የጥላቻ፣ የመናናቅ፣ ያለመተማመን፣ የቂም በቀልና የመገዳደል አስከፊ ስሜትን ለማስወገድ ብሄራዊ እርቅ ግድ ይላል!

Wednesday, 27 July 2016 14:21

 

ከአዳነ ታደሰ

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል

ከሃምሌ 5 2008 ዓ.ም ጀምሮ በጎንደርና አካባቢዋ የተቀሰቀሰውን ግጭት   ስከታተለው ነበር። ለዚህ ግጭት መነሻው ሲንከባለል የመጣው የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የማንነት ጥያቄ መሆኑን ብዙዎቻችን የምንስማማ ይመስለኛል። መንግስት ከጥያቄው ጋር የሚያያዝ አይደለም ቢልም። ታዲያ ባለፉት 2 ዓመታትና አሁንም በጎንደር የተቀሰቀሰው ግጭት ላይ ያየነው የመንግስት እርምጃ፣ የህብረተሰቡ ተቃውሞ አገላለጽና የመረጃ ሰጭዎች ሚና ቢያሳስበኝ ነው ብዕሬን አንስቼ የበኩሌን ለማለት የፈለኩት። የነዚህ አካላት ሚና ቅጣጫውን እየሳተ ቢቀጥል የነገ የሃገራችን ዕጣ ፈንታ ላይ የሚሳድረውን ተጽዕኖ ለመግለጽና መፍትሄ የምለውን ሃሳብ ጠቁሜ ለማለፍ ነው።

የሚነሱ ጥያቄዎችን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቅድሚያ ትኩረት መስጠት የሰለጠነ  መንግስት መገለጫ ነው።  በዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት እድለ ቢስ እንደሆነ እዚህ ደርሷል። በተጨባጭ ባለፉት 25 ዓመታትም ችግሮችንና የሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችን በሰለጠነ መንገድ ሊፈታ የሚችል ስርአትና መንግስት ሳይሆን እያየን ያለነው ችግሮችንና የሚነሱ ጥያቄዎችን ሁሉ በሃይል ለማፈን ተግቶ የሚሰራ ስርአት ነው። መንግስት የሚነሱ ጥያቄዎችን በጅምላ የግንቦት 7 እጅ፣ የሻቢያ እጅና የኦነግ እጅ አለበት እያለ ምክንያት መደርደርና ዶመንተሪ ፊልም በመስራት የህዝቡን ጥያቄ ማቃለል ለበለጠ ግጭት መቀስቀስ ምክንያት እየሆነ እያየን ነው። መንግስት ከዚህ የተለመደ ድርጊቱ መቆጠብ ካልቻለና መልስ የመመለስ ድፍረቱና ወኔው እየከዳው ከሄደ ነገ ከነገ ወዲያ  ኢትዮጵያንና ህዝቧን  ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል አደጋ ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን ብዬ እሰጋለሁ። ስለዚህ መንግስት ፖለቲካዊም ሆነ አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እንዲያስችለው የራሱን ካድሬዎች በአዳራሽ ውስጥ ሰብስቦየወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ጸረ ሰላም ሃይሎችን አወገዘ የሚል ቲያትር ለመስራት ሳይሆን የጉዳዩ ባለቤት ከሆነው  የህብረተሰብ ክፍል ጋር ግልጽና ቀጥተኛ ውይይት ለማድረግ  መድረክ ማመቻቸት አለበት እላለሁ። ጥያቄዎችን የማዳፈኑ ስራ ቆሞ ዘለቄታዊ መፍትሄ ላይ ማተኮር አለበት።

