ቆሻሻ በጣም ጠንቀኛ ካወቁበት ግን እጅግ በጣም ጠቃሚ

Wednesday, 20 July 2016 14:20

 

ወሰንሰገድ መሸሻ በላቸው / This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. /

መፀዳጃ ቤትን ሰዎች መጠቀም የጀመሩት በሙሴ ዘመን ከ1300–1200 ዓ.ዓ እንደሆነ ይገመታል። በግሪክና በሮማውያን የስልጣኔ ዘመን ለመፀዳጃ ቤት አጠቃቀም ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ በወቅቱ የነበረው አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል በመፀዳጃ ቤት ይገለገል እንደነበርና ከተሞቹም ፀድተውና ከተላላፊ በሽታዎች መራቢያነት ነፃ ሆነው እንደነበር ታሪክ አስፍሮታል።

ከግሪክና ከሮማውያን ስልጣኔ ውድቀት በኋላ የተተካው የመካከለኛው ዘመን ለሳኒቴሽን አቅርቦትና ይዘት መሻሻል ትኩረት ካለመሰጠቱ የተነሳ በሐይጂንና በመፀዳጃ ቤት አጠቃቀም ጉድለት ምክንያት በተከሰቱ ወረርሽኞች የተነሳ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውንና በዚህም የተነሳ ይህንን ወቅት የኋላ ቀርነት፣ የበሽታዎች፣ የችግርና የመከራ ዘመን ስለነበር የጨለማው ዘመን/ዳርክ ኤጅ/ መባሉን ባለፈው ሳምንት በሰንደቅ ጋዜጣ መግለፃችን ይታወሳል። በዚህ ሳምንት ደግሞ በቆሻሻ ጉዳትና ጥቅም ላይ ተመስርተን የምንለው ይኖረናል።

ቆሻሻ የሚለው ስያሜ ወይም ቃል በተጠቀሰ ቁጥር ጥሩ ስሜትን ወይም ነገሮችን አያሳስበንም። ቆሻሻ የራሱ የሆነ የተለምዶ ትርጉም አለው። ትርጉሙ የቆሻሻን ምንነት ከመግለፅ ባሻገር የስሜታችንና የአመለካከታችንም ነፀብራቅ ነው።

ቆሻሻ በፈሳሽ፣ በጥጥርና በጋዝ ተከፍሎ በሶስት ዓይነት ይመደባል። የጋዝ ቆሻሻ ምንጮች በአብዝሃኛው ጥጥርና ፈሳሽ ቆሻሻ ናቸው። ቆሻሻ የሚለው ቃል ስሜታዊ (Emotive) ነው። በሳይንስ ግን ከስሜታዊ ቃላት ይልቅ ስሜታዊ ያልሆነ ቃላት ይመረጣል።

በዘልማድ ቆሻሻ የምንለው ብዙ ነገሮችን ያካትታል። በመዝገበ ቃላት ለቆሻሻ /ለቤት ውስጥ ቆሻሻ/ የሰጡት ብያኔ (Definition) ‹የቤት ጥራጊ፣ አቧራ፣ ጥቀርሻና ልዩ ልዩ ዕድፍ› የሚል ነው። ቆሻሻ ግን እንደሚታወቀው ከዚህ የሰፋ ትርጉም አለው። በሳይንስና ቴክኖሎጂ ለቆሻሻ የተሰጠው ትርጉም ደግሞ ቆሻሻ በአምራቹ ወይም በሚጥለው ሰው ምንም ዋጋ ወይም ጥቅም እንደሌለው የሚገመት ቁስ (Material) ነው ብሎት፣ ከቤት ውስጥ የሚወጡ ጋርቤጆች፣ እበት፣ አዛባ፣ ፍግ፣ ከጋራዥ የሚወጡ የቅባት ዘይቶችንና ከኢንዱስትሪ የሚወጡ የምርት ትራፊዎችንና ዝቃጮችን መሆኑንም ይጠቁመናል።

