክለት ያለበት ውህድ ነው። ከመኖሪያ ቤት የሚወጣው ፍሳሽ የሰው ዓይነ ምድርና ሽንት፣ በምግብ ዝግጅት፣ በግል ንፅሕና አጠባበቅ፣ በልብስ፣ በእቃ እጥበት የተገለገልንበት ፍሳሽ ነው። ከጎርፉ አደጋ ጋር ቀያቸውን በችግር ለሚለቁ ወገኖች የሚጠብቃቸው አለመመቻቸት አባባሽ ሁኔታን ይፈጥራል ብሎ ማሰቡ አያሳፍርም። 

ይህንን ድሮ ሐይጅን በሚባል እራሱን በቻለ ሁኔታ በክፍል ውስጥ እንድንማረው ግዴታ ነበርና ተማርነው። ከብሔር ፖለቲካው ጋር ሊያገናኘው የሚችለው ሳይገባን እንደግብረገብ ትምህርት ከመስመር ተወገደ።

አደገኛ ኬሚካሎችን ጨምሮ መራዥና ገዳይ ነገሮችን ይዞ የሚለቀቀው የኢንዱስትሪ ፍሳሽ ቆሻሻ፣  ከሆስፒታሎች በአብዛኛው ጎጂ የሆኑ ባክቴሪያዎችና ጀርሞችን በብዛት ተሸክሞ የሚወጡት ፍሳሾች ከየድርጅቶቹም ሆነ ከየቤቱም በእቅድ ባልተሰሩ ጎዳናዎችና መፋሰሻዎች እየተለቀቁ ከተማዋን እያገሟት የሚንዶለዶሉት ፍሳሽ ቆሻሻዎችና አዲስ አበባን ሊቀብራት የደረሰው ደረቅ ቆሻሻ መፍትሄ ሳይበጅለት ንፅህናችሁን ጠብቁ ብሎ ለዜጎቹ የሚያዝ አመራር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱን ተሸክሟል።

በሐይጂን ትምህርት ላይ የምግብ ዝግጅት ከመጀመሩ በፊትም ሆነ ከምግብ ዝግጅት በኋላ፣ ከመፀዳጃ ቤት መልስና ከአንዱ የምግብ ስራ ወደ ሌላኛው ስንሸጋገር እጅን በሳሙና መታጠብ፣ እጅ ላይ ቁስል ካለ እስኪድን አለመስራት አለበለዚያ በፕላስተር መሸፈን፣ የቤት እንስሳ ውሻ፣ ድመት የመሳሰሉና ልዩ ልዩ በሽታ አስተላላፊ ተህዋስያንን ተሸካሚ ስለሚሆኑ በእጅ አለመንካትና ሁሉም ነገር ንፁህ ሆኖ መቀመጥ ወይም ንፁህ መሆን እንደሚገበው የያኔው ትውልድ በደንብ ተምሮታል።

መፀዳጃ ቤትን ሰዎች መጠቀም የጀመሩት በሙሴ ዘመን ከ1300 - 1200 ዓ.ዓ እንደሆነ ይገመታል። በግሪክና በሮማውያን የስልጣኔ ዘመን ለመፀዳጃ ቤት አጠቃቀም ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ በወቅቱ የነበረው አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል በመፀዳጃ ቤት ይገለገል እንደነበርና ከተሞቹም ፀድተውና ከተላላፊ በሽታዎች መራቢያነት ነፃ ሆነው እንደነበር ታሪክ አስፍሮታል።

ከግሪክና ከሮማውያን ስልጣኔ ውድቀት በኋላ የተተካው የመካከለኛው ዘመን ለሳኒቴሽን አቅርቦትና ይዘት መሻሻል ትኩረት ካለመሰጠቱ የተነሳ በሐይጂንና በመፀዳጃ ቤት አጠቃቀም ጉድለት ምክንያት በተከሰቱ ወረርሽኞች የተነሳ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል። በዚህም የተነሳ ይህንን ወቅት የኋላ ቀርነት፣ የበሽታዎች፣ የችግርና የመከራ ዘመን ስለነበር የጨለማው ዘመን/ዳርክ ኤጅ/ ተብሏል።

ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ሁኔታዎች እየተሻሻሉ መጥተው የኢንዱስትሪ አብዮት በአውሮፓ እየተስፋፋና ስር እየሰደደ ሲሄድ ዘመናዊ ይዘት ያላቸው ደረቅና በውሃ የሚሰሩ መፀዳጃ ቤቶች አገልግሎት ላይ ከመዋላቸውም በላይ ዛሬ በቱቦ መስመር የሚሰሩና ከመፀዳጃ ቤት ለሚወጡ ዓይነ ምድርና ሌሎች ፍሳሽ ቆሻሻዎች ማስወገጃ መስመሮችን እስከመጠቀም ተደርሷል። በመሆኑም ከተላላፊ በሽታዎች መጠበቅ ያስቻለና ለኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።

የሳኒቴሽን አገልግሎት የኅብረተሰብ የእድገት ደረጃን ተከትሎ ዛሬ ካለበት ለመድረስ ዘመናትን ተሻግሯል። የተለያዩ መፀዳጃ ቤቶች እንደየአገሩ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊና ቴክኖሎጂያዊ የእድገት ደረጃ አገልግሎት ላይ እየዋሉ ናቸው።

አገራችን ካሉባት የጤና ችግሮች 80 በመቶ ያህሉ ተላላፊ በሽታዎች እንደሆኑና የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት በስፋት አለመለመድ ኅብረተሰቡን ለሕመምና ለሞት ዳርጎታል።

ባለንበት ክ/ዘመን የህዝብ ብዛት በመጨመሩ የሰዎች ፍላጎትም በከፍተኛ ደረጃ በማደጉ ለቴክኖሎጂ እድገት ድርሻውን ተወጥቷል። ሆኖም የሚመረተውና የተጠቀሙበት አገልግሎቱን ሲጨርስ መጣልን በማስገደዱ የቆሻሻ ክምችት ተፈጠረ። ከየትኛው አቅጣጫ የሚጣሉ ደረቅ ቆሻሻዎች በአግባቡ ካልተያዙ፣ ወደ ሌላ ጥቅም በጥንቃቄ ካልተለወጡና ካልተወገዱ አካባቢን በመበከል ለጤና ጉዳት ያደርሳሉ። ደረቅ ቆሻሻ የሚለው ቃል ጠጣር፣ ከፊል ጠጣር የሆኑ ከምግብም ሆነ ከሌሎች የወዳደቁ፣ ከዓይነ ምድር ውጭ የሆኑትን ሁሉ ያጠቃልላል።

የመንግስት የጤና ጉዳይ ማስጠንቀቂያው በሽታው ሲከሰት የሚያሳየውን ምልክቶች ሲገልፅ በሽታው ከሰውነት ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችንና ፈሳሽን ያስወግዳል ብሏል። በተደጋጋሚ/አጣዳፊ/ ተቅማጥ ትውከትም ስለሚያስከትል በዚህም የተነሳ የሰውነት ፈሳሽና ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን መጠን ያዛባል። በተጨማሪም የውሃ ጥም /የሰውነት ድርቀት/፣ የአፍ መድረቅ፣ የዓይን ወደ ውስጥ መሰርጎድ፣ እንባ አልባ መሆን፣  የሽንት መቀነስ፣ የቆዳ መሸብሸብና አጠቃላይ የሆነ የድካም ስሜት ያስከትላልም ይላል።

ይህ መንግስታዊ ማስጠንቀቂያ ምንም እንኳን መንግስት ሐይጂንን ከት/ቤት አስወግዶ በየቤቱ አገሬውን በጅምላ አስተምራለሁ ቢልም በማስጠንቀቂያ ማስተማሪያው ወረቀት ላይ አተት/በሽታው በዋናነት በንፅህና መጓደል በተለይም በተበከሉ ምግቦችና የመጠጥ ውሃዎች አማካኝነት በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው በከፍተኛ ፍጥነት እንዴት እንደሚተላለፍ ለህዝብ የገለፀውን ማየቱ ለህዝቡም የሚጠቅም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሆኖ ስላገኘነው እኛም ለአንባቢዎቻችን እንዲህ አቅርበነዋል።

በበሽታ አምጭ ተዋስያን የተበከለ የምንጭ፣ የጉድጓድ፣ የወንዝ፣ የዝናብ፣ የቧንቧና ወዘተ ውሃን በመጠቀም፣ በበሽታ አምጭ ተዋስያን የተበከለ የውሃ ማጠራቀሚያና መገልገያ እቃዎች በመጠቀም፣  በበሽታ አምጭ ተዋስያን የተበከሉ ምግቦችን በቆሻሻ ውሃ የተመረዙ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን በመጠቀም፣ ንፁህ ባልሆነ እጅ ምግብን በማዘጋጀትና ውሃን በመጠቀም የሚተላለፍ በሽታ መሆኑን አስታውቋል።