በእኔ እምነት ጥያቄና ተቃውሞ የሚያቀርበው የህብረተሰብ ክፍልም ፍጹም ሰላማዊና ህጋዊ በመሆን ተቃውሞ የማቅረብ ባህሉን ከምንግዜውም በበለጠ ማሳደግ አለበት እላለሁ። ባለፉት 2 አመታትና በቅርቡም በጎንደር እንዳየነው አቅጣጫቸውን የሳቱ ድርጊቶች ከእንግዲህ መስተዋል የለባቸውም። በምንም መልኩ ህብረተሰቡ ከግጭትና ከብጥብጥ ሳይሆን ትርፍ የሚያገኘው ከሰላም ነው የሚል እምነት አለኝ።  የእሳት ዳር ፖለቲከኞች ግጭት ሲፈጠርጉሮ ወሸባዬ የሚያበዙት በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ ካላቸው ጥማት መሆኑን ህብረተሰቡ መረዳት አለበት። በደሃው ህዝብ ደም 4ኪሎ ለመግባት የሚሰራ ግጭትን የማባባስ ርካሽ ፖለቲካን ህዝቡ መጠየፍ ይኖርበታል። በእኔ እምነት በብጥብጥና በሁከት ዘላቂ የሆነ የስርአት ለውጥ ሳይሆን የሚመጣው በተቃራኒው ኢህአዴግ የተባለን አባገነን አንስቶ እንቶኔ የተባለ አምባገነን መንግስትን መተካት ነው ውጤቱ የሚሆነው። ህዝቡ የእሱን ተቃውሞ ተገን አድርገው የሃገርና የህዝብ ሃብት ላይ ውድመት ለማድረስ የሚንቀሳቀሱትንና ዘርን ከዘር ለማጋጨት የሚጥሩትን አካላት በመከላከል ጨዋነቱንና ለብዙ ዘመን ጠብቆ ያቆየውን የመቻቻል ባህሉን ማሳየት አለበት። በኣጠቃላይ ግን እንደዚህ ዐይነት  ከማንነት ጋር፣ ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር፣ ከልማት ጥያቄ ጋር፣ ከዞንና ከክልልነት ጋር ተያይዞ የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሳውም የህብረተሰብ ክፍል መጠንቀቅ ያለበት ጥያቄው የሃገር አንድነትን፣ የህዝቡን አብሮ የመኖር ታሪካዊ ትስስርና የመቻቻል ባህሉ አደጋ ውስጥ እንዳይወድቅ ነው።  

ሌላው በሃገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚተላለፉ የመገናኛ ብዙሃን፣ በህትመት ውጤቶችና በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚተላለፉ መልዕክቶችና መረጃዎች ግጭቶችን የማያባብሱ መሆን አለባቸው። የሚነሱ ተቃውሞዎችና ግጭቶችን ተከትሎ በነዚህ አካላት የሚተላለፈው አብዛኛው መረጃ ግን የህዝቡን አብሮነት የሚያናጋና የሃገራችንን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚጥል እየሆነ ነው። ኢህአዴግ ዘረኛ ነው፤ ከፋፋይ ነው ብለው ስለአንድነታችን የሚሰብኩን ከውጭ ወደ ሃገር ውስጥ የሚተላለፉ ፕሮግራሞች ግጭቱና ብጥብጡ ሞቅ ሲል ማርሽ ቀይረው ግጭቱ እንዳይበርድ ዘረኝነትን የሚሰብኩ ከሆነ ዘረኛና ከፋፋይ ከሆነው ኢህአዴግ በምንድን ነው የሚለዩት? ስለዚህ ለነገ ለከነገወዲያ የሃገራችን መጻኢ እድል ጠቃሚ የሆኑ እሴቶቻችን እንዲጠበቁና ችግሮችና ክፍተቶች ሲኖሩ ደግሞ ሙያዊ በሆነ መንገድ የማጋለጥ ታሪካዊ ላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

የመንግስት የመገናኛ ብዙሃንም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሃቅ ላይ የተመረኮዘ መግለጫና ሚዛናዊ የሆነ ዘገባ በአብዛኛው ስለማያቀርቡ የሚነሱ ግጭቶችን ከማብረድና ሰላምና መረጋጋት  ከማምጣት ይልቅ ሲያባብሱት እያየን ነው። የተለመደ እና ለ25 አመት ስልችት ያለንን ግጭት በተከሰተ ቁጥር የሚያቀርቡትን ድራማና ዶክመንተሪ ፊልም መቀነስ አለባቸው። አላማቸው ግጭት ሲታ ማብሰር ሳይሆን ግጭቶችና አለመግባባቶች ሲፈጠሩ መረጃ ማቀበልና ዳግም እንዳይፈጸሙ ህብረተሰቡን ማስተማር መሆን ይገባዋል። ህብረተሰቡ መረጃ ፍለጋ ወደ ሌላ የሚሄደው የመንግስቱ ሚዲያ እውነቱን ስለሚደብቅ ነው። ዛሬ ዛሬ የመንግስት ሚዲያ ግጭቶች ተፈጥረው በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት ሲዘግብ ዘገባውን በሁለት እጥፍና በሶስት እጥፍ ማባዛት የተለመደ ሆኗል። በዚህም የተነሳ ምክንያታዊ ሆኖ ነገሮችን የሚያገናዝበው የህብረተሰብ ክፍል እየቀነሰ፤ ምክንያታዊነት የጎደለው፣ ጯሂውና አሉባልተኛው እንዲበራከት እያደረገ ነው። በእውነቱ ከሆነ በመንግስት ሚዲያው አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በጣም ተሰላችቷል። ስለዚህ የመንግስት ጋዜጠኛው ከካድሬት ተግባሩ ወጥቶ ሙያው ወደሚጠይቀው ስነ-ምግባር ውስጥ ገብቶ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ማገልገል አለበት።