ከብዙ ዘመናት በፊት በተለይ በገጠር አካባቢ ጠጣር ቆሻሻን ለማስወገድ መቅበር ቀላል አማራጭ ነበር። ሙሴ ለእስራኤል ልጆች ቆሻሻን በተለይ አይነ ምድርን ለማስወገድ የመቅበር ስርአት እንደ ደነገገላቸው መፅሐፍ ቅዱስ ላይ ተቀምጧል።

ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ3000-1000 ዓመት በተስፋፋው በሚኖአን ስልጣኔ ጊዜ የቀርጤስ ከተማ በነበረችው በቀኖሲስ ጠጣር ቆሻሻዎች በትላልቅ ጥልቅ ጉድጓድ መቅበር የተለመደ ባህል ነበር። በአንፃሩ ሮማውያን እስከ 19ኛው ክ/ዘመን ድረስ የታወቀ የቆሻሻ ማስወገጃ ዘዴ ስላልነበራቸው የተለያዩ የቆሻሻ አይነቶችን በየከተማው ዳር ተከማችተው ነበር።

አርኪዮሎጂስቶች በየከተሞቹ የተከመሩ ቆሻሻዎችን በመመርመር ስለጥንታዊ ከተሞች ታሪክና ገመና ብዙ መረጃዎችን አግኝተዋል። ከተሞቹ ለዘመናት በዙሪያቸው ያከማቿቸው የቆሻሻ ክምር ተራሮች አንዳንድ ከተሞችን እንዳሰመጧቸውና ነዋሪዎች ያንን ቦታ እየለቀቁ በቅርብ በሚገኝ አምባ ላይ ይከትሙና ኑሮአቸውን ይመሰርቱ እንደነበርም ታሪክ አስፍሮታል።

የመካከለኛው ዘመን የጀርመን ከተሞች በራሳቸው የቆሻሻ ክምር ከመቀበር አደጋ ለመዳን ሲሉ ከገጠር ወደ ከተማ እህል ጭነው የሚመጡ ጋሪዎች ወደ መጡበት ሲመለሱ የከተማውን ቆሻሻ ወስደው ገጠር እንዲያከማቹት መመሪያ አውጥተው ነበር።

የስኮትላንድ ዋና ከተማ በሆነችው በኤዲንብራ ከ18ኛው እስከ 19ነኛው መቶ ክ/ዘመን በተወሰነ ቦታ ተከምሮ የነበረው ቆሻሻ እንዳይጨምር ለማድረግ ቆሻሻዎቹን በመምረጥ ፍላጎቱ ላላቸው የተለያዩ ድርጅቶች ለመሸጥ የከተማይቱ ሹማምንት አዘዙ።

በጥንታዊቷ ለንደን ግሬስ ኢንሌይን በተባለ ቦታ አብዋራማ ቆሻሻ እስከ 1815 ድረስ ሲቆለል ቆይቶ ነበር። በናፖሊዮን ወረራ ፈራርሳ የነበረችውን ራሽያን ዳግም ለመገንባት ለሚያስፈልገው የሸክላ ስራ እንዲሆን አብዋራማው ቆሻሻ እየተሸጠ ወደ ራሽያ ተጫነ። እ.ኤ.አ. እስከ 1962 ድረስ 41 የሸክላ አምራች ድርጅቶች ከዚሁ ቁልል ቆሻሻ ለሸክላ ምርት የሚያስፈልጋቸውን ሸመቱ። እ.ኤ.አ. እስከ 1969 ድረስ ከእነዚህ ድርጅቶች ጥቂቶቹ ከዚሁ የቆሻሻ ክምር ለሸክላ ምርት የሚውል ጥሬ ሀብት ይገዙ ነበር።