አተትን ለመከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎችንም የመንግስት ማስጠንቀቂያው አመላክቷል። ውሃ አፍልቶና አቀዝቀዞ መጠጣት፣ በውሃ ማከሚያ መድኃኒት የታከመ ውሃ መጠጣት፣ ምግብንና የምግብ ዕቃዎች ንፅህና በደንብ መጠበቅ፣ መፀዳጃ ቤትን አዘጋጅቶ በአግባቡ መጠቀም፣ ከመፀዳጃ ቤት መልስ፣ ምግብን ከማዘጋጀት በፊት፣ ምግብ ከማቅረብ በፊት፣ ምግብ ከመመገብ በፊትና ህፃናትን ካፀዳዱ በኋላ እጅን በሚገባ በውሃና ቢቻል በሳሙና አለበለዚያ በአመድ በደንብ መታጠብ፣ ስጋንና አሳን ሌሎች ምግቦችን በደንብ አብስለው በትኩስነታቸው መመገብ እንደሚገባ ማስጠንቀቂያው ይመክራል።

ይሁንና በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን የሚኖሩት የሴሉላር/የሴሎች ሕክምና ጠበብቶች ከዚህ ተቃራኒውን ይመክራሉ። ምግብ አብስሎ መብላት ሞት አማጭ ራስን በራስ መግደል ነው ይላሉ። በአንድ ሰው አካል ውስጥ ከ1 ትሪሊየን የሚበልጡ ህዋሳት አሉ።

በሽታዎች የተለያዩ ሆነው ይታዩ እንጂ ሁሉም አንድ ናቸው የሚሉት የዘርፉ ጠበብቶች በሽታዎች ሁሉም የሚጀምሩት በሴሎች ደረጃ ነው ይላሉ። ስለዚህ በሽታዎች ሁሉ የሚነሱት በሴሎች ከሆነ ፈውሳቸውም በሴሎች ነው ብለው ያምናሉ።

የዘርፉ ጠበብቶች በሽታው በአንድ ሴል ስለሚጀምር ፈውሱም የሚጀምረው በአንድ ሴል ነው ይላሉ። ሴሎች በትክክል ስራቸውን እንዳይሰሩ የሚያደርጉ ንጥረ ነገሮች ለበሽታው መጀመር ምክንያት በመሆናቸው ሴሎች በትክክል ስራቸውን እንዲሰሩ አስፈላጊውን ንጥረ ነገር ይሰጣሉ። ከውጭ የሚገቡትን ጎጂ ኬሚካሎችንም ያቆሟቸዋል ይላሉ።

ለሴሎቻችን የሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮች የሚገኙት ከምግብ በመሆኑ እነዚህ ንጥረ ነገሮች ህያው መሆን አለባቸው። ምግባችንን ቀቅለን፣ ጠብሰን የምንበላ ከሆነ ፈጣሪ በመጀመሪያውኑ በምግብ ውስጥ ያስቀመጣቸውን ህያው ሞለኩዩልስ ስለምናጠፋቸው የሞቱ ንጥረ ነገሮችን እየበላን ሞታችን ስለሚፋጠን ምግብን አብስላችሁ አትብሉ ብለው በጥብቅ ይመክራሉ።

ጀርሞች፣ ባክተሪያዎች፣ ቫይረሶች፣ ፈንገስ… የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ከሰው ልጆች ጋር ያሉ ፍጥረቶች ናቸው። የህክምና አባት ሂፖክራቲስ የምትበሉት ምግብ መድኃኒታችሁ ይሁን፣ መድኃኒታችሁ ደግሞ የምትበሉት ምግብ ይሁን ብሏል። የምንበላው ምግብ ህያው ሞለኪዩሎችን፣ ንጥረ ነገሮችን ያዘለ ከሆነ አካላችን በሽታን የመከላከል ኃይሉ ስለሚጠነክር በባክተሪያዎች፣ በጀርሞች፣ በቫይረስ፣ በፈንገስና በመሳሰሉት አንጠቃም። ሳይበስሉ የሚበሉ /የተፈጥሮ መልካቸው በእሳት ኃይል ያልጠፋ/ ህያው የሆኑ በተፈጥሮ እንዳሉ ያሉትን ተክሎችን መመገቡ እጅግ ጠቃሚ ለመመገብ አስቀድሞ በበለጠ ማፅዳትና ጥንቃቄ ማድረግ ግዴታ መሆኑንም አስጠንቅቀዋል።