ሌላው አብዛኛው በማህበራዊ ድረ ገጽም የሚተላለፈው መረጃ  ሀገርንና ህዝብን የሚጠቅም ሳይሆን በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ውሎ አድሮ እንደሃገርም እንደ ህዝብም ዋጋ የሚያስከፍለን እንዳይሆን እሰጋለሁ። ግጭቶች ሲፈጠሩና ሲነሱግፋበለው የሚል፣ ግጭቶጭና ብጥብጦች ሲቆሙ ጸጉሩ የሚቆምና የሚቆጭ የማህበራዊ ድረ ገጽ ጸሃፊ እየበዛ ነው። አንዱን ዘር ሌላኛው ላይ እንዲነሳ ዘወትር ቅስቀሳ የሚያደርጉ፣ ሆነ ብለው የተዛባ መረጃ የሚያቀርቡ አካላት ድርጊታቸው ማንም የማይኖርባትን ሀገር ለመፍጠር ካልሆነ በስተቀር የሃገር ተቆርቋሪነት ተግባር አይደለም። የእከሌ ብሄር ይሄን እያደረገ ነው ምን ትጠብቃለህ የሚል እየተበራከተ ነው። የኔ ብቻ ሃሳብ የበላይነት ማግኘት አለበት በሚል የጥፋት መርዝ የሚረጩ እኩይ አላማ ያነገቡ አካላት ቀላል የሚባል ቁጥር የላቸውም። የእነዚህንም አካላት የተሳሳተ ቅስቀሳ ተከትሎ የጥፋት ጎዳና ውስጥ የሚገባውም የህብረተሰብ ቁጥር እየበዛ ነው። ይሄ የነገዋን የሃገሬን መጻኢ እድል አስፈሪ ያደርገዋል። እንደዚህ አይነት መርዝ የሚረጩ የማህበራዊ ሚዲያ ጸሃፊዎች ሁሉም የሚኖርባትን ኢትዮጵያ የማየት ፍላጎት ያላቸው አይመስለኝም። ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር የሁሉም ብሄር ተወላጆች መኖሪያ ቤት እንደሆነች መረዳት ያስፈልጋል። አለበለዚያ  በሚዲያ ሃላፊነት የጎደለው ቅስቀሳ በሩዋንዳ የደረሰውን የዘር ጭፍጨፋ ታሪክ በማስታወስ ይሄን ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት በእሳት መጫወቱን ማቆም አለባቸው።  በኢትዮጵያ በዚህ መልኩ የሚነሳው ግጭት ከሩዋንዳውም የበሳ ሊሆን እንደሚችል ብዕር የምናነሳና በቴሌቪዥን መስኮት አንደበታችንን የምንከፍት አካላት ልናውቅ ይገባል። ስለዚህ እነዚህ መረጃ የሚሰጡ ተቋማትና ግለሰቦች  በሚያቀርቡት ዘገባና በሚጽፉት ጽሁፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ታሪካዊና ሙያዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት የነገ ሃገራችንን ሲዖል ሳትሆን ገነት ለማድረግ መትጋት አለባቸው።