የኬሚካል ማዳበሪያ እስከተሰራበት ጊዜ ድረስ የከተማዎችን ቆሻሻ የማስወገድ ኃላፊነት ለተሰጠው አካል  የከብቶች ፍግ ጥሩ የገቢ ምንጭ ነበር። ዘመናዊው የኬሚካል ማዳበሪያ መመረት ሲጀመር ግን ገበሬዎች ወደ እበትና ፋንድያ ፊታቸውን አዞሩ። በዚህ የተነሳም በመካከለኛው ዘመን በነበሩት የአውሮፓ ከተሞች እበትና ፋንድያ የማስወገድ ስራ አድካሚና ወጪን የሚጠይቅ ተግባር ሆነ።

ይህንን የተፈጥሮ ማዳበሪያ/ፍግ ለመጠቀም የተነሳሱት ሰዎች ወደ እርሻ ቦታችን የምናጓጉዝበት የትራንስፖርት ወጪ ይሸፈንልን የሚል ጥያቄ አነሱ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአውሮፓና በአሜሪካን ያሉ አንዳንድ ከተሞች በተለያዩ ስፍራዎች የቆሻሻ ማቃጠያ ስፍራ (Incinerator) መገንባት ጀመሩ። በእንግሊዝ ምድር የመጀመሪያው ማቃጠያ እ.ኤ.አ. በ1874 ተሰራ። ቁጥሩም ወደ 200 አደገ። ከእነዚህ ውስጥ 65ቱ በእንፋሎት የሚሰራ ኤሌክትሪሲቲ እንዲያመነጩ ሆነው የተዘጋጁ ናቸው።

ቴክኖሎጂው እየተሻሻለና የሚመረቱት ምርቶች በአይነትና በብዛት እጅግ እየጨመሩ መጡ። የኢንዱስትሪም ሆነ ሌሎች ቆሻሻዎች የሚያስከትሉት የአካባቢ ብክለትና የጤና ቀውስ ግንዛቤ በሁሉም ወገን ተፈጠረ።

ከሰል ጋዝ ተመርቶ ከወጣለት በኋላ እንደ ሬንጅ ያለ ዝቃጭ ኮልታር ወይም የከሰል ሬንጅ የሚባለው ይቀራል። ይህ ሬንጅ/ኮልታር በዘመኑ ከፍተኛ የከሰል ጋዝ ያስፈልግና በገፍ ይመረት ስለነበር በዚያው መጠን ከፍተኛ የከሰል ሬንጅም ተፈጠረ። 

በዚህ ሂደት የኢንዱስትሪ ከተሞች የከሰል ሬንጅን በአንድ ክልል ማከማቸት በመጀመራቸው በጥቂት ጊዜ ውስጥ የከሰል ሬንጁ ተራራዎችን በመስራቱ ማስወገዱ በጣም ከበዳቸው። እ.ኤ.አ. እስከ 1840 የከሰል ሬንጅ ጥቅሙ አልታወቀም። ሆኖም አንዳንድ ኬሚስቶች የከሰል ሬንጁ ለአንዳንድ ጠቃሚ ኬሚካሎች ምርት እንደጥሬ እቃነት እንደሚውል ተገነዘቡ።

በ1819 ጋርሰንና ኮድ የሚባሉ ኬሚስቶች ከከሰል ሬንጅ ናፍታለን (Naphthalene) አምርተዋል። በ1834  ሩንጌ የሚባል ኬሚስት አኒላይንን (Aniline)፣  ካዪናሊን(Quinaline)፣ ፓይሮል እና (Pyrrole) ፌኖል (Phenol) የሚባሉ ኬሚካሎችን ከከሰል ሬንጅ አምርተዋል። በ1842 ከከሰል ሬንጅ ለኢንዱስትሪ የሚያገለግሉ ማሟሙያዎች (Solvents)፣ ቶሉዩንና (Toluene) ቤንዚን (Benzene) ለማምረት ተቻለ። ሆኖም እነዚህ ግኝቶች የከሰል ሬንጅ በሚያመርቱ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ፈፅሞ አይታወቁም ነበር።