መንግስታዊ ማስጠንቀቂያውም ማናቸውንም ከቤት የሚወጣ ደረቅ ወይም ፈሳሽ ቆሻሻ ውሃን እንዳይበክል በአግባቡ በተመደበለት ሥፍራ ማስወገድ፣ በዚህ በሽታ የተያዘን ሰው በፍጥነት ማስመርመርና ህክምና እንዲያገኝ መደረግ አለበት ይላል።

ሆኖም በየዓመቱ በወረርሽኝ መልክ እየተከሰቱ በርካታ ሰዎችን ከሚገድሉት በሽታዎች አንዱ የኮሌራ በሽታ ህክምና እንደዚህ ባልተስፋፋበት ወቅትም እየተከሰተ ኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ቅድመ ጥንቃቄና አስተማማኝ የሆነ ህዝባዊ እውቀት የሞላበት መፍትሄ የየዘመኑ ሰዎች ያደርጉ ነበር።

አደገኛው የኮሌራ በሽታ እጅግ አደገኛ የሆነ ቫይብሪዮ ኮሌራ የሚባል በሽታ አማጭ ባክተሪያ ነው። ወደ ሰው የሚተላለፈውም አንድ ሰው በቫብሪዮ ኮሌራ የተጠቃን ወይም የተበከለን ውሃ አሊያም ምግብ በሚመገብበት ጊዜ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

በየጊዜው የአካባቢ ንፅህናን በሚበክሉና ባልታከመ ውሃ ወይም ከቆሻሻ ጋር ከየትኛውም ሥፍራ እየተደባለቀባቸውና እየተበረዙ በሚፈሱ ወንዞችም ሆኑ ወራጅ ውሃ ውስጥ በቅለው ለምግብነት የሚውሉ አትክልቶች፣ የመጠጥ ውሃዎችን የሚያበላሹ ቆሻሻዎች በመጠቀም የሚከሰት በሽታ ነው።

ለዚህ ለባክተሪያው መፈጠር አንዱ ምክንያት የሆነው የአየር ፀባይ ለውጥና በውሃ ውስጥ የሚኖሩ እንስሳት ናቸው። ቫይብሪዮ ኮሌራ በአይን የማይታይ ረቂቅ ህዋስ ሲሆን በፈሳሽም ይሁን በደረቅ ምግብ አማካይነት ወደ ሆድ ከገባ በኋላ ኮሌራ ቶክሲን የተባለ አሲድ በማመንጨት የትንሹን አንጀት ልብስ ያቃጥለዋል።

በዚህም በሽታ ሰዎች በአጣዳፊ ተቅማጥ ስለሚያዙ አስፈላጊውን ህክምና ካላደረጉ በአንድ ሰዓት ውስጥ በሰውነት ውስጥ ያለው ፈሳሽ ምግብ አልቆ ባዶውን ይቀራል። በተለይ ህመምተኞቹ አስቀድመው በምግብ የተጎዱ ዓይነት ከሆኑ በቅፅበት ይሞታሉ። ባጠቃላይ እንደ ሰዎቹ አቅምና ጥንካሬ እስከ 3 ሰዓት በዛ ቢባል እስከ 4 ሰዓት ሳይሞቱ መቆየት እንደሚቻል የገለፀው የዘርፉ ጥናት በጣም ጠንካራ የሆኑ ሰዎች ለ18 ሰዓት ብቻ በሕይወት ሊቆዩ ይችሉ ይሆናል ብሎ ስጋቱን አረጋግጧል።

የበሽታው ምልክቶች በጉልህ እስኪታዩ ድረስ ያለው ጊዜ ኢንኩቤሽን ፔሬድ በመባል ይታወቃል። የበሽታው ምልክቶች መታየት ፍጥነትና ጥንካሬ በአብዛኛው ወደ ሰውነት በገቡት በሽታ አማጭ ባክተሪያዎች ብዛት የሚወሰን ቢሆንም ምልክቶቹ ከ4-12 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ በጉልህ መታየት ይችላሉ። የመጀመሪያውና ዋነኛው የበሽታው ምልክት ተቅማጥ ነው። ተቅማጡም ውሃማና ቀለሙ ቡናማ ሲሆን በትንሹ የጀመረው ተቅማጥ መጠኑንና የሚመጣበትን ጊዜ እያሳደገና እየጨመረ ይሄዳል።