በጎንደርና አካባቢዋም ሆነ በቅርብ አመታት በሃገሪቱ የሚነሱ አብዛኞቹ ግጭቶች ዋነኛው መነሻ ምክንያት ሃገሪቱ የምትከተለው ቋንቋንና ብሄረሰባዊ ማንነትን ዋነኛ መስፈርት ያደረገው የፌደራል አደረጃጀት ነው የል እምነት አለኝ። ኢህአዴግ የሚከተለው የፌደራል ስርአት ባለፉት 25 አመታት እንዳየነውና እነሱ እንደሚሉት የብሄር ብሄረሰቦችን ጥያቄ በአግባቡ እየመለሰ፣ የሃገራችንና የህዘቡን አንድነት እያጠናከረ ሳይሆን በየጊዜው አዳዲስ ጥያቄዎችን እየወለደ መንግስትም ለመመለስ እየተቸገረ የግጭትና የመበታተን ስጋት እየተፈጠረ ነው። በቅርብ ግዜ እንኳን በቁጫ ህዝብ፣ በወለኔ ህዝብ፣ በኮንሶ ህዝብ፣ በቅማንት ህዝብ፣ በሲዳማ ህዝብ ወዘተ...... የሚነሳው ጥያቄ መንግስት እያዳፈነው ነው እንጂ ውስጥ ውስጡን እየተብላላ ነው። ታዲያ እነዚህን ሀሉ ጥያቄዎች የወለደውና መመለስ ያቃተውም የኢህአዴግ ፌደራሊዝም ነው። ስለዚህ አትዮጵያን ለመሰለች የራሷ ነባር ታሪክ ላላት ሃገር የሚመጥንና ለቁመናዋ የሚገባ ይዘት ያለው ፌደራላዊ አደረጃጀት ያስፈልጋል እላለሁ።  ኢህአዴግ የሚከተለው የፌደራል አደረጃጀት ባለፉት 25 ዓመታት በተግባር ተፈትሾ ግጭቶች፣ ልዩነቶችና አለመግባባቶች እንዲበራከቱ ከማደረግ የዘለለ ጠብ ያደረገልን ነገር የለም። በኢትዮጵያ መገንባት ያለበት የፌደራል ስርአት ቋንቋን፣ የመሬት አቀማመጥን፣ የህዝብ ብዛትን፣ የህብረተሰቡ አብሮ የመኖር ታሪካዊ ትስስርን፣ አስተዳደራዊ አመቺነትንና የኢኮኖሚ ጥቅምን የመሳሰሉት ጉዳዮች የአከላለል መመዘኛዎች ያደረገ ሊሆን ይገባል።  በተለያዩ ቦታዎች  ከፌደራሊዝም አደረጃጀቱ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥቄዎችን በአግባቡ መመለስ ያቃተው የፌደራል ስርአት ዳግም ራሱን ሊፈ  ይገባል።

በኔ እምነት ግን የዚችን ሀገር ሁለንተናዊ ችግርበዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው ብሔራዊ እርቅ ነውየብሔራዊ እርቅመድረክ ጥያቄ መንግስት እንደሚለው እና እንደሚያስበው አላማው ስልጣን የመጋራትም ሆነ የመጋፋት ጥያቄ አይደለም። ጥያቄው ላለፉት 25 ዓመታት የተፈጠሩ ችግሮችን የመፍታት ጥያቄ ብቻም ተደርጎ መታየት የለበትም። ጥያቄው ለብዙ ዘመናት በአገራችን ፖለቲካ ስር እየሰደደ የመጣውን የጥላቻ፣ የመናናቅ፣ ያለመተማመን፣ የቂም በቀልና የመገዳደል አስከፊ ስሜትን የማስወገድና የኃይል የስልጣን ሽግግር ወደ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር  ለመለወጥ የሚያስችል ታሪካዊ መሰረት የመፍጠር ጥያቄ ነው። የእርቅና የመግባባት ጥያቄ ለሌላ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያነት የምናነሳው ጥያቄ ሳይሆን በወቅቱ የአገራችን ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ጥያቄውን እንደ ጥያቄ ለማንሳት የሚያስገድዱ መሰረታዊ ምክንያቶች በመኖራቸው ነው።