በ1856 ዊሊያም ሄነሪ ፐርኪን የተባለ እንግሊዛዊ የኮሌጅ ተማሪ ከከሰል ሬንጅ ለሚመጣ በሽታ መከላከያ የሚያገለግል ኳይኒን የተባለ ኬሚካል ለማዘጋጀት ይሞክራል። ይህ ሙከራው ባይሳካለትም እጅግ ተፈላጊ የሆኑ ለልብስ ማቅለሚያ የሚያገለግሉ ኬሚካሎችን ግን አዘጋጀ። ከዚያ በኋላ የከሰል ሬንጅ እንደ ቆሻሻ መጣሉ ቀርቶ እንደ እንቁ የሚቆጠር ምርጥ ጥሬ እቃ ሆነ። ከዛሬ 157 ዓመት በፊት የነዳጅ ዘይት እምብዛም አይታወቅም ነበር። ከከሰል በሚመረት ምርት ይገለገል የነበረው ትውልድ የነዳጅ ዘይት ድፍድፍን ማለት ፔትሮሊየምን ከከርሰ ምድር ማውጣት የጀመረው በ1859 ነበር።

ቆሻሻን ወደ ወንዝ መጣል በጣም የተለመደ ሆኗል። የወንዝ ውሃን መበከል በሌላ አካባቢ ለመስኖ፣ ለአሳ እርባታ ወይም ለመጠጥ የሚውል በመሆኑ በመርዝ ህዝብን በጅምላ ከመጨረስ የባሰ ይከፋል። የአንድ ወንዝ መበከል የሌላ ወንዝም መበከልንም ያስከትላል። አንዳንድ ወንዞች ደግሞ ወደ ሐይቅ ይገባሉ፣ ወይም ሐይቁን አቋርጠው ስለሚያልፉ ሐይቁንም ይበክላሉ። 

የመሬትን 71% የሸፈነው ውሃ ቢሆንም ለመጠጥ፣ ለእርሻና ለኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውለው መጠን እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። በገፀ ምድርና በከርሰ ምድር ውስጥ ያለው ውሃ ለህዝቡ/ለእያንዳንዱ ሰው ይከፋፈል ቢባል 292 ትሪሊየን ሊትር ውሃ ይደርሰዋል። ይሁን እንጂ 99.997% የሚሆነው ውሃ በውቅያኖስ፣ በሐይቆች፣ በወንዞችና በመሳሰሉት የሚገኝና ለሰው አገልግሎት ለማዋል አመቺ ባለመሆኑ አይጠቀሙበትም።

ቀሪው 0.003% በከርሰ ምድር ውስጥ በጉድጓድ፣ በምንጭና በመሳሰሉት መልክ የሚገኝና በሁሉም ቦታ በእኩል ያልተሰራጨ ተፈጥሮ የቸረችን ህዝባዊ ሀብት ነው። የዓለም የውሃ ስርጭት በመቶኛ ሲሰላ ውቅያኖስ 97.134%፣ በህዋ 0.001%፣ በመሬት ላይ/በበረዶ ክምር 2.225%፣ ጠጣር በረዶ 0.009%፣ በወንዞች 0.0001%፣ በከርሰ ምድር ውስጥ/በአፈር እርጥበት መልክ 0.003%፣ እስከ 1000 ሜትር በሚደርስ የጉድጓድ ጥልቀት 0.303% መሆኑን ጥናቶች ገልፀዋል።

ለመጠጥና ለልዩ ልዩ አገልግሎት የምንጠቀምበት የውሃ መገኛዎች የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ ናቸው። የገፀ ምድር ውሃ ወደ ወንዞች በመፍሰስ ሐይቆችን፣ ኩሬዎችን… ይፈጥራል። ውሃ በአፈር ውስጥ በመስረግ የከርሰ ምድር ውሃን ያስገኛል። ይህም ውሃ 95% የሚሆነውን በዓለም የንፁህ ውሃ መገኛ ምንጭም ነው።