በተጨማሪም የአፍንጫ መድማት፣ የቆዳ መድረቅ፣ የሰውነት መዛል፣ የሆድ ህመም፣ የእግር ቁርጥማትና ማስመለስ፣ ትኩሳትና ራስ ምታት የኮሌራ በሽታ ምልክቶች ናቸው። ቫይብሪዮ ኮሌራ የተባለው ባክቴሪያ የሚራባው እርጥበት አዘል ቆሻሻ ባለበት አካባቢ ነው።

በሐገራችን አስፈሪ ድርቅ ተከስቶ በሰዎችም ሆነ በተፈጥሮ ላይ አስከፊ አደጋ ደቅኖ እንደነበር ይታወሳል። የድርቁን ችግራችንን ሳንወጣ በከፍተኛ ጎርፍና ኃይለኛ ዝናብ ያልተጠበቀ አደጋ ተደፍቶብናል። እናም ይህም ያስፈራናል።

ዓለማችን በተለያዩ ምክንያቶች በወረርሽኝ በሽታ ብዙ ሰዎቿንና ፍጥረታትን አጥታለች። አንዱ ቦታ የተነሳው በሽታ በዚያ ቦታ በማንኛውም አጋጣሚ በተከሰተ ሰው አማካይነት ሰውየው የተቀበለውን ተላላፊ ነገር ይዞ እሱም በየደረሰበት እየበከለ ያዳርሰውና ወረርሽኙ በየቦታው ተዛምቶ ህዝብን በጅምላ ይጨርሳል።

በተለያዩ ቫይረሶች ሳቢያ የተለያዩ ዓይነት ፈጣን የሆኑ በሽታዎች በስፋት ተሰረጫጭተው ማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ሰዎችን በጅምላ ጨርሰዋል። አንትራክስ፣ የስፔን ጉንፋን/ስፔን ፍሉ፣ የወፍ ጉንፋን በርድ ፍሉ፣ የዓሳ ጉንፋን፣ የአሳማ ጉንፋን ስዋይን ፍሉ በዓለም ዙሪያ በተከሰተው ቅርርብ ሳቢያ በትንፋሽና በአየር በፍጥነት ተበትነው ወደ ሁሉም በቀላሉና በፍጥነት ስለሚተላለፉ በሚሊየን የሚገመቱ ሰዎችን በብዙ ሐገራት ጨርሷቸዋል። ዚካ ቫይረስ የሚባለው ደግሞ በሚወለዱ ህፃናት ላይ ያስከተለው አደጋ በቀላሉ የሚገመት አልነበረም።

ኤድስና ኢቦላም ዓለም አቀፍ በሽታ የሆኑ የቫይረስ ውጤቶች ናቸው። ህመምተኛውን ደም በማስመለስና በማስተፋት፣ ራስምታት፣ ብርድ ብርድ ማለትና በ24 ሰዓታት ውስጥ የሚገድል በሽታ ነው። ከበርካታ ስቃዮች በኋላ የሚገድለው ኢቦላ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ያለን ቢሆንም ከዝንጀሮ ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ ተደርጎ ይወሰዳል። በባለሙያዎች በላብራቶሪ የተፈጠረ ባክተሪያ መሆኑንም የሚገልፁት እጅግ ብዙዎቹ ናቸው።

አንትራክስ ቫይረስ የወፍ ጉንፋን ዓይነት ሲሆን ሽብርተኞች በላበራቶር የፈጠሩት ቫይረስ ተደርጎ ተወስዷል። አንትራክስ በኤሽያ በተለይም በቻይና በተከሰተበት ወቅት ጆርጅ ቡሽና የአልቃይዳው መሪ ቢላደን የተፋጠጡበት አስቸጋሪ ጊዜ ስለነበር ቢላደን ለጆርጅ ቡሽ የላከለት በሽታ እንደሆነ ተደርጎ መቀለዱና በሽታውን ለማስፋፋትም ሆነ ብለው የተደራጁ ሰዎች እንደነበሩ መገለፁም አይዘነጋም።

መነሻው በደቡብ አሜሪካ ከሜክሲኮ ከተማ በትንሽ ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ ከሚገኘው የአሣማ እርባታ ጣቢያ የተነሳውና አስቀድሞ አሳማዎቹን በመቀጠልም በአሳዎቹ ተንከባካቢዎች ላይ የታየው ይህ የቫይረስ በሽታ ተስፋፍቶ በአውሮፓ የተለያዩ ሀገራት አሜሪካን ጨምሮ እንዲሁም በተለያዩ የሰሜን አሜሪካ ስቴቶች ተስፋፍቶ ብዙ ሰዎችን ፈጅቷል።

