የጎንደሩ ሕዝባዊ ሰልፍና ወቅታዊው የሀገሪቱ ሁኔታ፤

Wednesday, 03 August 2016 14:44

 

ከስናፍቅሽ አዲስ

የሰሞኑ ዋና ጉዳይ የእሁዱ የጎንደር ከተማ ሰልፍ ነው። ምንም እንኳን የአንጋፋዎቹን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ቢያጣም ማህበራዊ ሚዲያዎቹና የግል መገናኛ ብዙሃን በስፋት ዘግበውታል። ሰልፉ ፍቃድ እንደሌለው ሰልፉ ከመካሄዱ ከሁለት ቀናት በፊት አቶ ንጉሡ ጥላሁን የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ለፋና ብሮድካስቲንግ ገልጸው ነበር። ችግሩ የተፈጠረው እዚህ ጋር ይመስለኛል። ሰልፍ እናድርግ የሚሉ ጠያቂዎች ወደ ጎንደር ከተማ ከንቲባ ሄደው ጥያቄ ማቅረባቸውን እና ሰልፍ ማድረግ የሚፈልጉትም ለሀምሌ 17 ቀን እንደሆነ ገልጸው ነበር። በወቅቱ ፈጣን ምላሽ ባለማግኘታቸው ሰልፉ ለሀምሌ 24 ቀን ተላለፈ። ቢሮ ሃላፊው በመግለጫቸው ሰልፍ ለማድረግ የጠየቀ የለም የሚለው አነጋገር በሰልፍ ጠያቂዎቹና በመንግስት መካከል አለመተማመን የገነባ የመጀመሪያው ችግር ይመስለኛል።

የሰልፍ ዋነኛ ትኩረት የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጉዳይ ነው። ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ መንግስት በሌላ ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ ያላቸውን ግለሰቦች ለመያዝ ሙከራ አደረገ። እነዚህ ግለሰቦች ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላትም ናቸው። በሰዓት እላፊ አፍኖ ለመውሰድ የተደረገ ሙከራ ነው ሲሉ የወልቃይት ማንነት ጥያቄ አባላት ጉዳዮን በተመለከተም ለቪኦኤ እና ለጀርመን ድምጽ ራዲዮ መግለጫ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።

ይሁን እንጂ ለጸጥታ ሀይሎች እጄን አልሰጥም አሉ ከተባሉት ኮሎኔል ደመቀ ጋር የተፈጠረውን ተኩስ ተከትሎ የከተማው ህዝብ ሆ ብሎ ተነሳ። ከአርባ ስምንት ሰዓታት በላይ ውጥረት የነገሰባት ጎንደር ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተኩስ በገጠሙ ታጣቂዎች የሰው ህይወት አለፈባት። የጸጥታ ኃይሎችም ሲቪሎችም ሞቱ። ሰላም ባስ ተቃጠለ። ያም ሆኖ በከፍተኛ ድርድር ችግሩ እንዲበርድ ተደረገ። በድርድሩ ወቅት መንግስት አሸባሪ ብሎናል። በቴሌቨዥን የተላለፈው ዜና ይታረም በሚል የሰላም ድርድሩ ላይ ከፍተኛ ቅሬታቸውን ያስተጋቡ አካላትም ነበሩ። ይህንን ተከትሎ ነው የእሁዱ ሰልፍ።

እሁድ ጎንደር ያስተናገደችው ሰልፍ ችግሩ ምን ያክል ህዝባዊ እንደሆነ ማሳያ ነው። ይሄንን የክልሉ መንግስት ሳያውቀው ይቀራል ማለት አይቻልም። በትግራይ ወልቃይት የትግራይ ነው በሚል የተካሄደውን ሰልፍ ዓይነት እኛም ጎንደር ላይ እና በሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች እናደርጋለን ብለው ጥያቄ ያቀረቡ አካላት ሰልፉን እንዲያካሂዱ ፍቃድ አላገኙም። በእርግጥ ህገ መንግስቱ ለሰላማዊ ሰልፍ የመንግስትን እውቅና የሚፈልግ ቢሆንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ግን በሬድዮ ፋና ፍቃድ አልሰጠንም ሲሉ ተደምጠዋል። የጠየቀ አካል የለም የሚለው ማለባበሻ ግን ውሎ አድሮ የእሁዱን ሰልፍ ለአደባባይ ሲያበቃው ተጋለጠ።