ውሃ በከተሞችና በገጠር ከፋብሪካ ከኢንዱስትሪ፣ ከመኖሪያ ቤቶች፣ ከሆስፒታሎች፣ ከት/ቤቶች፣ ከትላልቅ ንግድ ድርጅቶችና ከመሳሰሉት በሚወጡ ደረቅ ፍሳሽና መርዛማ ቆሻሻዎች፣ በሰው ዓይነ ምድር፣ በፀረ ተባይና በፀረ ሰብል ማጥፊያ መድሃኒቶች፣ መርዛማ ኬሚካሎች ለመሬት ማዳበሪያ በሚረጩ ኬሚካሎች፣ በልዩ ልዩ እፅዋት እንስሳትና አውሬዎች፣ የቧንቧ መስመሮች፣ ንፅሕና በሌላቸው የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖችና በቤት ውስጥ ውሃን ባልተጠበቀ እቃ በመቅዳትና ሳይከደኑ በማስቀመጥ ወዘተ ሊበከል ይችላል።

ለዚህም ነው የውሃ ጥራትን ለመጠበቅ ሲባል የውሃ መበከልን የሚፈጥሩትን ሁሉ ለይቶ ማወቅ ግድ የሚሆነው። ሁለቱ የውሃ ብክለት መነሻዎች ከተወሰነ ቦታ የሚነሱ/ፖይንት ሶርስ/ እና ከተበታተነ አቅጣጫ የሚነሱ/ነን ፖይንት ሶርስ/ የሚባሉት ናቸው።

ከፋብሪካ/ከኢንዱስትሪ፣ ከመኖሪያ ቤቶች፣ ከጤና ድርጅቶችና ከንግድ ድርጅቶች የሚወጡ ደረቅ ፍሳሽና መርዛማ ቆሻሻዎች፣ ከፍሳሽ ማጠራቀሚያ ኩሬዎች የሚወጡ፣ ከመፀዳጃ ቤቶች ከሴፕቲክ ታንክ፣ ከኦክሲዴሽን ፖንድ፣ ከፈሳሽ ማስረጊያ ጉድጓዶች የሚለቀቁ፣ ከነዳጅ ማደያና ጋራዦች የሚወጡ ፍሳሾችና፣ ከደረቅ ቆሻሻ ማከማቻና ማስወገጃ ቦታዎች የሚወጡ ቆሻሻዎች ወዘተ የመሳሰሉት ከተወሰነ ቦታ የሚነሱት ናቸው።

በቃጠሎ ምክንያት፣ በህንፃ ስራዎችና ከእርሻ ቦታዎች ተጠርገው የሚወጡ ጠጣርና ፍሳሽ ቆሻሻዎች፣ ለመሬት ማዳበሪያነት ከሚጨመሩ ኬሚካሎችና ከሚረጩ ፀረ ሰብልና ፀረ ተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች፣ ጨውነት ካለው ውሃ በመስኖ የሚጠጡ እርሻ ቦታዎች የሚመነጩ ቆሻሻዎች፣ ከገጠርና ከተሞች አካባቢ ተጠርገው የሚገቡ የካርበን ውህድ ያልሆኑ ማእድኖች ለምሳሌ ጨው፣ ሊድ፣ ሜርኩሪ፣ ሳልፌት፣ ናይትሬት፣ ዝቃጭና ሬድዮ አክቲቭ ነገሮች እንዲሁም የካርበን ውህድ የሆኑ ነገሮች ለምሳሌ ነዳጅና ግሪስ፣ ፕላስቲክ፣ ዲተርጀንትስና የካሎሪን ውህዶች የመሳሰሉት ከተበታተነ አቅጣጫ የሚነሱ ተብለው የተፈረጁ ናቸው።