ይህ በትንፋሽ አማካኝነት የሚተላለፈውን በሽታ ወደ ሐገሮቻቸው እንዳይገባ ብራዚልና አርጀንቲና ማንኛውም ከሜክሲኮ አውሮፕላኖች እንዳይመጡና በረራዎች ለጊዜው እንዲቋረጡ አድርገዋል። 

ሌሎች የአውሮፓ ሐገራትም ከሜክሲኮ የሚነሱም ሆነ በሜክሲኮ በኩል የሚመጡ ተጓዦች በሙሉ አጠቃላይ የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ ትእዛዝ አስተላልፈው ነበር። የአሜሪካው ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ሴኔቱ ለበሽታው መከላከያ በጀት እንዲያፀድቅላቸው ያቀረቡና የጤና ጥበቃ ሚንስትር ቅድመ መከላከል እንዲያካሂድ በአፍላው አዘው ነበር።

የአሳማ ጉንፋን ስዋይን ፍሉ ካሁን በፊት ድሮ በ1950ዎቹ ታይቶ የነበረ በሽታ እንደነበርና አዋይን ኢንፍሉዌንዛ ተብሎ በብዙ ጥናቶች ተገልፆ ነበር። መልኩን እንደ ኤችአይቪ እንደሚቀያይር የሚታወቀው ይህ ቫይረስ ከ2001 አጋማሽ በኋላም ተከስቶ ብዙ ጉዳቶችንም አድርሷል።

በአሳማ አርቢነታቸው የሚታወቁት ዩናይትድ ስቴት፣ ሜክሲኮ፣ ካናዳ፣ ደቡብ አሜሪካ፣ አውሮፓ/በተለይም እንግሊዝ፣ ስዊድንና ጣሊያን/ በኬንያ፣ በቻይና፣ በታይዋን፣ በጃፓን እና ሌሎች የምስራቅ እስያ ሀገራት ለበሽታው ተጋላጭ ሆነው ነበር። የአሳማ ጉንፋን አማጭ ቫይረስ ልክ እንደ ኤችአይቪ ራሱን የሚደብቅና የበርካታ ቫይረሶች ውህድ በመሆኑ አንደኛው የአንደኛው አጋዥ በመሆን የሚሰጡትን መድኃኒቶች የመዋጋት ብቃትን መላበስ ችሏል።

ኤችአይኤን የተባለው ቫይረስ በውስጡ ለብቻው የተለያዩ ጀነቲክ ባህሪያት ያለበት ስለሆነ ይህ ነጠላ ቫይረስ በህመምተኛው ላይ ለየት ያለና ራሳቸውን ችለው ሊጠቀሙ የሚችሉ ምልክቶች በተናጥል የሚታይና የጀርባ የሰውነት ክፍል ትኩሳት፣ የማስነጠስና ራስን እስከመርሳት የሚያደርስ ራስ ምታትን ያመጣል።   

ሌላኛው የስዋይን ቫይረስ ውህድ አካል የሆነው አትይፐስዋይን ቫይረስ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ የራሱን የማጥቃት ስልት በመጠቀም የተለያዩ ጉዳቶችን የሚያደርስ ቫይረስ ሲሆን እንደቀድሞዎቹ ቫይረሶች በውስጡ የተለያየ ጀነቲክ ባሕሪያትን የያዘ በመሆኑ እሱን ለማጥፋት የሚሰሩ መድኃኒቶችን  ስለሚላመድ ያመክናቸዋል።

የአሳማ ጉንፋን በአሳማዎቹ ላይ መከሰቱን የሚያሳይ ፈጣን ምልክት ማግኘት ማስቸገሩ በሽታውን አስጊ ማድረጉንና የአሳማዎች በሽታን የመቋቋም አቅመ ደካማነት የበኩሉን ድርሻ አበርክቷል። በዚህ የተነሳም ከአሳማ ወደ አሳማ በቀላሉ በንክኪና በትንፋሽ በፍጥነት ይተላለፋል።

ከአሳማ ወደ ሰው ደግሞ በሁለት መንገድ እንደሚተላለፍ መረጃዎች ገልፀዋል። ሰዎች ከአሳማ ጋር በሚኖር የአካል ንክኪ የሚተላለፈው በዋናነት የተቀመጠ ሲሆን በትንፋሽና በደንብ ያልበሰለን የአሳማ ሥጋ በመመገብም ይተላለፋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
663 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 891 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us