የሰልፉ እውቅና ማግኘት ብዙ ጥቅሞች እንደሚኖሩት ከሰልፉ በኋላ የተገነዘበው ብአዴን በማዕከላዊ ኮሚቴ የፌስ ቡክ ገጹ ጠቆም አድርጓል። እርግጥ ሰልፉ እውቅና አግኝቶ ቢሆን ኖር የኦሮሚያ፣ የሀብታሙ አያሌውና የበቀለ ገርባ ዓይነት አጀንዳዎች ምናልባትም ላይነሱ ይችሉ ይሆን ነበር። በእርግጥ አሁን ላይ ከመገመት ያለፈ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም። በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራዋ ምትክ የብአዴን ባንዲራ ሊውለበለብም ይችል ነበር። ያ ሁሉ አልሆነም። በእኛ ሀገር የግምታቸው ተቃራኒ የሆኑ የፖለቲካ ኃላፊዎች የድምዳሜያቸው መነሻ ሲከሽፍ እንደ አቅም ማነስ የሚታይበት ሁኔታ አልተለመደም። የሰልፉ ዓላማ ብጥብጥ ለማስነሳት ነው በሚል ህብረተሰቡን አስጠንቅቀው የነበሩ የስራ ኃላፊዎች እራሳቸው በሰላም መጠናቀቁን ድጋሚ ማወጃቸው ፈገግ ያሰኛል።

ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ተጀምሮ የተጠናቀቀው ሰልፍ ብዙ ትምህርት የሚገኝበት ነው። ለተቃዋሚዎችም ሆነ ለመንግስት የሚያስተምረው ብዙ ነገር አለ። ህዝብም እንደ ህዝብ ሊማርባቸው የሚችሉ ክስተቶችን አስተናግዷል። ይህ ግን አስተባባሪዎቻቸው በሚገባ ያልተለዩ ሰላማዊ ሰልፎች ለየትኛውም አጀንዳ ክፍት መሆናቸውና ሰልፈኛው እራሱ በማያምንበት አጀንዳ ተሰልፎም ሊውል እንደሚችል ይጠቁማል።

ከሰልፉ ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ የባንዲራ ጉዳይ ነው። ኮኮቡ የሌለውና በህገ መንግስቱ የተቀመጠው ባንዲራ በሰልፉ ላይ በፍጹም አልታየም። ኮኮብ የሌለበት ባንዲራ ያጥለቀለው ሰልፍ ነበር። ጎንደር ይሄንን ባንዲራ በአደባባይ ያውለበለበችው በዚህ ሰልፍ አይደለም። ባንዲራውን ከግንቦት ሰባት ጋር ለማያያዝ መሞከሩ ውሃ አያነሳም። ከግንቦት ሰባት መመስረት በፊት ጎንደርም ሆነች ብዙ የአማራ ከተሞች ለህዝባዊ ኩነቶቻቸው ከፍ የሚያደርጉት የቀድሞውን ባንዲራ ነው። ይሄ ከኢትዮጵያ ህዝብ የተሰወረ አይደለም። የአማራ ክልል መንግስት ድንገት ሰልፉ ላይ የተመለከተው ጉዳይ አድርጎ መግለጫ መስጠቱ አሁንም አለመተማመኑን ያጎላዋል። ሌላው ቢቀር የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች በሚታደሙበት የጎንደር ዓመታዊ የጥምቀት በዓል ኮኮብ የሌለው ባንዲራ የሚያሽቆጠቁጣት ከተማ መሆኗን የማያውቅ የለም። በጎንደር የኢትዮጵያ ካርታ ኤርትራ የማትቆረጥበት መሆኑን ያላየ የብአዴን አመራር ካለ ማንን እየመራ እንደሆነ እራሱን ይፈትሽ።