ውሃ በአይን ጠርቶ/ኩልል ብሎ በመታየቱ ብቻ ያልተበከለና ለጤና ተስማሚ ነው ብሎ መገመት ያስቸግራል። አብዝሃኞቹ ውሃ ወለድ በሽታዎች የሚተላለፉት በዓይናችን ለማየት በማንችላቸው ጥቃቅን በሆኑ ቫይረሶች፣ ፕሮቶዞዋና ባክቴሪያ በሚባሉ ተህዋስያን አማካይነት ነው።

ሃገሪቱ ባሏት 12 ተፋሰሶች/ ከዚህ ውስጥ አራቱ ውሃ የሌላቸው/ በዓመት 123 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የገፀ ምድር ተተኪ ውሃና 2.6 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የብሮስ ምድር ውሃ ሃብት ባለቤት መሆኗን ከተለያዩ የውሃ ማስተር ጥናቶች መገንዘብ ተችሏል። በሌላ በኩል በሃገሪቱ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን ከ31% ያልዘለለ ሲሆን በገጠር 23% በከተማ 74% እንደሆነም ሰነዶቹ አብራርተዋል።

ፍሎራይድ በመሬት ውስጥ በብዛት ከሚገኙት ጥሪተ ነገሮች መካከል በ13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በተፈጥሮ በተለያዩ ቦታዎች ይገኛል። ጥሪተ ነገሩ ከሌሎች ነገሮች ጋር ባለው ፈጣን የመዋሃድ ባህሪ በአብዝሃኛው በውህድ መልክ ሲገኝ በተናጥል ተለይቶ ሲታይ 19 አቶማዊ መጠን ቁስ አካል /atomic mass unit/ የሚመዝን፣ የሚሰነፍጥና የሚከነክን ሽታና ቢጫ መልክ ያለው ጋዝ ሲሆን በማቀዝቀዝ ወደ ፈሳሽነትና ጠጣርነት ለመቀየር የሚቻል ነው። ሶስቱ ዋና ዋና የፍሎራይድ ምንጮች ፍሎሮስፔር

(Fluorspare (C2 F2)፣ ክሪዩላይት  (Cryoliter (Na3 AlF6)እና አፓይት (Apatite (Ca 10 F2 (Po4)6  ናቸው።

ሰዎች ፍሎራይድን ከሚመገቡበት ምግብ፣ ከሚጠጡት ውሃ፣ ከመድኃኒት፣ ከሲጋራ፣ ከአየር ወዘተ ሲያገኙት እንስሳት ደግሞ ከሚጠጡት ውሃ፣ ከሚመገቡት ምግብ እንዲሁም አትክልቶች፣ ከአፈርና ከአየር ያገኙታል። በሰው አካል ውስጥ እስከ 1.5 ሚ.ግ. ፍሎራይድ ለአጥንትና ለጥርስ ጥንካሬ ሲያገለግል ከመጠን ሲያልፍ ግን በጥርስ፣ በአጥንትና በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ የጤና ችግር ያስከትላል። ፍሎራይድ በብዛት በሚገኝባቸው አገሮች ይህ ችግር የጎላ ነው። በአገራችንም በሰሜን ሸለቆ አካባቢዎች ችግሩ በጉልህ ታይቷል።

ፍሎራይድ በብዛት የሚገኝባቸው አገሮች አርጀንቲና፣ አልጀሪያ፣ አውስትራሊያ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኢትዮጵያ ወዘተ… ሲሆኑ ፍሎራይድ በኢትዮጵያ በስምጥ ሸለቆ በሚገኙ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር የውሃ መገኛዎች በብዛት ይገኛል። ለምሳሌ በላንጋኖ 64 ሚ.ግ. በሊትር፣ በቆቃ 22 ሚ.ግ. በሊትር፣ በዝዋይ 14.19 ሚ.ግ. በሊትር፣ በወንጂ 12.5 ሚ.ግ. በሊትር፣ በመቂ 9 ሚ.ግ. በሊትር፣ በጅማ ከተማ 9 ሚ.ግ. በሊትር፣ በናዝሬት 7 ሚ.ግ. በሊትር፣ በአዋሳ 6 ሚ.ግ. በሊትር ይገኛል።