እዚህ ላይ መንግስትም ሆነ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የብሄራዊ እርቅ የመፍጠር ጥያቄ የሚያዩበትን መነጽር ሊያስተካክሉ ይገባል እላለሁ። መንግስት የተጣለ የለም በማለት ጉዳዩን የባልና የሚስት ጸብ ይመስል ሲያቃልለው ይታያል። ይሄ በኔ እምነት የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ካለመረዳት ሳይሆን ከተለመደው የኢህአዴግ የግትርነት ባህሪና ጉዳዮችን አምኖ ካለመቀበል የሚመነጭ የቆየ ችግር ነው። በዚህ 25 ዓመት ውስጥ ዘርን አስታኮ ችግር አልተፈጠረም? ባለፈው ትውልድ ተሰራ የተባለ ጥፋትን ህዝቡ እንዳይረሳ ሃውልት አልተገነባም? በእምነት ልዩነት ግጭቶች አላየንም? ታቀዋሚ ፓርቲ ከተቃዋሚ ፓርቲ የጎሪጥ የሚተያይበት ዘመን ላይ አይደለንም? ገዥውን ፓርቲ በሃይል ከስልጣኑ ለማውረድ ነፍጥ ይዞ ጫካ የገባ የለም? ጥላቻ መናናቅ አልነገሰም? በእኔ እምነት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ይሄን የቆየና ስር የሰደደ ችግራችንን ለመቅረፍ ነው ብሄራዊ እርቅ የሚያስፈልገው። ስልጣኑና 4ኪሎ ቤተ መንግስት መግባቱ ግን በምርጫና በምርጫ ስርዓት ብቻ ነው  መሆን ያለበት ጥያቄው በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ አይደለምና።

አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆነ ብለው ጥያቄውን በማንሻፈፍ የብሄራዊ እርቅ ጥያቄውን የስልጣን ጥያቄ በማድረግ መስመር ሲያስቱት ይስተዋላል። የብሄራዊ እርቅን የብሄራዊ አንድነት መንግስት፣ የሽግግር መንግስት ማቋቋም በሚል ከስልጣን ጥያቄ ጋር የማይገናኘውን ጉዳይ እያገናኙ ይሄን ለዘመናት የቆየ የሃገራችንን ችግር ለመፍታት አላማ ያደረገ አስተሳሰብ ዋጋ ያሳጡታል።

ሃገራችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጐሰኝነትን መሰረት ያደረገ የጥላቻና የቂም በቀል ስሜት የታመቀት፣ ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳይሆን በጎሳ ማንነታቸው ተቧድነው የየራሳቸውን ጎጆ የቀለሱባት፣ ከብሔራዊ ጥቅምና ስሜት በላይ የእኔነትና የአካባቢ ተቆርቋሪነት በእጅጉ የዳበሩባት፣ አንድ ከሚያደርጉን ይልቅ ልነቶቻችን ቦታ አግኝተው የምንራኮትባት፣ሃገራችን ላይ ሆነን ሃገርህ የትነው ተብለን መጠየቅ የህይወታችን አንዱ አካል የሆነባት፣ የኔ ዘር ከዛኛው ይበልጣል በሚል ክርክር የምንገጥምባት ሃገር እየሆነች ነው። ይሄንን ለነገዋ ሃገራችን አንድነት፣ ሰላምና መረጋጋት እንቅፋት የሆነ አደጋን ለመከላከል ነው የብሄራዊ እርቅ መድረክ የሚያስፈልገው። ወቅቱ የፍቅር፣ የመተሳሰብና የመቻቻል ስሜት እየሟሸሸ መጥቶ የጎሳ ልዩነትን መሰረት ያደረገ የጥላቻና የመናናቅስሜት የዳበረበት ሆኗል።  ሰዎች ከአንዱ ሃግር ወደ አንዱ ሃገር ለስራ፣ ለመዝናናትና ለትምህርት ሲሄዱ የሚሳቀቁበት፣ ሃገራቸው ላይ ሆነው መላ ሃገራቸውን የሚናፍቁበት ግዜ ላይ ናቸው። ለዚህ ነው ብሄራዊ እርቅ የሚያስፈልገን። ይሄንን አይኑን ያፈጠጠ ሃቅ ተቀብለን ለመፍትሄው ዛሬ ላይ መረባረብ ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው። ስለዚህ የብሄራዊ እርቅ ጥያቄን ኢህአዴግ የተጣላ የለም  የሚለውን ሹፈቱን አቁሞ ተቃዋሚዎችም በሽግግር መንግስት ስም የስልጣን ጥያቄ አድርገን ማቅረባችንን አቁመን አንድ አይነት መግባባት ላይ መድረስ አለብን። የነገዋ ኢትዮጵያ በዛሬ የቤት ስራችንን መስራት ላይ ትወሰናለች። አለበለዚያ ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ እንዳይመጣ። የሚሻለው የቆየውንና አሁን ያለውን ጥላቻ፣ ቂም በቀል፣ መናናቅና አለመቻቻል በብሄራዊ እርቅ ከሃገራችን ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ   ማጥፋት ነው። ቸር እንሰንብት። (ይህ ጽሁፍ የግል አቋሜን ነው የሚያንጸባርቀው።)

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
508 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 889 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us