የባንዲራው ጉዳይ የጎንደር ብቻ አይደለም። ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደሴ፣ ደብረታቦር የጥምቀትና መስቀል በዓላት በባለ ኮኮብ አልባው ባንዲራ የሚያሸበርቁ ናቸው። ይሄ እውነታው ሆኖ ሳለ ጎንደር አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ የያዙ ሰልፈኞች በእሁዱ ሰልፍ መታየታቸው ህገ መንግስታዊ ጥሰት እንደሆነ አዲስ ነገር ተደርጎ የሰልፉ ጀርባ ሌላ አካል እንደሆነ ለመነሻ ፍንጭነት መጠቀም የሚያዋጣ መስመር ላይሆን ይችላል።

ወቅታዊው የሀገር ስጋት፤

አሁን አንድ ነገር መመልከት ጀምረናል። ሃይ ባይ የሌላቸው ሀገሪቷን የሚበትን አጀንዳ የሚያራምዱ ግለሰቦች ተበራክተዋል። ዘርን ወክሎ በአደባባይ ሌላ ዘር ላይ የስነ ልቦና ጥቃት የሚያደርስ ጀብደኛ ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው። ይሄን የደህንነቱ መስሪያ ቤት ሊያተኩርበት ይገባል። ሀብታሙ አያሌው ህክምና ያግኝ ለሚለው ጥያቄ ወንድ ከሆናችሁ ጫካ ግቡ የሚሉ የህወኃት ደጋፊ ፌስ ቡከሮች እየበዙ ነው። ይሄ የህወኃትም ሆነ የትግራይ ህዝብ አጀንዳ አይደለም። አዲስ አበባ ቆሸሸች ብሎ ሃሳቡን ለሚገልጽ ሰው ወንድ ከሆንክ ጫካ መግባት ነው ብሎ የኢህአዴግ ደጋፊነት አይታየንም። ከሻዕቢያ ባልተናነሰ ጫካ መግባትን የሚሰብኩ እና የሚቀሰቅሱ የኢህአዴግ ደጋፊዎችን በአደባባይ እያየን ነው። ድርጅቱ ራሱን መፈተሸ አለበት። አሁን ራሱን ይፈትሽ ስንል ለድርጅቱ ህልውና ብቻ አይደለም። ሀገር እንዳትፈርስ ነው። ሰዎች በእከሌ ባስ አልሄድም ብለው እከሌ ባስን የሞት መንገድ እስኪያደርጉት የስጋት ድባብ ባጠላባት ሀገር ላይ ሰፊ ስራ ለመስራት ሆደ ሰፊ መሆን ይጠይቃል። በአካባቢ ሹማምንቶች ላይ የሚጣለው ሙሉ እምነትም ወሰን ቢኖረው መልካም ነው። በኮንሶ፣ በቁጫ፣ በወለኔ የሚነሱ ጥያቄዎች ህዝባዊ ይሁኑ አይሁኑ እንኳን ለማየት ምቹ መድረክ ጠፍቷል። በሪፖርት ላይ እምነቱን የሚጥል ድርጅት ከፈተና ሊወጣ አይችልም። የምናቀውም የምንቃወመውም መንግስት ኢህአዴግ ነው የሚሉ አካላትን ጆሮ ሰጥቶ ማዳመጥ ያስፈልጋል። የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች መግለጫዎች መንግስታዊ ተክለ ቁመና ሊኖራቸው ይገባል። አሁን ሻዕቢያ እና ኦነግ ናቸው ተብሎ የተነገረው ህዝብ በአስር ቀን ውስጥ የራሳችን ጥፋት ነው። ስራ አጥነት ነው፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው እየተባለ መንግስት የሚልህን እመን ማለት ሊከብድ ይችላል።

በመጨረሻም የጋራ ሀገር አለችን። ብዙ ስርዓቶች ሀገሪቷን ይዘው አልሄዱም። የትኛውም ወገን የሚያደርገው እንቅስቃሴ ሀገሪቱን ከብተና የሚታደግ መሆን አለበት። ስለ ህዝቡ አብሮ መኖር እና መስተዋድድ ሊጠነቀቅ ይገባዋል። የንጹሃን ዜጎችን ሰላማዊ ዋስትና ማረጋገጥ አለበት። ከሁሉም በፊት ሀገርን ማስቀደም ይገባል። ሀገር ሳትኖር ሁሉ ነገር ቢኖር ትርጉም የለውም።  

  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
598 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 921 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us