ፍሎራይድ ከአፈር ከግራናይት ባዛልት ድንጋዮች/አለት/ ከሼል ከሸክላ እሳተ ገሞራ ከፈነዳባቸው አካባቢዎች ከካልሲየም ፎስፌት ከጉድጓድ ውሃዎች ከጨው፣ ከጨው ማውጫ ቦታዎች ከምግብ/ከባህር ምግቦች ከሻይ ቅጠል ወዘተ…/ ፍሎራይድ ከሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች/ብረታብረት፣ የአልሙኒየምና የብረት ማጣሪያ ኬሚካል፣ የአሲድ፣ የማዳበሪያ፣ የነዳጅ፣ ከህንፃ ሥራ፣ ከሸክላ፣ ከብረት፣ ከመስተዋት ማምረቻዎች፣ ከመድኃኒትና የኮስሞቲክስ፣ የውሃ መጠበቂያ ቅመሞችና ፀረ ህዋስ መድኃኒቶች ይገኛል።

በተፈጥሮ/ከአፈር ከድንጋይ ከጉድጓድ ውሃዎች በሰው ሰራሽ ችግሮች (Anthropogenic Sources)፣ ከኢንዱስትሪዎች ፍሎራይድ በብዛት የሚገኝበት ከሰል በማቀጣጠል፣ በምግብ የደረቁ የባህር ምግቦች 326 ሚ.ግ. ከሻይ ቅጠል 32 ሚ.ግ. እንዲሁም ከአየርና ከውሃ ይገኛል።

ፍሎራይድ ወደ ሰውነት አካል በውሃ በምግብና በአየር ከገባ በኋላ 20.25% በጨንጓራ፣ 75-80% በትንሹ አንጀት፣ በድምሩ 86-90% በሰውነት ይመጠጣል/ይሰራጫል። ከተመጠጠው ፍሎራይድ ውስጥ 0.5% ወደ አጥንት፣ 1%  ወደ ጥርስ፣ ቀሪው ከ 5-20% በአይነምድር፣ ከ50-70% በሽንት፣ 5% በላብ ይወገዳል።

ሰዎች በፍሎራይድ መልክ የመመረዙ እድል የሚያጋጥማቸው ፍሎራይድ የበዛበት ውሃና ምግብ በመጠቀምና በፍሎራይድ በተበከለ አየር አካባቢ ሲኖሩ ነው። ከፍተኛ ፍሎራይድ መጠን በሰውነት ጤናማ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ በማድረግ የአጥንትና የጥርስ መበስበስና የሌሎች የሰውነት ክፍሎች የጤና መታወክ(Non Skeletal Manifestation) ያስከትላል።

በውሃ ውስጥ የፍሎራይድ መጠን እስከ 1 ሚ.ግ. በሊትር ድረስ ቢኖር ለአጥንትና ለጥርስ ጥንካሬ ይረዳል። መጠኑ 1.5 ሚ.ግ. በሊትር እስከ 2 ሚ.ግ. ሲደርስ የጥርስ መበስበስና በቀላሉ መነቀልን ያስከትላል። በፍሎራይድ መጠኑ 8 ሚ.ግ. በሊትር ሲደርስ 10% የሚሆነውን የሰውነታችን የመገጣጠሚያ ክፍሎች ፈሳሽ መድረቅን ያስከትላል። በውሃ ወይም በምግብ የፍሎራይድ መጠኑ 20 ሚ.ግ. በሊትር ሲደርስ በታይሮይድ ዕጢዎች ላይ የጤና ችግር ማስከተልን በውሃ ወይም በምግብ የፍሎራይድ መጠኑ 100 ሚ.ግ. በሊትር ሲደርስ የሰውነት እድገት መጓተትን፣ በውሃ ወይም በምግብ የፍሎራይድ መጠኑ ከ500 ሚ.ግ. በሊትር ሲበልጥ ወዲያውኑ እንደሚገድል የተደረጉ ጥናቶች ያስረዳሉ።

ፈንገስ/ዘረንጉዳይ ህመም የተባለው የቆዳ በሽታ በማንኛውም የሰውነት ክፍል ላይ የሚወጣ ቢሆንም በተለይም ላሽ፣ በራስ የሚወጣ ፈንገስ፣ ፀጉር በሌለው ሰውነት ላይ የሚወጣ ቋቁቻ፣ በእግር ጣቶች ጣብቂያ የሚወጣ ጮቅ፣ በጉያ ጣብቂያ የሚወጣ ችግር ነው። አብዛኛው የፈንገስ /ዘረንጉዳይ ኢንፌክሽን እንደቀለበት ክብ ሰርቶ ይታይል። የማሳከክ ስሜት ሊያስከትል ይችላል። በራስ ቅል ላይ የሚታየው ላሽ በክብ ቅርፅ ስለሚበላ ፀጉርን በመንቀል መላጣ ያደርጋል። ቆዳውም እየተቀረፈ ይወድቃል። ፈንገሱ የጣት ጥፍር ሲያጠቃ ጥፍሩን ወፍራምና ቅርፀ ቢስ ያደርገዋል።

ፈንገስ የወጣበት አካባቢ በሚገባ ከታጠበ በኋላ በደንብ እንዲደርቅ ለአየርና ለፀሐይ ብርሃን በደንብ ተጋልጦ እንዲናፈስ ማድረግ ያስፈልጋል። የውስጥ ልብስንና የእግር ካልሲን በንፅህና መያዝና ላብ እንዳያመጣ በየጊዜው ቀያይሮ መልበስ ችግሩን ለማቃለል ይረዳል። በልጆች ላይ የወጣ የፀጉር ላሽ ዕድሜያቸው ከ11-14 ዓመት በሚደርስበት ጊዜ በራሱ ይጠፋል። ትልቅ የራስ መመለጥና መግል የያዘ እብጠት ሲያስከትል በሙቅ ውሃ በተነከረ ጨርቅ ማሸግ። ከቆሰለው የራስ ክፍል ያለውን ፀጉር በሙሉ ለቅሞ መንቀል ያስፈልጋል።

ጭርትና ሌሎችም የፈንገስ ኢንፌክሽኖች ተላላፊ ናቸው። ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው እንዳይዛመቱ ማድረግ ሲያስፈልግ ቋቁቻ፣ ጭርትና ሌላም የፈንገስ ኢንፌክሽን ያለባቸው ልጆች ከሌሎች ጋር እንዳይተኙ ማድረግ። ልጆች ከፈንገስ ነፃ ካልሆኑ በስተቀር ልብሳቸውን ተቀያይረው እንዳይለብሱና በአንዱ ሚዶ እንዳይጠቀሙ መከልከል። ለታመመ ልጅ አስፈላጊና የማያዳግም ህክምና መስጠት ግድ ይላል። በፊትና በገላ ላይ የሚወጡ ነጭ ነጠብጣብ ነገሮች በአንገት፣ በደረትና በጀርባ ላይ የሚወጣ የተወሰነ ቅርፅ የሌለው ጠቆርና ነጣ ያለ ነጠብጣብ ቋቁቻ ሊሆን ይችላል። አብዝሃኛውን ጊዜ የማሳከክ ስሜት ያስከትላል። እነዘዚህ ሁሉ ከንፅህና ጉድለትና ከቆሻሻ የሚመነጩ ችግሮች መሆናቸውን ማስተዋል ይገባናል።¾

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
955 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 829 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us